Tuesday 21 August 2012


ቅ/ሲኖዶስ የቀብር ቀን እንዲቀየር የቀረበውን ጥያቄ አልተቀበለውም

  • የፓትርያርኩ ቤተሰቦች “በሕግ እንጠይቃለን” እያሉ ነው፤ ፓትርያርኩ የቤተሰቦቻቸው ወይስ የቤተ ክርስቲያን?
  • የሰላም እና አንድነት ጉባኤ ልኡካን አዲስ አበባ ይገባሉ፤ ጉባኤው ልዩነት በአንድነት ሳይፈታ ሌላ ፓትርያርክ የመሾሙን ጉዳይ ቅ/ሲኖዶስ እንዲያስብበት ተማፅኗል፤ የመንግሥትንም እገዛ ጠይቋል።
  • የአዲስ አበባ ሰንበት ት/ቤቶች አንድነትለፓትርያርኩ ሥርዐተ ቀብር አፈጻጸም ዝግጅት እያደረገ ነው።
(ደጀ ሰላም፤ ነሐሴ 15/2004 ዓ.ም፤ ኦገስት 21/ 2012/ READ THIS NEWS IN PDF)፦የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ዜና ዕረፍት ከተሰማበት ቀን አንሥቶ አጠያያቂ ከኾኑት ጉዳዮች መካከል ሐዘናቸውን በሚገልጹ አንዳንድ ወገኖችና ብዙኀን መገናኛ ዘንድ የሚሰማው “ቤተሰቦቻቸው” የሚለው ቃል ነው፡፡



ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ በፓትርያርክነታቸው የነበራቸው የአባትነት ሓላፊነት ለብዙኀኑ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ካህናትና ምእመናን እንጂ በሥጋ ለሚዛመዷቸው ቤተሰቦቻቸው አልነበረም፡፡ ፓትርያርክ ማለት ቅሉ ርእሰ አበው፤ አበ ብዙኀን አማለት እንደኾነ ይታወቃል፡፡

ሰሞኑን በመንበረ ፓትርያርኩ እየተገኙ ሐዘናቸውን የሚገልጹ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት ንግግርም ይህንኑ የሚያስረግጥ ነው፡፡ የኢሕአዴግ ሥልጠና ማእከል ዋና ዳይሬክተር አቶ አዲሱ ለገሠ÷“አቡነ ጳውሎስ ለሃይማኖቶች መቻቻል፣ ሰላምና ልማት በሠሩት ሥራ የአገራችን ብቻ ሳይሆን የዓለም አባት ናቸው፤ ለኅብረቱ ም/ቤት ፕሬዝዳንትነትም የተመረጡት በዚህ ሥራቸው ነው፤” ብለዋል፡፡ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ ካሳ ተክለ ብርሃን በበኩላቸው÷ “ከጥንት ጀምሮ የአገራችን ምሶሶ የኾነችው ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ለሰላምና ልማት ስትጥር ነበር፤ በዚህ ውስጥም ሁሉንም ድምፅ በማቻቻል ለሰላም አስተዋጽዖ ያደረጉት አቡነ ጳውሎስ አንዱ ባለድርሻ ናቸው፤” ሲሉ ተናግረዋል፡፡

ፓትርያርክም የሚሾመው በሥርዐተ ምንኵስና በድንግልና መንኵሰው ቤተ ክርስቲያንን ከሚያገለግሉ ሊቃነ ጳጳሳት፣ ጳጳሳትና ኤጲስ ቆጶሳት መካከል እንደመኾኑ መጠን÷ ፓትርያርኩ በምንኵስናቸው፣ በለበሱት አስኬማና በገቡት ቃል ኪዳን ቢያንስ ከገንዘብና ከዘመድ ፍቅር የመነነ፣ ምኑን የኾነ ምንኵስናዊ ግብር፣ አነዋወርና ሕይወት ሊኖራቸው እንደሚገባ ግልጽ ነው፡፡ ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ ራሳቸው አንደኛ ዓመት በዓለ ሢመታቸውን ሐምሌ 5 ቀን 1985 ዓ.ም ባከበሩበት ወቅት ተናግረውት እንደነበረው÷ “የፓትርያርክነት ሓላፊነቱ ከእግዚአብሔር ጋራ ቃል ኪዳን የተገባበት ስለሆነ የራስን ፈቃድ የሚፈጽሙበት አይደለም፤ በማስተዋል ሲመለከቱትም የበለጠ ምናኔ ነው፡፡” ስለሆነም ፓትርያርኩ የቤተ ክርስቲያን እንጂ የራሳቸውም የቤተሰቦቻቸውም እንዳልኾኑ በመገንዘብ ቢያንስ በሞተ ሥጋ ከዚህ ዓለም ከተለዩ በኋላ አነጋገሩም፣ የሐዘን አደራረሱም ሊታረም ይገባ ነበር፡፡

ከብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ፓትርያርክ ዘኢትዮጵያ ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ዜና ዕረፍት በኋላ ግን በፓትርያርኩ ቤተሰቦችና ዘመዶች፣ በብዙኀን መገናኛ በሚወጡት የዜና ዘገባዎች የሚታየው እና የሚሰማው ግን መነኰስ ባሕታውያኑን፣ መነኰስ ገዳማውያኑን ያስመኛል፡፡ እንደሚታወሰው ሁሉ÷ የቅዱስ ሲኖዶስ አስቸኳይ ጉባኤ የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ ሥርዐተ ቀብር ነሐሴ 17 ቀን 2004 ዓ.ም፣ ከቀኑ በ6፡00 ሰዓት በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል እንዲፈጽም ወስኖ አስታውቋል፡፡

ቅዱስ ሲኖዶስ ይህን ካስታወቀበት ማግስት ጀምሮ ቤተሰቦቻቸው፣ እነርሱን መጠጊያ ያደረጉት እነ እጅጋየሁ በየነና የ”ራእይ ለትውልዱ” ያሬድ ግርማ ሥርዐተ ቀብሩ የሚፈጸምበት ቀን ወደ ቅዳሜ፣ ነሐሴ 19 ቀን 2004 ዓ.ም እንዲራዘም እየጎተጎቱ ስለመሆናቸው ተነግሯል፡፡ ይህን ጥያቄያቸውንም ሐዘን ለመድረስ ወደ መንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት አዳራሽ ለሚመጡት ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት በመወትወት ለማሳመን ሲጥሩ መታየታቸውና አንዳንዶቹም “ሲኖዶሱን በሕግ እንጠይቃለን” እስከ ማለት መድረሳቸው ተዘግቧል፡፡ በእነርሱ ፍላጎት ሥርዐተ ቀብሩ ኀሙስ በሥራ ቀን መኾኑ ብዙ ሰው እንዲገኝ አያስችልም፤ አስከሬኑም ከቅድስተ ቅዱሳን ማርያም ገዳም በቀጥታ ወደ መንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል እንዲወሰድ መደረጉ ጉዞውን ያሳጥረዋል፡፡

በመኾኑም ሥርዐተ ቀብሩ የሚፈጸምበት ቀን ወደ ቅዳሜ፣ ነሐሴ 19 ቀን እንዲዛወር፤ አስከሬኑም ከቅድስት ማርያም በቀጥታ ወደ ካቴድራሉ መወሰዱ ቀርቶ በሠረገላው እንደተጫነ ወደ መስቀል አደባባይ እንዲያመራና ከዚያም ወደ ካቴድራሉ ተመልሶ እንዲፈጸም ቢደረግ ብዙ ሰው ተገኝቶ በተለያየ ቦታ ሐዘኑን ለመግለጽና ለመሰናበት ያስችለዋል፡፡ በአንድ ጊዜ በአንድ ቦታ እንደሚገኝ የሚጠበቀው ሕዝብ ብዛት“ለጸጥታ አጠባበቅ ከሚፈጥረው ጫና” አኳያ ሐሳቡ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናትን ድጋፍ አግኝቶ ጥያቄው ለቅዱስ ሲኖዶስ ቀርቦ እንደነበር ነው የዜናው ምንጮች የተናገሩት፡፡

ቅዳሜ፣ ነሐሴ 12 ቀን 2004 ዓ.ም ማምሻውን የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ ቤተሰቦች በተገኙበት ተሰብስቦ በጥያቄው ላይ የመከረው ቅዱስ ሲኖዶስ ግን የቀደመ ውሳኔውን በማጽናት በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት በመገኘት ሐዘንን መግለጽ እንደሚቻል፣ ሥርዐተ ቀብሩም ቀደም ሲል በተገለጸው አኳኋን እንዲከናወን መስማማቱ ተገልጧል፤ እስከዚያው የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ አስከሬን አሁን በሚገኝበት ሃያት ሆስፒታል ተጠብቆ ይቆያል፡፡

