ክርስትና ሰዉነት ለክርስቶስ ማደሪያ መቅደስነት የተሠራበት የድኅነት መንገድ ነው፡፡ሰው በነፍሱ ወይም ከትንሣኤ በኋላ ባለው ሕይወቱ ብቻ ሳይሆን በዚህ ምድር በሚኖርበት ጊዜም ሰዉነቱ የክርስቶስ ማደሪያ መቅደስ፣ኅሊናዉ ቃሉ የተቀረጸበት ጽላት፣ ልቡናዉም የበጎ ነገር ሁሉ ማደሪያ ታቦት እንዲሆን የተዘጋጀ ነዉ፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳዉሎስ‹‹ የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ እንደ ሆናችሁ የእግዚአብሔርም መንፈስ እንዲኖርባችሁ አታውቁምን?... ወይስ ሥጋችሁ ከእግዚአብሔር የተቀበላችሁት በእናንተ የሚኖረው የመንፈስ ቅዱስ ቤተ መቅደስ እንደ ሆነ አታውቁምን? በዋጋ ተገዝታችኋልና ለራሳችሁ አይደላችሁም፤ ስለዚህ በሥጋችሁ እግዚአብሔርን አክብሩ›› /1ኛ ቆሮ 6፤ 13- 19/ ሲል እንደገለጸልን ሰዉነታችን ለእኛ ፍላጎት ማከማቻነት የተዘጋጀ ቁምሳጥን ሳይሆን የእግዚአብሔርን ፈቃድ ለመፈጸም የተሰጠን ቅዱስ ንዋይ ነው፡፡ ሐዋርያዉ እንደገለጸዉ ገንዘብነቱም ለእግዚአብሔር ነዉ፡፡ አገልግሎቱም እግዚአብሔርን ማክበር ነው፡፡
በተለይ በሐዲስ ኪዳን የሰው ሰውነት ልዩ የእግዚአብሔር ምሥዋዕ ( መሥዋዕት ማቅረቢያ) ክቡር ንዋይ ነዉ፡፡ ራሱ እግዚአብሔርም አስቀድሞ በነቢዩ ‹‹ አዲስም ልብ እሰጣችኋለሁ፣ አዲስም መንፈስ በውስጣችሁ አኖራለሁ፣ የድንጋዩንም ልብ ከሥጋችሁ አወጣለሁ የሥጋንም ልብ እሰጣችኋለሁ። መንፈሴንም በውስጣችሁ አኖራለሁ በትእዛዜም አስሄዳችኋለሁ፥ ፍርዴንም ትጠብቃላችሁ ታደርጉትማላችሁ›› /ሕዝ 36፣ 26/ ሲል ያናገረው ሰውነታችን ሙሉ በሙሉ ለእርሱ ፈቃድ ብቻ የሚገዛና ፍጹም ማኅደረ እግዚአብሔር እንዲሆንም ስለሚሻ ነው፡፡ ‹‹ የድንጋዩንም ልብ ከሥጋችሁ አወጣለሁ›› የሚለው ጥንቱን በሰው ሰውነት ዉስጥ የድንጋይ ልብ ተገጥሞላቸዉ የነበረ ሆኖ ሳይሆን ሰዎች ለእግዚአብሔር ፈቃድ ሳይሆን ለራሳቸዉ ፍላጎት ሲገዙ ለዚያም ሲያደሉ መቆየታቸዉን ለመዉቀስና በሐዲስ ኪዳን ግን ይህን የሚረዱበት ጸጋ የሚሰጣቸው መሆኑን ለመግለጽ ነው፡፡
በብሉይ ኪዳን ጊዜ እግዚአብሔር መሥዋዕት እንዲሠዉልት ትዕዛዝ ሲሰጥ ሊጠቀሙባቸዉ ከፈቀዳቸው አንዱ ያልተወቀረ ድንጋይ ነበር፡፡ በኦሪቱ ‹‹የድንጋይም መሠዊያ ብታደርግልኝ ብረት በነካው ድንጋይ አትሥራው በመሣሪያ ብትነካው ታረክሰዋለህና›› /ዘጸ 20፤ 25/ ተብሎ ከመገለጹም በላይ በነቢዩ በኢያሱ ‹‹መሠዊያው ካልተወቀረና ብረት ካልነካው ድንጋይ ነበረ›› /ኢያ 