የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ጳውሎስ አስከሬን ሽኝት
ማውጫ፦ ዜና
- ግርግሩ መልክ ይያዝ::
- ሥርዐተ ቀብሩ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የቀጥታ ሥርጭት ይተላለፋል::
በብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፣ በጠቅላይ ቤተ ክህነት የየመምሪያው ሓላፊዎችና መላው ሠራተኞች፣ የየድርጅትና የየኮሌጁ ሓላፊዎችና ሠራተኞች፣ አገልጋዮችና ምእመናን ታጅቦ ወደ ቤተ ክርስቲያኑ ከገባ በኋላ በቅድስቱ ውስጥ ዐርፎ ጸሎተ ቅዳሴው በብፁዕ አቡነ ማቲያስ የካናዳ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ መሪነት እየተካሄደ ይገኛል፡፡ ከንጋቱ 12፡00 ላይ በመላው ኢትዮጵያ ገዳማትና አድባራት የደወል ድምፅ ተሰምቷል፡፡
በወጣው መርሐ ግብር መሠረት የቅዳሴው ሥነ ሥርዐት እንዳበቃ የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ አስከሬን በልዩ ሠረገላ ኾኖ በብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፣ በሚኒስትሮችና የመንግሥት ባለሥልጣናት፣ በገዳማትና አድባራት አስተዳዳሪዎች፣ በሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን፣ በሰንበት ት/ቤት ወጣቶች፣ በፖሊስ ሠራዊት ባንድ፣ በምእመናንና ምእመናት ታጅቦ ወደ መንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ጉዞ ያደርጋል፡፡ በዚህ ጉዞ የፖሊስ ሠራዊት ግራና ቀኝ በሰልፍ አስከሬኑን ያጅባል፡፡ የቅዱስነታቸው አስከሬን በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል እንዳረፈ የዕለቱ መርሐ ግብር በጸሎት ይዘጋል፡፡ ረቡዕ ለኀሙስ አጥቢያ ከምሽቱ 2፡00 እስከ ንጋቱ 12፡00 ሙሉ ጸሎተ ማሕሌቱ ሲከናወን ያድራል፡፡
በዛሬው የመርሐ ግብሩ ክንውን ሐዘንን ከመግለጽ ባሻገር በተለይም የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩን አስከሬን ይዞ ለማስገባት ከተመደቡት አባቶች ውጭ በአንዳንድ መነኰሳት ዘንድ የታየው ከፍተኛ ግርግር ሌላ ትርጉም የሚያሰጠው ነው፤ በቀጣይ የሥርዐተ ቀብሩ ሂደት ቢያንስ ከሚገኙት እንግዶችና በቴሌቪዥን ከሚሰጠው የቀጥታ ሥርጭት አንጻር ፈር መያዝና መስተካከል እንደሚገባው አስተያየት እየተሰጠበት ይገኛል፡፡
እስከ አሁን በሥነ ሥርዐቱ ላይ የቅብጥ፣ የሶርያ፣ የአርመንና ሕንድ /ማላባር/ ኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያን ልኡካን እንዲሁም የግሪክ ኦርቶዶክስ ተወካዮችና የመሳሰሉት እንግዶች እንደሚገኙ ማረጋገጣቸው ተገልጧል፡፡
ቀሪውን የቀብር ሥነ ሥርዐት ክንውን ከመርሐ ግብሩ ይመልከቱ፡፡
የቅዱስነታቸውን ነፍስ በአብርሃም ዕቅፍ ያኑርልን
ቸር ወሬ ያሰማን፤
አሜን፡፡
No comments:
Post a Comment