Saturday, 14 December 2013

ሰበር ዜና – ቅ/ሲኖዶስ የአፈጻጸም አቅጣጫ የሰጠበትን የአ/አ ሀ/ስብከት የመዋቅር፣ አደረጃጀትና ዝርዝር አሠራር ጥናት በመድረክ ለመሞገት አቅም ያነሳቸውና ውይይቱን ለማደናቀፍ ሲያሤሩ የቆዩ ጥቅመኛ የአጥቢያ አለቆችና የአስተዳደር ሠራተኞች በቦሌ ላሊበላ ሆቴል ኅቡእ ስብሰባ ሊያካሂዱ ነው፤ ሤረኞቹ ‹‹ይደግፉናል›› በሚል የሚነግዱባቸው አንዳንድ ሊቃነ ጳጳሳት ራሳቸውን ከሤራው እንዲያገሉና ለቅዱስ ሲኖዶሱ ውሳኔ ተፈጻሚነት እንዲቆሙ ይጠየቃሉ!!


ቅዱስ ሲኖዶስ በጥቅምት ወር ባካሄደው የመጀመሪያ የምልአተ ጉባኤ መደበኛ ስብሰባ÷ የአዲስ አበባ ሀ/ስብከት የመዋቅር፣ አደረጃጀትና የአሠራር መመሪያ ጥናት ረቂቅ በካህናት፣ በምእመናንና በሰንበት ት/ቤት ወጣቶች ተሳትፎ እንዲዳብርና በቋሚ ሲኖዶሱ አማካይነት በሥራ ላይ እንዲውልበመወሰን በሰጠው የአፈጻጸም አቅጣጫ መሠረት እየተካሄደ የሚገኘውን ጥናታዊ ውይይት ለማወክ አፍራሽ ተግባራትን ሲያራምዱ የቆዩ ጥቅመኛ የአድባራት አለቆች፣ ጸሐፊዎችና የአስተዳደር ሠራተኞችበቦሌ ላሊበላ ሆቴል ኅቡእ ስብሰባ መጥራታቸው ተሰማ፡፡

በምልአተ ጉባኤው የውሳኔ መግለጫ መሠረት÷ በብዙኃኑ ተሳትፎና ውይይት ለመዳበርና የበለጠ ለመስተካከል ክፍት የኾነውን የመዋቅር፣ አደረጃጀትና ዝርዝር የአሠራር መመሪያ በመድረክ ከመሞገት ይልቅ በአሉባልታዎችና አሻጥሮች ለማሰናከል የተለያዩ ሙከራዎችን ሲያደርጉ የቆዩት የለውጡ ተቃዋሚዎች÷ በዛሬው ዕለት ከቀትር በኋላ በኅቡእ የጠሩትን ስብሰባ ለማካሄድ ያቀዱት የገዳማቱና አድባራቱ ልኡካን በረዳት ሊቀ ጳጳሱ፣ የሀ/ስብከቱ ጽ/ቤትና የክፍላተ ከተማ ቤተ ክህነት ጽ/ቤቶች አስተባባሪነት ተከታታይ ዙር ውይይቶችን እያካሄዱ ባሉበት ወቅት ነው፡፡

የሀ/ስብከቱ የመዋቅር፣ አደረጃጀትና የሥነ ምግባር ችግሮች ለቤተ ክርስቲያናችን መሠረታዊ ተልእኮ መጠናከርና መስፋፋት ትኩረት በሰጠ አኳኋን እንዲስተካከል፤ መንፈሳዊ፣ ሰብአዊ፣ ፋይናንሳዊና ቁሳዊ ሀብቶቿ በአግባቡ ጥቅም ላይ እንዲውሉ ታስቦ በቅ/ሲኖዶሱ ዕውቅናና ይኹንታ የተዘረጋውን አሳታፊ መድረክ በመርገጥ በኅቡእ የተጠራውን ስብሰባ በዋናነት ያስተባበሩ የአጥቢያ አብያተ ክርስቲያን አስተዳዳሪዎችና ጸሐፊዎች ተለይተው መታወቃቸው ተገልጦአል፡፡

ኹኔታው በቅርበት የሚከታተሉ ሐራዊ ምንጮቹ እንደጠቆሙት፣ በዛሬው ዕለት በቦሌ ላሊበላ ሆቴል በኅቡእ ይካሄዳል የተባለውን ስብሰባ በዋናነት በማስተባበር ረገድ በዝርዝር የተጠቀሱት፡- የየካ ደብረ ሣህል ቅ/ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ፣ የገነተ ጽጌ ቅ/ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪና ጸሐፊ፣ የሲ.ኤም.ሲ ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ እና የሳሪስ ጻድቁ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ ናቸው፡፡

ከእኒህና ከመሰሏቸው ግለሰቦች አብዛኞች፡- ከገቢያቸው በላይ በልዩ ልዩ የዝርፊያ ስልቶች ባጋበሱት የምእመናን ገንዘብ ከአንድ በላይ መኖርያ ቤቶች፣ የጭነት፣ የሕዝብ ማመላለሻና የቤት መኪኖች፣ የኪራይና መነገጃ ቤቶች፣ የደለበ ባንክ ተቀማጭ፣ በቤተ ክርስቲያን የሥራ ሰዓት የግል ሥራ እየሠሩ ገቢ የሚያገኙባቸው ቢዝነሶች ያሏቸው መኾኑ ታውቋል፡፡ የተቋማዊ ለውጥ ሒደቱን የሚቃወሙትም እኒህን ሕገ ወጥ ጥቅሞች የሚያስጠብቁበት ክፍተት መተግበሩ አይቀሬ በኾነው የመዋቅር፣ አደረጃጀትና ዝርዝር አሠራር መምሪያ እንዳይስተካከል ለመከላከል መኾኑ ተነግሯል፡፡

No comments:

Post a Comment