Wednesday, 2 April 2014

የይሁዳ ክህደት ለ30 ዲናር፣ የእነዚህ ደግሞ የማኅበረ ቅዱሳንን ሀብት ለመዝረፍ

(ደጀ ሰላም፣ መጋቢት 22/2006 ዓ.ም፤ ማርች 31/2014. PDF)፦ የአስቆሮቱ ይሁዳ ጌታችንን አሳልፎ ሰጠው። ምህሩንና ጌታውን ክዶ፣ ስሞ ለግርፋት እና ለመስቀል ሞት ተስማማ። ይህንን የጌታን ሕማማት፣ ስቅላት፣ ሞትና ትንሣኤ በምናስብበት በአሁኑ ወቅት ማኅበረ ቅዱሳንን ለሕማም፣ ለስቅላት እና ለሞት አሳልፎ ለመስጠት የሚደረገው ትርምስ ተጀምሯል። ይሁዳ ለ30 ዶላር እነዚህ የዘመናችን ሰቃልያን ደግሞ “ማኅበሩ ያፈራውን ሀብት በሙሉ ለመዝረፍ ጊዜው አሁን ነው” ብለዋል። በዚህም በዚያም ክህደት እና ስቅለት።
መጋቢት 13/2006 ዓ.ም “በዓይነቱ ለየት ያለ” ስብሰባ በቤተ ክህነቱ ግቢ ተካሒዷል። ለየት ያለ የተባለው አጀንዳውና ቁመነገሩ ሳይሆን ቤተ ክህነቱ ባልለመደው ሁኔታ፣ ከቤተ ክህንቱ ይትባህል ውጪ በዐቢይ ጾም ወቅት ዩየተደረገ የ“ስቅሎ ስቅሎ ስብሰባ” (የስቀለው ስቀለው ስብሰባ) መሆኑ ነው። ፋክት መጽሔት “ለመጽሔቱ ዝግጅት ክፍል የደረሰው በድምፅ የተቀረፀ የውይይቱ ሙሉ” ክፍልን ጠቅሶ እንደገለጠው “ተሰብሳቢዎቹ ማኅበሩን በተመለከተ ያወጡት የአቋም መግለጫ÷


የማኅበሩና የዋነኛ መሥራቾችና አባላት የባንክአካውንት፣ ቀላልና ከባድ ተሸከርካሪዎች ጨምሮቋሚና ተንቀሳቃሽ ንብረቶች፣ ት/ቤቶች፣ የንግድተቋማት፣ የአክስዮን ተቋማት፣ የንዋያተ ቅድሳትማምረቻዎችና ማከፋፈያዎች፣ ከቀረጥ ነጻ የገቡናበመግባት ላይ ያሉ ዕቃዎች በሚመለከታቸውየመንግሥት መሥ/ቤቶች እንዲታገዱ በቅ/ሲኖዶስአማካይነት ደብዳቤ እንዲጻፍ፤
ከምእመናን በቀጥታም ኾነ በተዘዋዋሪ የሚቀበለውዓሥራት እየፈረጠመበት ስለኾነ እንዳይቀበል ይከልከል፤
የግቢ ጉባኤያት (የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት) እርሱ በሚቀርፀው ትምህርትእንዳይወሰዱብን በደንብ መሥራት፤
ተጠሪነቱ ከዋና ሥራ አስኪያጅነቱ ሥር ወጥቶ በሰንበት ት/ቤቶች ማ/መምሪያ ውስጥ አንድንኡስ ክፍል ይኹን የሚሉና የመሳሰሉት ይገኙበታል፡፡”

የተሰብሳቢዎቹ ማንነት እና ምግባራቸውን ለጊዜው ብንተተውና ጥያቄያቸውን ብቻ ተመርኩዘን ብንወያይ እንኳን ብዙ ሐጸጽ እና ኢ-ኦርቶዶክሳዊ ተግባራትን ማግኘት እንችላለን።
በዚህ በዐቢይ ጾም የሱባዔ ወቅት እንዲህ ያለውን የአድማ ስብሰባ ለማካሔድ ሲጠይቁ ፈቃድ የሰጠው አካል አንድም ቤተ ክህነቱንና ቤተ ክርስቲያኑቱን አያውቅም ወይም አያምንባትም፤ አንድም ከአቅሙ በላይ የሆነ ተጽዕኖ ተደርጎበታል። ሌላው ሁሉ ቢቀር አዲሱ ፓትርያርክ በዚህ የአመጽ ተግባር ላይ እጃቸውን አስገብተው መገኘታቸው ለዘመነ ፕትርክናቸው ትልቅ ጥቁር ጠባሳ ያስቀምጥባቸዋል። ምን ይሉኝ ማለት የማያውቁት ፓትርያርክ አቡነ ጳውሎስ እንኳን (አፈር ይቅለላቸውና) እንዲህ ያለ ስሕተት ሲሳሳቱ ታይተው አይታወቁም።