በሥርዐተ ቀብሩ ላይ ተገኝቶ የሐዘን መግለጫውን እንደሚያቀርብ ያስታወቀው በሰሜን አሜሪካ በስደት ላይ ከሚገኙ አባቶች ጋራ የሚካሄደውን የዕርቀ ሰላም ንግግር ሲያመቻች የቆየው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሰላምና አንድነት ጉባኤ ሁለት ልኡካን አዲስ አበባ እንደሚገቡ ተሰምቷል፡፡ ጉባኤው ባወጣው መግለጫ በሀገር ውስጥና በውጭ በሚገኙት አባቶች መካከል አንድነት መፍጠሩ ቅዱስ ሲኖዶስ ቅድሚያ የሚሰጠው አጀንዳ እንዲሆን፤ ልዩነት በአንድነት ሳይፈታ ፓትርያርክ የመሾሙ ጉዳይ እንዲታሰብበት ለቅዱስ ሲኖዶስ ማሳሰቡና መንግሥት ለአንድነት የሚደረገውን ጥረት እንዲያግዝ መጠየቁ ይታወሳል፡፡

በተያያዘ ዜና የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ገዳማትና አድባራት አጥቢያ አብያተ ክርስቲያን ሰንበት ት/ቤቶች በብፀዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ ሥርዐተ ቀብር አፈጻጸም ላይ የበኩላቸውን ተሳትፎ ለማድረግ የሚያስችላቸውን ቅድመ ዝግጅት በማካሄድ ላይ መኾናቸው ተነግሯል፡፡ የአዲስ አበባ ሀ/ስብከት ሰንበት ት/ቤቶች አንድነት ምንጮች ለደጀ ሰላም እንደገለጹት÷ ለብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ አባታዊ ክብር ሰጥቶ ከመሸኘት፣ ሥርዐተ ቀብሩንም ከቤተ ክርስቲያናችን ተቋማዊ ሓላፊነትና ገጽታ ተመልክቶ ለቀጣዩ በጎ ልምድ ከማቆየት አኳያ ምእመናኑ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል፡፡

በዚህም መንፈስ ከሁሉም የሀገረ ስብከቱ ሰንበት ት/ቤቶች የተውጣጡና በየክፍለ ከተማው የተሰባሰቡ መዘምራን የመዝሙር ጥናት በማድረግ ላይ መኾናቸው ተጠቁሟል፡፡ በቁጥር ከ138 በላይ በሚኾኑ የአዲስ አበባ አጥቢያ አብያተ ክርስቲያን ሰንበት ት/ቤቶች የተመሠረተው አንድነቱ በሀገር ዓቀፍ ደረጃ በሚቋቋመው የሰንበት ት/ቤቶች አንድነት የቤተ ክርስቲያንን ዕድገት ለማፋጠን፣ ቤተ ክርስቲያን ከምእመናኑ ሰባ ከመቶ የሚኾነው ወጣት አጠቃላይ አያያዝ የተመለከተ ፖሊሲና ስትራቴጂ እንድትቀርጽ ቀዳሚ ሚና በመጫወት ላይ ይገኛል፡፡

ቸር ወሬ ያሰማን፤
አሜን፡፡


7 comments:

Hailu said...

After the funerial ceremony, we must focus on how to restore the unity of our church.

We must not rash into another election that will noT solve the division that engUlfed our church for the past 20 years.

PRIORITY FOR UNITY!

Yeselamna Andinet Comitew Hasab Lidegef yigebal.
Anonymous said...
GOD IS WORKING,WE HAVE TO BE CAREFUL EVERY BODY.WE MUST PRAY, IT IS VERY VERY IMPORTANT THE UNITY OF OUR BELOVED CHURCH !!!
Anonymous said...
GOD IS WORKING,WE HAVE TO BE CAREFUL EVERY BODY.WE MUST PRAY, IT IS VERY VERY IMPORTANT THE UNITY OF OUR BELOVED CHURCH !!!
Anonymous said...
ANDINET YIQDEM
Anonymous said...
ANDINET YIQDEM
Anonymous said...
ቅዱስ እንደዚህ አይነት ጥያቄ መቀበልም የለበትም! ቤተክርስቲያን የምትሰራውን ታውቃለች:: 45,000, 000 ህዝብ (ቅዱስ ሲኖዶስ የሚወክለው) የወሰነውን በጣም ጥቂት በጣት የሚቆጠሩ ሰዎች ሊያፈርሱ አይገባም::
Anonymous said...
ደጀ ሰላሞች እባካችሁ ስለ እግዚአብሔር የሟች አቡነ ጳውሎስን ፎቶገራፈ ከዋናወ ድህረ ገጻችሁ ( Home page ) ላይ አንሱልን ግፍ ነው

No comments:

Post a Comment