ማውገዝ በዘይቤ፣ በአገባብ ይኹን በምስጢር ብዙ ፍችዎች አሉት፡፡ ማውገዝ መለየት፣ መካድ፣ መርገም፣ መፍረድ፣ ማሰር፣ መወሰንና ሥርዐት መሥራት ማለት ነው፡፡ ኢአማንያንን፣ መናፍቃንንና ክፉዎችን ከምእመናን፣ ከቤተ ክርስቲያን፣ ከጉባኤ እግዚአብሔር እና ከምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያን ማለትም ከቅዱስ ቍርባንና ከመሳሰለው ሁሉ የሚለይ መንፈሳዊ መቍረጫ ውግዘት ነው፤ “የሚያውኳችኹ ይቆረጡ” እንዲል(ገላ.5÷11)፡፡
ውግዘት መንፈሳዊ ሰይፍ ነውና ኢአማንያንን ከአማንያን ይለያቸዋል፡፡ ማውገዝ ሰይጣንን በሃይማኖትና በሥራ መካድ ነው፡፡ “ዘይፈቅድ ይጠመቅ ይምሀርዎ ያውግዝ ሰይጣነ ወይእመን በክርስቶስ - ሊጠመቅ የፈቀደውን ሰው ሰይጣንን እንዲክድና በክርስቶስ እንዲያምን ያስተምሩት፤” እንዲል (ዲድስቅልያ 34) ፡፡ በጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ላይ ልዩ ልዩ የክሕደት ትምህርት አንቅተው ያስተማሩ መናፍቃን ላይ የቤተ ክርስቲያን ርምጃ “ታወግዞሙ፤ ወትረግሞሙ፤ ትፈልጦሙ፤ ወትመትሮሙ” በሚሉ ኀይለ ቃላት በሃይማኖተ አበው መጽሐፍ ላይ ተገልጾ እናገኛዋለን፤ ፍቺውም ቤተ ክርስቲያን ታወግዛቸዋለች፤ ትረግማቸዋለች፤ ቆርጣ ትለያቸዋለች ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ማውገዝ መርገም ነው፤ መወገዝ መረገም ነው፡፡
ማውገዝ መፍረድ ነው፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለቅዱሳን ሐዋርያቱ የማሰርና የመፍታት ሥልጣን ሰጥቷቸዋል፡፡ ይህም እስከ ኅልፈተ ዓለም ድረስ የሚሠራ እንጂ በእነርሱ ብቻ ተወስኖ የቀረ አይደለም፡፡ “እውነት እላችኋለኹ፤ እናንተስ የተከተላችኹኝ በዳግመኛ ልደት የሰው ልጅ በክብሩ ዙፋን በሚቀመጥበት ጊዜ እናንተ ደግሞ በዐሥራ ሁለቱ የእስራኤል ነገድ ስትፈርዱ በዐሥራ ሁለት ዙፋን ትቀመጣላችኹ፤” ብሏቸዋል፡፡ (ማቴ.19÷28) ስለዚህ ሐዋርያት በምድር የፈረዱት ፍርድ በሰማይ አይገሠሥባቸውም፤ ማለትም በሥልጣነ ክህነታቸው በምድር ላይ የሠሩት ማንኛውም ዐይነት ሥራ፣ ውሳኔና ፍርድ በዳግም ምጽአት ይጸናል ማለት ነው፡፡ ይህም “በምድር ያሰራችኹት በሰማይ የታሰረ ይኾናል፤ በምድር የፈታችኹት በሰማይ የተፈታ ይኾናል፤” (ማቴ. 16÷19) በማለት ፈጣሪ ከሰጣቸው የማሰርና የመፍታት (የማውገዝ) ቃል ኪዳን ጋራ የሚዛመድ ነው፡፡