8፤ 31/ ተብሎ በመጻፉ ግልጽ ሆኖልናል፡፡ ይህን የመሰሉትና በኦሪት ዘመን የነበሩት ትዕዛዛት ግን መሥዋዕቱ ብዙዎቹ ለሐዲስ ኪዳኑ ሥርዓትና አምልኮ ምሳሌዎች ስለነበሩ እንርሱን የሚተካዉ አማናዊዉና ዋናዉ ሲመጣ በሐዲሱ ተተክተዋል፡፡ ለምሳሌ የኦሪቱ የደኅንነት መሥዋዕት በጌታችንና በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ አማናዊ ሥጋና ደም ተተክቷል፡፡ ሌሎቹም የመሥዋዕት ዓይነቶች እንዲሁ ተተክተዋል፡፡ ከዚሁ ከመሥዋዕት ዓይነቶች ጋርም መሠዊያዎቹም ተለዉጠዋል፡፡ በሐዲስ ኪዳን አንዱና ዋናዉ መሠዊያም የክርስቲያኖች ሰዉነት ነው፡፡ ይህንንም ሐዋርያዉ ቅዱስ ጴጥሮስ ‹‹ እናንተ ደግሞ እንደ ሕያዋን ድንጋዮች ሆናችሁ፥ በኢየሱስ ክርስቶስ ለእግዚአብሔር ደስ የሚያሰኝ መንፈሳዊ መሥዋዕትን ታቀርቡ ዘንድ ቅዱሳን ካህናት እንድትሆኑ መንፈሳዊ ቤት ለመሆን ተሠሩ ›› /1ኛ ጴጥ 2፤5/ በማለት በሐዲስ ኪዳን ሰዎች ራሳቸው ሕያዋን ( የመሥዋዕቱ) ድንጋዮች መሆናቸዉን ነግሮናል፡፡ የመሥዋዕቱ ድንጋዮች ከሆኑ ደግሞ ልክ በኦሪቱ እንደተገለጸዉ የተወቀሩ መሆን የለባቸዉም፡፡ አሁን ጥያቄዉ‹‹ ምንድን ነዉ መወቀር›› ሊሆን እንደሚችል እገምታለሁ፡፡
ቀደም ብለን በጥቅሶቹ እንደተመለከትነው በኦሪቱ ድንጋዩ ብረት ከነካዉ ወይም ከተወቀረ ይረክሳል፡፡ ስለዚህ መወቀር ወይም ለድንጋዩ ባዕድ በሆነው ብረት መነካት የለበትም፡፡ የእኛ ሰዉነትም የምሥጋና መሥዋዕትን ለእግዚአብሔር የምናቀርብበት መሠዊያ ስለሆነ እንደ ብረት ባዳዉ በሆነ በዘፈንና በመሳሰሉት መነካት መወቀርና መርከስ የለበትም፡፡ በክርስትና ሕይወት ዉስጥ እዉነተኛ አምልኮ የሚባለዉን ትልቁን የእግዚአብሔር መቅደስ እና ምሥዋዕ የሆነ ሰዉነቱንም ሊያረክሰዉ ከሚችለው ከዚህ ዓለም ዝባዝንኬ መጠበቅ መቻልና ቢቻል ለሌሎችም ሰዎችም የመንፈስም የቁስም ድጋፍ አድርጎ ሰዉነታቸዉን አመስጋኝ ማድረግ መቻል ነው፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ያዕቆብ ‹‹ንጹሕ የሆነ ነውርም የሌለበት አምልኮ በእግዚአብሔር አብ ዘንድ ይህ ነው፤ ወላጆች የሌላቸውን ልጆች ባልቴቶችንም በመከራቸው መጠየቅ፥ በዓለምም ከሚገኝ እድፍ ሰውነቱን መጠበቅ ነው›› /ያዕ 1፤27/ ሲል እንደገለጸው ዋናዉ የክርስቲያን ሥራ ( እዉነተኛ አምልኮ ) የዚህ ዓለም እድፍ ከተባሉ ከዘፈን፣ ከስድብ፣ ከዝሙት፣ … ከማንኛዉም ርኩሰት ሰዉነቱን መጠበቅ ነው፡፡
