ይህንን ደብዳቤ ላንቺ የምጽፈው የገናን በዓል ከልቤ የምወደው በዓል ስለሆነ ነው፡፡ የምወደው ደግሞ የገና ዛፍ ተተክሎ፣ በጥጥ ተውጦ፣ በከረሜላ ተከብቦ፣ በመብራትም አሸብርቆ ስለሚያስደስተኝ አይደለም፡፡ እንዲያውም እንዲህ ያለው ነገር ብዙም አይመስጠኝም፡፡ ቤተ ልሔም ዋሻ ውስጥ ለተወለደው ኢየሱስ ክርስቶስ ዛፍ ማሸብረቅ፣ በረዶ አይታ በማታውቅ ሀገር ውስጥ የበረዶ ምሳሌ የሆነውን ጥጥ ማግተልተል፤ ልጇን የምታለብሰው አጥታ የበለሶን ቅጠል ላለበሰች እናት ከረሜላና ኳስ ማንጠልጠል ለእኔ ትርጉሙ አይገባኝም፡፡ መቼም ፈረንጅ መሆን ከሚያስገኛቸው ጥቅሞች አንዱ እርሱ ሲያብድ የሠራውንም ቢሆን ፋሽን ነው ብሎ የሚከተለው አለማጣቱ ነውና ምን ይደረግ፡፡
እኔ የገናን በዓል የምወደው ቤታችን የሚጋገረውን ድፎ ዳቦ፣ በሠፈር የሚታረደውን ቅርጫ፣ በሰሞኑ የሚደረ ገውንም የገና ጨዋታ ብዬ እንዳይመስልሽ፡፡ ምንም እንኳን ባህሉ ደስ ቢለኝ፣ የኔ በመሆኑም ቢያኮራኝ፣ ብዙዎቹ ነገሮች ግን ከታሪክነት ወደ ተረትነት ሊቀየሩ በመዳረሳቸው የኔ ቢጤውን የዚህ ትውልድ ልጅ አንጀቱ ውስጥ አይገቡለትም፡፡ እኔ የተከራየሁባቸው ሰዎች ሁሉ እንኳን ድፎ ዳቦ መድፋትና ሻሂም በኤሌክትሪክ ማፍላት ስለሚከለክሉ እኔ ድፎ ዳቦን በቃል እንጂ በተግባር ረስቼዋለሁ፡፡ በአሁኑ ጊዜ በሬ ገዝቶ ቅርጫ መግባት የባንክ አክስዮን እንደመግዛት ሆኖ ስላገኘሁት፣ ጫጩቶቹን ጭልፊት እንደወሰደበት አውራ ዶሮ ‹ከዐቅሜ በላይ ነው› ብዬ ትቼዋለሁ፡፡ እዚህ ሀገር ቅርጫና ምርጫ እንግዲህ ላይሆንልን ነው መሰል፡፡
የገና ጨዋታ እንጫወትባቸው የነበሩት ሜዳዎች ሁሉ ወይ ኮንዶሚኒየም ተሠርቶባቸዋል፣ ወይ ታጥረዋል፣ ያለበለዚያም ለአንድ ሀብታም ተሰጥተዋል፡፡ በአሁኑ ጊዜ እንኳንስ ባዶ የሆነ ሜዳ ፀጉር ያልበቀለበት መላጣና ትንሽ ዘርጠጥ ያለ ቦርጭም ከተገኘ ቦታው ለግንባታ መዋሉ የማይቀር ነው፡፡ ታድያ የገና ጨዋታ ምናልባት ወደፊት የኮምፒውተር ‹ጌም› ሆኖ ሲመጣ ካልተጫወትነው በቀር በምን ዕድላችን፡፡ ደግሞምኮ ‹በገና ጨዋታ አይቆጡም ጌታ› የሚለው ግጥም ፋሽኑ ስላለፈበትና ‹ጌታም› ስለሚቆጡ፣ ተቆጥተውም የገና መጨዋቻውን ሜዳ ስለወሰዱት ወደፊት አዲስ ግጥም እስኪመጣ ድረስ ሐሳባችንን በይደር አቆይተነዋል፡:
