Monday, 3 February 2014

ንዋያተ ቅዱሳቱ የማን ናቸው?

ጥር 26 ቀን 2006 ዓ.ም.
ምንጭ፡- ሐመር መጽሔት 21ኛ ዓመት ቁጥር 8 2006 ዓ.ም.


የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የዜማ መሣሪያዎች ከቅዱስ ያሬድ ጀምሮ በርካታ ሊቃውንት ሲያገለግሉበት የነበረና የሰማያዊውን የዝማሬ ሥርዓት መነሻ ያደረገ፣ ሰማያዊውንም ዓለም የሚያሳስብ፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ቃልም መነሻ ተደርጎ የተመረጠ፣ ኢትዮጵያዊ መልክ ኖሯቸውም የተዘጋጁ ናቸው፡፡

እነዚህ የዜማ መሣሪያዎች ቤተክርስቲያናችን ይዛ በምትጠቀምበት ቅርጽና ይዘት የሚገኙት በኢትዮጵያና ኢትጵያውያን እጅ ብቻ ነው፡፡ ይልቁንም ደግሞ የአንድ ቤተ ሃይማኖት ማለትም የኦርቶዶክስ ሃይማኖት መጠቀሚያ ሆነው እያገለገሉ ያሉ ናቸው፡፡

ይህ በእንዲህ እያለ ግን ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ሌሎች ቤተእምነቶች በከበሮ፣ በመቋሚያና ጸናጽሉ በራሳቸው ተጠቅመው በራሳቸው መንገድ የራሳቸውን እምነት ሲያራምዱበት እየታየ ነው፡፡ በመድረኮቻቸው ያንን ሲያደርጉ ታይተዋል፡፡ በቴሌቪዥን ፕሮግራም ሲያስተላልፉ ተስተውሏል፡፡

በተመሳሳይ ዜማው የዝማሬ ሥርዓቱ የበዓላት ሥርዓቱ ንዋየ ቅድሳቱ ሁሉ ደረጃ በደረጃ በተለያዩ ቤተእምነቶች ቁጥጥር ሥር ወድቋል፡፡ የበዓላት ቀናቱ ጭምር በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ባሕረ ሐሳብ መሠረት የሚወጣ ቢሆንም እንደራሳቸው አደርገው በዓል ሲያደርጓቸው ልዩ ልዩ መርኀ ግብር ሲፈጸምባቸው ይታያል፡፡ ለዚህ ማሳያ የሚሆነው የመስቀል በዓል ነው፡፡ በዓለ መስቀል ኦርቶዶክሳውያንን ብቻ የሚመለከት በዓል ቢሆንም አሁን ግን በቤተክርስቲያኒቱ የበዓል ዐውድ ውስጥ ሌሎች ቤተእምነቶች የራሳቸውም እንደሆነ በሚያስመስል መንገድ ስለሚቀርቡ ግራ መጋባት እየፈጠረ ነው፡፡ ይሄ ነገር በዚሁ ከቀጠለ ቤተክርስቲያናችን የእኔ የምትለው የራሷ ነገር እየጠፋ ሊመጣ ይችላል፡፡


በመሆኑም የዝግጅት ክፍላችን በተለይ የዜማ መሣሪያ በሆኑ ንዋየ ቅድሳት ጋር በተያያዘ ሁለት ባለሙያዎችን ለማነጋገር ጥረት አድርጓል፡፡ ያነሣናቸው ጥያቄዎችም ከሕግ፣ ከቅርስ ጥበቃና እንክብካቤ አንጻር በመሆኑ ያነጋገርናቸው ባለሙያዎችም በእነዚሁ ጉዳዮች ላይ ባለሙያ የሆኑ ናቸው፡፡ እነሱም የሕግ ባለሙያ የሆኑት አቶ ጌታሁን ወርቁና በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህር የሆኑት መምህር መንግሥቱ ጎበዜ ናቸው፡፡ ሁለቱንም ባለሙያዎች ጠይቀን የሰጡንን መልስ እንደሚከተለው አቅርበነዋል፡፡

ሐመር፡- አንዱ ቤተእምነት የሌላውን ቤተእምነት የትኛውንም ዓይነት የአገልግሎት መጠቀሚያ ንዋየ ቅድሳት መጠቀሙ ሕጋዊ ሊሆን የሚችልበት አካሔድ አለ? ሌሎች ከዚህ ጋር ተያያዥ የሆኑ የሕግ ሐሳቦችን ቢያመለክቱን


አቶ ጌታሁን ወርቁ፡- የቤተእምነት አገልግሎት መጠቀሚያን በተመለከተ ያሉት ሕግጋት በጣሙን ግልጽነት የሚጎድላቸው ናቸው፡፡ የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ከተመሠረተችበት ጊዜ ጀምሮ የምትጠቀምባቸው ንዋየ ቅድሳት አሉ፡፡ እነዚህን ንዋየ ቅድሳት ሌሎች ቤተእምነቶች ሲጠቀሙ አስተውያለሁ፡፡ እናም ጥያቄው የመጠቀማቸው ሁኔታ ከምን ሕግ የመነጨ ነው፡፡ ወይም ቤተክርስቲያኗ ንዋየ ቅድሳቱን ራሷ ብቻ እንድትጠቀም የማድረግ መብት ይኖራታል ወይ የሚለው ነው ምላሽ የሚፈልገው ጭብጥ፡፡
በሕግ አንድ ሰው የተፈጥሮ ወይም በሕግ ሰውነት የተሰጠው ተቋም መብት ሊያገኝ የሚችለው ከሕግ አልያም ከውል ነው፡፡ የቤተክርስቲያኗን መብት ሕግ እውቅና ከሰጠውና ስፋትና ወሰኑን ካስቀመጠው መብቷን ለመጠየቅ መነሻ ይሆናል፡፡ ሁለተኛው ውል ሲሆን ሁለት ወይም ከዛ በላይ የሆኑ ሰዎች (ተቋማት) መብቶችንና ግዴታዎችን ለማቋቋም ለማሻሻል ወይም ለማቋረጥ የሚያደርጉት ስምምነት ነው፡፡ እንዲህ ዓይነት ስምምነት በነፃ ፈቃድና በችሎታ ከተደረገ፤ ከሕግና ከሞራል ተቃራኒ ካልሆነ በተዋዋይ ወገኖች መካከል ሕግ ሆኖ የሚያስገድዳቸው ይሆናል፡፡

