ርዕሰ አንቀጽ፡- የሀገሪቱን ሰላም ለማስከበር የቤተ ክርስቲያኒቱን ሰላም ማስከበር
(ደጀ ሰላም፤ ኤፕሪል 2/2011)፦ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ለኢትዮጵያ ያበረከትችውን አስተዋጽዖ መዘርዘር ለቀባሪው እንደማርዳት ነው። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በተለይ ሕግና ሥርዓትን አውጥታ፤ ካህናትና ምዕመናን በአንድነትና በመከባበር የቤተ ክርስቲያኒቱን ሥርዓተ እምነት፤ ዶግማና ቀኖና እንዲጠብቁና እንዲያስጠብቁ፤ በልማትና በማኅበራዊ ጉዳዮች በሕብረተሰቡ ዘንድ መረዳዳትና መቻቻል እንዲኖር አድርጋለች፣ በማድረግም ላይ ትገኛለች። ይህም ለሀገሪቱ ሰላምና መረጋጋት ከፍተኛ አስተዋጽዖ አድርጓል።
ቅድስት ቤተ ክርስቲያን እነዚህን ሁሉ ተግባራት ለዘመናት ስታከናውን የቆየችው በቤተ ክርስቲያኒቱ ውስጥ ያለውን መንፈሳዊና አስተዳደራዊ የሥልጣን ተዋረድ በመጠቀምና በማክበር ነው። ይህም አሠራር ለዘመናት ሳይፋለስ ቆይቷል። ይህንን ከሀገሪቱ ከ50% በላይ የሆነና በሚሊዮን የሚቆጠር ምዕመን ይዛ በሕግና በሥርዓት ባታስተዳድር ኖሮ የቤተ ክርስቲያንቱ ሰላም ብቻ ሳይሆን የሀገሪቱም ሰላም ሊደፈርስ እንደሚችል እሙን ነው። የቤተ ክርስቲያንን መንፈሳዊና አስተዳደራዊ የሥልጣን ተዋረድ ለማስጠበቅ እና በቤተ ክርስቲያንቱ አስተዳደራዊ ጉዳዮች ላይ ለሚወሰኑ ውሳኔዎች ተፈፃሚነት የሕግ ከለላ በመስጠት በየጊዜው የነበሩት ነገሥታትና የመንግሥት አካላት በቂም ባይሆን የበኩላቸውን አስተዋጽዖ አበርክተዋል።
ይሁን እንጂ በአሁኑ ወቅት የቤተ ክርስቲያኒቱን ዶግማና ቀኖና ለማፍረስና ሀብቷንና ንብረቷን ለመዝረፍ እንዲያመች መንፈሳዊና አስተዳደራዊ የሥልጣን ተዋረዷን መጣስ እየተለመደ መጥቷል። እነዚህን ሕገ ወጥ ተግባራት ለመከላከል የቤተ ክርስቲያኒቱ የበላይ ጠባቂና ወሳኝ አካል የሆነው ቅዱስ ሲኖዶስ እና በየደረጃው ያሉ እውነተኛ የቤተ ክርስቲያን አመራር አካላት የሚወስኗቸው ውሳኔዎችና አመራሮች ተግባራዊ እንዳይሆኑ ብዙ እንቅፋቶች እያጋጠሟቸው ነው። ለዚህም እንደማሳያነት በቦሌ የቆመው የፓትርያርኩ ሐውልተ ስምዕ መፍረስና በሐዋሳ ሀገረ ስብከት በተፈጠሩ ችግሮች ላይ የተወሰኑት ውሳኔዎችን ለማስፈፀም ያለውን ፈተና መግለፅ ይቻላል። ከዚህ አንጻር ስንመለከተው፦
1. የቤተ ክርስቲያንቱን ዶግማ፤ ቀኖና እና ትውፊት ለማስከበር እና የቤተ ክርስቲያንቱን ሀብት እና ንብረት ከውድመትና ከዝርፊያ ለመታደግ ጥረት በሚያደርጉ አባቶች ላይ እየተደረገ ያለው ዛቻ፤ ጫና እና ማስፈራሪያ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ የሚገኝ ጉዳይ እንጂ የሚቀንስ ሆኖ አለመገኘቱ፤ ይህም ጉዳይ“መንግሥት በሀገሪቱ የለም፤ ሕግና ሥርዓት አስከባሪ የለም፣ መንግሥት ለቤተ ክርስቲያኒቱ ደንታ የለውም”’ እስከኪባል ድረስ አድርሶታል።
