ከመብራቱ ጌታቸው
ከፌስቡክ ገጽ ላይ የተወሰደ
"ዘርህ ማነው?" ይሉኛል ፡ እኔ ግን የክርስቲያን ዘሩ ምንድን ነው? እላቸዋለሁ፡፡ "አማራ ነህ ?" ይሉኛል ፡ አዋ አማራ ወገኔ ነው እላቸዋለሁ።
"ትግሬ ነህ?" ይሉኛል ፡ አዋ ትግሬም ወገኔ ነው እላቸዋለሁ ፤ "ኦሮሞ ነህ?" ይሉኛል ፡ አዋ ኦሮሞም ወገኔ ነው እላቸዋለሁ። ለትግሬማ አድልቼ አማራን ጎድቼ ቢሆን ለአፍንጫየ አድልቼ አይኔን እንደማጥፋት በቆጠርኩኝ። ለአማራም አድልቼ ኦሮሞን ጎድቼ ቢሆን ለቀኝ እጄ አድልቼ ግራ እጄን እንዳማስቆረጥ በቆጠርኩኝ፡፡
ነገር ግን እኔ ክርስቲያን ነኝ። ክርስቲያንም ለመሆን ውዴታ አለኝ ፡ ክርስቶስንም ስለመምሰል ስራ አለብኝ። እንግዲህ አቡነ ተክለሃይማኖት ምናዊ ናቸው? እኔ ግን አቡነ የተክለሃይማኖት ልጅ ነኝ። ይህን እምነቴን የሚወስድብኝ አንዳች እንኳን ሃይል የለም ፤ ወይንስ አቡነ ሃብተ ማርያም ምናዊ ናቸው? እኔም የአቡነ ሃብተ ማርያም ልጅ ነኝ! ይህን እምነቴን የሚቀማኝ አንዳች እንኳን ሃይል የለም ፤ ወይንስ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ምናዊ ናቸው? እኔም አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ልጅ ነኝ ፡ ይህን እምነቴንም የሚቀማኝ አንዳች እንኳን ሃይል የለም፡፡ ስለክርስቶስ ፡ በክርስቶስ ፡ ለክርስቶስ ልጃቸው ሆንኩኝ ፡ እኔም ስለዚህ በክርስቶስ የሆነ ሁሉ ወንድሜ ፡ እህቴ ፡ አባቴም እናቴም ነው።
ከክርስትናየ ይልቅ ትግራዋይነቴ በልጦ ከሆነ ከክርስትናየ ይልቅ አማራነቴ አኩርቶኝ ከሆነ ፡ ከክርስትናየ ይልቅ ኦሮሞነቴ አይሎ ከሆነ እስካሁን በጨለማ እጓዛለሁ፡ የክርስትናውንም ብርሃን አላየሁም ፡፡
ነገር ግን እኔ በክርስቶስ የሁሉ ዘመድ ነኝ! ኢትዮጵያም ርስቴ ናት ፡ ኢትዮጵያውያንም ወገኖቼ ናቸው፡፡ አንዷን ክርስትናየን እወዳታለሁ ፡ አንዷ ኢትዮጵያዊነቴንም እወዳታለሁ፡፡ ክርስትና አንድ እንደሆነች ፡ ግማሽ መሆንም እንደማይስማማት ፡ ኢትዮጵያም አንድ ናት ፡ ጎዶሎ መሆን አይስማማትም፡፡
የክርስቶስም ሃሳብ ሁሉን አንድ አድርጎ በፍቅር ማኖር ሲሆን የዲያቢሎስ ሃሳብ ግን ሁሉን ከፋፍሎ እያናከሰ ማጋደል ነው፡፡ ነገር ግን እንደምን የብርሃን ልጆች በጨለማ ሰባኪዎች ይመራሉ?
እንደምን የፍቅር ክርስቶስ ልጆች ከጥላቻ አስተማሪወች ጋር ይተባበራሉ? ህይወት ነውና ወደክርስቶስ እንቅረብ ፡ የማይጠቅም ተራ ነውና ዲያቢሎስንና ሃሳቡን ግን እንቃወመው፡፡
No comments:
Post a Comment