ገዳማት እና አድባራት የልማት ፈንድ ያቋቁማሉ
/ምንጭ፡- ኢትዮ – ምኅዳር፤ ቅጽ 02 ቁጥር 51፤ ረቡዕ፣ ታኅሣሥ 23 ቀን 2006 ዓ.ም./
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሰሞኑን ለሀ/ስብከቱ ባለድርሻ አካላት ለውይይት ያቀረበው የአደረጃጀትና አሠራር ጥናት ሰነድ ካህናቱንና ምእመናኑን እያነጋገረ ነው፡፡ የጥናት ሰነዱን እንደማይቀበሉት የሚገልጹ ወገኖች፡- ‹‹ጥናቱ የቤተ ክርስቲያኒቱ ሊቃውንት ያልተሳተፉበትና በውይይት ያልዳበረ በመኾኑ በገለልተኛና ልምድ ባላቸው ምሁራን ይሰናዳ፤ ከነባሩ ሕገ ቤተ ክርስቲያንና ቃለ ዐዋዲ ጋራ የሚጋጭና የሚጣረስ ነው፤›› ይላሉ፡፡
ጥናቱ ‹‹ነባሩን ሠራተኛ በማፈናቀል በስመ ዲግሪና ዲፕሎማ ዕውቀት የሌለውን በመዋቅሩ ውስጥ በመሰግሰግ ቤተ ክርስቲያኒቱን ለመቆጣጠር ያለመ ነው፤›› የሚሉት እኒሁ ወገኖች፣ ‹‹የአጥኚው አካል ማንነት በግልጽ አይታወቅም፤ በቤተ ክርስቲያኒቱ የመጨረሻ ሥልጣን ያለውን የፓትርያርኩን ሥልጣን ይጋፋል፤›› የሚሉ ተቃውሞዎችን በመዘርዘር አቤቱታቸውን ለፓትርያርኩና ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽ/ቤት አቅርበዋል፡፡