Thursday, 5 July 2012


የታሰሩት የዋልድባ መነኰሳት በነዋሪው ተቃውሞ ለተቃጠለው የፕሮጀክቱ ዶዘር እና ለተጎዱት ሠራተኞች ሓላፊነት እንዲወሰዱ እየተገደዱ ነው



·         የወልቃይት ስኳር ልማት ፕሮጀክት ሠራተኞች በአካባቢው ሕዝብ እየተሳደዱ ነው::
·         ነዋሪው ሠራተኞቹን እስከ ማይ ገባከተማ ድረስ እንዳሳደዳቸው ተነግሯል::
·         የዓዲ አርቃይና ማይ ፀብሪ ወረዳዎች ሓላፊዎች በታሰሩት መነኰሳት እየተወዛገቡ ነው::
·         ከዋልድባ ሰቋር ኪዳነ ምሕረት ገዳም የተወሰዱት አምስት መነኰሳት በዓዲ አርቃይ ፖሊስ ጣቢያ እንደታሰሩ ናቸው::
(ደጀ ሰላም፤ ሰኔ 27/2004 ዓ.ም፤ ጁላይ 4/ 2012/ READ THIS NEWS IN PDF)፦ ባለፈው ሳምንት ቅዳሜ፣ ሰኔ 23 ቀን 2004 ዓ.ም÷ ከቀኑ ሰባት ሰዓት ላይ ከዋልድባ ሰቋር ኪዳነ ምሕረት ገዳም የተወሰዱት አምስት መነኰሳት በዓዲ አርቃይ ወረዳ ፖሊስ ጣቢያ በአንድ ቆርቆሮ ቤት ውስጥ እንደታሰሩ መኾናቸውን የስፍራው ምንጮች ለደጀ ሰላም ገለጹ፡፡


በተጠቀሰው ቀን በአራት ያህል ቶዮታ መኪናዎች በዓዲ አርቃይ ወረዳ ጸጥታ ሓላፊዎች እና በፌዴራል ፖሊስ ኀይሎች ከገዳሙ ከተወሰዱት አምስት መነኰሳት መካከል ሁለቱ ማለትም አባ ተክለ ሃይማኖት እና አባ ኀይለ ሥላሴ ወደ ዓዲ አርቃይ፤ የተቀሩት ሦስቱ ማለትም አባ ገብረ ማርያም (አባ ግርማይ)፣ አባ ኀይለ ኢየሱስ እና አባ ገብረ እግዚአብሔር በመጀመሪያ ወደ ማይ ፀብሪ (በአንዳንድ ምንጮች ጥቆማ ወደ ዛሬማ ቀበሌ) በኋላም ወደ ዓዲ አርቃይ መመለሳቸው ታውቋል፡፡ በአሁኑ ወቅት አምስቱም መነኰሳት በዓዲ አርቃይ ፖሊስ ጣቢያ በሚገኝ አንድ ቆርቆሮ ቤት ውስጥ ሌላ ሰው ሊጠይቃቸው በማይችልበት ኹኔታ ተቆልፎባቸው እንደሚገኙ ተጠቁሟል፡፡

አምስቱ መነኰሳት ለእስር በተዳረጉበት ኹኔታ ላይ የማይ ፀብሪ ወረዳ አስተዳደር ከዓዲ አርቃይ ወረዳ አስተዳደር ጋራ ውዝግብ ውስጥ መግባታቸው ተሰምቷል፡፡ የውዝግቡ መንሥኤ አምስቱ መነኰሳት የተወሰዱበት የዋልድባ ሰቋር ኪዳነ ምሕረት ገዳም በአማራ ብ/ክ/መ ሰሜን ጎንደር ዞን የሚገኝ በመኾኑና በሰሜን ምዕራብ ትግራይ ክልል ወደሚገኘው ማይ ፀብሪ ተወስደው በመታሰራቸው ላይ ሓላፊነት ላለመውሰድ ነው ተብሏል፡፡ የዓዲ አርቃይ ወረዳ አስተዳደር በበኩሉ ለአምስቱ መነኰሳት መታሰር የቅርብ ምክንያት የኾነውየስኳር ልማት ፕሮጀክቱ ዶዘር መቃጠልና በሠራተኞቹ ላይ የደረሰው ጉዳት የሚመለከተው በሰሜን ምዕራብ ትግራይ የሚገኘው የማይ ፀብሪ አስተዳደርን እንደሚል ተመልክቷል፡፡