ለእኔ የገና ጨዋታ ከጨዋታዎች ሁሉ የሚበልጥብኝ ከዚህ ሁሉ በተለየ ምክንያት ነው፡፡
መጻሕፍት እንደነገሩን፣ ሊቃውንትም እንዳስተማሩን፣ ሰዓልያንም እንዳቆዩን ኢየሱስ ክርስቶስን ፀንሰሽ ለቆጠራ ከናዝሬት ወደ ቤተ ልሔም በመጣሽ ጊዜ፣ ከተማው በሙሉ ገንዘብና ዘመድ ባላቸው ሰዎች ተይዞ ነበር አሉ፡፡ ይገርማል፤ ከተማ ገንዘብና ዘመድ ባላቸው ሰዎች መያዙ ከጥንት የወረስነው ነው ማለት ነው፡፡ ልክ እንደዚያው ጊዜ ዛሬምኮ ከተማው ገንዘብና ዘመድ ባላቸው ሰዎች ተይዞ እንኳን አዲስ ማደርያ ማግኘት ቀርቶ ዛሬ ባደሩበት ነገ መልሶ ማደርም አልተቻለም፡፡ የሀገራችን ባለ መሬትን ጸሎት መቼም ታውቂዋለሽ፡፡ ‹ከሀብታም ዓይንና ከክፉ መሐንዲስ ሠውረኝ ነው› አሉ የሚለው፡፡ ሀብታምም በዚያ ሲዞር ካየው ይህንን ላልማ ብሎ እንዳይነቅለው፤ ክፉ መሐንዲስም ካላጣው ቦታ በሳሎኑ ላይ የሚሄድ መንገድ ያወጣበት እንደሆነ ቤቱን አፍንጫዋን የተገጨች ቮልስ እንዳያስመስለው እየፈራ ነው፡፡
የሀገራችን ደራሲ አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ ‹ወለተ ነዳያን- የድኾች ልጅ› ብሎሻልና አንቺ ከስንቅ በቀር ምንም ያልነበረሽ በመሆንሽ ማንም ሊያስጠጋሽ አለመፈለጉን መጻሕፍቱ ሁሉ ተባብረው ጽፈዋል፡፡
እኔ መቼም በዚያች በገና ዋዜማ የሚያስጠጋሽ አጥተሽ እንዴት ልትንከራተቺ እንደምትችይ በዓይነ ኅሊናዬ አስበዋለሁ፡፡ ድሮስ ድኻን ማን ያስጠጋዋል፡፡ ድኻ ይሸጣል እንጂ አይገዛም፤ ድኻ ያበላል እንጂ አይበላም፤ ድኻ ያዋጣል እንጂ አይዋጣለትም፡፡
እኔም ታድያ እንዳንቺው ቤት ያጣሁ ከርታታ በመሆኔ እንደ ገና በዓል የምወደው በዓል የለም፡፡ ይኼው በቀደም እንኳን የተከራየሁባቸው ሴትዮ መጡና ‹ልጄ ከውጭ ሀገር ስለምትመጣ ቤቱን በሚቀጥለው ወር እንድትለቅ› አሉኝና ሄዱ፡፡ ሰው ችግሩ ሲጨምር ጸሎቱም በዚያው ልክ ይጨምራል ለካ፡፡ ድሮ ድሮ የዕለት ልብስ የዓመት ጉርስ ብዬ ነበር የምጸልየው፡፡ ዛሬ ዛሬማ የአከራዮቹ ልጅ ከአሜሪካ እንዳትመጣም መጸለይ ሊኖርብኝ ነው፡፡ አንዱን ደላላ እንዲያውም በቀደም አንድ ቤት ሊያሳየኝ ሲል ‹ልጃቸው አሜሪካ ናት ወይስ እዚህ› ብዬ ስጠይቀው ‹ምነው አንተ ውክልና ልትወስድ ነው እንዴ የምትገባው› ብሎ ሳቀብኝ፡፡