ማውገዝ መወሰን፣ ማሰር፣ ሥርዐት መሥራት ነው፡፡ የተሳሳተ እምነትንና ትምህርትን ይህ ሐሰት ነው ብሎ“ማሰር”፣ ይህ ደግሞ እውነት ብሎ “መፍታት” የማውገዝ ሥልጣንን የሚያሳይ ነው፡፡ ሰይጣንንና ሠራዊቱን ኀይል ማሳጣትና ማሰርም የማውገዝን ሥልጣን ያመለክታል፡፡
በአጠቃላይ ማውገዝ አጥፊውን ሰው በሥጋውና በነፍሱ ማሰር፣ መንፈሱን መግታት፣ ትምህርቱንና መጻሕፍቱን መከልከል ነው፡፡ እንዲህ ባለ ክፉ ሰው ላይ አድሮ የሚሠራውንም ርኵስ መንፈስ መቃወምና ማድከም፣ ሐሳቡና ዕቅዱ፣ የሰውዬውም ጠማማ እምነት ፍሬ ቢስ እንዲኾን ማድረግ ነው፡፡ ሰውዬው ቢሞት እንኳ ያደረበት መንፈስ የሚሞት አይደለምና የዘራው ክፉ ዘር እንዳያፈራ ማገድ የውግዘት ዓላማ ነው፡፡ ሰው ይኹን ተቋም እምነቱ፣ ድርጊቱ ተመርምሮ ሲደረስበት ክፉ ኾኖ ከተገኘ÷ ከሞተ በኋላም እንደ ግለሰብ ይኹን እንደ ሥርዐት (ተቋም) ሊወገዝ ይችላል፡፡ ይህ ባይሆን ኖሮ አርጌንስ ከሞተ ከ294 ዓመታት በኋላ ከነመጻሕፍቱ ባልተወገዘ ነበር፡፡ (የቤተ ክርስቲያን ታሪክ በዓለም መድረክ፤ ገጽ 86)
ውግዘትን የሚያስከትለው እምነትና ተግባር
አንድ ሰው በውግዘት የሚለየው በህልውና እግዚአብሔር ያላመነ ሲኾን ብቻ አይደለም፡፡ በገዛ ፈቃዱ ሥርዐትን ያፈረሰ ሰው በውግዘት ሊለይ ይችላል፡፡ አለመታዘዝ ያስወግዛል፤ “ወእመ ኢተአዘዘ ይትወገዝ መኑሂ በሕገ ቤተ ክርስቲያን፤ የማይታዘዝ ማንም ቢኾን በሕገ ቤተ ክርስቲያን መሠረት ይወገዛል” (ተግሣጽ ዘዮሐንስ አፈ ወርቅ ቁጥር 4)፡፡ ሥርዐት የማያከብር ከቤተ ክርስቲያን እንዲለይ ሐዋርያት በመልእክታቸው ጽፈዋል፡፡ ቃሉም “ወንድሞች ሆይ÷ ከእኛ እንደ ተቀበለው ወግ ሳይኾን ያለሥርዐት ከሚሄድ ወንድም ትለዩ ዘንድ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም እናዛችኋለን፤” የሚል ነው፡፡
ሰው በምግባር ሕጸጽ ይኹን በሃይማኖት ክሕደት ሊወገዝ ይችላል፡፡ አባ አብርሃም ሶርያዊ መማለጃ የሚቀበሉትንና ዕቍባት ያሏቸውን ሰዎች ዕቍባቶቻቸውን እንዲተዉ፣ ክፉ ልምዳቸውን ያርቅ ዘንድ ገዝቷል፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ ንግሥት አውዶክስያን ደኃን ስለበደለች ስለ ክፉ ምግባሯ ገዝቷታል፡፡ (ስንክ ዘታኅ 6፤ ድርሳነ ዮሐንስ የታሪክ ዓምድ)፡፡ ይኹን እንጂ ቶሎ ርምጃ የሚወሰደው ጥፋቱ የሃይማኖት ኾኖ ሲገኝ ነው፡፡ ስለዚህም ጌታችንና ቅዱሳን ሐዋርያት ካስተማሩን ውጭ “ልዩ ትምህርት” የሚያመጣ ሁሉ የተወገዘ ነው፡፡ ከቀድሞው ሌላ መሠረት መሥርቷልና፤ በአበው ትምህርት፣ ወግና ምሳሌነት የማይሄድ ሥርዐት አፍራሽ ነውና፡፡ (2ተሰ.3÷6)፡፡
