በዋልድባ የመነኰሳቱ ስደት፣ እስርና ድብደባ ተባብሶ ቀጥሏል
· የተሰደዱት መነኰሳትና መናንያን ቁጥር 13 ደርሷል::
· ሁለት መነኰሳት በማይ ገባ ወረዳ ታስረዋል::
· በጠ/ሚኒስትሩና በፓትርያርኩ አሟሟት “ውዥንብር ፈጥራችኋል” በሚል ተከሰዋል::
(ደጀ ሰላም፤ ነሐሴ 27/2004 ዓ.ም፤ September 2/ 2012/ READ THIS NEWS IN PDF)፦ በቤተ መንግሥቱም በቤተ ክህነቱም በተመሳሳይ ወቅት የደረሰብን ሐዘን አነጋጋሪ ከመኾን አልፎ ፍትሐ እግዚአብሔር የተፈጸመበት፣ የእግዚአብሔር መልእክትም የተላለፈበት እንደ ኾነ እየተነገረ ነው፡፡ እንደ አቶ ስየ ኣብርሃ ያሉ የተቃውሞ ፖለቲካ መሪዎች ሳይቀሩ በኹኔታው ላይ ቆም ብለን እንድናስብ እየመከሩ ናቸው፡፡
እያንዳንዱ አካል ሓላፊነት እንዳለበት ተገንዝቦ በወደፊት መንገዳችን ላይ ጋሬጣ ከመፍጠር ታቅበንበጎ ማሰብ፣ በጎ መናገር፣ በጎ ማድረግ እንደሚያስፈልግ፤ የዕርቅ፣ የይቅርታና የመቻቻል መንፈስ ለማስፈን መሥራት እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡ የመንግሥት ባለሥልጣናትና ብዙኀን መገናኛም የጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ድንገተኛ ኅልፈት “የሕዝቡን መንፈስ እንዳስተሳሰረው” እየዘገቡ ናቸው፡፡
በአንጻሩ የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩንና የጠቅላይ ሚኒስትሩን ኅልፈተ ሕይወት ተከትሎ በጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ጥቂት ሓላፊዎችና በአንዳንድ የመንግሥት አካላት ዘንድ የተያዘው አቋምና የሚፈጸመው ድርጊት በአስተሳሰብ ይኹን በተግባር የተባለውን በጎ የማሰብ፣ በጎ የመናገር፣ በጎ የማድረግ መንፈስየሚበርዝ ነው፤ ለተደጋጋሚ ሐዘንም እንዳይዳርገን ያሰጋል፡፡
በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት÷ ቋሚ ሲኖዶሱን ለማጠናከር እና ዐቃቤ መንበረ ፓትርያርኩን ለማገዝ ከሚል ቀና አስተሳሰብ በዐቃቤ መንበረ ፓትርያርኩ ብፁዕ አቡነ ናትናኤል ሐሳብ አቅራቢነት በተመረጡት ስምንት ብፁዓን አባቶች (የምዕራብ ወለጋ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ኄኖክ ተጨምረዋል) ላይ ውስጥ ውስጡን የተጀመሩትና ይፋ መውጣት የጀመሩት ክሦችና ስም ማጥፋቶች በማሳያነት ሊጠቀሱ ይችላሉ፡፡
ክሦቹና ስም ማጥፋቶቹ በይዘታቸው “እገሌ የእገሌ ማኅበር አባልና ደጋፊ ናቸው” ከሚሉ ፖለቲካዊ ክሦች ጀምሮ በጎጠኛና ጥቅመኛ አስተሳሰብ የዘቀጡ የቀድሞው ዘመነ ፕትርክና ግብረ በላዎች ፈጠራዎች ናቸው፡፡ ግለሰቦቹና ቡድኖቹ በኾነ መንገድ እንዲገቱ ካልተደረገም የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ ዜና ዕረፍት ከተሰማበት ማግሥት አንሥቶ ወደ መንግሥት አካል እንዳደረሱት የተዘገበው ይኸው ክሥና ስም ማጥፋት ብዙዎች የሚጓጉለት የዕርቀ ሰላም ሂደት መልካም ፍጻሜ እንዳይደርስ አሉታዊ ተጽዕኖ እንደሚፈጥር ተሰግቷል፡፡
