Sunday, 24 February 2013

የዕጩዎች ምርጫው እንደፈለጉት ያልሆነላቸው ጳጳሳት ሙግት ገጥመዋል


(ደጀ ሰላም፤ የካቲት 16/2005 ዓ.ም፤ ፌብሩዋሪ 23/2013/PDF)፦ የስድስተኛው  ፓትርያርክ  አስመራጭ   ኮሚቴ  በዛሬው   ዕለት  የዕጩዎቹን  ዝርዝር  ለቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ባቀረበበት ወቅት ምርጫው በፈቀዱት መልክ አልሔደላቸውም የተባሉ ጳጳሳት ሙግት ገጥመው መዋላቸውን የደጀ ሰላም ምንጮች ገለፁ።



አምስቱ እጩዎች  መሆን ያለባቸው ብፁዕ  አቡነ  ማትያስ፣  ብፁዕ  አቡነ  ማቴዎስ፣ ብፁዕ  አቡነ   ዮሴፍ፣ ብፁዕ  አቡነ  ሕዝቅኤል እና ብፁዕ  አቡነ  ኤልሳዕ  ናቸው የሚለውን ውሳኔ አስመራጭ ኮሚቴው ካሰማ  በኋላ  አስተያየት የሰጡት እጩ ፓትርያርክ ብፁዕ  አቡነ ማቴዎስ  “በቀደመው የአበው  ገዳማዊ  ሥርዓት  መሠረት  በዕጩነት መግባት  አይገባኝም።  አባቶቼ  ስለ እግዚአብሔር  ብላችሁ እኔን ተዉኝ” ሲሉ ተሰምተዋል፡፡ ይህንን የትህትና ንግግር  የተመለከቱ አንዳንድ አባቶች “እንዲህ ያለ ትህትና በዚህ ዘመን ማየታችን የሚደንቅ ነው” በማለት ሲናገሩም ተሰምተዋል፡፡ እጩነቱን በአኮቴት እንዲቀበሉ በቅዱስ ሲኖዶስ አባላት ግፊት የተደረገባቸው ብፁዕ አቡነ ማቴዎስ በመጨረሻ  የአባቶችን ቃል አድምጠው በዝምታ ተቀብለዋል ተብሏል፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ ሌሎቹ እጩ ፓትርያርኮችም ተመሳሳይ ሐሳብ  ለማንሳት ቢሞክሩም  በቅዱስ  ሲኖዶስ  አባላት  ግፊት  ጉዳዩን ለመቀበል ተገደዋል፡፡


ይህ በእንዲህ እንዳለ የአስመራጭ ኮሚቴው አሠራር፣ ጥቆማና ውሳኔ ትክክል አይደለም በሚል ከረር ያለ ሐሳብ ያሰሙት ብፁዕ አቡነ ሳሙኤል እና ብፁዕ  አቡነ አብርሃም  በየተራ  ባደረጉት ንግግር በተለይ በብፁዕ  አቡነ  ማትያስ  ለዕጩነት  መቅረብ ላይ ያላቸውን ተቃውሞ አሰምተዋል፡፡ ሊቃነ ጳጳሳቱ እንደተናገሩት የብፁዕ  አቡነ ማትያስ ዜግነት ጉዳይ ዕልባት ሳያገኝና ነገሩም በሥርዓቱ ሳይጣራ ከዝርዝሩ ውስጥ መግባታቸውን ኮንነዋል። አጠቃላይ የምርጫው ሒደት ትክክል አለመሆኑንም ለማስረዳት ሞክረዋል ተብሏል።


የሁለቱን አባቶች ተቃውሞ ያልተቀበለው ምልዓተ ጉባዔው ይህን ጥያቄ በዚህ ሰዓት ማንሳታቸው ተገቢ አለመሆኑን፣ “ትናንት ምርጫው እንዲካሔድ ስታቻኩሉ የነበራችሁ እናንተ ናችሁ፡፡ ‘ይዋልና ይደር፣ ጉዳዩን በጥሞና እንመልከተው’ ስንላችሁ አይሆንም ብላችሁ አጣደፋችሁት፡፡ አሁን ስምንት መቶ መራጭ መንገድ ከጀመረ በኋላ፣ የውጭ እንግዶች   እየተጠባበቅን ባለንበት ሁኔታ እንዲህ ያለ ግርግር ማንሳት ቤተ ክርስቲያኒቱን  ማዋረድ ነው” የሚል መልስ እንደተሰጣቸው ምንጮቻችን ገልጸዋል፡፡


