- በግብጹ የፓትርያርክ ምርጫ ቤተ ክርስቲያናችን በአምስት ብፁዓን አባቶች ትወከላለች
- የጠ/ቤ/ክህነቱ የመዋቅር ማሻሻያ እንዲጠና ቅዱስ ሲኖዶስ ትእዛዝ ሰጠ::
- የውጭ ግንኙነት መምሪያ በክፍለ አህጉር ዴስኮች ይደራጃል፤ የቤተ ክርስቲያንን ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ የሚዳስስ መጽሔት በእንግሊዝኛ ቋንቋ ይጀምራል::
- “አዲስ አበባ በአራት አህጉረ ስብከት መከፈሉ አስተዳደራዊ ችግሮችን በዘላቂነት ይቀርፋል፡፡” /የሕዝብ ግንኙነት መምሪያ/
- ሢመተ ፓትርያርክ በምርጫ ወይስ በዕጣ? ከግብጽ ምን እንማራለን?
(ደጀ ሰላም፤ ጥቅምት 16/2005 ዓ.ም፤ ኦክቶ. 26/2012/ READ THIS NEWS IN PDF)፦ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ጥቅምት 25 ቀን 2005 (እ.አ.አ ኖቬምበር 4 ቀን 2012) በሚካሄደው የግብጽ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን 118ኛ ፓትርያርክ ምርጫ ላይ የሚገኙ አምስት ብፁዓን አባቶችን በልኡክነት መሠየሙን የመ/ፓ/ጠ/ቤ/ክ ጽ/ቤት የሕዝብ ግንኙነት መመሪያ አስታወቀ፡፡
ከተጀመረ አራተኛ ቀኑን የያዘው የጥቅምት ቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ እስከአሁን ስለ ደረሰባቸው ውሳኔዎች ለማሳወቅ ትናንት ጥቅምት 15 ቀን 2005 ዓ.ም ከቀትር በኋላ በተጠራው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ የመምሪያው ሓላፊ አቶ እስክንድር ገብረ ክርስቶስ እንደ ገለጹት÷ በመንበረ ማርቆስየሚቀመጠውን 118ኛ ፓትርያርክ ለመምረጥ በዝግጅት ላይ የምትገኘው የግብጽ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ጥሪ አቅርቧል፡፡ በጥሪው መሠረት በመካሄድ ላይ ያለው የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ አምስት ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት በአባልነት የሚገኙበት ልኡካን ቡድን መሠየሙን የገለጹት የመምሪያው ሓላፊ የልኡካኑን ስም ዝርዝር ከመግለጽ ተቆጥበዋል፡፡
ከአኀት አብያተ ክርስቲያን አንዷ የኾነችው የግብጽ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የቀድሞውን ፖፕ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ሺኖዳ ሣልሳዊን ሞተ ዕረፍት ተከትሎ በመንበረ ማርቆስ ለሚተካው ቀጣይ ፖፕ ዘጠኝ ወራት የፈጀ የዝግጅት ሥራ ስታከናወን ቆይታለች፡፡ ከምንገኝበት ተመሳሳይ ወቅታዊ ኹኔታ አንጻር ሂደቱን በቅርበት የሚከታተሉ ኢትዮጵያውያን ኦርቶዶክሳውያን አገልጋዮች እና ምእመናን ከነባራዊ ኹኔታችን ጋራ የሚዛመድ ጠቃሚ የግብጽ ቤተ ክርስቲያን ተሞክሮዎችን መቀመር እንደሚገባ እያሳሰቡ ነው፡፡ ይህም የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ በቀጣይ በሚያየው የፓትርያርክ ምርጫ ሕግ ዝግጅት እና የፓትርያርክ ምርጫ ሂደት አዎንታዊ ሚና እንዳለው ከመመልከቱም በላይ በራሳቸው ጥረት የአኀት አብያተ ክርስቲያንን ሰነዶችና የኢትዮጵያን የግማሽ ምእተ ዓመት ልምድ በማገናዘብ የሕግ ረቂቅ መነሻ አዘጋጅተው ምልአተ ጉባኤው የሚያቋቁመውን አካል በተግባር ለማገዝ የቅዱስ ሲኖዶሱን ጥሪ የሚጠባበቁ ምሁራንና አገልጋዮች እንዳሉም ተሰምቷል፡፡
መላው የግብጽ ቤተ ክርስቲያን ካህናት እና ምእመናን መንፈሳቸውን የሚያስተባብሩበት የጾምና ጸሎት መርሐ ግብር በማወጅ፣ ከዋናው ሢመተ ፓትርያርክ አስቀድሞ ለመንበሩ ይገባሉ ተብለው የሚታሰቡትን አበው መነኰሳትንና ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳትን ማንነት፣ የትምህርት ደረጃ፣ ሞያዊ ሕይወት፣ አገልግሎትና ሌሎችንም ዝርዝር መረጃዎቻቸውን ይፋ በማድረግ በብዙኀን መገናኛ የምረጡኝ ቅስቀሳ ሥርዐት ጭምር ተመዛዝነውና ተበላልጠው በየደረጃው የሚያልፉበትን በመጨረሻም እየተጣሩ ከመጡት ሦስት ብፁዓን አባቶች ወይም መነኰስ መካከል ዐይኑን በጨርቅ የሸፈነ ሕፃንየሚያነሣው ዕጣ የሚወድቅለት የሚመረጥበት መንገድ የኢትዮጵያውያን አገልጋዮችንና ምእመናን ቀልብ የሳቡ የሢመተ ፓትርያርክ ሥርዐቶች ናቸው፡፡
የፓትርያርክ ምርጫ ሕጉ አጀንዳ በምልአተ ጉባኤው ከተመከረበት በኋላ የሰነድ ዝግጅቱ የሚጠናቀቅበት ጊዜ የቀጣዩን ፓትርያርክ ምርጫ ኹኔታና ወቅት እንደሚወስን አቶ እስክንድር ይናገራሉ፡፡ ከቀጣዩ ፓትርያርክ ምርጫ አስቀድሞ መጠናቀቅ ይገባዋል ተብሎ ስለሚታመንበት የዕርቀ ሰላም ውይይት ከጋዜጠኞች ጥያቄ የቀረበላቸው አቶ እስክንድር÷ “እርሱ ቅዱስ ሲኖዶሱ በቀጣይ አጀንዳዎች ላይ የሚያስተላልፈውን ውሳኔ ተከትሎ በሚኖረን የመግለጫው ‘phase’ ይታያል፤”ብለዋል፡፡
የፓትርያርክ ምርጫ ሕጉ ዝግጅት ሂደት እና ምርጫውን የሚያስፈጽመው አካል የሚቋቋምበት ኹኔታ የውጭ ተጽዕኖ እንዳይጫነው ስጋት የገባቸው ወገኖች ጥቂቶች እንዳልኾኑ የጉዳዩ ተከታታዮች ባላቸው ቀጥተኛ ትዝብት ለመረዳት ይቻላል፡፡ እኒህ ወገኖች የቤተ ክርስቲያናችን የፓትርያርክ ምርጫ ሕግና የፓትርያርክ ምርጫ ሂደት ካህናትና ምእመናን ስለዕጩዎች ማንነት የተሟላ መረጃና ግንዛቤ ይዘውበምርጫው የሚሳተፉበት፣ በመጨረሻም በመንበረ ተክለ ሃይማኖት የሚቀመጠው ቅዱስ አባት ሢመት ይደልዎ! ይደልዎ! ተብሎ በመንፈስ ቅዱስ ዕጣ የሚመረጥበት ሥርዐት እንዲኾን ይመኛሉ፡፡
በሌላ በኩል የሕዝብ ግንኙነት መምሪያው በመግለጫው እንዳመለከተው÷ ከጥቅምት 12 ቀን 2005 ዓ.ም ጀምሮ በሥራ ላይ የሚገኘው የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ እስከአሁን ድረስ በስድስት አጀንዳዎች ላይ ውሳኔ አሳልፏል፡፡ በዚህም መሠረት በሥራ ላይ የሚገኘው የ1991 ዓ.ም ሕገ ቤተ ክርስቲያን ከቀኖና ቤተ ክርስቲያን፣ ከሚሻሻለው ቃለ ዐዋዲና ከሌሎች ዝርዝር ሕጎች ጋራ ተዛምዶና ተጣጥሞ እንዲዘጋጅ የወሰነው ቅዱስ ሲኖዶሱ ሥራውን የሚያከናውን ኮሚቴ አቋቁሟል፡፡ ከቤቶችና ሕንጻዎች አስተዳደርና ልማት ድርጅት የቀረበለትን ሪፖርት በማዳመጥ ነባር ቤቶችና ሕንጻዎች በአግባቡ እንዲያዙ፣ የተጎዱት እንዲታደሱ፣ ቤተ ክርስቲያኒቱ ባሏት ክፍት ቦታዎች የከተማውን ማስተር ፕላን የጠበቁ ተጨማሪ ሕንጻዎች እንዲገነቡ፣ በቀድሞው መንግሥት ተወርሰው ዛሬም በመንግሥት ይዞታ ሥር የሚገኙ ቤቶችን የማስመለሱ ጥረት ተጠናክሮ ሂደቱ በአጭር ጊዜ እልባት እንዲሰጠው ወስኗል፡፡
የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከትን የአስተዳደር ችግሮች እንዲያጠና በቅዱስ ሲኖዶሱ የተሠየመው ኮሚቴ ባቀረበው የመፍትሔ ሐሳብ ጠቋሚ ጥናት ላይ ክርክር ያደረገው ምልአተ ጉባኤው÷ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የምሥራቅ፣ የምዕራብ፣ ሰሜንና ደቡብ ተብሎ በአራት አህጉረ ስብከት እንዲደራጅ መወሰኑን መግለጻችን ይታወሳል፡፡ ባለው ሕገ ቤተ ክርስቲያን መሠረት አራቱ አህጉረ ስብከት በማእከላዊነት የቅዱስ ፓትርያርኩ ልዩ ሀገረ ስብከት ኾነው በረዳት ሊቃነ ጳጳሳት መመራታቸውን እንደሚቀጥሉ በጋዜጣዊ መግለጫው ላይ ተመልክቷል፡፡ ይህም አደረጃጀት በሀገረ ስብከቱ የተንሰራፋውን የሙስናና የመልካም አስተዳደር ችግሮች በዘላቂነት ለመፍታት ያስችላል ተብሎ እንደታመነበት የሕዝብ ግንኙነት መመሪያው ሓላፊ አስረድተዋል፡፡ ከዚሁ ጋራ በተያያዘ የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት መዋቅር ዘመኑን የዋጀ፣ ቀልጣፋ፣ ግልጽነትና ተጠያቂነት ያለው ኾኖ ይስተካከል ዘንድ ጥናት ተደርጎ እንዲቀርብ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ መወሰኑን የመምሪያው ሓላፊ አስታውቀዋል፡፡
ምልአተ ጉባኤው በይቀጥላል በተወያየበት የውጭ ግንኙነት መምሪያ አገልግሎትን ስለ ማሻሻልና ተደራሽ ስለ ማድረግ በተመለከተ÷ በአፍሪካ፣ በመካከለኛው ምሥራቅ፣ በአውሮፓ እና በአሜሪካ የሚኖሩ አገልጋዮችና ምእመናን በቂ መረጃ ያገኙ ዘንድ ጠንካራ የኮሚዩኒኬሽን ሥራ የሚሠራባቸውና አህጉሮቹን የሚያገናኙ የክፍለ አህጉር ዴስኮች እንዲቋቋሙ፤ የቤተ ክርስቲያናችንን ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ በመደበኛነት የሚዳስስና በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚሰራጭ መጽሔት በእንግሊዝኛ ቋንቋ መዘጋጀት እንዲጀምር፣ ከዚህም አኳያ መምሪያው በመዋቅሩ ዘመኑን የዋጀና በተቋማዊ አሠራሩም ቀልጣፋ ይኾን ዘንድ በሰው ኀይልና በበጀት እንዲጠናከር ምልአተ ጉባኤው ትእዛዝ መስጠቱን አቶ እስኵንድር ገልጸዋል፡፡
በመምሪያው የሰው ኀይል አደረጃጀት ሥራው በቀጥታም ይኹን በተዘዋዋሪ የማይመለከታቸውና የግል ቢዝነሳቸውን በሞኖፖል ከሚያጧጡፉ ግለሰቦች ይልቅ÷ የቤተ ክርስቲያናችንን ትምህርት በወጉ ተምረው ሲያበቁ በመናገርም በመጻፍም ብቃት ያላቸው በውጭ ቋንቋዎችና ሥነ ጽሑፍ የሠለጠኑ ቋሚ ሠራተኞች መካተት እንደሚገባቸው የሚያጠያይቅ አይኾንም፡፡ ይህም መምሪያው በክብረ በዓላትና በአንዳንድ ዝግጅቶች ከዚህም ከዚያም ሰብስበው የትርጉም ሥራ ከሚያሠሯቸው የተወሰኑ ግለሰቦች ጥገኝነት የሚላቀቅበትን ዕድል ይሰጠዋል፡፡ በ31ኛው አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ላይ የትሪኒዳድና ቶቤጎ (ካሪቢያን) ተወካይ በራት ግብዣው ምሽት ላይ እንዳሉት÷ ስድስት ቀን ሙሉ በአማርኛ የቀረበውን ሪፖርትና ሲካሄድ የቆየውን ውይይት በእንግሊዝኛ የሚተረጉምላቸው ጠፍቶ ያዘኑበት አጋጣሚ ከመደገም ያተርፈናል፡፡
የጥቅምት ቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ዛሬን ጨምሮ በተከታይ ቀናት ውሎዎቹ÷ ዓመታዊ በጀትን፣ የሦስት ዓመት ዕቅድን፣ ሙስናን ለመዋጋት በሚያስችሉ የሞራልና የሥነ ምግባር ጉዳዮችን፣ የሀብትና ንብረት (ቅርስ) አጠባበቅን፣ የአብነት ት/ቤቶችንና ገዳማትን በቋሚ በጀት መደገፍንና ማጠናከርን፣ የፓትርያርክ ምርጫ ሕግንና የፓትርያርክ ምርጫን መወሰንን በሚመለከት ተወያይቶ የሚደርስበትን ድምዳሜ በቀጣይነት መግለጫ እንደሚሰጥበት የሕዝብ ግንኙነት መምሪያ ሓላፊው አቶ እስክንድር ገብረ ክርስቶስ ጨመረው አስታውቀዋል፡፡ ከዚህም ጋራ ወቅታዊ ኹኔታውን አስመልክቶ ኅብረተሰቡንና የሚዲያ ተቋማትን ከሚያሳስቱ በመላምት ከሚሰራጩ መረጃዎች መጠንቀቅ እንደሚገባ የመምሪያው ሓላፊ አሳስበዋል፡፡
ቸር ወሬ ያሰማን፤
አሜን፡፡
No comments:
Post a Comment