ዐለመኛው ቀበሌ ‹‹መታወቂያ ስጠኝ›› ሲሉት ‹‹አድራሻህ የት ነው?›› ብሎ ይጠይቃል፡፡ ደግሞ ድኻ ምን አድራሻ አለው፡፡ እንዳከራዩት ነው፡፡ ዛሬ ቀበሌ አንድ፣ ከሳምንት በኋላ ቀበሌ አሥራ አምስት፣ ከወር በኋላ ደግሞ ጭራሽ ከተማውን ለቅቆ ሊሄድ ይችላል፡፡ እኛኮ በፈጣሪ ፈቃድ ብቻ አይደለም የምንኖረው፣ በአከራዮቻችንም ፈቃድ ጭምር ነው፡፡ ለኛ ለከርታታ ዜጎች ከርታታ ቀበሌ ካልተመሠረተልን በቀር ዜግነታችን ጥያቄ ውስጥ ወድቋል፡፡አንደኛው ቀበሌ ተወልዶ፣ ሌላ ቀበሌ አድጎ፣ ሌላ ቀበሌ ሥራ ይዞ፣ ሌላ ቀበሌ አግብቶ፣ ሌላ ቀበሌ አርግዞ፣ ሌላ ቀበሌ ወልዶ፣ ሌላ ቀበሌ አድጎ፣ ሌላ ቀበሌ ለሚሞት ደኻ ‹‹ቋሚ አድራሻ› እንደሚሊ ቅጽ ያለ ምጸት የለም፡፡
ይኼው ምነው የከብት ጭራ ተከትለው ለሚዘዋወሩ አርብቶ አደሮች የሚዘዋወር ትምህርት ቤት ተከፍቶ የለም እንዴ? እንዴው ድንግል ማርያም በአማላጅነትሽ ምናለ ለኛስ ተዘዋዋሪ ቀበሌ እንዲቋቋምልን ብታደርጊ፡፡ ያለበለዚያ ደግሞ በፌድራል ሥር መተዳደር ነው ያለብን፡፡ ቢያንስ ከሀገር እስክንወጣ፡፡ የቀበሌ መታወቂያ ለማውጣት አድራሻ ስለሌለን በፓስፖርት ብቻ መንቀሳቀስ ይኖርብናል፡፡
የኛ ሠፈር ደላሎች እንኳን በመኪና ስትመጭና በእግርሽ ስትመጭ፣ ዝንጥ ብለሽ ስትመጭና እንደነገሩ ሆነሽ ስትመጭ ፈገግታቸው ይለያል፡፡ የሚከራይ ቤት የኔ ቢጤው ሲጠይቃቸው ‹ዋጋው ውድ ይሆንብሃል እንጂ› ይሉታል፡፡ ይወደድብኝ አይወደድብኝ የኔ ሐሳብ አስፈላጊ አይደለም፡፡ የሰውን ቤት ዋጋ በሚተምኑበት ዓይናቸው አለባበሴንና የሰውነት ይዞታዬን አይተው ዐቅሜን ይተምኑልኛል፡፡ አንዳንዴም ቀለል ካልሽባቸው ‹‹ለማን ነው?›› ይሉሻል፡፡ ተልከሽ የመጣሽ ነው የሚመስላቸው፡፡ እንኳን ደላላው የምትከራይው ግቢ ስትገቢ እንኳን ውሻው በጤና አያይሽም፡፡ አለባበስሽን አይቶ ከሚከራዩት ክፍሎች አንዱን ሳይሆን የርሱን ማደርያ የምትከራዪው ይመስለዋል መሰል ያጉረመርምብሻል፡፡
