Tuesday, 15 April 2014

‹‹ሰሙነ ሕማማት››


በዲ/ን ህብረት የሺጥላ
‹‹ሰሙነ ሕማማት›› መጽሐፍ ቅዱሳዊ ሥርዓት ነው፡፡ በርካታ ሰዎች ቤተ ክርስቲያንን ከመጽሐፍ ቅዱስ ውጭ የምትጓዝ አካል አድርገው ሊገልጧት ይሞክራሉ፡፡ ይህ እጅግ አላዋቂ መሆናቸውን ይመሰክራል፡፡ ቤተ ክርስቲያን ከመጽሐፍ ቅዱስ ያልተገኘና በሥጋዊና በደማዊ ዕውቀት ላይ የተመሠረተ ሥርዓት የላትም፡፡ ቅዱስ ሉቃስ በሐዋርያት ሥራ‹‹ከሕማማቱ በኋላ›› በማለት ስለ ሰሙነ ሕማማት የሚያወሳ ቃል ተጠቅሟል፡፡ (የሐዋ1.3) ሰሙነ ሕማማት የሁለት ቃላት ጥምር ውጤት ነው፡፡ ‹‹ሰሙን›› የሚለው ቃል ‹‹ሰመነ›› ከሚለው የግዕዝ ቃል የተገኘ ሲሆን ስምንት ቀኖች ወይም ሳምንት ማለት ነው፡፡ ‹‹ሕማማት›› የሚለው ቃልም እንደዚሁ ‹‹ሐመመ›› ወይም ‹‹ሐመ›› ከሚለው የግዕዝ ቃል የተገኘ ሲሆን መከራዎች ማለት ነው፡፡ ‹‹ሕማማት›› የምንለው ለብዙ ሲሆን ነው፡፡ ለአንድ ወይም ለነጠላ ሲሆን ደግሞ ‹‹ሕማም›› እንላለን፡፡ እንግዲህ ሁለቱን ቃላት በማናበብ ‹‹ሰሙነ ሕማማት›› ስንል ‹‹የመከራዎች ሳምንት›› ማለታችን ነው፡፡
ሕማማት ስንል ምን ዓይነት ሕማም ወይም ምን ዓይነት መከራ? በማን ላይ? የሚሉት ጥያቄዎች ምላሽ ማግኘት አለባቸው፡፡ ሰዎች ልዩ ልዩ አደጋ ሲደርስባቸው መከራ አገኛቸው ይባላል፡፡ በሽታ ሲይዛቸውና በደዌ ሲሰቃዩ መከራቸውን አዩ እንላለን፡፡ ያላቸውን ሲያጡና ኪሣራ ሲደርስባቸው ሌላው ቀርቶ ሲርባቸውና ሥራ ሲበዛባቸው እንኳን ተሰቃዩ መከራቸውን አዩ ይባላል፡፡

በሰሙነ ሕማማት የምናስበው የኢየሱስ ክርስቶስ መከራ ከላይ ለሰው ልጆች ከጠቀስነውና ከተለመደው ዓይነት መከራ ይለያል፡፡ የተለየ ጊዜ ተወስኖለት ሰሙነ ሕማማት፣ ሕማማተ መስቀል፣ ሕማማተ ክርስቶስ ወዘተ እያልን በተለየ መንገድና ሥርዓት የምንገልጽውም ልዩ መከራ ስለሆነ ነው፡፡

ሕማማት የምንለው ኢየሱስ ክርስቶስ በእደ አይሁድ የተቀበለው የሐሰት ክስ፣ ፍርድ፣ መጎተት፣ መገረፍ፣ መገፈፍ፣ እርግጫ፣ ጥፊ፣ ጡጫ፣ ችንካር በአጠቃላይ በበርካታ ድርሳናት የተገለጠው አይሁድ የፈጸሙበትን ግፍ ሁሉ ነው፡፡ የአምላካችንና የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ መከራ በዓላማው፣ በአፈጻጸሙ፣ በመጠኑ፣ በምክንያቱ በአጠቃላይ በሁሉም መልኩ ከሰው ልጆች መከራ ጋር አይመሳሰልም፡፡

ነቢዩ ኢሳይያስ ወልደ እግዚአብሔር ኢየሱስ ክርስቶስን ‹‹የሕማም ሰው ደዌንም የሚያውቅ ነው፡፡›› ይለዋል፡፡ (ኢሳ53.3) ኢየሱስ ክርስቶስ መከራ የተቀበለው ስለእኛ ሲል ነው፡፡ በእኛ ላይ መድረስ የነበረበትን መከራ ሁሉ እርሱ ተሸከመልን፡፡ የእኛን ሞት ተቀብሎ የእርሱን ሕይወት ለእኛ ሰጠን፡፡ ይህን ሲያስረዳን ነቢዩ ኢሳይያስ‹‹ሕመማችንንም ተሸክሞአል፡፡›› በማለት ጻፈልን፡፡ (ኢሳ53.4) ኢየሱስ ክርስቶስ መከራን የተቀበለው በፈቃዱ ነው፡፡