ንዋያተ ቅድሳትን በተመለከተ በቅድሚያ ግልጽ መሆን ያለባቸው የብያኔና በልማድ የሚታዩ ነጥቦች አሉ፡፡ የመጀመሪያው የንዋያተ ቅድሳት ትርጉም ነው፡፡ ከቃሉ ጥሬ ትርጉም ብንነሳ ንዋያተ ቅድሳት የሚባሉት ለእግዚአብሔር አምልኮ መፈፀሚያ የሚሆኑ ዕቃዎች ናቸው፡፡ በቤተክርስቲያን ትምህርት እነዚህን ንዋያት በቅዱስ ሜሮን የሚከብሩ ለዜማ፣ ለቅዳሴ፣ለምስጋና የተለዩ ዕቃዎች ናቸው፡፡ እነዚህን ንዋያት በተመለከተ ቤተክርስቲያን ብዙም አከራካሪ ያልሆነ መብት አላት፡፡ በተግባርም እነዚህ ንዋያት ሲሰረቁ፣ ሲዘረፉ ወዘተ ለፖሊስና ለፍ/ቤት አቤቱታ በማቅረብ ስታስመልስ የቆየችው ከዚሁ በመነሳት ነው፡፡ በሌላ በኩል ግን በቅዱስ ሜሮን የከበሩም ቢሆን የንዋያተ ቅድሳት ስፋት ከመስቀሉ፣ ከበሮ ጀምሮ ጧፍና እጣንም ሳይቀሩ የሚካተቱበት ነው፡፡ ጧፍ በየቦታው ከመመረቱና ለተለያዩ ማኅበራዊ አገልግሎት ከመዋሉ አንፃር በቅዱስ ሜሮን ቢከብርም እንደሌሎች ንዋያት ጠንካራ የሕግ ጥበቃ ላይሰጠው ይችላል፤ ይህም የሆነው ከማስረጃ አስቸጋሪነት አንጻር ነው፡፡ በቅዱስ ሜሮን ከብረው ንዋያተ ቅድሳት ያልሆኑት ግን የተለየ ምልከታ ሊደረግላቸው ይገባል፡፡ በሜሮን ባይከብሩም በቤተክርስቲያኗ ለዘመናት አምልኮ፣ ምስጋና ለመፈጸም ግብዓት የሚሆኑ ዕቃዎችን ለምሳሌ ከበሮ፣ ጸናጽል፣ መቋሚያ፣ ጥንግ ድርብ ወዘተ የመሳሰሉትን መሳሪያዎች በተመለከተ ግን ቀደም ሲል ያየናቸውን ያህል ግልጽ የሕግ ጥበቃ ሥርዓት አለመኖሩን አምናለሁ፡፡

በሕግ ደረጃ ለቤተክርስቲያኗ መብት መነሻ የሚሆኑት በፍትሐ ብሔር ሕጉ የተደነገገው የንብረት ሕግ፣ ስለቅርስ ጥናትና አጠባበቅ የወጣው አዋጅ እንዲሁም የቅጅና የተዛማጅ መብቶች ጥበቃ አዋጅ ናቸው፡፡ በእነዚህ ሕግጋት ቤተክርስቲያኗ በሕግጋቱ ላይ መብቷ እንዲታወቅና እንዲጠበቅ የተደነገጉትን ሁኔታዎች ካሟላች ባለመብት ሆና ሌሎች እንዳይጠቀሙ የምትከላከልበት ሁኔታ ይኖራል፡፡

በንብረት ሕግ በንብረት ላይ ሰፊ ጥበቃ የሚሰጠው መብት የሀብትነት (ባለቤትነት) (Ownership) መብት ሲሆን ይህ መብት በንብረቱ የመገልገል፣ ንብረቱን ለሌላ መጠቀሚያ የማከራየት ወይም የመሸጥ የመለወጥ መብትን ያጠቃልላል፡፡ በአንድ ዕቃ ላይ የባለቤትነት መብት ያለው ሰው /ተቋም መብት ሳይኖረው እጁ ካደረገው ሰው ወይም ከያዘው ሰው ሀብቱ ይገባኛል ሲል ለመፋለምና ማናቸውንም የኃይል ተግባር ለመቃወም እንደሚችል በፍትሐ ብሔር ሕግ ቁጥር 1206 ተደንግጓል፡፡ በሕጉ ባለሀብትነት (ባለቤትነት) የሚረጋገጠው እንደ ንብረቱ ዓይነት ነው፡፡ የሚንቀሳቀስ ግዙፍ ነገር ባለይዞታ የሆነ ሰው በራሱ ስም እንደያዘውና የዚሁ ነገር ባለቤት/ባለሀብት/ እንደሆነ ይገመታል ሲል ሕጉ በ/ፍ/ብ/ሕ/ቁ 1193 ደንግጓል፡፡ በዚህ ድንጋጌ መሠረት ተራ ተንቀሳቃሽ (Ordinary Corporeal chattels) ባለቤትነት እጅ በማድረግ (በመያዝ) ብቻ ባለቤት ይኮናል፡፡ ሆኖም ሕጉ በልዩ ሁኔታ ልዩ ተንቀሳቃሽ ንብረት በመባል የሚጠሩትን መኪናን የመሰሉትን የምዝገባ መስፈርቶች በልዩ አዋጅ በማስቀመጡ ንብረቱን በእጅ ከማድረግ ባለፈ ካልተመዘገበ የባለቤትነት መብት አያስገኝም፡፡ ሁለተኛው የባለቤትነት ማረጋገጫ የማይንቀሳቀስ ንብረትን የሚመለከት ሲሆን በአስተዳደር ክፍል ባለቤትነቱ ታውቆና ተመዝግቦለት የባለሀብትነት የምስክር ወረቀት የተሰጠው ሰው /ተቋም የንብረቱ ባለቤት ይሆናል፡፡

