Tuesday, 26 February 2013

የ5ቱ እጩ ፓትርያርኮች አጭር የሕይወት ታሪክ


PDF http://bit.ly/YwKqd1:- የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን 6ኛውን ፓትርያርክ ለመምረጥ በዝግጅት ላይ እንደምትገኝ ይታወቃል፡፡ በዚህም መሠረት ቅዱስ ሲኖዶስ አስመራጭ ኮሚቴ በመሠየም እጩ ፓትርያርኮችን ለመምረጥ ብፁዐን ሊቃነ ጳጳሳት፤ ከካህናት፤ ከሰንበት ትምህርት ቤቶች፤ ከማኅበረ ቅዱሳን፤ እንዲሁም ከምእመናን ጥቆማ እንዲያካሔዱ ተደርጓል፡፡ በተካሔደው ጥቆማ መሠረት አስመራጭ ኮሚቴው ጥቆማውን በግብአትነት በመጠቀም አምስት ሊቃነ ጳጳሳትን በእጩነት በማቅረብ የካቲት 16 ቀን 2005 ዓ.ም ለቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ አቅርቧል፡፡ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤም ከየካቲት 16 – 18 ቀን 2005 ዓ.ም. ድረስ ውይይት በማካሔድ አምስቱም ሊቃነ ጳጳሳት በእጩነት እንዲቀርቡ አጽድቋል፡፡


የካቲት 21 ቀን 2005 ዓ.ም. ለሚካሔደው የ6ኛው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ የፓትርያርክ ምርጫ የቀረቡት ብፁዐን ሊቃነ ጳጳሳት፡-  ብፁዕ አቡነ ማትያስ በኢየሩሳሌም የኢትዪጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ገዳማት ሊቀ ጳጳስ፤ብፁዕ አቡነ ኤልሳዕ የሰሜን ጎንደር ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፤ ብፁዕ አቡነ ዮሴፍ  የባሌ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፤ ብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤል የምዕራብና የደቡብ አዲስ አበባ፤ የከፋ ቤንች ማጂ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስና የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ፤ ብፁዕ አቡነ ማቴዎስ የወላይታና ዳውሮ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ናቸው፡፡ በዚህም መሠረት አጭር የሕይወት ታሪካቸውን እንደሚከተለው እናቀርባለን፡:


ብፁዕ አቡነ ማትያስ

የቀድሞው የአባ ተክለማርያም ዐሥራት የአሁኑ ብፁዕ አቡነ ማትያስ በ1934 ዓ.ም ተወለዱ፡፡ ቅዳሴ፣ ዜማ፣ ቅኔ፣ ባሕረ ሐሳብ፣ የመጻሕፍተ ሐዲሳት ትርጓሜ ተምረዋል፡፡ በ1948 ዓ.ም ከብፁዕ አቡነ ማርቆስ ዲቁናን ጮኸ ገዳም ተቀብለዋል፡፡ ከመ/ር ዐሥራተ ጽዮን ኰኲሐ ሃይማኖት መአረገ ምንኩስናን አግኝተዋል፡፡ በ1955 ዓ.ም በ1969 ዓ.ም ከብፁዕ አቡነ መቃርዮስ መአረገ ቁምስናን ተቀብለዋል፡፡


በጮኸ ገዳም በቄሰ ገበዝነት፣ በመጋቢነት በልዩ ልዩ ገዳማዊ ሥራ አገልግለዋል፡፡ በገዳሙ ውስጥ በነበራቸው ቆይታ ሐዲስ ኪዳንን አስተምረዋል፡፡ ከ1964 -- 68 ዓ.ም በቅድስት ሥላሴ ካቴድራል በቅዳሴና በልዩ ልዩ አገልግሎቶች ተመድበው አገልግለዋል፡፡ ከ1968 ዓ.ም ጀምሮ ለሦስት ዓመታት የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ተክለ ሃይማኖት አቡነ ቀሲስና ምክትል ልዩ ጸሐፊ በመሆን ሠርተዋል፡፡ ጥር 13 ቀን 1971 ዓ.ም በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ተክለ ሃይማኖት አንብሮተ እድ ብፁዕ አቡነ ማትያስ በኢየሩሳሌም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ገዳም ኤጲስ ቆጶስ ሆነው ተሹመዋል፡፡ በአሁኑ ሰዓትም በኢየሩሳሌም የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ገዳም ሊቀ ጳጳስ ናቸው፡፡




           ብፁዕ አቡነ ኤልሳዕ

 የቀድሞው አባ ኅሩይ ወልደ ሰንበት የአሁኑ ብፁዕ አቡነ ኤልሳዕ በ1930 ዓ.ም ተወለዱ ጸዋትዎ ዜማ፣ ቅኔ፣ ትርጓሜ መጻሕፍት፣ ፍትሐ ነገሥት፣ ባሕረ ሐሳብና ሐዲስ ኪዳንን ተምረዋል፡፡ በ1945 ዓ.ም ከብፁዕ አቡነ ሚካኤል ዲቁና በ1964 ዓ.ም ምንኩስናን በደብረ ሊባኖስ ገዳም ተቀብለዋል፡፡ በ1965 ዓ.ም ከብፁዕ አቡነ ሚካኤል ቅስና በ1969 ዓ.ም ከብፁዕ አቡነ ሰላማ ቁምስናን ተቀብለዋል፡፡ በደብረ ጽጌ ገዳም በመዘምርነትና በቅዳሴ አገልግለዋል፡፡ ጥር 13 ቀን 1971 ዓ.ም  በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ተክለ ሃይማኖት አንብሮተ እድ የከፋ ሀገረ ስብከት ኤጲስ ቆጶስ ተብለው ተሹመዋል፡፡ በአሁኑ ሰዓት የሰሜን ጎንደር  ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ናቸው፡፡


               ብፁዕ አቡነ ዮሴፍ


ነሐሴ  16  ቀን  1944  ዓ.ም  በሰሜን  ሸዋ  ክፍለ  ሀገር  በሸኖ አውራጃ  ልዩ  ስሙ  ጨቴ  ጊዮርጊስ  በተባለው  ቦታ ተወለዱ፡፡ የቀድሞ ስማቸው  ቆሞስ  አባ ኀይለጊዮርጊስ ኀይለ ሚካኤል ይባላል፡፡ ፊደል የቆጠሩት ዜማን የተማሩት ቅኔን የተቀኙት በሀፋፍ ማርያም በኢቲሳ ደብረ ጽላልሽ ገዳም ነው፡፡ ቅዳሴን በዳግማዊ ምኒሊክ መታሰቢያ የቀሳውስት ማሠልጠኛ ት/ቤት ተምረዋል፡፡ በሰዋሰወ ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ መንፈሳዊ ት/ቤት ለ4 ዓመታት ተምረው በዲፕሎማ ተመርቀው ዘመናዊ ት/ርታቸውን እስከ 12ኛ ክፍል በማጠናቀቅ በምዕራብ ጀርመን እሸት ኬርከሌ መንፈሳዊ ት/ቤት ስለ ገዳማት አስተዳዳር አጥንተዋል፡፡ ሐምሌ 5 ቀን 1991 ዓ.ም. በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ አንብሮተ እድ ብፁዕ አቡነ ዮሴፍ የምዕራብ ሐረርጌ ሀገረ ስብከት ጳጳስ ተብለው ተሹመዋል፡፡ በአሁኑ ሰአት የባሌ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ናቸው፡፡


ምንጭ፡- ዜና ቤተ ክርስቲያን 31ኛ የዓመት ቁ.3፣ ጥር 4 ቀን 1971 32ኛ ዓ.ም ቁ.4



           ብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤል


የቀድሞ ስማቸው መልአከ ምሕረት አባ ሀብተ ማርያም ይባላል፡፡ ግንቦት 7 ቀን 1946 ዓ.ም በደቡብ ወሎ አማራ  ሳይንት ልዩ ስሙ ደብረ ብርሃን ለንጓጥ ሥላሴ ተወለዱ፡፡ አባታቸው ግራ ጌታ መኮንን ኀይሉ እናታቸው ወ/ሮ አታላይ ደርሰህ ይባላል፡፡ ዜማ፣ አቋቋም፣ ቅኔ፣ ፍትሐ ነገሥት ትርጓሜ ተምረዋል፤ የቅኔ መንገድ ከነአገባቡ ተምረው በመምህርነት ተመርቀዋል በ1956 ዓ.ም ከብፁዕ አቡነ ገብርኤል ዲቁና ተቀብለዋል፡፡


ጳጉሜን 3 ቀን 1981 ዓ.ም በደብረ ሊባኖስ ገዳም ሥርዓተ ምንኩስና ፈጽመዋል፡፡ ኅዳር 12 ቅን 1982 ዓ.ም የቅስና ማዕረግ ከብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ፤ ከብፁዕ አቡነ ቄርሎስ መዓርገ ቁምስና ተቀብለዋል፡፡  ከ1982 – 87 ዓ.ም በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት በደብረ ሰላም ቅዱስ እስጢፋኖስ በጽርሐ ጽዮን ጎላ ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን የመጽሐፍ መምህር ሆነው አገልግለዋል፡፡ ከሠኔ 20 ቀን 1987-1990 ዓ.ም በምሥራቅ ሐረርጌ ሐደሬ ጤቆ መካነ ሥላሴ ደብር፣


