Friday 31 August 2012

የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን የተዘረጋባትን የተሐድሶ ወጥመድ ይፋ አድርጓል የተባለ “ሰነድ” ይፋ ሆነ

(ደጀ ሰላም፤ ፌብሩዋሪ 5/2011፤ ጥር 29/2003 ዓ.ም)፦ 

ከ1920ዎቹ ሁለተኛ አጋማሽ ጀምሮ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን አስተምህሮ እና ትውፊት በመለወጥ ፕሮቴስታንታዊ ለማድረግ በተለያዩ የቤተ ክርስቲያኒቱ አካላት እና መዋቅሮች ላይ ትኩረት ሰጥተው የሚሠሩ የተሐድሶ ኑፋቄ ማኅበራት እና ድርጅቶች በተለዋዋጭ ስልቶች ሲማስኑ መቆየታቸው ይታወቃል፡፡ ይህ ጥረታቸው ያሰቡትን ያህል ያልተራመደላቸው የተሐድሶ መናፍቃኑ ቤተ ክርስቲያኒቱን ‹‹ከውስጥ እያጠቁ ወደ ውጭ በመገስገስ እና ከውጭ ከበባውን አጠናክሮ ወደ ውስጥ በመግፋት›› ሙሉ በሙሉ ለመቆጣጠር አልያም ውጥንቅጧን አውጥቶ ለሁለት ለመክፈል ስልት ቀይሰው፣ በተለይም የቤተ ክርስቲያኒቱን የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ማእከል አድርገው በመንቀሳቀስ ላይ ስለመሆናቸው የሚገልጽ ሰነድ ሰሞኑን ለደጀ ሰላም ደርሷል፡፡

በልማት ስም የሚንቀሳቀሱ ዓለም አቀፋዊ እና ሀገር አቀፍ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች እና የፕሮቴስታንት የእምነት ተቋማት በሚያደርጉላቸው ከፍተኛ የገንዘብ፣ የሥልጠና እና የስልት ቅየሳ እየታገዙ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን ከውስጥ በማተራመስ እና ከውጭ በማስጨነቅ አዳክሞ ፕሮቴስታንታዊ አድርጎ ለመውረስ (Reformed Church) አልያም የቤተ ክርስቲያኒቱን አስተዳደራዊ እና ተያያዥ ችግሮች ሃይማኖታዊ ይዘት በመስጠት ምእመኑን ማነሣሣት፣ ጉዳዩ የተሟላ ሃይማኖታዊ እና ሕዝባዊ መልክ ሲይዝም እንደ ሕንድ ቤተ ክርስቲያን ለሁለት ለመክፈል የተሐድሶ ኑፋቄ ማኅበራት እና ድርጅቶች በእያንዳንዷ ቀን በቤተ ክርስቲያናችን ላይ የሚሸርቡት ሤራ እና የሚያደርሱት ጥፋት ‹‹እጅግ አስፈሪ እና አሳሳቢ›› እየሆነ መምጣቱ በሰነዱ ላይ ተገልጧል፡፡ ሁኔታው እስከ አሁኑ እንደሚታየው እንደ ሌለ ተቆጥሮ ዝም ከተባለና ተገቢው ስልት ተነድፎ ተመጣጣኝ ቅንጅታዊ ሥራ ካልተሠራ የቤተ ክርስቲያን ህልውና ከባድ ጥያቄ ምልክት ላይ ሊወድቅ እንደሚችል ተመልክቷል፡፡

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የተሐድሶ መናፍቃኑ ታላቁ ሤራ ከቀድሞው በተለየ አኳኋን በመቐለ አባ ሰላማ ከሣቴ ብርሃን ቅዱስ ፍሬምናጦስ እና በአዲስ አበባው የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጆች ጠንካራ አደረጃጀት ፈጥሮ ጥቂት በማይባሉ መምህራን፣ ደቀ መዛሙርት እና ሠራተኞች በመታገዝ እየተካሄደ እንዳለ ሰነዱ ያትታል፡፡ ‹‹የቴዎሎጂ ት/ቤቶችን ማእከል አድርጎ የተሐድሶ ማኅበራትን እና የፕሮቴስታንታዊ-ተሐድሶውን ኑፋቄ በበላይነት በመምራት ቤተ ክርስቲያንን በአጭር ጊዜ የመውረስ›› ሕልም ይዞ የተነሣው ይኸው እንቅስቃሴ ዋና ጽ/ቤቱን በአዲስ አበባ ከፍቶ በሰባት ተጨማሪ ክልላዊ ቅርንጫፍ ቢሮዎች እስከ ወረዳ ድረስ የተዋቀረ መሆኑ ተገልጧል፡፡ የማኅበሩ የስልት አፈጻጸም ዐቅድ እንደሚያሳየው የተሐድሶው መነሻ እና ሞተር የቴዎሎጂ ት/ቤቶች መምህራን፣ ደቀ መዛሙርት እና ምሩቃን ሆነው ከእነዚህ በመነሣት ጠቅላይ ቤተ ክህነቱን፣ ከዚያም በየደረጃው ያሉ የቤተ ክርስቲኒቱን አካላት እስከ ሰበካ ጉባኤ ድረስ በመያዝ በመጨረሻ ምእመኑን ሁሉ መለወጥ ነው - ‹‹መምህራኑን መለወጥ የትምህርቱን ይዘት መለወጥ ነው፡፡ ለዚህም ለመምህራኑ በውጭ አገር(በተለይ እንግሊዝ) ነጻ የትምህርት ዕድል ይሰጣል፡፡ የእነርሱን ባህል ተምረው የመጡት መምህራን ኦርቶዶክሳውያኑን መምህራን የማጥላላት ሥራ ይሠራሉ፤ ተማሪዎችም ባልጠረጠሩት መንገድ የቤተ ክርስቲያናቸው ተቃዋሚ እና አፍራሽ ኀይል ሆነው እንዲወጡ ያደርጋሉ፡፡››

