Friday, 7 February 2014

"እግዚኦ አርእየኒ እመከ = አቤቱ እናትህን አሳየኝ"

በቴዎድሮስ በለጠ

"ሰባኪው" በአትሮንሱ ላይ "ቆሟል" .......የቆመበትን እንኳ አያውቅ ( ሊቁ ድንግልን አትሮንሱ ለቃለ አብ ይላታልና...)

ምዕመናን ይጠይቃሉ " ስለ ድንግል ማርያም አስተምረን" ?
ጥያቄውን "ይመልስባቸዋል" እንዲህ ሲል "እኛ እዚህ ድረስ የመጣነው ጌታን ልንሰብክላችሁ እንጂ ስለ ማርያም ልናወራላችሁ አይደለም.... እስኪ ቅዱስ ጳውሎስን ተመልከቱ ስለ ጌዴዎንና ስለ ባርቅ ስለ ሶምሶንም ስለ ዮፍታሔም""""እንዳልተርክ ጊዜ ያጥርብኛል አለ እሱ ጊዜ ያለው ስለ ጌታ ብቻ ለመመስከር ነው...."
ይህ በአይሁድ ምኩራብ ፥ በተንባላት አውድ አልያም በመናፍቃን አዳራሽ የተነገረ እንዳይመስላችሁ በቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን መድረክ ላይ በድፍረት የተፈጸመ እንጂ :: እውነትም ሥፍራው የምሕረት አደባባይ ነው አምላክ ለቁጣና ለመአት የቅጣት ሠይፉን የሚያዘገይበት ለትዕግስትና ለይቅርታ የፍቅር እጁን የሚዘረጋበት "አውደ ምሕረት"! .... እንግዲህ ምን እንላለን "እግዚኦ ተዘከራ ለአሐቲ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን እንተ ሀለወት እምጽንፍ እስከ አጽናፈ ዓለም" 

ብቻ ስለ ሰባኪ ተብዬ ግለሰቦች ማውራት አልሻም በመጽሐፍ እንደመጣባቸው የሚተነፍሱትን እንደነዚህ ያሉትን ተዉአቸው ከቁጥርም አትክተቷቸው ተብሏልና "እስትንፋሱ በአፍንጫው ውስጥ ያለበትን ሰው ተዉት እርሱ ስለ ምን ይቈጠራል?" (ኢሳ. 2:22) ባይሆን ግን ህዝቡ ጥያቄው ተመለሰበት እንጂ አልተመለሰለትምና ተከታዮቹን ነጥቦች ለመልሳችን ትምክህት የሚሆኑ ሐዋርያት ጠቅሶ ማስረዳት ይገባል:: ምክንያቱም እነዚህ የከበሩ ሐዋርያት ጥያቄውን ወደ ህዝቡ ለመለሱና በመልክ በቁመና እንዲደመጡ ለሚመስላቸው ይህን ብለዋልና "በመልክ እንጂ በልብ ለማይመኩ የምትመልሱላቸው መልስ እንዲኖራችሁ፥ በእኛ ልትመኩ ምክንያት እንሰጣችኋለን" (2ኛ. ቆሮ.5:12) መልካም ቆይታ....
"አርእየኒ እመከ = እናትህን አሳየኝ" ....
