- አንድ የዋልድባ አብረንታንት ገዳም መነኰስ ወደ ማይ ፀብሪ ተወስደዋል።
- የገዳሙ መነኰሳት የግዴታ መታወቂያ እንዲወስዱ ተደርገዋል።
- ፓትርያርኩ ዕግድ የጣሉበት የጀርመን የተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፍ ተካሒዷል።
ትናንት፣ ሐምሌ 13 ቀን 2004 ዓ.ም፣ ከቀኑ 11፡30 ላይ ከዚሁ ወረዳ በመጡ የጸጥታ ኀይሎች አባ ገብረ ሥላሴ ዋለልኝ የተባሉ የዋልድባ አብረንታንት ገዳም መነኰስ ተይዘው ወደ ማይ ፀብሪ መወሰዳቸውን ምንጮቹ ገልጸዋል፡፡ መነኰሱ በጸጥታ ኀይሎቹ መወሰዳቸውን የገዳሙ ማኅበር አባላት በአካል እየተከታተሉ ለመጠየቅና ለመቃወም ያደረጉት ጥረት በጸጥታ ኀይሎቹ የኀይል ርምጃ የተነሣ ከተወሰነ መንገድ በኋላ መገታቱ ተነግሯል፡፡
በትናንትናው ዕለት ከተወሰዱት አባ ገብረ ሥላሴ ዋለልኝ በተጨማሪ ባለፈው ሳምንት አባ ገብረ ሚካኤል የተባሉ ሌላ መነኰስ ተይዘው መታሰራቸው ተባብሶ የቀጠለውን የአስተዳደሩን ጅምላ ርምጃ የሚያመለክት መኾኑ ተመልክቷል፡፡ ባለፈው ወር መጀመሪያ የፕሮጀክቱ ግድብ አካባቢ ለተቃጠሉት የሥራ መሣሪያዎችና ለተጎዱት ሠራተኞች “ሓላፊነት ውሰዱ” በሚል ከዋልድባ ሰቋር ኪዳነ ምሕረት አንድነት ገዳም ወደ ዓዲ አርቃይ የተወሰዱት አምስት መነኰሳት ከሳምንት እስርና እንግልት በኋላ መለቀቃቸው ታውቋል፡፡
ለደኅንነታቸው ሲባል ስማቸው ያልተገለጸ አንድ የገዳሙ መነኰስ ለአሜሪካ ድምፅ ሬዲዮ የአማርኛ ቋንቋ አገልግሎት እንደተናገሩት÷ የወረዳው አስተዳደር በመነኰሳቱ ላይ ስለሚወስደው የግፍ ርምጃ የዋልድባ ዶንዶሮቃ ቅዱስ ሚካኤል አብረንታንት ገዳም እየተነጋገረበት ይገኛል፡፡
በሌላ ዜና የፀለምት - ማይ ፀብሪ ወረዳ አስተዳደር አስተላልፎታል በተባለ ትእዛዝ የዋልድባ አብረንታንት ገዳም መነኰሳት ያለ ፍላጎታቸው መታወቂያ እንዲይዙ መደረጋቸው ተገልጧል፡፡ ምንጮቹ እንዳብራሩት “እናንተን መንግሥት አልገዛችኹም” በሚል ተዘጋጅቶ ለገዳሙ መነኰሳት የታደለው ይኸው መታወቂያ÷ “በምዕራብ ትግራይ ፀለምት ወረዳ የዋልድባ አብረንታንት ገዳም ምክሆን ለገዳማተ ኢትዮጵያ ማኅበረ ዘቤተ ሚናስ” የሚል ጽሕፈት እንደሰፈረበት ተናግረዋል፡፡ በገዳሙ ማኅተም ላይ የሚነበበው የቀደመው ስያሜው“ዋልድባ አብረንታንት ገዳም ምክሆን ለገዳማተ ኢትዮጵያ ማኅበረ ዘቤተ ሚናስ” የሚል ነው፡፡ ይህ ዐይነቱ የመታወቂያ እደላ የዋልድባ ሰቋር ኪዳነ ምሕረት ዘገዳመ ዋሊ ቅድስት ደቂቁ ለሳሙኤል ርእሰ ገዳማት ዘኢትዮጵያ እና የዋልድባ ዳልሽሐ ኪዳነ ምሕረት አንድነት ገዳምን ይመለከት እንደኾነ ምንጮቹ አላረጋገጡም፡፡