የእንቅስቃሴው ዓላማ ተደርገው ከተቀመጡት ውስጥ፣ ‹‹የኢትዮዽያ አብያተ ክርስቲያናት በክርስቶስ ጥላ ስር ተሰብስበው እንዲያመልኩ እና በአንድ እንንዲተባበሩ ማድረግ፣ በቤተ ክርስቲያኒቷ ውስጥ ከስንዴ ጋራ አብረው የገቡትን ትምህርቶች እና መጻሕፍት(አስተምህሮ) ማስወገድ፣ ቤተ ክርስቲያንን ምንም ከማይጠቅም ወግ፣ ልማድ እና በብልሃት ከተፈጠሩ ተረታዊ ትምህርቶች ተለይታ እውነት የሆነው ክርስቶስ እንዲሰበክ ማድረግ፣ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ራሱን የቻለ እንደ ማኅበረ ቅዱሳን ያለ ማኅበር ማቋቋም›› የሚሉት ይገኙባቸዋል፡፡

ሰነዱ እንቅስቃሴውን ለመደገፍ እና ለማበረታታት በግንባር ቀደምነት የሚሠራውን Serving in Mission(SIM) የተባለ የአሜሪካ ሚሲዮናዊ ድርጅት በመጥቀስ እንደሚያስረዳው፣ ከነገረ መለኮት ኮሌጆች ባሻገር የካህናት ማሠልጠኛዎች፣ ገዳማት እና አድባራት፣ የቤተ ክህነት መሥሪያ ቤቶች እና የተለያዩ የመንግሥት የትምህርት ተቋማት የእንቅስቃሴው ስትራተጂክ ቦታዎች ናቸው፤ የለውጡ መሪዎችም ‹‹በእምነት እና በዕውቀት የታመነባቸው የነገረ መለኮት ተማሪዎች፣ ልዩ ልዩ መምህራን፣ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የሚያገለግሉ ቀሳውስት እና ዲያቆናት፣ ሰንበት ትምህርት ቤቶች፣ ምእመናን እና ልዩ ልዩ ድርጅቶች ናቸው፤›› ይላል፡፡

በአሁኑ ወቅት እንቅስቃሴውን በዋናነት የሚመሩት (ኮሌጆቹ እንደተቋም እና ብዙኀን የተቋማቱ መምህራን፣ ደቀ መዛሙርት እና የአስተዳደር ሠራተኞ ቀናዒ ኦርቶዶክሳውያን መሆናቸው እንደተጠበቀ ሆኖ) መቐሌ ከሣቴ ብርሃን ኮሌጅ የነበሩና ያሉ ተማሪዎች እና መምህራን ሲሆኑ በቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅም አስተማማኝ መሠረት እንዳለው ታውቋል። ሤራውን የሚመራው ማኅበር በ2002 ዓ.ም የተለያዩ ስብሰባዎችን እና ውይይቶችን በማድረግ ከፍተኛ እንቅስቃሴዎችን ሲያካሂድ ቆይቷል። በ2002 ዓ.ም መጨረሻ መቀመጫውን እንግሊዝ ያደረገ አንድ የፕሮቴስታንት ድርጅት ለቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ አቅርቦት ስለነበረው የሥልጠና ጥያቄ ሰነዱ እንደሚከተለው ጽፏል፤

በ2002 ዓ.ም መጨረሻ ላይ ለቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ አንድ የሥልጠና ጥያቄ ቀረበ። ሥልጠናውን ለመስጠት ጥያቄውን ያቀረበው በእንግሊዝ የሚገኝ አንድ የፕሮቴስታንት ድርጅት ነው፤ የተጠየቀውም ለኮሌጁ 30,000 ብር ለመስጠት እና በዚህም ገንዘብ ለኮሌጁ ተማሪዎች እና ምሩቃን የአምስት ቀናት ሴሚናር ለመስጠት ነበር። በሴሚናሩ ላይም ከእንግሊዝ ሀገር የሚመጣ አንድ የፕሮቴስታንት ፓስተር ስለ ሥነ ፍጥረት፣ ስለ አዳም አወዳደቅ፣ ስለ ነገረ ድኅነት፣ እግዚአብሔር ለዚህ ዓለም ስላለው. . . ዕቅድ ትምህርት እንዲያስተምር ነበር። በዚህ ጥያቄ ዙርያ የኮሌጁ መምህራን እና አመራሮች ሁለት የተለያዩ ሐሳቦች ያዙ። አንዳንዶች ‹‹ሥልጠናው መካሄድ አለበት›› ሲሉ ሌሎቹ ደግሞ ተቃወሙ። ከተቃወሙት ውስጥ ‹‹ለሴሚናሩ የመጣውን ገንዘብ ተቀብለን ትምህርቱ ግን በኢትዮጵያውያን መምህራን ይሰጥ›› የሚል ሐሳብ ቢያቀርቡም የእንግሊዙ ድርጅት አልተስማማም። ስለዚህም በብፁዕ አቡነ ጢሞቴዎስ ቁርጥ ያለ አባታዊ ውሳኔ ለድርጅቱ ገንዘቡ ተመለሰለትና ሥልጠናው ሳይሰጥ ቀረ። ድርጅቱ እያደረገ ያለው ‹‹ርዳታ›› እና አጠቃላይ ዓላማው የእንግሊዝ የፕሮቴስታንት ድርጅት የሕንድን ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ለሁለት የከፈለበትን ታሪክ በእኛም ቤተ ክርስቲያን ለመድገም ነው። ይህን የጥፋት ሥራ የተጀመረው ለቤተ ክርስቲያኒቱ ‹‹ርዳታ›› በማቅረብ ስም ነው። ይህ ከላይ የተገለጸውን ሥልጠና ለማካሄድ አስቦ የነበረውና ገንዘብ የሰጠው የእንግሊዝ የፕሮቴታንት ድርጅት የሕንድ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያንን ከሁለት በመክፈል ሰይጣናዊ ልምድ ያካበተ ድርጅት ነው፡፡ አሁንም በሕንድ ያገኙትን ድል እኛም ላይ ለመድገም እየቋመጡ ይገኛሉ፡፡ እነዚህን እንቅስቃሴዎች በዋነኛነት እያስተባበረ ያለው በመቐሌ ዩኒቨርስቲ በፊዚክስ ዲፓርትመንት በመምህርነት የሚሠራ ሰው መሆኑ ታውቋል። በዚህ ሰው እና በሌሎች ሰዎች እንቅሰቃሴ ምክንያት የመቐሌው የከሣቴ ብርሃን ኮሌጅ በከፍተኛ ደረጃ የፕሮቴስታንት ተጽዕኖ አድሮበታል። የከሣቴ ብርሃን መንፈሳዊ ኮሌጅ በአሜሪካ ከሚገኘው ‹‹ብርጅ ኦፍ ሆፕ››(Bridge of Hope) የሚባል ድርጅት ጋራ ጠንካራ ኢ-ኦርቶዶክሳዊ እንቅስቃሴ እያደረገ ነው።