በአሁኑ ጊዜ ብዙ ሰዎች ያለ ዘፈን መኖር የሚቻል ሁሉ እስከማይመስላቸዉ ደርሰዋል፡፡ በርግጥ በሀገር ቤት ያሉ ዘመዶቻችን ያለ እንጀራ መኖር የማይቻል እንደሚመስላቸዉ ሁሉ አንዳንድ ከተሜዎችንም ያለ ዘፈን መኖር የማይቻል ቢመስለን የሚደንቅ አይደለም፡፡ የእኛን እንጀራ ፈጽሞ መኖሩን የማያዉቁና ሌላ ምግብ የሚመገቡ እንዳሉት ሁሉ ልክ እንዲሁ ዘፈን የማያውቁና በሌላ ዜማ (ምግበ ነፍስ) የሚኖሩም ብዙ ሰዎች መኖራቸዉን ማወቅ ጠቃሚ ነው፡፡ በተለይ በአሁኑ ዘመን በከተማዉ አካባቢ የሚያድገዉ አብዛኛው ሰው በአንድም በሌላም መንገድ ሳይወድም ጭምር ዘፈን የመስማትና ሳይታውቀዉ ቃናዉን የመልመድ፣ ጣዕም አድርጎ የመቀበልም ግዴታ ወድቆበታል፡፡ እንዲያዉም የሚናገርልን አጥተን ነዉ እንጂ እዉነቱን እናገር ካልን ነፍሳችን በማትፈልጋቸዉ ነገሮች አስገድዶ መደፈር ተፈጽሞባታል ልንል እንችላለን፡፡ ከዚህም የተነሣ በሒደት ስለተለማመድነዉ በሱስ ከተያዙ በኋላ ከዚያ ለመውጣት ሲሞክሩ እንደሚቸገሩት እኛም ሳናዉቀውም ቢሆን ተገደን ወይም በአጋጣሚ ከለመድነው ዘፈን ለመዉጣት ብንፈልግ እንኳ ሊቸግረን ይችላል፡፡አንድን ነገር አቅቶናል ማለት ይቻል ይሆናል፤ ነገር ግን አሁንም የተፈቀደ ነው ማለት አይደለም፡፡ አንዳንድ ሰዎች ለራሳቸዉ የሚያቅታቸዉን ሁሉ የተፈቀደ እንዲሆን የመከራከር ዝንባሌም ይታይባቸዋል፡፡ መጾም ያቃተዉ ጾሙን፣ ማስቀደስ ያቃተው ቅዳሴዉን፣ … እያለ የሚቀንስ ከሆነ ሰነባብቶ ያለ ምንም ነገር ሊቀር እንደሚችል መረዳት አያዳግትም፡፡ እንዲህ ያለ ሰው ለራሱ የሚስማሙትና ሰዉነቱን ደስ የሚያሰኙ ነገሮችን ሲያይና ሲሰማ ብቻ ትክክል ስለሚመስለዉና መለኪያው ለራሱ መስማማቱና አለመስማማቱ ወይም መመቸቱና አለመመቸቱ ስለሆነ በመጽሐፍ ቅዱሳዊዉና በቀኖናዊዉ መለኪያ ለመጓዝ ይከብደዋል፡፡ ስለዚህ ዘፈንን ለምደነዋል ወይም የዘፈን ‹‹ ጣዕም ›› ያስደስተናል ማለት ግን ስሕተትነቱን ሊያጠራጥረን አይችልም፡፡ በሚሰጠን ደስታም በመለካት መዘናጋት ተገቢ አይደለም፡፡ መለኪያዉ ደስታ ቢሆንማ እነ ዝሙትና ስካርም ስሕተት ሊሆኑ አይችሉም ነበር፡፡
አንዳንዱ ሰው ደግሞ በራሱ ሀሳብና ፍልስፍና በመጓዝ የመጽሐፍ ቅዱስ አንዳንድ ቃላትን ከፍላጎቱ ጋር አስማምቶ በመተርጎም ስሕተቱን ትክክል ነዉ ብሎ ለመከራከርም ወደ ኋላ አይልም፡፡ ዘፈንም ይህ ከሚደረግላቸዉ ነገሮች አንዱ መሆኑ ግልጽ ነዉ፡፡ ‹‹ ስሙን በዘፈን ያመስግኑ›› /መዝ 149፤ 3/ የሚለዉንና የመሳሰሉትን በመጥቀስ ዘፈንን በመጽሐፍ ቅዱስ የተፈቀደ ወይም ያልተከለከለ አድርጎ ማቅረብ ትልቅ ስሕተት ነዉ፡፡እንዲህ(ዘፈን) እየተባሉ የሚጠሩት በዘጸ 15 ፤ 1- 21 እንደተገለጹት ያሉት መዝሙራ ናቸዉ፡፡ እነዚህ በእኛ በጥምቀትና በመሳሰሉት በዓላት በሕዝባዉያን ዘንድ እግዚአብሔርን ለማመስገን የሚዉሉ ዜማዎች እንጂ የዚህ ዓለም ዘፈኖች አይደሉም፡፡ ‹‹ ያመስግኑ›› የሚለዉ ግስ በራሱ የጉዳዩን ምንነትም በደንብ ያስረዳል፡፡ ከዚህ አለፍ ሲሉም ቢያንስ በተወሰነ ጊዜ ለምን አንዘፍንም ለማለት ‹‹ አንዳንድ ጊዜማ በዋልድባም ይዘፈናል›› የሚለዉን አባባል በመጥቀስ በሆነ ጊዜ በዋልድባም የሚዘፈን አስመስለዉ የሚነግሩን አሉ፡፡ አባባሉ የመነጨዉ ግን በገዳሙ መነኮሳት ከተደረገዉ ሳይሆን በዋልድባ ዙሪያ ዝሆንና አንበሳ አድነዉ ድል ሲቀናቸዉ በድንኳኖቻቸው ይዘፍኑ ከነበሩት የጎንደር ነገሥታትና መኳንንት ታሪክ ነው /ኅሩይ ወልደ ሥላሴ፣ ዜና ሐዋርያት፣ 103/ ፡፡ እነዚህን የመሰሉ ሌሎች ታሪኮችንና ጥቅሶችን አብዝተን በመጥቀሳችን ዘፈን ምን ያህል እንደተቆጣጠረን እናሳይ እነደሆን እንጂ የተፈቀደ ልናደርገዉ አንችልም፡፡
በአጭሩ ዘፍንን የሚፈቅድ መንፈሳዊ ሕግም ሆነ ሥርዓት የለም ፤ እንዲያዉም አብዝተዉ ይኮንኑታል እንጂ፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ሐዋርያ ዘፈንን የሥጋ ሥራ እንደሆነ ሲነግረን /ገላ 5፤ 22/ ነቢዩ ኢሳይያስ ደግሞ ‹‹በዚያም አጋንንት ይዘፍናሉ››/ ኢሳ 13፤ 21/ በማለት የአጋንንት ሥራ ያደርገዋል፡፡ በሌላም ቦታ ሰዎች ሲዘፍኑ አጋንንት እንደሚደሰቱና አብረው ተሳታፊ እንደሚሆኑ ‹‹… እየዘፈኑም ከአጋንንት ጋር ይጫወቱ ነበር፡፡ አጋንንትም ጫወታቸዉንና ዘፈናቸዉን ያደንቁላቸዉ ነበር ›› / 1ኛ መቃ 36፤ 27-28/ ተብሎ ተጽፎልናል፡፡ በሥርዓት መጻሕፍትም ‹‹ ዘፋኞች አትሁኑ›› /ዲድስቅልያ 7/ ተብሎ ታዝዟል፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ‹‹ ዘፈንን ትተዉ ዘንድ እማልዳችኋለሁ›› ሲል ሐዊ ደግሞ ‹‹ በዘፈን ጸንተዉ የሚኖሩ ይፈረድባቸዋል›› ይላል፡፡
መንፋሳዊ ምሥጢሩ ግን አንድ ነዉ፤ መወቀር፡፡ ዘፈን ሰዉነታችን በሚያማልሉ ሥጋዊ ፍላጎቶች ተጠምዶ በኃጢኣት መዶሻ ተወቅሮ በመርከስ ለእግዚአብሔር መሥዋዕት ለማቅረብ እንዳይችል የሚያደረከሰዉ ነገር ነዉ፡፡ የዛሬዉ ጉዳያችን ዘፈን ስለሚመለከት እንጂ ሰዉነታችን ተወቅሮ የሚረክሰዉ በዘፈን ብቻ ነው ማለት አይደለም፡፡ ብዙዎች ከመሠዊያዉ የራቁበት ምሥጢር የኽው ነዉ፤ በልዩ ልዩ ነገሮች መወቀር፡፡
No comments:
Post a Comment