Thursday, 5 July 2012


ሰበር ዜና - የዋልድባ ሰቋር ኪዳነ ምሕረት ገዳም በፌዴራል ፖሊስ ተከቧል


·        አራት መነኰሳት በፖሊስ ተይዘው ተወስደዋል፤ ሌሎቹ መነኰሳት እየተደበደቡ ተበታትነዋል።
·        የገዳሙ የሱባኤ ወቅት በፖሊስ የኀይል ርምጃ እየታወከ ነው።
·        በዛሬማ ወንዝ ላይ የሚገነባውን የወልቃይት ስኳር ልማት ፕሮጀክት ግድብ የሚሠራው ሱር ኮንስትራክሽን  ለቆ መውጣቱ እየተነገረ ነው፤ በምትኩ የቻይና ተቋራጭ የገባ ቢኾንም በእርሱም ላይ ተቃውሞው መቀጠሉ ተሰምቷል።
(ደጀ ሰላም፤ ሰኔ 24/2004 ዓ.ም፤ ጁላይ 1/ 2012/ READ THIS NEWS IN PDF)፦ በሰሜን ጎንደር ሀ/ስብከት ዓዲ አርቃይ ወረዳ የዋልድባ ሰቋር ኪዳነ ምሕረት ገዳም ከማይ ፀብሪና ዓዲ አርቃይ ወረዳዎች በአምስት መኪና ተጭነው በመጡ የፌዴራል ፖሊስ ኀይሎች ሥምሪት ውስጥ እንደሚገኝ የስፍራው ምንጮች ለደጀ ሰላምገለጹ፡፡


ትናንት፣ ሰኔ 23 ቀን 2004 ዓ.ም፣ ከቀኑ ሰባት ሰዓት ጀምሮ ገዳሙን በተቆጣጠረው የፖሊስ ኀይል አራት የገዳሙ መነኰሳት ተይዘው ወደ ወረዳው ፖሊስ ጣቢያ የተወሰዱ ሲኾን ሌሎቹ መነኰሳት ደግሞ ለሱባኤ (ሕርመት) ከተሰበሰቡበት በቆመጥ እየተደበደቡ መበታተናቸው ተጠቁሟል፡፡

ከአራቱ መነኰሳት መካከል ሦስቱ፣ አባ ኀይለ ኢየሱስ፣ አባ ግርማይ፣ አባ ገብረ እግዚአብሔርእንደሚባሉ ተረጋግጧል፤ የአራተኛውን መነኰስ ስም ለማወቅ አልተቻለም፡፡ ማኅበረ መነኰሳቱን የማሳደዱ ተግባር ከገዳሙ ውጭም የቀጠለ ሲኾን ፖሊስ አባ ገብረ ሕይወት የተባሉ ሌላ የገዳሙ መነኮስን ለመያዝ በደባርቅ ከተማ አሠሣ እያደረገ መኾኑ ተገልጧል፡፡ የአሠሣው እና ስምሪቱ መጠናከር ምክንያት፣ ከግንቦት 22 ቀን አንሥቶ የዋልድባ ሰቋር ኪዳነ ምሕረት ገዳም ሴት መነኰሳዪያት፣ የወልቃይት ስኳር ልማት ፕሮጀክት በገዳሙ ላይ የሚያደርሰውን አካባቢያዊና ማኅበራዊ ጉዳት በመቃወም “ኑና ገዳሙን ተረከቡ፤ እኛ መሰደዳችን ነው” በሚል ለሕዝቡ ጥሪ ካስተላለፉ በኋላ በተለይም በዛሬማ ቀበሌና በእንዳባጉና ወረዳ ዲማ ቀበሌ እየተጠናከረ የመጣው የተቃውሞ እንቅስቃሴ መኾኑ ተመልክቷል፡፡  

በዋልድባ አብረንታንት ገዳም፣ በዋልድባ ሰቋር ኪዳነ ምሕረት ገዳም እና በዋልድባ ዳልሽሐ ኪዳነ ምሕረት አንድነት ገዳም በየዓመቱ ከሰኔ 21 - ኅዳር 8 ቀን የሱባኤ ወቅት ነው፡፡ ገዳሙ ዓመት እስከ ዓመት ሱባኤ የሚያዝበት፣ አባቶች ያለማቋረጥ ከእግዚአብሔር የሚገናኙበት የሰማይ በር ቢኾንም፣ ይህ ወቅት ግን ከሌላው ጊዜ ተለይቶ ማንም አቋርጦ ለመውጣት የማይፈቀድበት ነው፡፡ በአንድነትና በፍቅር ተሰብስበው የሚኖሩትማኅበረ መነኰሳት ጭው ካለው በርሓ ገብተው በቋጥኝና በዋሻ እንደሚኖሩት ግሑሳን ባሕታውያን ከሰው ተለይተው በአንድ ቦታ ተወስነው በጾም፣ በጸሎትና በስግደት መንፈሳዊ ተጋድሏቸውን የሚያጠናክሩበት ወቅት ነው፡፡