የእንቅስቃሴው መሠረታዊ መንሥኤ፣ ‹‹ኢትዮጵያ ክርስትና በ‹ነበር› እንደቀረባቸው ሌሎች አገሮች በታሪክ ብቻ ለምልክት የምትወሳ አለመሆኗ፣ በምዕራባውያን ሚስዮናውያን አለመመሥረቷ እና በእነርሱ መንገድ አለመቃኘቷ የማያስደስታቸው በአንጻሩ በአፍሪካውያን እና በሌሎችም ዘንድ ያላት ተፈላጊነት የሚያሰጋቸው የጭፍን ግሎባላይዜሽን ኀይሎች ክፋት ነው፤›› - እንደ ሰነዱ ገለጻ፡፡ በዚህ ክፋት ከተቻለ የቤተ ክርስቲያኒቱን ማንነት በማንኛውም ወጪ እና መንገድ(ፖሊቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ. . .) በመለወጥ ፕሮቴስታንታዊ ለማድረግ ካልተቻለ ደግሞ ውስጧ ሆነው የሚወጓት እና የሚያደሟት በፕሮቴስታንት ሳምባ የሚተነፍሱ እና ለእነርሱ የቆሙ ጥቅመኛ ደጋፊዎችን እና ተከታዮችን በማፍራት ያላትን ነገር በይገባኛል መካፈል እና አንድነቷን በመክፈል ለማዳከም እና ወደ ዋናው ግብ ለመድረስ አበክረው ይንቀሳቀሳሉ፡፡

ይህ እንቅስቃሴ በአጠቃላይ ፕሮቴስታንታዊ ባልሆኑ የእምነት ተቋማት ላይ ያነጣጠረ ሲሆን በተለይም ደግሞ በኦርቶዶክሳውያን አብያተ ክርስቲያናት ላይ(የምሥራቅ ኦርቶዶክስን ጨምሮ) በከፍተኛ ትኩረት፣ የገንዘብ ኀይል፣ ስልት እና ቴክኖሎጂ በመታገዝ እየተሠራበት ይገኛል፡፡ ይህንንም ጉዳይ ሰነዱ እንደሚከተለው አብራርቶታል፤

‹‹የፕሮቴስታንት ሚሲዮናውያን እነዚህን አብያተ ክርስቲያናት ወደ እነርሱ ለመውሰድ ከ19ኛው መቶ ዓመት ጀምሮ ብዙ ስልት ሲቀይሱ እና ሲደክሙ ኖረዋል፡፡ በ20ኛው መቶ ዓመት መጀመሪያ ላይ የግብጽ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያንን ‹እናድሳለን› በሚል ከውስጧ ለመለወጥ እንቅስቃሴ ጀምረው ነበር፡፡ ያን ጊዜ ግብጽ በቅኝ አገዛዝ ሥር ስለ ነበረችና ሀገሪቱ የነበረችበት አጠቃላይ ሁኔታ የተመሰቃቀለ ስለ ነበር ያን አጋጣሚ በመጠቀም ቤተ ክርስቲያኒቷን ለመውረስ ተዘጋጅተው ነበር፡፡

ሆኖም ግን የእነ ሊቀ ዲያቆን ሀቢብ ጊዮርጊስ መነሣት እና በሰንበት ት/ቤቶች፣ በቴዎሎጂ ኮሌጆች እና በመሳሰሉት ሁለ ገብ ዘርፎች ያደረገው ድካም እና ውጤቱ፣ ወደ ኋላ ላይም የእነ ‹ድሀው› ማቴዎስ መነሣትና በእነርሱ እንቅስቃሴ የአስቄጥስ ገዳምና ገዳማዊ ሕይወት ተዳክሞ ከነበረበት ሁኔታ እንደ ገና ማበቡ፣ እንዲሁም የእነ አቡነ ሺኖዳ ትውልድ መነሣትና በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት እየተጠናከረ የመጣው መንፈሳዊ እንቅስቃሴ ቤተ ክርስቲያኒቷን ከነበረችበት የተወሳሰበና የደከመ ደረጃ ወደ አዲስ ጥንካሬና ሁለ ገብ ዕድገት አወጣት፡፡ በዚህም ፕሮቴስታንቶች ቤተ ክርስቲያኗን በተሐድሶ ሽፋን ለመለወጥ የነበራቸው ክፉ ምኞት ሳይሳካላቸው ቀረ፡፡

በሕንድ ቤተ ክርስቲያን ላይም ተመሳሳይ የመውረር ዘመቻ አድርገዋል፡፡ የሕንድ ቅኝ ገዢ የነበረችው እንግሊዝ በመሆኗ የአንግሊካን ፕሮቴስታንቶች በሁለት በኩል ዘመቱባቸው፡፡ ይህም በአንድ በኩል ኦርቶዶክሳውያኑን ወደ እነርሱ ጎራ እንዲቀላቀሉ ከውጭ ሆኖ በመጋበዝ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ከውስጥ ሆኖ ቤተ ክርስቲያኗ ትታደስ በማለት ነበር፡፡ ይህም አካሄድ ተሳክቶላቸው የሕንድ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያንን መክፈል ችለዋል፡፡ ሁለቱም - ኦርቶዶክሳውያኑም ተሐድሶዎቹም በአንዲት ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሆነው ይገባናል ስላሉ መንግሥት በፍርድ ቤት የነበሩትን ሕንፃ አብያተ ክርስቲያናት ከሁለት ማካፈል ግዴታ ሆነበት፡፡ በዚህም በአንግሊካኖቹ ላኪነት ተሐድሶ(ፕሮቴስታንት) የሆኑት ‹ማር ቶማ› የተባለ ቤተ ክርስቲያን አቋቋሙ፡፡ እነዚህ የተገነጠሉትን እምነታቸው ፕሮቴስታንት ስለ ሆነ ‹ኦሬንታል ፕሮቴስታንት - Oriental Protestant› ይሏቸዋል፡፡››

