በዲያቆን ህብረት የሺጥላ
እመቤታችን በብሉይ ኪዳን አበው ሁሉ ዘንድ በብዙ ትንቢቶችና በብዙ ኅብረ አምሳል ትነገር ነበር፡፡ በአዲስ ኪዳን ግልጥ ባለ መልኩ ለመጀመሪያ ጊዜ የተጠቀሰችው ቅዱስ ሉቃስ ስለ ብሥራተ መልአክ በተረከበት አንቀጽ ነበር፡፡ መተዋወቅ ከስም የሚጀምር በመሆኑ ቅዱስ ሉቃስ በወንጌሉ ‹‹የድንግሊቱም ስም ማርያም ነበረ›› ሲል የእመቤታችንን ስመ ተጸውዖ በመግለጥ ለዓለም ሁሉ ያስተዋውቃታል፡፡ (ሉቃ1.27)
1ኛ. ስሟ የተለየ ስለመሆኑ
በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በብሉይና በአዲስ ኪዳን ማርያም በሚለው ስም የተጠሩ ከስምንት የማያንሡ ሴቶች አሉ፡፡ የሙሴ እኅት ማርያም፣ ባለሽቱዋ ማርያም፣ መግደላዊት ማርያም፣ የቀለዮጳ ሚስት ማርያም፣ …እያሉ የሁሉንም መጠቀስ ይቻላል፡፡ ነገር ግን አንዳቸውም ከድንግል ማርያም ወላዲተ አምላክነት በኋላ የተሰየሙ አይደሉም፡፡ ማርያም በሚለው ስም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሱ ሴቶች ሁሉ በእርሷ ዘመንና ከእርሷ በፊት የተሰየሙ ናቸው፡፡ ነገር ግን የእቤታችን ክብርና ማዕርግ /ደረጃ/ ይፋ ከሆነ በኋላ ማለትም የአምላክ እናትነቷ ከተገለጠ በኋላ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በዚህ ስም የተጠራች አንዲትም ሴት የለችም፡፡
ገድላትንና ድርሳናትን ስናገላብጥ አመተ ማርያም፣ ማርያማዊት፣ ቤተ ማርያም፣ ዘማርያም፣ ኪዳነ ማርያም፣ ሀብተ ማርያም፣ አስካለ ማርያም፣ ገብረ ማርያም፣ … ወዘተ በሚል ስሟን እንደ ዘውድ በማድረግ ከሌላ ቃል ጋር በማዛረፍ የተጠሩ ሰዎች ብዙ እናገኛለን፡፡ እውነተኞች ክርስቲያን ወላጆች በዚህ መንገድ ልጆቻቸውን በመሰየም ይታወቃሉ፡፡ ይህንንም በማድረግ ‹‹ወንድ ወይም ሴት ልጁን በስምሽ የሰየመውን እኔ አከብረዋለሁ፤ ሞገሰ እሆነዋልሁ፤ አድነዋልሁ፡፡›› ብሎ አምላክ ለእናቱ የሰጠውን ቃል ኪዳን ተጠቅመውበታል፡፡ ይሁን እንጂ አንዳቸውም ስሟን ያለዘርፍ ሌጣውን በመውሰድ ማርያም እየተባሉ አልተጠሩበትም፡፡
በመጽሐፍ ቅዱስ ከድንግል ማርያም ወላዲተ አምላክነት በኋላ እንዲሁም በገድላትና በድርሳናት ውስጥ ማርያም በሚለው ስም በነጠላ የተሰየሙ ሰዎችን አለማግኘታችን እንዲሁም በትውፊታችንም የሌለ መሆኑ አንድ ቁም ነገር ያስተምረናል፡፡ እርሱም ስሟ በፈጣሪ ዘንድ መክበሩንና ለማንኛውም ሰው መጠሪያ መሆን የማይገባው መሆኑን ነው፡፡
