Sunday, 16 February 2014

የቤተክህነቱ የእግድ "ቀጭን" ትእዛዝ ምን ያመለክተናል?

ከመለሰ ዘነበወርቅ

በዚህ ሳምንት ማህበረ ቅዱሳን ከ200 በላይ የአብነት ት/ቤቶች መምህራንን ከተለያዩ የሃገር ውስጥና ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ተወካዮች ጋር በመሆን በችግሮቻቸው ዙሪያ እንዲሁም ለቤተክርስቲያን በሚያበረክቱት ግልጋሎት ላይ ለመምከር ያዘጋጀውን ጉባኤ ከፓትሪያርክ አቡነ ማትያስ በተላከች አንዲት ደብዳቤ ሊታገድ ችሏል። ለመሆኑ ይህ እግድ ምን ይነግረናል?
1ኛ. የመጀመሪያው እና ዋናው ነገር በቤተክህነቱ ውስጥ ምን ያክል አምባገነናዊነት እንደነገሰ ያሳየናል።
ማህበሩ በድምጸ ተዋህዶ ሬድዮ ፕሮግራሙ እንዳሳወቀን በዚህ ዓመት ጉባኤውን እንደሚያካሂድ በአመታዊ እቅዱ ውስጥ እንዳካተተና በአመቱ መግቢያ ላይ ለሚመለከተው የቤተክህነቱ አካል አሳውቋል። ቤተክህነቱ በወቅቱ ይህን ማህበሩ ማከናወን እንደማይችል ማሳወቅ ይችል ነበር። ለወራት ያለምንም ተቃውሞም ሆነ አስተያየት ከቆየ በኋላ ጊዜው ሲደርስና ማህበሩም ለዝግጅቱ ከፍተኛ ወጪ ካወጣበት በኋላ ሰዓታት ሲቀሩት የእግድ ደብዳቤ ማስጠት ከአምባገነንነትም በላይ ነው። ያሳዝናል! ያሳፍራልም!

2ኛ. ቤተክርስቲያንን እንደመዥገር ተጣብቀዋት አላንቀሳቅስ ያሉ ሰዎች አሁን ደሞ ፓትርያርኩን እንደከበቧቸው ያሳየናል። ይህ ጉባኤ ምን ያህል ቤተክርስቲያንን እንደሚጠቅም የቤተክህነቱንም ስራ እንደሚያግዝ ሆን ተብሎ በነዚህ ሰዎች ፓትርያርኩ እንዳያውቁ ተደርጓል ወይም የተንሻፈፈ መረጃ እንዲደርሳቸው ሆኗል። ይህ ደሞ ከማህበሩ ጋር ፓትርያርኩን ለማጋጨት ሆን ተብሎ የተዘየደ እንደሚሆን ግልጽ ነው።

3ኛ. በቤተክህነቱ ውስጥ ህገ ወጦች ምን ያክል እንደነገሱበት ያሳየናል። በመሰረቱ የቅዱስ ፓትሪያርኩም አሿሿም አወዛጋቢነቱን ለታሪክ አስረክቦ ተጨማሪ ታሪኮችንም እየጻፈ እንደሚገኝ ማስታወሱ መልካም ነው። ማህበሩ ጉባኤውን እንደሚያዘጋጅ ከወራት በፊት በተገቢው ህጋዊ መንገድ ከማሳወቁም በላይ ወቅቱም ሲደርስ ለቤተክህነቱ ሃላፊዎች በተገቢው ህጋዊ መንገድ አሳውቋል። ሆኖም ግን በተመሳሳይ ወቅትና ህጋዊ መንገድ ማገድም ካስፈለገ በምክንያት ማገድ ሲቻል ሰአታት ሲቀሩት እግድ ደብዳቤ ማውጣት የቤተክህነቱ ሃላፊዎች ምን ያክል በህግ እንደማይመሩ የሚያመለክት ነው።

4ኛ. ቤተክህነቱን የወረሩት ወሮበሎች ጦርነታቸት ከማህበሩ ጋር ብቻ እንዳልሆነ የሚያሳይ ነው። ይህ ጉባኤ ቢካሄድ ጥቅሙ "ማህበሩ አዘጋጀ" ከመባል ውጪ የማህበረ ቅዱሳን እንዳልሆነ ለማናችንም ግልጽ ነው። በጉባኤው ላይ የተገኙትም አባቶች ኪሳቸውን አያደልቡበትም ይልቁንም ቤተክርስቲኗ ለዘመናት መፍታት ያልቻለችውን የልማት ችግር እንደሚያግዝ ሰው የሆነ ሁሉ ሊረዳው የሚችል ጉዳይ ነው። ስለዚህ በአባ ሰረቀ አቀነባባሪነት የተሰራው ይህ ወንጀል ሰዎቹ ምን ያክል የቤተክርስቲያን ጠላትነታቸውን ያሳዩበት ገጠመኝ ነው።

ቤተክርስቲያንን ለማፍረስ የሚራወጡ ሰዎች ለዘመናት መልካቸውን እየቀያየሩ ሲያስቸግሩ ኖረዋል ወደፊትም ይኖራሉ። አሁን በእኛ ዘመን ደሞ እነዚ መጥተዋል እኛም ስለ ማንነታቸውም ሆነ ስለሚሰሩት አፍራሽ ተግባራት በንቃት መከታተል ስናውቅ ደሞ ላላወቁ የማሳወቅ ግዴታ አለብን። እግዚአብሄር አምላክም ከቤተክርስቲያን ጋር ነውና መጥፋታቸው እውነት ነው።

No comments:

Post a Comment