በአንዳንድ የመንግሥት መዋቅሮች የሚፈጸመው ተግባር ከገጠመን ተደራራቢ ሐዘን የመማርንና ስሕተትን የማረም ዝንባሌ የሚታይባቸው አይደሉም፡፡ የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩንና የጠቅላይ ሚኒስትሩን ሕመምና ኅልፈት ተከትሎ በዋልድባ አብረንታንት ገዳም ላይ የተጀመረውና የቀጠለው የማሳደድ፣ የመደብደብና የማሰር ርምጃው ዛሬም አልተገታም፡፡ ለአቶ መለስ በጽኑ መታመም በ‹መተተኛነት› ሲወነጀሉና ሲታሰሩ የቆዩት ማኅበረ መነኰሳቱ ከድንገተኛ ሞታቸው በኋላ ደግሞ “ታጋይን በመግደል” ተከሰው ለድብደባና ለስደት እየተዳረጉ ነው፡፡
ቀደም ሲል ባስነበብነው ዜናችን እንዳመለከትነው÷ እስርና ድብደባ ሲደርስባቸው ከቆዩት አበው መካከል ስድስት የአብረንታንት መነኰሳት ወደተለያዩ ሥፍራዎች ተሰደዋል፡፡ ከትናንት ጀምሮ በደረሰን መረጃ መሠረት ደግሞ ለመሰደድ የተገደዱት መነኰሳት እና መናንያን ቁጥር 13 ደርሷል፡፡
የመነኰሳቱና መናንያኑ ስም ዝርዝር የሚከተለው ነው፡- 1) አባ ገብረ ማርያም ገብረ ዮሐንስ (ጎንዴ)፤ 2) አባ ገብረ ማርያም ወልደ ሳሙኤል፤ 3) አባ ገብረ ጊዮርጊስ ገብረ ማርያም፤ 4) አባ ገብረ ሥላሴ ዋለልኝ፤ 5) አባ ኀይለ ኢየሱስ ወልደ ሳሙኤል (ሁለት ተመሳሳይ ስም ያላቸው አባቶች)፤ 7)አባ ገብረ ሕይወት፤ 8) መናኝ ገብረ ጊዮርጊስ፤ 9) መናኝ ኀይለ መለኰት፤ 10) መናኝ ኀይለ ማርያም፤ 11) መናኝ ታዴዎስ፤ 12) መናኝ ገብረ እግዚአብሔር፡፡
አባ ወልደ ሩፋኤል የተባሉት አባት ክፉኛ መደብደባቸውን ያመለከቱት ምንጮቹ ከዚህ ሳምንት ሰኞ፣ ነሐሴ 22 ቀን 2004 ዓ.ም፣ በምዕራብ ትግራይ ዞን ማይ ገባ ወረዳ (ወልቃይት አስተዳደር) ታስረው እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡ አባ ገብረ ሥላሴ ገብረ እግዚአብሔር እና አባ ኀይለ ሚካኤልየተሰኙት እኒህ ሁለት አባቶች÷ ከዋልድባ አብረንታንት ገዳም ተልከው በማይ ሕርገጽ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን በማገልገል ላይ የሚገኙ አባቶች እንደነበሩ ታውቋል፡፡
ለሁለቱ አባቶች መታሰር በመንሥኤነት የቀረበበባቸው ‹ክሥ› በአንድ በኩል “አቡነ ጳውሎስንና አቶ መለስን በአንድ ጊዜ የገደላችኹ እናንተ ናችሁ” በሚል ቢነገርም በሌላ በኩል ደግሞ “ሱባኤ ይዘናል እያላችኹ በሁለቱ መሪዎች አሟሟት ላይ ኅብረተሰቡ ውዥንብር ውስጥ እንዲገባ አድርጋችኋል” የሚል እንደ ኾነ ተዘግቧል፡፡ ለአሜሪካ ድምፅ ሬዲዮ ዋልድባን አስመልክቶ መግለጫ የሚሰጡትን አባት “ደብቃችኋል፤ ያሉበትን ተናገሩ” በሚል ጥያቄም እንግልት እየደረሰባቸው እንደሚገኝ ነው የዜናው ምንጮች ጨምረው የገለጹት፡፡
የማይ ገባ ወረዳ የወልቃይት ስኳር ልማት ፕሮጀክት ጽ/ቤት እና የሠራተኞች ካምፕ የሚገኝበት ወረዳ ነው፡፡ የማይ ሕርገጽ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን ደግሞ ለፕሮጀክቱ በሚገነባው የዛሬማ ወንዝ ግድብ ሳቢያ ውኃ ከሚሸፍናቸውና ከሚነሡ በርካታ አብያተ ክርስቲያን መካከል አንዱ እንደኾነ መዘገቡ ይታወሳል፡፡