ምእመናን ከትሕትና እና ከአክብሮት በመነሣት ስሟን በቀጥታ ወስደው አለመጠቀማቸው ከድንግል ማርያም ሕይወትና ታላቅነት የተነሣ ምንም ያልተጨመረበት ስሟ ብቻ ምን ያህል የማይደፈር እንደሆነ መረዳት ይቻላል፡፡ ‹‹ማርያም›› የሚለውን ስም ለእመቤታችን የብቻዋ ሆኖላታል፡፡ የሚወዱትንና የሚያከብሩትን ሰው ይሰጡታል እንጂ አይወስዱበትም፡፡ ያለውንም ይጠብቁለታል እንጂ አይነኩበትም፡፡ ስሟን በተመለከተ እውነተኞች ምእመናን ያደረጉትም ይህንን ነው፡፡ በሚቻላቸው ሁሉ ስሟን አከበሩት፤ ጠበቁትም፡፡ ምንም ምሳሌው ተራ ቢመስልም ታዋቂ ሰዎች በሕይወት ዘመናቸው ይገለገሉበት የነበረውን ቤትና ንብረት አክብሮ እንደ ቅርስ በመጠበቅ ፋንታ እኔ ልገልገልበት እንደማይባል ማለት ነው፡፡ በቅርስነት የተመዘገቡ መገልገያዎችም ይከበራሉ፣ይጎበኛሉ፣ ይጠበቃሉ እንጂ ለዕለት ተግባር አይውሉም፡፡ የድንግልም ስም እንዲሁ ይከበራል፣ ይመሰገናል እንጂ ለሌሎች ሴቶች ስያሜ ማድረግ አይገባም፡፡ የቤተ መቅደስን ንዋያተ ቅደሳት ለዕለት ተግባር ለግላችን እናውለው እንደማይባል የአማናዊት መቅደስ የድንግል ማርያምን ስም ያለዘርፍ ምእመናን ሊሰየሙበት አይገባም፡፡
2.ኛ ስሟ እና ማዕርጓ
‹‹ማርያም›› የሚለው ስም ምንም በራሱ ክቡር፣ ብቁና ምሥጢረ ብዙ ቢሆንም ስሟን ለመጀመሪያ ጊዜ ያስተዋወቀው ሐዋርያው ሉቃስ እንኳን በተለያየ አንቀጽ ደጋግሞ ሲጠቅሳት ስሟን በሌጣ ማርያም እያለ አልጠራትም፡፡ ለምሳሌ፡- በጰራቅሊጦስ ዕለት ጸጋ መንፈስ ቅዱስ ለመቶ ሃያው ቤተሰብ ከመውረዱ አስቀድሞ ሁሉም በአንድነት ተስብስበው ይጸልዩ እንደነበር ሲመሰክር የሐዋርያትን ስም አንድ በአንድ ከዘረዘረ በኋላ ‹‹እነዚህ ሁሉ ከሴቶችና ከኢየሱስ እናት ከማርያም ከወንድሞቹም ጋር በአንድ ልብ ሆነው ለጸሎት ይተጉ ነበር፡፡›› ይለናል፡፡ የሐዋርያት ሥራን የጻፈው ቅዱስ ሉቃስ መሆኑ የታወቀ ነው፡፡ (የሐዋ1.14)
በዚህ አንቀጽ ሠላሳ ስድስቱ ቅዱሳት አንስት አብረው የነበሩ ቢሆንም እንደ ሐዋርያት በስም አልተጠቀሱም፡፡ ‹‹ሴቶች›› ብቻ ብሎ አልፎአቸዋል፡፡ ከሴቶቹ በስም የተጠቀሰችው ድንግል ማርያም ብቻ ናት፡፡ የሚያስደንቀው በስም መጠቀሷ ብቻ አይደለም፡፡ ቅዱስ ሉቃስ አምላክን ከመጽነሷ በፊት ‹‹የድንግሊቱም ስም ማርያም ነበረ›› በማለት ያስተዋወቀን ቢሆንም አሁን ግን በክብረ ድንግልና ላይ ክብረ ወሊድ እንደተደረበላት ስላወቀ ‹‹የኢየሱስ እናት ማርያም›› ሲል ጠቀሳት፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ እውነተኛ አምላከ ነው፡፡ የኢየሱስ እናት ማለት የአምላክ እናት ማለት እንደሆነ አያከራክርም፡፡ ስለዚህ በነጠላው ‹‹ማርያም›› በማለት ፋንታ ወላዲተ አምላክ ማርያም ወይም ‹‹የኢየሱስ እናት ማርያም›› ማለትን የተማርነው ከመጽሐፍ ቅዱስ ነው፡፡
