(ደጀ ሰላም ጥቅምት 29/2005 ዓ.ም፤ ኖቬምበር 8/2012/ READ THIS NEWS IN PDF)፦ በቅዱስ ሲኖዶስ የተቋቋመው ኮሚቴ በአዲስ አበባ ሀ/ስብከት የገነገነውን ሙስናና ሌሎችም የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመፍታት ያቀረበውን ጥናት የመረመረው የጥቅምት ቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ሀገረ ስብከቱ በአራት አህጉረ ስብከት ተከፍሎ እንዲደራጅ መወሰኑን መዘገባችን ይታወሳል፡፡ ስለ አከፋፈሉ እና አደረጃጀቱ መነሻ “አቤት ባዩ በዛ፤ ጩኽት በዝቷልና” በማለት የምልአተ ጉባኤውን ውሳኔ ለጋዜጠኞች ያስረዱት የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ ብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤል÷ ሁሉም አጥቢያ አብያተ ክርስቲያን በየአካባቢያቸው እንዲስተናገዱ በፓትርያርኩ ጊዜ በአባቶችና ሊቃውንት ተጠንቶ ቀጠሮ ተይዞበት የቆየ ጉዳይ እንደነበር ተናግረዋል፡፡
በአራቱ ዐበይት ማእዝናት ለተደራጁት አህጉረ ስብከት ምልአተ ጉባኤው ብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤልን ለምሥራቅ እና ሰሜን አዲስ አበባ አህጉረ ስብከት፣ ብፁዕ አቡነ ዳንኤልን ለምዕራብ እና ደቡብ አህጉረ ስብከት መመደቡን መዘገባችንም ይታወሳል፡፡ ከዚሁ ጋራ በተያያዘ ምልአተ ጉባኤው “የሥራ አስኪያጅነት ልምድና ዕውቀት አላቸው” የተባሉ አምስት ዕጩዎችን በማወዳደር ሦስት አዳዲስ ሓላፊዎችን ለሥራ አስኪያጅነት መርጧል፡፡ በቀደሙት ዘገባዎቻችን በተደጋጋሚ እንዳመለከትነው ጉዳያቸው እልባት ያላገኘውንና በሂደት የሚታየውን ንቡረ እድ ኤልያስ ኣብርሃን በአራተኛነት በሥራ አስኪያጅነት ሾሟል፡፡
በዚህም መሠረት ብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤል በሊቀ ጳጳስነት በሚመሩት ምሥራቅ አዲስ አበባ ሀ/ስብከት የመ/ፓ/ጠ/ቤ/ክ የስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልእኮ መምሪያ ምክትል ሓላፊ የነበሩት ሊቀ ኅሩያን ሠርጸ አበበ፣ በሰሜን አዲስ አበባ ሀ/ስብከት ንቡረ እድ ኤልያስ ኣብርሃ በሥራ አስኪያጅነት ተሹመዋል፡፡ ብፁዕ አቡነ ዳንኤል በሊቀ ጳጳስነት በሚመሩት የምዕራብ አዲስ አበባ ሀ/ስብከት የቀድሞው የሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ዋና ሓላፊ የነበሩትና በኋላም ወደ መንፈሳዊ ፍ/ቤት የተዛወሩት መልአከ ጽዮን አባ ኅሩይ ማንደፍሮ፣ የቀድሞው የአዲስ አበባ ሀ/ስብከት የካህናት አስተዳደር ክፍል ሓላፊ የነበሩት ንቡረ እድ አባ ዮሐንስ ገብረ ማርያም በደቡብ አዲስ አበባ ሀገረ ስብከት በሥራ አስኪያጅነት ተሹመዋል፡፡
በ1991 ዓ.ም የወጣውና በሥራ ላይ በሚገኘው ሕገ ቤተ ክርስቲያን አንቀጽ 35 ንኡስ አንቀጽ 3 እና አንቀጽ 36 መሠረት የሁሉም አህጉረ ስብከት ማእከል የኾነው የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ቅዱስ ሲኖዶስ በሚያወጣው ልዩ ደንብና መመሪያ መሠረት ቅዱስ ሲኖዶሱ በሚሠይመው የአስተዳደር ዓቢይ ኮሚቴ እንደሚመራ ይደነግጋል፡፡ በድንጋጌው መሠረት የዓቢይ ኮሚቴው ተጠሪነት ለቋሚ ሲኖዶሱ ሲሆን ከቅ/ሲኖዶስ ሦስት፣ ከጠቅላይ ቤተ ክህነት ሦስት እና ከአዲስ አበባ ሦስት በድምሩ ዘጠኝ አባላት እንደሚኖሩት፣ የአገልግሎት