በተያያዘ ዜና÷ ዛሬ፣ ነሐሴ 27 ቀን 2004 ዓ.ም በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል የቀብር ሥነ ሥርዐታቸው ለሚፈጸመው ለጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ /ገብረ እግዚአብሔር/÷ ትናንትተሲዓት በኋላ በመንበረ ፓትርያርክ ቅድስተ ቅዱሳን ማርያም ገዳም ጸሎት ተደርጎላቸዋል፡፡ ከምሽቱ 2፡00 ጀምሮ በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ጸሎተ ማሕሌቱ ሲካሄድ አድሯል፡፡ ሌሊቱንየጠቅላይ ሚኒስትሩ አስከሬን በሚገኝበት በታላቁ ቤተ መንግሥት ጸሎተ ፍትሐት የተደረገ ሲኾን ሥርዐቱም በቀጥታ የቴሌቪዥን ሥርጭት ተላልፏል።
በወጣው መርሐ ግብር መሠረት÷ ጠዋት አስከሬኑ መስቀል፣ ጽንሐሕና ጥላ በያዙ ካህናትና በሚመለከታቸው አካላት ታጅቦ ወደ መስቀል አደባባይ ከወረደ በኋላ ዋናው መርሐ ግብር በዚያው ተከናውኖ ፕሮግራሙ እንደተጠናቀቀ አስከሬኑ በካህናት፣ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ቤተሰቦች፣ ከሀገር ውስጥና ከውጭ በመጡ የመንግሥታትና ተቋማት ተወካዮች ታጅቦ ወደ ካቴድራሉ ያመራል፡፡ በካቴድራሉ አስከሬኑ በተዘጋጀለት ሥፍራ ሥርዐተ ቀብሩ እንደተፈጸመ መድፍ እንደሚተኰስም ተገልጧል፡፡
በሥርዐተ ቀብሩ ለሚከናወነው አገልግሎት ከመላው የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ገዳማትና አድባራት የተመረጡ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን - መዘምራን ጥንግ ድርብ እንደለበሱ ማምሻውን ጥበቃው ወደተጠናከረበት የካቴድራሉ ቅጽር በጥብቅ ፍተሻ ሲገቡ ታይተዋል፡፡ የመንፈሳዊ አገልግሎቱን አጠቃላይ መርሐ ግብር የሚያስተባብሩት የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅ ንቡረ እድ ኤልያስ ኣብርሃ ሲኾኑ መዘምራኑን የሚቆጣጠሩትና የሚያስተባብሩት ደግሞ በቀድሞው ዘመነ ፓትርያርክ የመጨረሻ ወራት በጡረታ የተገለሉትና በንቡረ እድ ተስፋይ ተወልደ የተተተኩት የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን መጋቤ ካህናት ሊቀ ማእምራን ኀይለ ሥላሴ ዘማርያም ናቸው፡፡ መጋቤ ካህናቱ በትጥቅ ትግሉ ተሳትፎ የነበራቸውና የካህናት አስተዳደር መምሪያን በሐላፊነት የመሩ ናቸው፡፡
ቸር ወሬ ያሰማን፤ አሜን፡፡
5 comments:
please make sub topics on the following issues
soset tililik zenawoch nachew
1.waldiba
2.betekihinetu gaa yalew yemengist chanaa
3.ye-prime ministiru sirat kebir
More details please
God Bless you
MAHARENA KIRESTOSE
BAENETA MAREIAME MAHARANA KIRESTTOSE..
MEMANANE ENALEKESA LABATAKERESTSINE,
enazanem lebe setachawe
nafease yemare.