Thursday, 16 August 2012

የአቡነ ጳውሎስ ጳውሎስ ዜና ዕረፍት አጭር ሪፖርታዥ


  • የአቡነ ጳውሎስን ቀብር የሚያስፈጽም ኮሚቴ በመ/ፓ/ጠ/ቤ/ክ ጽ/ቤት ተቋቁሟል፤ መኖሪያ ቤታቸውና ቤተ መጻሕፍት ወመዘክሩ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት በተገኙበት ታሽጓል፤
  • ጥቂት ብፁዓን አበው ወደ ባልቻ ሆስፒታል ሄደዋል፤ አስከሬናቸው በባልቻ ሆስፒታል ይገኛል፤ ጥቅመኛዋ እጅጋየሁ በየነ “አልሞቱም፤ አስከሬናቸው ይመርመርልኝ” እያለች በማወክ ላይ ትገኛለች::
     ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፣ የአድባራትና ገዳማት አለቆች በአስቸኳይ ወደ አዲስ አበባ እንዲገቡ ጥሪ ተደርጓል::
  • የአቡነ ጳውሎስን ቀብር የሚያስፈጽም ኮሚቴ በመ/ፓ/ጠ/ቤ/ክ ጽ/ቤት ተቋቁሟል::
  • ዐቃቤ መንበረ ፓትርያርክ ይሾማል፤ ከቋሚ ሲኖዶሱም ጋራ እየመከረ ይሠራል::(ሕገ ቤተ ክርስቲያን)
  • “ውሉደ ጳውሎስ” /እነ እጅጋየሁ በየነ/ በፓትርያርኩ ስም “ጳውሎስ ፋውንዴሽን”ለማቋቋም እየተሯሯጡ ነው፤ የሀብት ቅርምቱን ለማመቻቸት ይኾን?
  • በፓትርያርኩ በተለያዩ ዘመዶቻቸው ስም በአንድ የመንግሥታዊው ባንክ ቅርንጫፍ ሦስት አካውንቶች ውስጥ ከ22 ሚልዮን ብር በላይ እንደሚገኝ ተጠቁሟል::
(ደጀ ሰላም፤ ነሐሴ 10/2004 ዓ.ም፤ ኦገስት 16/ 2012/READ THIS NEWS IN PDF) ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ፓትርያርክ ዘኢትዮጵያ ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ዛሬ፣ ነሐሴ 10 ቀን 2004 ዓ.ም፣ ንጋት ላይ በዳጃዝማች ባልቻ ሆስፒታል ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል፡፡



ፓትርያርኩ ከትናንት በስቲያ፣ ነሐሴ 8 ቀን 2004 ዓ.ም ማምሻውን ወደ ደጃዝማች ባልቻ ሆስፒታል ገብተው ሕመማቸውን ለረጅም ጊዜ ሲከታተሉላቸው በቆዩት የሆስፒታሉ ዶክተሮች ሕክምና ቢደረግላቸውም በቆየባቸው በሽታ ዛሬ ንጋት 11፡00 ላይ መሞታቸውና አስከሬናቸውም በዚያው እንደሚገኝ ተረጋግጧል፡፡ አቡነ ጳውሎስ የምንገኝበትን የፍልሰታ ለማርያም ጾምበድሬዳዋ ጻድቁ አቡነ አረጋዊ ወቅድስት አርሴማ የሴቶች ገዳም የማሳለፍ ልማድ ቢኖራቸውም በዘንድሮው ሱባኤ ግን መሰንበቻቸውን ያደረጉት የፕትርክናው መንበር በሚገኝበት በአዲስ አበባ ቅድስተ ቅዱሳን ማርያም ገዳም ነበር፡፡

