Monday, 13 January 2014

አርባ አራቱ ታቦት የሚለው ታሪክ መነሻው ምንድን ነው ?

እውን ታቦት አርባ አራት ብቻ ? 
(ከኦርቶዶክስ እና መጽሃፍ ቅዱስ)

መግቢያ ጎንደር በኢትዮጵያ የመንግሥት ታሪክ ከአክሱምና ላሊበላ ቀጥሎ ትልቋ የመንግሥት ማዕከል ነበረች፡፡ በመንግሥት ማዕከልነት የተቆረቆረችው በአፄ ፋሲል (1624-1660 ዓ.ም) ነው፡፡ ጎንደር የመንግሥት ማዕከል ብቻ ሳትሆን በጊዜው የመንፈሳዊ ትምህርት ማዕከልም ነበረች፡፡ በኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን የመጻሕፍት እና የአቋቋም ትምህርት ይበልጥ የተስፋፋውና በየሀገሩ ያሉ ሊቃውንት በመናገሻ ከተማዋ ጎንደር በነገሥታቱ አማካይነት በመሰባሰባቸው ሲሆን ከዚያን ዘመን ጀምሮ እስከዛሬ ድረስ መንፈሳዊ ትምህርት በስፋት የሚሰጥባት የትምህርት ማዕከል ለመሆን ችላለች፡፡

በአሁኑ ሰዓት በሰሜን ጎንደር በሚገኙ 21 ወረዳዎች ከ2117 ያላነሱ ገዳማትና አብያተ ክርስቲያናት ሲኖሩ በዋና ከተማዋ ደግሞ ከ92 ያላነሱ አብያተ ክርስቲያናት ይገኛሉ፡፡ በአብነት ት/ቤት ረገድም የመጻሕፍት ጉባዔያት፣ የአቋቋም ምስክር፣ የቅኔ አብያተ ጉባዔያት እንዲሁም የዜማ ት/ቤቶች በከተማዋ እና በዙሪያዋ በሚገኙ ወረዳዎች ይገኛሉ፡፡ በአሁኑ ሰዓት በከተማዋ ከ92 ያላነሱ አብያተ ክርስቲያናት ቢኖሩም በአብዛኛው ስማቸው ደጋግሞ የሚነሳው የ44ቱ ብቻ ነው፡፡ በተለያየ ጊዜ በተለይም ጎንደርን ከማያውቁት ሰዎች ጋር ባደረኩት ውይይት 44ቱን ታቦታተ ጎንደርን በተመለከተ የተለያየ ግንዛቤ እንዳለ ለመገንዘብ ችያለሁ፡፡ አንዳንዶቹ በመላው ኢትዮጵያ የሚገኙት የአብያተ ክርስቲያናት ታቦታት ስያሜ ብዛት ሲመስላቸው ሌሎቹ ደግሞ በጎንደር በጥምቀት በዓል ወደጥምቀተ ባህር የሚወርዱትን ብቻ ስሉ ይደመጣሉ፡፡ ጎንደር ከተማ እየኖሩም የ44ቱን ዝርዝር በውል የማያውቁ ብዙ ሰዎች ገጥመውኛል፡፡ አርባ አራቱ ታቦታተ ጎንደር ከቤተ መንግሥቶቹ በተጨማሪ ታሪካዊዋ ጎንደር የምትታወቅበት ቅርስ ነው፡፡ ጎንደር ከተማ በአፄ ፋሲል የመንግሥት ከተማ ከመሆኗ አስቀድሞ የአካባቢው ነዋሪዎች ተክለዋቸው የነበሩ አብያተ ክርስቲያናት ነበሩ፡፡ ለምሳሌ ቀሐ ኢየሱስ፣ አርባዕቱ እንስሳ፣ አበራ ጊዮርጊስ፡፡ 

ጎንደር የመንግሥት ከተማ ከሆነችበት እስከ ጎንደር ዘመን ማክተሚያ ፈፃሜ መንግሥት አፄ ተክለ ጊዮርጊስ (1772-1777) ድረስ 18 ነገሥታት የነገሱ ሲሆን እነዚህም አብዛኛዎቹ አብያተ ክርስቲያናትን አሠርተዋል፡፡ እንግዲህ 44 የሚባሉት አብያተ ክርስቲያናት ጎንደር የመንግሥት ከተማ ከመሆኗ አስቀድሞ የተተከሉበትን ጨምሮ እስከ ፈፃሜ መንግሥት ተክለ ጊዮርጊስ (1772-1777) ድረስ የተተከሉትን ብቻ ሲሆን ቁጥራቸውም 44 ነው፡፡ ከዚያ ወዲህ ከዘመነ መሣፍንት እስከ አሁን የተተከሉ በርካታ አብያተ ክርስቲያናት ቢኖሩም ከ44ቱ የሚቆጠሩ አይደሉም፡፡ በአጠቃላይ አርባአራቱ ታቦታተ ጎንደር በጎንደር ዘመን በጎንደር ከተማና አካባቢው የሚገኙና የነበሩ 44 አብያተ ክርስቲያናት ጥቅል ስም ነው፡፡ ስለዚህ አርባ አራቱ ታቦት ሲባል ይህን ታሪክ ተከትሎ የመጣ ስያሜ እንጂ በ ቤተክርስትያናችን ቁጥር ስፍር የሌላቸው ታቦታት ነው ያሉት! ምክንያቱም ሁልጊዜም አዲስ ቤተ ክርስቲያን በሚሰራበት ጊዜ ታቦት ከእጽ ወይም ከእብነ በረድ ተቀርጾ በላዩ " ኢየሱስ ክርስቶስ አልፋ ኦሜጋ " ተብሎ ይጻፍበታል! የመጀመሪያውና የመጨረሻው ማለት ነው ፡፡ ይህ ቃል ከተጻፈበት በኋላ በኤፒስ ቆጶሱ እጅ ተባርኮና ሜሮን ተቀብቶ በመንበሩ ይሰየማል (ይቀመጣል) ፣በቅዳሴም ጊዜ ሕብስቱና ወይኑ ወደ ቤተ መቅደስ ሲገባ ቄሱ ሥርዓተ ቅዳሴውን የሚያከናውነው ሕብስቱን ሥጋ መለኮት ፣ ወይኑን ደመ መለኮት ወደ መሆን የሚለውጠው በዚህ በታቦቱ ላይ ነው ፡፡ሥጋዬን ብሉ ደሜንም ጠጡ እያለ ያመኑትን ሁሉ የሚጠራበት የምሕረት ምሥዋዕ (መሠዊ) ነው ፡፡ ታቦት በ ሐዲስ ኪዳን እውነተኛው የሕይወት ምግብ የክርስቶስ ሥጋና ደም የሚቀርብበትና የሚፈተትበት መሠዊያ ነው ፡፡

ስለዚህ በአርባ አራት ቁጥር ብቻ የሚወሰን ሳይሆን እልፍ አዕላፍ መሆኑን ልብ ልንል ይገባል! "ለሚጠይቃቹ ጥያቄ ሁሉ እንዴት መልስ መመለስ እንዳለባቹ ታውቁ ዘንድ ንግግራቹ ሁል ግዜ በጨው እንደተቀመመ በፀጋ ይሁን" ቆላስይስ 4:6 በሚቀጥለው.... 

*ተቃዋሚዎች ታቦት አያስፈልግም ለማለት የሚጠቅሱት ጥቅሶች እና የቤተክርስትያን የማያዳግም ምላሽ!

No comments:

Post a Comment