በተያያዘ ዜና በጀርመን አገር በፓትርያርኩ እንዳይካሄድ ታግዶ የነበረውና ዋልድባን የሚመለከተው ሰላማዊ ሰልፍ ሐምሌ 12 ቀን 2004 ዓ.ም ተካሂዷል። የአውሮፓዋ የንግድ ማዕከል የሆነችው የጀርመኗ የፍራንክፈርት ከተማ በዚሁ እለት በሁለት ወገን የተከፈሉ በኢትዮጵያውያን የተዘጋጁ ሰላማዊ ሰልፎችን አስተናግዳለች። ከቀናት በፊት በዘገብነው መሠረት የዋልድባ ገዳምን በልማት ምክንያት መነካት ተከትሎ የጀርመን የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ ካህናትንና ምእመናንን የሚያሳትፍ ሰላማዊ ሰልፍ በሊቀ ካህናት ዶ/ር መርዓዊ ተበጀ ተጠርቶ የነበረ ሲሆን ይህንንም ተከትሎ በፓትርያርኩ ፊርማ ከኢትዮጵያ ደብዳቤ ተልኮ ሰልፉ እንዲሰረዝ አስቸኳይ ትዕዛዝ መሰጠቱ ይታወሳል። ይሁንና ሰልፉ በተባለው እለት የተካሄደ ሲሆን በፍራንክፈርት መሐል ከተማ በጸሎት የተጀመረው የተቃውሞ ሰልፉ ወደ ቆንስላ ጽ/ቤቱ ከማቅናቱ በፊት ለሚመለከታቸው የጀርመን መንግሥት አካላት በጀርመንኛ ቋንቋ የተዘጋጀ በዋልድባ ገዳም እየተካሄደ ያለውን ያልተገባ ሥራ የሚያስረዳ ጽሑፍ በሊቀ ካህናት ዶ/ር ቀሲስ መርዓዊ በኩል ተሰጥቷል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የተቃውሞ ሰልፉ አለመቅረት ያሳሰባቸው የመንግሥትና የፓትርያርኩ ባለሟሎች የሰላማዊ ሰልፉን ተሰሚነት ለማደብዘዝ ሌት ተቀን በማሰብ ባጭር ጊዜ ውሳኔ በተመሳሳይ ቀን እና ሰዓት የዋልድባን ልማት እንደግፋለን የሚል የድጋፍ ሰልፍ አዘጋጅተዋል። ቆንስላ ጽ/ቤቱ ጋር በመቆም ድጋፋቸውን ሊያሰሙ በጥቂት ቁጥር ከወጡት መካከል አብዛኞቹ የአንድ አካባቢ ተወላጆች ከመሆናቸውም ባሻገር የጉዳዩን ሃይማኖታዊ ፋይዳ በሚገባ ያላጤኑና በፍራንክፈርቱ የቅ/ማርያም ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ - አባ ሲራክ- ዘርን መሠረት ያደረገ የመከፋፈል እኩይ ሴራ ሰለባ የሆኑ የተነገራቸውን የተሳሳቱ መረጃዎች በፓለቲካ መነጽር ብቻ በመመልከት ድጋፍ ሊሰጡ ተሳትፎ ያደረጉ ናቸው። ይህ ሲሆን ግን አባ ሲራክ በየትኛውም በኩል በተካሄዱት ሰልፎች ሳይገኙ መቅረታቸው ጥያቄን ሳይፈጥር አላለፈም።
በሁለቱም በኩል የተዘጋጁትን የሰላማዊ ሰልፎች ያስተባበሩት በቆንስላ ጽ/ቤቱ ገብተው ንግግር ያደረጉ ሲሆን የሰላማዊ ሰልፎቹ ከማብቃታቸው በፊት በመንግሥት በዋልድባ ላይ እያደረገ ያለውን እንቅስቃሴ ከተቃወሙት ሰልፈኞች መካከል ጉዳዩን የፓለቲካ ይዘት ለማስያዝ የሞከሩ አንዳንዶች ቢኖሩም በሊቀ ካህናት ዶ/ር መርዓዊ “ሰልፉን ያዘጋጀንበትን ዓላማ የሳተ አካሄድ ነው” በሚል ተግሳጽ መፈክራቸውን እንዲያቆሙ ተደርገዋል። ከእኩለ ቀን አንስቶ ለሦስት ተከታታይ ሰዓታት የተካሄደው ሰልፍ ከሰዓት በኋላ አስር ሰዓት ተኩል ገደማ በጸሎት ተጠናቋል።
ቸር ወሬ ያሰማን። አሜን።
No comments:
Post a Comment