የአገራችን ትውፊትም ይህን የተከተለ ነው፡፡ አንዲት ሴት ከመጠሪያ ስሟ በተጨማሪ ወይዘሪት እገሊት ስትባል ትኖርና ስታገባ የጋብቻ ክብር ስለሚጨመርላት ወይዘሮ እገሊት ትባላለች፡፡ ልጅ ስትወልድ ደግሞ የእገሌ/የእገሊት እናት ትባላለች፡፡ መውለድ ራሱ ታላቅ ክብር ነውና፤ ምስጋናንም ያበዛል፡፡ ዘለፋ ስለ ልያ ወንድ ልጅ በወለደች ጊዜ ልያ ያውም እርሷ ራሷ ላልወለደችው ልጅ ‹‹ደስታ ሆነልኝ ሴቶች ያመሰግኑኛል›› ያለችው ስለዚህ ነው፡፡ ንጉሥ ጳጳስ የወለደች ሴት ደግሞ ክብሯ እጥፍ ይሆናል፡፡ ጻድቅ፣ ቅዱስ የወለዱ እናቶች እንዴት የተከበሩ ናቸው? አምላክን የወለደች የድንግል ማርያምን ክብር መግለጫ ምን ቋንቋ ምን እንደበት ይኖራል?
ኤልሳቤጥ ለድንግል ማርያም እጅግ የቅርብ ዘመዷ አክስቷ ናት፡፡ ባገኘቻት አጋጣሚ ስሟን ስትጠራ ኖራለች፡፡ አምላክን ጸንሳ ወደ እርሷ በሄደች ጊዜ የተቀበለቻት በሚያስደንቅ መንገድ ነበር፡፡ በአክብሮት ቃል ‹‹የጌታዬ እናት ወደ እኔ ትመጣ ዘንድ እንዴት ይሆንልኛል?›› አለች፡፡ (ሉቃ1.43) ይኸውም መንፈስ ቅዱስ አምላክን ጸንሳ ወደ እርሷ መምጣቷን ስለገለጠላት ነው፡፡ መውለድ ብቻ ሳይሆን መጽነስም እናት ለመሰኘት በቂ ነው፡፡ ተጸንሰው ለመወለድ የማይደርሱ ቢኖሩም የኢየሱስ ክርስቶስ በሥጋ መወለድ እንኳን ተጸንሶ ከዚያም በፊት ቢሆን የማይጠረጠር ስለነበር ‹‹የጌታዬ እናት›› ብላ ኤልሳቤጥ ምስክርነቷን ሰጠች፡፡ ‹‹የጌታዬ እናት›› ያለችው አዲስ ምሥጢር ተገልጦላት እንጂ ‹‹ማርያም›› የሚለው ቀድሞ የምታውቀው ስም ጠፍቷት አይደለም፡፡
ኤልሳቤጥ ኢየሱስ ክርስቶስ የአማልክት አምላክ የጌቶች ጌታ መሆኑን የምታምን ታላቅ ሴት ናት፡፡ ሐዋርያው ቶማስ የእጁን ተአምራት የቃሉን ትምህርት እየተመለከተ ቢቆይም በጥርጥር ይፈተን ነበር፡፡ ‹‹ጌታዬ አምላኬም›› ለማለት የቻለው እጁን በጎኑ ካስገባ በኋላ የመለኮት እሳት እጁን ሲፈጀው ነበር፡፡ ኤልሳቤጥ ግን የአምላክን እናት ተመልክታ በማኅፀን ያለውን ሕጻን ‹‹ጌታዬ›› ለማለት በቃች፡፡ ‹‹የጌታዬ እናት›› ማለቷ የአምላኬ እናት ማለቷ ነው፡፡ የጌታ እናት እመቤት እንደምትባል ለማንም ግልጽ ነው፡፡ ልጇን ‹‹ጌታዬ›› የሚል ሰው እናቱን ‹‹እመቤቴ›› ማለት አይከብደውምና፡፡ ስለዚህ ድንግል ማርያምን እመቤታችን እንላታለን፡፡
