Monday, 25 November 2013

………... ጾምን ቀድሱ ………….
                                                                                                                     በገጣሚ ልዑል ገ/እግዚአብሄር
                                                                                                                     ከፌስቡክ ገጹ ላይ የተወሰደ


የሥጋ አውታሩ በዝንጥል ይመታል 
ዕለታዊ ምቱ .... በሆድ ተጎብኝቷል 
አፍለኛ ንጣቴን ሽበት አድክሞታል 
በሥጋ ላይ በዝቶ ሥጋን አግምቶታል!

ሆዴን ሳበዛበት “ልተኛ ልተኛ” ይለኛል 
ሸክሙን ስነሳው .... ተጣፍቶ ይቀለኛል 
ያ ልብላህ ያልሁት ሥጋ ጥርስ ሰርቶ ነክሶኛል 
በስድሳ ሰማንያ ሸውዶ ...... መቃብር ከቶኛል! 

Tuesday, 5 November 2013

ሰኮናቸው ያልተሰነጠቀና የማያመሰኩ እንስሳት (የዘመናችን ተሐድሶዎች)(የመጨረሻ ክፍል)

ሠለስቱ ደቂቅን ያዳናቸው ማን ነው ?
በዲ/ን ብርሃኑ አድማስ

ታዲያ ሠለስቱ ደቂቅን ያወጣቸው ማን ነው? ለሚለው የተሐድሶዎች ጥያቄ የቀረበ መልስ
መጀመሪውንም መጽሐፍ ቅዱሱ ገብርኤል ነው አይልም፡፡ መጽሐፍ ቅዱሱ የሚለው የሚከተለውን ነው፤ ‹‹ የዚያን ጊዜም ንጉሡ ናቡከደነፆር ተደነቀ ፈጥኖም ተነሣ አማካሪዎቹንም፤ ሦስት ሰዎች አስረን በእሳት ውስጥ ጥለን አልነበረምን? ብሎ ተናገራቸው። እነርሱም፦ ንጉሥ ሆይ፥ እውነት ነው ብለው ለንጉሡ መለሱለት። እርሱም፦ እነሆ፥ እኔ የተፈቱ በእሳቱም መካከል የሚመላለሱ አራት ሰዎች አያለሁ፤ ምንም አላቈሰላቸውም የአራተኛውም መልክ የአማልክትን ልጅ ይመስላል ብሎ መለሰ ›› /ዳን 3 ፤ 24 -25/ ፡፡ በዚህ ገለጻ መሠረት አራተኛውን ያየው ንጉሡ ናቡከደነጾር ነው፡፡ እርሱም አየሁ ያለው አራተኛ ሰው ነው፡፡ የጨመረበት ቢኖር አራተኛው የአማልክትን ልጅ ይመስላል የሚለውን ነው፡፡ ለመሆኑ አራተኛውን ሰው እርሱ ብቻ ለምን አየ ? ሌሎቹ ለምን አላዩም ? አንደኛው የጥያቄው ቁልፍ ምስጢር ያለው እዚህ ላይ ነው፡፡ እውነቱን ለመናገር ይህ ሰው ጥንቱንም ሠለስቱ ደቂቅን ወደ እሣት የጣለው ራሱን ምስል አቁሞ ለምስሉ ሕዝቡን በማሰገድ ራሱን አምላክ አድርጎ ሊያስመልክ ነበር፡፡ ታዲያ ራሱንና እርሱን የመሰሉትን አምላክ አድርጎ የሚቆጥር ከሆነ የሚያየውን አራተኛውን ሰው ‹‹ የእኛን ልጅ ይመስላል ወይም እኛን ይመስላል›› ለምን አላለም? ከዚያ ይልቅ አርቆ ሌሎች አማልክትን የሚያመልክ አስመስሎ ‹‹ የአማልክትን ልጅ›› ይመስላል ያለበት ምስጢር ምንድን ነው ? ይህን ያለበት ምክንያቱ ያየው ነገር አራተኛው አካል ከህልውና ያለው በዘር በሩካቤ የተወለደ ሰው እነርሱ ሳያዩት እሳቱ ውስጥ ገብቶ ሳይሆን ነገሩ መገለጥ ስለሆነ ነው፡፡

የሌለውን ፍለጋ - ክፍል ሁለት (ለተስፋዬ ገ/አብ የተሰጠ ምላሽ)

በዲ/ን ዳንኤል ክብረት

በይምርሐነ ክርስቶስ ጣራ ላይ የሚገኘው የዳዊት ኮከብ

ባለፈው ሳምንት ተስፋዬ ገብረ አብ አቡነ ተክለ ሃይማኖትን በተመለከተ ያነሣቸውን ነጥቦች ማየት ጀምረን ‹የሦስቱን ተክለ ሃይማኖቶች› ጉዳይ ለዛሬ አቆይተነው ነበር፡፡ እንቀጥል፡፡

