Monday, 29 October 2012

የቅ/ሲኖዶስ የቅዳሜ ውሎና ውሳኔዎች፤ ስብሰባው አልተጠናቀቀም


ቤተ ክህነታችን ለመጀመሪያ ጊዜ የአጭር እና የመካከለኛ ጊዜ ስትራቴጂያዊ ዕቅድያዘጋጃል፤

ለአዳሪ እና አብነት ት/ቤቶች ማጠናከርያ 10 ሚልዮን ብር በጀት ተመድቧል፤

የካህናት ማሠልጠኛዎች በየክልሉ ይቋቋማሉ፤ በየቋንቋዎቹ የመጽሔቶችና ጋዜጦች ኅትመት ይጀመራል፤

የሥርዐተ ምንኵስና አፈጻጸም በየገዳማቱ ሕግ መሠረት ጠብቆ “ልማት እንዲጠናከርባቸው” ይደረጋል፤

የጋዜጠኛ መ/ር ካህሳይ ገብረ እግዚአብሔር “ብፁዓን እነማን ናቸው?” መጽሐፍ በሊቃውንት ጉባኤ ተመርምሮ የውሳኔ ሐሳብ እንዲቀርብበት ተወስኗል፤

የአቡነ ጳውሎስ “ንብረት” ተሰብስቦ ወደ ሙዝየም እንዲገባ ተወስኗል፡፡ ሐውልታቸውስ?

ብፁዕ አቡነ ፋኑኤል  የዋሽንግተን ዲሲና አካባቢው ሀ/ስብከት ጸሐፊ የኾኑትን ቀሲስ ዶ/ር መስፍን ተገኝን ከሥልጣነ ክህነት በማገድ የወሰዱት ርምጃ “በግል ጥላቻ የተገፋ ነው”ያለው ምልአተ ጉባኤው ካህኑም ሊቀ ጳጳሱም ለዕርቀ ሰላሙ በሚያመሩት ብፁዓን አባቶች አቀራራቢነት ተነጋግረው መፍትሔ እንዲሹ ትእዛዝ ሰጠ

በሕገ ወጡ የዋሽግተን ዲሲ የውጭ ጉዳይ ተጠሪ ጽ/ቤት ላይ አስቀድሞ የተላለፈው ውሳኔ ተፈጻሚ ኾኖ “የጽ/ቤቱ ባለሙሉ ሥልጣን” በሚል በአህጉረ ስብከቱ ሥራ አስኪያጅነት ተሹሞ የነበረው ኀይለ ጊዮርጊስ ጥላሁን በአቡነ ጳውሎስ ቀጥተኛ ትእዛዝ ከተሰጠው ሓላፊነት ተወግዶ በቃለ ዐዋዲው መሠረት አዲስ ሥራ አስኪያጅ እንዲሾም ተወስኗል

የአቡነ መቃርዮስ የኤርትራ ጉብኝት እንደማይወክላቸው በስደት የሚገኙት አባቶች ገለጹ፤

በድሬዳዋ ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን የተፈጸመውን ሙስናና የሀ/ስብከቱን የአስተዳደር ችግር የሚያጠራው የመ/ፓ/ጠ/ቤ/ክ ልኡክ ነገ ወደ ስፍራው ያመራል፡፡



(ደጀ ሰላም፤ ጥቅምት 19/2005 ዓ.ም፤ ኦክቶ. 29/2012)፦ ጥቅምት 12 ቀን የተጀመረው የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ቅዳሜ ዕለት እንደሚጠናቀቅ ተጠብቆ የነበረ ቢኾንም በአጀንዳ ተ.ቁ 19 “ልዩ ልዩ ጉዳዮችን በተመለከተ” በሚል ርእስ የቀረቡት የመነጋገሪያ ነጥቦች በመበርከታቸው ሳቢያ ወደ ሰኞ፣ ጥቅምት 19 ቀን 2005 ዓ.ም መራዘሙ ተመልክቷል፡፡ የመ/ፓ/ጠ/ቤ/ክ ጽ/ቤት የሕዝብ ግንኙነት መምሪያ ካለፈው ሳምንት ኀሙስ የምልአተ ጉባኤው አራተኛ ቀን ውሎ ወዲህ በቅዱስ ሲኖዶሱ ውሳኔ ስለተሰጠባቸው አጀንዳዎች ለማሳወቅ ቅዳሜ፣ ጥቅምት 17 ቀን 2005 ዓ.ም ከቀትር በኋላ በጽ/ቤቱ በጠራው ስብሰባ ምልአተ ጉባኤው ውሳኔ ያሳለፈባቸውን አምስት አጀንዳዎች አስታውቋል፡፡
የሕዝብ ግንኙነት መምሪያ ሓላፊ አቶ እስክንድር ገብረ ክርስቶስ እንደገለጹት÷ የፓትርያርክ ምርጫ ሕግ ዝግጅት እስከ ኅዳር 30 ቀን 2005 ዓ.ም ድረስ ተጠናቆ የቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት በሚጠራው ልዩ የምልአተ ጉባኤ ስብሰባ ረቂቁ ቀርቦ እንደሚጸድቅ ይጠበቃል፡፡ የሕጉን መጽደቅ ተከትሎ ስላሉት ኹኔታዎች ሓላፊው ሲያስረዱ÷ “ደንቡ ከጸደቀ በኋላ የቀጣዩ ፓትርያርክ ምርጫ ቀን ይወሰናል፤ አስመራጭ ኮሚቴ ይቋቋማል፤ በዕጩዎች ጥቆማ የስድስተኛው ፓትርያርክ ምርጫ ሂደት ይጀመራል፤”ብለዋል፡፡
የሕገ ቤተ ክርስቲያን ማሻሻያው እና የፓትርያርክ ምርጫ ሕግ ረቂቅ ለምልአተ ጉባኤው ቀርቦ የሚታይበት ወቅት የዕርቀ ሰላም ውይይቱ በሚካሄድበት ሰሞን ከመኾኑ አኳያ በጊዜው መቀራረብ ላይ ጥያቄዎች እየተነሡ ነው፡፡ ቅዱስ ሲኖዶሱ ለዕርቀ ሰላሙ ውይይት የወከላቸው ሦስት ብፁዓን አባቶች ኅዳር 25 ቀን ወደ አሜሪካ አምርተው ውይይቱ ከኅዳር 26 - 30 ቀን 2005 ዓ.ም በዳላስ ቴክሳስ እንደሚቀጥል ያስታወሱት አስተያየት ሰጪዎች÷ ምልአተ ጉባኤው በሕግጋቱ ላይ የሚያደርገው ውይይትና የሕግጋቱን መጽደቅ ተከትሎ ወዲያው ይካሄዳል የተባለው የስድስተኛ ፓትርያርክ ምርጫ የዕርቀ ሰላሙን ሂደት የሚታገሥና ከዕርቀ ሰላሙ ውጤት (ፍጻሜ) ከሚያስከትላቸው አዲስ ኹኔታዎች ጋራ የሚስማማ እንዲኾን በመጠየቅ ላይ ናቸው፡፡ ወቅቱ በዘመናችን የቤተ ክርስቲያናችንን አንድነት ለመመለስና ለማጠናከር ዕድል ያገኘንበት ከመኾኑ አኳያ በጥንቃቄ ልንራመድ እንደሚገባ የሚያሳስቡት አስተያየት ሰጪዎቹ÷ በሁሉም ወገኖች በኩል ዕርቀ ሰላሙ መልካም ፍጻሜ እንዲኖረው ያለውን ዝግጁነት በአስረጅነት ያቀርባሉ፡፡
በምልአተ ጉባኤው ፊት ቀርቦ ስለ ዕርቀ ሰላሙ ሂደት ሪፖርት ያቀረቡትና ለተሰነዘሩትም በርካታ ጥያቄዎች ምላሽ የሰጡት “የሰላምና አንድነት ጉባኤው” አባላት ለኅዳር ወር መጨረሻ የተቀጠረው የዕርቀ ሰላም ውይይት ለቤተ ክርስቲያን ሰላምና አንድነት እንደ ጉባኤ ለሚያደርጉት ጥረት የመጨረሻው ሙከራ/ዕድል ከመኾኑ አኳያ የቻሉትን ሁሉ እንደሚጥሩ አስታውቀዋል፡፡ አራተኛው ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ በጻፉትና በምልአተ ጉባኤው ላይ ቀርቦ በተደመጠው ደብዳቤያቸው ወደ መንበራቸው መመለስ እንደሚሹ ገልጸዋል፡፡
በስደት ከሚገኙት ብፁዓን አባቶች መካከል በተለይም ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ ለቅዱስ ሲኖዶሱ እንደጻፉት በተገለጸው ደብዳቤ የቀኖናው ጥሰት በሁሉም ወገኖች ዘንድ የተፈጸመ በመኾኑ ተለይቶ የሚወቀስ አይኖርም፤ የጋራ ሓላፊነት ሊወሰድበት የሚገባና እንዳይደገምም ተደርጎ መቋጨት ያለበት ጉዳይ ነው፡፡ በስደት ላይ ከሚገኙት አራት ብፁዓን አባቶች መካከል አንዱና በዕርቀ ሰላም ንግግሩ ዋነኛው ተሳታፊ የኾኑት ብፁዕ አቡነ መልከ ጼዴቅ በኅዳር መጨረሻ ለሚካሄደው ውይይት ዐቃቤ መንበረ ፓትርያርኩን ጨምሮ በሹመት ቀደምትነት ያላቸው ብፁዓን አባቶች እንዲወከሉ ጠይቀዋል፡፡ ለዕርቀ ሰላሙ ውጤታማነት ዕንቅፋት እንዳይፈጥር የተሰጋው የአቡነ መቃርዮስ የኤርትራ ጉብኝትም ከግለሰባዊ አቋም የመነጨና በስደት የተቋቋመውን ሲኖዶስ ይኹን ሌሎች አባቶችን እንደማይወክል፣ ይካሄዳል በተባለው የውጨው ሲኖዶስ ስብሰባም ቀርቦ አቋም እንደሚወሰድበት በብፁዕ አቡነ መልከ ጼዴቅ ደብዳቤ ላይ መገለጹ ተመልክቷል፡፡
በአራተኛው ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ደብዳቤ ላይ “ወደ መንበር መመለስ” የሚለው አገላለጽ፣ በብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ ደብዳቤ ደግሞ በሹመት ቀደምትነት ያላቸውን ብፁዓን አባቶች ብቻ ለዕርቀ ሰላም ውይይት መጋበዛቸው ምልአተ ጉባኤውን በከፍተኛ ደረጃ ማወያየቱ ተዘግቧል፡፡
ከምልአተ ጉባኤው አጀንዳዎች መካከል አንዱ በኾነው የገዳማት ጉዳይ÷ የገዳማት አስተዳደርን በጥብቅ ለመከታተል ይቻል ዘንድ የሚታዩ የሕግ ክፍተቶች እንዲስተካከሉ መወሰኑን አቶ እስክንድር ገልጸዋል፡፡ የገዳማቱ አስተዳደር፣ የአህጉረ ስብከት ጽ/ቤቶች፣ የመ/ፓ/ጠ/ቤ/ክ የገዳማት አስተዳደር መምሪያ ከምእመናንና ከመንግሥት አካላት ጋራ በየደረጃው የሚተባበሩበት ይኸው የሕግ ክፍተቶች ማስተካከያ የሥርዐተ ምንኵስናውን አፈጻጸም በየገዳማቱ ሕግ ከማጥበቅ ጀምሮ ገዳማት የልማት ተግባራቸውን አጠናክረው ለመቀጠል የሚያስችል ነው ተብሏል፡፡
ከየት እንደመጡ፣ ለምን እንደመጡና እነማን እንደኾኑ ሳይታወቁ በገዳማቱ ውስጥ በዘፈቀደ ወጣ ገባ እያሉ በስመ ምንኵስና በመኖር ለገዳማቱ ችግር የሚፈጥሩ፣ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ወይም የተወሰነ የአገልግሎት ቦታ ሳይኖራቸው በከተማ እየዞሩ የዋሃን ምእመናንን የሚያጭበረብሩ (ግለሰቦችን ወደ ውጭ በመላክ፣ በትዳርና ሥራ አፈላላጊ የድለላ ተግባር ጭምር በመሰማራት)፣ ምንጩ የማይታወቅ ሀብት (ቤት፣ መኪና) በማፍራት አስከፊ ውጤት እየታየበት የሚገኘውን የሕገ ወጥ መነኰሳት ጉዳይ ለመቆጣጠርና ወደቀደመው የጠበቀ ሥርዐተ ምንኵስና ለመመለስ ጥረት ለማድረግ መታሰቡ ነው የተመለከተው፡፡
አዳሪ ት/ቤቶችንና የአብነት ት/ቤቶችን በተመለከተ ምልአተ ጉባኤው ዐሥር ሚልዮን ብር የማጠናከሪያ በጀት መድቧል፡፡ ካህናት ማሠልጠኛዎች በየአህጉረ ስብከቱ የሚቋቋሙ ሲሆን ሥልጠናው የቋንቋን ልዩነት ከግምት ያስገባ እንደሚኾን ተመልክቷል፡፡ በ31ው የመንበረ ፓትርያርክ አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ላይ በተመከረበት መሠረት የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ጠቅላይ ቤተ ክህነቱ የአጭርና የመካከለኛ ጊዜ የቤተ ክርስቲያን ዕቅዶችን አዘጋጅቶ እንዲያቀርብ መመሪያ ሰጥቷል፡፡ ስትራቴጂያዊ ዕቅዱ ከሦስት እስከ አምስት ዓመት የሥራ ጊዜ የሚኖረው ሲሆን ቋሚ ቅዱስ ሲኖዶስ ለመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት በሚያስተላልፋቸው ጥቅል የዕቅድ መነሻዎች መሠረት እንደሚዘጋጅ፤ የክትትል፣ የድጋፍ አሰጣጥ፣ የግምገማና የግብረ መልስ (Feedback) ሥርዐት አብሮ እንደሚሰናዳለት ተጠቁሟል፡፡
ምልአተ ጉባኤው “በልዩ ልዩ ጉዳዮች” አጀንዳ ሥር ከተመለከታቸው በርካታ ጉዳዮች መካከል በሐምሌ ወር 2004 ዓ.ም በዜና ቤተ ክርስቲያን ጋዜጣ ምክትል አዘጋጅ መ/ር ካህሳይ ገብረ እግዚአብሔር“ብፁዓን እነማን ናቸው?” በሚል ርእስ የተዘጋጀው ባለ 60 ገጽ መጽሐፍ ይገኝበታል፡፡ ቅዱስ ሲኖዶሱ የመጽሐፉን ሙሉ ይዘት በንባብ ያዳመጠ ሲኾን ከወንጌሉ አንቀጸ ብፁዓን፣ ከሐዲስ ኪዳን የቀኖና (ሥርዐት መጻሐፍት)፣ ከቤተ ክርስቲያን ታሪክና ከወቅቱ የቤተ ክርስቲያናችን ኹኔታ አንጻር በግላጭ የሚያነሣቸው ነጥቦች፣ የሚሰነዝራቸው ነቀፋዎችና ትችቶች በሊቃውንት ጉባኤ ተመርምረው የውሳኔ ሐሳብ እንዲቀርብለት ትእዛዝ ሰጥቷል፡፡
“ምንኵስና በኢትዮጵያ” በሚለው የቀደመ መጽሐፋቸው ስለ ‹ደፋርነታቸው› እና ‹የማይነካውን ስለመንካታቸው› የሚገልጽ የአንባቢያን አድናቆት እንደተቸራቸው የገለጹት አቶ ካህሳይ “ብፁዓን እነማን ናቸው?” በተሰኘው መጽሐፋቸው መግቢያ “ብፅዕና በሥራ እንጂ በሹመት እንደማይገኝ” በማስረዳት እንደሚሟገቱ ገልጸዋል፡፡ “ብፅዕናና ጵጵስና በኢትዮጵያ” በሚለው የመጽሐፋቸው ክፍል ቤተ ክርስቲያናችን “ብፁዕ” የሚለውን የክብር ስም ከራሷ ልጆች ለተሾሙት ጳጳሳት መጠቀም የጀመረችው በ1945 ዓ.ም ለመጀመሪያ ጊዜ ከወጣው የቅዱስ ሲኖዶስ ደንብ ጀምሮ ነው የሚሉት ጸሐፊው የቅዱስ ሲኖዶሱ አወቃቀር (ሊቃውንትና ምእመናን ተሳትፎ)፣ የኤጲስ ቆጶሳት አመራረጥ፤ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ለመንጋው ስለሚያደርጉት ጥበቃና ስለ ምእመናን ቁጥር ማፀፅ/ማነስ፤ ስለ ጳጳሳት ደመወዝተኛነት፣ የግል ሀብትና ንብረት ማፍራትና ስለ አወራረስ (ውርስ)፤ ስለ ጳጳሳት የሹመት ዕድሜ፣ ዜግነት፣ የትምህርት ደረጃና የአስተዳደር (አመራር) ችሎታ ከ1945 ዓ.ም ጀምሮ በ1984 ዓ.ም፣ በ1988 ዓ.ም፣ በ1991 ዓ.ም እየተሻሻሉ የወጡ የሕገ ቤተ ክርስቲያኑን አናቅጽ ከመጽሐፈ አብጥሊስ እንዲሁም ከወንጌሉ አንቀጸ ብፁዓን ጋራ በማነጻጸር ተችተዋል፤ በየጉዳዩም ይበጃል ያሏቸውን ሐሳቦች ሰጥተዋል፡፡
ዘመናችን ከእውነት ይልቅ ሐሰት ያየለበት፣ አድርባይነት የተስፋፋበት፣ መንፈሳዊ ሕይወት በዓለማዊ ኑሮ የተዋጠበት ጊዜ እንደኾነ የገለጹት መ/ር ካህሳይ÷ “ዛሬም ቢኾን የብርዔ አፍንጫ የሸተተውን ሁሉ መጻፌን እቀጥልበታሉ”፤ - “በቤተ ክርስቲያን ስም የሚነግዱትን፣ ለቤተ ክርስቲያን መኖር ሲገባቸው በቤተ ክርስቲያን የሚኖሩትን ከመዋጋት ወደ ኋላ አልልም፤ እንዲህ በማድረጌም እግዚአብሔር በቀኜ እንደሚቆም አልጠራጠርም” ይላሉ።
በዚሁ “ልዩ ልዩ ጉዳዮች” አጀንዳ ሥር በሰሜን አሜሪካ ሦስቱ አህጉረ ስብከት በተለይም በዋሽንግተን ዲሲና አካባቢው ሀገረ ስብከት አስተዳደር ጉባኤ እና በሊቀ ጳጳሱ ብፁዕ አቡነ ፋኑኤል መካከል የተፈጠረውን የአስተዳደር ችግር በተመለከተ ምልአተ ጉባኤው የወከላቸው ብፁዕ አቡነ ኤልሳዕና ብፁዕ አቡነ ገሪማ ከሦስት የአስተዳደር ጉባኤው ልኡካን ጋራ መወያየታቸው ተገልጧል፡፡ በዚህም መሠረት ቅዱስ ሲኖዶሱ ሊቀ ጳጳሱ ብፁዕ አቡነ ፋኑኤል የሀገረ ስብከቱን ፀሐፊ የቀሲስ ዶ/ር መስፍን ተገኝን ክህነት በማሰር ያስተላለፉት የእግድ ውሳኔ “የተጋነነና የግል ጥላቻን የሚያንጸባርቅ ነው” ብሏል፡፡ የሃይማኖት ክሕደት፣ የሥርዐተ ቤተ ክርስቲያን ጥሰት በሌለበት ኹኔታ በአስተዳደር ለተፈጠረ ችግር የተላለፈው ውግዘት “ውግዘት አይደለም፤ መፍትሔም አይኾንም” ብሏል - ምልአተ ጉባኤው፡፡ በመኾኑም ኅዳር 25 ቀን 2005 ዓ.ም ለዕርቀ ሰላሙ ውይይት የሚመጡት ብፁዓን አባቶች ጸሐፊውን ቀሲስ ዶ/ር መስፍንና ሊቀ ጳጳሱን ብፁዕ አቡነ ፋኑኤልን በማገናኘትና በማነጋገር ለአለመግባባቱ እልባት ሰጥተው እንዲመለሱ ወስኗል፡፡
በሌላ በኩል ቀደም ሲል የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ “በሰሜን አሜሪካ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የውጭ ጉዳይ ተጠሪ ጽ/ቤት” በሚል ከሕገ ቤተ ክርስቲያንና ከቃለ ዐዋዲው በተፃራሪ ከቅዱስ ሲኖዶስ ዕውቅና ውጭ የተቋቋመው መዋቅር እንዲዘጋ ያስተላለፈውና ተግባራዊ ሳይሆን የቀረው ውሳኔ ተፈጻሚ እንዲኾን አዝዟል፡፡ በዚህ ውሳኔ መሠረት “የጽ/ቤቱ ባለሙሉ ሥልጣን” እና “የሦስት አህጉረ ሥራ አስኪያጅ” በሚል በአቡነ ጳውሎስ የተሾመው ኀይለ ጊዮርጊስ ጥላሁንና ያደራጃቸው መዋቅሮቹ አብረው እንደሚወገዱና በምትኩ አህጉረ ስብከቱ በነበራቸው መዋቅር እንደሚቀጥሉ ለመረዳት ተችሏል፡፡ ለዋሽንግተን ዲሲና አካባቢው ሀ/ስብከትም ሊቀ ጳጳሱ ለዐቃቤ መንበረ ፓትርያርኩ በሚያቀርቡትና ቅዱስ ሲኖዶሱ በሚወስንበት መሠረት አዲስ ሥራ አስኪያጅ እንደሚሾም ታውቋል፡፡
የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ “የታሸገው መንበረ ፓትርያርክ ጉዳይ” በሚል በአጀንዳ ተ.ቁ (18) ባደረገው ውይይት በአምስተኛው ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ መኖሪያ ቤት የሚገኙ ንብረቶች (የቅርብ ምንጮች ፓትርያርኩ በታመሙበት ሰሞንና ዜና ዕረፍታቸው በተሰማበት ቀን ሌሊት ከመመዝበር የተራረፉቱ ናቸው ይላሉ) በሙሉ መለያ ቁጥርና መዝገብ ተሰጥቷቸው ወደ ቤተ መጻሕፍት ወመዘክር (ሙዝየም) እንዲገቡ፣ ዜና ዕረፍታቸው ከተሰማበት ዕለት ረፋድ ጀምሮ የታሸገው መንበረ ፓትርያርክ እንዲከፈት ትእዛዝ ሰጥቷል፤ ቤተ መጻሕፍት ወመዘክሩም ተከፍቶ አገልግሎቱን ይቀጥላል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ÷ ለአንድ ሌሊት ማንነታቸው ባልታወቁ ሰዎች በጥቁር ጨርቅ ተሸፍኖ ለአንድ ሌሊት ያደረው የአቡነ ጳውሎስ ሐውልተ ስምዕ ተነሥቶ በሙዝየም እንዲቀመጥ ቅዱስ ሲኖዶስ በጥቅምት 2002 ዓ.ም ምልአተ ጉባኤው ያስተላለፈው ውሳኔ ፓትርያርኩ ካረፉም በኋላ ተፈጻሚ አለመኾኑ የቅዱስ ሲኖዶሱ ታላላቅ ውሳኔዎች በተግባር ይፈጸሙ ዘንድ በመ/ፓ/ጠ/ቤ/ክህነቱ ላይ በሚያሳርፉት አስገዳጅነት ረገድ አሁንም ጥያቄ ለማንሣት እንደማሳያ መጠቀሱን እንደቀጠለ ለመረዳት ተችሏል፡፡ በአንጻሩ ሐውልቱን “በጥቁር ጨርቅ ሸፍነዋል” በሚል የተጠረጠሩት አንድ የቦሌ መድኃኔዓለም ካቴድራል ጥበቃ ሐውልቱን በማስተከል ከፍተኛ ሚና በተጫወተችው እጅጋየሁ በየነ ጠቋሚነት ለተወሰኑ ቀናት ታሰረው መለቀቃቸው ተሰምቷል፡፡
በተያያዘ ዜና ቅዱስ ሲኖዶሱ ቀደም ሲል በቋሚ ሲኖዶሱ በተወሰነው መሠረት የድሬዳዋ ሳባ ደብረ ኀይል ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን ሕንጻ ግንባታ የተፈጸመውን ሙስናና በሀ/ስብከቱ ሥራ አስኪያጅ መጋቤ ሐዲስ አባ አረጋዊ ነሞምሳ ላይ የሚታየውን ከፍተኛ የአስተዳደር ችግር መርምሮ የመፍትሔ ሐሳብ እንዲያቀርብ የተቋቋመው ኮሚቴ በአስቸኳይ ወደ ስፍራው እንዲያመራ ተእዛዝ ሰጥቷል፡፡ ምልአተ ጉባኤው የኮሚቴው ስምሪት ስለምን እንደ ዘገየ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጁን የጠየቀ ሲሆን “በሥራዎች መደራረብ” የሚል ምላሽ መሰጠቱ ተመልክቷል፡፡ ኮሚቴው ወደ ስፍራው ከመድረሱ አስቀድሞ ትኩረት ለማስቀየስና ጉዳዩን ለማወሳሰብ እየጣሩ የሚገኙት ሥራ አስኪያጁ አባ አረጋዊ የመንግሥት ባለሥልጣናትን ደጅ እየጠኑ ከመኾናቸውም በላይ÷ በዘንድሮው የ31ው አጠ/ሰ//መ/ጉባኤ ላይ ሀ/ስብከቱ ያከናወነውና በራሱ ያመነጨው አንዳችም የልማት ገቢ ሳይኖር በዋናነት ከአጥቢያ አብያተ ክርስቲያን በተሰበሰበ የ20 በመቶ የፐርሰንት ገቢ ከምድቡ የደረጃ ተሸላሚ በሆነበት ውጤት በአስተዳደራቸው የተመረረውንና መሠረታዊ መፍትሔ የሚሻውን ምእመንና ካህን አንድነት ለማላላት እየሞከሩ ይገኛሉ፡፡ ሦስት አባላት የሚገኙበትና በም/ሥራ አስኪያጁ የሚመራው አጥኚ ኮሚቴ ነገ ማክሰኞ፣ ጥቅምት 20 ቀን 2005 ዓ.ም ወደ ድሬዳዋ እንደሚያመራ ተነግሯል፡፡
ምልአተ ጉባኤው ዛሬም ቀጥሎ በሚውለው መደበኛው ስብሰባው ከሚያከናውናቸው ጉዳዮች መካከል÷ አቤቱታ የቀረበባቸውን የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅ፣ የሰዋስወ ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ መንፈሳዊ ኮሌጅ፣ ዝውውር የጠየቁ ብፁዓን አባቶችን ጉዳይ የሚመለከተው የብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ኮሚቴ በተመለከተ በሚያቀርቡት ሪፖርቶች ላይ እንደሚወስን ይጠበቃል፤ የቀጣይ ስድስት ወራት የቋሚ ቅዱስ ሲኖዶስ አባላትንም ይመርጣል፡፡
ቸር ወሬ ያሰማን፤
አሜን፡፡
5 comments:
Anonymous said...
Egizabehare macharashawen yasamerawe
tagetane enetsaley
Anonymous said...
yakidosane amelake eredane
Anonymous said...
chare yasamane
amen
Anonymous said...
kahisayin betam yemadenkew sew new. ewketu ena le ewnet yalew merar meswaytinet yasdesitegnal. metsihafu endet yigegnal? debub africa yalenew endet enagignew?
egzer tena ena rejim edme yistew!
Ahati_Betechrstian said...
ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ወደ መንበራቸው ተመልሰው እርቀ ሰላም ወርዶ የተከፋፈልነው አንድ ሆነን ለማየት ነው የኛ የእናት ቤተ ክርስቲያን ልጆች ተቀዳሚ ፍላጎት እና የዘወትር ጸሎታችን::

‹የትግሬ ምንቸት ውጣ … የጎንደር ምንቸት ግባ›› ይሆንብናል ብላችሁ የምትሰጉ ቅድሚያ ለቤተ ክርስቲያን ሳይሆን ለራሳችሁ የምታስቡም አይዙአችሁ አትፍሩ(አትስጉ) አይሆንባችሁም ምክንያቱም ቅዱስነታቸው አሁን መንበሩ ላይ ተቀምጠው የአስተዳደሩን ስራ መስራት እንደማይፈልጉ በሁላችንም ዘንድ የታወቀ ነው እሳቸውም የተናገሩት ነው::

እባካችሁ አዲስ "ፓትርያርክ" ይመረጥ የምትሉ ሰዎች መለስ ብላችሁ አስተውሉ:: የሚያመጣውንም ችግር እዩት:: ፓትርያሪካችን ብጹዕነታቸው እስካሉ ድረስ ስራውን የሚሰራ ( የሚሰራላችሁ ) እንደራሴ አባት ይመረጥ እና ስራው ይሰራ::

No comments:

Post a Comment