Friday, 24 January 2014

ፓትርያርኩ: የቤተ ክርስቲያኒቷ የመዋቅር ለውጥ ሕግ ረቂቅ ‹‹የእኔ ጩኸት ነው›› አሉ

ለአደረጃጀትና አሠራር ለውጥ የሚሰማው የካህናቱና ምእመናኑ ጩኸት በርክቷል

(ፋክት መጽሔት፤ ቅጽ ፪ ቁጥር ፳፱ ጥር ፳፻፮ ዓ.ም.)

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በአስተዳደራዊ መዋቅሯ ትክክለኛውን መሥመር ይዛ ወደ ቀደመ የቅድስናና ንጽሕና ክብሯ እንድትመለስ በአደረጃጀትዋና አሠራሯ ላይ እየተካሔደ የሚገኘው የተቋማዊ ለውጥ ጥናት፣ ‹‹ከጅምሩም የእኔ ጩኸት ነው፤ የእኔ አጀንዳ ነው፤ ዛሬ ከደረሰበትም ወደ ኋላ አይመለስም፤›› ሲሉ ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ ቃል ገቡ፡፡

ፓትርያርኩ ይህን የተናገሩት፣ የአዲስ አበባ ሀ/ስብከት የአደረጃጀትና አሠራር ለውጥ ጥናት ሳይዘገይ ተግባራዊ እንዲኾን ጥያቄ ያቀረቡ የገዳማትና አድባራት አስተዳዳሪዎችን፣ የጽ/ቤት ሠራተኞችን፣ ካህናትን፣ መምህራንና ምእመናንን ጥር 2ና 5 ቀን 2006 ዓ.ም. በጽ/ቤታቸውና በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት አዳራሽ ተቀብለው ባነጋገሩበት ወቅት ነው፡፡
ከሌሎች አህጉረ ስብከት በተለየ ኹኔታ የበርካታ ገዳማትና አድባራት፣ የብዙ ንዋያተ ቅድሳትና ቅርሶች፣ የሰው ኃይልና ፋይናንስ ሀብቶች የሚገኝበት የዐዲስ አበባ ሀ/ስብከት÷ በአስተዳደር መዋቅሩ፣ በሒሳብ አሠራርና ቁጥጥሩ መሠረታዊውን ክህነታዊና የስብከተ ወንጌል ተልእኮ በሚደግፍ አኳኋን ሥር ነቀል ለውጥ እንዲካሔድበት በባለሞያዎች የቀረበውና በተለያዩ ዙሮች የተወያዩበት የአደረጃጀትና አሠራር ለውጥ ጥናት የቤተ ክርስቲያኒቱን ብሩህ የልማትና የመልካም አስተዳደር ትንሣኤ ያሳያቸው መኾኑን ካህናቱና ምእመናኑ በከፍተኛ ስሜት ገልጸዋል፡፡

ካህናቱና ምእመናኑ፣ የአደረጃጀትና አሠራር ለውጥ ጥናቱ የቅ/ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ በሰጠው የአፈጻጸም አቅጣጫ መሠረት በውይይቱ በተሰበሰቡት አስተያየቶችና ትችቶች ታርሞና ተስተካክሎ በቋሚ ሲኖዶሱ በአስቸኳይ እንዲጸድቅ፣ በተሳካና በተሟላ መንገድ ተግባራዊ ለማድረግና ዘለቄታዊነቱም ለማረጋገጥ ይቻል ዘንድም ከአስተዳደር ሠራተኞች፣ ከካህናት፣ ከሰንበት ት/ቤቶችና ከምእመናን የተውጣጣ የተቋማዊ ለውጥ አስፈጻሚ አካል እንዲቋቋም ጠይቀዋል፡፡

በሀ/ስብከቱ የፓትርያርኩ ረዳት ሊቀ ጳጳስ ኾነው በተሾሙትና የአደረጃጀትና የአሠራር ለውጥ ጥናቱን ለማስፈጸም እየሠሩና እየደከሙ ባሉት ብፁዕ አቡነ እስጢፋኖስ ላይ የሥነ ምግባር ጉድለትና ጠባየ ብልሹነት ይታይባቸዋል ባሏቸው ‹‹ውስን ጎጠኛና ሙሰኛ አስተዳዳሪዎችና ጸሐፊዎች›› የሚካሔድባቸው የስም ማጥፋት ዘመቻና ውንጀላ ከሥርዐተ ቤተ ክርስቲያን ውጭና ተቀባይነት የሌለው መኾኑን በመግለጽ ቅ/ሲኖዶሱ በአዋኪዎችና መዝባሪዎች ላይ ሕጋዊና የሥነ ሥርዐት ርምጃዎች በመውሰድ የአባቶችን ክብር፣ የቤተ ክርስቲያኒቱን መብትና ጥቅሞች የሚያስጠብቅ ጠበቅ ያለ ሕግ እንዲያወጣም አመልክተዋል፡፡