ዋልድባን በአራቱም ማእዝናት የከበቡት የእንሰያ (ምሥራቅ)፣ ዛሬማ (ምዕራብ)፣ ተከዜ (ሰሜን)፣ ዛሬማና ወይባ(ደቡብ) የተሰኙት ታላላቅ ወንዞችም በሰኔ የሞሉ እስከ ኅዳር አይጎድሉም፡፡ ከሱባኤው ፍጻሜ በኋላ፣ ኅዳር ስምንት ቀን የአርባእቱ እንስሳ ክብረ በዓል ቀን፣ ወንዞቹን ተሻግረው በምሥራቅ - ፀለምትና በምዕራብ - ወልቃይት በሚገኙ የገዳሙ እርሻ ቦታዎች ከተዘጋጀው ድግስ የሚቀምሱ አሉ፡፡ ለዚህም በተለይም ማይ ለበጣታላቁ የማኅበሩ መገናኛ ቦታ ነው፡፡

የዘንድሮው የገዳሙ የሱባኤ ወቅት ግን ይህን ለዘመናት የቆየ የአበው ሥርዐትና ትውፊት የሚደግምበትን የጥሞና ጊዜ የታደለ አይመስልም፡፡ የወልቃይት ስኳር ልማት ፕሮጀክት በገዳሙ ህልውናና ክብር ላይ በጋረጠው ስጋት ሳቢያ የሰቋር ኪዳነ ምሕረት ማኅበረ መነኰሳት በተለይም ከግንቦት 22 ቀን ጀምሮ “ኑ ፣ ታቦቱን፣ ቅርሱን ተረከቡ፤ እኛ እንፈልሳለን (ወደ በርሓ እንሰወራለን)” በሚል ለምእመኑ መልእክት አስተላልፈዋል፡፡ ይህን ተከትሎም ከስድስት ያላነሱ የዓዲ አርቃይ ወረዳ ቀበሌዎች (ሳንቅ፣ ዛሬማ፣ ያሊ፣ የጥራይና፣ ጅሮሰ፣ ነብራና ፍድቃ) አርሶ አደሮች ከግንቦት 23 እና 24 ቀን አንሥቶ ዛሬማና ሰቋር ላይ በመሰብሰብ ተቃውሟቸውን አጠናክረው መቀጠላቸው ተነግሯል፡፡

የአማራ ብ/ክ/መ ፖሊስ ኮማንደርና የሰሜን ጎንደር ዞን ብአዴን ጽ/ቤት ሓላፊ ግንቦት 27 እና 28 ቀን ዛሬማ ቀበሌ ላይ የወረዳ አመራሮችንና ምእመኑን በአንድነት ጠርተው ስለ ፕሮጀክቱ ለማሳመን ስብሰባዎችን አካሂደዋል፡፡ ይኹንና በዚያው ዛሬማ ቀበሌ የመድኃኔዓለም ታቦት ማረፊያ ዋርካ ሥር በመገናኘት ስብሰባው አሳታፊ አለመኾኑንና በስብሰባው ላይ ተገኝተው አቋማቸውን እንዳይገልጹ መከልከላቸው አግባብ አለመኾኑን በመቃወም እስከ 50 ያህል ወጣቶችን ለእስር ከመዳረግና በጭከና ከመደብደብ በቀር ውጤት እንዳላስገኘላቸው ነው የተዘገበው፡፡ ግንቦት 29 ቀን ከታሰሩት ኀምሳዎቹ ወጣቶች መካከል “ወጣቱን ለስብሰባና ሰላማዊ ሰልፍ ቀስቅሰዋል፤ ከተቃዋሚዎች ጋራ በመገናኘት እንቅስቃሴውን አስተባብረዋል፤” በሚል ስምንት ወጣቶች ተለይተው ከዛሬማ ቀበሌ 40 ኪ.ሜ ወደሚርቀው የወረዳው ከተማ (ዓዲ አርቃይ ፖሊስ ጣቢያ) ሲወሰዱ ሌሎቹ በዋስና በገንዘብ ቅጣት ደረጃ በደረጃ መለቀቃቸው ተገልጧል፡፡