በከፍተኛ ትኩረት፣ የገንዘብ ኀይል፣ ስልት እና ቴክኖሎጂ የሚታገዘውን ይህንኑ ፀረ- ኦርቶዶክሳዊ ተዋሕዶ እንቅስቃሴ በፀረ-ፕሮቴስታንታዊ-ተሐድሶ ተጋድሎ ለማምከን የፊት ለፊት ፍልሚያ የሚጀመርበት ጊዜ ሩቅ እንዳልሆነ ሰነዱ ያበሥራል፡፡ የተሐድሶ ማኅበራትን እና ድርጅቶችን በዋናነት የሚመሩ እና የሚያስተባብሩ ከ76 በላይ ቀንደኛ የመንፈቀ ሉተራውያን አዝማቾች በስም ዝርዝር እንደተለዩ ሰነዱ ጨምሮ አጋልጧል፡፡ ብፁዓን አባቶች ጉዳዩን በበለጠ እንደሚረዱት እና እንደሚያሳስባቸው ያመለከተው ሰነዱ፣ ሰባክያነ ወንጌል በስብከት ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያንም በጽሑፍ ምላሽ በመስጠት ምእመኑን እንዲያነቁ፣ ከመንበረ ፓትርያሪኩ ጀምሮ ያለው የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ መዋቅርም በየደረጃው የተሰገሰጉትን የተሐድሶ ኑፋቄ አስፈጻሚዎች በጥብቅ እየፈተሸ ቀኖናዊ እና አስተዳደራዊ ርምጃ የሚወሰድበትን ሁኔታ እንዲያመቻች ጠይቋል፡፡

ባለፉት ዐሥር ዓመታት በዋናነት አርክ ክርስቲያን ሰርቪስ፣ የታላቁ ተልእኮ አገልግሎት(ግሬት ኮሚሽን ሚኒስትሪ)፣ የ‹‹ሙሉ ወንጌል›› ክንፍ፣ የ‹‹መካነ ኢየሱስ›› ክንፍ እና በሌሎችም መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ከፍተኛ የገንዘብ እና ሁለ ገብ ድጋፍ ሲደረግለት የቆየው የተሐድሶ ኑፋቄ እንቅስቃሴ ከድርጅት ወደ ድርጅቶች፣ ከግለሰብ ወደ ማኅበር፣ ከኅቡእነት ወደ ግልጽነት፣ ከመፍራት ወደ ድፍረት፣ ከአንድ ከተማ ወደ ሀገር አቀፍ፣ ከጓዳ ወደ ሜዳ እንደተሸጋገረ ተገምግሟል፡፡ እንደ ሰነዱ ማብራሪያ በይፋ ታውቀው በስም የተዘረዘሩት፣ በሂደት ላይ ያሉት እና ገና ያልታወቁት የተሐድሶ ማኅበራት በተለያየ ደረጃ በሚያደርጉት እንቅስቃሴ የሚመሩበት አጠቃላይና ከ1990 ዓ.ም ወዲህ ጎልቶ የታወቀው አዲሱ ስልታቸው ‹‹የጥንቷ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ትክክል ነበረች - The ancient Orthodox was the right church›› የሚል ነው፡፡ ይህም ማለት ቤተ ክርስቲያንን ከውጭ ከመቃወም ይልቅ ውስጥ ገብቶ ምእመን መስሎ ከፕሮቴስታንት እምነት እና ባህል ውጭ ያለውን ነገር ሁሉ፣ ‹‹ይህ የጥንቷ ቤተ ክርስቲያን አይደለም›› እያሉ ቤተ ክርስቲያኗ ኦርቶዶክሳዊ ዶግማዋ፣ ቀኖናዋ እና ትውፊቷ በሙሉ ጠፍቶ ፍጹም የጠራች የነጣች ድኃ ፕሮቴስታንት እስክትሆን ድረስ መሥራት ነው፡፡ ከዚህ አኳያ በተለያዩ ኅትመቶቻቸው በሚያወጧቸው ጽሑፎቻቸው ‹‹የትግሉን ሜዳ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ማድረግ አለብን››፣ ‹‹ከቤተ ክርስቲያን መውጣት ቀረ››፣ ‹‹የወጣህ ተመለስ›› እያሉ በመዛት ላይ እንደሚገኙ አስታውቋል፡፡

በጥንቃቄ የተነደፉ፣ ከአንዱ ተግባራቸው ወደ ቀጣዩ ለማሸጋገር የሚያስችላቸው እና ተመጋጋቢነት ባለው መንገድ የተቀየሱ የማንሸራተቻ ስልቶች እንዳሏቸውም ሰነዱ ይተነትናል፡፡ በመጀመሪያ ‹‹ቤተ ክርስያኒቱን ፕሮቴስታንት ለማድረግ ወራጁ ውኃ ላይ (ሕዝቡን መውሰድ) ሳይሆን ምንጩ ላይ መሥራት›› የሚል ነው፡፡ ለዚህም የቤተ ክርስቲያኒቱ የወደፊት ምንጭ የሆኑትን መፍለቂያዎች መለየት እና እነርሱን ለመያዝ የሚቻልባቸውን ሥሥ ገላ መፈለግ ነው፡፡ እነዚህ ምንጮችም ገዳማት እና አብነት ትምህርት ቤቶች፣ የነገረ መለኮት ት/ቤቶች ደቀ መዛሙርት እና መምህራን፣ ሰንበት ትምህርት ቤቶች፣ ዩኒቨርስቲዎች እና በውስጣቸው የሚካሄዱ መንፈሳዊ ጉባኤያት፣ የቤተ ክህነት አስተዳደር እና የተለያዩ መንፈሳዊ ማኅበራት ጽዋ ማኅበራት ናቸው፡፡ እነዚህን ምንጮች ከመለየት ቀጥሎም የእያንዳንዳቸውን ደካማ እና ጠንካራ ጎን በማወቅ ሁሉንም እንዳስፈላጊነቱ ለመጠቀም የሚቻልበትን መንገድ መንደፍ ነው፡፡