“ጌታችንን የማይወደው” ሁሉ የተወገዘ ነው፡፡ “ጌታችንን የማይወደው” ማለት ምግባር ያጎደለ ማለት ነው፡፡“ብትወዱኝ ትእዛዜን ጠብቁ” (ዮሐ.19÷15) ስለተባለ ያልወደደ አይታዘዝምና ምግባር ሊኖረው አይችልም፡፡ የሰው አስተሳሰቡም ኾነ ሥራው ውስብስብና እንደጊዜው የሚለዋወጥ ረቂቅ ነው፡፡ ስለሆነም የሚያስወግዙ ክፉ ተግባራትን ሁሉ በተናጠል በመዘርዘር ወስኖ ማስቀመጥ አይቻልም፤ ነገር ግን በሥርዐተ ቤተ ክርስቲያን ከተዘረዘሩት
የማውገዝ ሥልጣን
ማውገዝ ለእግዚአብሔር የባሕርይ ገንዘቡ ነው፡፡ “ምድር ከአንተ የተነሣ የተረገመች ትኹን” (ዘፍጥ.3÷17)፤“ብንክደው እርሱ ደግሞ ይክደናል” (2ጢሞ.2÷13)፤ “በሰው ፊት የሚክደኝን እኔ ደግሞ በሰማያት ባለው በአባቴ ፊት እክደዋለኹ” (ማቴ.10÷33)፡፡ ስለኾነም ሥርዐተ ውግዘትን የሠራ፣ የወሰነ፣ ያሰረ፣ የታሰረውንም የሚፈታ፣ የሚዘጋ፣ የሚከፍት እግዚአብሔር ነው፡፡ (ራእ.3÷7፤ 5÷9)፡፡
ለእግዚአብሔር የባሕርይ ገንዘቡ የኾነው እግዚአብሔር በገንዘቡ የወደደውን ለማድረግ ሥልጣን አለውና በቸርነቱ ይህን ሥልጣን ለአባቶቻችን ካህናት በጸጋ ሰጥቷቸዋል፡፡ (ማቴ.20÷15) “በዘአእመረ መንፈስ ቅዱስ”እንዲሉ “እርሱ መንፈስ ቅዱስ ባወቀው” ይህን ታላቅ ሥልጣን ለካህናት የሰጣቸው ሕገ ወጥ የኾኑ ሰዎችን ሕገ ወጥ የኾኑ ሰዎች ምእመናንን እንዳያናውጧቸው ለምእመናን ድኅነትና ዕረፍት አስቦ ነው፡፡ ቅዱሳን ሐዋርያት የሚያስሩበትንና የሚፈቱበትን ሥልጣነ ክህነት የተቀበሉት ጌታችን እፍ ብሎባቸው “መንፈስ ቅዱስን ተቀበሉ፤ ኀጢአታቸውን ይቅር ያላችኋቸው ይቀርላቸዋል፤ የያዝችኹባቸው ተይዞባቸዋል፤” (ዮሐ.20÷22) ባላቸው ጊዜ ነው፡፡
ይህ የክህነት ሥልጣን በሐዋርያት ብቻ ተወስኖ አልቀረም፡፡ በእግረ ሐዋርያት እየተተኩ፣ የእነርሱን አሰረ ፍኖት ተከትለው እስከ ዳግም ምጽአት ድረስ ለሚነሡና ብቁ ኾነው ለሚገኙ ሁሉ ይህ የሥልጣነ ክህነት ቃል ኪዳን ተነግሯል፡፡ ይህም “እኔ እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ሁል ጊዜ ከእናንተ ጋራ ነኝ” (ማቴ.28÷20) በማለት በተናገረው ቃል ታውቋል፡፡ ሌላውም ምንጭ “ከመለኰትህ ገናንነት ምስጢር ለደቀ መዛሙርትህ እንዳልሰወርኽ እነርሱም ከእኛ የሰወሩት የለም፡፡ ለቤተ ክርስቲያን ሥርዐት ሊቀ ጳጳስ፣ ኤጲስ ቆጶስ፣ ቀሳውስት፣ ዲያቆናት አድርገው ሾሙን እንጂ” በማለት ለቅዱሳን ሐዋርያት የተሰጣቸው የክህነት ሥልጣን ለሐዋርያውያን አበውና ለሊቃውንት መተላለፉን ያስረዳል፡፡ (ቅዳሴ አትናቴዎስ ቁ.1)፡፡