በቀደሙ ዘገባዎቻችን እንደገለጽነውና በሰሞኑ የሱባኤው ቅዳሴ ውሎዎች እንደተረጋገጠው÷ አቡነ ጳውሎስ የጀመሩትን ጸሎተ ቅዳሴ ለመጨረስ ተስኗቸው ቅዳሴው ከሥርዐተ ቤተ ክርስቲያን ውጭ ሌሎች ሊቃነ ጳጳሳት /እነ ብፁዕ አቡነ ገሪማ/ እየተተኩ እንዲጠናቀቅ ሲደረግ ነበር፡፡ የዐይን እማኞች እንደተናገሩት÷ ፓትርያርኩ በጸሎተ ቅዳሴው መካከል በወንበር ላይ እንደተቀመጡ ሁለት እግራቸውን ፊት ለፊታቸው በሚገኝ ሌላ ወንበር ላይ ሰቅለው ታይተዋል፤ ወደ መኖሪያቸው ሲወጡም ይኹን ሲገቡ ዙሪያቸውን በረዳቶቻቸው ተደግፈው ነው፡፡ ከቆየባቸው የስኳር በሽታና ሌሎችም ሕመሞቻቸው መወሳሰብ ጋራ በተያያዘ ሁለቱም እግሮቻቸው ከአውራ ጣታቸው ጀምሮ እስከ ጉልበታቸው ድረስ በከፍተኛ ደረጃ ተጎድቷል፡፡ እግራቸው እንዲቆረጥ ጤናቸውን በሚከታተሉላቸው የሀገር ውስጥና የውጭ ሐኪሞች ሲነገራቸውን ቢቆይም ፓትርያርኩ የሐኪሞቹን ምክርና ማሳሰቢያ ችላ ብለው በውጭ ምንዛሬ በሚገዟቸውና በመርፌ በሚወስዷቸው መድኃኒቶች ራሳቸውን ሲያስታምሙ ቆይተዋል፡፡ አቡነ ጳውሎስ ከትናንት በስቲያ ወደ ሆስፒታል የገቡት ታዲያ በዚሁ እግራቸው ላይ በከፍተኛ ጥዝጣዜ እየተሠቃዩ በነበረበት ኹኔታ ነበር፡፡


በኻያኛ ዓመት በዓለ ሢመታቸው አከባበርና ከዚያም ወዲህ በቋሚ ቅዱስ ሲኖዶስ በሚካሄዱት ስብሰባዎችጥልቅ የመቀዘዝ ስሜት ይታይባቸው የነበሩት አባ ጳውሎስ÷ ትምክህታቸውን በሚገልጹባቸውና እንደአለኝታም በሚቆጥሯቸው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ በጽኑ መታመም ክፉኛ መደናገጣቸውናግራ መጋባታቸው፤ በግንቦቱ የርክበ ካህናት ቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤም በሃይማኖት ሕጸጽ ከተጠየቁወዲህ [በመጽሐፍ መልክ ባሳተሙት የዶክትሬት ጥናታቸው ሕጸጹ የተገለጸባቸውን አንቀጾችና ዐረፍተነገሮች አላካተቱምበአያሌው መጨነቃቸው፤ ከወርኀ ግንቦት ጀምሮ ከቅዱስ ሲኖዶሱ በላይ አመራር ሰጪለመኾን ሕገ ወጥ ቡድኖችን በማደራጀት ያደረጓቸው ጥረቶች መክሸፋቸው፤ ከዚህም ሁሉ ጋራ ቀደም ሲልበሄዱበት እርሳቸውን አክብረው የሚከተሏቸው በርካታ ጳጳሳት የሸሽዋቸው መኾኑ እዚህም እዚያምከሚሰማው የቤተ ክርስቲያን አባቶች፣ ምእመናንና ወዳጆች ሐዘንና ጸሎት ጋራ ተደማምሮ የፈጠረባቸውአካላዊና መንፈሳዊ መጎሳቆል ለተመልካች በጉልሕ የሚረዳ እንደ ነበር የጠቅላይ ቤተ ክህነት ምንጮችለደጀ ሰላም ተናግረዋል፡፡