ቀጣዩ ምዕራፍ በእነዚህ ምንጮች ውስጥ ኦርቶዶክሳዊ በመምሰል ሰርጎ መግባት እና ለሥራ ምቹ ሁኔታን መፍጠር ነው፡፡ የአፈጻጸም ስልቶቹም እውነተኛ ኦርቶዶክሳዊ እና የቤተ ክርስቲያን ጠበቃ እና ተቆርቋሪ መስሎ መታየት፣ ኦርቶዶክሳዊውን ዶግማ፣ ቀኖና እና ሥርዐት ለጊዜው አለመንቀፍ፣ በሕይወት እና በአገልግሎት ምሳሌ ሆኖ መታየት፣ ተአማኒነትን ለማግኘት ማንኛውንም መንገድ መጠቀም፣ የአገልግሎት መድረክ መያዝ - ሐላፊነት፣ ሥልጣን መያዝ እና በሕዝብ ልብ ውስጥ ለማደር መሥራት ናቸው፡፡ በዚህ መቆናጠጫ ቦታ ከያዙ በኋላ የቤተ ክርስቲያኒቱ ምእመናን በአንድ በኩል ዶግማዋን እና ቀኖናዋን እንዳያውቁ ስብከት ላይ ብቻ መጻፍ እና ማስተማር ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ ‹‹ቤተ ክርስቲያኒቷ ትምህርቷ እና እምነቷ ትክክል ስላልሆነ መታደስ አለባት›› በማለት ይለፍፋሉ፡፡

ይኸውም የቤተ ክርስቲያኒቱን የትምህርት ጉባኤያት ይዘት ‹‹ከትምህርት ወደ ስብከት›› መቀየር፣ ‹‹ክርስቶስን አስኳል አድርገን እንሰብካለን›› ማለት፣ ‹‹ኦርቶዶክስ እውነተኛ ቤተ ክርስቲያን ነበረች፣ ግን በየጊዜው የተጫኑባት ገለባዎች አሉ፤ ቤተ ክርስቲያን ተሐድሶ ያስፈልጋታል፤ የጥንቷን ቤተ ክርስቲያን መመለስ አለብን››. . . ወዘተ እያሉ ደጋግሞ መስበክ እና ሕዝቡ ሲደጋገም እንዲቀበለው ወይም ተቃውሞውን እንዲያለዝብ ማድረግ፤ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ የባሕርይ አምላክነት፣ ስለ ነገረ ቅዱሳን፣ ነገረ ማርያም እና የተጋድሎ ሕወይት ማለትም ጾም፣ ጸሎት፣ ስግድት ወዘተ አስመልክቶ አለ ማስተማር፣ ማስረሳት፤ በዚህ ዙሪያ ማስተማር ለሕይወት የማይጠቅም ርባና የለሽ እንደ ሆነ ማስወራት፤ ስለ ፕሮቴስታንት፣ ለመናፍቃን ምላሽ. . . ወዘተ አለማስተማር ማለት ነው፡፡ ማኅበራትን በሕዋስ (cell) መልክ በማደራጀት፣ ከቤተ ክርስቲያን ውጭ ጉባኤያትን ማስለመድ፣ በመንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች (NGOs) ስም ራስን ማደራጀት እና ቀስቶቹ የተነጣጠሩባቸው አካላት የገንዘብ ችግር ስላለባቸው ምንጩ ያልታወቀ ነጻ ርዳታ መስጠት ተቆጣጣሪ የሌላቸው መስመሮች የሚዘረጉባቸው ቀጣይ ስልቶች ናቸው፡፡

የቤተ ክርስቲያኒቱ መገለጫ የሆኑትን ነገሮች(Icons) በማስረሳት እና በማስጠላት(ጾም፣ ጸሎት፣ ስግደት፣ ሲኖዶስ፣ ጳጳሳት፣ ሊቃውንት፣ ሰንበት ት/ቤቶች የባህል፣ የአስተምህሮ፣ የቀኖና፣ የዶግማ እና የሥርዐትን ድንበር ማጥፋት፤ ምእመኑ በቤተ ክርስቲያን አስተዳደር፣ በአባቶች፣ በገንዘብ አያያዝ፣ በምግባር በመሳሰሉት የተነሣ ቤተ ክርስቲያንን እንዲጠላ በማድረግ፣ ቤተ ክርስቲያንን ያረጀች ያፈጀች ‹‹አሮጊቷ ሣራ›› አድርጎ በመሣል ቤተ ክርስቲያንን ማስጠላት ሌላው የማንሸራተቻ ስልት ነው፡፡ ይህን ተከትሎ የሚመጣው ተሐድሶ እንኳን እንደ ሆነ የማያውቅ ግን ተሐድሶ የሆነ ትውልድ መፍጠር እና ሳያውቀው የሚደግፍ ቲፎዞ ማፍራት ነው፤ ስልቶቹም ተቆርቋሪ በመምሰል፣ ገንዘብ እና ርዳታ በመስጠት፣ የቤተ ክርስቲያኒቱን ተቋማት እና ሕዝቡን መያዝ እና ቲፎዞ እንዲሆን ማድረግ፣ ኦርቶዶክስን የማያውቅ-ፕሮቴስታንት የሆነ-ነገር ግን ተሐድሶ(ፕሮቴስታንት) መሆኑን እንኳ የማያውቅ ምእመን ማፍራት ናቸው፡፡

ከመጀመሪያ ጀምሮ ያሉትን ስልቶች ወደዚህ ውጤት እንዲያደርሱ አድርጎ በሚገባ በመተግበር የቤተ ክርስቲያኒቱን አስተዳደራዊ እና ተያያዥ ችግሮችን ሃይማኖታዊ ይዘት በመስጠት ምእመኑን ማስከተል፣ ጉዳዩ ሙሉ በሙሉ ጠንካራ ሃይማኖታዊ እና ሕዝባዊ ይዘት ሲይዝ እንደ ሕንድ ቤተ ክርስቲያን ለሁለት መክፈል አልያም ቤተ ክርስቲያኗን ባለችበት ከእነ ምእመኗ እና ሕንፃዋ ሙሉ በሙሉ ፕሮቴስታንታዊ አድርጎ መውረስ የስልቱ የመጨረሻ ግቦች ናቸው፡፡