የማኅበሩ ንብረት ለመሆኑ የማን ነው?
ይህንን በሥርዓት አስረግጦ መመለስ ያስፈልጋል። ደጀ ሰላም እስከምትረዳው ድረስ ማኅበሩ ሕጋዊ ሰውነት ያገኘው ከቤተ ክርስቲያኒቱ ነው። ቤተ ክርስቲያን ይሁነኝ ብላ ያቆመችው፣ ነፍስ የዘራችበት ማኅበር ነው። በአገሪቱ ሕግ መሠረት ማንኛውም ተቋም ሕጋዊነት ሳይኖረው መንቀሳቀስ አይችልም። ማኅረሩ ቅዱሳን በኤን.ጂ.ኦ ሕግ በመንግሥት መዝገብ ፈቃድ ያወጣ ሳይሆን ቅዱስ ሲኖዶስ በሰጠው ፈቃድ፣ በቤተ ክርስቲያኒቱ ዕውቅና የሚንቀሳቀስ ነው።
በምሳሌ እናስረዳ። አራዳ ጊዮርጊስ ያስገነባው ሕንጻ፣ የልደታ ቤተ ክርስቲያን ግንቦች፣ የምስካየ ኅዙናን ገዳም ት/ቤት የማን ንብረት ናቸው ተብሎ ይጠየቃል? አቡነ ጳውሎስ ያሠሩት መንበረ ፕትርክናው የማን ነው ተብሎ ይጠየቃል? አንዱ ገዳም እርሻ ቢኖረው የማን እርሻ ነው ይባላል? እንዲህ የሚል ሰው ቢመጣም መልሱ ቀላል ነው። “ይህ ንብረት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ነው” የሚል ነው።

የምስካየ ኅዙናን ገዳም ት/ቤት የቤተ ክርስቲያኒቱ ቢሆንም የማስተዳደር ኃላፊነቱ የገዳሙ ነው። የአራዳ ጊዮርጊስ ንብረት፣ የመርካቶው ራጉኤል ሕንጻዎችም ወዘተ ወዘተ የቤተ ክርስቲያን ናቸው የሚያስተዳድሯቸው ግን አጥቢያዎቹ ናቸው።
ታዲያ የማኅበረ ቅዱሳን ንብረት የተለየ እንደሆነ ተደርጎ የሚቀርበው ለምንድነ ነው? የቤተ ክርስቲያን ንብረት መሆኑ እየታወቀ፣ ነገረ አስተዳደሩ በማኅበሩ ጠቅላላ አባላት ምርጫ በሚሰየሙ የሥራ አመራር እና የሥራ አስፈጻሚ አካላት መሆኑ እሙን ሆኖ ሳለ 

የሌላ አካል ሀብት እንደሆነ አድርጎ ማቅረቡ ለምን አስፈለገ?
መልሱ ግልጽ ነው። ንብረቱን ለመዝረፍ፣ ሀብቱን ለመመዝበር ያቆበቆበ፣ የቋመጠ፣ የአጥቢያዎችን ንብረት በመዝረፍ ሚሊዬነር የሆነ የብላው እንብላው ቡድን ፍላጎት ነው። አዎ፣ ማኅበሩ ከአባላቱ ላብ ባገኘው የፈቃድ ድጋፍ እና አገልግሎቱ በገባቸው ኦርቶዶክሳውያን ርዳታ ሕንጻውን ጨርሷል። አሁን ሲያዩት ያጓጓል። ለእነ ሆድ አምላኩ ዝርፊያ የማይመች ይህንን የመሰለ ነገር አይቶ ማለፍ አይቻላቸውም። ስለዚህም አይሁድ ጌታን በሰላላ ዲናር ክህደት ለመስቀል ሞት እንዳበቁት፤ በግዑ ለእግዚአብሔር (የእግዚአብሔር በግ) ክርስቶስን አርደው ሳይበሉት እንደቀሩት፣ እነዚህ የዘመናችን ተረፈ አይሁድም ማኅበረ ቅዱሳንን ለመስቀል ቋምጠዋል። ላይበሉት፣ ላይጠቀሙበት።

