Friday, 3 January 2014

እነሆ የጌታ ልደት ደረሰ

ከታምራት ፍሰሃ
ፌስቡክ ገጽ ላይ የተወሰደ

እነሆ የጌታ ልደት ደረሰ ፡ የጭፈራ ጊዜም ደረሰ ፡ የዳንስና የእስክስታ የመጠጥና የዝሙት ጊዜም ደረሰ። ኦርቶዶክሳዊት ቤተክርስቲያን የጌታዋን ልደት ድምጿን ከፍ አድርጋ ታውጃለች ፤ የዚህ አለም ገዢ ዲያቢሎስ ደግሞ ይህን ቅዱስ ጥሪ ማንም እንዳይሰማው ይህን አለም በልዩ ጩኸት በክሎታል ፤ ጭኸቱንም በሚዲያዎች በኩል ያደርጋል። “እንኳን ለጌታ ልደት አደረሳችሁ” ይሉናል። ቀጠል አድርገውም “እዚህ ክለብ ብትሄዱ ለገና ልዩ ዝግጅት ተዘጋጅቷል ፡ ጭፈራው ዘፈኑ ሌላ ነው ፡ መጠጡ ምግቡ ልዩ ነው ፡ ሆይታው ሞቅታው ልዩ ነው ፡ ኑ ና ጌታችሁን እያሳዘናችሁ የዲያቢሎስን ፈቃድ ፈፅሙ” ሲሉ በጥበብ እንሰማቸዋለን፤ በጌታችን ልደት ሰይጣን የሚከብርበት ፡ በክርስቲያኖች ልደት ዲያቢሎስ የሚደምቅበት ፡ በመድሃኒት ክርስቶስ መገለጥ ፡ የዚህ አለም ገዢ ሃሳዊው መሲህ የሚታይበት ይህ ዘመን እንደምን ክፉ ነው?

እነሆ የጌታ ልደት ደረሰ ፡ ቡና ቤቶችም ሰውን ለማስከር ተዘጋጁ። ዘማውያንም አይኖቻቸውን ተኳሉ ፡ ዘፋኞችም ፡ ዳንሰኞችም ፡ አጃቢዎችም ሁሉ ቀኗን በናፍቆት ጠበቋት ፡ ሚድያዎችም ዘፈን ሊጋብዙ ዝግጅታቸውን ጨረሱ፤ ጌታችንስ በዚህ ጨለማ ላይ ብርሃኑን ሊያበራ ተገለጠ። ዲያቢሎስ ግን ከእንስሳ በላይ ሊሆን የተጠራውን ክቡር ሰው ከብርሃኑ ይልቅ ጨለማውን መርጦ ለጨለማው እንዲተባበር ሊያደርገው ይጥራል ፤ እንግዲህ የዚህ አለም ገዥ ባለሟሎች ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋራ ምን ህብረት አላቸው? የዲያቢሎስ ተልእኮ አስፈፃሚወች ከጌታችን ከክርስቶስ ጋር ምን ህብረት አላቸው? በጌታ ቀን ጌታ እንዲያዝን ያደርጉታል። በክርስቲያኖች ቀን ክርስቲያኖችን ያስከፋሉ ፡ ለአለም በሚያበራው በእውነተኛ ብርሃን ምትክ የዚህን አለም ጨለማ ብርሃን አድርገው አድምቀው በሁሉ ፊት ያጎሉታል ፡፡ ለዚህ ደግሞ ከሚዲያዎች የበለጠ ታላቅ መሳሪያ ዲያቢሎስ አላገኘም፡፡

ነገር ግን በጌታ ቀን ጌታ የሚወደውን ቢያደርጉ እንደምን በጎ ነበር? ድሆችን ቢያስቡ ፡ የተራቡትን ቢያበሉ ፡ በጎወችን ቢያነቃቁ እንደምን በጎ ነበር? ድሆች እንዲረዱ ህዝቡን ሁሉ ቢያስተባብሩ ፡ የጎዳና ልጆች ምሳ እንዲያገኙ ቢደክሙ ፡ በየመንደሩ ያሉ ኦርቶዶክሳውያን ወጣቶች እንዴት ድሃን እየረዱ እንዳሉ ቢያሳዩ ፡ የታክሲ ሹፌሮች ተባብረው ጤፍ ፡ ስንዴ ፡ ስኳር ወዘተ እየገዙ ለድሃ እንደሚያከፋፍሉ ቢዘግቡ ፡ የሰፈር ወጣቶች ህብረት ፈጥረው ከጥቂት ገቢያቸው ላይ እየቀነሱ በየወሩ የተቸገሩትን እንደሚረዱ ቢናገሩ እንዴት መልካም ነበር? ለአድራጊወቹ አነቃቂ ፡ ለሚሰሙትም በጎ አርአያ በሆነ ነበር ፡ ዲያቢሎስም ባዘነ ፡ ክርስቶስም ደስ በተሰኝ ነበር ፡ ገናም ይህ ነበር ፡ የጌታም መምጣት ስለዚህ በጎነት ነበር፡፡ ነገር ግን በክርስቲያኖች ቀን ክርስቲያኖችን ያሳዝናሉ ፡ አንድም ክርስቲያኖችን አለማዊ ለማድረግ ይደክማሉ፡፡

እነሆ የጌታ ልደት ደረሰ ፡ አለም ግን ይህን እንዳታይ አይኗ ታውሯልና በጨለማው ዲያቢሎስ ልታጌጥ ትዘጋጃለች፡፡

እኛ ግን የተሰቀለውን ክርስቶስን እንሰብካለን፡፡

No comments:

Post a Comment