ቅድስት ኤልሳቤጥ በነጠላው ‹‹ማርያም›› በማለት ፋንታ ‹‹የጌታዬ እናት›› በማለት አክብራ መጥራቷን ልብ ማለት ያስፈልጋል፡፡ እንደ ሐዋርያው ሉቃስና ዮሐንስ ‹‹የኢየሱስ እናት›› ብላ እንዳትጠራት ገና ሕፃኑ በማኅፀን ነውና ስላልተወለደ ስም አልወጣለትም፡፡ በመልአኩ ትንቢትና የምሥራች ቃል መሠረት ከተወለደ በኋላ ‹‹ኢየሱስ›› ተባለ፡፡ ሐዋርያትና ሌሎችም ቅዱሳን ‹‹የኢየሱስ እናት›› በማለት ኅብረታቸውን ያሳዩት ሕጻኑ ከተወለደ በኋላ ነው፡፡ ሕዝቡን ከኃጢአታቸው የሚያድናቸው ስለሆነ ነው፡፡ ድንግል ማርያምን አክብሮ መጥራት በእርሷ የተደረገውን ታላቅ አምላካዊ ሥራ መረዳትና የመንፈስ ቅዱስ ማደሪያ መሆን ይጠይቃል፡፡
ቀጥለን የምንመለከተው ቅዱስ ዮሐንስ ወንጌላዊውን ነው፡፡ ዮሐንስ ከመስቀል ስር ቆሞ ሳለ ድንግል ማርያም በአደራ የተረከበ ከእርሷም ጋር ለአሥራ አምስት አመታት የኖረ ሐዋርያ ነው፡፡ ካለው መንፈሳዊ ጸጋ ባሻገር አብሮ በመኖርም ስለ እመቤታችን ብዙ ለማወቅ ታድሎአል፡፡ ይህ ሐዋርያ ስለ እመቤታችን ሰፋ አድርጎ በመጻፍ ይታወቃል፡፡ በጻፈው ወንጌል ውስጥ በቃና ዘገሊላ የአማላጅነቷን ነገር፤ በራእይ መጽሐፉ ደግሞ የስደቷን ነገር በስፋት ጽፏል፡፡ ይሁን እንጂ በአንድም ስፍራ ስሟን በነጠላ ‹‹ማርያም›› ብሎ አልጠራትም፡፡ ለአብነት ያህል በቃና ዘገሊላ ሠርግ ቤት የሆነውን ሲናገር ‹‹የኢየሱስም እናት በዚያ ነበረች፡፡›› ብሏል፡፡ ደጋግሞ የጠቀሳትም በዚሁ መንገድ ነው፡፡ (ዮሐ2.1፤ ዮሐ2.3) አስቀድመን እንደተመለከትነው ‹‹የኢየሱስ እናት›› ማለት ወላዲተ አምላክ ማለት መሆኑ ግልጥ ነው፡፡
እመቤታችን በመጽሐፍ ቅዱስ በብዙ ስፍራ የተጠቀሰች ስለሆነ በእያንዳንዱ ቦታ የተጠቀሰችበት አግባብ ራሱን የቻለ መልእክት እንዳለው ማስተዋል ያስፈልጋል፡፡ የእስካሁኑ ማብራሪያ ዋና አላማ በስሟ ላይ ተጨማሪ ሆነው በቤተ ክርስቲያን የምንሰማቸው ስያሜዎች መሠረታቸው መጽሐፍ ቅዱስ እንደሆነ ማሳየት ነው፡፡
ምእመናን ድንግል ማርያምን በተለያየ ስም መጥረታቸው ፍቅራቸውን፣ አክብሮታቸውን፣ እምነታቸውን የሚገልጥ በመሆኑ የሚያስመሰግን እንጂ የሚያስነቅፍ አይደለም፡፡ የቤተሰብእ አባላት በሙሉ ሌላውን የቤተሰብእ አባል በየራሳቸው እነርሱ በወደዱት መንገድ በመጥራትና በማቆላመጥ ፍቅራቸውን ይገልጻሉ፡፡ ነቢያትና ሐዋርያት የሃይማኖት ቤተሰብእ እንደመሆናቸው መጠን ድንግል ማርያምን በተለያየ ስም የጠሩአት በዚህ መሠረት ነው፡፡ ኢሳይያስ ‹‹እነሆ ድንግል ትጸንሳች›› ባለ ጊዜ ‹‹ድንግል›› ብሎ ጠራት ማለት ነው፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹ከሴት ተወለደ›› ባለ ጊዜ ሴት ብሎ ጠራት፡፡ ቅዱስ ዳዊት ‹‹ልጄ ሆይ ስሚ›› ባለ ጊዜ ‹‹ልጄ›› አላት፡፡ ጠቢቡ ሰሎሞን ‹‹መልካሟ ርግቤ፣ ሙሽራዬ …›› እያለ በብዙ ኅብረ ቃል ሲጠራት ኖሮአል፡፡ ምእመናን ይህንን አብነት አድርገው እንደየፍቅራቸው ይጠሯታል፡፡ እርሷም ሰምታ ፈጥና ትደርስላቸዋለች፡፡
‹‹ማርያም›› የሚለው ስም ሙሉ እና ብቁ መሆኑን ገልጠናል፡፡ በስሟ ላይ ተጨማሪ የሆኑትን የማዕርግ ስሞች የጠቃቀስነው አክብሮ የመጥራትን አስፈላጊነት ለማስረዳት እንጂ ማርያም ብሎ በነጠላ መጥራትም ኃጢአት ወይም ክህደት ነው ለማለት አይደለም፡፡ በቤተ ክርስቲያን የሥርዓተ አምልኮ መጻሕፍት ‹‹ማርያም›› የሚለው ስም ያለ ዘርፍ የተጠቀሰበትም ብዙ አንቀጽ አለ፡፡ ዋናው ቁም ነገር ሐሳቡን መረዳት ነው፡፡
እግዚአብሔር የኃጥአንን ስም እንደሚያጠፋ ሲናገር ለቅዱሳን ስም ግን ልዩ ክብር መስጠቱን ራሱ መስክሯል፡፡ በቤቱ የማይጠፋ ስም የሰጣቸው እርሱ ነው፡፡ (ኢሳ56.5) በስማቸው ቀዝቃዛ ውኃ ለሚያጠጣ ሰው ዋጋውን እንደሚከፍለው ቃል የገባው ስማቸው እንዲታሰብና እንዲከበር ስለፈለገ ነው፡፡ (ማቴ10.42) ስለእመቤታችን ስም አጠራር ትኩረት ሰጥተን ይህን ያህል የጻፍነውም ፈጣሪ ያከበረውን እኛ መናቅ እንደሌለብን ለማሳሰብ ነው፡፡
ሰው ከስሙ ባሻገር ያለውን ማዕርግ ግምት ሰጥቶ መጥራት ይገባል፡፡ በወታደር ቤት፣ በሕክምና፣ በመንፈሳዊ ስፍራዎች እና በየሙያ ዘርፎች ውስጥ አገልግሎት ሰጪዎች በስማቸው ላይ የሚጨመር የማዕርግ ስም እንዳላቸው የታወቀ ነው፡፡ እነዚህን ሰዎች ማክበር እና በአግባቡ መጥራት በሃይማኖት ጎዳናም ቢሆን ያስመሰግናል እንጂ አያስነቅፍም፡፡
3ኛ. የስሟ ትርጓሜና ምሥጢር
ማርያም የሚለው ስያሜ የትመጣው ዕብራይስጥ ነው፡፡ እንደማንኛውም ቃል የራሱ የሆነ ዘይቤአዊና ምሥጢራዊ ፍቺዎች አሉት፡፡ ዘይቤአዊ ፍቺው ቃሉ በሚገኝበት ቋንቋ ውስጥ የያዘው ቀጥተኛ ፍቺ ሲሆን ምሥጢራዊ ፍቺው ደግሞ ከዚያ ውጭ የሚኖረው ፍቺ ነው፡፡ ስለዚህ ማርያም የሚለው ስም በቋንቋው ካለው ዘይቤአዊ ፍቺ በላይ በብዙ ምሥጢር ይፈታል፡፡ የአንድ ቃል ምሥጢራዊ ፍቺ ከዘይቤው ጋር የሚስማማበት ጊዜ እንዳለ ሁሉ ከዘይቤው በተቃራኒ የሚሄድ ምሥጢራዊ ፍቺ ሊኖረው እንደሚችልም የታወቀ ነው፡፡