እኔ ግን አምላኬን ዘወትር የምለምነው ይህንን ነው "አርእየኒ እመከ = እናትህን አሳየኝ" ከምን አገኘኸው የሚል አይጠፋም....... በእመቤታችን የተአምሯ መጽሐፍ ላይ አባ ይስሐቅ የሚባል ደገኛ አባት ወደ ፈጣሪው "እርእየኒ እመከ" (እናትህን አሳየኝ) እያለ ሰባት ዓመት ሲጸልይ ኖሯል ይለናል:: በአምላክም በጎ ፈቃድ ድንግል ተገልጻለት "እረፍትህ ደርሷል እጣ ክፍልህ ከእኔ ነው" ብላቸው አርጋለች (መዝ.44 ትርጓሜን ይመልከቱ)..... እርሱስ እንዲህ ያለውን ተስእሎ (ልመና) ከምን አገኘው ካላችሁኝ ደግሞ በቅዱስ መጽሐፍ ቆርኔሌዎስ ቅዱስ ጴጥሮስን በቤተ ክርስቲያን ታሪክ ጢባርዮስ ቄሳር ፍቁረ እግዚእ ዮሐንስን ለማየት ይመኙ እንደነበር ስለሚያውቅ.... ታዲያ ለደቅስዮስ ወንበር ለኒቆላዎስ አጽፍ የሰጠች ልመናን የምትሰማ አፍጣኒተ ረድኤት ድንግል ለአባ ይስሐቅም የልቡን መሻት ፈጽማለታለች:: መቼም ስለ ነገረ ድኂን እና ምክንያተ ድኂን (Meaning and Means of Salvation) ያልተረዳ ሰው ይህን አገላለጥ በጭፍኑ ይነቅፋል በተለይም ደግሞ ድንግል ማርያም በነገረ ድኅነት ያላትን ሥፍራ ካለመገንዘብና ቤተክርስቲያናችንም በዚህ ረቂቅ መንገድ ላይ ያላትን ጥልቅ አስተምህሮ ካለመረዳት ይመነጫል ተመልከቱ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ያለ ጥርጥር ታላቅ ለሆነው ተዋህዶ መዝገበ ምሥጢር ፤
በሥጋ የተገለጠው አማኑኤል ያረፈባት ዙፋን፥
በመንፈስ የጸደቀውን ክርስቶስን የወለደችልን ንግሥት፥
ለመላእክት የታየውን የፍትረት ሁሉ ደስታ ያየንባት መጽሔት፥
በአሕዛብ የተሰበከው የክብር ጌታ ከሰማያት የወረደባት መሰላል ፥
በዓለም የታመነ መድኃኔዓለምን ያስገኘችልን ቤተ ፈውስ ፥
በክብር ወደአረገው አምላክ የምታደርሰን የእርቅ መደምደሚያ። አዎ ምክንያተ ድኂን እርሷ ናት
...... ለእርሷ የተሰጣት ምድራዊው ሥጦታ ብቻ ያይደለ ሰማያዊ ሃብት ሁሉ ነው "ተውህቦ ምህረት ለሚካኤል ወብሥራት ለገብር ኤል ወሀብተ ሰማያት ለማርያም ድንግል" እንዲል የዚህን ሁሉ ጸጋ ምንጭ ሊቁ አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ ሲነግረን ".......ብዙኃት ሀብታተ እግዚአብሔር ወመክፈልተ ሠናያት አላ እም አሐዱ መንፈስ:: ወቱኬ ጰራቅሊጦስ ዘአቀባ ለድንግል እምከርሰ እማ ከመኢትጌጊ ለዓለም አንጽሐ ከመ ኢትርሳሕ ቀደሳ ከመ ኢትርኮሰ ወረሰያ ታቦተ ለወልድ ዋህድ:: አብ ሠምራ ወልድ ተሰገወ እምኔሃ ወመንፈስ ቅዱስ ከለላ::~~~> ብዙ የእግዚአብሔር ስጦታዎችና በጎ እድል ካንዱ መንፈስ ቅዱስ የሚገኝ ነው እንጂ:: ይኸውም ጰራቅሊጦስ እንዳትበድል ድንግልን ከእናቷ ሆድ ጀምሮ ለዘለዓለም የጠበቃት አደፍ ጉድፍ እንዳይገኝባት ያነጻት እንዳትረክስ የቀደሳት ለወልድ ዋህድ (ለአንዱ ወልድ) ታቦት (ማደርያ) ያደረጋት እርሱ ነው:: አብ ወደዳት ወልድ ከእርሷ ሰው ሆነ መንፈስ ቅዱስ ጋረዳት::"ይለናል::
