(አንድ አድርገን ሐምሌ 23 ቀን 2004 ዓ.ም)፡- የዛሬ 102 ዓመት ወደ ኋላ ሄደን ታሪካችንን ስንቃኝ በጊዜው ዋልድባ ገዳም ቤተ ሚናስና ለቤተ ጣዕመ ክርስቶስ ማህበረ መነኮሳት መካከል በተነሳው የኃይማኖት ችግር በገዳሙ ውስጥ ያሉትን አባቶች ለብዙ ጊዜ ካከራከራቸው በኋላ ከማዕከላዊ መንግስት አፄ ምኒሊክ ዘንድ ጉዳዩ ደርሶ ምን ዓይነት መልስ እንደጻፉላቸው ለእናንተው አስተማሪ ሆኖ ስላገኝነው ለማቅረብ ወደድን፡፡
ቅድመ ታሪክ
አባ ጣዕመ ክርስቶስ ወደ ዋልድባ ገዳም ሲገቡ ከውጭ መንኩሰው ነበር ፤ ስምረትን ግን የተቀበሉት ዋልድባ ገባም ውስጥ ማይፈዴ በተለይ አይጠየፍ ከተባለው ቦታ መሆኑን መዛግብት ያስረዳሉ ፤ ስምረትንም ያነሱአቸው አባት ናኩቶ ለአብ የመንፈስ ቅዱስ ልጃቸው የሆኑት አባ ገብረሚካኤል ናቸው ፤ እኒህ ሰው የሚታመሙትን መነኮሳት ሁሉ ሳይሰቀቁና ሳይጠየፉ ሁሉን አቅፈው ደግፈው ስለሚያስታምሙ አይጠየፍ የሚል ቅጽል ስም ተሰቷቸዋል ፤ ስለዚህ አብዛኛውን ጊዜ አባ ገብረሚካኤል በማለት ፋንታ አባ አይጠየፍ እየተባሉ ይጠሩ ነበር ፤ ይህን በጎ ተግባር ሲፈጽሙበት የነበረውም ቦታ በርሳቸው ስም አይጠየፍ እየተባለ እስከአሁን ይጠራል፡፡
አቡነ ጣዕመ ክርስቶስ ወደ ዋልድባ ገዳም የገቡት በ1823 ዓ.ም ነበር ፤ አባ ጣዕመ ክርስቶስ ከቤተ እስጢፋኖስ ቤት ገብተው ጥቂት ዘመን እንደቆዩ ለእስጢፋኖስ ቤት አበምኔት ሆኑ ፤ ወዲያው የአባ እስጢፋኖስ ስም ተዘርዞ የአባ ጣዕመ ክርስቶስ ስም ተተክቶ ቤተ ጣዕመ ክርስቶስ ተብሎ ተሰየመ፡፡ ነገር ግን የአቡነ እስጢፋኖስ ስም ተሰርዞ የአባ ጣዕመ ክርስቶስ ስም ቢተካም ፊት እንደቆየው ስርዓት በሊቀ አበምኔቱ ሥልጣን ስር ሆነው በሰላምና በፍቅር ቆዩ እንጂ ከሊቀ አበምኔቱ ስልጣን ስር ወጥቼ እራሴን ችዬ እኖራለሁ ሲሉ ያቀረቡት ሃሳብ አልነበረም፡፡
አባ ጣዕመ ክርስቶስ ካረፉ በኋላ ፤ ሲያስተዳድሩት የነበረው ማህበር እየተዳከመ እና እየተመናመነ ስለሄደና የቀሩትንም ጥቂቶቹ መነኮሳት በዋሻ የነበረውን ችግርና ፈተና ሊቋቋሙት ባለመቻላቸውና ክፉ ዘመን ስለገባ መጻህፍቶቻቸውን ትተው ቀርተው የነበሩ 5 መነኮሳት በሙሉ ከገዳሙ ወጥተው ሄዱ፡፡ በዚህ ጊዜ ሊቀ አበምኔት የነበሩት ገብረ ክርስቶስ የሚናስ ልጅ ጌታዬ መምህር ማኅጸንተ ጊዮርጊስ ደወል ደውለው ማህበሩን ከውነው የአቡነ እስጢፋኖስን መጻህፍት ሰብስበው ምልክት አድርገው ወደ እቃ ግምጃ ቤት እንዲቀመጥና ወደ ፊት የእስጢፋኖስ ልጆች በመጡ ጊዜ አትከልክሏቸው ስጧቸው ብለው ለመነኮሳቱ ተናገሩ ፤ ከተሰደዱት ከ5 መነኮሳት የችግር ጊዜው ካለፈ በኋላ ሁለቱ በ1886 ዓ.