ይህ ሁሉ ሲኾን የዋልድባ ገዳም የሚገኝባቸው ሦስቱ አህጉረ ስብከት ይኹን ወረዳ ቤተ ክህነት ጽ/ቤቶች ድምፃቸውን ባለማሰማታቸው ምእመኑ ከዘንድሮው ዓመት ጀምሮ “የነፍስ ዐሥራት በኵራት” ሲል የሚጠራውን መባዕና የሰበካ ጉባኤ አስተዋፅኦ እንደማይከፍል ለወረዳ ቤተ ክህነት በጻፈው ደብዳቤ ማስታወቁ ተመልክቷል፡፡ የወረዳ ቤተ ክህነት ጽ/ቤቱ ጉዳዩን ለአህጉረ ስብከቱ ጽ/ቤቶች ያስታወቁ ቢኾንም ምን ምላሽ እንደተሰጠ ለማወቅ አልተቻለም፡፡

የተቃውሞው ከዕለት ወደ ዕለት መጠናከር ያሳሰበው የክልሉ (የአማራ ብ/ክ/መ) አስተዳደር፣ ፕሬዝዳንቱን አቶ አያሌው ጎበዜን፣ የክልልና ዞን ጸጥታ ሓላፊዎች እንዲሁም የብአዴን ጽ/ቤት ሓላፊዎች በተገኙበት ሰኔ ሰባት ቀን 2004 ዓ.ም ዓዲ አርቃይ ላይ ስብሰባ ጠርቶ ነበር፡፡ በዚህ ስብሰባ ከዋልድባ አብረንታንት ቤተ ጣዕማና ቤተ ሚናስ፣ የሰቋር ኪዳነ ምሕረትና ዳልሽሓ ኪዳነ ምሕረት ገዳማት ከእያንዳንዳቸው ዐሥር፣ ዐሥር መነኰሳት፤ 28 የቀበሌ አመራሮችና “የልማት አርበኛ” የተሰኙ አርሶ አደሮች እንዲሳተፉ ጥሪ ተደርጎላቸው ነበር፡፡

የክልል፣ የዞንና ወረዳዎች (ደባርቅ፣ ፀለምት - ማይ ፀብሪ፣ ዓዲ አርቃይና ጎንደር) አመራሮች የታደሙበት ይኸው ስብሰባ ልጆቻቸው በታሰሩባቸው ወላጆች ጥያቄ ከዓዲ አርቃይ ወደ ዛሬማ እንዲዞር የተደረገ ቢኾንም በስብሰባው ከተሳተፉት ብዙኀኑ “ከጎንደር እስከ ማይ ፀብሪ ያሉ የኢሕአዴግ ደጋፊዎችና የተለየ ሐሳብ የማያነሡ ናቸው” ብለዋል ታዛቢዎች፡፡ ከዋልድባ አብረንታንት ዘቤተ ጣዕማ ስድስት መነኰሳት ቢገኙም ከዋልድባ አብረንታንት ዘቤተ ሚናስ ማኅበር የታየ አልነበረም፡፡ ከሰቋር እና ዳልሽሓ የተገኙትም የተወሰኑት የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ኤልሳዕ በጸሎት ሲያሳርጉ ከመሰብሰቢያው ወጥተው ሄደዋል፤ የቀሩትም ባሉበት በመቀመጥ ተቃውሟቸውን ገልጸዋል፤ መስቀላቸውንም ለመሳለም ፈቃደኛ አልኾኑም፡፡

በዚሁ ስብሰባ እንደ ማይ ፀብሪው አስተዳዳሪ አቶ ሲሳይ መረሳ ያሉ የመንግሥት ባለሥልጣናት፡- “ሃይማኖትን ሽፋን እያደረጋችኹ የፖለቲካ ዘመቻ ታደርጋላችኹ፤ የፀረ ሰላም፣ ፀረ ልማት ተቃዋሚ ፓርቲዎች ሰለባ ኾናችኋል፤ የእነርሱን ድምፅ ነው የምታስተጋቡ” በማለት ግልጽ ዘለፋ ማሰማታቸው ተገልጧል፡፡ “ብትስማሙና ልማት ቢለማ ምናለበት?” የሚሉ ልመናዎችም ተደምጠዋል፡፡ መነኰሳቱ በበኩላቸው “በልቅሶ ነው ያለነው፤ ዐፅም ወጥቶ ውኃ አይቆምም፤ ቤተ ክርስቲያን እየፈረሰ በሚለማ ልማት አንስማማም፤ ዋልድባ ቅንጣት ያህል አትነካም›፤ ይህ የሃይማኖት ጉዳይ እንጂ ፖለቲካ አይደለም” በሚል ቁርጡን ማስታወቃቸው ተነግሯል፡፡