ሐምሌ 5 ቀን 1984 ዓ.ም የተሾሙትና ለኻያ ዓመታት በፕትርክና የቆዩትን የአቡነ ጳውሎስን የቀብር ሥነ ሥርዐት ለማስፈጸም ጠቅላይ ሥራ አስኪያጁ ብፁዕ አቡነ ፊልጶስ እና ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ዛሬ ጠዋት ከመከሩበት በኋላ “የቀብር አስፈጻሚ ኮሚቴ” መቋቋሙ ተዘግቧል፡፡ የፓትርያርኩ የሕዝብ ግንኙነት ጽ/ቤትና ፕሮቶኮል ሓላፊዎችም በየአህጉረ ስብከቱ ስልክ በመደወል ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፣ የገዳማትና አድባራት አለቆች በአስቸኳይ ወደ አዲስ አበባ እንዲገቡ ጥሪ በማስተላለፍ ላይ ይገኛሉ፡፡

በአሁኑ ሰዓት በርካታ አባቶች፣ አገልጋዮችና ምእመናን በመንበረ ፓትርያርኩ የስብከተ ወንጌል አዳራሽ በመገኘት ኀዘናቸውን እየገለጹ ሲኾን ስለ ጸሎተ ፍትሐቱ እና የቀብር አፈጻጸም መርሐ ግብሩ የቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት እና የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት የሚያወጣው መግለጫ እየተጠበቀ ነው፡፡

የአቡነ ጳውሎስ ኅልፈተ ሕይወት በመጀመሪያ የደጀ ሰላም ዜና መገለጹን ተከትሎ በርካታ ወገኖች የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከዓለማዊው አገራዊው ኹኔታ አኳያ በወሳኝ ኹኔታ ላይ እንደምትገኝ፣ በሹመታቸው ቤተ ክርስቲያንን ለሁለት የከፈሉት አቡነ ጳውሎስ በሞታቸውም እንደይከፋፍሉን ይልቁንም ቀጣይ ርምጃዎች ያለፉትን ስሕተቶች የሚያርሙና እንዳይደገሙ የሚያደርጉ፣ ለቤተ ክርስቲያናችን ሁለንታዊ አገልግሎት መጠናከርም የሚያግዙና ብሔራዊ ክብሯን የሚመልሱ በመኾናቸው ላይ የተረጋጋና ጥንቃቄ የተሞላበት ሥራ እንዲሠራ እያሳሰቡ ይገኛሉ፡፡

በፓትርያርኩ ሞት ሰበብ ዘመዶቻቸውና የጥቅም ተጋሪዎቻቸው የቤተ ክርስቲያን ሀብት እንዳያሸሹ ማሳሰቢያ እየተሰጠም ይገኛል፡፡ በተለይም የ”አቡነ ጳውሎስ ቁም ተዝካር” በተባለው ኻያኛው በዓለ ሢመት አከባበር ላይ የግል ጥቅማቸውን ሲያሳድዱ የነበሩት ውሉደ ጳውሎስ (እነ እጅጋየሁ በየነ) በአቡነ ጳውሎስ ስም የሚጠራ “ጳውሎስ ፋውንዴሽን”እናቋቁማለን በሚል እየተሯሯጡ እንደሚገኙ ተዘግቧል፡፡