አንዱን ደላላ እንደምን ተሟግቼ ቤት ሊያሳየኝ ሄደ፡፡ አከራይዋ ሴትዮ መጀመርያ እጄን አዩት፡፡ በኋላ ደላላው እንደነገረኛ ከሆነ መኪና መያዝ አለመያዜን ከያዝኩት ቁልፍ ለማረጋገጥ ነው አሉ፡፡ እንዲያውም በኋላ ለብቻው ጠርተው ‹መዝገብ ቤት ነው አይደል›› ብለው ጠይቀውታል፡፡ ‹‹እንዴት ዐወቁ›› ሲላቸው ‹‹ያዘው ቁልፍ የአሮጌ ቁም ሳጥን ቁልፍ ነው›› አሉት፡፡
ከዚያ ደግሞ ፊቴን አዩት፤ ፊቴን አይተው ሲጨርሱ ከንፈራቸውን መጠጡልኝ፡፡ ‹ወላጅ አልባ› ሕጻን መስዬ ታየኋቸው መሰል፡፡ እኔ ደግሞ ማዘናቸውን አይቼ አይጨክኑብኝም መስሎኝ ፈገግ ስል፣ ኮስተር ብለው ጫማዬን በጎሪጥ ቦረሹት፡፡ ጫማዬን አለማስጠረጌ የቆጨኝ ያኔ ነው፡፡
‹ካንተ ቀደም ብሎ አንድ ሰው መጥቶ ተከራዬው› አሉኝ፡፡ ሰውነቴን ሁሉ ‹ሲቲ ስካን› ካነሡኝ በኋላ የምርመራው ውጤት ይኼው ሆነ፡፡ ተሰናብተን ስንወጣ ደላላውን በዓይናቸው ጠቅሰው ወደ ኋላ አስቀሩት፡፡ እኔም ከግቢው ወጣሁ፡፡ አንድ አሥር ደቂቃ ቆይቶ እየተነጫነጨ መጣ፡፡
‹ምን ዓይነት ሴትዮ ናቸው› ይላል ደጋግሞ፡፡ የሆነውን ይነግረኝ ዘንድ ወጥሬ ያዝኩት፡፡
በመጨረሻ ‹ወቀሱኝ› አለኝ፡፡
‹ምን አድርገህ› ስል ጠየቅኩት፡፡
‹ይህኮ የተከበረ ግቢ ነው፤ ካመጣህ ሁነኛ ሰው አምጣ፤ እኔ ተከራይ እንጂ አትክልተኛ አልፈልግም› አሉኝ አለ፡፡ እንግዲህ ቅጥነቴን አይተው የለበስኩ ሳይሆን ልብሱን እንደመስቀያ ያንጠለጠልኩት መስሏቸዋል ማለት ነው፡፡
ለነገሩ የርሳቸው ይሻላል፡፡ አስቀድመው ቁርጡን የተናገሩት፡፡ አንዳንዶቹኮ ለግቢያቸው የሚያወጡት ሕግ ከወኅኒ ቤት ሕግ የባሰ ነው፡፡ ማታ ከ12 ሰዓት በኋላ መግባት፣ ጠዋት ከ12 ሰዓት በፊት መውጣት አይቻልም፡፡ በሳምንት ከሁለት ቀን በላይ ልብስ ማጠብ አይፈቀድም፡፡ ማንኛውንም ነገር በኤሌክትርክ መጠቀም አይቻልም፡፡ ሲወጡና ሲገቡ ለባለቤቶቹ ሰላምታ መስጠት ያስፈልጋል፡፡ ቴፕና ሬዲዮ ድምጹን ከፍ አድርጎ መክፈት አይፈቀድም፡፡ ጓደኛ ማብዛት አይቻልም፡፡ እና እዚህ ከመከራየት አንድያውኑ ሂሳቡን ለመንግሥት ከፍሎ ቃሊቲ መታሠር አይሻልም፡፡
(ይቀጥላል)
© ይህ ጽሑፍ በአዲስ ጉዳይ መጽሔት ላይ የወጣ ነው፡፡
No comments:
Post a Comment