Thursday, 5 July 2012


“ማህበረ ቅዱሳን አክራሪና ጽንፈኛ ማህበር ነው” በማለት በጦላይ ጦር አካዳሚ ለአመራሮች ስልጠና ተሰጠ


  • ·        የምንሰማ እና የምናየው ነገሮች መልካም ባለመሆናቸው ምክንያት ላልተወሰነ ጊዜ “አንድ አድርገን” የመረጃ ምንጭ መሆኗን አቋርጣለች፡፡


(አንድ አድርገን ሰኔ 27 2004 ዓ.ም)፡- የመንግስት አካሄድ ከቀን ቀን እየከፋ እየመጣ ነው ፤ ነገሩ ከተነሳበት ጊዜ አንስቶ እስከ አሁን ድረስ የምንሰማው እና የምናየው ነገር ጥሩ አይደለም ፤ በየዓመቱ ከሰኔ እስከ መስከረም አጋማሽ በቀበሌ ፤ በክፍለ ከተማ ፤ በክልል በወረዳ ደረጃ ያሉ የኢህአዴግ አባላት ጦላይ ጦር ማሰልጠኛ ካምፕ  በመላክ ፖለቲካዊ ትምህርት እንደሚማሩ ይታወቃል ፤ ሀገሪቱ በተለያዩ ሀገራት ሰላም ማስከበር ብላ የምትልካቸው ከወታደር አንስቶ እስከ ጀኔራል ድረስ ያሉ ሰዎች ጦላይ ሳይደርሱ የፖለቲካ መርፌ ሳይወጉ ደቡብ ሱዳንም ሆነ ቡሩንዲ መሄድ አይቻልም ፤ ለተራ ወታደር ከሶስት እስከ ስድስት ወር የሚደርስ በተለያዩ ነገሮች ላይ ያተኮረ ስልጠና ሲሰጥ በአመራር ደረጃ ያሉት ደግሞ እስከ ሁለት ወር የሚያቆይ ስልጠና እንደሚወስዱ ይታወቃል ፤ የዛሬ 2 ዓመት ገደማ ከተለያዩ የኦሮሚያ ክልል የሚገኙ ከ800 በላይ የኦህዴድ አባላትን ወደ አዲስ አበባ በማምጣት የተለያዩ ፖለቲካዊ የስልጣን ተዋረድ ላይ ያስቀመጣቸው ኢህአዴግ ለሁለት ወር ያህል ጦላይ ማሰልጠኛ ሄደው በቪዲዮ ኮንፍረንሲንግ ሲስተም  አማካኝነት ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጀምሮ የተለያዩ ሚንስትር ዴታዎች አማካኝነት ስልጠና ከወሰዱ በኋላ ለሁሉም አባላት አዲስ አበባ ውስጥ በኪራይ ቤቶች የሚገኙ ቤቶችን  ያለምንም ክፍያ እንደተሰጣቸው  ይታወቃል ፤ ኪራይ ቤት ለታጣላቸው ከተማዋ ውስጥ ያሉትን  ኮንዶሚኒየም ቤቶች መርጠው አባል እስከሆኑ ድረስ እንዲኖሩበት ተሰቷቸው ፤ በአሁኑም ሰዓት ድርጅቱን በማገልገል በገጸበረከት በተበረከተላቸው ቤቶች ውስጥ ኑሯቸውን እየኖሩ ይገኛሉ ፤ አሁን እኛን ይህ ጉዳይ ለመጻፍ ሳይሆን አነሳሳችን ጦላይ የጦር አካዳሚ ምን አይነት ስልጠና እንደሚሰጥ ? ፤ ምን አይነት አመራሮች ወደ ቦታ ሄደው እንደሚሰለጥኑ ?  ለምን አላማ እንደሚታጩ ? ቦታው ያለውን ገጽታ ለናንተው ለማስገንዘብ ያህል  ነው፡፡

በአሁኑ ሰዓት ጦላይ ጦር አካዳሚ ከቀበሌ አንስቶ እስከ ከተማ መስተዳድር ኃላፊዎች  ፤በክልላዊ መንግስት ደግሞ ከታችኛው ከወረዳ የስልጣን እርከን አንስቶ እስከ ክልላዊ መስሪያ ቤት ባለስልጣናት የሚገኙ የኢህአዴግ አባላትን  በመመልመል ስልጠና እየወሰዱ ይገኛሉ ፤ የትግራይ ፤ የአማራ ፤ የደቡብ እና የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስቶች የኢህአዴግ አባላት ገብተው የተማሩት ነገርና የተሰጣቸው መመሪያ ከዚህ በፊት በየዓመቱ ከሚሰለጥኑት ስልጠና የተለየ መሆኑን የደረሱን መረጃዎች ያስረዳሉ ፤ በስልጠናው ላይ ሰፊውን ጊዜ የወሰደው እና ራሳቸው ቋጥረውት አልፈታ ያላቸው ጉዳይ ቢኖር እነሱ እንደሚሉት የ”አክራሪነትና የጽንፈኝነት” አጀንዳ ነው ፤ በስልጠናው ላይ  ማህበረ ቅዱሳን የኦርቶዶክስ አክራሪ ማህበር እንደሆነ ፤ አመራሮቹ በያሉበት ቦታ ላይ ወደ ስራ ሲመለሱ አካሄዱን እንዲከታተሉትና እንዲዋጉት ፤ ከፍተኛ ክትትል በማድረግ በየደረጃ ያሉ አመራሮች እርምጃ እንዲወስዱበት ፤ ማህበሩ ጽንፈኛ አቋም እንዳለው ህገመንግስታዊ የእመነት ነጻነቶችን እንደሚጋፋ  ፤ ለሀገር አስጊ የሆነ ማህበር እንደሆነ እና መሰል ጉዳዮች ላይ ያጠነጠኑ አጀንዳዎችን በማንሳት  አስረግጠው  ለኢህአዴግ አመራር ስልጠና ሰጥተዋል ፤ ይህ መረጃ የደረሰን በስልጠናው ላይ ከተካፈሉ በአካል ከምናውቃቸው አመራሮች  አማካኝነት ነው ፤  ይህ በስልጠና ደረጃ የተደረገ ተግባር መሆኑ ለየት ያደርገዋል ፤ ሌላ ሌላውን ትተነዋል፡፡