ንዋያተ ቅድሳትን በተመለከተ (በቅዱስ ሜሮን ያልከበሩትን) የተለየ ሕግ ባለመኖሩ ልዩ ተንቀሳቃሽ ንብረት በሚለው የማይወድቁና የምዝገባ ሥርዓት ያልተመዘገበላቸው ናቸው፡፡ ስለዚህ እነዚህ ዕቃዎች ከገበያው በሽያጭና በስጦታ የሚገኙና የገዛቸው ሰው ባለሀብት (ባለቤት) የሚሆንባቸው በመሆኑ ሁሉም ቤተ-እምነት የዕቃዎቹ ባለቤት የመሆን እድላቸው የተዘጋ አይደለም ማለት ነው፡፡ በዚህ መነሻነት ቤተክርስቲያን የራሷን ንዋያት መጠበቅ፣ ሌላው እንዳይጠቀም የማድረግ መብት ያላት ንዋያተ ቅድሳቱ በእጇ ገብተው እየተጠቀመችባቸው ካሉ ብቻ ይሆናል፡፡

ሁለተኛው ለመብት አጠባበቅ መሠረት የሚሆነው ስለቅርስ አጠባበቅ የወጣው አዋጅ ቁጥር 209 /1992 ዓ.ም ነው፡፡ በዚህ አዋጅ ትርጓሜ መሠረት “ንዋየ ቅድሳት” በአንቀጽ 2(6) “ግዙፍነት ያለው ቅርስ ” በሚለው ምድብ ይወድቃሉ፡፡ ግዙፍነት ያለው ቅርስ ማለት በእጅ የሚዳሰሱ፣ በዓይን የሚታዩ የሚንቀሳቀሱና የማይንቀሳቀሱ ባህላዊና ታሪካዊ ወይም ሰው ሠራሽ ቅርሶችን ይጨምራል፡፡ “የማይንቀሳቀስ ቅርስ” ውስጥ የብራና ጽሑፍ ከወርቅ ፣ ከብር፣ ከነሐስ፣ ወይም ከብረት ወይም ከመዳብ ከሌሎች ንጥረ ነገሮች ከእንጨት፣ ከድንጋይ፣ ከቆዳ፣ ከዝሆን ጥርስ፣ ከቀንድ፣ ከአጥንትና ከአፈር ወይም ከሌሎች ነገሮች የተሰሩ ቅርሶችና ምስሎች ይገኙበታል፡፡ በዚህ ብያኔ መሠረት የቤተክርስቲያን ንዋያተ ቅድሳት የሚንቀሳቀሱ ቅርሶች ናቸው፡፡ በዚህ አዋጅ አንቀጽ 14 መሠረት ቤተ ክርስቲያን የንዋያተ ቅድሳቶቿ ባለቤት መሆን የምትችል ሲሆን ንዋያተ ቅድሳቱ በቅርስ ጥበቃ ባለሥልጣን ተመዝግበው የሕግ ጥበቃ ይሰጣቸዋል፡፡ ቤተክርስቲያን በዚህ አዋጅ መሠረት ያስመዘገበቻቸው ቅርሶች ከመሠረታዊ ዓላማቸው፣ ከታሪካዊ አመጣጣቸውና ሊሰጣቸው ከሚገባው ክብር ዝቅ የሚያደርጉ ተግባራትን ለቅርስ ባለሥልጣን ሪፖርት በማድረግ የንዋያተ ቅድሳቱን አጠቃቀም ጥበቃ እንዲደረግ ለመጠየቅ ትችላለች፡፡

የመስቀል በዓል አከባበር በዓለም ቅርስነት የመመዝገቡ እውነታ ደግሞ ለቤተክርስቲያኗ ተጨማሪ ጥበቃ እንደሚ ያስገኝላት ይታሰባል፡፡ የመስቀል በዓል ምዝገባ ባህላዊና ሃይማ ኖታዊ ሥርዓቶችን አካትቶ የተመዘገበ በመሆኑ ሃይማኖታዊ በሆኑት መጠን ቤተክርስቲያኗ ከምዝገባው መብት ታገኛለች፡፡ ንዋያተ ቅድሳቱ (አለባበሱ፣ ዝማሬው፣ ንዋያተ ቅድሳቱና ውሕደታቸው) በምዝገባው መሠረት በተመሳሳይና በወጥነት ሳይበረዙ እንዲተላለፉ የማድረግ መብት አላት፡፡ ይህ መብት ሥርዓቱን እንዳመጣበት እንዳይቀጥል የማድረግ ውጤት ያላቸውን የአለባበስ፣ የዝማሬ፣ ወይም የንዋያተ ቅድሳት አጠቃቀም እንዲከላከል ለኢትዮጵያ መንግሥት ወይም ለዩኔስኮ እስከማቅረብ እንደሚደርስ መረዳት ይችላል፡፡

ሦስተኛው ለመብት ጥበቃው መሠረት የሚሆነው የቅጅና ተዛማጅ መብቶች ጥበቃ አዋጅ ቁጥር 410/1996 ዓ.ም ነው፡፡ በዚህ አዋጅ መሠረት ንዋያተ ቅድሳቱ በራሳቸው ተለይተው ሳይሆን ከዝማሬ፣ አቋቋም፣ ቅዳሴ ወ.ዘተ ጋር ተዋሕደው ሕጉ ጥበቃ ሊያደርግላቸው ይችላል፡፡ ለምሳሌ ከበሮ፣ መቋሚያ፣ ጸናጽል ከዜማው ጋር በቅኔ ማኅሌት የሚደረገው ክንውን (Performance) መብት ጥበቃ ሊያገኝ ይችላል፡፡ በዚህ አዋጅ መሠረት ጥበቃ ለማግኘት የዜማ ሥራው ወጥ (Original) እንዲሁም የተቀረጸ ወይም ግዙፍነት ያገኘ ሊሆን ይገባዋል፡፡ ይህም ማለት ሥራው ለሕዝብ የቀረበ ወይም የታተመ መሆን አለበት፡፡ በዚህ ረገድ ቤተክርስቲያን ያሉዋትን የንዋያተ ቅድሳት አጠቃቀም በተመለከተ በሚወጡ ቪዲዮዎች፣ ለሕዝብ ሲቀርብ፣ ተቀርጾ ሲተላለፍ ወዘተ ሌሎች በታየው /በቀረበው/ በታተመው መሠረት የንዋያተ ቅድሳቱን ውሕደት እንዳይጠቀሙ የመከላከል መብት ይኖራታል፡፡ ይህ መብት በአብያተ ክርስቲያናቱ ወይም በግለሰብ አማኞች (ማኅበራት፣ ግለሰብ ዘማርያን ወዘተ) ሊጠየቅ ይችላል፡፡

ከላይ በመግቢያው እንደገለጽኩት ሁለተኛው የመብት ምንጭ ውል ሲሆን በሃይማኖት ተቋማት ስለአምልኮ አፈፃፀም፣ ስለአማኞች ስርቆት (Sheep stealing)፣ አንዱ የሌላውን የአምልኮ መፈጸሚያ፣ የአምልኮ ዕቃን ስለመጠቀም አለመጠቀም፤ የጋራ የሆኑ ጉዳዮች ላይ በአንድነት ስለመሥራት የተደረገ ስምምነት ካለ ይህ ገዥ መሆኑ አይቀርም፡፡ እንደሚ ታወቀው በክርስትና ስም ያሉ ቤተ-እምነቶች የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ኅብረት አባል በመሆናቸው እርስ በርሳቸው ባላቸው ግንኙነት አንዱ ሌላውን የሚጎዳ ድርጊት እንዲሠራ የማይፈቅዱበት ሁኔታ ይኖራል፡፡ እምነት በልብ የሚታመን ብቻ ሳይሆን በአፍ የሚነገር በድርጊት የሚገለጥ ነው፡፡ አለባበስ፣ ዝማሬ፣፣ በተለያዩ ንዋያተ ቅድሳት በመጠቀም አምልኮ መፈፀም የእምነቱ አካል ነው፡፡ አንዱ ቤተ እምነት የሌላውን ፈቃድ ሳያገኝ ለዘመናት ሲጠቀምበት የነበረውን የአምልኮ መፈፀሚያ የሚጠቀም ከሆነ በኅብረት የመኖራቸው ነገር ትርጉም ያጣል፡፡ አንዱ የሌላውን የሆነውን ሀብት፣ ትውፊት ያለፈቃድ የሚወስድ ከሆነ አብያተ ክርስቲያናቱ በጋራ የገቡትን ውል ወይም ስምምነት መጣስ ነው፡፡ ይህ መብቱ የተጣሰበት ቤተ-እምነት ስምምነቱን መሠረት በማድረግ መብቱ እንዲከበርለት የመጠየቅ መብት ይኖረዋል ማለት ነው፡፡ ሙሉ/ ስምምነቱ በአብያተ ክርስቲያናቱ መካከል እንደ ሕግ ስለሚቆጠር መብቱ ለተጣሰበት ቤተ እምነት መፈጸሙ መፍትሔ /Remedy/ እንደሚሆን ማሰብ ይቻላል፡፡

እስካሁን የተመለከትነው ከንብረት መብትና ከቅርስ አንጻር ያለውን የመብትና ግዴታ አተያይ ነው፡፡ አንዱ ቤተእምነት አምልኮውን ከሚፈጽምበት መጠቀሚያ አንጻር መብቱ የሚሰጠው ስለመሆኑ ነው፡፡ በሌላ በኩል ግን በቤተ እምነቶች መካከል አምልኮን ከመፈጸሚያ ዕቃ (መሣሪያ) አንጻር የሚነሱ አለመግባባቶችም ከእምነት ነጻነትና ከሕዝብ ደኅንነት አንጻር ሊታይ ይችላል፡፡ አንዱ ቤተእምነት የሌላውን ቤተእምነት ሀብት ወይም የአምልኮ መሣሪያ መጠቀሙ ለዘመናት ሲጠቀምበት የነበረውን የቤተ እምነት ተከታዮች ቅር የሚያሰኝ ወይም ቁጣ የሚያስነሳ ሊሆን ይችላል፡፡ እንዲህ ዓይነት ጉዳዮች በእኛ ሀገር የሕግ ሥርዓት መፍትሔ የሚያገኙት ደግሞ የእምነት ነፃነትን ጥበቃ የሚሰጠው ሕገ መንግሥቱ ወይም ከሕዝብ ደኅንነትና ሰላም መጠበቅ በወጣው የወንጀል ሕጉ ነው፡፡ በዚህ ረገድ ሁለቱን ሕግጋት ከተነሳንበት አንፃር መፈተሸ ተገቢ ይሆናል የሚል እምነት አለኝ፡፡

የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 27(1) “የሃይማኖት፣ የእምነትና የአመለካከት ነፃነት በሚል ርዕስ” ማንኛውም ሰው የማሰብ የሕሊና እና የሃይማኖት ነፃነት አለው፡፡ ይህ መብት ማንኛውም ሰው የመረጠውን ሃይማኖት ወይም እምነት የመያዝ ወይም የመቀበል ሃይማኖቱንና እምነቱን ለብቻ ወይም ከሌሎች ጋር በመሆን በይፋ ወይም በግል የማምለክ የመከተል የመተግበር፣ የማስተማር ወይም የመግለጽ መብትን ያካትታል» ሲል ይደነግጋል፡፡

ይህ ሕገመንግሥታዊ ድንጋጌ ለሃይማኖት ነፃነት ዋስትና የሚሰጥ ቢሆንም የሃይማኖት ነፃነት ገደብ የለውም ማለት አይደለም” የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 27(5) “ሃይማኖትንና እምነትን የመግለጽ መብት ሊገደብ የሚቻለው የሕዝብን ደኅንነት፣ ሰላምን፣ ጤናን፣ ትምህርትን፣ የሕዝብን የሞራል ሁኔታ፣ የሌሎች ዜጎችን መሠረታዊ መብቶችና ነፃነቶች እና መንግሥት ከሃይማኖት ነፃ መሆኑን ለማረጋገጥ በሚመጡ ሕጎች ይሆናል” በማለት ደንግጓል፡፡ በዚህ ድንጋጌ መሠረት የሚገደበው የሃይ ማኖት መብት / የመረጡትን እምነት መያዝ ሳይሆን አገላለጹ ነው፡፡ የእምነት /አመለካከት/ መብት ፍጹማዊ በመሆኑ አይገደብም፣ መገደብም አይቻልም፡፡ ሃይማኖትን የመግለጽ መብት ለሕዝብ ሰላምና ደኅንነት ሲባል ገደብ ሊጣልበት ይችላል፡፡ የአንድ እምነት የአምልኮ ሥርዓቶች ኅብረተሰቡን የሚረብሹ፣ የሕዝብን ሥርዓትና ደኅንነት የሚያናጉ፣ በኅብረተሰቡ ሕይወት፣ ህልውና እና ንብረት ላይ ከባድ አደጋ የሚያደርሱ ሆነው ከተገኙ መንግሥት ሕግ ማውጣት እና ገደቡም በአግባቡ እንዲመራ በማድረግ ገደብ ሊጥል ይችላል፡፡

በቤተ እምነት መካከል የሚታየው የአንዱን የአምልኮ መፈፀሚያ መሳሪያ ሌላው ያለፈቃዱ የመጠቀሙንም ነገር እኔ የማየው ከእምነት አገላለጽ ነው፡፡ አንዱ ቤተእምነት ለዘመናት ሲዘምርበት፣ ሲያመሰግንበት የቆየበትን ሥርዓት እና የአገልግሎት መጠቀሚያ ሌላው ሲጠቀም በአማኞቹ መካከል አለመግባበት ይከሰታል፡፡ እምነቱ በኅሊና ብቻ ያለ ሳይሆን አማኙ የሚለብሰውም፣ የሚዘምረውም፣ የሚጠቀምበትን የንዋያተ ቅድሳት ዓይነት የሚያካትት ነው፡፡ ስለዚህ የራሱ ባልሆነው የተጠቀመው ቤተ እምነት የሌላውን ቤተእምነት መብት የሚነካ ነው፡፡ እንዲህ ባለ ጊዜ ታሪክን፣ የቤተ እምነቶቹን ሥርዓት፣ የዳበረ ልማድን መሠረት አድርጎ ክልከላ ካልተደረገበት ሥርዓት አልበኝነት ይነግሣል ለሕዝቡም ሰላምና ደኅንነት ስጋት መሆኑ አይቀርም፡፡ ስለዚህ መንግሥት በሕገ መንግሥቱ በግልጽ የተቀመጠውን የሃይማኖት ነፃነት ገደብን መሠረት በማድረግ ቤተእምነቶች መካከል የሚታየውን አንዱ አንዱን የማንቋሽሽ ድርጊት፣ የአንዱን ቤተእምነት የአምልኮ መጠቀሚያ ያለአግባብ መጠቀምን የመሰሉ በሕዝቡ ውስጥ ረብሻና ሁከት የመፍጠር አቅም ያላቸውን አሠራሮች መስመር ሊያስይዝ ይገባል፡፡ ይህ አካሄድ የሃይማኖት ብዙኅነትንም የሚያስቀር እና የአማኞችን ማንነት በማያሻማ መልኩ እንዲገለጽ የማያደርግ በመሆኑ የሕጉ ጣልቃ ገብነት አስፈላጊ ነው፡፡ በአንዳንድ ሀገራት እንኳን የሃይማኖት መገለጫው (የአምልኮ መሳሪያው) የቃላት አጠቃቀም እንኳን የሕግ ጥበቃ ይሰጠዋል፡፡ ቢቢሲ በድረገጹ እ.ኤ.አ ኦክቶበር 14 ቀን 2013 እንደዘገበው የማሌዥያ ፍርድ ቤት ከሙስሊም እምነት ውጭ ያሉ እምነቶች “አላህ” የሚለውን ቃል መጠቀም እንደማይችሉ ፍርድ ሰጥቷል፡፡ ለፍርዱ መነሻ የተደረገው አመክንዮ ቃሉ ከሙስሊም እምነት ውጭ ያሉ እምነቶች ጥቅም ላይ ቢውል ሕዝባዊ ሥርዓት አልበኝነት (Public disorder) ስለሚያስከትል ነው፡፡ ቴሌግራፍ የፍ/ቤቱን ተጨማሪ ምክንያት ሲገልጹ “The usage of the word will cause confusion in the community” በማለት ዘግቦታል፡፡ የዚህ ፍርድ የፍትሃዊነት ክርክር እንደተጠበቀ ሆኖ ከዚህ ፍርድ በመነሣት የተነሳንበትን ጉዳይ ከመረመርነው የአንዱን ቤተ እምነት የእምነት መፈጸሚያ ሥርዓትና መሳሪያዎች መጠቀም በኅብረተሰቡ ውስጥ የሚመጣውን መደናገርና በማንነት ፍለጋ (ጥበቃ) ሊከተል የሚችለውን ሁከት ማሰብ አስቸጋሪ አይሆንም፡፡