1) የሰባተኛው መክዘ ተክለ ሃይማኖት

ተስፋዬ የጠቀሳቸው የሰባተኛው መክዘ ተክለ ሃይማኖት የሉም፡፡ እስካሁንም እንደርሱ ፈጠራቸውን የሚናገሩ እንጂ ማስረጃ ያመጡ አልተገኙም፡፡ ይህንን ነገር መጀመሪያ ያነሣው የግብጽ ቤተ ክርስቲያን ገድለ ተክለ ሃይማኖትም ስለ ጽላልሽ (ኢቲሳ) ተክለ ሃይማኖት እንጂ ስለ ሰባተኛው መክዘ ሌላ ተክለ ሃይማኖት አይናገርም፡፡ ገድለ ተክለ ሃይማኖትን በተመለከተ ልዩ ልዩ ቅጅዎች ቢገኙም ሁሉም ግን በተወለዱበት ቦታ፣ በተወለዱበት ዘመን፣ በወላጆቻቸው ስም፣ በሠሯቸው ሥራዎችና በገዳማቸው ላይ የሚተርኩት ታሪክ ተመሳሳይ ነው(Encyclopedia Aethiopica, Vol., IV,.P.833) በአንድ ወቅት ታላቁን የታሪክና የኢትዮጵያ ጥንታውያን መዛግብት ሊቅ ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌን ስለዚህ ጉዳይ ስጠይቃቸው ‹አለኝ ያለ ማስረጃውን ያምጣ፣ የለም የምንለው ፈልገን ልናመጣ አንገደድም›› እንዳሉት አለን የሚሉት እስኪያመጡ ድረስ የምናውቀውን ይዘን እንቀጥላለን፡፡

Sunday, 3 November 2013

ሰኮናቸው ያልተሰነጠቀና የማያመሰኩ እንስሳት (የዘመናችን ተሐድሶዎች)

ሠለስቱ ደቂቅን ያዳናቸው ማን ነው ለሚለው የተሐድሶዎች ጥያቄ የቀረበ መልስ
በዲ/ን ብርሃኑ አድማስ

ሰሞኑን በተለይ በርከት ባሉት በመጽሐፈ ገጽ ወዳጆቼ በኩል  ‹‹ ሠለስቱ ደቂቅን ያዳናቸው ማን ነው? ›› የሚል ጥያቄ በተደጋጋሚ ቀርቦልኛል፡፡ በተሐድሶዎች በተሰራጨ አንድ የቪዲዮ ቁራጭ ላይ በሦስቱ ድርሳናት ማለትም በድርሳነ ገብርኤል ላይ ገብርኤል ፤ በድርሳነ ሚካኤል ላይ ሚካኤል ፤ በድርሳነ ራጉኤል ላይ ደግሞ ራጉኤል አዳናቸው ተብሎ ስለተገለጸ ትክክሉ የቱ ነው፤ በርግጥ ያዳናቸውስ ማን ነው የሚል ነው፡፡ በዚያም ጊዜ ሆነ ዛሬ ከአንዳንዶቹ መልእክት እንደተረዳሁት የድንጋጤ ስሜትም የተሰማቸው አሉ፡፡ ይህን ሌሎች ተመሳሳይ ድርጊቶችንም ስመለከት ለጉዳዩ ቢያንስ አንዲት ትንሽ መጣጥፍ እንዳአቅሜ  እንኳ ለጊዜው መስጠት እንዳለብኝ ስለተሰማኝ ጥያቄውን ለላካችሁልኝ ሁሉ ይህችን መቆያ እንካችሁ ብያለሁ፡፡ ዋናው ወይን ሁልጊዜም ወደ ኋላ መምጣቱ አይቀርምና እርሱን አብረን ከወይን አዳዩ እንጠብቃለን፡፡

ከላይ ያነሣሁትንና ሌሎች ተመሳሳይ ጉዳዮች ብዙ ጊዜ የሚረብሹን ለምንድን ነው ብየ ሳስብ ብዙዎቻችን ወግ ባለውና ለእኛ በሚሆን መንገድ አለመማራችን የመጀመሪያውን ስፍራ ሊይዝ ይችላል፡ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ  ደግሞ በዚህ ጽሑፍ በዋናነት የምንመለከተውን የመሰሉ ጥያቄዎች እያነሡ ገድላትን፤ ድርሳናትንና ሌሎች አዋልድንም የሚነቅፉና የሚያጸይፉ ሰዎች ቁጥራቸው በርከት እያለ መጥቷል፡፡ ከዚህም የተነሣ በተለያዩ ሚዲያዎች የተለያዩ ጽሑፎችና የምስል ወድምፅ ስብከቶች ይቀርባሉ፡፡ በዚህም ስለቅዱሳት መጻሕፍት ትርጓሜ ወይም ምሥጢራት ግንዛቤያችን አነስተኛ የሆነብንን ሰዎች በትንሹም ቢሆን ሊረብሸን ይችላል፡፡እኔም ዝም ብየ በአንዲት ብጣሽ ጉዳይ ላይ ብቻ እንዲህ ነው ወይም እንዲያ ነው ከማለቴ በፊት ነገሩን ከመሠረቱ ለመረዳት እንዲያመቸን ቅዱሳት መጻሕፍት ላይ የሚነሡ ጥያቄዎችን ብቻ ሳይሆን የማንጠየቃቸውንም በአግባቡ ተረድተን እንድንጠቀም የሚረዳውን መንገድ ጠቆም ላድርግ፡፡ ስለዚህ አስቀድመን ቅዱሳት መጻሕፍትን እንዴት ልንረዳ እንደምንችል ላቅርብና በሚቀርበው ጥያቄ ሁሉ ሳንረበሽ መልሱን እንድንጠብቅ ለማመላከት ልሞክር፡፡