(አንድ አድርገን ሐምሌ 28 ፤ 2004 ዓ.ም)፡-ባሳለፍንው እሁድ በደብረሊባኖስ ገዳም ችግር መፈጠሩን ገልጸን ችግሩን አጣርተን እንደምንመለስ ቃል ገብተን ነበር ፤ በዚህ ዓመት አንጻራዊ ሰላም ከሰፈነበት ገዳም ውስጥ አንዱ ደብረሊባኖስ ነው ፤ ከየካቲት ወር ጀምሮ ዝቋላና አሰቦት ገዳም የእሳት ፈተና ሲያጋጥማቸው ታላቁ ገዳም ዋልድባ ደግሞ የህልውና ፈተና አጋጥሞታል ፤ በዚህ ጊዜ አንዳች ነገር ያልተሰማበት ገዳም ቢኖር ደብረ ሊባኖስ ብቻ ነው ፤ ይህን ሰላም የማይፈልጉት ሰዎች ባለፈው እሁድ በፈጠሩት ችግር ብዙዎችን እስር ቤት እንዲወርዱ ምክንያት ሆኗል ፤ “ማርያም” ነኝ ብላ በተነሳችው ሴት ተከታዮቿ እና ይህን በሚቃወሙ መነኮሳት እና የአካባቢው ምዕመን መካከል ግጭት ተፈጥሯል ፤ ፤ የዛሬ ዓመት ደብረ አሚን አቡነ ተክለኃይማኖት ቤተክርስትያን ችግር በመፍጠር ምዕመኑን በማታለል ፖሊስ ይዟቸው የነበሩት እነዚህ ሰዎች በጊዜው ክስ ስላልተመሰረተባቸው እንደ ተራ ወንጀል ተቆጥሮላቸው እስር ቤት አድረው በቀላሉ በመለቀቃቸው አሁን በቤተክርስቲያናችን ላይ ሌላ ችግር እየፈጠሩ ይገኛሉ፡፡
በቁጥር 25 የሚሆኑት
እነዚህ ሰዎች መጀመሪያ ቦታው ላይ ከደረሱ በኋላ ወደ ደብረ አስቦ ዋሻ ወርደው ነበር ፤ ደብረ አስቦ ዋሻ ደርሰው ወደ
ቤተክርስቲያኑ ከተመለሱ በኋላ መሪያቸውን ማርያም እንደሆነች ፤ ለሌላዋ ሰሎሜ ፤ ለወንዱ ዮሴፍ በማለት ራሳቸውን በገዳሙ
ላገኟቸው ጥቂት ምዕመናን ማስተዋወቅ ጀመሩ ፤ የዛሬ 2000 ዓመት የተከናወነን ተግባር አሁን እነርሱ እንደሚያከናውኑትና ራዕይ
ተገልጾላቸው ከኢትዮጵያ እና ከኤርትራ ጠርዝ ከሚገኝ ገዳም እንደመጡ ተናገሩ ፤ ይህን ህልም የሚመለስል ነገር ግን በአደባባይ
እየተፈጠረ ያለን ክህደት የተመለከቱት የገዳሙ የአብነት ተማሪዎች መነኮሳት አባቶችን በመጥራት የሚሰሩትን ስራ እንዲመለከቱ
አደረጉ ፤ ይህን ጊዜ መነኮሳት በትህትና እዚህ ማስተማር እንደማይችሉ ፤
የገዳሙን ክብር ለመጠበቅ ሲባል ገዳሙን በሰላም እንዲለቁ ረጋ ብለው በአባታዊ ምክርና ተግሳጽ ተናገሯቸው ፤ ይህን
ነገር የሰሙት እነዚህ 25ቱ ሰዎች ቀድሞ ራሳቸውን ለድብድብ ስላዘጋጁ በተላለፈላቸው ነገር ባለመስማማት ፤ ከገዳሙ ማንም
እንደማያስወጣቸው በመግለጽ በአብነት ተማሪዎች ፤ በጥቂት ምዕመናንና በእነዚህ ፀጉረ ልውጥ ሰዎች አማካኝነት ግጭት ተለኮሰ ፤
ይህን ጊዜ 25ቱ ሰዎች በአንድ ወገን ሲሆኑ ምዕመኑ ፤ የአካባቢው ሰውና የአብነት ተማሪዎች በሌላ ወገን ሆነው የለየለት ድንጋይ
ውርወራ ጀመሩ ፤ በገዳሙ አካባቢ ችግር እንደተከሰተ መረጃ የደረሰው የአካባቢው ፖሊስ ጥቂት የፖሊስ ኃይል ወደ ቦታ ልኮ ግጭቱን
ለማስቆም ቢሞክርም ችግሩ ከአቅሙ በላይ በመሆኑ ከደብረ ጽጌ
ወረዳ ፖሊስ ችግር መፈጠሩን ፤ መቆጣጠር እንዳቃተውና ከአቅሙ በላይ መሆኑን በመጠቆም ከወረዳው ተጨማሪ ፖሊሶች በማስላክ
በቁጥጥር ስር ለማዋል ሞክሮ ነበር ፤ ነገር ግን ለሁለተኛ ጊዜ የተጨመሩት ፖሊሶች ግጭቱን ማስቆም ስላልቻሉ ከፍቼ ከተማ ልዩ የፖሊስ ኃይል ተልኮ ግጭቱን
ለማስቆም ያላሰለሰ ጥረት በማድረግ ከሰዓታት በኋላ በቁጥጥር ስር ማዋል ቻለ ፤ ፖሊስ ግጭቱን በቀላሉ ማስቆም ያልተቻለበት አንዱ