‹‹የተለመዱ የተሐድሶ ስትራቴጂዎች ናቸው›› የሚላቸውን ሲያስረዳም፣ ‹‹አባቶችን መከፋፈል እና የአንዱ ደጋፊ የሌላው ነቃፊ መምሰል፣ የጥላቻ ጽሑፎችን በማሰራጨት ምእመናንን ማደናገር፣ ፖለቲካዊ ክሶችን ማቅረብ፣ ከገዳማት እናቶችን ማስኮብለል፣ የነጋዴዎች እና የብፁዓን አበው ደጋፊ መስሎ መቅረብ፣ ብዙ ውስጠ ወይራ የሆኑ የጽዋ ማኅበራትን መመሥረት፣ ጉባኤያትን ከቤተ ክርስቲያን ውጭ እንዲካሄዱ እገዛ ማድረግ፣ በተቻለ መጠን የውስጥ ለውስጥ(Underground) ሥራዎችን በይበልጥ አጠናክሮ መቀጠል(ለዚህም ከገድላት የተወሰኑ መቀበል)፣ የፎርጅድ ጽላት ዝግጅት፣ የሙዳየ ምጽዋት ብርበራ፣ የቤተ ክርስቲያን ቃጠሎ እና ንዋየ ቅድሳት ዘረፋ፣ የቤተ ክርስቲያንን ሕንጻ በግለሰብ ስም ማዛወር፤ የሕንጻ አሠሪ ኮሚቴ አባል በመሆን፣ በከተሞች ታላላቅ ጉባኤያትን በማዘጋጀት በገዳማት እና አድባራት ስም ገንዘብ ማሰባሰብ እና ለግል ጥቅም ማዋል፣ ፎርጅድ ማኅተሞችን በማዘጋጀት በአባቶች ስም ልመና ማካሄድ፣ በባሕታዊነት ስም መነገድ እና አስነዋሪ ድርጊቶችን በአደባባይ እና ሰዉ በሚያይባቸው ቦታዎች በመፈጸም ሕዝቡ ባሕታዊ እና መነኩሴ እንዲጠላ ማድረግ፣ ገዳማት ውስጥ እየገቡ በተለያዩ ሰንካላ ሰበቦች ሁከት መፍጠር እና ጠብ አስነሥቶ የተወሰኑትን አስወጥቶ ይዞ በመጥፋት እነዚያን የመናፍቃን ሰለባ ማድረግ፣ ገዳማትንም መፍታት›› እንደሆኑ በዝርዝር አመልክቷል፡፡

በአሁኑ ወቅት ‹‹እናድሳለን›› በሚል ሽፋን ከውጭ ወደ ውስጥ ሠርጎ በመግባት ምእመኑን እስከ ሕንፃ ቤተ ክርስቲያኑ የመረከብን ስልት አንግበው የሚሠሩ 14 የተሐድሶ ማኅበራት እና ድርጅቶች ማንነት እና የትኩረት አካባቢዎች ከዝርዝር ስልቶቻቸው ጋራ በሰነዱ ተብራርቷል፡፡

ለአብነት ያህል፣ የተሐድሶ ድርጅቶች አባት በሆነው ግሬት ኮሚሽን ሚኒስትሪ የተቋቋመው ‹‹የምሥራች አገልግሎት በኢትዮጵያ›› የተባለው ማኅበር በትግራይ፣ ጎጃም፣ ጎንደር እና ወሎ ላይ ትኩረት አድርጎ የሚሠራ ድርጅት ነው - ‹‹ደቡብ ኢትዮጵያን ይዘነዋል፤ የቀጣዩ ዐሥር ዓመት የትኩረት አቅጣጫ ሰሜን ኢትዮጵያ ነው፤›› የሚል መፈክር ያስተጋባል፡፡ የዚህ ድርጅት ዋነኛ ተልእኮ የተሳሳቱ አዋልድ መጻሕፍትን ወደ ገዳማት እና ሰንበት ት/ቤቶች እያስገቡ መበከል ነው፡፡ ወንዶችን ሴት በማስመሰል ወደ ገዳም ያስገባል፡፡ በገዳማት እና ሰንበት ት/ቤቶች ተመሳስሎ በመግባት ፕሮቴስታንታዊ ትምህርትን ያስፋፋል፡፡ በትግራይ አብነት ተማሪዎች ላይ ጠንክሮ እየሠራ ነው፡፡ ከዚህ ውጭ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን ሥር መሠረቷን ነቃቅሎ ለመጣል ይረዳኛል ያለውን መንገድ ለማወቅ ጥናት አስጠንቶ የራሱን ሰዎችም ሆነ ሌሎች ተባባሪዎችን በማሳተፍ ተግባራዊ ለማድረግ በመሯሯጥ ላይ የሚገኝ ድርጅት ነው፡፡

እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ አርባ ዙር የሥልጠና ሥራዎችን ሠርቷል፤ የሚያሠለጥነውም የአብነት መምህራንን፣ ተማሪዎችን፣ ካህናትን እና ዲያቆናትን ነው፡፡ ከ500 በላይ ዲያቆናት እና የሰንበት ት/ቤት ተማሪዎች ይህን ተልእኮ ይሠራሉ፡፡ ከእነዚህ ብዙዎቹ የሚሳተፉት ለቤተ ክርስቲያናቸው እየሠሩ እንደ ሆነ እየተነገራቸው እና እየመሰላቸው ነው፡፡ ከ22,000 መነኮሳት መካከል 3,000ውን እንዴት መውሰድ እንደሚችል የመጀመሪያ ዙር ስልት ቀይሷል፡፡ ዛሬ የአማራን ክልል በሰፊው ለማዳረስ እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ ነው፡፡ የሥልጠና ቦታው መቐሌ ከተማ ውስጥ ነው፤ የራሱ የሆነ የሚዲያ መንገድም አለው፡፡

