………... ጾምን ቀድሱ ………….
በገጣሚ ልዑል ገ/እግዚአብሄር
ከፌስቡክ ገጹ ላይ የተወሰደ
የሥጋ አውታሩ በዝንጥል ይመታል
ዕለታዊ ምቱ .... በሆድ ተጎብኝቷል
አፍለኛ ንጣቴን ሽበት አድክሞታል
በሥጋ ላይ በዝቶ ሥጋን አግምቶታል!
ሆዴን ሳበዛበት “ልተኛ ልተኛ” ይለኛል
ሸክሙን ስነሳው .... ተጣፍቶ ይቀለኛል
ያ ልብላህ ያልሁት ሥጋ ጥርስ ሰርቶ ነክሶኛል
በስድሳ ሰማንያ ሸውዶ ...... መቃብር ከቶኛል!
አወይ!!!
በደሌ ተጎዳጉዶ መሠረት ሆኖታል
ወጥ ቤት ሲቆመው ከጥድቁ ይልቃል
ያ ወረት የጎረሰው ከሩቅ ነጽሮኛል
እኔ በሥጋ እሱ በመንፈስ ጓደኛው አርጎኛል!
ክልዔቱ ተጣምረው ከሰማይ ርቀዋል
በተራ ተዛዝለው ገደል አዝግመዋል
እርከኑን ተሻግረው ገባር በር ሰርተዋል
ወንጌሉን ጠርቅመው ሁለት ሆድ ከፍተዋል!
ጉሮሮ ቢቆለፍ ለነፍሴ ምግቧ ነው
ሥጋዬን ሳደክመው ለሰማይ ይቀርበው
ምቾቴን ስክደው ምኞት እንዳይደግመው
ያብባል ጥውልጉ ቁስለ ነፍስ ሲፍቀው!
ጭቃ በጭቃ ላይ እንዴት ቤት ሊሰራ?
መንፈሱ ተዳክሞ በሸክላው ሊጠራ
ዕዳ ሲበራከት አንድ በአንድ ቆጠራ
የቆረጠው ተስፋ ገብያ ላይ ሊደራ!
ሆዴን ላጠበው ነው ድልድይ ልዘረጋ
ቁስለቴን ሊፈውስ የሰማይ ቤት አልጋ
ስሜቴን ከልክዬው ባለ ብዙ ዋጋ
ፍስኩን ነስቼው ከጦሙ ልጠጋ!
“መሀረኒ አብ”
እኔማ በድንግዝግዝ ሲቃ ተናንቆኝ አቃሰትሁ
በገደል ማሚቱ ጩኼ ጩኼ በባዶ ደጋገምሁ
ከ ፍል ውሃ ከጋለ ብርት በእምነት ተተፋሁ
በምህረት ቃልኪዳን በእጆቹ ተዳሰስሁ!
ያምረኛል መመሰጥ ያ የአትክልት ቦታ
በልጓም አስሬ ሆድ ክጄ ጧት ለታ
የቅዱሳን ማኅበር ኅብረ ፍቅር ገበታ
በእንግድዬው አገር ላይ ታቹን ስመታ!
በፊቱ ለመቆም ሆዴ እግር አውጥቷል
ራሱን ሲቀጣ ፈጣሪውን አይቷል
ዘላለም ሊደላው መንገድ አበጃጅቷል
ለረጅም ስደቱ ላይርበው ሰንቋል!
ማ ያናውጠኛል? ነፋስ ቢበረታ
ሆዴን አስረዋለሁ ሲመሻሽ ልፈታ
የጠላቴን ጦሩን በቀኝ ክንድ መከታ
ትጥቆቼን ታጥቄ በሜዳው ስረታ!
ምላሴን ነሳሁት ሰውን ‘ዳይበላ
ልቤን ከለከልሁት አሳዳጅ ላይጠላ
እግሮቼ ከመንገድ ላይሄዱ ከሌላ
የእጆቼ ንጽህና በጥቅም ላይሰላ!
ከእንግዲህ…
ብልቶች ተባብረው ዓለም ላይ ዘመቱ
ዐይን..ዕዝን..እግር..እድ በጦም ተካተቱ
አንደበት ጠጠር ነክሷል ርቋል ከሐሜቱ
ዛሬ መዐዛ ሊሸተው ጠፍቶለት ግማቱ!
በቃ!
በተስፋ ገብቼ በሽልም ያውጣኛ
በማመን ጠይቄ ጩኸቴን ይስማኛ
የጦም ’ለት ይቀደስ ቸርነት ይስጠኛ
አካል ሁሉ ጦሞ አዲስ ሰው ያርገኛ::
……………. አሜን!!! ………….
—
No comments:
Post a Comment