በዚሁ ስብሰባ ዋዜማ፣ ሰኔ ስድስት ቀን 2004 ዓ.ም፣ በዓዲ አርቃይ ከተማ አስጋሪት ማርያም በተሰኘችው ቤተ ክርስቲያን ውስጥ የተገናኙ የከተማው ወጣቶች ስብሰባው ወደሚካሄድበት ዛሬማ ቀበሌ በመሄድ ድምፃቸውን ለማሰማት እየተመካከሩ በነበረበት ወቅት የወረዳው ፖሊስ ደርሶ በሽመል በመደብደብ እንዲበተኑ ማድረጉን የዐይን እማኞች ተናግረዋል፡፡ በወረዳው ፖሊስ ጣቢያ ፊት ለፊት በምትገኘው የእመቤታችን ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ተሰብሰበው የነበሩት ቁጥራቸው ከ30 የማያንሱ ወጣቶች ከተበታተኑ በኋላ ፖሊስ በየቤቱ በመዞር ወላጆች ልጆቻቸውን ይህን ዐይነቱ የተቃውሞ ምክክር ከማድረግ እንዲቆጠቡ የማይመክር ከኾነ ጥብቅ ርምጃ እንደሚወስድባቸው ሲያሳስብ መዋሉ ታውቋል፡፡

በተያያዘ ዜና፣ ንድፉ በትግራይ ውኃ ሥራዎች ዲዛይንና ሱፐርቪዥን ተሠርቶ በትግራይ ውኃ ሥራዎች ኮንስትራክሽን ግንባታው የተጀመረውን የዛሬማ ወንዝ ግድብ ሥራ ተረክቦ ሲመራ የቆየው ሱር ኮንስትራክሽን ሥራውን አቋርጦ መውጣቱ ተሰምቷል፤ ምክንያቱ ቁፋሮው የሚካሄድበት ቦታ ከመሬት በሚፈልቅ ውኃ እየተሞላ ማስቸገሩና የምእመኑ ተቃውሞ ያሳደረው ግፊት ነው ተብሏል፡፡ በአሁኑ ወቅት ስሙ ያልተገለጸ አንድ የቻይና ተቋራጭ የግድቡን ሥራ ለመቀጠል የተተካ ቢኾንም በተመሳሳይ አስቸጋሪ ኹኔታ ውስጥ እንደሚገኝ ተዘግቧል፡፡ የሱር ኮንስትራክሽን መውጣት ከተጠቀሰው ምክንያት ጋራ መያያዙን የሚጠራጠሩ ሌሎች ምንጮች በበኩላቸው፣ በግድቡ ዲዛይን (የስኳር ልማት ፕሮጀክቱ ውኃ አጠቃቀም) ላይ መሠረታዊ ለውጥ በማድረግ ሥራውን ለመቀጠል ሳይታሰብ እንዳልቀረ ያላቸውን ሐሳብ ገልጸዋል፡፡
ቸር ወሬ ያሰማን፣
አሜን።

7 comments:

Anonymous said...
ያገሬ ወጣት፤ ይኽ ከዛሬ ፩ ሺ ፪፻ ዓመት ጀምሮ ኢትዮጵያን የማጥፋት ዕቅድ አንዱ ክፍል ነው። እስከ ፳ኛው ክፍለ ዘመን በወረራና ነገሥታቱን በማታለል ተሞክሮ ብዙ ብዙ ጥፋት አድርሰውብናል። ዋልድባ ባድማ እስኪሆን ድረስ፤ አክሱም የከርከሮ መፈንጫ፣ ደብረ ሊባኖስ የዛር መንደር ሆነው ነበር። ባለፉት ፷ ዓመታት ግን ከውስጣችን ባንዶችን በመመልመል፤ ራሳችንን በራሳችን [እርስ በርሳችን] እንድንጠፋፋ የደገሱት የተሳካላቸው ይመስላል።
የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ከምድረ ገጽ እንድትጠፋ ከሚሹት መኻከል ዋነኛዋ ቫቲካን ናት። ቫቲካን [ይኸን ቃል የምጠቀመው መሪዎቹን ከምእመኑ ለመለየት ነው]፤ አቅም በተሰማት ጊዜ ሁሉ በኢትዮጵያ ላይ ከመዝመት ተቆጥባ አታውቅም። ስለዚህም በቤተ ክህነት እንደነ አባ ጳውሎስ ያሉ ኑፋቄን በገሃድ የሚዘሩ፤ በመንግሥት ሥልጣን ላይ ደግሞ አገርን በሕገ መንግሥት የሚያፈርሱ እንዲቀመጡ ለማድረግ ጣሊያን ከወጣ ጀምሮ ጉድጓድ ስትምስ ኖራለች።
ይኽ ሁሉ ድካሟ ለምንድነው የሚሉ ጥያቄዎች ይነሱ ይሆናል፤ መልሱ ኑፋቄዋን በአደባባይ የምትረታት የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ብቻ ስለሆነች ይሆናል።
ታስታውሱ እንደሆነ ከ፲፱፻፹፬ - ፲፱፻፹፯ ዓ.ም. ድረስ ከፍተኛ የተደራጀ የመጻሕፍት ዘረፋ በጎንደር፣ በጎዣም፣ በሸዋና በወሎ በግልጥ ይካሔድ ነበር። ይኽ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን እነኛን ለማስረጃ ትጠቀምባቸው የነበሩትን መጻሕፍት አስወግዶ፤ በሌሎች በ፲፯ኛው ክፍለ ዘመን ግዕዝ በተማሩ ጀስዊቶች የተጻፉ፤ በኑፋቄ የተሞሉ የብራና መጻሕፍት ለመተካት ነበር። ከአስር ዓመታት በኋላም እነዚያ መጻሕፍት ወደ አማርኛ “በሊቆች” እየተተረጎሙ፤ ለኛ ለማይማኑ እየተሸጡ ይገኛሉ። እናም ጎበዝ ግዕዝ ማንበልበልና ወደ አማርኛ መተርጎም የዘመናችን የመናፍቃን ስልት ሆኗልና እንወቅባቸው።
ደርግ የጥንት ታሪካችንን በሩሲያ አብዮት ታሪክ ቀይሮ እኛነታችንን እንድንዘነጋ አደረገ፤ ታሪክ ዐዋቂ የነበሩትንም ገድሎ በመጨረሱ ታሪኩን በደንብ የማያውቅ ትውልድ ሆነ የዛሬው ወጣት። ስለዚህም በአሁኑ ጊዜ አጭበርባሪዎች እንደ ፍላጎታቸው ሊዘውሩት እየሞከሩ ይገኛሉ።
ወደ ዋናው ነገር ልመለስና፤ ዛሬ በዋልድባ ላይ የተዘመተው የዚህ የጥፋት ዘመቻ ዋናውና ምናልባትም የመጨረሻው ምዕራፍ ላይ የደረሱ ስለመሰላቸው ነው። ይሁንም እንጂ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን መሠረቷ አለቱ ኢየሱስ ክርስቶስ ስለሆነ አይሳካላቸውም፤ እኛ ግን ከታሪክና ከኅሊና እንዲሁም ከአምላካችን ወቀሳ ለመዳን የሚገባንን ሁሉ ማድረግ ይጠበቅብናል።
Anonymous said...
መዝሙር 21
እጅህ ጠላቶችህን ሁሉ ታግኛቸው፥ ቀኝህም የሚጠሉህን ሁሉ ታግኛቸው።

