(ደጀ ሰላም፤ ነሐሴ 10/2004 ዓ.ም፤ ኦገስት 16/ 2012/ READ THIS NEWS IN PDF)፦ ኻያኛ ዓመት በዓለ ሢመታቸውን ከሐምሌ 5 ቀን 2004 ዓ.ም ጀምሮ እስከ ወሩ መገባዳጃ ሲያከበሩ የቆዩት አምስተኛው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ በጠና ታመው ነሐሴ 8 ማምሻውን ወደ ደጃዝማች ባልቻ ሆስፒታል ከገቡ በኋላ በሕክምና ሲረዱ ቆይተው ማረፋቸውን ምንጮቻችን እየገለጹ ነው። አቡነ ጳውሎስ በምንገኝበት የፍልሰታ ለማርያም ጾም የሰሞኑ ውሏቸው በመንበረ ፓትርያርክ ቅድስተ ቅዱሳን ማርያም ገዳም ጸሎተ ቅዳሴ ላይ እንደነበሩ መዘገባችን የሚታወስ ሲሆን ፓትርያርኩን ለሕልፈት ያበቃውን ሕመም ለይተው አልገለጹም፡፡
እግራቸው ከጉልበታቸው በታች በከፍተኛ ደረጃ መጎዳቱንና የጤናቸው ኹኔታ አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱ የሚነገርላቸው ፓትርያርኩ÷ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እንደሚስተዋለው የአባ ጳውሎስ መውጣትና መግባት ግራና ቀኝ በሚይዟቸው ሰዎች ድጋፍ እንደሚከናወን የተዘገበ ሲሆን ራሳቸውን ችለው መራመድ ይኹን ከመኪናቸው መውጣትና መውረድም እንደተሳናቸው ተመልክቷል፡፡ አቡነ ጳውሎስ ለረጅም ጊዜ ሕመማቸውን ሲከታተሉ በቆዩበት የደጃዝማች ባልቻ ሆስፒታል ዶክተሮች ከፍተኛ ክትትል ላይ መኾናቸውንና አስጊ በሚባል ኹኔታ ውስጥ እንደሚገኙ ምንጮችን ጠቅሰን መዘገባችን ይታወሳል፡፡
ደጀ ሰላም ዜናውን እየተከታተለች ማቅረቧን ትቀጥላለች።
ቸር ወሬ ያሰማን፤
አሜን፡፡
No comments:
Post a Comment