ኢየሱስ ክርስቶስ በፈቃዱ መከራን ተቀበለ ማለት ግን ግድሉኝ፣ ቸንክሩኝ አላቸው ማለት አይደለም፡፡ አይሁድ መከራ ሲያደርሱበት እነርሱን መቃወም፣ ማጥፋት፣ ወይም እንዳያገኙት ማድረግ ሲችል መከራን ተቀበለ ማለት ነው፡፡

ኢየሱስ ክርስቶስ እርሱ ስለ እኛ ብሎ የተቀበለውን መከራ እንድናስብ ይፈልጋል፡፡ ይህንንም አማናዊ ሥጋውንና ደሙን በሰጠን ጊዜ ‹‹ይህን ለመታሰቢያዬ አድርጉት›› በማለት አጽንቶ አዞናል፡፡ (ሉቃ22.19) ቅዱስ ጳውሎስ ስለ ሥጋውና ደሙ ባስተማረበት አጭር አንቀጽ ውስጥ ‹‹ለመታሰቢያዬ አድርጉት›› ያለውን ደጋግሞ የጠቀሰው ስለዚህ ነው፡፡ (1ቆሮ11.24፤ 1ቆሮ11.25) ሥጋውና ደሙ በመከራው ጊዜ የተሰጠን የሕይወት ስጦታ ነው፡፡ ስለዚህ በሥጋውና በደሙ መከራውን እናስባለን፡፡ ይህን ለማዘከር ቅዱስ ጳውሎስ‹‹ሥጋውን በበላችሁ ደሙን በጠጣችሁ ጊዜ ዕለት ዕለት ሞቱን ትናገራላችሁ››በማለት ጽፎልናል፡፡

በነገራችን ላይ ‹‹ዕለት ዕለት ሞቱን መናገር›› ማለት ሕማሙን ማሰብ ማለት ነው፡፡ ‹‹መናገር›› በመጽሐፍ ቅዱስ አስተምህሮ መሠረት ‹‹ማሰብ›› ሆኖ የሚተረጎምበት ጊዜ አለ፡፡ ሰው የሚናገረው የሚያስበውን ነውና፡፡ የልብ ሐሳብ በንግግር የሚገለጥ ስለሆነ መናገር የሐሳብ መገለጫ ወይም መዲና ነው፡፡ ማሰብ መነሻ ሲሆን መናገር መድረሻ በመሆናቸው እንደ አንድ ይታያሉ፡፡ ከዚህ የተነሳ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ማሰብ ለማውሳት ‹‹በልቡ እውነትን የሚናገር›› ይላል፡፡ (መዝ14.2) እስኪ መለስ ብላችሁ ጥቅሱን አስተውሉት ልብ ያስባል እንጂ ይናገራልን? ነገር ግን መናገር ከማሰብ ጋር ያለውን ጥብቅ አንድነት ለማሳወቅ መጽሐፍ ቅዱስ ቃላቶቹን በዚህ መንገድ አዘዋውሮ ይጠቀምባቸዋል፡፡ ሆነ ተብሎ እንጂ በስሕተት የተጻፈ እንዳልሆነ ልብ ይበሉ፡፡

ቤተ ክርስቲያን እነዚህን የመጽሐፍ ቅዱስ ቃላት አክብራ በመያዝ ዘወትር በቅዳሴ ሥጋውና ደሙን እያዘጋጀች ‹‹ንዜኑ ሞተከ እግዚኦ - አቤቱ ሞትህን እንናገራለን፡፡›› ትላለች፡፡ ‹‹አቤቱ ሞትህን እንናገራለን›› ማለትም ሁለት ዓይነት አፈታት አለው፡፡ አንዱ ግልጽና ቀጥተኛ ሲሆን ለሌላ ሰው ስለ ሞትህ እናውጃለን ማለት ነው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ በላይኛው አንቀጽ እንደተረዳነው ሞትህን እናስባለን ማለት ነው፡፡

ቅዱስ ጳውሎስ እንደተናገረው አዚም ያለበት ሰው ካልሆነ በስተቀር እውነተኛ ክርስቲያን በልቡ ኢየሱስ ክርስቶስን እንደተሰቀለ ሆኖ ዘወትር ይመለከተዋል፡፡ (ገላ3.1) የአምላካችንን ሕማማት የምናስበው በቅዱስ ቃሉ መሠረት ‹‹ዕለት ዕለት›› ወይም ዘወትር ነው እንጂ በአመት ለአንድ ሳምንት ብቻ አይደለም፡፡