ም ተመልሰው መጥተው ከገዳሙ ገብተው በቆየው ስርዓት መሰረት ለመቀመጥ ማህበሩን ጠየቁ ፤ በዚህ ጊዜ መከራውን ታግሰው ፤ ታቦታቸውንና መጻህፍቶቻቸውን ጠብቀው ማህበሩ እንዳይፈታ ተንከባክበው ከውነው የቆዩት ገብረ ክርስቶስ የሚናስ ልጆች ከእኛ ጋር ተቀላቅላችሁ ልትኖሩ ሌላ ደውል ላትተክሉ አበምኔትም ላትሾሙ በዚህ ቃል ግቡና ተቀመጡ አሏቸው፡፡ እነርሱም ለጊዜው ከዚህ የተሻለ አማራጭ መንገድ ስላልነበራቸው በዚህ ውል ተስማምተው ስምምነቱንም በጽሁፍ ተጻጽፈው ከማህበሩ ተቀላቀሉ ፡፡ ከማህሩ ተቀላቅለው ለ7 ዓመት አብረው ከኖሩ በኋላበ1893 ዓ.ም ከዋሻ ተነስተው ወደ ጥንት ቦታቸው አሁን ወዳሉበት ወረዱ ፤ በዚያ ጊዜ የአቡነ ጣዕመ ክርስቶስ ልጆች መበርከት ጀመሩ ፤ ይህን ሁኔታ እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም “ራሳችንን ችለን ደውል እንተክላለን ፤ አበምኔትም አንሾማለን” ሲሉ ክርክር አበቀሉ ፤ የቤተ ሚናስ ቤቶችም “የለም ቃላችሁን ልታፈርሱ መሃላችሁን ልትጥሱ አይገባም ፤ ከእኛ መለየት የለባችሁም” ሲሉ ተከራከሩ ፡፡ ነገሩ ከዚያው ከቤታቸው መፍትሄ ሊያገኝ ባለመቻሉ ተያይዘው ወደ አጼ ምኒልክ ዘንድ አዲስ አበባ በ1900 ዓ.ም ሄዱ ፤ ሁለቱም ወገኖች ከእቴጌ ጣይቱ ብጡል ቀርበው ነገራቸውን አስረዱ ፤ እቴጌም ለማስማማት ብዙ ጥረት አደረጉ ፤ ነገር ግን የሁለቱ ማኅበራት ተወካዮች ሊስማሙ ባለመቻላቸው “ወደፊት አንድ መፍትሄ እስኪደረግለት ድረስ እንደ ጥንቱ ሁናችሁ ቆዩ” ብለው አሰናበቷው ፡፡ ስለሆነም እቴጌ “እንደ ጥንቱ” ሲሉ ደውላችሁን ተክላችሁ ፤ አበምኔታችሁን መርጣችሁ ፤ በሊቀ አበምኔታችሁ ስር ሆናችሁ ቆዩ ማለታቸው ነበር እንጂ አንደኛውን ለይታችሁ ተቀመጡ ማለታቸው አልነበረም፡፡ ስለሆነም ይህን ምክንያት በማድረግ ቤተ ሚናስና ቤተ ጣዕመ ክርስቶስ ፈጽመው ተለያዩ ፤ ከላይ እስጢፋኖስ ዝቅ ሲል የጣዕመ ክርስቶስ ልጆች የሆኑት የጣዕመ ክርስቶስ ቤት ብለው ክፍል ለዩ ፤ ከኛ መለየት አይገባችሁም ብለው ሲከራከሩ የነበሩት ከላይ የገብረ ክርስቶስ ዝቅ ሲል የሚናስ ልጆች የሆኑት ቤተ ሚናስ ብለው ክፍል ለዩ ፤ ይህ ሁሉ የሆነው በ1900ዓ.ም ነበር ፡፡