ለ‹ፋውንዴሽኑ› መቋቋም ያስፈልጋል የተባለውን ገንዘብም እንደተለመደው ከአድባራትና ገዳማት እንዲሁም ሌሎች የተለያዩ የቤተ ክርስቲያኒቱ ኢኮኖሚያዊ ምንጮች ለመሰብሰብ ሲዘጋጁ መቆየታቸውን የገለጸው ምንጩ ወ/ሮ እጅጋየሁ በየነን፣ መልአከ ፀሐይ በቀለ ተሰማ (ቤቴል ቅዱስ ሚካኤል)፣ ሰሎሞን በቀለን (ቦሌ መድኃኔዓለም)፣ ቀሲስ ግሩም መልአክ ታዬ (ትንሣኤ ዘጉባኤ ማተሚያ ቤት፣ ዳንኤል ሰይፈ ሚካኤል (ጠቅላይ ቤተ ክህነት) በዋና አደራጅነት ጠቅሰዋል፡፡ የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ጽ/ቤት በጉዳዩ ላይ ጠንካራ ክትትል በማድረግ የወይዘሮዋንና ሌሎች አካላትን ችግር ፈጣሪነት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለማቆም እየሠራ እንደሚገኝ ተዘግቧል፡፡

በአቡነ ጳውሎስ እምቢተኛነት ሳይካሄድ በቀረውና ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት በተለይም ብፁዕ አቡነ ናትናኤል ከእምባ ጋራ “የቤተ ክርስቲያን አምላክ ይፈረድ” በሚል ሐዘናቸውን ከገለጹበት የሐምሌው ልዩ የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ በኋላ በቋሚ ሲኖዶስ የተቋቋመው ሦስት አባላት የሚገኙበትና በብፁዕ አቡነ ሉቃስ የሚመራ ኮሚቴ በሰሜን አሜሪካ ከሚገኙ አባቶች ጋራ የሚካሄደው የሰላምና ዕርቅ ንግግር ተጠናክሮ እንዲቀጥል ለአስታራቂ ኮሚቴው ምላሽ የሚሰጥ ጽሑፍ በመዘጋጀት ላይ እንደነበርም ተነግሯል፡፡ የሰላምና ዕርቅ ንግግሩ እንዳይቀጥል ዕንቅፋት ሲፈጥሩ የቆዩት አቡነ ጳውሎስ ሞታቸው በሂደቱ ላይ የሚፈጥረው ተጽዕኖ ገና የሚታይ ይኾናል፡፡

ቸር ወሬ ያሰማን፣ አሜን።

በ1991 ዓ.ም የወጣውና በሥራ ላይ የሚገኘው ሕገ ቤተ ክርስቲያን
ፓትርያርክ ድኅረ ዕረፍት ወይም ከሥልጣን መውረድ (አንቀጽ 16) ኹኔታዎች
በአንቀጽ 17 ንኡስ አንቀጽ 1 – 3 የሚከተለውን ይላል፡፡

አንቀጽ 17 - ዐቃቤ መንበረ ፓትርያርክ
1.          ፓትርያርኩ በሞት ሲለይ ወይም በዚህ ሕግ አንቀጽ 16 መሠረት ከሥልጣኑ ሲወርድ ቅዱስ ሲኖዶስ በሹመት ቀደምትነት ካላቸው ሊቃነ ጳጳሳት መካከል በዕለቱ ዐቃቤ መንበረ ፓትርያርክ መርጦ ይሾማል፡፡ የተተኪው ፓትርያርክ ምርጨም ይካሄዳል፡፡
2.         የተተኪው ፓትርያርክ ምርጫ አፈጻጸም እንደጊዜውና እንደ ሥራው ኹኔታ እየታየ ከ40 እስከ 80 ቀን ባለው ጊዜ ይኾናል፡፡
3.         የዐቃቤ መንበረ ፓትርያርኩ ተግባር፡-
ሀ) ዐቃቤ መንበረ ፓትርያርክ ጊዜያዊ ጉዳዮችን ከቋሚ ሲኖዶስ ጋራ እየመከረ ያከናውናል፡፡
ለ) በፓትርያርኩ ምርጫ ጊዜም የቅዱስ ሲኖዶስ ሊቀ መንበር ኾኖ ምርጫውን ያስፈጽማል፤ እርሱ ግን ከምርጫው አይገባም፡፡

ቀጣይ ዜናዎችን ይከታተሉ

No comments:

Post a Comment