በዲ/ን ዳንኤል ክብረት

በይምርሐነ ክርስቶስ ጣራ ላይ የሚገኘው የዳዊት ኮከብ
ባለፈው ሳምንት ተስፋዬ ገብረ አብ አቡነ ተክለ ሃይማኖትን በተመለከተ ያነሣቸውን ነጥቦች ማየት ጀምረን ‹የሦስቱን ተክለ ሃይማኖቶች› ጉዳይ ለዛሬ አቆይተነው ነበር፡፡ እንቀጥል፡፡
1) የሰባተኛው መክዘ ተክለ ሃይማኖት
ተስፋዬ የጠቀሳቸው የሰባተኛው መክዘ ተክለ ሃይማኖት የሉም፡፡ እስካሁንም እንደርሱ ፈጠራቸውን የሚናገሩ እንጂ ማስረጃ ያመጡ አልተገኙም፡፡ ይህንን ነገር መጀመሪያ ያነሣው የግብጽ ቤተ ክርስቲያን ገድለ ተክለ ሃይማኖትም ስለ ጽላልሽ (ኢቲሳ) ተክለ ሃይማኖት እንጂ ስለ ሰባተኛው መክዘ ሌላ ተክለ ሃይማኖት አይናገርም፡፡ ገድለ ተክለ ሃይማኖትን በተመለከተ ልዩ ልዩ ቅጅዎች ቢገኙም ሁሉም ግን በተወለዱበት ቦታ፣ በተወለዱበት ዘመን፣ በወላጆቻቸው ስም፣ በሠሯቸው ሥራዎችና በገዳማቸው ላይ የሚተርኩት ታሪክ ተመሳሳይ ነው(Encyclopedia Aethiopica, Vol., IV,.P.833) በአንድ ወቅት ታላቁን የታሪክና የኢትዮጵያ ጥንታውያን መዛግብት ሊቅ ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌን ስለዚህ ጉዳይ ስጠይቃቸው ‹አለኝ ያለ ማስረጃውን ያምጣ፣ የለም የምንለው ፈልገን ልናመጣ አንገደድም›› እንዳሉት አለን የሚሉት እስኪያመጡ ድረስ የምናውቀውን ይዘን እንቀጥላለን፡፡