ሕገ መንግሥቱን መሠረት አድርጎ የወጣው የወንጀል ሕግም በተለይ በአደባባይ የሚፈጸሙ የሃይማኖት ሥርዓትን የሚያውክ፣ ወይም ያስተሃቀረን ሰው የሚቀጣ ድንጋጌ አለው፡፡ ሕጉ በአንቀጽ 792 “የሃይማኖት ሰላምና ስሜት መንካት በሚል ርዕስ” ማንም ሰው አስቦ በአደባባይ፡-

ሀ) የተፈቀደውን ሃይማኖታዊ ሥርዓት፣ ሥነ በዓል ወይም ሃይማኖታዊ ተግባር እንዳይፈፅም የከለከለ፣ ያወከ ወይም ያስተሐቀረ እንደሆነ፤ ወይም

ለ) ለሃይማኖታዊ ሥነሥርዓት ብቻ የሚያገለግለውን ቦታ፣ ሥዕል፣ ወይም ዕቃ ያረከሰ እንደሆነ

ከአንድ ሺሕ ብር በማይበልጥ መቀጮ ወይም ከሁለት ዓመት በማይበልጥ ቀላል እስራት ይቀጣል፡፡” ሲል ይደነግጋል፡፡

በዚህ ድንጋጌ መሠረት ‹‹ንዋየ ቅድሳት›› በ “ለ” ለሃይማኖት ሥነ ሥርዓት ብቻ የሚያገለግል ዕቃ” በሚል የሚሸፈኑ ሲሆን እነዚህን ዕቃዎች ‹ያረከሰ› በሕግ ተጠያቂ እንደሚሆን ይደነግጋል፡፡ ‹ያረከሰ› የሚለው ቃል ለዳኞች ትርጉም የተተወ ቢሆንም ከቃሉ ጥሬ ትርጉም ‹ከዓላማው ውጭ የተጠቀመ፣ ከእምነቱ ሥርዓት ያፈነገጠ ወ.ዘ.ተ» አጠቃቀም እንደሚመለከት መገንዘብ አከራካሪ አይሆንም፡፡ ለአብነት በክርስትና ቤተእምነቶች መካከል ያለውን የዶግማና የቀኖና ልዩነት ላስተዋለ ንዋየ ቅድሳቱን (ከበሮውን፣ ጸናጽልና መቋሚያውን› በታሪክ በትውፊት በቆየ ልማድ ከሚጠቀምበት ቤተ እምነት ዓላማ፣ ሥርዓትና አሠራር ውጭ መጠቀም ተገቢ አለመሆኑን መረዳት ይቻላል፡፡ ድርጊቱ በወንጀል ሕጉ የሚያስቀጣ ከሆነ ለማንኛውም ቤተ-እምነት ተከታይ የሌላውን ሥርዓት፣ ትውፊት እና አምልኮ መሣሪያ የመጠቀሚያ መብት እንደማይኖር መገንዘብ ይቻላል፡፡

ሐመር፡- ቤተ ክርስቲያኗ እንዴት የንዋየ ቅድሳቷን ይዞታ ታስከብር?

አቶ ጌታሁን ወርቁ፡- ከላይ እንደተመለከትነው የቤተክርስቲያን ንዋያተ ቅድሳት በሌሎች ቤተ-እምነቶች እየተጠቀሙ መቀጠል የራሱ የሆነ አሉታዊ ውጤት እንዳለው መገንዘብ ከባድ አይደለም፡፡ የቤተ እምነቷ መብት መነካት፣ አማኙ ወደ አልተፈለገ ሁከትና ክርክር መግባት፣ በቤተ እምነት መካከል የጥላቻ ስሜት መዳበር ወ.ዘ.ተ ያልተፈለጉ ውጤቶች ናቸው፡፡ ይህን ለማራቅ ቤተክርስቲያኗ የራሷን ንዋያተ ቅድሳት መጠበቅ አለባት፡፡ ከቤተክርስቲያኗ የሚጠበቀውን ለመመልከት ያህል ቢያንስ ሦስት መፍትሔዎች መጠቆም ይቻላል፡፡

