‹‹የጎንደር ምንቸት ውጣ … የትግሬ ምንቸት ግባ›› በቤተ ክህነት (ነመራ ዋቀዮ ቶላ )
ይህ የቤተ ክክነታችን ችግር እውነታን የዳሰሰ ጡመራ የዛሬ አራት ዓመት አካባቢ ደጀ ሰላም ብሎግ አስነብባን ነበረ:: አሁንም በተለምዶ ስደተኛ ሲኖዶስ እየተባለ የሚጠራው ቡድን “መንበሩ ለእኔ ይገባኛል” እያለ ነው::ስደተኛው ሲኖዶስ የመሰረቱት በስደት ላይ ያሉት የጎንደር ተወላጅ የሆኑት ብፁዓን አበው “በትግሬዎቹ/በወያኔ ተገፍተን መንበራችን ተቀማን” እያሉ ለ20 ዓመታት ያህል ምእመናን ሲያምሱ ኖረዋል:: በዚህም ምክንያት ቤተ ክርስቲያኒቷ በፍቅር መስፋፋት ሲገባት በውጩ ዓለም በጥላቻ እና በጎጠኝነት ለቁጥር በሚያስቸግር ሁኔታ ተከፋፍላለች:: እውነት የጎደሬዎቹ ወደ መንበር መምጣት የቤተ ክርስቲያኒቱ ችግር ይፈታ ይሆን??? አሐቲ ተዋሕዶ በአባቶች መካከል የተፈጠረው መከፋፈል አጥብቃ ትቃወማለች:: ጎጠኝነትን ግን ታወግዛለች:: በስደት ላይ የሚገኙት ብፁዓን አባቶች ከቅዱስ ሲኖዶስ ጋር ታርቀው ወደ አገራችው እንዲመለሱም እንፈልጋለን:: የአባቶች መታረቅ የሚመጣው ግን እውነታዎች ሳይደባበቁ በግልጽ አውጥተው ሲነጋገሩ ብቻ ነው ብላ አሐቲ ተዋሕዶ ታምናለች:: የሚከተለውን የነመራ ዋቀዮ ቶላ ጽሑፍ አንብቡት:: መልካም ንባብ::
የቤተ ክርስቲያን ነገር እንዲህ ‹‹አነሰ ሲሉት ተቀነሰ›› እየሆነ፣ እንዲመሯት የተሾሙት አበው እንዲህ ከጎረምሳ ባላነሰ እልኸኝነትና ማን አለብኝ ባይነት ሲመላለሱ ነገሩ ሁሉ ብዙዎችን ግራ እንዳጋባ አለ፡፡ ይህ ዛሬ በቤተ ክርስቲያንና በሃይማኖት ስም የሚፈጸመውን ታሪክ-ይቅር-የማይለው-ድርጊት ለመቃወም ብዕሬን በድጋሚ ለማንሳት ወደድኹ፡፡ አስቀድሜ የቀድሞው 4ኛው ፓትርያርክ ሲመቱን እንዳይፈጽሙ ከሚጠይቋቸው ጋር ለመደመር አንዲት የተማጽኖ ደብዳቤ አቅርቤ ስለነበረ ነው ይህን ‹‹በድጋሚ›› ያልኩት፡፡ የዚህ ጽሑፍ ዋና ዓላማ‹‹በእውነቱ ይህ ሁሉ ቱማታ ለኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን በማሰብ ነውን? ወይስ ከጀርባው ሌላ ምክንያት አለው›› የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ መሞከር ነው፡፡
