የስድስተኛው ፓትርያሪክ አስመራጭ ኮሚቴ፣ ካህናትና ምእመናን ቀጣዩ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አባት ሊኾን ይገባል ያሉትን እንዲጠቁሙ ባስተላለፈው ጥሪ መሠረት ከተበሰበሰቡት በሺሕዎች ከሚቆጠሩ ካህናትና ምእመናን ጥቆማዎች መካከል፣ የልማትና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ሳሙኤል እጅግ ከፍተኛውን የጠቋሚዎች ቁጥር በማግኘት በከፍተኛ ብልጫ መምራታቸውን ለምርጫው ሂደት ቅርበት ያላቸው ምንጮቸ ገለጹ፡፡
ከየካቲት 1 - 8 ቀን 2005 ዓ.ም በተሰበሰበውና ከቅዳሜ የካቲት 9 ቀን ጀምሮ እየተካሄደ በሚገኘው አግባብነት ያላቸው ጥቆማዎች ቆጠራ ከአንደኛው እስከ ሦስተኛ የወጡ አባቶች ማንነት ተለይቷል፡፡ በዚህም መሠረት ካህኑንና ምእመኑን በስፋት ለማሳተፍ በተሰበሰበው ጥቆማ ብፁዕ አቡነ ሳሙኤል በእጅግ ከፍተኛ የጠቋሚዎች ቁጥር የመጀመሪያውን ደረጃ በመያዝ መምራታቸው ተረጋግጧል፡፡ በሁለተኛ ደረጃ ብፁዕ አቡነ ገብርኤል፣በሦስተኛ ደረጃ ደግሞ ብፁዕ አቡነ ማቴዎስ የከፍተኛ ጠቋሚዎችን ቁጥር ማግኘታቸው ተገልጧል፡፡
ኮሚቴው በጠቋሚዎቻቸው ብዛት አራተኛና አምስተኛ ደረጃ ያገኙትን የተቀሩትን ሁለት አባቶች ማንነት በነገው ዕለት በሚያካሂደው ቆጠራ እንደሚያውቃቸው ይጠበቃል፡፡ የጥቆማውን ውጤቶችና ምልከታዎች እንደ ግብአት (popular vote?) በመያዝ በምርጫ ሕጉ በሰፈረው ድንጋጌ በተጨማሪ መመዘኛዎች ለቅዱስ ሲኖዶስ የሚያቀርባቸውን አምስት አባቶች የካቲት 14 ቀን እንደሚያቀርብ መገለጹ ይታወሳል፡፡ አሁን ሾልኮ የተሰማው የጥቆማ ደረጃ ውጤት፣ የተጠቀሱትን ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ከአምስቱ ዕጩዎች ለመካተት ያበቃቸው እንደኾነ ቆይተን የምናየው ይኾናል፡፡
የዜናው ዝርዝር ይቀጥላል፡፡
No comments:
Post a Comment