ይህ ከሆነ ከጥቂት ጊዜ በኋላ “መሬቱንም ውሃውንም አካፍሉን የአባታችንን የእስጢፋኖስን መጻህፍቶች አስረክቡን” ብለው ጠየቁ ፤ የቤተሚናስ ማህበርም ጠብቀው ያቆዩትን መጻህፍት የእስጢፋኖስ ድረሻ የሆነውን አስረከቡ ፤ እንዲሁም መሬቱንና ውሃውንም ከፍለው ሰጡ ፤ በዚህ ገዳም ውስጥ ከአቡነ ሳሙኤል ቀጥለው በጣም ጎልተው የሚታወቁት አቡነ ሚናስ ናቸው፡፡ አቡነ ሚናስ የማህበሩ መብራትና ምሰሶ የፍቅር የአንድነት ሃይማኖት ምንጭ የነበሩ ትልቅና ቅዱስ የሆኑ አባት ናቸው፡፡ ከተለያዩም ወዲህ ቤተ ሚናስ ለብቻቸው አንድ መምህር መሾም ጀመሩ እንዲህም ከተደረገ በኋላ ለጠቡና ለክርክሩ መነሻ የሆነውን የአትክልት ቦታ እንዲሁም በገጠር ያለውን ርስት ጉልት ተከፋፈሉ ፡፡ ሌላ ቤተክርስትያን እንዳይተከል ተደርጎ ጥንት አባቶቻቸው በአንድ ላይ ሁነው ሲጸልዩባት የነበረችው የአቡነ ገብረክርስቶስ ታቦት በታቦተ ኪዳነምህረት ብቻ እንዲጸልዩ ተስማሙ ፤ በዚህ ዓይነት ነገሩ አልቆ ለጥቂት ጊዜ ሰላም ተፈጥሮ እንደኖሩ በአትክልቱ እና በጉልቱ ሲያጣላቸው የነበረው ሰይጣን ነገሩን ወደ ኃይማኖት አዞረና በኃይማኖት ምክንያት(በሚስጥረ ስላሴ) ጥል ተጀመረ፡፡ በፊት በርስቱ ሲጣሉ የነበሩ ሁለቱ ማህበራት ችግራቸው አልፎ አልፎ ካሆነ በቀር ወደ ውጭ አይወጣም ነበር ፤ በዚያን ወቅትም ብዙዎች መነኮሳት አይተባበሩም ነበር፡፡ በኃይማኖት ምክንያት በተነሳው ጠብና ክርክር ግን ሁሉም ተባበሩ ፤ ብዙ ትሩፋትና ተዓምራት በተሰራባት ቦታ ሁከትና ጸብ ጸናባት ፤ መካነ ፈላስያን መካነ ግሁሳን ገዳማት የተባለችው ቦታ የሁከት ቦታ ከመባል ደረሰች ፤ በኃይማኖት ምክንያት በተነሳው ጥል ከገዳማቸው ተነጋግረው መፍትሄ ሊሰጡት ባለመቻላቸው ጠቡና ክርክሩ እየባሰ ሄዶ አጼ ምኒልክ ዘንድ አደረሳቸው፡፡ አጼ ምኒልክም በጊዜው በነበሩ ሊቃውንት አማካኝነት ይህን ደብዳቤ ላኩላቸው፡፡
ሞአ አንበሳ ዘእምነገደ ይሁዳ ዳግማዊ ምኒልክ ሥዩመ እግዚአብሔር ንጉሠ ነገሥት ዘኢትዮጵያ
በሃይማኖት ነገር አንድ መለኮት ሶስት መለኮት በማለት እርስ በርሳችሁ ስለተጣላችሁበት አባቶቻችን ሐዋርያት300 ሊቃውንት ከጻፉት መጻህፍት አዋጥተን እንጽፍላችኋለን ቃሉም ይህ ነው፡፡
ወላጅ መለኮት(አብ) ተወላጅ መለኰት(ወልድ) ሠራጺ መለኮት በአካል ሦስት በግብር ሦስት በስም ሦስት ነው ፤ በመለኰት በባሕርይ በፈቃድ አንድ ነው ፤ እንጂ 3 መለኰት ብሎ በአኃዝ አይነገርም፡፡
ምስክር አግናጥዮስ የጳጳሳት አለቃ በአንጾኪያ እንዲህ ብሏል ፤ “ይህች ሦስትነት ያለመለየት ያለመለወጥ በሦስት አካላት በአንድ መለኰት የተካከለች ናት እነዚህን ሦስቱ አካላት በጌትነት በክብር ፍጹማን ናቸው በአንድ መለኮት አንድነትም አንድ ናቸው፡፡ ይኽውም ሦስትነት ከእርሱ የሚገኝ አንድ ብርሃን ነው በዓለም ሁሉ ሙሉ ነው፡፡”