ማኅበሩ አጠቃላይ የገቢና የወጪ ሥርዓቱን የሚያካሒደው ዘመኑ በፈቀደው ጥበብ ሁሉ እንጂ ጊዜ ባለፈበት እና ለዝርፊያ እና ለሙስና በተጋለጠ ያረጀ ያፈጀ የሒሳብ አሠራር አይደለም። እነዚህ ሰቃልያንና ዘራፍያን ይህንን ያውቃሉ። ገንዘቡ እኛ በምንፈልገው መልክ ይሰብሰብ ማለታቸው ለዚያ ነው።
አሁን ስለተጀመረው የቤተ ክህነቱ የመዋቅርና አስተዳደራዊ ለውጥ እና በቤተ ክርስቲያኒቱ ውስጥ ስለተስፋፋው ዝርፊያ በቅድስት ማርያም ዩኒቨርስቲ የአካውንቲንግ መምህር እና በቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ የሦስተኛ ዓመት ተማሪ” የሆኑት አቶ ምሐባው ዓለሙ ለአዲስ ጉዳይ መጽሔት ያሉትን ለማስረጃ እንጥቀስ።

“ስለ ፋይናንስ ሥርዓቱ ሲነሣ ብዙ ሰዎች ቤተ ክርስቲያኒቱ የምትጠቀምበት ዘመናዊ አሠራር (double entry) ይመስላቸዋል፡፡ ነገር ግን ቤተ ክርስቲያን አኹን እየተጠቀመችበት ያለው የፋይናንስ ሥርዓት ዓለም በ፲፯ኛው መ/ክ/ዘየተወውንና የነጠላ ሒሳብ አሠራር (single entry) የሚባለውንና በሞዴል የሚሠራ የሒሳብ አሠራር ነው፡፡ በዓለም ላይእንዲኽ ዓይነት የሒሳብ አሠራር የሚከተል ምንም ተቋም የለም፡፡ በመኾኑም ይኼን ተረድቶ የፋይናንስ ሥርዓቱን ማዘመን ይገባል፡፡ ይኼ የሒሳብ አሠራር በፍጹም ምቹ አይደለም፡፡ የሒሳብ አሠራሩ በራሱ ነጠላ ነው፡፡ ወጪን ወጪ ይላል እንጂ ምክንያቱን አይናገርም፡፡ ስለዚኽ ወጪን ከነምክንያቱ ገቢን ከነምንጩ የሚጠቅሰው የሁለትዮሽ (ደብል) አሠራር ሥርዓት የላትም፡፡ ይኼ አሠራር ደግሞ በአፋጣኝ መለወጥ አለበት፡፡”
ግለሰቡ “የቤተ ክርስቲያን ፈተናዎች” የሚልና ስለ ዝርፊያው ጥልቅ ምንነት አይን ገላጭ የሆነ ማስረጃ ያቀረቡ ናቸው። ዝርፊያው ምን ያህል የጎላ መሆኑን ሲያብራሩ ያሉትን እናክል፦
አዲስ ጉዳይ፡- በአኃዛዊ ስሌት የገንዘብ ዘረፋው ምን ያህል ይደርሳል?
አቶ ምሐባው፦ እኔ በየዓመቱ ቤተ ክርስቲያን በመቶ ሚልዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ ትመዘበራለች ብዬ በመጽሐፌ ላይ ገልጩ ነበር፡፡ ይኹን እንጂ አሁን ከቀድሞ በተሻለ ጉዳዩን ስመለከተው ቤተ ክርስቲያን በምዝበራ የምታጣው ሀብት ከመቶ ሚልዮኖች የሚልቅ መሆኑን ለመረዳት ችያለሁ፡፡ (አዲስ ጉዳይ፤ ቅጽ 8 ቁጥር 206፤ መጋቢት 2006 ዓ.ም.)
በዚህ ምዝበራ ላይ የተሰማሩት እነማን ናቸው? ፖለቲካዊ አቋማቸው ምንድነው? ይህ ሁሉ ሚሊዮን እና ሚሊዮን የምእመናን ላብና ደም፣ የቤተ ክርስቲያን ንብረት የሚዘረፈው በነማን ነው? ብለን ትንሽ ገፋ አድርገን ስንጠይቅ ከፍ ብለን የጠቀስነውን የአመጽ ስብሰባ ወደሚያደራጁት አካላት እንመጣለን።