የመጀመሪያው ቤተክርስቲያኗ የራሷን ንዋየ ቅድሳት መለየት፣ መቁጠርና መመዝገብ ነው፡፡ ንዋያት ቅድሳቱን በተመለከተ ታሪካቸውን፣ አመጣጣቸውን፣ ትርጉማቸውን ወ.ዘ.ተ በማጥናት የመለየትና ከመመዝገብ ጋር ትውፊታቸውን እንዲጠብቁ በመቅረጽ (በፎቶ፣ በቪዲዮ ወ.ዘ.ተ) ማተም እና ማሳወቅ ይጠበቅባታል፡፡ እነዚህን ድርጊቶች መከወኗ በአንድ በኩል በቅርስነት ለማስመዝገብ (በሀገር ውስጥም በዓለም አቀፍ ደረጃም) የሚጠቅማት ሲሆን በተጨማሪ በንብረት ሕግ፣ በቅጅና ተዛማጅ መብቶች ጥበቃ አዋጅ መብቷን ለመጠቀም ያስችላታል፡፡

ሁለተኛው መብት የመጠየቅ ሥራ ነው፡፡ ከላይ እንደተመ ለከትነው አንዳንዶቹ ሕግጋት ያለፈቃድ የሌላ ቤተእምነትን ሥርዓትና የአምልኮ መገልገያ እቃዎችን መጠቀምን በአንድም በሌላ ይከለክላሉ፡፡ እንዲህ ዓይነት ድርጊት የሚፈጽሙ ቤተ እምነቶችን በውይይት፣ ካልሆነም በዓለምአቀፍ የአብያተ ክርስቲያናት ኅብረት በኩል መጠየቅ የማይጎረብጥ መፍትሔ ነው፡፡ ከዚህ መፍትሔ ጎን ለጎን ቤተክርስቲያኗ እንደ አግባብነቱ መብቶቿን ከፖሊስ፣ ከመንግሥት (ከፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር)፣ ከኢትዮጵያ አእምሯዊ ንብረት ጽ/ቤት ወይም ከፍ/ቤት መጠየቅ ትችላለች፡፡

የመጨረሻው ቤተ ክርስቲያኗ ከመንግሥት ጋር በምታ ደርገው ትብብር የሚገኝ መፍትሔ ነው፡፡ ንዋየ ቅድሳትን በሌላ ቤተ እምነት የመጠቀም ድርጊት በዋናነት ሊቆም የሚችለው መንግሥት በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 27 (5) መሠረት የእምነት ነፃነት አገላለጽ ገደብን በሕግ ወይም በመመሪያ መደንገግ ሲችል ነው፡፡ ቤተክርስቲያኗ በቤተ እምነቶች መካከል በዜማ፣ በንዋየ ቅድሳት፣ ወ.ዘ.ተ ጋር በተያያዘ የሚደረጉ ገደቦች የሀገሪቱን ታሪክ፣ ለዘመናት በኅብረተሰቡና በቤተእምነቶቹ የዳበረውን ልማድ ትውፊትና መቻቻል መሠረት ማድረግ እንደሚገባው በመገንዘብ መንግሥት ገደቦቹን በተግባር እንዲተረጉማቸው መጠየቅ ይገባል፡፡ መመሪያውን ወይም ደንቡን ወይም ሕጉን የማውጣት ግዴታ በዋናነት የመንግሥት ቢሆንም ቤተክርስቲያኗ ሕጉ እንዲወጣ ግፊት ማድረግ፣ ከመንግሥትና ከቤተእምነቶች ጋር መተባበር ይጠበቅበታል፡፡ ይህ ግፊት “ሳይቃጠል በቅጠል” እንዲሉ በቀጣይ በስፋት ሊመጡ የሚችሉና የመቻቻልን መርህ የሚቃረኑ የቤተ- እምነት ድርጊቶች እንዳይኖሩ የራሱን አስተዋጽኦ ያደርጋል፡፡

ሐመር-የመዝሙር መገልገያ መሣሪያዎችን ጨምሮ ንዋየ ቅድሳት ከቅርስነት አንጻር ያላቸው ቦታና ጥቅም ምንድነው?

መንግሥቱ ጎበዜ፡- ቅርሶች የሰው ልጆች በየዘመናቸው መንፈሳዊ አእምሮአቸውን ለማርካት፣ መሠረታዊ ኑሯቸውን ለማሟላትና ሥነ ልቦናዊ ፍላጎቶቻቸውን ለማሳካት ሲሉ ለረጅም ዘመናት ከአካባ ቢያቸው ጋር በነበራቸው ግንኙነት ያከናወ ኗቸው የሥራና የፈጠራ ውጤቶች ናቸው፡፡ ከእነዚህም መካከል ለሥርዓተ አምልኮ መፈጸሚያ ይጠቀሙባቸው የነበሩ ክቡር ዕቃዎች በዋናነት ይጠቀሳሉ፡፡ እነዚህም የከበሩና ውድ ሀብቶች ባላቸው ታሪካዊና ባህላዊ ጠቀሜታ፣ ሥነ ጥበባዊ ይዘት፣ ያላቸው ፋይዳ፣ ምልክታዊነትና ናሙናነ ታቸው እንዲሁም ዕድሜያቸው ታይቶ ቅርስ ተብለው ለመጠራትና ለመታወቅ የሚችሉት ናቸው፡፡

ከዚህ አንጻር የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት፣ መምህራንና ምእመናን በየዘርፉ ሠርተውና ጠብቀው ለትውልድ ያስተላለፏቸው ቅርሶች በዓይነትም በብዛትም የትየለሌ ናቸው፡፡ ከእነዚህም መካከል የያሬዳዊ መዝሙር መሣሪያዎች ይጠቀሳሉ፡፡ ቤተ ክርስቲያኗ ለዘመናት ጠብቃ ያቆየቻቸው እነዚህ ቅርሶች ሥርዓተ አምልኮን በሚገባ ለማከናወን፣ ትምህርተ ሃይማኖትን ለማስተላለፍ፣ መንፈሳዊ በረከት ለማግኘትና ለመሳሰሉት ሃይማኖታዊ አገልግሎት የሚውሉ ናቸው፡፡