ይህ ሁሉ ክብር የታደላትን እመ አምላክን ክብሯን ለመስማት እና እርሷን ለማየት የለመነው ምዕመን ሊኮነን አይገባውም እስኪ ልበ አምላክ ዳዊት "አንዲት" ብሎ ባቀረባት ልመና ላይ የጠየቀውን እንመልከት "እግዚአብሔርን አንዲት ነገር ለመንሁት እርስዋንም እሻለሁ በሕይወቴ ዘመን ሁሉ በእግዚአብሔር ቤት እኖር ዘንድ፥ እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኘውንም አይ ዘንድ፥ መቅደሱንም እመለከት ዘንድ።" (መዝ.26:4 )... አይገርማችሁም የንጉሥ ዳዊት መሻቱ በህይወቱ ዘመን ሁሉ በቤቱ እየኖረ መቅደሱን መመልከት ነው.... በተመሳሳይ በቤተ ክርስቲያንም የተገኘው ምዕመን ጥያቄው አማናዊትዋን መቅደስ ማየት ነው ታዲያ በምኑ ይኮንኑታል .... ሌልም አገባብ እንመልከት ድንግል ማርያም በምድር ኑሮዋ የዕድሜዋን አንድ አራተኛ ያሳለፈችው ከወንጌላዊው ቅዱስ ዮሐንስ ጋር ነው ለአገላለጹ እንዲያመች ቅዱስ መጽሐፍ እንዲህ ይላል "ከዚህ በኋላ ደቀ መዝሙሩን። እናትህ እነኋት አለው። ከዚህም ሰዓት ጀምሮ ደቀ መዝሙሩ ወደ ቤቱ ወሰዳት።" (ዮሐ. 19 :27) አስተውሉ ወደ ቤቱ ነው የሚለው እንኳን ቤትና እንደ ሰማይ ወፎች መሰማርያ እንደ ቀበሮም ጉድጓድ የሌለውን ጌታ ሲከተሉ መርከብ መረባቸውን ጥለው ሁሉን ትተው አልነበረምን "ታንኳዎችንም ወደ ምድር አድርሰው ሁሉን ትተው ተከተሉት።" እንዲል (ሉቃ. 5:11) ቅዱስ ጴጥሮስም ይህን ሲያጸና .... "በዚያን ጊዜ ጴጥሮስ መልሶ፦ እነሆ፥ እኛ ሁሉን ትተን ተከተልንህ፤ እንኪያስ ምን እናገኝ ይሆን? አለው።" ይለናል (ማቴ. 19:27) ታዲያ የዮሐንስ ቤቱ ከየት የተገኘ ይሆን ቤቱ ያለው ልቡን ህሊናውን ህይወቱን ነው እንጂ.... አዎ በልቡ የዓለም ሁሉ ገዢ የሆነ ንጉስን የወለደች ድንግልን ሲዘከራት ኖረ
ለነገሩ ስለድንግል ማርያም ክብር ለመናገር አይደለም ለመጠየቅም ቢሆን በድንግል በረከት መጎብኘት በመንፈስ ቅዱስ ጸጋ መቃኘት ይጠይቃል እንደ ቅድስት ኤልሳቤጥ (ሉቃ.1:41-42).... "ኤልሳቤጥም የማርያምን ሰላምታ በሰማች ጊዜ ፅንሱ በማኅፀንዋ ውስጥ ዘለለ፤ በኤልሳቤጥም መንፈስ ቅዱስ ሞላባት፥ በታላቅ ድምፅም ጮኻ እንዲህ አለች። አንቺ ከሴቶች መካከል የተባረክሽ ነሽ፥ የማኅፀንሽም ፍሬ የተባረከ ነው።" እንግዲህ በመጽሐፍ ቅዱስ እውቀትና በመንፈስ ቅዱስ እርዳታ ያልታገዘ ሰው ይህን ሊመሰክር ጊዜ ቢጣ ምን ይደንቅ እንዲያውም የሚገርመው ሊመሰክር ቢቃጣው ነው....