Tuesday, 24 December 2013

ቤተ ክርስቲያን ከ290 ሚልዮን ብር በላይ በኾነ ውጭ ሁለገብ የሥልጠና ማዕከል ልትገነባ ነው




የአደረጃጀትና አሠራር ጥናት ሰነዱ አካል የኾነው የሥልጠናና የሰው ሀብት ልማት ፖሊሲው ከአፈጻጸም ዝርዝር መመሪያው ጋራ ተዘጋጅቷል የአደረጃጀትና አሠራር ለውጥ ጥናታዊ ውይይቱ ተጠናቅቋል የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን÷ ከአድልዎና ሙስና የጸዳ፣ ሥርዐተ እምነትዋን የሚጠብቅ፣ መንፈሳዊ ዕሴቶችዋን የሚያንጸባርቅ፣ ሞያዊ ብቃትን ማዕከል ያደረገ፣ ዘመኑን የዋጀና የተቀላጠፈ አሠራር እንዲኖራት ያስችላል የተባለ ሁለገብ የማሠልጠኛ ማዕከል ለመገንባት የፕሮጀክት ጥናቱን አጠናቅቃ ማዘጋጀቷ ተገለጸ፡፡
በአዲስ አበባ ዙሪያ ካሉት የኦሮሚያ ወረዳዎች በአንዱ ለመገንባት ጥናቱ ተጠናቅቆ እንደቀረበ ለተገለጸውና ብር 292,260,281 ያህል በጀት የተያዘለት ለዚህ ሁለገብ የሥልጠና ማዕከል ግንባታ ፕሮጀክት ተፈጻሚነት፣ በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የፓትርያርኩ ረዳት ሊቀ ጳጳስና የጅማ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ እስጢፋኖስ ከኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት ጋራ መነጋገራቸውንም የሀ/ስብከቱ ምንጮች ለኢትዮ ምኅዳርዝግጅት ክፍል አስታውቀዋል፡፡

በቤተ ክርስቲያኒቱ ባለሞያዎች ተጠንቶ ሰሞኑን ለውይይት የቀረበው የአዲስ አበባ ሀ/ስብከት የመዋቅር፣ የአደረጃጀትና የአሠራር ጥናት ሰነድ ረቂቅ አካል የኾነው ሁለገብ የማሠልጠኛ ማእከል ፕሮጀክቱ÷ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቀድሞ የነበራትን መንፈሳዊ፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ አስተዋፅኦ አጠናክራ ለመቀጠል ትችል ዘንድ ዘመኑን የዋጀና የተቀላጠፈ አሠራር እንዲኖራት የማድረግ አጠቃላይ ዓላማ ይዞ የተነሣ ነው፡፡

ለጥናቱ በተደረገው የኹኔታዎች ዳሰሳ÷ ስብከተ ወንጌልንና ትምህርተ ወንጌልን ከማጠናከርና ከማስፋፋት ይልቅ በደጋፊ ተግባራት ላይ ማተኮር፣ የአገልጋዮች የሥራ ትጋት መቀነስና ተነሣሽነት ማጣት፣ ምእመናን ሓላፊነት ለመውሰድ ያለመቻል፣ የቤተ ክርስቲያን ችግር በዓለማዊ ፍ/ቤት መታየቱ ለቤተ ክርስቲያኒቱ ክብረ ነክና የአገልግሎት ጊዜን አባክኗል ተብሏል፡፡

በዳሰሳው ግኝቶች÷ ጥፋተኞች ያለአንዳች ተጠያቂነት በሹመትና በዝውውር መታለፍ፣ በሰበካ ጉባኤያትና በአስተዳደር ሠራተኞች፣ በካህናትና ምእመናን መካከል አለመግባባቶች መፈጠር የመሳሰሉ የመዋቅር፣ አደረጃጀትና አሠራር እንዲሁም ሥነ ምግባራዊ ችግሮች፤ የቅጥር፣ ዝውውር፣ ሹመት፣ ዕድገትና ጥቅማጥቅም ጋራ የተገናኙ የሰው ኃይል አስተዳደር ችግሮች መኖራቸው ታውቋል፡፡

ከፋይናንስና ቁጥጥር ድክመቶች ጋራ በተያያዙ ብልሹ አሠራሮች ደግሞ የቤተ ክርስቲያን ሀብትና ንብረት አላግባብ መባከናቸው በዋናነት የተለዩ ሲኾኑ ችግሮቹን÷ የጥናቱ አካል በኾነውና የቤተ ክርስቲያኒቱን ዕሴቶች ያንጸባርቃል በተባለው የአገልጋዮች ማስተዳደርያ ፖሊሲና ዝርዝር የአፈጻጸም መመሪያ ከመፍታት ባሻገር በሥልጠናና የሰው ሀብት ልማት ፖሊሲውና ዝርዝር የአፈጻጸም መመሪያው መሠረት በአገልጋዮች አመለካከት፣ ክህሎትና ዕውቀት ላይ አተኩሮ በሚሠራበት የሁለገብ ማዕከሉ የአቅም ማጎልበቻ ሥልጠናዎችም ለመቅረፍ መታሰቡ ተመልክቷል፡፡

በብዙ ሚልዮን የሚቆጠሩ ምእመናንና በብዙ መቶ ሺሕ የሚታሰቡ ካህናት ያሏት ቤተ ክርስቲያኒቱ፣ ዘመኑን የዋጀና ሁለ አቀፍ የኾነ የሥልጠና ማዕከል በመገንባት በመንፈሳዊና ማኅበራዊ ተቋሞቿ መልካም አስተዳደርን፣ ምቹና ቀልጣፋ አሠራርን ማስፈኗ ለአገር ዕድገትና ልማት እጅግ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንደሚያበረክት በፕሮጀክቱ ዝርዝር ዓላማዎች ላይ ተገልጧል፡፡