ምክንያት እነዚህን ሰዎች በቀላሉ ማወቅ አለመቻሉ ነበር ፤ ከእነዚህ 25 ሰዎች በስተጀርባ ያሉ ለአካባቢው አዲስ የሆኑ ሰዎች
ድንጋይ ውርወራ ላይ ከመሳተፋቸው በተጨማሪ ሁለት የሙስሊም ቆብ የለበሱ ግለሰቦችም እንደነበሩ ከቦታው ከነበሩ የአይን እማኞች
ለማረጋገጥ ተችሏል ፤ በዚህ ሂደት የፖሊስ ምክትል አዛዡ የመፈንከት አደጋ ደርሶበታል ፤ ፖሊስ ሁኔታውን ከተቆጣጠረ በኋላ
25ቱን ሰዎች በቁጥጥር ስር ሲያውል ፤ ከእነሱ ጀርባ ሆነው ድንጋይ በመወርወር መከታ የሆኗቸው ሁለት የሙስሊም ቆብ የለበሱ
ሰዎች እና ሌሎቹ ግን በጊዜው መያዝ አልቻለም፡፡ መጀመሪያ የነበሩት ሰዎች 25 ቢሆኑም ግጭቱ ሲነሳ ግን ለመቆጣጠር እስኪከብድ
ድረስ በዝተው ታይተዋል ፡፡
(የዛሬ ዓመት በምስራቅ
ሀረርጌ ሂርና አካባቢ ከወሎ አካባቢ ተነስቶ የቤተክርስቲያንን
ትምህርት ጠንቅቆ የተማረ የእስልምና ተከታይ ሰው የቤተክርስትያን አስተዳዳሪ ሆኖ እንደሰራና በጊዜው በወንድሞች ብርቱ ክትትል
ተደርሶበት ፖሊስ እስር ቤት እንዳወረደው በወቅቱ መጻፋችን ይታወቃል )
ፖሊስ እነዚህን ሰዎች
በቁጥጥር ስር ካዋላቸው በኋላ ቃላቸውን ሲሰጡ ራዕይ ተገልጦላቸው ከኤርትራ እና ከኢትዮጵያ መሃል ከሚገኝ ገዳም ተነስተው
እንደመጡም ገልጸዋል ፤ በተጨማሪም የማኅበረ ሥላሴ ገዳም አባል
ለመሆናቸው መታወቂያቸው አቅርበዋል ፤ ሁሉንም ታሳሪዎች ፖሊስ ለተጨማሪ ምርመራ እስር ቤት አቆይቷቸዋል፡፡
ይህ ጉዳይ ያሳሰበው
ጠቅላይ ቤተክህነት ሁኔታውን ለማጣራት እና ተፈጠረ የተባለውን ችግር ለመመልከት የቤተክህነት ምክትል ስራ አስኪያጁን አቶ ተስፋዬ
ውብሸትን ከ3 ቀን በኋላ ወደ ቦታው ልኳል ፤ ቤተክህነቱ የሚታወቅበት አንዱ ጸባይ ቀድሞ የመከላከል ስራ ካለመስራቱም በተጨማሪ
ችግሮች ከተፈጠሩ በኋላ ዘግይቶ መንቃት መቻሉ ነው ፤ ከ3 ወር በፊት በዝቋላ ገዳም በተከሰተው የእሳት አደጋ እሳቱ ደኑን
ለማጥፋት ጥቂት ቀናት ሲቀረው የአደጋውን አጣሪ ቡድን ወደ ቦታው መላኩ ይታወሳል ፤ ከዚህ በተጨማሪም ይህን የመሰለ ገዳሙን
“ነበር” የሚያስብል የእሳት ሰደድ እየተንቀለቀለ ሳለ ከቤተክህቱ ወደ ገዳሙ እንዲሄዱ የተመረጡት ሰዎች ቦታው ለመሄድ የቀን
አበሉ ያንሳል ሙግት ውስጥ መግባታቸውም የሚታወስ ነው፡፡
ይህ መረጃ “አንድ
አድርገን” ኢትዮጵያ ውስጥ መዘጋቷ መረጃው እንዲዘገይ አንዱ ምክንያት ሆኗል ፤ አሁን ግን የመዘጋት ችግሩን አዲስ ድረ-ገጽ
በመክፈት ችግሩን ለጊዜው ደግመው እስኪዘጉት መፍታት ስለቻልን ወደፊት በአዲሱ ድረ-ገጽ(www.andadirgen.org) መረጃዎችን እንደ
ቀድሞ በወቅቱ ለማቅረብ እንሞክራለን፡፡ ውጥረት የበዛባት ፊኛ “የት ሄጄ ልፈንዳ” ያለችውን ነገር ትዝ አስባሉን ፤ ከወደ
አሜሪካ ብሎጋችንን ለማዘጋት ሚስጥራዊ ስብሰባ ያደርጋሉ ፤ መንግስት ደግሞ ብሎጋችን ለመዝጋት ለሚመለከተው አካል ደብዳቤ ይጽፋል
፤ እኛስ “የት ሄደን እንጻፍ ፤ የትስ ሄደን ያየነውንና የሰማነውን እንመስክር?”
ስለዚች ወይዘሮ መረጃዎችን በቅርቡ እናቀርባለን፡፡
እኛንም ቸር
ያሰማን
No comments:
Post a Comment