ቅዱስ ጎርጎርዮስ ገባሬ መንክራት እንዲህ አለ "...... በምን አይነት ቃላት ድምጻችንን ከፍ አድርገን የእርሷን ድንግልናዊ ክብር እንገልጻለን? በምን አይነት ማሳያዎችና የክብር አዋጆች ነው የእርሷን እንከን አልባ የሆነውን ተምሳለቷን የምናወድሰው? በምን አይነት ዜማ ወይም ቃል ነው ከመላ እክት በላይ በክብር ከፍ ያለውን እርሷን የምናከብረው? እርሷ ፍሬ እንደሚያፈራ ዝግባ በመንፈስ ቅዱስ ከለላነት በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የተተከለች ናት:: በ እርሷ ምክንያት የክርስቶስ ልጆች የሰማያዊ መንግስት ወራሾች ሆነናል::... እርሷ የቅዱሳን ሐውልታቸው ናት...." እንግዲህ ከአባቶቻችን ያገኘናት ሃይማኖታችን ይህች ናት “ዛቲ ይእቲ ሃይማኖት ቅድስት እንተ ሠርዕዋ ወወሰንዋ አበው በሀገረ ኒቅያ ትኩን ብርሃነ ለእለ ኢተምህሩ ከመ ያእምሩ ምንት ምክንያቱ ዘውስተ ክፍላት እንተ ለኩሉ ነገር ይእመኑ ቦቱ ~~~> አምነውበት ጸንተውበት ይኖሩ ዘንድ የተነገረውን ነገር ሁሉ በየክፍሉ ያለው ምክንያቱ ምን እንደሆነ ያውቁ ዘንድ ላልተማሩት እውቀት እንድትሆን አባቶቻችን በኒቂያ የወሰኗት የደነገጓት የከበረች ሃይማኖት ይህች ናት”(ሃይ. አበ. ዘሠለስቱ ምዕት. ም.19 ፡ ቁ.11)
ልሳነ መዓዛ የተሰኘ ኅሩይ ንዋይ ቅዱስ ጳውሎስ "ጊዜ ያጥርብኛልና" ሲል ምን ማለቱ ነው? ንቋቸው አጥቅቷቸው አቃሏቸው ነውን? ሊያውም ስለ ነቢያትም እንዳልተርክ ነው ያለው ልብ አድርጉ "እመቦ ዘያስተሐቅር ነቢያት ያግህስ ርእሶ እምመአተ ዋህድ~~~> ነቢያትን የሚያቃልል ከአንዱ ወልድ መአት ራሱን ያርቅ" እንዲል የጌታ ወንድም ያዕቆብም "ወንድሞች ሆይ፥ የመከራና የትዕግሥት ምሳሌ የሆኑትን በጌታ ስም የተናገሩትን ነቢያትን ተመልከቱ።"(ያዕ. 5:10) ይለናል:: ቅዱስ ጳውሎስም በፍጹም ተጋድሏቸውን ዘርዝሮና ክብራቸውን ዘክሮ መጨረስ ባይቻለው እንዲህ አለ:: ደግሞም "ጊዜውን ያሳጠረና ጊዜው ያጠረበት ለየቅል ነው" አዎ ስለቅዱሳን ክብር ለመመስከር ጊዜውን የሚያሳጥር ለ "ነገረ-ዘቅ" የሚጣደፍ ሰው እና ቅዱሳኑን ሲዘክር ሲያከብር ጽናታቸውንን ሲመሰክርና ተጋድሏቸውን ሲናገር ውሎ ጊዜ የሚያጥረው ሰው ይለያያል:: ይልቁንም ቅዱስ ጳውሎስ ግን እንደ ደመና የከበቡን ምስክሮች ለመዳናችን ምክንያቶች የጽናታችን አብነቶች እያለ ሲያወሳቸው አይተናል "እንግዲህ ምን እላለሁ? ስለ ጌዴዎንና ስለ ባርቅ ስለ ሶምሶንም ስለ ዮፍታሔም ስለ ዳዊትና ስለ ሳሙኤልም ስለ ነቢያትም እንዳልተርክ ጊዜ ያጥርብኛልና እነርሱ በእምነት መንግሥታትን ድል ነሡ፥ ጽድቅን አደረጉ፥ የተሰጠውን የተስፋ ቃል አገኙ፥.....።" (ዕብ. 11:32) ምነው ታዲያ ጊዜውን ካሳጠረ ስለምን በቁጥር