ከመንፈሳዊ አገልግሎት ሌላ በቤተ ክርስቲያን የሚገኙ ቅርሶች የታሪክ ምስክር፣ የመረጃ ምንጭ፣ የማንነት መገለጫ፣ ዘርፈ ብዙ ዕውቀት የሚሰጡ ትምህርት ቤቶች፣ የልማት መሠረትና የምጣኔ ሀብት የጀርባ አጥንት፣ ዘመናትን የሚያተሳስሩ ድልድዮች፣ የሩቁን አቅርበው የራቀውን አጉልተው የሚያሳዩ መነጽሮች፣ የራስን ማንነት የሚያሳዩ መስታወቶች፣ በተገቢው ሁኔታ ለመኖር የሚያስችሉ የጥበብ መንገዶች፣ የአገርን መልካም ገጽታ ለመገንባት የሚያግዙ የዲፕሎማሲ አውታሮች፣ በመረጃ ላይ ውሳኔ ለመስጠት የሚያስችሉ ጠቃሚ ሰነዶች እና የሀገር አንድነት ግንባታ የማኅበረሰብ ትስስር መሠረቶች ናቸው፡፡

ሐመር-አንዱ ቤተእምነት የሌላውን ንዋየ ቅድሳት ለአገልግሎቱ መጠቀሙ እንደ ራሱ አድርጎ በአደባባይ የመጠቀሙ ልማድ ከቅርስ ጥበቃ አንጻር የሚያስከትላቸው ችግሮች ካሉ ቢያመለክቱን

መንግሥቱ ጎበዜ፡- በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክርስቲያን ቅርሶች ዙሪያ በርካታ ችግሮች የሚታዩ ሲሆን ከእነዚህም መካከል በቅርስ ባለቤትነትና የይዞታ መብት ላይ ከሌሎች አካላት ጋር የሚያወዛግብና የቤተ ክርስቲያን ቅርሶች ይጠቀሳሉ፡፡ ከዚህ አንጻር የብራ መጻሕፍትና ለአክብሮተ ቁርባን የሚውሉ ንዋያተ ቅድሳት በሌሎች የእምነት ተቋማት አገልግሎት ሲሰጡ ይስተዋላሉ፡፡ በመሠረቱ የቤተ ክርስቲያን ቅርሶች ከቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ፣ ሥርዓተ እምነትና ትውፊት ጋር ከፍተኛና ቀጥተኛ የሆነ ቁርኝት ስላላቸው በሌሎች ቦታ አገልግሎት ላይ መዋላቸው አግባብ ነው ብዬ አላምንም፡፡ ይህ ሁኔታ በሂደት ቤተ ክርስቲያኗን የባለቤትነት መብቷንና መለያ ምልክቶቿን ሊያሳጣት ይችላል የሚል ስጋት አለኝ፡፡ ጉዳዩ በዚህ ከቀጠለ በእምነት ላይም ግራ መጋባት ሊፈጥር ይችላል፡፡ በመሰረቱ የሌላውን ንብረት ሳያስፈቅዱ መውሰድ መጠቀም ከሥርቆት ተለይቶ አይታይም፡፡

ሐመር- ችግሮች አሉ ካልን መወሰድ ያለባቸው መፍት ሔዎች ምንድናቸው?

መንግሥቱ ጎበዜ፡- የኢ/አ/ተ/ቤ/ክርስቲያን የቅርሶች ባለቤነት መብቷን ለማስከበር በርካታ ሥራዎችን መሥራት ይጠበቅባታል፡፡ ከሁሉ በፊት ግን ቅርሶቿ አሁን ያሉበትን አጠቃላይ ሁኔታ ማጥናትና ለአያያዝ፣ ለቆጠራ፣ ለዕይታ፣ በሚመች መንገድ መገኘታቸውን መለየት ይኖርባታል፡፡ ቅርሶችን በዓይነት፣ በቦታ፣ በይዘት፣ በዕድሜና በመሳሰሉት መስፈርቶች መዝግቦ በመያዝ ለቆጠራ፣ ለቁጥጥርና ለአስተዳደር ሥራ አመቺ እንዲሆኑ ማድረግ ይቻላል፡፡ ቅርሶችን በአግባቡ መዝግቦ የትና በምን ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ ለይቶ ማወቅም ከዝርፊያ፣ ከአያያዝ ጉድለቶች የሚፈጠሩ ችግሮችን ለመቅረፍ ትልቅ አስተዋጽኦ ይኖረዋል፡፡ ከዚህ ሌላ ዘመናዊ የምስል ወድምፅ ክምችት ሥርዓት እና አገልግሎት መዘርጋት ቅርሶቹ ተለይተው እንዲታወቁ፣ ሕጋዊ ጥበቃ እንዲደረግላቸውና ተገቢውን እንክብካቤ ለማግኘት ይረዳል፡፡ ከዚህ ሌላ ቤተ ክርስቲያኗ በቅርሶች ጥበቃ ዙሪያ ጠንካራ መመሪያዎችን፣ ደንቦችንና ፖሊሲዎችን ቀርጻና ተቋማትን አጠናክራ መንቀሳቀስ ይጠበቅበታል፡፡

እነዚህና የመሳሰሉ ተግባራት ከተከናወኑ በኋላ የቅርሶቿን የባለቤትነትና የይዞታ መብት ለማስከበር አስፈላጊ የሆነውን ሕጋዊ ክትትልና እርምጃ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ተባብራ ማስኬድ ትችላለች የሚል እምነት አለኝ፡፡

No comments:

Post a Comment