ፓትርያርኩ በብዙ መቶዎች ለሚቆጠሩ የአስተዳደር ሓላፊዎችና ሠራተኞች፣ ካህናትና ምእመናን ጥያቄ በሰጡት ምላሽ÷ ለቤተ ክርስቲያኒቱ ዕድገት፣ አንድነትና ጥቅም በሚሠሩና በሚደክሙ በብፁዓን አባቶች ላይ በተቃዋሚዎች የሚሰነዘረው የስም ማጥፋት ዘመቻና ውንጀላ አግባብነት የሌለውና ማንንም የማይጠቅም መኾኑን በመጥቀስ በግብረ ገብነት፣ በቤተ ክርስቲያን ልጅነትና በሰከነ አእምሮ ሐሳብንና ልዩነትን መግለጽ እንደሚገባ መክረዋል፡፡ የአስተዳደር ሓላፊዎቹና ሠራተኞቹ፣ ካህናቱና ምእመናኑ በአደረጃጀትና አሠራር ለውጥ ጥናቱ ዕጣ ፈንታ ላይ ያላቸውን ስጋትና ጥያቄ በርጋታ በማቅረባቸውም ምስጋናቸውን ገልጸውላቸዋል፡፡

‹‹ገና ከመግባቴ[ከበዓለ ሢመታቸው ቀን ጀምሮ] ሙስናና የገንዘብ ብክነት እንዲጠፋ ሓላፊነትና ተጠያቂነት ያለበት አስተዳደር እንዲሰፍን ብዬ የተናገርኹትን ታስታውሳላችኹ›› በማለት ንግግራቸውን የጀመሩት ፓትርያርኩ የተጀመረው የአደረጃጀትና የአሠራር ለውጥ ጥናት አኹን ከደረሰበት ወደኋላ የሚመለስበት ምንም ምክንያት እንደማይኖረው ገልጸዋል፡፡ የጥናት ሰነዱ ከቤተ ክርስቲያኒቱ ባህልና ቋንቋ አንጻር የሚገመግመው፣ የዘመኑ ምሁራንና ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ያሉበት ኮሚቴ መሠየሙን አቡነ ማትያስ አስታውቀዋል፡፡

የኮሚቴው ግምገማ ወጣም ወረደ መጨረሻው ለቅ/ሲኖዶስ እንደሚቀርብ ፓትርያርኩ ጠቁመው፣ ኮሚቴው የጥናት ሰነዱን የበለጠ አጠናክሮ እንጂ አዳክሞ ያመጣዋል የሚል እምነት እንደሌላቸው፣ ተዳክሞ ከመጣም ሐቋንና እውነቷን በመያዝ እንደማይቀበሉት በአጽንዖት ተናግረዋል፡፡ ፍላጎታቸው ቤተ ክርስቲያኒቱ ትክክለኛ መሥመሯን እንድትይዝ መኾኑን ሲገልጹም ‹‹ይኼ ወደኋላ ይመለሳል ብላችኹ የምትጠራጠሩ ከኾነ እንዴ! ጩኸቴን ቀሙኝ ሊኾን ነውኮ፤ ጩኸቱኮ የእኔ ነው በመጀመሪያ፤ እንዲኹ በቀልድ አይደለም፤ በውነቱ ከዚኽ ደርሰን ወደኋላ እንመለሳለን ማለት ዘበት ነው፤ በጭራሽ አይሞከርም፤ ኹሉም ከዚኽም ከዚያም ይምጣ፤ ኹሉም የሚናገረውን አዳምጣለኹ፤ ኹሉም የሚናገረውን እያስተናገድኹ ግን ከእውነተኛ የቤተ ክርስቲያኒቱ ጥቅም ግን ወዲያና ወዲኽ አልልም፤›› በማለት ነበር፡፡

No comments:

Post a Comment