Thursday, 8 November 2012

ቀሲስ በላይ መኰንን ከሰዋስወ ብርሃን ቅ/ጳውሎስ መንፈሳዊ ኮሌጅ ዋና ዲንነት ተነሡ


(ደጀ ሰላም ጥቅምት 29/2005 ዓ.ም፤ ኖቬምበር 8/2012/ READ THIS NEWS IN PDF)፦ ባለፉት የዜና ዘገባዎቻችን ስንጠቅሳቸው የነበሩትና በሰዋስወ ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ መንፈሳዊ ኮሌጅ ዋና ዲን የነበሩት ቀሲስ በላይ መኰንን ከዚህ ሓላፊነታቸው መነሣታቸው ታውቋል፡፡ የደጀ ሰላም ምንጮች እንደሚገልጹት ከሆነ በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት ሰሞኑን በሚደረገው የከፍተኛ ሓላፊዎች ሽግሽግ ቀሲስ በላይ መኰንን የሕግ አገልግሎት መምሪያ ሓላፊው አማካሪ ኾነው መመደባቸውን እየተነገረ ነው፡፡ በርካታ ዋና ዲኖች በፍጥነት በሚቀያየሩበትና የከፍተኛ ትምህርት ተቋም ሳይሆን የመቅጫ ቦታ ተደርጎ በሚታሰበው መንፈሳዊ ኮሌጅ ለስድስት ወራት የቆዩት ቀሲስ በላይ በጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ውሳኔ ከሓላፊነታቸው መነሣታቸው የታወቀው “በእድሳትና ለዲግሪ መርሐ ግብር መጀመር ይደረጋል በተባለው ዝግጅት” ሰበብ የመንፈሳዊ ኮሌጁ የመማር ማስተማር ሂደት ከሁለት ወራት በላይ በተስተጓጎለበት፣ ይህንንም ተከትሎ የደቀ መዛሙርቱ (በተለይም የሰሚናር ኮርሰኞቹ) አቤቱታ ጎልቶ በሚሰማበት ኹኔታ ውስጥ ነው፡፡

በቀደመው ዘገባችን ባስነበብነው ሐተታ የኮሌጁ ሥርዐተ ትምህርት የስድሳ ዓመት ዕድሜ ያስቆጠረ ነው መባሉን የሚቃወሙ የተቋሙ ምንጮች እስከ አራት ጊዜ ያህል መሻሻሉንና የደቀ መዛሙርቱ ተቃውሞ የሥርዐተ ትምህርትን ምንነት ከመረዳት ጀምሮ የግንዛቤ ችግር እንዳለበት ያስረዳሉ፡፡ የደቀ መዛሙርቱን ጤንነት በተመለከተ ከቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ጋራ ቋሚ የሕክምና አገልግሎት ውል መኖሩንና አገልግሎቱም እየተሰጠ መኾኑን፤ በምግብ፣ በመኝታ አገልግሎት እና በወር ለኪስ የሚሰጠውን ሠላሳ ብር ጨምሮ የተጠቆመው ችግር አለ ብለው እንደማያምኑ ይልቁንም ችግሩ የመማር ማስተማሩ ሥነ ዘዴ ንባብና ጽሕፈትን በማጣመር ጠንከር ብሎ መሰጠቱ የማይወድላቸው ጥቂት ደቀ መዛሙርት÷ “በትውልድ ማንነት በመቧደን እና በማደም በተለይ በአስተዳደር ላይ ከተቀመጡ ሰዎች የትውልድ ማንነት ጋራ በሚቃረን አኳኋን በየሰበብ አስባቡ የሚፈጥሯቸው መጠላለፎች እና ተንኮሎች ናቸው” ይላሉ፡፡
አንድ ሰው መርጦ የማይወለድበትን የትውልድ ማንነት የጠብና ክፍፍል መንሥኤ የማድረግ ጎጠኝነት እና ‹ፖለቲከኝነት› በዋና ዲኑ በቀሲስ በላይ ላይም እንደሚታይ ምንጮቹ ይመሰክራሉ፡፡ የቡድን ጥቅምን ከማሳደድ፣ ኦርቶዶክሳዊነትን ከማዋረድ፣ የመናፍቃን ተልእኮን በውስጥ አርበኝነት ከማስፈጸም ጋራ በተያያዘ በቅዱስ ሲኖዶስ ሳይቀር ጉዳያቸው ለታዩትና በዚህ የጡመራ መድረክ ስማቸው ደጋግሞ ከሚነሣ ግለሰቦች ጋራ በተያያዘ ቀሲስ በላይ ባላቸው የሕግ ሙያና ፖለቲካዊ ትስስር ዋነኛው አጋር፣ ሽፋን ሰጪ ኾነው መቀጠላቸውን በቁጭት ይናገራሉ፡፡
በዕሥራ ምእቱ በዓል አከባበር የቀድሞው ፓትርያርክ አቡነ ጳውሎስ “ሰማዕት ዘእንበለ ደም” በተባሉበት መድረክ አባ ገዳው ያበረከቱላቸውንና በሺሕዎች ተመልካቾቻቸው ፊት ያከናነቧቸውን የቡልኮ ሸማ ስጦታ መቀበላቸው ብዙዎች ቅዱስነታቸው ለእምነቶች መከባበር እና መቻቻል እንደሚሠሩ ለማስረዳት ታላቅ አጋጣሚ አድርገው እንደሚጠቅሱላቸው ለ80 ቀን መታሰቢያቸው ከወጣውና የሐዘንተኞች አስተያየት ሰፍሮበት ከነበረው መዝገብ ተመልክተናል፡፡ የአባ ገዳውን ስጦታ ክዋኔ ከኋላ ላስተባበሩት ቀሲስ በላይ ግን ያ አጋጣሚ “ተመልከቱ÷ አባ ጳውሎስን ቡልኮ አስለበስኳቸው!” በሚል ተሣልቆ የተወጠነ እንደነበር በራሳቸው ቃል እያስካኩ ሲናገሩ ያደመጧቸው ምንጮች ያስታውሳሉ፡፡
በምንጮቹ አስተያየት የአንዱን ስጦታ የሌላው መቀለጃ ያደረጉት ቀሲስ በላይ የራሳቸው መተዳደሪያ ሥራ ይዘው ሲያበቁ የቤተ ክርስቲያኒቱን አገልግሎት መንሸራሸሪያና የጥቅም ትስስር መፍጠሪያ በማድረጋቸው ጠ/ቤ/ክህነቱ ከተቋማዊ ለውጥ ግስጋሴው ጋራ ሊራመዱ የማይችሉትን ግለሰብአስተዳደራዊ ሓላፊነት ላይ ከማስቀመጥ ቢታቀብ መልካም እንደነበር ያወሳሉ፡፡

No comments:

Post a Comment