ለምሳሌ፡- የረቡዕና የዐርብ አጽዋማት የሕማማቱ መታሰቢያ ናቸው፡፡ በአንድ ዕለት ውስጥ የተመደቡት ሰባት የጸሎት ክፍለ ጊዜያት የሕማማቱ መታሰቢያ ሰዓታት ናቸው፡፡ እኩለ ሌሊት የተያዘበት፣ ማለዳ ለፍርድ የቆመበት፤ ሠለስት የተገረፈበት፣ እኩለ ቀን የተሰቀለበት፣ ዘጠኝ ሰዓት ቅድስት ነፍሱን ከክቡር ሥጋው በፈቃዱ የለየበት፣ ሠርክ ወደ መቃብር የወረደበት ሰዓታት በመሆናቸው ለሕማሙ መታሰቢያና ለጸሎት ጊዜነት ተመድበዋል፡፡

ይህም ብቻ አይደለም ቤተ ክርስቲያን ከሕማማቱ ጋር ያልተዛመደ ሥርዓት የላትም ማለት ይቻላል፡፡ ከበሮ፣ ጸናጽል፣ መቋሚያ ከሕማማቱ ጋር የተያያዘ ምሳሌነት አላቸው፡፡ ሁሉንም በዚህ ቦታ ማተት ጊዜ ይወስዳል፡፡ በምንዘምርበት ጊዜ ስናጨበጭብ በጥፊ መመታቱን፣ ስናሸበሽብ ደግሞ ወዲህ ወዲያ መንገላታቱን ወዘተ እያመላከትን ነው፡፡

ማኅሌቱ፣ ቅዳሴው፣ ሰዓታቱ፣ ዑደቱ ሁሉ ሕማማቱን እንድናስብ የሚያደርጉ ናቸው፡፡ በአጠቃላይ የቅዱስ ያሬድ መጻሕፍት፣ ዜማዎቹ፣ የዜማው ምልክቶች የኢየሱስ ክርስቶስን ሕማማት ለማሰብ በሚያግዝ መንገድ የተዘጋጁ ናቸው፡፡ የሕንጻ ቤተ ክርስቲያን አሠራርም ሕማማቱን ያዘክራል፡፡ በውስጥና በውጭ እንዲሁም በጉልላቱ ላይ መስቀል ማኖር ሕማማቱን እንጂ ሌላ ምን ያሳስባል? ከዚህም በተጨማሪ በቤተ ክርስቲያን ሕማማቱን የሚያሳስቡ ቅዱሳት ሥዕላት በየመልኩ ተስለው ይሰቀላሉ፡፡

ከዚህ ሁሉ በተጨማሪ ቤተ ክርስቲያን የጌታችችን ሕማማት የምታስብበት ልዩ ሳምንት እና ልዩ ሥርዓት አላት፡፡ ወቅቱ ከዐቢይ ጾም ጋር ተያይዞ ባለው የመጨሻው ሳምንት ሲሆን ‹‹ሰሙነ ሕማማት›› ይባላል፡፡

የሕማማት ሳምንት የሚታወቅበት ልዩ ሥራ ደግሞ ጾም፣ ጸሎት፣ ስግደትና መጻሐፍትን ማንበብ ሲሆን ይህም ‹‹ግብረ ሕማማት›› ይባላል፡፡ በሰሙነ ሕማማት ሊሠራ የሚገባው ሥራ ማለት ነው፡፡ ይህን ሥርዓት ለማካሄድ የሚረዳው የቤተ ክርስቲያን መጽሐፍ እንደ ግብሩ ‹‹ግብረ ሕማማት›› ተብሏል፡፡

የጌታችን የመከራው መታሰቢያ እንዲደረግ የመጽሐፍ ቅዱስ ትእዛዝ መሆኑን ከላይ አብራርተናል፡፡ ያ ደግሞ እንዲሁ በዘፈቀደ የሚደረግ አይደለም፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ‹‹ሁሉ በአግባብና በሥርዓት ይሁን›› ይላልና፡፡ (1ቆሮ14.40) ቤተ ክርስቲያን በግብረ ሕማማት መጽሐፍ መሠረት ሕማማቱን የምትዘከረው በዚህ ምክንያት ነው፡፡

‹‹እንበለ ደዌ ወሕማም እንበለ ጻማ ወድካም አመ ከመ ዮም ያብጽሐኒ ወያብጽሕክሙ እግዚአብሔር በሰላም፡፡›› አሜን!



በዲያቆን ኅብረት የሺጥላ
E-mail - hibretyes@yahoo.com

No comments:

Post a Comment