ዘመኑም ለሦስት ዓመት እንደሚኾን ተመልክቷል፡፡ ይህ ድንጋጌ ሳይሠራበት እንደ ቆየ የሚተቹት የጉዳዩ ተከታታዮች ምልአተ ጉባኤው ሀ/ስብከቱን በአራት ከመከፋፈል ይልቅ ድንጋጌውን ተግባር ላይ በማዋል፣ የወረዳ ቤተ ክህነቶችን አቅም በማጎልበት፣ የአድባራትና ገዳማት አለቆችን ተጠያቂነት ከፍ በማድረግ ሀ/ስብከቱን እንደ አንድ አጠናክሮ ለመምራት ይቻል የነበረበትን አማራጭ በመጥቀስ በአዲሱ አደረጃጀት የተሾሙት ሥራ አስኪያጆች ግልጽነትንና ተጠያቂነትን እስካላሰፈኑ ድረስ በቀድሞው ሙሰኛ አስተዳደር የተዘረጋው የጥቅም ሰንሰለት (ኔት ወርኪንግ) የመጠለፋቸውን አይቀሬነት በመጠቆም ያሳስባሉ፡፡
የ31ኛው የመንበረ ፓትርያርክ አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ከሀ/ስብከቱ በቀረበለት የዕቅድ ክንውን ሪፖርት ላይ በወሰደው ግንዛቤ÷ በአዲስ አበባ ተጨባጭ ኹኔታ ገዳማትና አድባራት ከፍተኛ የሀብት ክምችት ያለባቸው የብዙ ባለሀብትና ንብረት ባለቤቶች ከመኾናቸው የተነሣ በቃለ ዐዋዲው ሕግና መምሪያ ተደግፎ በታማኝነት ከተሠራ በሀ/ስብከቱ በሁሉም የሥራ ዘርፎች ተኣምር መፍጠር እንደሚቻል ታምኖበታል፡፡ ለዚህም የቅጥር፣ ዕድገት፣ ዝውውር አሠራሩ ከጎጠኝነት እና ከጉቦኝነት በማጽዳት በመንፈሳዊነት እና ሙያዊ ብቃት ላይ የተመሠረተ ማድረግ፤ የሰበካ ጉባኤ በቃለ ዐዋዲው መሠረት መደራጀትና የአባላት አስተዋፅኦ በትክክል መክፈል፤ የሒሳብ ምርመራን በጊዜውና በትክክል ማካሄድ፤ የፐርሰንት ገቢው በየደረጃው በቅጽ ተሞልቶ በጊዜው ማቅረብ እንደሚገባ ተመልክቷል፡፡ በሀ/ስብከቱ 63 አብያተ ክርስቲያን ለዕጣን አዙር ጭምር 120 የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ ማግኘታቸው ለአጠቃላይ ጉባኤው ብሥራት ቢሆንም በሰንበቴ እና ቀብር ቤት ስም የግል መጠቃቀሚያ መኾኑ ተገትቶ ለቤተ ክርስቲያን ልማት እንዲሠራበት የአህጉረ ስብከት ጽ/ቤቶች ጥብቅ ቁጥጥር እንዲያደርጉ ገና ካርታ ያልተሰጣቸውም አብያተ ክርስቲያን እንዲሰጣቸው ጉባኤው አጥብቆ ጠይቋል፡፡
በተያዘው ዓመት ሀገረ ስብከቱ የያዛቸው ጥቅል ዕቅዶች ሲታዩ ከአድባራትና ገዳማት እንዲሁም ራሱ ከሚፈጥራቸው ገቢዎች ከብር 80 ሚልዮን በላይ ለመሰብሰብ ታቅዷል፤ ከሀ/ስብከቱ እስከ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ድረስ በቋሚና ጊዜያዊነት ተቀጥረው የሚሠሩ ሠራተኞችና እንዲሁም ምእመናን ዳታ በመሰብሰብ በሙያ፣ በአገልግሎት ዘመንና በሥራ አፈጻጸም የመለየትና የመተንተን፤ ገዳማቱና አድባራቱ በያዟቸው ቦታዎች በፕላን የተደገፈ የልማት ሥራ እንዲሠሩባቸውና ገቢያቸው ከፍ እንዲል አስፈላጊውን እገዛና ክትትል ማድረግ፤ የሙያ ማሻሻያ ሥልጠናዎች፤ በጸደቁ ሕጎች፣ ደንቦችና መመሪያዎች መሥራት እንዲቻል የጋራ ግንዛቤ ማስጨበጫ ወርክሾፖች፤ የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ ላላገኙ ገዳማትና አድባራት እንዲያገኙ ከፍተኛ ጥረት ይደረጋል፡፡ በአዲስ መልክ በመደራጀት ላይ የሚገኙት አራቱም የአህጉረ ስብከት ጽ/ቤቶች ከየራሳቸው ተጨባጭ ኹኔታ ጋራ አገናዝበው ለእኒህ ጥቅል ዕቅዶች ዝርዝር አፈጻጸሞችን በማስቀመጥና በተግባር በመፈጸም “በወር ሠላሳ ቀን ገንዘብ ላይ ነህ” የሚባልበትን የቀድሞውን ሀ/ስብከት መጥፎ ገጽታ በአርኣያነት የሚጠቀስ እንደሚያደርጉት ይጠበቃል፡፡
ቸር ወሬ ያሰማን፣
አሜን
No comments:
Post a Comment