በኢትዮጵያ መንበረ ሥልጣን ለመቀመጥ በተለያዩ ገዢዎችና ነገሥታት መካከል አያሌ ጦርነቶች እየተደረጉ አንዴ አንዱ አንዴም ሌላው እያሸነፉ፣ አንዴ መንግሥቱን ወደ ላስታ ሌላ ጊዜም ወደ ሸዋ በሌላውም ወደ ጎንደርና ትግሬ ሲያዘዋውሩት እንደቆዩ በመጨረሻም ጠንካራ መሪ በጠፋባቸውና መሳፍንቱ የይስሙላ ነገሥታ እያስቀመጡ እስከ መግዛት እንደ ደረሱ የቅርቡ ታሪካችን እማኝ ነው፡፡ ይህ የጥቃቅን መሳፍንት ዘመን በታላቁ ባለ ራዕይ መሪ በቋራው አንበሳ በአጼ ቴዎድሮስ ከተፈጸመ በኋላ አገሪቱ በአንድነት ለመቆየት ችላ ነበር፡፡ እርሳቸውን ተከትለው የተነሱት የትግሬው ዮሐንስም አገሪቱን በአንድነት ለመጠበቅ ችለዋል፡፡ የአድዋው ባለድል እምዬ ምኒልክም ዓለምን ባስደነቀው ጀግንነታቸው፣ ለዕድገት ከነበራቸው ትልቅ ተስፋ ባለፈም ከሁሉም በተሻለ የአገርን አንድነት ለመጠበቅ ችለዋል (ምኒልክንና ኦሮሞን አስመልክተው ለሚነሱት ጥያቄዎች መልስ መስጠት ከርዕሱ ውጪ ስለሆነ ታልፏል)፡፡ ከዚያ ወዲህ አንደኛውኑ መንበረ መንግሥቱ ወደ መሐል አገር ተሸጋግሮ ሊቆይ ችሏል፡፡ ዘመነ መሳፍንት እንዲህ ባለው መልኩ ፍጻሜ አግኝቷል ቢባልም ሽኩቻውና ፉክክሩ ዛሬ ድረስ ቀጥሏል፡፡
ይህ በተለይ ግዘፍ ነሥቶ የታየው ባለፉት ሠላሳ ዓመታት በተደረጉት ‹‹የራስን ዕድል በራስ የመወሰን›› ትግሎች ነው፡፡ በዘመነ መሳፍንት አስተሳሰብና ኋላም ከኮምኒስቶች በተዳቀለው አመለካከት ላይ የተገነባው ውየናና የአገራችን ዘመነኛ ፖለቲካ ሁሉም ራሱን ለቤተ መንግሥቱ ሲያጭና ሲያፎካክር ቢቆይም የተሳካለት ግን የትግሬው መሳፍንት ልጆች የሚመሩት ወያኔ ነው፡፡ እነሆ እስከ ዛሬ መንበሩን ጨብጧል፡፡
ታዲያ ይህ ሁሉ ታሪክና ሐተታ ከቤተ ክህነቱ ጋር ምን አገናኘው መባሉ ተገቢ ጥያቄ ነው፡፡ በእኔ አመለካከት የቤተ ክህነታችንና የመነኮሳቱ ችግር ይኸው ሥልጣንን ለመያዝ የመሽቀዳደም መሳፍንታዊ አመለካከት ነው፡፡ ሐሳቤን ትንሽ ዘርዘር አድርጌ ላብራራ፡፡ ቤተ ክህነት ምንም እንኳን መንፈሳዊ አገልግሎት የሚከናወንበት መንፈሳዊ አስተዳደር ቢሆንም ለብዙ ዘመናት ከቤተ መንግሥቱ ጋር በነበረው ቅርበት ምክንያት ቤተ መንግሥቱ ውስጥ ያለው በጎም ሆነ ክፉ ስሜት ተጋሪ መሆኑ አይቀርም፡፡ ከዚህም ስሜት አንዱ ሥልጣንን በአካባቢ የመያዙ ጉዳይ ነው፡፡ ቀደም ብሎ ለረጅም ዘመናት ግብጻውያን ጳጳሳት እየተሸሙ ይላኩ ስለነበረ የአገሬው መነኮሳት ራሳቸው ከሁሉ በላይ አድርገው አዛዥ ናዛዥ ለመሆን ዕድሉ አልነበራቸውም፡፡ ቤተ ክርስቲያናችን በአስተዳደር ራሷን ችላ፣ የራሷን ልጆች ጳጳሳት አድርጋ መሾም ስትጀምር ግን ለብዙ ጊዜያት ታፍኖ የቆየው ‹መሳፍንታዊ› አስተሳሰብ ተገለጠ፡፡ የሚሾሙትን አበው ሃይማኖት ሳይሆን ወንዝና አውራጃ ማጥናት፣ የራስን ‹ወገን› ለማብዛት መሽቀዳደም ተጀመረ፡፡ በዚህ ረገድ ሥልጣን ‹ከእጄ አምልጣ ሸዋ ገብታ ቀረች› የሚለው የጎንደር ቡድን በአቋራጭ የጥንት ‹‹የበላይነቱን›› (የበላይነት ከነበረ ማለት ነው) ለማስመለስ ቆርጦ ተነሣ፡፡ ከራሱ ቡድን ውጪ ያለ ቄስንም ጳጳስንም ከመጤፍ ሳይቆጥር ራሱን ብቻ እያኩራራና እያጋነነ፣ ሌላውን እየናቀና እየገፋ፣ የዘረኝነትን አዝመራ እያስፋፋና እያጎለመሰ ሄዶ ድንገት በትግሬዎቹ መሳፍንት ልጆች ኃይልና ብልጠት ተበልጦ ሁሉን ለማጣት ተገደደ፡፡ ፓትርያርኩ ከሥልጣናቸው ወረዱ፡፡ ሌሎቹም ጎንደሬዎች ይዘውት የነበረው ወንበር ከሥሩ ተፈነቀለ፡፡ ‹‹የጎንደር ወጪት ይውጣ … የትግሬ ወጪት ይግባ›› ተባለ፡፡ ሥልጣን ከጎንደር ወደ ትግሬ ገባች፡፡ መርቆርዮስ ወረዱ … ጳውሎስ ወጡ፡፡ በዘመነ መሳፍንትኛ ብትመለከቱት የቋራው ካሳ ወረደ የትግሬው ካሳ ተሾመ እንደማለት ነው፡፡ ዘረኝነትን እያስፋፉ በሌላው ሲቀልዱ ኖረው በራሳቸው ብልሃት የመጣ ሌላ ዘረኛ ወንበራቸውን ቀማቸው፡፡ ተደላድሎም ተቀመጠ፡፡ ዛሬ እርሱን በዘረኝነት ቢያሙት ማንም የሚሰማቸው የለም፡፡ ‹ስልቻ ቀንቀሎ … ቀንቀሎ ስልቻ››፡፡ መቸም ዛሬ እውነትን መፈለግ ሞኝነት ስለሆነ ‹‹አንዱ ባንዳ ሰደበኝ›› ወይም ምናልባት ‹‹አንዱ ወያኔ ስሜን አጠፋው›› ሊሉ ይችሉ ይሆናል፡፡ በእነርሱ የዘር ጨዋታ ውስጥ የለሁበትም፡፡ የማንም ፍርፋሪ ፈላጊም አይደለሁም፡፡ ሁለቱም ቡድን ቤተ ክርስቲያናችንን እያጠፋና እያመሰ መሆኑን ነው የማውቀው፡፡
ስለዚህ የዘረኝነትን በሽታቸውን በሃይማኖት ስም ከሚያስታምሙት ‹‹በሽታቸውን አውቀው መድኃኒት ቢፈልጉለት›› ይሻላል፡፡ ዘረኝነቱን እነርሱ ሲያስፋፉት ትክክል የሚሆንበትና እነ አባ ጳውሎስ ሲያደርጉት ግን ስሕተት የሚሆንበት ምክንያቱ አይታየኝም፡፡ ሁለቱም ቡድኖች የመሳፍንት ዘመን ተፍካካሪዎች እንጂ የሃይማኖት ሰዎች አይመስሉም፡፡ ግባቸውም ቤተ ክርስቲያኒቱን መጠበቅ፤ ማሳደግና ማስፋፋት አይደለም፡፡ ጭንቀታቸው የወንበር ጉዳይ ነው፡፡ የሚያሳዝነው ግን ይህንን ሁሉ ምዕመን እንዲህ ያለጠባቂና እረኛ ማስቀረታቸውና አባት አልባ ማድረጋቸው ነው፡፡ ስለዚህ በእውነት ለቤተ ክርስቲያን የሚያስቡ ሁሉ የነገሮችን ምንጭና መነሻ ማጤን አለባቸው፡፡ በሃይማኖትና በአገር ስም የግላቸውን ፈቃድ ለመፈጸም ደፋ ቀና የሚሉ ሰዎችን ስሜትና ፍላጎት ስናስፈጽም መኖር የለብንም፡፡ በተለይም ምዕመናን ከነዚህ ዘረኛ መነኮሳት ቅጥ ያጣ ውድድር ራሳቸውን ገሸሽ ማድረግ አለባቸው፡፡ እኛ በምንሰጣቸው ድጋፍ ነው እንዲህ ቤተ ክርስቲያኒቱን መጫወቻ ያደረጓት፡፡
No comments:
Post a Comment