Sunday, 2 September 2012


የፓትርያርኩ ቀብር ላይ ትልቁ ስህተት


(አንድ አድርገን ነሐሴ 27 2004 ዓ.ም)፡-ፓትርያርኩ ቅዳሴውን አቋርጠው ፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ህዳሴውን አቋርጠው ከዚህኛ ዓለም ወደዚያኛው ዓለም ከሄዱ ቀናት ተቆጥረዋል ፤ ቤተመንግሰቱም ሆነ ቤተክህነቱ አስጨናቂ የሆነ የሀዘን ድባብ ወርሶታል ፤ የፓትርያርኩ አስከሬን ለ6 ቀናት አፈር ሳይቀምስ ሲቆይ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ደግሞ ለ13 ቀናት ያህል ቆይቷል ፤ የፓትርያርኩን ሥርዓተ ፍትሐት ላይ የምስራቅ አብያተ ክርስትያናት ፤ የግብጽ ኦርቶዶክስ ፤ የአርመንና የህንድ ኦርቶዶክስም ጸሎተ ፍትሀት አድርገዋል ፤ ከእነዚህ አብያተክርስትያናት ጋር የኢትዮጵያ ኦርዶክስ ተዋህዶ እምነት የዶግማና የእመነት አንድነት ስላላት  ጸሎተ ፍትሀት ማድረጋቸው በስርዓተ ቤተክርስትያናችን ተቀባይነት አለው፡፡ 


በእጅጉ የሚገርመው ደግሞ የእመነትና የዶግማ አንድነት የሌላቸው ከእኛ ጋር የማይቀድሱና የማይቆርቡትንም የግሪክ ቤተክርስትያን ተወካይ መሪዎችን ጸሎተ ፍትሀት እንዲያደርጉ መጋበዙ ስርዓተ ቤተክርስትያንን ያፋለሰ ነው፡፡ በወቅቱ ለሚመለከታው ክፍሎች ጉዳዩ እንዲደርሳቸው ቢደረግም ግሪኮቹ እንዳያኮርፉ በሚል ሰበብ አንድ ኢትዮጵያዊ ሊቀ ጳጳስ አዘዋል ተባለ ፤ ይህ በጣም ያሳዝናል ያስቆጣልም ፡፡ በርግጥ ማንኛውም  ዓይነት ያለው ማህረሰብ ሁሉ ሀዘኑን በአግባቡ መግለጥ ይችላል ፤ ለምሳሌ የሃይማኖት ተቋማት የጋራ ጉባኤ ሼህ አህመዲን አብዱላሂ የተሰማቸውን ጥልቅ ሀዘን በግላቸው የገለጹ ሲሆን በወከሉት ተቋም ስም ደግሞ የሀዘን መግለጫ አሰምተዋል ፤ ይህ በእጅጉ ትክክለኛ የሆነ አካሄድ ነው ፤ የሃይማኖቶችን ወንድማማችነት የሚያሳይ ነው ፤ የሃይማኖቶቹ መልካም መገለጫቸውም ጭምር ነው ፤ ጥቂት ሙስሊሞች በጊዜው ከክርስትያኑ እኩል ነጭ ቆባቸውን ጭንቅላታቸው ላይ ደፍተው የአቡነ ጳውሎስ ቀብር ላይ ሲታደሙ መመልከት ራሱ ውስጥን ደስ ከማሰኝት በተጨማሪ ያላቸውን ቁርኝት ያመላክታል ፤   በተመሳሳይ የቫቲካን ቤተክርስትያን ፤ የኖርዌይ ቤተክርስትያን እና የመላው አፍሪካ አብያተክርስትያናት  ጽህፈት ቤትና የዓለም አብያተክርስትያናት ጽ/ቤት ተወካይ ያሰሙት የሀዘን መግለጫ ምንም እንኳን ትርጉሙ ለማህበረሰቡ ያስተላለፈ ባይሆንም  በቋንቋቸው እንደሰማነው የቅዱስ ፓትርያርኩን ዓለም ዓቀፋዊ ስብዕና የመሰከረ መሆኑን ብዙዎች በዕለቱ የመሰከሩት ነው፡፡

የግሪክ ቤተክርስትያንም ልክ እንደዚሁ ስለ ቅዱስነታቸው ምስክርነት እንዲሰጡ መጋበዝ ሲገባ ነገር ግን ጸሎተ ፍትሀት እንዲያደርሱ ማድረግ ከየት የመጣ ሥርዓት ነው ? በዚህ ሁኔታ ውስጥ አቡነ ጳውሎስ በህይወት ቢኖሩ ይወቀሱበት ነበር ፤ እሳቸው ግን ተያዙ ፤ ተገነዙ ፤ ያልተያዙት  በአውደ ምህረት አዘዙ  ፤ ተናዘዙ ፡፡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶን የእምነት ልዩነትና የግሪክ ክርስትያኖችን ልዩነት አለማወቅ ወይስ ትርጉሙ ምንድነው ? በሌሎች አማኞች ጸሎተ ፍትሀት እንዲደረግ ማድረጉ ትርጉሙ በሥጋ የተለዩንን ፓትርያርክ የሚመለከት ? ወይስ በሕይወት ያሉትን ሥርዓት አስፈጻሚ የሚመለከት ? ይህን ጥያቄ የሚመልስ ማነው ? ለዚህ ሁሉ ሊወቀስ የሚገባው ማነው ? 

ነፍሳቸውን ይማርልንና አቡነ ጳውሎስ ሲሾሙ ጀምሮ በስርዓተ ቤተክርስትያን መፋለስ ምዕመኑ ጉርምርምታ ነበረው ፤ አሁንም ገና ቀድመው የነበሩት ፓትርያርክ ይምጡ ወይም ቀጣዩ አባት  ሳይታወቁ ይህን የመሰለ ትልቅ ስህተት መስራት ተገቢ አይደም ፤ ከዓመታት በፊት መረጃዎች እንደ አሁኑ ጊዜ የመረጃ ቴክኖሎጂው ባልተስፋፋበት ጊዜ በሰሚ ሰሚ ነበር ተጨምረው ፤ ተቀንሰውና ዘግይተው ነበር ሰዎች ዘንድ የሚደርሱት ፤ አሁን ግን እንኳን የተደረገው ይቅርና ሊደረግ የታሰበው ነገር ምዕመኑ ዘንድ ለማድረስ በቀላሉ የሚቻልበት ጊዜ ላይ ተደርሷል ፤ ስለዚህ ስህተት ሰርቶ መሸፋፈንም ሆነ ከተጠያቂነት ለመሸሽ ስለማይቻል ወደፊት ያሉ ነገሮች እጅጉን ቢታሰቡበት መልካም ነው እንላለን ፤ የተፈጸመን ስህተት ለማንም ብለን አይናችን እያየ ጆሯችን እየሰማ መደበቅ አንችልም ፤ ምዕመኑ እንዲያውቀውና በወቅቱ ጥያቄ እንዲያቀርብ ከመጻፍም ወደ ኋላ አንልም ፤ በማንም ጊዜ ይፈጸም ፤ ማንም ይፈጽመው ከስርዓተ ቤተክርስትያን ውጪ የሆነን ነገር ዝም አንልም ፤ ችግሮች መፍትሄ እንዲኖራቸው ዳግምም እንዳይሰሩ ከተፈለገ ችግሮችን ለቅሞ ማውጣት ግድ ነው ፤ አሁንም ያለፍንበትን መንገድ ላለመሄድ ቁጭ ብሎ ማሰብን ይጠይቃል፡፡(ሌሎች በርካታ ችግሮችን አስተውለናል ነገር ግን ይህን ያህል ክብደት ስለሌላቸው ትተናቸዋል)






“ነገር ግን ሁሉ በአገባብና በሥርዓት ይሁን።” 1ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 1440  “የሰው ልጅ ሆይ፥ ልብ አድርግ ስለ እግዚአብሔርም ቤት ሥርዓትና ሕግ ሁሉ የምናገርህን ሁሉ በዓይንህ ተመልከት በጆሮህም ስማ የቤቱንም መግቢያ የመቅደሱንም መውጫ ሁሉ ልብ አድርግ።” ትንቢተ ሕዝቅኤል 44፤5 “የእግዚአብሔርን ትእዛዝና ሥርዓት ትጠብቅ ዘንድ ነው እንጂ አምላክህ እግዚአብሔር ከአንተ የሚፈልገው ምንድር ነው?” ኦሪት ዘዳግም 10፤13 “ሰሎሞንም እግዚአብሔርን ይወድድ ነበር፥ በአባቱም በዳዊት ሥርዓት ይሄድ ነበር” መጽሀፈ ነገስት ቀዳማዊ 3፤3 እኛም እንደ ሰለሞን አባቶቻችን ባስቀመጡልን ስርዓተ ቤተክርስትያን ለመሄድ እግዚአብሔር ይርዳን፡፡

ቸር ሰንብቱ 

 መነሻ ሀሳብ ፡- ዕንቁ መጽሄት (ሊቀ ጠበብት ዘሪሁን ሙላቱ ከጻፈው ላይ የተወሰደ)

No comments:

Post a Comment