9 በተቈጣህም ጊዜ እንደ እሳት እቶን አድርጋቸው፤ እግዚአብሔር በቍጣው ያጠፋቸዋል፥ እሳትም ትበላቸዋለች።

10 ፍሬአቸውን ከምድር ዘራቸውንም ከሰው ልጆች ታጠፋለህ።

11 ክፋትን በአንተ ላይ ዘርግተዋልና፥ የማይቻላቸውንም ምክር አሰቡ።

12 ወደ ኋላቸው ትመልሳቸዋለህ፤ ፍላጻን በፊታቸው ላይ ታዘጋጃለህ።

13 አቤቱ፥ በኃይልህ ከፍ ከፍ በል፤ ጽናትህንም እናመሰግናለን እንዘምርማለን። abetu ye honebenen neger aseb.
Anonymous said...
"አቤቱ የሆነብንን አስብ፤ ተመልከት ስድባችንንም እይ። ርስታችን ለእንግዶች ፥ ቤቶቻችን ለሌሎች ሆኑ። ድሀ አደጎችና አባት የሌለን ሆነናል፤ እናቶቻችን እንደ መበለቶች ሆነዋል። ውሃችንን በብር ጠጣን ፡ እንጨታችንን በዋጋ ገዛን። አሳዳጆቻችን በአንገታችን ላይ ናቸው ፤ እኛ ደክመናል ዕረፍትም የለንም።" ሰቆቃወ ኤርሚያስ 5:1-5
asbet dngl said...
አይዞችሁ ጌታ ቅርብ ነው:: በአጭር ቀን በርግጠኝነት ለውጥ እናያለን:: ለሁሉም በጾለት እንበርታ::
የቋራው said...
አሁን ሰዓቱ ወደመፍትሔው መሄድ ብቻ ነው ነገሩን ለመዘበዝብ ጊዜው እያጠረ ነው። ይመፍትሔው ይህ ነው፦ መጀመሪያ በቤተክርስቲያናችን ከፍተኛ የአመራር ቦታ የተቀመጡትን ሰዎች የቤተክርስቲያናችንን መብትና ጥቅም ስላላስከበሩ ማስወገድና በምትካቸው ለቤተክርስቲያን እስከሞት ድረስ ለመታመን የሚችሉትን ማስቀመጥ ነው። ትልቁ ችግር ይህ ሁሉ ግፍ በዚህች ቤተክርስቲያን ላይ ሲፈጸም የቅዱሳን አገር እንዲህ ስትወድም እኛም አብረን ከእነርሱ ጋር በመሆን የአጥፊቹ ስም ካልተጠራ ምናምን እያልን፤ እንዲሁም በቤተክርስቲያን ላይ በመንግስት እየተፈጽሙ ያሉትን በደሎች መቃወም ፖለቲካ ውስጥ መግባት እንደሆነ በመቁጠር የጥፋቱ ተባባሪዎች ሆነን እንገኛለን። አንቱ ብሎ ስድብ የለም ይላል ያገሬ ሰው። ምን እስኪሆን ነው የሚጠበቀው? ድሮውንም ስርዓት አፍርሰው መንበረ ፕትርክናውን አፋልሰው ስለሆነ በስልጣን ላይ የተቀመጡት ለስልጣንና ለገንዘብ ብቻ እንጅ ለቤተክርስቲያን እንደማይገዳቸው ከታወቀ ቆይቷል። ከ40-50 ሺህ ሰው የሥራ እድል ይፈጥራል ብለው ሊያሞኙን ሞክረዋል። በዚህን ያህል የሰው ቁጥር የተመሰረተ ከተማ ወደፊት ከ40 እና 50 ዓመት በኋላ 200ሺህ እስከ 300ሺህ ሰው የሚኖርበት ታለቅ ከተማ መሆኑ ሳይታለም የተፈታ ነው። ይህ ሁሉ ሰው ደግሞ የሚኖረው ግድቡ ውሃ ውስጥ ሳይሆን ለመኖር ምቹ ወደሆነው ቦታ ሔዶ ነው። በዛሬማ ወንዝ ላይ ድልድይ ሰርቶ መሃል ገዳሙ ውስጥ መከተሙ አይቀሬ መሆኑን መረዳት እንዴት ቅዱስ ሲኖዶስ ጠቅላይ ቤተክህነት ሳያስተውሉት ቀረ? ሁሉም ለሆዱ ብቻ ያደረ ስለሆነ ምን ይደግ? የሚደረገውማ በቃ በቃችሁን ብሎ ማስወገድ ነው። ይህ ደግሞ ስማቸውን ባለመጥራት፣ የእነርሱን ቡራኬ ባለመሳተፍ፣ እነዚህን የቤተክርስቲያንና የአገር አጥፊዎች አሽቀንጥሮ ለመጣል በሚደረገው ትግልና እንቅስቃሴ ውስጥ ሁሉ ተሳትፎ በማድረግ ነው። የሰው ሥራ አለ የእግዚአብሔር ሥራ አለ እኛ የራሳችንን ሳንሰራ ከእግዚአብሔር ብቻ ብንጠብቅ መልስ አይገኝም። ቤተክርስቲያንና አገርን ከሚያጠፉ ሰዎች ዘንድ እንለይ። ከዚያ በኋላ ጸሎት ብቻ ስራቸው ለሆነው በጸሎት እንዲያግዙን እንንገር መስራት የምንችለው ደግሞ በሁሉም ዘርፍ ቤተክርስቲያናችንን ለማስከበር እንነሳ። አለበለዚያ ቱርክን ግብጽን ወዘተ መሆናችን አይቀርም!
haile michael zedebretsige said...
የቅድሰት ቤተክርስቲያን የመጨረሻው የላዕላይ ሥልጣን ያለው ቅዱስ ስኖደስ እንደሆነ ይታወቃል :: ይህ ቅዱስ ስኖደስ የሚወስናቸው ውሳኔዎች በመንፈስ ቅዱስ መሪነት ለቤተክርስቲያን የሚበጁ እንደሆነ ተግባራዊም መደረግ እነዳሉበት እሙን ነው::ነገር ግን ቅዱስ ስኖደስ የሚወስናቸው ውሳኔዎች በፓትርያርኩ እምብተኝነት በመንግሥት ከለላ ሰጭነት ተግባራዊ መደረግ ከተተው ቆይቶአል፡፡ ቅዱስ ስኖደስም ጥርስ የሌለው አንበሳ ሆኖአል ማለት ይቻላል፡፡ይህን በማየታችንም የቅድሰት ቤተክርስቲያን ልጆች በቁጭት ከመብገን ባለፈ መፍትሔ ማምጣት አልቻልንም፡፡ይልቁንም መፍትሔ ማማጣት ያለባቸው አባቶች ጳጳሳት ብቻ እንደሆኑ በማመን በአባቶች ላይ ያለንን ተስፋ እስከ መቁረጥ የደረስንም አለን፡፡ ይህንንም በደጀ ሰላም በአንድ አድርገን የጡመራ መድረኮች ከምሰጡ አስተያያቶች መረዳት ይቻላል፡፡



