"የዕርቀ ሰላም ሂደቱ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል" ቅ/ሲኖዶስ አስታወቀ
- “የሃይማኖት መሪዎች ጊዜ ሳያልፍ አንድነታቸውን እንዲያጠነክሩ ጸሎቴ ነው” /ፕ/ር ኤፍሬም ይሥሐቅ/
- ከመጪው ግንቦት በፊት የሚፈጸም የፓትርያርክ ሹመት እንደማይኖር እየተነገረ ነው::
- ማኅበረ ቅዱሳን ስለዕርቀ ሰላሙ ያለውን አቋም በግልጽ ዐውጆ ሂደቱን እንዲያግዝ ተጠይቋል::
- “በአሐቲ ቤተ ክርስቲያን መርሕ የቤተ ክርስቲያን ፍጹም አንድነትና ሰላም እንዲጠበቅ እንሠራለን” /የነገረ መለኰት ምሩቃን ማኅበር/::
(ደጀ ሰላም፤ መስከረም 2/2004 ዓ.ም፤ September 12/ 2012/ READ THIS NEWS IN PDF)፦ በቅርቡ በመንግሥት በኩል ይኖራል ተብሎ የሚጠበቀው የአመራር ሽግግርና የሚተካው ርእሰ መንግሥት ከተለወጠው ዘመንና ከቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ኅልፈት ጋራ ተያይዞ ከታየው የሕዝብ ጨዋነት፣ ይቅር ባይነትና ርኅራኄ አኳያ የሚመጥኑ ተፈላጊ ለውጦችን ለማምጣት የሚያስችል እንዲኾን እየተጠየቀ ባለበት በአሁኑ ወቅት በቤተ ክህነቱም በኩል ከቀጣዩ ርእሰ አበው ሹመት አስቀድሞ መከናወን ያለባቸው ተግባራት እንዳሉ እየተገለጸ ነው፡፡ በጠቅላይ ሚኒስትሩና በፓትርያርኩ ኅልፈት ተገቢውን ሰው መተካትና የተፈጠረውን ክፍተት ማሟላት ሕገ መንግሥታዊ እና ሕገ ቤተ ክርስቲያናዊ ግዴታ ነው፡፡ በግዴታው አፈጻጸም ሂደት የሚታየው የመንግሥት ይኹን የቤተ ክህነት ባሕርይና ብቃት ለየራሱ ከጎሰኛነትና ጥቅመኛነት በላይ ኢትዮጵያንና የኢትዮጵያን ቤተ ክርስቲያንን በማስቀደም ሊጠናቀቅ እንደሚገባው ተመልክቷል፡፡
በቤተ ክርስቲያን በኩል ጠቅላይ ቤተ ክህነቱና በተዋረድ እስከ አጥቢያ ድረስ የተዘረጉት መዋቅሮቹ በአመዛኙ የመጥፎ ነገር ሁሉ ተምሳሌት የኾኑባቸው ተቋማዊ ገጽታዎች በመሠረቱ የሚለወጡበት መንፈሳዊና ሥልጡን አመራር እንዲኖረው፤ ከዚህም አኳያ አስፈላጊው የመዋቅራዊ ዲዛየን ለውጥ እንዲያደርግ እየተጠየቀ ሲሆን የቤተ ክርስቲያንን አንድነት በመመለስና ሰላሟን በማረጋገጥ ረገድም በሰሜን አሜሪካ በስደት ከሚገኙት አባቶች ጋራ የተጀመረው የዕርቀ ሰላም ሂደት እንዲጠናከርና ወርቃማው ጊዜ ሳያልፍ ከፍጻሜ እንዲደርስ የሚያሳስቡ መልእክቶች እየተላለፉ ነው፡፡
በዐቃቤ መንበረ ፓትርያርኩ የሚመራውና እስከ ዋናው ፓትርያርክ ምርጫ ድረስ በተጨማሪ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት እንዲጠናከር የተደረገው ቋሚ ቅ/ሲኖዶስ ኦርቶክሳውያን ምእመናን ስለ ውዲቱ አገራቸውና ስለ እናት ቤተ ክርስቲያናቸው መንፈሳቸውን የሚያስተባብሩበት የሁለት ሱባኤ ጸሎተ ምሕላ ከማወጅ አንሥቶ ከዘመኑ መለወጥ ጋራ ለቤተ ክህነቱ ተቋማዊ ለውጥ የሚያግዙ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች በማከናወን ላይ እንዳለ ተገልጧል፡፡ ከዚህም ጋራ ደግሞ በሸኘነው ዓመት የመጨረሻ ሳምንትም የዕርቀ ሰላሙን ሂደት የተመለከተ ደብዳቤ በአሜሪካ ለሚገኘው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሰላምና አንድነት ጉባኤ መጻፉ ተዘግቧል፡፡
የቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት በቁጥር 6/9/812/2004 በቀን 01/13/2004 ዓ.ም ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሰላምና አንድነት ጉባኤ በጻፈውና በልኡኩ ቀሲስ ዶ/ር አማረ ካሳዬ በኩል በላከው በዚሁ ደብዳቤው÷ ጉባኤው በመልእክተኞቹ አማካይነት የላከው ደብዳቤ በቅዱስ ሲኖዶስ ስብሰባ ላይ ቀርቦ መነበቡንና የልኡካኑን ማብራሪያ ማዳመጡን ገልጧል፡፡ “ቀድሞ በተጀመረው የሰላም ሂደት እንቀጥላለን” ያለው ደብዳቤው ቤተ ክርስቲያኒቱ በደረሰባት ሐዘን ምክንያት ትክክለኛ ጊዜውን ወደፊት እንደሚያስታውቅ አመልክቷል፡፡ ቅዱስ ሲኖዶስ በሰጠው ምላሽ ላይ አስተያታቸውን የሰጡ የመንበረ ፓትርያርኩ ምንጮች እንዳመለከቱት÷ ዕርቀ ሰላሙ ቀጥሎ ስለሚካሄድበት ቀንና ቦታ፤ ለውይይቱ ስለሚወከሉት ብፁዓን አባቶች፤ የዋናው ፓትርያርክ ምርጫ ሕግ/ደንብ ዝግጅት በጥቅምቱ የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ ላይ ቀርበው ለመምከር የታሰበ በመኾኑ ከመጪው የርክበ ካህናት ቅ/ሲኖዶስ አስቀድሞ የሚፈጸም የፓትርያርክ ሹመት እንደማይኖር ያላቸውን ግምት ተናግረዋል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ በስደት በውጪው ዓለም በሚገኙት አባቶች በኩል ተደጋግሞ እንደሚነገረው መፍትሔው ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆርዮስን ወደ መንበራቸው መመለስ ብቻ መሆኑን አበክረው በመግለጽ ላይ ሲሆኑ ደጀ ሰላምን ጨምሮ ሌሎች ምዕመናን እና ጉዳዩ የሚያገባቸው ወገኖች የቀድሞው ፓትርያርክ ድምጻቸውን እንዲያሰሙ በመጠየቅ ላይ ናቸው። በዐበይት በዓል ስንኳን ለመንፈስ ቅዱስ ልጆቻቸው አባታዊ ቡራኬ እና ቃለ ምዕዳን ሲሰጡ የማይታዩትን እና የማይሰሙት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆርዮስ በምን ሁኔታ ላይ እንዳሉ፣ ስለ አጠቃላይ የቤተ ክርስቲያኒቱ ሁናቴ ምን እንደሚያስቡ እንደማይገልጹ፣ አሁን ያሉበት የጤና አቋም በምን ዓይነት ሁኔታ እንደሆነ ማንም እንደማይናገር በግልጽ የሚታይ ሲሆን በስደት ላሉት አባቶች መልስ በመስጠት በኩል ብቸኛው ሰው ብፁዕ አቡነ መልከ ጼዴቅ ብቻ ናቸው።
በሌላ በኩል የአገር ሽማግሌዎች ቡድን አባል የሆኑት ፕሮፌሰር ኤፍሬም ይሥሐቅ የሃይማኖት አባቶች ጊዜው ሳያልፍ አንድነታቸውን እንዲያጠነክሩ ጠይቀዋል፡፡ ፕሮፌሰሩ ጳጉሜን 2004 ዓ.