‹‹ከሣቴ ብርሃን›› - በአገሪቱ ውስጥ በሰፊው ተሰራጭቶ የሚገኘው ሌላው ዋነኛ የተሐድሶ ድርጅት ነው፡፡ መሥራቾቹ በ1990ዎቹ መጀመሪያ በኑፋቄያቸው ከኮሌጆች የተባረሩ፣ ከተመረቁ በኋላ አበው አውግዘው የለዩአቸው፣ በራሳቸው ጊዜ ኑፋቄውን ይዘው በቤተ ክርስቲያን ውስጥ አንቆይም ብለው በፍቅረ ንዋይ ተታልለው የወጡ ‹ወገበ ነጭ› ደባትራን መዘምራን የነበሩ ሰዎች ናቸው፡፡ ያቋቋማቸው ያው አባታቸው ፕሮቴስታንት ሲሆን አሁን ግን ራሱን ችሎ መሥራት የሚችልበት ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡ አዲስ አበባ ላይ የአብነት ተማሪዎችን የሚያሠለጥንበት አራት የሥልጠና ጣቢያዎች አሉት፡፡ ጎንደር እና ባሕር ዳር ላይ ብዙ ሰዎች የተሳተፉበትን ሥልጠና አካሂዷል፡፡ ጎንደር ላይ ለካህናት እና ለአብነት ተማሪዎች በይፋ ሥልጠና ሰጥቷል፡፡ አስተማሪዎቹ ከተለያዩ አጥቢያዎች በኑፋቄ ችግር የተባረሩ ናቸው፡፡

(ማስታወሻ፦ በዚሁ ስም የሚጠራ እና በተለይም በአሜሪካ ግዛት ውስጥ አገልግሎት የሚሰጥ ማህበር አለ። ይህ በነመምህር ዘበነ ለማ የተቋቋመው “ከሳቴ ብርሃን” ማህበር እውነተኛ የተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በመሆኑ ከዚህኛው ጋር እንዳይምታታ እናሳስባለን።)

ማኅበሩ በሚያወጣቸው የኅትመት ውጤቶች ብዙዎችን ግራ አጋብቷል፡፡ ኅትመቶቹ ግልጽ አድራሻ የላቸውም፡፡ ሆኖም ግን ‹‹በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን የተዘጋጁ›› ይላሉ፡፡ የተለያዩ ኅትመቶች ያሏቸው ሲሆን ዋና ዋና ኅትመቶቻቸው፣ መጥቅዕ፣ ርግብ፣ ትምህርተ ድኂን፣ ገድል ወይስ ገደል፣ የተቀበረ መክሊት፣ ይነጋል . . . ወዘተ ናቸው፡፡ ኅትመቶቻው ሁሉ የሚያቀነቅኑት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በተሐድሶ ስም ተለውጣ ፕሮቴስታንታዊ እንድትሆን ነው፡፡ ኦርቶዶክሳዊ የሆነውን ዶግማ፣ ቀኖና ማንኛውንም ነገር ሁሉ ይነቅፋሉ፤ ኢትዮጵያዊ የሆነን ነገር በመንገሽገሽ ይተቻሉ፡፡

በ1984 ዓ.ም ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ በቅዱስ ሲኖዶስ ተወግዞ ከቤተ ክርስቲያን ቢባረርም በመንፈሳዊ ኮሌጆች እና በቤተ ክርስቲያን ዙሪያ ደቀ መዛሙርትን እና ምእመናንን በማጥመድ እንዲሁም በሌሎች ተንኮሎች ተመልሶ ለመግባት እና ቤተ ክርስቲያንን የማድማት እና የፕሮቴስታንት ቀለብ የማድረግ ሥራውን ለመቀጠል ጥረት እያደረገ የሚገኘው ‹‹ሃይማኖተ አበው›› ከአዲስ አበባ ማኅደረ ስብሐት ልደታ ለማርያም ቤተ ክርስቲያን የበከላቸው ወጣቶች ጥርቅም የሆነው ‹‹የቅድስት ልደታ ማኅበር›› ሌላው ነው፡፡ ኦርቶዶክሳዊ በመሰለ ውስጡ ግን ፕሮቴስታንታዊ በሆነ አቀራረብ እና ስልት ‹‹የርቀት ትምህርት›› በሚል ስም የሚሰጠው ብዙዎችን እያሳሳተ ይገኛል፡፡ ትምህርቱ የሚሰጠው በነጻ ነው፡፡ አካሄዱ አደገኛ ነው፡፡ የግእዝ ቃላትን ይጠቀማል፡፡ አሠራሩን በቤት ለቤት እና በሰንበት ት/ቤቶች ውስጥ ሕዋስ መር እና ግለሰባዊ(Cell based and Individual based) በሆነ መልኩ ያካሂዳል፡፡ በየሀገረ ስብከቱ ቅርንጫፍ ከፍቶ በእስር ቤቶች እና ኮሌጆች ላይ እየሠራ ይገኛል፡፡

‹‹የእውነት ቃል አገልግሎት›› - ከሰዋስወ ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ ከፍተኛ መንፈሳዊ ት/ቤት በኑፋቄው በአባቶች ተወግዞ በወጣው ግርማ በቀለ በተባለው ግለሰብ የተመሠረተ ነው፡፡ ይህ ማኅበር ወይም ድርጅት የርቀት ትምህርቶችን ማስተማር፣ በራሪ ጽሑፎችን ማሰራጨት እና ቤተ ክርስቲያናችንን የሚነቅፉ መጻሕፍትን ማሳተም እና ማሰራጨት ላይ በርብርብ እየሠራ ይገኛል፡፡ ለዚሁ ዓላማ መሳካትም ከመንፈሳዊ ኮሌጅ የሚወጡ አንዳንድ ተማሪዎችን እየወሰደ በማሠልጠን መልሶ በማስገባት ትምህርቶችን መበከል አንዱ ስልቱ ነው፡፡ የትኩረት አቅጣጫው የነገረ መለኮት ምሩቃን እና ተማሪዎች ሲሆን በተናጠልም በቡድንም ትምህርቶችን በየአቅጣጫው ያሰራጫል፡፡ ትልቁ ተልእኳቸው በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚገኙ ጉባኤያትን እና ዐውደ ምሕረቶችን መቆጣጠር ነው፡፡ በአዲስ አበባ ሦስት ቢሮ አለው፡፡ በሰሜን ሰቆጣ እና ደሴ ላይ ይሠራል፡፡