አትናቴዎስ ፤ ሐዋርያውም የእስክንድርያ ሊቀ ጳጳሳት “አብ አምላክ ነው ወልድም አምላክ ነው ፤ መንፈስ ቅዱስም አምላክ ነው ፤ ግን ሦስት አማልክት አይባሉም ፤ አንድ አምላክ ነው እንጂ ሁለተኛም የሦስቱ አካላት መለኰት እንደሆነ ቅዱሳት መጽሐፍት ያስረዳሉ እነዚህም አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ ናቸው ፤ መለኮት አንድ ነውና የአብ የወልድ የመንፈስ ቅዱስ የባሕርይ አንድነታቸው ነው ፤ የሦስቱ አካላት መለኰት አንድ እንደሆነ በዚህ አወቅን፡፡ እነርሱም በመለኮት ከአብ ጋር አንድ ነውና መለኮት የማይከፈል አንድ ሲሆን ሥላሴ በሦስት አካል ፍጹም ነው፡፡ በሦስቱ አካላት ስም እንደማያምኑ እንደተረገሙ እንደ ፎጢኖስ እንደ መርቅሎስ ሦስቱን አካላት አርዮስም እንደካደ የሦስቱን አካላት አንድ መለኮት አንክድም አናቃልልም” ብሏል፡፡
ባስልዮስ የቂሳርያ ኤጲስ ቆጶስ “የሶስቱ አካላት መለኮት ፍጹም አንድነትን ልናውቅ ይገባል ፤ የእነርሱ የሚሆን አንድ መለኮትን አንድ በማድረግ እናዋህድ በአብ ወላዲነት አስራጺነት መለኮት አንድ አንደሆነ ኃይማኖትን እንመን ፡፡ ወልድ ከአብ ተወልዶአልና መንፈስ ቅዱስም ከአብ ተገኝቷልና አብ ከወልድ ወልድም ከመንፈስ ቅዱስ ሳይቀድም ፤ ወልድ ከአብ በመወለዱ መንፈስ ቅዱስም ከአብ በመስረጹ የፈጣሪያችን የሦስትነቱ መለኮት አንድ ይሆናል” ብሏል፡፡
ቄርሎስም የእስክንድርያ ሊቀ ጳጳስ “አብ በአካሉ ፍጹም አንድ ነው ፤ ወልድም በአካሉ ፍጹም አንድ ነው ፤ መንፈስ ቅዱስ በአካሉ ፍጹም አንድ ነው ፤ እነዚህ ሦስቱ እንደ መንግስት ማዕረግ አይደሉም ባሕርያቸው አንድ አገዛዛቸው አንድ ነው እንጂ” ብሏል፡፡
ዮሐንስም የኢየሩሳሌም ኤጲስ ቆጶስ እኒህ ሦስቱ አካላት በመልክዕ ፍጹም ሆነው በመለኮት አንድ እንደሆኑ እናምናለን ብሏል ፡፡ ጎርጎርዮስም ዘእንዚናዙ ስለ ሦስት አካላት ትክክልነት ስለማይከፈል ስለ መለኮት አንድነቱ እንዲህ አለ ፤ “ከሁሉ አስቀድሞ በአካል ልዩ በክብር አንድ የሚሆን ሦስትነትን እናስተምራለን እነዚህም አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ ናቸው፡፡”
ሥላሴ በመለኮት አንድነት መለየት የለባቸውም ፤ አካላት ግን በባሕርይ መለየት ሳይኖር እየአንዳንዱ አካል በገጽ በመልክ ፍጹም ነው ብሏል፡፡ ዮሐንስም የእስክንድርያ ሊቀ ጳጳሳት “እኛስ ወልድን ከአብ ከመንፈስ ቅዱስ ጋር በመለኮት አንድ እንደሆነ እናምናለን” አለ ፡፡ የሦስቱ አካላት መለኮት አንድ እደሆነ የማያምን ሰው ቢኖር እኛ እናወግዘዋለን ብሏል፡፡
