Tuesday, 9 October 2012

ዋልድባን ለመታደግ በዋሽንግተን ዲሲ ትላንት ጉባኤ ተደረገ፣ ይበል የሚያሰኙ እንቅስቃሴዎችም ተደርገዋል






በPDF ለማንበብ እዚህ ይጫኑ 

በትላንትናው ዕለት መስከረም ፳፯ ቀን ፳፻፭ ዓ.ም. በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ክርስቲያኖች አንድነት (ዋልድባን ለመታደግ የሚንቀሳቀሰው ዓለም አቀፍ ኮሚቴ ዋሽንግተን ዲሲ ንዑስ ክፍል) አስተባባሪነት የተጠራው ጉባኤ ተካሂዶ ውሏል። በጉባኤውም ላይ ካህናት አባቶች፣ ሰባኬ ወንጌል፣ እንዲሁም በርካታ ከዋሽንግተን ዲሲና አካባቢው በመጡ የጉባኤው ታዳሚዎች በተገኙበት በርካታ ቁም ነገሮችን ተነጋግሮ እና ጉባኤው ተጠቃሏል። በቀጣይነትም ሥራዎችን በእቅድ ይዞ ለመሥራት ብሎም በአባባቢው የሚገኙትንም መዕመናን እንዲሁም በመላው ዓለም የሚገኙትን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን አማኞችን በማስተባበር ለሥራ የተነሳሱ ካህናትን፣ መምህራንን፣ ዘማሪያን፣ በትውልድ ኢትዮጵያውያን የሆኑ በምዕራቡ አለም በተለያየ ሀላፊነት ላይ ያሉትን ምሁራንን እንዲሁም አጠቃላይ የኢት ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ምዕመናን በማስተባበር የዋልድባ ገዳም መፍረስ ሳይሆን አፈሯ እንኳን እንዳትነካ (ሳትነካ) ለመጪው ትውልድ ለማስተላለፍ ቁርጠኝነት ያሳዩበት እና በብዙ ሃዘንም እየደረሰ ያለውን እንግልት በተለያየ መልኩ ለማሳየት ተሞክሯል።

በጉባኤው ላይ በምሁራን በርካታ ግንዛቤዎችን እና ምልከታዎችን ለተሰብሳቢው ማሳየት ተችሏል ከነዚህም ውስጥ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ገዳማት እና መካናት አካባቢ የሚገኙት ደኖች እና እጽዋቶች ያላቸው ተዋጽዖን በተለይ (Environmental effect) የሚያሳድሩትን ተጽዕኖ፣ በዕጽዋት ዝርያን (specious) ማግኛ ቦታዎች እንደሆኑ እና በተለይም በዋልድባ አካባቢ በሚሰሩት የግድብ እና ድልድይ ወይንም ልማት ሥራዎች ሊመጡ የሚችሉ  በርካታ ሳይንሳዊ ክስተቶች የተካተተበትና ጥሩ ግንዛቤ መስጫ የሆነ መርኅግብር እንደነበር ለመረዳት ችለናል፥ ይበልጡኑ ጥናቱ የቀረበው የ Environmental science ባለሙያ በሆኑ ኢትዮጵያዊ የቀረበ ሙያዊ እይታ በመሆኑ በቀጣይነት በርካታ ምሁራን እና ባለሙያዎች ሊሳተፉበት ብሎም በሙያቸው በዋልድባ ዙሪያ በሚሰሩት ፕሮጀክቶች ሊያመጡ የሚችሉትን ማኅበራዊ እንዲሁም ባህላዊ ጉዳቶች ለመላው ኢትዮጵያውያን ማቅረብ ቢቻል ነገ ተቆርቋሪው ትውልድ ማምጣት እና ይሄንን የተጀመረውን ትግል ዋልድባ ገዳምን የመታደግ ሥራን ሊያቀለው እንደሚችል እና የመንግሥትም ተወካዮች እኛ ያልነው ብቻ መሆን አለበት የሚለውን ትተው ኢትዮጵያውያን ምሁራን እንዲሁም የገዳሙን አባቶች ውትወታ እና ጥያቄ በቅጡ ሊያጤኑት ይገባል ብለን እናምናለን።

በተጨማሪ በጉባኤው ላይ ከቀረቡት የምሁራን ምልከታ ሌላው ክፍል በዋልድባ ገዳም ላይ የሚሰራው የወልቃይት ስኳር ፋብሪካ ከርሱም ጋር ተያይዞ በሚመጡት የመንደር ምሥረታ፣ የግድብ ሥራ፣ የፋብሪካ ሥራ፣ እንዲሁም የከተማ ምሥረታ በአጠቃላይ በፕሮጀክቱ ምክንያት ሊደርሱ ስለሚችሉ መጠነ ሰፊ የሆኑ ችግሮች፣ ግድቡ ስለሚያስከትለው ችግሮች በግድቡ ላይ ስለሚኖረው ማስተንፈሻ (spill way) መንግሥት ግልጽ የሆነ መረጃዎችን ባለመስጠቱ ወደፊት ሊያስከትለው የሚችለውን ችግር፣ የግድቡ ከፍታ በቀጣይነት ከ80 እስከ 100 ሜትር ከፍታ ቢጨምር ሊያመጣ የሚችለውን ትርፋማነት ከዚህም ጋር ተያይዞ የገዳሙን የመኖር እና ያለመኖር የሚወስን ክስተቶች እንደሆኑ በባለሙያው የግድብ ሥራ እና የstructural design master of science (MS.) Engineer እንዲሁም በኢትዮጵያ የተለያዩ የwater work design Engineer በሆኑ ባለሙያ ገለጻ የተደረገ ሲሆን በዚህ ጥናታቸውም ላይ መንግሥት እራሱ ያመናቸውን ግድቡ ሲያልቅ ግድቡ ወደ ገዳሙ ክልል 330 ሜትር እንደሚገባ እና ያም ማለት 15.33 ኪ. ሜትር ርቀት ላይ ዋልድባ አበረንታት ገዳም ስለሚገኝ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ የችግሩ ተጠቂ እንደሚሆን በገለጻው ተብራርቷል። ግድቡ ሲጠናቀቅ ግድቡ ከሚይዘው 3.8 ሚሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውሃ ሃይቅ መሰል የውሃ ክምችት ወይም ውሃ የሚተኛበት 40 % የሚሆነው የውሃው መጠን በዋልድባ ጋዳም ይዞታ ላይ እንደሆነ በግልጽ መረጃ ለማሳየት ተችሏል። በተጨማሪ እንደባለሙያው ገለጻ ከዚህ በፊት ባላቸው ልምድ በሌሎችም ሃገሮች እንደሚታዩት አንድ ግድብ የመጀመሪያ ፕላኑ እንደሚያሳየው ባለው ቁመት ብቻ እንደማይቀር እና አሁን  ባለው ግድብ ላይ በ100 ሜትር ብቻ ቢጨምር ከ485 AD ጀምሮ ክብሩን እና ቅድስናውን ጠብቆ የቆየውን የአበረንታት መድኅኒዓለም ገዳምን (በዋልድባ ገዳም ከሚገኙት ሦስት ገዳማን ዋነኛው) ሙሉ ለሙሉ በውሃው እንደሚሸፈን እና እንደሚጥለቀለቅ እነዚህ መረጃዎች ያሳያሉ።

በአጠቃላይ በገለጻው መሠረት የኢትዮጵያ መንግሥት በአቀደው መሰረት ለ1600 ዓመታት በብዙ ነገሥታት እና የሚትዮጵያ መሪዎች ታፍሮ እና ተክብሮ የኖረው ቅዱሱ ገዳም ፈርሶ ለመሥራት ያቀዳቸው

    ለስኳር ፋብሪካ አገልግሎት የሚውል ግድብ ግንባታ
†    የስኳር ፋብሪካ ግንባታ
    ለስኳር ፋብሪካ የሚውል የሸኮራ አገዳ እርሻ
†    ለስኳር ፋብሪካ የሚውሉ የአገልግሎት መኪናዎች ማመላለሻ መንገዶች እና ድልድዮች
†    የመዝናኛ ሠፈር ለነዋሪዎች
†    በዝርዝር አስፍሮ ባይገልጸውም የስኳር ፋብሪካው ያለ መኖሪያ ቤቶችና ሰፈር አገልግሎት ሊሰጥ   
     ስለማይችል የመኖሪያ ሰፈር (አዲስ ከተማ) በዋልድባ ይከትማል። 

በመጨረሻ ጉባኤው የዚህ የዋሽንግተን ዲሲ ንዑስ ኮሚቴ ሥራዎችን በቀጣይነት ሊሠራ ባቀደው መሰረት ለተሰበሰቡት አባቶች እና ምዕመናን እቅዶቹ ቀርበው ምዕመናንም አዎንታዊ ምላሾችን መስጠት ጀምረዋል፥ ከቀረቡት እቅዶች አራቱ እንደሚከተለው ነው
† ዋልድባን ለመታደግ የሚንቀሳቀሰውን ተቋም በሕጋዊ መልኩ አስመዝግቦ ሕጋዊ ሰውነቱን ማሰጠት
† የዚህ ተቋም መረጃዎችን የሚያደርስበት በተለይ ለእንግሊዝኛ ተናጋሪዎች ድኅረ ገጽ ማዘጋጀት
† ተቋሙ እና ምዕመናን ሊገናኙበት የሚችሉበት ብቸኛ መሳሪያ የሬዲዮ ጣቢያ ማቋቋም
† እነዚህን ተቋሙ የሚያገኛቸውን መረጃዎች ለሕዝቡ ማድረስ አስፈላጊ በመሆኑ ይበልጡን በኢትዮጵያ ውስጥ ለማድረስ በCD/DVD ተዘጋጅቶ እንዲበተን እቅዶቹን ቀርበው ነበር።