ም ታትሞ ከወጣው “ዕንቍ” መጽሔት ጋራ ባደረጉት ቃለ ምልልስ÷ ለሕዝቡ ፍቅርን ለመስበክ፣ መተባበርን፣ ይቅር መባባልንና መከባበርን ለማስተማር የሚተጉት የሃይማኖት አባቶች ይቅር ለመባባል ሽምግልናን በመፈለጋቸው እንደሚያዝኑና እንደሚያፍሩ ተናግረዋል፡፡ “የእኛ የዕርቅ ኮሚቴ አለ፤ ብዙዎቹ አባ ጳውሎስ ዘንድ እየተመላለሱ ሰላም እንዲኾን ብዙ ሞክረዋል፤ እርሳቸውም ሰላም እንዲመጣ ፈልገው ነበር፤ ነገር ግን ይህ ሰላም ሳይመጣ፣ ቤተ ክርስቲያኒቷ አንድነቷን ሳትፈጽም በመሞታቸው አዝናለኹ” ያሉት ፕሮፌሰር ኤፍሬም የሃይማኖት መሪዎች ይቅር ተባብለው፣ በመካከላቸው ያለውንም ጥላቻ አጥፍተው መታየት እንደሚገባቸው በማውሳትም “ለሁለት የተከፈለው ሲኖዶስ አንድ እንደሚኾን ተስፋ አለኝ፡፡ እግዚአብሔር ለእነርሱም መንገዱን ያሳያቸው፡፡ መንገዱን ጨርቅ ያድርግላቸው፡፡ እግዚአብሔር ልባቸውን ይክፈት፡፡ ጊዜ ሳያልፍ አንድነታቸውን እንዲያጠነክሩ እግዚአብሔር እንዲረዳቸው ጸሎቴ ነው፡፡” ሲሉ መክረዋል።
በተያያዘ ዜና ከነሐሴ 30 - ጳጉሜን 2 ቀን 2004 ዓ.ም በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት አዳራሽ በተካሄደው የማኅበረ ቅዱሳን ዐሥረኛ ጠቅላላ ጉባኤ መክፈቻ ላይ የተገኙ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፣ የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ የሰላምና አንድነት ጉባኤ ልኡክና የነገረ መለኰት ምሩቃን ማኅበር ተወካይ ማኅበረ ቅዱሳን በዕርቀ ሰላሙ ላይ ያለውን አቋም በግልጽ ዐውጆ ሂደቱን እንዲያግዝ ጠይቀዋል፡፡ ማኅበረ ቅዱሳን አጽራረ ቤተ ክርስቲያን በበዙበት ወቅት በመንፈስ ቅዱስ ፈቃድ ተመሥርቶ በአጭር ጊዜ በአባቶች ቡራኬ የተጠናከረና የተስፋፋ የቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ጠበቃና አለኝታ የኾነ ማኅበር ነው፤” ያሉት የሲዳሞ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ገብርኤል ናቸው፡፡ ብፁዕነታቸው ማኅበሩ ኢትዮጵያዊም ዓለም አቀፋዊም ማኅበር እንደ መኾኑ የቅድስት ቤተ ክርስቲያን አንድነት እንዳይናጋ “በወርድም በቁመትም መሥራቱን” አጠናክሮ እንዲቀጥል አሳስበዋል፡፡
በማኅበሩ የምሥረታ ዘመን በነበሩበት የከፋ ሀገረ ስብከት የበኩላቸውን እገዛ እንዳደረጉ ያስረዱት አሁን የካናዳ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ማቲያስ÷ ማኅበረ ቅዱሳን ቅዱስ ሲኖዶስን በዙሪያው ኾኖ የሚጠብቅ፣ የቅዱስ ሲኖዶሱን ውሳኔዎች በማስፈጸም ረገድም ቋሚ ተጠሪ መኾኑን ገልጸው በተጀመረው የዕርቀ ሰላም ንግግር “እንዲገባበት ያስፈልጋል” ብለዋል፡፡ ማኅበረ ቅዱሳን የተሸበረውን ያረጋጋል እንጂ ሽብር አይፈታውም” በማለት ቃለ ምክራቸውን የጀመሩት ብፁዕ አቡነ ኤልሳዕ የሰሜን ጎንደር ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ናቸው፡፡ በቤተ ክህነት አጽናኝም አሸባሪም መኖሩን የተናገሩት ብፁዕነታቸው ÷ የማኅበሩ አባላት በቀን ለእናት ሀገር ኢትዮጵያ፣ በማታ ደግሞ ‹ለአባት አገር› ለቤተ ክርስቲያን እንደሚሠሩ ገልጸዋል፡፡ ይኹንና ማኅበሩ በዕርቀ ሰላሙ ሂደት ዙሪያ ስላለው አቋም እውነትም ሐሰትም የተቀላቀለበት ስለሚወራ ቤተ ክርስቲያን ተከፋፍላና ሰላሟን አጥታ በተቸገረችበት ጉዳይ ማኅበሩ አቋሙን በግልጽ ዐዋጆ እንዲገባበትና የበኩሉን እገዛ እንዲያደርግ ጠይቀዋል - “እናንተ ብትገቡበት አያቅታችኹም፡፡”
ከአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅነት እስከ የሰንበት ት/ቤቶች ማ/መምሪያ ሓላፊነት ድረስ ከማኅበረ ቅዱሳን ጋራ የግጭትም የፍቅርም ግንኙነት እንደነበራቸው ያስታወሱት እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ የካሊፎርኒያና አካባቢው ሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅ የነበሩት የሰላምና አንድነት ጉባኤው ልኡክ አባል ሊቀ ካህናት ኀይለ ሥላሴ ዓለማየሁ÷ ማኅበረ ቅዱሳን “እኛ ያላየነውን እያየ በርካታ የቤተ ክርስቲያን ልጆችን ከመናፍቃን ምርኮ ማዳኑን” ለአገልግሎት በተዘዋወሩባቸው የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ግቢ ጉባኤያት መረዳታቸውን ገልጸዋል፡፡ ቤተ ክርስቲያኒቱን ከማኅበሩ፣ መንግሥትን ከማኅበሩ ለማጋጨት የሚሞክሩ አካላትን ለይቶ ማወቅ እንደሚያስፈልግ የተናገሩት ሊቀ ካህናት ኀይለ ሥላሴ÷ በአሉባልተኞች የሚነዛውን አጉል አስተሳሰብ ሰብሮ ማኅበሩን መደገፍ ቤተ ክርስቲያንን ማገልገል እንደኾነ “ባትደግፉት ዕወቁት፤ ካወቃችኹት በኋላ ትደግፉታላችኹ” በማለት አስረድተዋል፡፡
ይህም የማኅበሩ አባላት አይሳሳቱም ማለት እንዳልኾነ፣ ሲሳሳቱ ሌላ ጥላቻ መፍጠር ቤተ ክርስቲያንን ከመበደል ተለይቶ የማይታይ በመኾኑ ምክር እንደሚያስፈልጋቸው የተናገሩት ሊቀ ካህናት ኀይለ ሥላሴ÷ ማኅበሩ መንፈሳዊ አገልግሎቱን እንዳይስት የብፁዓን አባቶች ድጋፍ እንደሚያሻው አሳስበዋል፡፡ ለጠቅላላ ጉባኤው ተሳታፊዎች ባስተላለፉት መልእክትም “የሚያገለግለው ዲግሪውና ዲፕሎማው ሳይሆን ሕይወታችኹ ነው፤ ማኅበረ ቅዱሳንን የማያውቅ ማኅበረ ቅዱሳን [አባልና አመራር] እንዳይኖራችኹ አደራ እላለኹ፤”ብለዋል፡፡
በጠቅላላ ጉባኤው ላይ በተጋባዥነት ተገኝተው መልእክታቸው ካስተላለፉት አካላት መካከል የእናት ቤተ ክርስቲያንን ሰፊ አዝመራ ለመሰብሰብና ለመከባከብ፣ ከአጥፊና ከዘራፊ ለመጠበቅ በተማሩት ትምህርትና በተሰጣቸው ድርሻ ለማገልገል የተቋቋመው የነገረ መለኰት ምሩቃን ማኅበር አንዱ ነው፡፡ የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ እስከ አሁን ድረስ ከ1500 በላይ በ”Modern Theology” የሠለጠኑ ምሩቃንን ማውጣቱን የገለጹት የማኅበሩ ተወካይ መ/ር ማንያዘዋል አበበ÷ ከምሩቃኑ ብዙዎቹ በጠረፍ አገር፣ ከአንድ መቶ ያላነሱ ከሀገር ውጭ፣ የተወሰኑት ደግሞ በአዲስ አበባ እንደሚገኙ አስረድተዋል፡፡
መ/ር ማንያዘዋል አበበ |
ይህ በእንዲህ እንዳለ የክረምት የጨለማው ወራት ተፈጽሞ የበጋው፣ የጥቢው ብርሃን የሚፈነጥቅበት በፀሐይ አቆጣጠር መስከረም 1 ቀን 2005 ዓ.ም፤ በፀሐይና ጨረቃ ጥምር ኢትዮጵያዊ አቆጣጠር 2013 ዓ.ም እነኾ ብቷል፤ ዘመኑም ተሞሽሯል - እ ን ቍ ጣ ጣ ሽ !!!