ስጀምር ስለ ቤተክርስቲያን ችግር እንደየሚናችን ሁላችንንም እንደሚያገባን መረዳት አለብን ፡፡አባቶች ድቁና ቅስና ልሾሙ እኛ ምእመናን የሚንመሰክርበት አሠራር መኖር አለበት፡፡ እርግጥ ነው ሊያሥር ልፈታ ልያጠምቅ ቀድሶ ልያቆርብ አንድ ሰው የግድ ቅስናና ከዚያ በላይ የክህነት ደረጃ ልኖረው ግድ ይለዋል ፡፡ ግን አንድ ሰው ካህን ስላልሆነ በአስተዳደር በገንዘብ አያያዝ ጉዳይ ወዘተረፈ አያገባውም ማለት አይደለም ፡፡



በእርግጥ አባቶች መሔድ ያለባቸውን ደረጃ እስከመጨረሻ ሔደዋል የሚል ድምዳሜ ባይኖረኝም ከአቅማቸው በላይ የሆነ ጉዳይ ያለ ይመስለኛል:: እንደ እኔ እምነት አብዘኞቹ አባቶች ስለቤተክርስቲያን ነፍሳቸውን እንኩዋን አሳልፈው ልሰጡ የተዘጋጁ ናቸው::ነገር ግን ነፍሳቸው አልፋ ሥራ መሠረት አለበት ::የደርግ መንግሥት ብሆን ገድሎ ስለምፎክር አባቶች ለሃይማኖታቸው ስሞቱ ምእመኑ ይሰማል ወደ ቀጣይ እርምጃም የሔዳል: አሁን ባለው ሁኔታ ግን ገና ከማሰባቸው ልገደሉ ይችላሉ:: በሌላ ምክንያት እንደ ሞቱም የውሸት ወሬ ወዲያው ይቀነባበራል ፡፡ስለዚህ አባቶች ሥራ የማይሠራበት ለምእመናን ስለ ሃይማኖታቸው ጥብዐት የማይጨምር ከንቱ ሞት ከምሆን ጊዜ ከመጠበቅ ወጭ ምንም ማድረግ አይችሉም፡ ታፍነዋል፡፡



መፍትሔው ያለው በምእመናን እጅ ነው፡፡

1)ምእመናን በአንድነት መንግሥት በሃይማኖታችን ጠልቃ መግባቱን እንዲያቆም ይልቁንም ቤተክርስቲያኒቱን ለማዳከም ከሚሠራው ግልጽና ስውር ሤራ እንዲታቀብ መጠየቅ ፡፡ይህንን በግንባር ቀደምትነት በማስተባበር የሰንበት ትምህርት ቤቶች ትልቅ ሚና መጫወት ይችላሉ ፡፡ ምቹ ሁኔታ ያላቸውም እነርሱ ናቸውና ::

2)በቤተክርስቲያን ጉዳይ ሁሉም ምእመን እንደሚያገበው መረዳት

3)በየትኛው የቤተክርስቲያን አገልግሎት ማን መሳተፍ እንደሚችል ግልጽ ግንዛቤ መያዝ

4)ሕግጋተ ቤተክርስቲያንና ሥርዓተ ቤተክርስቲያንን ማወቅ

ከላይ ከ2-4 የተጠቀሱትን ለማሳወቅ መምህራነ ቤተክርስቲያን ትልቅ ኃላፊነት አለባቸው፡፡

የሰማን በማሰማትና በማስረዳት ዛሬ ነገ ሳንል መሥራት ያለብን ይመስለኛል፡፡ ምክንያቱም የቤተክርስቲያን ጉዳይ ከእጃችን ወደ መውጣት እየተቃረበ ነው፡፡

ፓትርያርኩ ከውስጥ የተሐዲሶ መናፍቃን አርበኞችን ሲያደራጁ መንግሥት ከውጭ የሃይማኖት ነጻነት በሚል በፍርድ ቤት ቤተክርስቲያንን ለሁለት ለመክፈል እየቁዋመጠ ነው፡፡

መንግሥት ቤተክርስቲያንን ለማዳከም ከመጀመሪያው አጀንዳ እንደ ነበረው ከዚህ በፊት በሰፊው ማንበባችንና ማስነበባችን ይታወሳል፡፡

ይህ ስባል “እግዚአብሔር ያውቃል መጸለይ ብቻ……” የሚትሉትን ረስቼ አይደለም:: ግን እግዚአብሔር በሰው አድሮ እንደሚሠራ መረዳት ያለብን ይመስለኛል :: በእርግጥ ሁሉም በጎ ሥራ በጸሎትና በእግዚአብሔር ኃይል ነው የሚሠራው፡፡