ከሳምንት በፊት “አዲስ ራእይ” ላይ ያለውን ሀሳብ ማስረዳት እንደሞከርነው መንግስት ግቡን ለመምታት ያመቸው ዘንድ በህዝቡ መሃል ይህን ጉዳይ ለማስረጽ እና ጊዜው ሲደርስ እርምጃ ሲወስድ ጠያቂ አካል እንዳይኖር ለማድረግ በኢቲቪ አማካኝነት የተሰራውን ፊልም አስመልክቶናል ፤ የ10 ሰዓት ቃለ መጠይቅ የ1፡30 ፊልም ወጥቶታል ፤ አዲስ ራእይ መጽሄትን መሰረት አድርጎ ቀጭን መመሪያ በመስጠት በኢቲቪ ጋዜጠኞች የተሰራው ፊልም  ከአዲስ ራእይ መጽሄት ቃል በቃል ከአንድ አንቀጽ በላይ በማንበብ ለፊልሙ እንደ ግብአት ተጠቅመውበታል ፤ (የተሰራውን ፊልም ጋዜጠኛው ያነበበውን የአዲስ ራእይ አንቀጽ ከቀናት በኋላ አነጻጽረን እናቀርብሎታለን)፡፡  

ስለዚህ ይህን ስራ እየተሰራ ያለው ከጠቅላይ ሚኒስትሩ አንስቶ እስከ ታችኛው አመራር ድረስ የእዝ ሰንሰለቱን ጠብቆ መሆኑን እነዚህ ነጥቦች አስረጅ ናቸው ፤ የሚቀጥለው እርምጃው ህዝቡን እስከ ታች ድረስ ወርዶ ማወያየት ይሆናል ፤ በህዝቡ ዘንድ ተቀባይነት ለማግኝት ያስችለው ዘንድ በስትራቴጂያዊ አካሄድ ስብሰባዎች ያካሄዳሉ ፤ እስከ አሁን ድረስ ህዝቡን ያሳተፈ ሳይሆን የኢህአዴግ አባላት የጠራ አቋም በዚህ ጉዳይ ላይ እንዲይዙ ስብሰባዎችን በተለያዩ ቦታዎች ላይ አድርገዋል ፤ ቀጥሎም በእስልምናም ይሁን መልስ ተደርገው በኦርቶዶክሳዊያን የተዘጋጁ መጽሃፍቶችና ሲዲዎች ላይ ያተኩራል የሚል ወሬም ደርሶናል ፤ እያለ እያለ ግቡን እስኪመታ ድረስ የጀመረውን መንገድ ይቀጥላል ፡፡

የመንግስትን አካሄድ በመመልከት ከዚህ በፊት በንዝህላልነት ከቆምንባቸው ጊዜያት በተሻለ ሁኔታ የወደፊት የሚመጣውን ነገር ግምት ውስጥ በማስገባት ሁኔታዎችን ልንከታተላቸው ይገባናል ፤ አሁንም የተሰራውን ፊልም በደንብ ማህበረሰቡ እንዲመለከተው “በተመልካች ጥያቄ” በማለት ለቀጣይ ቅዳሜ ፊልሙን ደግመው ለማቅረብ ኢቲቪ ፕሮግራም ይዞልናል ፤ ህዝቡ የሰጠው አስተያየት አሁንም እየሰጠ ያለው ይቅርታ የሚያስጠይቅ ሆኖ ሳለ በህዝብ አስተያየት ብለው ፕሮግራሙን ለመድገም ማስታወቂያ እያስነገሩ ይገኛሉ ፤ የትኛው ህዝብ ነው ይደገም ያለው ?
የአሁኑን የጦላይ ስልጠናን ውጤት አሁን ላይ ላንመለከተው እንችላለን ከወራት በኋላ ግን ስለቤተክርስትያን ማንኛውም ምዕመን ጥያቄ ሲያነሳ የዛኔ ጦላይ የተረገዘው የሚወለድበት ጊዜ ይሆናል ፤  እንዴት ይህ ጉዳይ ከምን ተነስቶ እዚህ ደረጃ ደረሰ ብለው ሃሳብ አይግባዎት ፤ ነገ የሚደረግን ህገ-ወጥ ተግባርና የእጅ አዙር ተጽህኖን በማሰብ ራስዎን ለዚያ ጊዜ ያዘጋጁ ፤ ያለፍንበትን ያለንበትንና የምንሄድበትን መንገድ እናስተውል ፤ በግለሰብ ደረጃ አቋም ይኑረን ፡፡ ‹‹ተሰለፉ፥ ዝም ብላችሁ ቁሙ፥ የሚሆነውንም የእግዚአብሔርን መድኃኒት እዩ እግዚአብሔርም ከእናንተ ጋር ነውና አትፍሩ፥ አትደንግጡም፥›› መጽሐፈ ዜና መዋዕል ካልዕ 20 ፤17 ይላል ፡፡

ነገሮች ረገብ ሲሉ ቁጥጥሩም ላላ ሲል እንገናኛለን./……….

ቸር ሰንብቱ…..

No comments:

Post a Comment