አዲሱ ዓመት ሁለት ዐይነት የአከባበር ጠባይ አለው - ብሔራዊ እና ሃይማኖታዊ፡፡ ሕዝበ ክርስቲያኑም ኾነ ሌላው በብሔራዊ ስሜቱ የሀገር ልብስ ለብሶ ብሔራዊ ዘፈን እየዘፈነ አርዶ ጠምቆ ሲበላ፣ ሲጠጣ፣ ሲገባበዝ፣ ሲጠያየቅ ይውላል፡፡ በሃይማኖታዊ ትውፊቱ ደግሞ ወደ ሰበካው ቤተ ክርስቲያን እየሄደ ለዚህ ያደረስኽኝ አምላኬ ተመስገን፤ የከርሞ ሰው በለኝ፤ ተርፎ ለሚቀረው ዕድሜ አትንፈገኝ፤ ብሎ ፈጣሪውን ይለምናል፡፡ ካህናቱም በቤተ ክርስቲያን ለበዓሉ የሚገባውን ስብሐተ እግዚአብሔር ያደርሳሉ፤ ኋላም መምህሩ ወይም መሪጌታው ካባ ላንቃ ለብሶ መስቀሉን ይዞ በዓመቱ የሚውሉትን አጽዋማትና በዓላት ያውጃል፤ ባሕር ሐሳብ ያወጣል፡፡ ፍሬያተ ምድር - ዕጣኑ፣ ጧፉ፣ ዘቢቡ፣ ስንዴው - በመሶበ ወርቅ እየቀረበ ይባረካል፡፡
በቤተ ክርስቲያናችን ሥርዐት እያንዳንዱ ወንጌላዊ አንዳንድ መጠሪያ ዓመት አለው፡፡ ይህም ማለት በአራተኛው ዓመት መጨረሻ ለመጀመሪያው ይደርሰዋል፤ “በዮሐንስ እረስ በማቴዎስ እፈስ” እንዲሉ፡፡ ያለፈው 2004 ዓ.ም ዘመነ ዮሐንስ ሦስተኛው ሚሌኒየም ከገባበት 2001 ዓ.ም ዘመነ ማቴዎስ ተነሥቶ የተጀመረው የአራት ዓመት ዐውድ የተፈጸምበት ነው፡፡ ዐዋጅ፤ ዐዋጅ፤ ዐዋጅ፤ ዮሐንስ ተሻረ ማቴዎስ ተሾመ፤ “ዮም ሠረቀ ለነ ዘመነ ማቴዎሰ ወንጌላዊ ቡሩክ ያብጽሐነ እስከ ዘመነ ማርቆስ ዜናዊ በሰላመ እግዚአብሔር አብ አሜን፡፡”
ቸር ወሬ ያሰማን፣
አሜን
8 comments:
This Like Kahinat is cheating us... What he did here in USA few months back was a real fact to disrupt the effort of MK. NOw he is going there and trying to be MK as it is correct.
Like kahinat Hulem endemilew... Akahedewon Biyasamiruna balubet bitsenu tiru new...
ቁሙና አንድ ላይ ሆነን ለቤተ ክርስቲያናችን የወደፊት እጣ በሰው ሰውኛ የሚቻለንን እናድርግ!
እኔ በደካማው አዕምሮዬ ሳንሰላስለው የብጹዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሪዎስ ወደ መንበራቸው መመለስ የግድ ይመስለኛል::
እሳቸው ግን ብቅ ብለው ቡራኬያቸውን ቢሰጡን እንዴት መልካም ነበር:: ለነገሩ የቤተ ክርስቲያኗ ሁኔታ እንዲህ ተበላሽቶ ሲያዩት ግኑኝነታቸውን ከአምላካቸው ጋር አድርገዋል:: እንደምሰማው ከሆነ በጣም የጸሎት አባት ናቸው:: ምግብ እንኳን አልበላ እያሉ አንጀታቸው ታጥፎ በእግዚአብሔር እርዳታ ነው የዳኑት!
የቤተ ክርስቲያናችንን አንድነት ለማየት ያብቃን!!!