የቤተክርስቲያን ጉዳይ ሳይቃጠል በቅጠል እንዲሉ ከእጃችን ሳይወጣ ዛሬ ነገ ሳንል እንታደግ ፡፡
Anonymous said...
ከዚህ በላይ መልዕክታቸውን የተውት "የቋራው" በሚል እራሳቸውን የጠሩት ሰው በትክክል ያስቀመጡት ይመስለኛል ከዚህ ወዲያ እነዚህን በቤተክነቱ ውስጥ ተሰግስገው የቤተክርስቲያኗን ደም የሚመጡ ወዲያ ትቶ ሥራን መስራት ይሻላል ካህናት፣ ቆሞሳት፣ ጳጳሳት ስም ብቻ ከፈጣሪ ካላገናኙን ወይ የእምነት ተቋማችን እንዲህ መንግሥት እንዳሻው ሲያደርጋት ዝም የሚሉ ከሆነ ህሄ ሃገረ ስብከቴ አይደለም ካሉ እነሱ ለነፍሳቸው ሳይሆን ለሆዳቸው ያደሩ ናቸው ማለት ነው በእውነት በተለይ አሜሪካን ሃገር የሚኖሩ መነኩሳት ካህናት ቀሳውስት እንዴት ስለ ቤተክርስቲያን መናገር ይከብዳቸውል ቤተክርስቲያና እኮ ናት እዚህ ያደረሰቻቸው እነዙ ግን ፈረጅያቸውን ለብሰው መኮፈስ እና እኛ ፖለቲካ ውስጥ አንገባም እያሉ እራሳቸውን መኮፈስ ብቻ በእውነት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ አማኞች በሙሉ መስቀላቸውን እንኳ መሳለም የለባችሁም እውነቱ መናገር እስካልቻሉ ድረስ እስከ መቼ ስንጠፋ ዝም ብለው የሚመለከቱ ከሆነ እኔ በበኩሌ ከተራ ካድሬ ለይቼ አላያቸውም ተራ ዱርዪዎች ናቸው ብዪ ነው የማምነው እንዴት እዚህ ደረጃ ያደረሱንን ወላጆቻችንን እንክዳለን እናቴ በችግር ተቆራምዳ ጠላ ሸጣ እንጨት ሰብራ የቀይ ጥቁር ሆና ያሳደገችንን እናቴን እንዴት በችግሯ በመጦሪያዋ ጊዜ እክዳታለሁ እንዴት ከመሰል አብሮ አደግ የሰፈሬ ልጆች ሳልለይ እነሱ የደረሱበት ያደረሰችኝን እናቴን እክዳለሁ ዛሬ ሁሉ በእጄ ሲሆን ይህንን በእውነት አምላክም ይቅር የማይለው ክህደት ነው ስለዚህ ጥቁር የለበሱ ካህናት መነኩሳት ቆሞሳት ጳጳሳት እንዲሁም ዲያቆናት በሙሉ ዛሬ ለዚህች ቤተክርስቲያን የበኩላችሁን ያላደረጋችሁ ሃላፊነታችሁን ካልተወጣችሁ አሳድጋ ለወግ ለማዕረግ ያደረሰችን እናትን ለመግደል እንዲሁም ለመስቀል እንደመዋዋል ነው የሚቆጠረው ያንን ደግሞ ሃጢያት ማንም ሊፈታችሁ ስለማይችል እራሳችሁን ምን እንደምትሉት አላውቅም።
በመጨረሻ ለማኅበረ ምዕመናን እና ምዕመናት በሙሉ እባካችህ አባቶቻችን የምንላቸው በሙሉ እንደ አባት መሆን ካልቻሉ ተዋቸው ለሆዳቸው ያደሩ ከርሳሞች ከሆኑ ተዋቸው ለስጋቸው ያደሩ ልፍስፍሶች ከሆኑ ተዋቸው አለበለዚያ ግን ዓይናችን እያየ ቤተክርስቲያናችን ጠፍታ ነገ ክር እንኳ ለማሰር የሰዎችን ፈቃድ የምንጠይቅበት ሊሆን እንደሚችል ይታየኛል ዛሬ ካልነቃን እና የራሳችንን የመፍትሄ ሃሳብ ካላደረግን ነገ ኦርቶዶክስ ነኝ ለማለት የሚያስችለን ወኔውም ብቃቱም ሊኖረን አይችልም እላለሁ እግዚአብሔር ብርታቱን እና ማስተዋሉን ይስጠን
ቸር ይግጠመን አሜን

No comments:

Post a Comment