ማርያም የሚለው ስም ትርጉሙ በዋናነት የሚመነጨው ስያሜው ከተገኘበት የቋንቋ ዘይቤ ይልቅ የዚህ ስም ባለቤት ከሆነችው ከድንግል ማርያም ክብር፣ ምግባርና ትሩፋት በአጠቃላይ ከሕይወቷ አንጻር ነው፡፡ እንዲህ ከሆነ ደግሞ የስሟ ትርጉም ምንም ያህል ቢሰፋ በዛ የሚባል አይሆንም፡፡ ሕይወተ ማርያም ምሥጢሩ ጥልቅ ነውና፡፡ ስሟ የሚበልጠውን አንድምታና ሐተታ ያገኘው አኗኗሯ ከታወቀ፤ ወላዲተ አምላክነቷ ከተገለጠ በኋላ ዘግይቶ እንጂ በሕፃንነቷ ገና ስም ሲወጣላት ወይም ሲሰየምላት አይደለም፡፡
የላይኛውን አንቀጽ በምሳሌ ለማስረዳት ይሁዳ ማለት ከተጠራበት ቋንቋ አንጻር በእግዚአብሔር የሚታመን /አማኝ/ ማለት ነው፡፡ ይሁን እንጂ ይሁዳ ጌታውን በመሸጥ ክህደቱ ስለተገለጠ በእኛ ዘንድ ይሁዳ ማለት ከዘይቤው በተቃራኒ ከሃዲ እንደማለት ይቆጠራል፡፡ የይሁዳን ታሪክ በሚያውቁ ዘንድ ይህ ስም የቋንቋ ዘይቤውን ትቶ የይሁዳን ግብር እየተከተለ ይተረጎማል ማለት ነው፡፡ ከዚህ የተነሣ ከዳተኛን ሰው ይሁዳ እንለዋለን፡፡ እንዲህ ያለውን ሰው ይሁዳ በምንልበት ጊዜ ከሃዲነቱን ገልጠን ነቀፍነው እንጂ በቋንቋው ዘይቤ መሠረት አላወደስነውም፡፡
በተመሳሳይ መንገድ አርዮስ ማለት ከተሰየመበት ቋንቋ አንጻር የተመለከትነው እንደሆነ ፀሐይ ማለት ነው፡፡ ነገር ግን አርዮስ ኢየሱስ ክርስቶስን ፍጡር በማለቱ የሚታወቅ ከሃዲ ስለሆነ ከአርዮስ ክህደት መታወቅ በኋላ አርዮስ ማለት ፀሐይ ከሚለው የዘይቤ ፍቺ ይልቅ በአርዮስ ግብር አንጻር ይተረጎማል፡፡ ስለሆነም አንድን ሰው በዘመናችን አንተ አርዮስ ብንለው አንተ ከሃዲ ማለታችን እንጂ በቋንቋው መሠረት ‹‹ፀሐዩ›› እያልን እንዳላወደስነው ግልጽ ነው፡፡ የሰው ስም ከቋንቋው ዘይቤ ይልቅ የተጠራበትን ሰው ግብር ይዞ ሊተረጎም መቻሉ በዚህ እናውቃለን፡፡
በተሰጡት ሁለት ገላጭ ምሳሌዎች መሠረት ‹‹ማርያም ብሂል - ማርያም ማለት›› እየተባለ ስመ ማርያም ሲተረጎም ብዙ ጊዜ ሰምተናል፤ አንብበናልም፡፡ አንዱን ለመጥቀስ ያህል ማርያም ማለት ጥዕምት/ጣፋጭ/ ማለት ነው፡፡ ማር በምድር ጣፋጭ ምግብ እንደሆነ በሰማይም ያም የሚባል ጣፋጭ ምግብ አለ፡፡ ሁለቱን አገናኝተው በሰማይና በምድር የተወደድሽ ነሽ ሲሉ ማርያም ብለዋታል›› እየተባለ ሲተረጎም የቋንቋ ዘይቤውን ሳይሆን የድንግል ማርያምን ምግባርና ሕይወት ተከትሎ የሚተረጎም መሆኑን ማስተዋል ያስፈልጋል፡፡ እውነታው ድንግል ማርያም በሰማይም በምድርም የተወደደች እጅግ በጣም ጣፋጭ መሆኗ ነውና፡፡
