Friday, 12 October 2012

የቃለ ዓዋዲው ማሻሻያ ረቂቅ ይመከርበት!


መስከረም 30 ቀን 2005

ሰበካ ጉባኤ በካህናትና በምእመናን ኅብረት ላይ የቆመ መሠረታዊ የቤተ ክርስቲያናችን አስተዳደራዊና መዋቅራዊ ሥርዐት ነው፡፡ ከመንበረ ፓትርያርክ እስከ አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት ባሉት መንፈሳዊና አስተዳደራዊ ጉዳዮች ላይ በየደረጃው አመራር ይሰጣል፣


ዕቅድ ያወጣል፣ ውሳኔ ያሳልፋል፡፡ ጉባኤው ቤተ ክርስቲያናችን ከመሬት ስሪት ተነሥታ በሕዝብ ባለቤትነት ላይ የተመሠረተችበትና ሕጋዊ ሰውነት ያገኘችበትም የሕግ አካል ነው፡፡

በየደረጃው በሚያወጣቸው ዕቅዶች፣ በሚሰጣቸው አመራርና በሚያሳልፋቸው ውሳኔዎቹ ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን ይጠብቃል፡፡ አገልግሎቷንም የተሟላ እንዲሆን ያደርጋል፡፡ የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮች በሐዋርያዊ ተግባር እንዲደራጁ በማድረግ ችሎታቸውን ተጠቅሞ ኑሮአቸውን ያሻሽላል፡፡ ምእመናንን ለማብዛትና በመንፈሳዊ ዕውቀት ጎልምሰው በምግባርና በሃይማኖት ጸንተው በክርስቲያናዊ ሕይወት እንዲኖሩ ያደርጋል፡፡

እነዚህን ዓላማዎቹን ከማስፈጸም አኳያ ጾታ ካህናትና ጾታ ምእመናን /ጳጳሳት፣ ቀሳውስት፣ ሊቃውንት፣ ወጣቶች/ በምልዐት የተወከሉበትም በመሆኑ አሳታፊ ነው፡፡

ይሁንና በአጥቢያ ሰበካ ጉባኤ ደረጃ የምእመናን ንቃተ ሕሊና እየዳበረ ቢሆንም ተሳትፎው በሚፈለገው ደረጃ እያደገ አይደለም፡፡ ሰበካ ጉባኤ በወረዳ ቤተ ክህነትና በመንበረ ጵጵስና አካባቢ የተረሳም ይመስላል፡፡ በየዓመቱ የመንበረ ፓትርያርክ አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ቢካሔድም፤ በጉባኤውም አልፎ አልፎ ሥልጠናዎች መስጠታቸው ቢበረታቱም ወደ መሬት የማይወርዱ ወደ ተግባር የማይለወጡ መሆናቸውን እንረዳለን፡፡

ዘንድሮም ከጥቅምት 6-11 ቀን 2005 ዓ.ም ጀምሮ ሠላሳ አንደኛው የመንበረ ፓትርያርክ አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ በጽርሐ መንበረ ፓትርያርክ ይካሔዳል፡፡ እናም ተገቢ /የካህናት፣ የወጣቶችና የምእመናን/ የውክልና ተሳትፎው እንዲጠበቅ፣ ከተለመደው ሪፖርታዊ መግለጫ በዘለለ ቁም ነገራዊ አጀንዳ ተኮር ቢሆን፤ አጀንዳዎቹ በወቅታዊና ዘላቂ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ያተኮሩ፣ አወያይና አሳታፊ ሊሆኑ ይገባል እንላለን፡፡

ከሪፖርት አቀራረብ ጋር በተያያዘም የአህጉረ ስብከት ሪፖርት በጠቅላይ ሥራ አስኪያጁ ተጠቃሎ ቢቀርብና የቁጥጥር አገልግሎት ሪፖርት ተጠያቂነትንና ግልጽነትን ከማስፈን አኳያ ራሱን ችሎና ለብቻው ተለይቶ ቢቀርብና ተገቢ የሆነ ውይይትም ሊደረግበት ይገባል፡፡