በዚያው በዓዲ አርቃይ ወረዳ የፍትሕና ጸጥታ ዘርፍ ሓላፊው ‹‹ሓላፊነታቸውን በአግባቡ አልተወጡም›› በሚል ወደ ሲቪል ሰርቪስ እንዲዘዋወሩ መደረጉ ከዚሁ ውዝግብ ጋራ ሳይያያዝ እንደማይቀር ምንጮቹ ያላቸውን አስተያየት ጨምረው ገልጸዋል፡፡
‹‹ሕዝብን ለተቃውሞ ቀስቅሰዋል፤ ከውጭ ሚዲያዎች ጋራ ይገናኛሉ›› በሚል እየተዋከቡ ከሚገኙት ወንድና ሴት የገዳሙ ማኅበረ መነኰሳት መካከል÷ ቅዳሜ ዕለት የተወሰዱት አምስት መነኰሳት÷ ባለፈው ሳምንት አጋማሽ የዛሬማ ወንዝ ግድብ በሚሠራበት የፕሮጀክቱ ስፍራ ላይ ለተቃጠለው ዶዘርና ለተጎዱት የፕሮጀክቱ ሠራተኞች ‹‹ሓላፊነቱን ውሰዱ›› የሚል ጫና በጸጥታ ኀይሎች እየተደረገባቸው መኾኑን ምንጮቹ ገልጸዋል፡፡ አምስቱ መነኰሳት ሰኔ ሰባት ቀን 2004 ዓ.ም በዛሬማ ቀበሌ ከክልል፣ ዞንና ቀበሌ አመራሮች ጋራ ስለ ስኳር ልማት ፕሮጀክቱ (ግድቡ ግንባታ) ተደርጎ በነበረው ስብሰባ ተገኝተው የነበረ ሲኾን÷ ከእነርሱም መካከል በስብሰባው ላይ ንቁ ተሳትፎና ግልጽ ተቃውሞ ሲያሰሙ በነበሩቱ ላይ ጫናው በርትቶ እንደሚገኝ ተነግሯል፡፡

የዜናው ምንጮች ጨምረው እንዳመለከቱት÷ ፕሮጀክቱ በዋልድባ ገዳም ህልውናና ክብር ላይ ከሚያደርሰው ተጨባጭና ታሳቢ ስጋቶች የተነሣ በአካባቢው የተቀሰቀሰው ተቃውሞ በያዝነው ሳምንትም ተጠናክሮ ቀጥሏል፡፡

ባለፉት ቀናት ነዋሪው በጦር መሣርያ ሳይቀር የፕሮጀክቱን ሠራተኞች የፕሮጀክቱ ጽ/ቤት እስከሚገኝበት ማይ ገባ ወረዳ (ከተማ) ድረስ እያስፈራራ ማሳደድ መጀመሩም በአስረጅነት ተጠቅሷል፡፡ ከፕሮጀክቱ ስፍራ በእግር አንድ ሰዓት ወደሚወስደው የሠራተኞች መኖርያ እና የፕሮጀክቱ ጽ/ቤት ወደሚገኝበት ማይ ገባ ከተማ እግሬ አውጭኝ ብለው ከሸሹት ሠራተኞች መካከልም በጥይት ተመትተው የቆሰሉ ሳይኖሩ እንደማይቀር ተገምቷል፡፡

ቸር ወሬ ያሰማን፣
አሜን።

2 comments:

Dillu Zegeye said...
የላይኛው ጠለምት ፣ የዲማ ምጫራ ፥ የዲማ ሰቆጣ ፥ የግልቤና ፥ የጭንፍራ ። የድብ ባሕር ወርዳ ፣ የላሄን ፥ የአድ አርቃይ ፥ የብራና ዋስያ ። የበየዳ ወረዳ ፣ የልዋሬ ፥ የሰየምት ፥ የፎጋይ ። የመላው ጃናሞራ ሕዝብ ፤ የደባርቅ ውረዳ ሕዝብ ማለት የእንጎት ፥ የቦዛ ፥ የሳንቅ -ቆላ ወገራ ፤ የመላ ጠገዴ ሕዝብ ፣ የመላ ወልቃይት ሕዝብ፤ የደጋ ወገራ ፥ የጉንዳ መረባ ፥ የጃኒፈንቀራ ፤ የጃንወራ ፥ የአጅሬ ..ሕዝብ ታሪካዊውንና መንፈሳዊውን የዋልድባ ገዳም ክጥፋት ለማዳን ከአስመሳዮቹ ሳይሆን ከእውነተኛ መናንያኑ መነኮሳት ጋር አብረህ እንድትቆም ፈጣሪህ እግዚአብሔርና ታሪክ አደራውን የጣሉብህ መሆኑን ልትዘነጋው አይገባም። ዋልድባ የቅዱሳን መካነ መቃብር ብቻም ሳይሆን የፀረ ፋሺስቱ ብሔራዊ ጀግኖቻችን የነ ዳጃዝማች ነጋሺ ወርቅነህና ብዙ ስፍር ቁጥር የሌላቸው ወገኖቻችንም ክቡር አጽም የሚገኝበት ቅዱስ ቦታ ነው። ስለዚህ አይዞህ አምላከ ቅዱሳን ካንተ ጋር መሆኑን ሳትጠራጠር ለዚህ ቅዱስ ገዳም ዘብ ቁም !!

No comments:

Post a Comment