ከየካቲት 1990-93 ዓ.ም የድሬዳዋ ደብረ ምሕረት ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን፣ ከሠኔ 1 ቀን 1993 ዓ.ም - ሐምሌ 1 ቀን 1994 ዓ.ም ጀምሮ ለጵጵስና መአርግ እስከ በቁበት ዘመን በአዲስ አበባ ቦሌ ደብረ ምጽላል እግዚአብሔር አብ ቤተ ክርስቲያን አገልግለዋል፡፡ ከሐምሌ 1 ቀን 1994 ዓ.ም የሰሜን ወሎ ደብረ ሮሐ ቅዱስ ላሊበላ ገዳም አስተዳዳሪ ሆነው አገልግለዋል፡፡ ነሐሴ 22 ቀን 1997 ዓ.ም በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ አንብሮተ እድ ብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤል የከፋ ሀገረ ስብከት ጳጳስ ተብለው ተሹመዋል፡፡ በአሁኑ ሰዓት የምዕራብና ደቡብ አዲስ አበባ ፤ የከፋ ሸካ ቤንች ማጂ አህጉረ ስብከት  ሊቀ ጳጳስና የቅዱስ ሲኖዶስ ጸሐፊ ሊቀ ጳጳስ ናቸው፡፡



           ብፁዕ አቡነ ማቴዎስ

በ1955 ዓ.ም በሰሜን ሸዋ በምንጃር ሸንኮራ ወረዳ ልዩ ስሙ ምንታምር ቀበሌ ከአቶ ጌታነህ የኋላሸትና ከወ/ሮ አምሳለ ወርቅ

ማሞ ተወለዱ፡፡


አቋቋም፣ ቅኔ ከነአገባቡ ቅዳሴ ኪዳን አንድምታ፣ ዜማ፣ ሠለስት፣ አርያም፣ ጾመ ድጓ፣ ቁም ዜማ ተምረዋል፡፡ በ1969 ዓ.ም ከብፁዕ አቡነ መቃርዮስ ዲቁና ተቀብለው ቅስና ከብፁዕ አቡነ ሳሙኤል ተቀብለዋል፡፡ በ1975 ዓ.ም በደብረ ዝቋላ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ገዳም ሥርዓተ ምንኩስና ፈጽመዋል፡፡ በሰዋሰው ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ መንፈሳዊ ትምህርት ቤት ለ4 ዓመታት ያህል ተምረው በዲፕሎማ ተመርቀዋል፡፡ በሆላንድ ሆህ እስኩለ የቲዎሎዲ ትምህርት ቤት ገብተው ለ4 ዓመታት ተምረው በቲኦሎጂ የመጀመሪያ ዲግሪ ተቀብለዋል፡፡


በሰሜን ሸዋ ሀገረ ስብከት በሰበካ ጉባኤ አደራጅነት፣ በሰ/ት ቤት ሓላፊነት፣ አ/አ ሀገረ ስብከት ሸሮ ሜዳ መንበረ ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን በሰባኪነት፣ በሐረር ደብረ ገነት መድኀኔዓለም ቤተ ክርስቲያን በአ/አ ሀገረ ስብከት በአቃቂ መድኀኔዓለም በአስተዳዳሪነት በቃሊቲ ቅዱስ ገብርኤል በሳሎ ደብረ ፀሐይ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን በመካነ ሰማዕት ቅዱስ ቂርቆስ ደብርና በሐረር ደብረ ገነት መድኀኔዓለም አብያተ ክርስቲያናት በአስሪተዳዳሪነት አገልግለዋል፡፡ በውጭ ሀገር በአሜሪካ ዳላስ ቅዱስ ሚካኤል በአውሮፓ ሲውዘርላንድ በጀኔሻ፣ በሎዛን፣ በዙሪክና በበርንባዝል ከተሞች ባሉ አድባራት በቀዳሽነትና በሰባኪነት አገልግለዋል፡፡


ነሐሌ 22 ቀን 1997 ዓ.ም በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ አንብሮተ እድ ብፁዕ አቡነ ማቴዎስ የዋግ ሕምራ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ሆነው ተሾሙ፡፡ በአሁኑ ሰዓት የየወላይታና ዳውሮ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ናቸው፡፡


በዲ/ን ኅሩይ ባየ
http://www.eotcmk.org/site/index.php/-mainmenu-24/--mainmenu-26/1217-5http://www.eotcmk.org/site/index.php/-mainmenu-24/--mainmenu-26/1217-5

No comments:

Post a Comment