2. ባለፈው ዓመት በተደረገው በብፁዓን አበው ላይ የደረሰውን ድብደባ፤ አፈናና ዛቻ የፈፀሙት ግለሰቦች ለፍርድ አለመቅረብና ሕጋዊ ቅጣት አለማግኘት ምዕመኑ በመንግሥት ላይ ያለውን ተስፋ እስከመጨረሻው እንዲሟጠጥ አድርጎታል።
3. በዚህ ዓመትም በጥቅምት ወር በተደረገው ጉባኤ ላይም ቢሆን ብዙ ብፁዓን አባቶች የማስፈራሪያ ዛቻዎች በስልክ እና በአካል ተሰንዝረዋል። አሁንም የቤተ ክርስቲያኒቱ ዶግማና ቀኖና እንዲጠበቅ፤ ሀብቷ እና ንብረቷ እንዳይዘረፍ፤ እና የቤተ ክርስቲያኒቱ መንፈሳዊና አስተዳደራዊ የሥልጣን ተዋረድ እንዲጠበቅ በሚታገሉ አባቶች ላይ ከእነዚህ ቡድኖች የሚሰነዘረው ማስፈራሪያ ቢጨመር እንጂ አልቀነሰም።
4. በጥቅምቱ የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ በቅዱስ ሲኖዶሱ የተወሰኑት ውሳኔዎችንም ለማስፈፀም አለመቻሉ በቤተ ክርስቲያኒቱ ውስጥ ሆነው በዝርፊያና የቤተ ክርስቲያንን ሰላም በማደፍረስ ምዕመኑን ተስፋ በማስቆረጥ ሥራ ላይ የተሰማሩት ቡድኖች በቤተ ክርስቲያኒቱ ብሎም በሀገሪቱ ሰላም እና ልማት ላይ ከፍተኛ አደጋ እንደሚጥሉ ለማወቅ ማስረጃና ጥልቅ ምርምር አያሻውም።
5. አሁንም ቢሆን መንግሥት በራሱ የሚያደርገውን አስተዳደራዊ በደል ምዕመኑ የሚታገሰውን ያህል በእምነቱ ሲመጣበት ሊታገስ እንደማይችልና የቤተ ክርስቲያኑ ዶግማና ቀኖና እንዲጠበቅ፤ ሀብቷ እና ንብረቷ እንዳይዘረፍ፤ እንዲሁም የቤተ ክርስቲያኒቱ መንፈሳዊና አስተዳደራዊ የሥልጣን ተዋረድ እንዲጠበቅ አስፈላጊውን መስዋዕትነት መክፈል እንደሚችል አውቆ መንግሥትሊያስብበት ይገባል።
5. አሁንም ቢሆን መንግሥት በራሱ የሚያደርገውን አስተዳደራዊ በደል ምዕመኑ የሚታገሰውን ያህል በእምነቱ ሲመጣበት ሊታገስ እንደማይችልና የቤተ ክርስቲያኑ ዶግማና ቀኖና እንዲጠበቅ፤ ሀብቷ እና ንብረቷ እንዳይዘረፍ፤ እንዲሁም የቤተ ክርስቲያኒቱ መንፈሳዊና አስተዳደራዊ የሥልጣን ተዋረድ እንዲጠበቅ አስፈላጊውን መስዋዕትነት መክፈል እንደሚችል አውቆ መንግሥትሊያስብበት ይገባል።
6. በፖለቲካው ረገድ በቅርቡ በሰሜን አፍሪካ በኢ-ፍትሐዊ አስተዳደሮች ላይ የተደረገው ዓይነት ሕዝባዊ አመጽ ለመሪዎች መባረር ምክንያት እንደሆነው ሁሉ ይህ በቤተ ክርስቲያን ላይ የሚደረገው በደል ማቆም ካልተቻለ በኢትዮጵያ ምዕመኑ ወደዚህ ዓይነት ቁጣ ሊራመድ እንደሚችል መንግሥት ሊረዳው ይገባል።
7. ስለሆነም የቤተ ክርስቲያኒቱ መንፈሳዊና አስተዳደራዊ የሥልጣን ተዋረድ እንዲጠበቅ እና በቤተ ክርስቲያንቱ የበላይ ጠባቂና ወሳኝ አካል በሆነው በቅዱስ ሲኖዶስ እና በየደረጃው ባሉ እውነተኛ የቤተ ክርስቲያን አመራር አካላት የሚወሰኑት ውሳኔዎችና አመራሮች በእምነቱ ቀኖናዊ አሠራር መሠረት ተፈጻሚ እንዲሆኑና ከላይ ለተጠቀሱት ለእውነተኛ የቤተ ክርስቲያንቱ አካላት መንግሥት አስፈላጊውን የሕግ ከለላሊሰጥ ይገባል እንላለን።
8. መንግሥት የሀገሪቱን ሰላም ለማስከበር የቤተ ክርስቲያኗን ሰላም ማስከበር ይጠበቅበታል።
ቸር ወሬ ያሰማን፣ አሜን
No comments:
Post a Comment