እነዚህ ከላይ የተጠቀሱት እቅዶች በቀረቡበት ወቅት ምዕማናኑ አዎንታዊ ምላሻቸውን በመስጠት በርካታ በጉባኤው ላይ የተገኙት ምዕመናን ለመሳተፍ ቃል በመግባት፣ እንዲሁም በተለያየ ሙያዎች ሊረዱ እንደሚችሉ ቃል የተገባ ሲሆን በቀጣይነት ከላይ የተጠቀሱትን እቅዶች ተግባራዊ ለማድረግ በተለይ በርዕሰ አድባራት ደብረ ሰላም ቅድስት ማርያም ዋሽንግተን ዲሲ ቤተክርስቲያን የተቋቋመው የዋልባን ጉዳይ የሚያጠና ኮሚቴ እንዲሁም በደብረ ገነት መድኅኒዓለም ቴምብፕል ሂል ቤተክርስቲያን የተቋቋመው ኮሚቴ ከዚህ ኮሚቴ ጋር በጋራ ሥራዎችን ተገናኝተው እንዲሰሩ በርካታ ምዕመናን ሃሳባቸውን ሰጥተው የቤቱም ሃሳብ እንደሆነ በዚህ ጉባኤ ላይ ይበል የሚያሰኝ ሥራ እንደሆነ ብዙዎች ያምናሉ። እንደሚታወቀው ይህ ኮሚቴ እስከ አሁን በርካታ ሥራዎችን እየሰራ ሲሆን በተለይ በዋሽንግተን ዲሲና አካባቢው በሚገኙ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ባሉበት ቦታ ሁሉ ኮሚቴው በአካል በመሄድ የዚህ ሥራ ተባባሪ እንዲሆኑ፣ ባለፈው ለተደረጉ ጉባኤያት ለሕዝቡ የጉባኤ ጥሪ እንዲተላለፍ ትብብር እንዲደረግላቸው ጥያቄ ቢያቀርቡም በዋሽንግተን ዲሲ እና አካባቢው ከሚገኙት በግምት 20 ወይም ከዛ በላይ በሚሆኑት አጥቢያዎች ከሁለት ወይም ሦስት አጥቢያዎች በስተቀር በሌሎቹ አጥቢያዎች ፍቃደኝነታቸውን ሳያሳዩ በመቅረታቸው ይበልጥ ደግሞ በአካባቢው በሚገኙ አንዳንድ ካሕናት እና መምህራን “ዋልድባ አልተነካም” እነዚህ ሰዎች “ጸረ ሰላም እና ጸረ ልማት” ናቸው በማለት ቤት ለቤት በመሄድ እንዲሁም በመድረክ ላይ ሕዝበ ክርስቲያኑን እያዋከቡት መሆናቸውን በሃዘን ምዕመናን አቤቱታቸውን አሰምተዋል።  

በአጠቃላይ በዚህ ጉባኤ በርካታ መረጃዎች የተሰጡበት፣ ምዕመናን አለኝታቸውን ያሳዩበት፣ በዋሽንግተን ዲሲ አካባቢ በሚገኙ አጥቢያዎች መልካም ጅምር ተሳትፎ ያሳዩበት በመሆኑ፣ የተለያዩ ምሁራን፣ ትላልቅ አባቶች እና እናቶች የተሳተፉበት በመሆኑ፣ የብዙ ወጣት የሰንበት ት/ቤት ወጣቶችን ያሳተፈ በመሆኑ ኮሚቴው ይበልጥ ሥራዎችን ለመሥራት በቁርጠኝነት የተነሳሳበትን መልካም ጅምር እና ሂደትን ያሳየ ጉባኤ እንደሆነ ለመረዳት ችለናል። በጉባኤው ላይ የተሳተፉትንም ሆነ በተለያየ ምክንያት መገኘት ፈልገው ለመገኘት ያልቻሉትንም በአጠቃላይ የዋልድባ ገዳም መፍረስ እና የገዳሙ አባቶች ላይ እየደረሰ ያለውን ግፍ እና እንግልት ለማስቆም በሚደረገው ጥረት ላይ ተባባሪ ለመሆን ለምትፈልጉ ምዕመናን ጥያቄ ቢኖርም ለመጠየቅ ቢያስፈልግዎ በሚከተለው አድራሻችን እርዳታዎንም ሆነ አስተያየትዎን ለመቀበል ዝግጁ መሆናችንን ከወዲሁ ለመግለጽ እንወዳለን።
Save Waldba Foundation
PO Box 56145
Washington, DC 20040

በስልክ ቁጥራችን   571-224-2869 ወይም 571-299-0975/ 703-307-9478

እግዚአብሔር አምላክ ቅድስት ሀገራችንን እና ቅድስት ቤተክርስቲያናችንን በረደኤት ይጠብቅልን
ቸር ይግጠመን። 

No comments:

Post a Comment