ታዲያ ይሄ የዘረፋ ቡድን፣ በመንግሥት ጥበቃ እንዴት ሊያገኝ ቻለ? 
የፓርቲያቸው አባላት የሆኑ ሰዎች በቤተ ክርስቲያን ዝርፊያ ላይ ሲሰማሩ አበጃችሁ እየተባሉ ከአባላት ድጎማ በመሰብሰብ በሚያገኘው ሳንቲም ቤተ ክርስቲያኒቱን የሚረዳ ስብስብን ለማጥቃት ዘመቻ ሲጀመር መንግሥታዊ ጥበቃ አለማድረግ በዘመቻው ከመተባበር ተለይቶ አይታይም።
ከሁሉ ከሁሉ አዲሱ ፓትርያርክ እና አዲሱ አስተዳደራቸው እየተከተለ ያለው አካሔድ ግን ያልተጠበቀ ባይሆንም ለታሪካቸው የማይበጅ እና አሳፋሪ የሚባል ነው። በየሳምንቱ አዳዲስ ደብዳቤ ለማኅበረ ቅዱሳን ለማብረር የማይደክሙ ሰዎች ምእመናንን የሚጠቅም ሥራ ለመሥራት እጃቸውና እግራቸው ሲተሳሰር ማየት ያሳፍራል። “በነገሩ የለሁበትም” እያሉ የሚምሉ የሚገዘቱት አቡነ ማቴዎስም (ሥራ አስኪያጅ) ሆኑ ፓትርያርኩ አቡነ ማቲያስ ከታሪክ ተወቃሽነት ሊያመልጡ አይችሉም።
ቢያንስ ቢያንስ “ኧረ ዐቢይ ጾም ነው፤ ሰው ምን ይለናል” ማለት ማንን ገደለ? ወይስ የቆሎ ተማሪው “ቀራንዮም ቀራንዮ፤ ካህናቱም ካህናቱ” እንዳለው ሆነ? 

ታሪክ፦ ተማሪው ፍርፋሪ ፍለጋ በእንተ ስማ ለማርያም እያለ ወደ ቀራንዮ ቤት ክርስቲያን ሄደ አሉ።፡ከዚያ ካህናቱ ሳይራሩለት ይቀራሉ። እያዋዛ መናገር የሚችለው ተማሪም “ቀራንዮም ቀራንዮ፤ ካህናቱም ካህናቱ” አለ ይባላል። አሁንም በዚህ የጌታ ጾም እንደቀደሙት ካህናተ አይሁድ “ስቅሎ ስቅሎ” ማለት በስምም በግብርም አያመሳስላችሁም? ቤተ ክርስቲያንን ብሎ የተሰበሰበው ይህ ትውልድ ግን በዳዊት ቃል፦


“”ፍታሕ ሊተ እግዚኦ አምላኪየ በከመ ጽድቅከ፤
ወኢይትፈስሑ ላዕሌየ።
አቤቱ አምላኬ እንደ ጽድቅህ ፍረድልኝ፤
በላዬም ደስ አይበላቸው” (መዝ 35፡24) እንደሚል ባይዘነጉት ግሩም ነው።


ቀጥሎም፦
“ሐሰስክዎ ለእግዚአብሔር ወተሰጥወኒ፤
ወእምኵሉ ምንዳቤየ አድኀነኒ፤
እግዚአብሔርን ፈለግኹት መለሰልኝም፤
ከመከራዬም ሁሉ አዳነኝ።” (መዝ. 33፡ 4) ማለቱ አይቀርም። እግዚአብሔርን ያለ ትውልድ ነዋ።


ጆሮ ያለው ይስማ።


ቸር ወሬ ያሰማን፤
አሜን

No comments:

Post a Comment