በዘንድሮው የመንበረ ፓትርያርክ አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ በቃለ ዐዋዲው ማሻሻያ ረቂቅ፣ ተቋማዊ ማሻሻያ (Structural Reform)፣ በዕርቀ ሰላሙ እውንነት ላይ፣ በፓትርያርክ ምርጫ አፈጻጸም ሥርዐት ላይ አተኩሮ እንዲወያይና የውሳኔ አሳብ ለቅዱስ ሲኖዶስ እንዲያሳልፍ ቢደረግ፤ ከአምስተኛው ፓትርያርክ ዕረፍት በኋላ ቤተ ክርስቲያኒቱ ያለችበትን ነባራዊ ሁኔታ የሚያሳይና በቀጣይነት ሊደረጉ የሚገባቸውን የሚጠቁም ሰነድ በዐቃቤ መንበሩ የሚመራው ኮሚቴ አዘጋጅቶ የጉባኤው ተሳታፊ እንዲወያይበት ሊደረግ ይገባል፡፡ ጉባኤው ዕቅድና በጀት መትከል ቢጀምር፣ የክትትልና ቁጥጥር ሥልትን አቅጣጫ ቢበይን ለቤተ ክርስቲያን ሁለንተናዊ ዕድገት ጠቃሚ መሆኑን እናምናለን፡፡

ሌላው ቢቀር እንኳን የቃለ ዓዋዲው ማሻሻያዎች ላይ የመንበረ ፓትርያርክ ሠላሳ አንደኛ አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ተሳታፊዎች እንዲመክሩበትና እንዲያዳብሩት ዕድሉ ሊሰጣቸው ይገባል፡፡

ይህን ስንል የቃለ ዓዋዲው መሻሻል የአሁኑንና የቀጣዩን ዘመን የቤተ ክርስቲያናችንን ሐዋርያዊ አገልግሎት፣ ርምጃ ለማስቀጠል የላቀ አዎንታዊ ተፅዕኖ ያለው መሆኑን በመገንዘብ ነው፡፡

በዚህ መልኩ የቃለ ዓዋዲው መሻሻል ተግባራዊ መሆን ለመዋቅር ማሻሻያችን መርሕ ይሆናል፤ የሕግ አውጪውን፣ ሕግ አስፈጻሚውንና የሕግ ተርጓሚውን ተግባር፣ ሥልጣንና ሓላፊነት በመለየት፡-

  • ተጠያቂነትና ግልጽነት እንዲሰፍን፣
  • የቤተ ክርስቲያናችን ሀብት /የሰው ኀይል፣ የገንዘብና ንብረት/ በአግባቡ ጥቅም ላይ እንዲውል፣
  • ቤተ ክርስቲያናችን በመንፈሳዊነት ምሳሌያዊ የሆነችና ሞራላዊ የበላይነት ያላት ተቋም እንድትሆን /በብኩንነት፣ ምዝበራና ዘረፋ ላይ/ ያስችላታል፡፡

በዓለም አቀፍም ደረጃ /በውጭው ዓለም/ ላለችው ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችንም የበለጠ የመስፋፋትና የአንድነት በርን ይከፍታል እንላለን፡፡

ስለዚህ የዘንድሮ የመንበረ ፓትርያርክ አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ በቃለ ዓዋዲው ማሻሻያ ላይ ለመምከር ባለቤትም፣ ባለሥልጣንም ነውና ይመለከተዋል፡፡ አሁን ባለንበት ሁኔታ ከዚህም የተለየ፣ ከዚህም የበለጠ አጀንዳ ሊኖረው አይገባም፡፡ ቢያንስ ቢያንስ በቃለ ዐዋዲው ማሻሻያዎች ላይ ይምከር! ማሻሻያዎቹን ያዳብር! እንላለን፡፡

  • ምንጭ፡- ስምዐ ጽድቅ ጋዜጣ 20ኛ ዓመት ቁጥር 2  ከጥቅምት 1-15 ቀን 2005 ዓ.ም.

No comments:

Post a Comment