ከአሕዛብ ይልቅ መናፍቃንን፣ ከመናፍቃን ይልቅ ደግሞ የተወገዙ ሰዎችን መጠንቀቅ ይገባል
በአግባቡ ለተወገዙ ሰዎች ያለአግባብ መቆርቆር የአጋንንት ወዳጅ ከመኾን አይዘልም፤ በእግዚአብሔር ሥራ የማይደሰቱ፣ ሰይጣንና ግብረ አበሮቹን የማያወግዙ ሁሉ በእግዚአብሔር ላይ ያመፁ ናቸውና፡፡ በሃይማኖትና በምግባር ከተወገዙ ሰዎች መራቅ ይገባል፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ “ወንድሞች ሆይ፣ ከእኛ እንደተቀበለው ወግ ሳይኾን ያለሥርዐት ከሚሄድ ወንድም ሁሉ ትለዩ ዘንድ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም እናዛችኋለን” በማለት በግልጽ ተናግሯል፡፡ (2ተሰ.3÷6)፡፡ ይህ ቃል ቁርጥ ትእዛዝ እንጂ ምክር አይደለም፤ “እናዛችኋለን” ይላልና፡፡ ከትእዛዝም ጥብቅ ትእዛዝ መኾኑን ደግሞ “በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም” የሚለው ሐረግ ምስክር ነው፡፡ ይህ የሐዋርያው የብቻው ትእዛዝ ሳይኾን በዘመኑና ከእርሱ በኋላ የሚነሡ ቅዱሳን አበው ሁሉ ትእዛዝ ነው፡፡ “እናዛችኋለን” ይላል እንጂ “አዛችኋለኹ” አይልምና፡፡
ምግባር እና ሃይማኖታቸው ከከፋ ከኀጥአን፣ ከቀራጮችና ከአረመኔዎች ጋራ እንዳንተባበር መጽሐፍ ቅዱስ አስጠንቅቆናል፡፡ 1ቆሮ.5÷9፤ 15÷33፤ 2ኛዮሐ. ቁ.10 እና 11፤ 2ቆሮ.6÷14-16፡፡ ከክፉ ሥራችን አንመለስም ብለው በውግዘት የተለዩ ሰዎች ደግሞ ምድባቸው ከአሕዛብ፣ ከአረማውያን፣ ከኀጢአተኞች፣ ከዐመፀኞችና ከመናፍቃን ጋራ ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱሳችን “ቤተ ክርስቲያንን ባይሰማት እንደ አረመኔ እንደ ቀራጭ ይኹንልህ” የሚለው እንደእነዚህ ያሉትን ነውና፡፡ (ማቴ.8÷17) ፡፡ ሥራቸውና ክፋታቸው በግልጽ ከሚታወቅ ከአሕዛብና መመለክያነ ጣዖታት ይልቅ መጠንቀቅና አለመተባበር የሚገባው መናፍቃንን ነው፡፡ ከመናፍቃን በላይ ደግሞ ከተወገዙ ሰዎች መጠንቀቅ ይገባል፤ ምክንያቱም ከአሕዛብ ይልቅ መናፍቃን፣ ከመናፍቃን ይልቅ ደግሞ የተወገዙ ሰዎች ተመሳስሎ የመኖር ሰፊ ዕድል ስላላቸው ነው፡፡ ተመሳስለው ከኖሩ ደግሞ ሌሎችን በቀላሉ ወደራሳቸው የጥፋት ጎዳና ይስባሉ፡፡
ምንጭ፡- ዲያቆን ኅብረት የሺጥላ፤ ትምህርተ ውግዘት፤ 1999 ዓ.ም
No comments:
Post a Comment