ፕሮጀክቱ የሥልጠና ማዕከል ብቻ ሳይኾን ወላጆቻቸውን በኤች.አይ.ቪ እና በተለያየ ምክንያት ያጡ ጎዳና ተዳዳሪ ሕፃናትን በማሰባሰብ ተከባክቦ በሥነ ምግባር የማሳደግ፣ ከቀለም ትምህርታቸው ጎን ሞያዊ ክሂሎታቸውን በማዳበር ራሳቸውን ችለው ሥራ ፈጣሪ እንዲኾኑ በማስቻል ብቁ ዜጋ የማድረግ፤ ጧሪ ቀባሪ የሌላቸውን አረጋውያንና አካል ጉዳተኞችን በማሰባሰብ ኑሯቸውን የማሻሻል ዝርዝር ዓላማዎች እንዳሉትም ተዘግቧል፡፡

በተያያዘ ዜና ከኅዳር 17 – ታኅሣሥ 14 ቀን 2006 ዓ.ም ድረስ በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የመዋቅር፣ አደረጃጀትና አሠራር ጥናት ረቂቅ ላይ በሰባት ተከታታይ ዙሮች ሲካሄድ የቆየው ውይይት ተጠናቅቋል፡፡

የጥቅምት ቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ በሰጠው የአፈጻጸም አቅጣጫ መሠረት መካሄዱ የተገለጸውና በቁጥር ከ2500 በላይ ተሰብሳቢዎች ተገኝተውበታል የተባለው ይኸው ውይይት÷ የጠቅላይ ቤተ ክህነት የድርጅትና የመምሪያ ሓላፊዎች፣ የሀ/ስብከቱና የክፍላተ ከተማ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት ሓላፊዎች፣ የ169 ገዳማትና አድባራት አለቆች፣ ጸሐፊዎች፣ የአስተዳደር ሠራተኞች፣ የአብነት መምህራን፣ የካህናት፣ የሰንበት ት/ቤት አመራሮችና የምእመናን ተወካዮች እንደተሳተፉበት ተነግሯል፡፡

የመዋቅር፣ አደረጃጀትና አሠራር ለውጥ ጥናት ረቂቁ÷ በሕገ ቤተ ክርስቲያንና በቃለ ዐዋዲው ለአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ተለይቶ በተሰጠውልዩ መተዳደርያ ደንብ የማዘጋጀት ድንጋጌና የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ በግንቦት 2005 ዓ.ም ባስተላለፈው ውሳኔ መሠረት በሀ/ስብከቱ የፓትርያርኩ ረዳት ሊቀ ጳጳስ ትእዛዝ በተቋቋመ የቤተ ክርስቲያኒቱ ባለሞያዎች ቡድን የተሠራ መኾኑ ተገልጦአል፡፡

በድምሩ ከአንድ ሺሕ ገጾች በላይ ያሉትን 13 የአስተዳደር ፖሊሲዎችና የአሠራር ዝርዝር መመሪያዎች ሠርቶ ያቀረበው 15 አባላት ያሉት የባለሞያ ቡድኑ÷ በመንፈሳዊው ከዲቁና እስከ ማዕርገ ክህነት ያላቸው፣ በሰበካ ጉባኤያት ለረጅም ጊዜ ያገለገሉና በማገልገል ላይ ያሉ፣ ከሀገረ ስብከቱም የተውጣጡ፣ ዘመናዊውን ትምህርት በከፍተኛ ደረጃ የቀሰሙና የተለያየ ሞያዊ ልምድ ያካበቱ መኾናቸው በሁሉም የውይይት ዙሮች ሲገለጽ ሰንብቷል፡፡

ምንም ዐይነት ክፍያ ሳይፈጸምለት ለስድስት ወራት ባከናወነው ጥናትም ቤተ ክርስቲያኒቱን ከብር ሁለት ሚልዮን በላይ ወጭ መታደጉ የለውጡ ከፍተኛ ተጠቃሚዎችና ግንባር ቀደም አስፈጻሚዎች ይኾናሉ ከተባሉት ከካህናቱና ምእመናኑ ‹‹የቤተ ክርስቲያኒቱ የልደት ቀን ነው፤ የአስተዳደር ትንሣኤዋን የምናይበት ነው፤›› አሰኝቷል፡፡

በአንዳንድ አድባራት በእልቅናና በአስተዳደር ሠራተኝነት የሚገኙ ጥቂት ሓላፊዎች፣ ‹‹ጥናቱ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያንን አላካተተም፤ የአጥኚዎቹ ማንነት አይታወቅም፤›› በሚል እያሰሙት ከሚገኙት ተቃውሞ በስተቀር የተቋማዊ ለውጥ ጥናቱ በመድረክ፣ በቡድን ውይይትና በቅጽ በተሰበሰበው የተሳታፊዎች መመዘኛ አስተያየት መሠረት ከ92 – 99 በመቶ የካህናት፣ ሊቃውንት፣ የሰንበት ት/ቤት ተወካዮችን ከፍተኛ ድጋፍ ማግኘቱ ተነግሯል፡፡ በቀጣይም በቅ/ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ውሳኔ በተሰጠው የአፈጻጸም አቅጣጫ መሠረት ከውይይቱ በተገኘው ግብዓት ታርሞና ተስተካክሎ በቋሚ ሲኖዶስ ከጸደቀ በኋላ የማስተግበርያ ዕቅድ ወጥቶለት ደረጃ በደረጃ ተፈጻሚ እንደሚኾን ተገልጦአል፡፡

No comments:

Post a Comment