‹‹ማኅበረ ኪዳነ ምሕረት›› - የገዳም ኑሮ ሲከብዳቸው የኮበለሉ ሰዎች የመሠረቱት ማኅበር ነው፡፡ ‹‹ብቃት ደረጃ ላይ ደርሰናል›› የሚሉ ሰዎችን በመከተል እና ሴቶችን በመድፈር ነውር ይታወቃሉ፡፡ መሥራቹ ግለሰብ በጽላት ዘረፋ ተይዞ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ በማረሚያ ቤት ይገኛል፡፡ በተለይ በሰሜን ሸዋ፣ ደቡብ ወሎ፣ ወለጋ፣ አዲስ አበባ ዙሪያ ባሉ የኦሮሚያ(ምዕራብ ኢትዮጵያ) ከተሞች ይንቀሳቀሳል፡፡

‹‹የቅድስት ማርያም የስብከተ ወንጌል ማስፋፊያ ማኅበር›› - ይህ ማኅበር በቅርብ ጊዜ የተቋቋመ(እነ በጋሻው ደሳለኝ እና ያሬድ አደመ በዋናነት የሚሳተፉበት) ሲሆን የተቋቋመባቸው ዋና ዋና ዓላማዎች፡- (1)የትምህርት አሰጣጡን ይዘት ከመሠረታዊ የቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ ይልቅ ግራና ቀኝ ወደማያስለይ እና መሠረታዊ ቁም ነገር ወደማያስጨብጥ ተራ ወግ እና ተረት መለወጥ ነው፤ የዚህ ተግባር ዓላማም ምእመኑ መሠረታዊ የሆነውን የቤተ ክርስቲያኑን አስተምህሮ እንዳያውቅና እንዲህ ከሆነም የሚጫንበትን ኑፋቄ ሳያቅማማ እና ሳይለይ እንዲቀበል ለማድረግ ነው፡፡ (2)የስብከተ ወንጌሉን አቅጣጫ ለቤተ ክርስቲያናችን ወካይ ዓርማ (Icon) የሚባሉትን ነገሮች የሚያጥላላ እና የሚያናንቅ ማድረግ ነው፡፡ በዚህም ሕዝቡ ለቤተ ክርስቲያን ያለውን አክብሮት እንዲቀንስ እና እንዲጥል ከዚያም በውስጡ ቤተ ክርስቲያኑን እንዲጠላ ማድረግ ነው፡፡ (3)ሃይማኖታዊ ልዩነቶችን ማጥፋት፤ ይህም ፕሮቴስታንታዊውን አስተምህሮ አሾልኮ በማስገባት ‹‹አንድ ነን፣ እዚህም እዚያም የሚሰበከው ጌታ ነው፤. . . ወዘተ›› በማለት ከውስጥ ሆኖ መለወጥ ነው፡፡ (4)የተለያዩ ማኅበራትን በሕዋስ(Cell) ደረጃ በየጉራንጉሩ መመሥረት እና ማቋቋም፤ እነዚህን ጥቃቅን ማኅበራት አህጉረ ስብከት ስለማያውቋቸው እና የሚቆጣጠሩበትም መንገድ ስለ ሌላቸው እነዚህ የሚያዘጋጇቸው ጉባኤያት፣ የሚጋብዟቸው ሰባክያን እና በዚያም የሚሰጠው ትምህርት ለዓላማቸው የተመቸ ይሆናል፤ እየሆነም ነው፡፡ (5) በስብከቶቻቸው እና በጽሑፎቻቸው የፕሮቴስታንቶችን ምንጮች መጠቀም፣ ለዚህም በቅርብ ጊዜ ያሳተሙት መጥሐፍ ሐሳቡ ብቻ ሳይሆን ርእሱ ሳይቀር የፕሮቴስታንት ፓስተር ከጻፈው መጽሐፍ የተወሰደ ነው፡፡

ማኅበረ ተስፋ ኪዳነ ምሕረት - የተደራጀው ከሐዋሳ ደብረ ምሕረት ቅዱስ ገብርኤል ሰንበት ት/ቤት በሃይማኖታዊ ችግሮች በተባረሩ እና በወጡ አካላት ነው፡፡ ከክልሉ በፀረ-ኤች. አይ.ቪ/ኤድስ መከላከያ እንቅስቃሴ ስም ፈቃድ በማውጣት በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛል፡፡ የሚሠራቸው ሥራዎች ከቤተ ክርስቲያን ፈቃድ ውጭ ጉባኤያትን በማዘጋጀት እና ገንዘብ በማካበት ነው፡፡

ወቅታዊው የቤተ ክርስቲያን ጉዳይ በሚያሳስባቸው የመንበረ ፓትርያሪኩ ምንጮች የተላከልን ይኸው ባለ 50 ገጽ ሰነድ ሁኔታው ጠቅላይ ቤተ ክህነቱን በእጅጉ ከሚያሳስብበት ደረጃ ላይ በመድረሱ በሚመለከታቸው አካላት መካከል የተሐድሶ ኑፋቄን ምንነት እና የሚያስከትለውን አደጋ ተረድቶ የጋራ ግንዛቤ ከመያዝ አኳያ እና መወሰድ በሚገባቸው ርምጃዎች ዙሪያ ተከታታይ ውይይቶች እየተካሄደበት እንደሆነ ተመልክቶበታል፡፡

የፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ኑፋቄ በቤተ ክርስቲያናችን አገልግሎት እና ህልውና ላይ ስለጋረጠው ግልጽ አደጋ የተለያዩ መረጃዎችን ስታድርስ የቆየችው ደጀ ሰላም ዘግይቶም ቢሆን ከሚደረገው ከዚህ እንቅስቃሴ ጎን እንደምትቆም እያረጋገጠች ወደፊት የሰነዱን ይዘቶች እንዳመቺነቱ በመከፋፈል ለማስነበብ ጥረት ታደርጋለች፡፡

2 comments:

  1. እያንዳንዳችን እግዚአብሄር ይርዳን:: ይህንን ሥራ ለሚሰሩ ሰዎች ደግሞ እግዚአብሄር የተበላሸው ልቡናቸው እግዚአብሄር ያድስላቸው:: እግዚአብሄር ከዘመኑ ፈተና ሁሉ ሁላችንን ይተብቅ:: እመብርሃን መጨረሻችንን ታሳምርልን:: አሜን::

    ReplyDelete
  2. Egziabher Tehadisowochin Kemidre getse yatifalin

    ReplyDelete