ተክለ-ስብዕናቸውን በመገንባት፣ የትምህርት ደረጃቸውን ከፍ በማድረግ፣ የመንፈሳዊ ኮሌጅ ተማሪዎችን በማስተባበር  የምረጡኝ  ቅስቀሳ ላይ  እንደሰነበቱ ሲነገርባቸው የሰነበተው ብፁዕ  አቡነ ሳሙኤል እና እርሳቸውን ለማስሾም ደፋ ቀና እያሉ ነው፣ የአባቶችን እርቅ አኮላሽተዋል የሚል ወቀሳ የሚሰማባቸው ብፁዕ አቡነ አብርሃም ባለቀ ሰዓት የምርጫው ተቃዋሚ ሆነው መቅረባቸው “የሚያስቡት ለቤተ ክርስቲያኒቱ  ሳይሆን  ለራሳቸው ነው” የሚል አስተያየት እንዳሰጠባቸው ደጀ ሰላማውያን ተናግረዋል፡፡


ከዚህ ቀደም 6ኛው ፓትርያርክ ሊሆኑ የሚችሉት ብፁዕ አቡነ ማትያስ ዘኢየሩሳሌም ናቸው የሚለውንቅድመ ትንበያ ምንጮችን ጠቅሳ ዘገበችው ደጀ ሰላም አረጋዊው አባት ለፓትርያርክነት ቢበቁ ከትህምርትም፣ ከመንፈሳዊነትም፣ ከብስለትም፣ ከልምድም አንጻር የሚበዛባቸው እንደማይሆን ትረዳለች። ዛሬ የተነሣባቸው ተቃውሞም “ይህ ይጎድላቸዋል” ከሚል አንጻር ሳይሆን ከዜግነት ጋር በተገናኘ ነው።


በአንዳንድ መገናኛ ብዙኃን የተሐድሶ ቀንደኛ ተከታዮች ከሆኑት ከነ አባ ሰረቀ ጋር ተገናኝቶ የተዘገበባቸውም ሐሰት መሆኑ አረጋዊው አባት የጥቃቱ ሰለባ የሆኑበትን ምክንያት እንድንመረምር ያደርገናል። ደጀ ሰላም ባለፈው ጽሑፏ እንዳለችው ምእመናን ቅዱስ አባታችን ብለው በሙሉ ልብናበፍቅር የሚታዘዙት አባት ይፈልጋሉ” በርግጥም። ይህንን ለማግኘት ደግሞ በቂም በቀል እና የራስን ደጋፊ በማስሾም ሳይሆን ለቤተ ክርስቲያን የሚበጀውን በመሻት መሆን አለበት። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እያየን ያለነው ግርግር ግን ቤተ ክህነቱ እና ጥቅመኛ ቡድኖች እንዴት መስመር የለቀቀ መንገድ እየተከሉ መሆኑን የሚያመለክት ነው።


ዞሮ ዞሮ የሚሰየመው አባት የቤተ መንግሥቱ ይሁንታ (ኢንዶርስመንት) ያለው፣ ቀድሞ ያለቀ ነገር፣ የተበላ ዕቁብ መሆኑን መዘንጋታቸው ግን ገርሞናል። አሁን ደርሶ ምርጫው ይሸጋገር ማለት ራሳቸው በጀመሩት ጨዋታ መሐል ላይ ደርሶ “ይቋረጥልን” እንደማለት ይሆናል። የቤተ ክርስቲያኒቱ አንድነት እንዳይመጣ ተግታችሁ ሰርታችኋል። አንድነቱ ሲቀበር የመጨሻውን ምስማር የመታችሁትን አትርሱት። ተሳክቶላችኋል። ያቺ ያለማችኋትን “ወንበር” ግን ተሸውዳችኋል።


በዛሬው ጉባዔ ተቃውሞ በብርቱ የቀረበባቸው አረጋዊው ብፁዕ አቡነ ማትያስ ዘኢየሩሳሌም ጉዳዩን በዝምታ ማለፍ መርጠዋል፡፡ ውይይቱ በዚህ መልኩ  ከተከናወነ በኋላ አምስቱ እጩዎች ጉዳይ የተጠናቀቀ ሲሆን ሰኞ በፊርማ ይቋጫል ተብሏል። ቅ/ሲኖዶሱ ካጸደቀው ዘንዳ የሚቀረው የምርጫውን ሒደት ለሕዝብ ይፋ ማድረግ እንደሚሆን ይጠበቃል፡፡ ድራማው ይቀጥላል!!!!!


ቸር ወሬ ያሰማን፣ አሜን

No comments:

Post a Comment