ከላይ በተብራራው መንገድ ማርያም የሚለው ስም በብዙ መንገድ ይተረጎማል፡፡ ይህን ሳይረዱ የቃሉን ዕብራይስጢነት ብቻ በመጥቀስ የስሟን ትርጓሜ የሚነቅፉ ዘይቤ እንጂ ምሥጢር ምን መሆኑን ያልተረዱ ናቸው፡፡ መናፍቃን የቋንቋ ዘይቤውን ብቻ በመያዝ ማርያም የሚለው ስም የዕብራይስጥ ቃል ሆኖ ሳለ ማር ደግሞ የአማርኛ ቃል መሆኑ እየታወቀ ልብ ወለድ ካልሆነ በቀር እንዴት ተደርጎ በዚህ መልኩ ይተረጎማል?እያሉ ሲተቹ ይደመጣል፡፡ ለዚህ አጭሩና ግልጡ መልስ ከላይ የተሰጠው ምሳሌና ማብራሪያ ነው፡፡ ማርያም የሚለው ስም ሕይወቷን መሠረት አድርጎ እንጂ ቋንቋውን መሠረት አድርጎ የተተረጎመ አይደለም፡፡
በዚህ መሠረት የእመቤታችንን ስም የተለያዩ መጻሕፍት እና ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን እንዴት እምደተረጎሙት ምንም ቀደም ሲል የሰማችሁትና የምታውቁት ቢሆንም በድጋሚ ላስታውሳችሁ፡፡
ማርያም ማለት የብዙኀን እናት ማለት ነው፡፡ አንድም ማርያም እያንዳንዱ ፊደል በየራሱ ሲነበብ ማ ማለት ማኅደረ መለኮት፣ ር ማለት ርግብየ ይቤላ፣ ያ ማለት ያንቀዓድዑ ኀቤኪ ኩሉ ፍጥረት፣ ም ማለት ምስአል ወምስጋድ ወመስተሥርእየ ኃጢአት ማለት ነው፡፡ ይህም ሰሎሞን ርግቤ ሲል የሚጠራሽ የመለኮት ማደሪያው እኛ ምእመናን ወደ አንቺ በማንጋጠጥ ጸሎትና ስግደት ለሥላሴ የምናቀርብብሽ መስገጃችንና መማጸኛችን እውነተኛ መቅደሳችን አንቺ ነሽ ማለት ነው፡፡
አንድም ማርያም ማለት ጸጋ ወሃብት ማለት ነው፡፡ አስቀድሞ ለወላጆቿ ኋላም በዮሐንስ ወንጌላዊ በኩል ጸጋ ሆና ለምእመናን በሙሉ ተሰጥታናለች፡፡ ስለዚህ ጸጋና ሀብታችን ናት፡፡ አንድም ማርያም ማለት ወላዲተ አምላክ ማለት ነው፡፡ አንድም ማርያም ማለት ተላኪተ እግዚአብሔር ወሰብእ ማለት ነው፡፡ ይህም ስለ አማላጅነቷ የሚተረጎም ነው፡፡
እናታችን ማርያም በምእመናን ዘንድ ብዙ ነገር ትሆናለች፡፡ ለሐዋርያት ስብከታቸው ናት፡፡ ለነቢያት ሞገሳቸው ናት፡፡ ለሰማዕታት ደግሞ እናታቸው ናት፡፡ ለመላእክት ደግሞ በንጽሕናዋ እኅታቸው ናት፡፡ ለተማሪ ስንቅና የሃይማኖት ምሥጢር ናት፡፡ ለወታደር ምሽግ ናት፡፡ ለታረዙ ልብስ ናት፡፡ የስሟ አተረጓጎም ምሥጢሩ ለገባው ማርያም ማለት በዚህ ሁሉ ሊፈታ የሚችል ነው፡፡
በረከትዋ ይደርብን!
ወስብሐት ለእግዚአብሔር!
ዲያቆን ኅብረት የሺጥላ
መስከረም 2005
No comments:
Post a Comment