ብንያም ፤ የእስክንድርያ ሊቀ ጳጳሳት በአካል ሦስት በባሕርይ አንድ የሚሆኑ በተመሰገኑ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ እናምናለን እንበል ሦስት አካላት በስራው ሁሉ በማድረግ ፤ በመናገር በመለኮት አንድ ናቸው ብሏል፡፡
ባስልዮስም የአንፆኪያ ሊቀ ጳጳሳት እነርሱ መለኰት ባሕርይ እንደሆኑ በእነርሱ አምናለሁ እታመናለሁ ልዩ ልዩ የሚሆኑ አካላት ከመለኰታዊ ባሕርይ ልዩ ናቸው አልልም መለኮትስ አካላት ነው ፤ እነዚህ ልዩ የሚሆኑ ገጻት ናቸው፡፡
አባ መቃርስም የእስክንድርያው ሊ ጳጳስት እኛ የሦስቱ አካላት ባህርይ አንድ እንደሆነ የሦስቱ አካላት ባሕርይም መለየት እደሌለበት እናውቃለን መለኮት ሦስቱን አካላት አንድ እንደሚያደርግ የታወቀ ነው ብሏል፡፡ ዮሐንስም የእስክንድርያው ሊቀ ጳጳሳት በአካል ሦስት በመለኮት አንድ ናቸው ፤ አንድነትን ሶስትነትን የተናገረ ጎርጎርዮስ የሦስቱ አንድ ነው ሦስቱም በመለኮት አንድ ናቸው ብሎ ተናግሯል፡፡
ሁለተኛም ከቴዎዶስዮስ እኛስ ብዙ አማልክትን የሚያምኑ በባህርይ መለኮቱ በማይከፈል በአንድ እግዚአብሔር ልዩ ባሕርያትን የሚናገሩ የመናፍቃን ነገር እንነቅፋለን ደግመኛም የአብ የወልድ የመንፈስ ቅዱስ መለኮት ሦስት ነው የሚሉት እናወግዛለን ብሏል ፡፡
ዮሐንስም የአንጾኪያ ሊቀ ጳጳስ አብ ሕይወት ነው ወልድ ህይወት ነው ፡፡ መንፈስ ቅዱስም ሕይወት ነው ፤ ዳግመኛ አብ አንድ ይባላል ወልድም አንድ ይባላል ፤ መንፈስ ቅዱስም አንድ ይባላል ከአካላት አንዱም አንዱ በባህርይ አንድ ናቸው ፤ አንድ አምላክ ናቸው ፤ ግን ሶስት አማልክት አይባሉም ማመናችንም እንደ ሦስት ሰዎች ሦስት አማልክት ብለን በሦስት መለኮት አይደለም ፤ ልዩ በሆኑ በሦስቱ አካላት በሦስቱ ገጻት አንድ ባሕርይ አንድ መለኮት ገንዘብ በሚሆኑ ገጻት በስም በግብር ሦስት ናቸው ብለን እናምናለን እናሳምናለን ብሏል፡፡
እንግዲህ በዚህ ጸንቶ መኖር ነው ፤ ከዚህ ቃል የወጣ ሰው ቢገኝ በሥጋው መንግስት ይቀጣዋል በነፍሱም አባታችን አቡነ ማቴዎስ አውግዘዋል፡፡
በግንቦት በ24 ቀን 1902 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተማ ተጻፈ፡፡
ቸር ሰንብቱ
ግብአት ፡- የዋልድባ ገዳም ታሪክ (ከበሪሁን ከበደ)
4 comments: