በአያሌው ዘኢየሱስ
ዓለም ያሏት ፈተናዎች ብቻ እንጂ ምንም የሚወደድ ነገር ስለሌላት ከእርሷ ምንም አልፈልግም።
ዓለም ለመስጠት በጣም ድሀ ስለሆነ ከእርሷ ምንም አልፈልግም። እኔ የምፈልገው ሁሉ በዓለም ካለ ዓለም ገነት ሆናለች ማለት ነው። በውስጧም ከቁሳዊ ነገሮች በስተቀር ምንም የለም። በእርግጥ እኔ የምፈልገው ሰማያዊ ነገሮችን ነው። ለመንፈሳዊ ህይወቴ እንዲጠቅመኝ።
እኔ ከዓለም አይደለሁምና ከዓለም ምንም አልፈልግም። እንደሚገምቱኝ ትቢያ አይደለሁም፡ መለኮታዊ እስትንፋስ እንጂ። ቀድሞ በዘላለም ህይወት ከእግዚአብሔር ጋር እኖር ነበር። በዚህች ምድር ላይ ያስቀመጠኝ እርሱ እግዚአብሔር ነው። ከጥቂት ጊዜያት በኋላ ትቼያት ወደ እግዚአብሔርእመለሳለሁ። ስለዚህ ከዚህች ዓለም ምንም አልፈልግም። "ከአብ ወጥቼ ወደ ዓለም መጥቻለሁ፤ ደግሞ ዓለምን እተዋለሁ፤ ወደ አብም እሄዳለሁ።" ዮሐ 16፥28
ከዓለም ምንም አልፈልግም፤ የምፈልገውንም እተዋለሁ። የምፈልገው ከዓለሙ ከሥጋና ከምድራዊ ነገሮች ሁሉ ነጻ መውጣትን ነው። እንደ ቀድሞው ወደ እግዚአብሔር ተመልሼ የአፉ እስትንፋስ በመሆን ምንም ዓይነት ነገር የማያጠፋኝ መሆንን ነው የምሻው።
እኔ የምፈልገው ህያውና ዘላለማዊ ነገሮችን ሲሆን ዓለም ግን ይህ የላትም። ስለዚህ ከዓለም ምንም አልፈልግም። በዓለም ያለው ብቻ ሳይሆን ዓለም ራሷ ታልፋለችና የሚያልፍ ነገር አልፈልግም።
ብጠይቀው ሁሉን የሚሰጠኝ እርሱ እግዚአብሔር አለኝና ከዓለም ምንም አልፈልግም። እርሱ ሁሉ አለው ኃያልም ነው። ከእርሱ ጠይቄ የማጣው ስለሌለኝ በእርሱ ደስ ይለኛል። የምፈልገውን ሁሉ ሳልጠይቀው ይሰጠኛል። የሚሰጠኝም መልካሙንና የሚጠቅመኝን ነው። በእርሱ እጅ ላ ነኝና ከዓለም ምንም የምሻው ነገር የለኝም።
ዓለም የምትሰጠኝ የሚጠቅመኝን ሳይሆን የሚያጠፋኝን ስለሆነ ከዓለም ምንም አልፈልግም። ዓለም የሰጠቻቸውን የተቀበሉ ሁሉ የዓለም ባሮች ናቸው። ሥጋዊ ደስታን ሰጥታ የነፍስ ቅድስና ወስዳባቸዋለች። ምድራዊውንም ተድላ ሰጥታ የሰማያዊውን መንግስት ቡራኬ ነጥቃቸዋለች። ዲያብሎስ የዚህን ዓለም መንግስታትና ክብራቸውንም ሁሉ ሰጥቷቸው ወድቀው እንዲሰግዱለትና እንዲያመልኩት አድርጓቸዋል። ሰዎች ነፍሳቸውን እንዲያጎድሉ ዲያብሎስ ምን ጊዜም ያለውን ሁሉ ይሰጣቸዋል። ለእኔ ግን "...በእውነት ከሁሉ ይልቅ ስለሚበልጥ ስለ ክርስቶስ ኢየሱስ ስለ ጌታዬ እውቀት ነገር ሁሉ ጉዳት እንዲሆን እቆጥራለሁ።" ፊል 3፥8
ይህ ዓለም ከሚሰጠው ይልቅ የሚወስደው እጅግ የሚበልጠውን ነው። ይህን የሚፈልጉትንም ስለሚያጠቃቸው ከዓለም ምንም አልፈልግም።
እኔ ከዓለም በላይ ነኝና ከዓለም ምንም አልፈልግም። እኔ በእግዚአብሔር መልክና ምሳሌ የተፈጠርኩ የእግዚአብሔር ልጅ ነኝ። እኔ የመንፈስ ቅዱስ ቤተ መቅደስና የእግዚአብሔር ማደሪያ ነኝ። የእርሱን ቅዱስ ሥጋና ደም እንድቀበል የተፈቀደልኝ ብቸኛ ፍጥረት ነኝ። ስለዚህ እኔ ከዓለም ስለምበልጥ ዓለም ከእኔ ይፈልጋል እንጂ እኔ ከዓለም አልፈልግም። እኔ የሰማይና የምድር ቁልፍ አለኝ። እግዚአብሔር አምላክ እኔን በፍጹም ፍቅርና ትህትና የዓለም ብርሃንና የምድር ጨው ነህ አለኝ። ማቴ 5፥13-14
የቀደሙት አባቶች እንደኖሩት መኖር ስለምፈልግ ከዓለም ምንም አልፈልግም። ምድር እነርሱ ይረግጧት ዘንድ አትፈልግም ነበር። በዚህ መልኩ እነርሱ ከዓለም ምንም ሳይፈልጉና ሳይቀበሉ ኖሩ። ይሁን እንጂ ለዓለሙ ሁሉ በረከት ነበሩ። ስለ እነርሱ ጸሎትና ልመና እግዚአብሔር ለምድር ውኃን ሰጠ።ዓለሙንም እስከ ዛሬ ከጥፋት ታደገ።
ኃጥያት ወደ ዓለም ገብቶ በክሎታልና ከዓለም ምንም አልፈልግም። ኃጥያት ወደ አለም ከመግባቱ አስቀሞ እግዚአብሔር አምላክ የፈጠረው ሁሉ እጅግ መልካም ነበር (ዘፍ 1፥31)። አሁን ግን ያ እግዚአብሔር የተመለከተው እጅግ መልካም ነገር ሁሉ ረክሷል። ስለዚህ ከብርሃን ይልቅ ጨለማን ከምትመርጠው ከዚህች ክፉ ዓለም ምንም አልፈልግም።
እኔ የምፈልገው አንተንብቻ ስለሆነ ከዓለም ምንም አልፈልግም። አንተ እስከመጨረሻው ስለወደድከኝ ራስህን ለእኔ አሳልፈህ ሰጥተኸኛል። አንተ ካለ መኖር ወደ መኖር አምጥተህ ከባርነት ይልቅ በነጻነት እንድኖር አድርገኸኛልና የምፈልገው አንተን ነው። ስለዚህ ከዓለሙ ነጻ ሆኜ አንተን ለማወቅ እውቀትን ከሰጠኸኝ ከአንተ ጋር መኖርን እፈልጋለሁ።
(የግብጽ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ሺኖዳ 3ኛ ከጻፉት "የነፍስ አርነት" መጽሃፍ የተወሰደ።)
No comments:
Post a Comment