በዝተው በተጋድሎ ጸንተው ስላሉ ምስክሮች እንዲህ ምዕራፉን ሙሉ ማተት አስፈለገው... እንኳን ቅዱሳኑን ይቅርና በምድር እንኳ መልካም ምግባር በጎ ትሩፋት የታየባቸውን አንስቶ መዘከርና ማመስገን አርአያነታቸውንም ለሌሎች ማሳየት ይገባል:: ቅዱስ ዮሐንስ ወንጌላዊ ስለጋይዮስ እንዲህ አለ " ወዳጅ ሆይ፥ ምንም እንግዶች ቢሆኑ፥ ለወንድሞች በምታደርገው ሁሉ የታመነ ሥራ ትሠራለህ፥ እነርሱም በማኅበር ፊት ስለ ፍቅርህ መስክረዋል፤ ...ልጽፍልህ የምፈልገው ብዙ ነገር ነበረኝ፥ ዳሩ ግን በቀለምና በብርዕ ልጽፍልህ አልወድም፤ነገር ግን ወዲያው ላይህ ተስፋ አደርጋለሁ፥" (3ኛ. ዮሐ.1:5 ) ቅዱስ ዮሐንስ ለማየት ተስፋ ያደረገው እንዲህ የተመሰከረለትን ደገኛ ሰው ጋይዮስን ነው ስለ እርሱ በጽሑፍ መግለጡ ብቻ አላደርስ ቢለው ሊያየው ይናፍቅ ነበር:: በአካል ለማግኘት ጊዜውን ያሳጠረ ሳይሆን ፍቅራቸውን እና ናፍቆቱን ለመግለጽ ጊዜ ያጠረው ማኅቶተ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ጳውሎስም "እኛ ግን፥ ወንድሞች ሆይ፥ በልብ ያይደለ ፊት ለፊት ለጥቂት ጊዜ አጥተናችሁ፥ በብዙ ናፍቆት ፊታችሁን ለማየት እጅግ ሞከርን፤ ወደ እናንተ ልንመጣ ወደን ነበርና፥ እኔ ጳውሎስም አንድና ሁለት ጊዜ፥ ሰይጣን ግን አዘገየን።" (1ኛ . ተሰ. 2:17) ይላል አዎ ዛሬም ይህን እንዳይናገሩ ብዙ ሰይጣን ያዘገያቸው ሰዎች ድል ተነስተው ቅዱሳንን ለማየት ጊዜአቸውን አሳጠሩ እኛ ግን(ሃይ. አበ. ዘአባ ዘካርያስ. ም.108፡ቁ.23) “ወዓዲ ንትአመን ቦሙ በቃል ወበምግባር እምነተ ጽድቅተ ወናስተበቁዕ ኀቤሆሙ ከመ ያፈድፍዱ አእምሮቶሙ ዲቤነ ወከመ ይኩኑነ መራሕያነ ፍኖት ርትዕት ከመ ንርከብ ፍኖተ እንተ ትወስድ ለገቢረ ሠናይ ዘንትዌደስ ባቲ በደኃሪትነ ወከመ ይሕንጹ ደኃሪተነ በሠናይ ሕንጻ ላዕለ መሠረት ጽኑዕ ዘኢያንቀለቅል እንተ ይእቲ ሕንጻ መምህራን ትሩፋን ወባቲ ናጽንዕ ሃይማኖተነ እስከ ተፍጻሚተ ህይወትነ: ለእግዚእነ ሎቱ ስብሐት እስከ ለዓለመ ዓለም አሜን ~~~> ዳግመኛም በቃል በሥራ የተረዳች እውነተኛ ሃይማኖትን እናምንባቸዋለን:: እውቀትንም በ እኛ ላይ ያሳድሩብን ዘንድ ወደ እነርሱ እንማልዳለን በዘመናችን ፍጻሜ የምንመሰገንባትን በጎ ሥራን ለመስራት የምታበቃ መንገድን ለማግኘት ወደ ቀናች ሃይማኖት ይመሩን ዘንድ ፍጻሜአችን በማይናወጥ በጸና ሃይማኖት ላይ በተመሰረተ በበጎ ምግባር ያጸኑልን ዘንድ ወደ እነርሱ እንማልዳለን ይህችውም ፍጹማን መምህራን ያስተማሯት ትምህርት ናት እስከ ዘመናችን ፍጻሜ ድረስ ሃይማኖታችንን በ እርሷ እናጽና ለጌታችን ክብርና ምስጋና ይግባው አሜን! ” 

ይቆየን!!

No comments:

Post a Comment