Saturday, 30 June 2012
Thursday, 28 June 2012
..........መርከቤ...!......በልዑል ገ/እግዚአብሄር ከፌስቡክ ገጽ ላይ የተወሰደ
የሰማይ መስኮት ተከፈተ
የፀሐይ ውበት ተከተተ
የፀሐይ ውበት ተከተተ
ነጎድጓድ ተደባለቀ
መብረቅ ተባረቀ
የምድር ፍልቅልቂት ፈሰሱ
የውሃ ቆሬዎች ተቸለሱ
መብረቅ ተባረቀ
የምድር ፍልቅልቂት ፈሰሱ
የውሃ ቆሬዎች ተቸለሱ
እንዴ...
መሬት ከውሃ ነው
..........................የተሰራች ?
መሠረቷ ግድግዳዋ
......................ማይ የሆነች!
ግራ ቀኙ ጎርፍ
ላይ ታቹ ዝናመ ዶፍ
አለ ጣይ በረዶው ተኮሰ
ዝርጉ ባህር ተን ተነፈሰ
እምቡቅ እምቡቅ
ማየ አይህ መረቅ
ላይ ታቹ ዝናመ ዶፍ
አለ ጣይ በረዶው ተኮሰ
ዝርጉ ባህር ተን ተነፈሰ
እምቡቅ እምቡቅ
ማየ አይህ መረቅ
ያ ክምችት የውቅያኖስ ሙላት
ነፈረ ተንተከተከ ምድርን አጋላት
ነፈረ ተንተከተከ ምድርን አጋላት
እንጃልኝ....
ከሥጋ ከእፁ ከፍጥረቱ
አንዱም ላይተርፍ ከጥፋቱ
ከሥጋ ከእፁ ከፍጥረቱ
አንዱም ላይተርፍ ከጥፋቱ
አቤት ቁጣ...
ለምን ሰማይ ጎረፈ
ሙላቱ እስተላይ ሰፈፈ?
ክህደቱ:-
የጠፈሩን ቧንቧ ከፈተው
የእልቂቱን ዝናም አዘነመው
ሀጥያቱ:-
የምድርን ምድጃ ለኮሰው
የረጋውን ውሃውን አጋለው
ለምን ሰማይ ጎረፈ
ሙላቱ እስተላይ ሰፈፈ?
ክህደቱ:-
የጠፈሩን ቧንቧ ከፈተው
የእልቂቱን ዝናም አዘነመው
ሀጥያቱ:-
የምድርን ምድጃ ለኮሰው
የረጋውን ውሃውን አጋለው
እንግዲህ...
ክህደት ከሀጥያት ከተራመደ
ጎርፍ ከንፍር ተዛመደ ::
ክህደት ከሀጥያት ከተራመደ
ጎርፍ ከንፍር ተዛመደ ::
አይኔ እያየ...
ፍጥረት በውሃ ሲወሰድ
በሞቀባት መሬት ሲነድ
ፍጥረት በውሃ ሲወሰድ
በሞቀባት መሬት ሲነድ
እኔ ግን...
የማትሰጥመውን ተመለከትኩ
የማትበገረውን ተከተልኩ
ጎፈር እንጨት በዙሪያዋ
አልቦ ሽንቁር መለያዋ
በጉርጆች የተሰራች
የማትሰጥመውን ተመለከትኩ
የማትበገረውን ተከተልኩ
ጎፈር እንጨት በዙሪያዋ
አልቦ ሽንቁር መለያዋ
በጉርጆች የተሰራች
በለምለሞች የተዋበች
ውብ መርከብ መዳኛ
ስርግው ልሂቅ ተአምረኛ
ጣራ ክዳኗን ዶፍ አልበሳው
ግድግዳዋን ግለት አልበገረው
ነፋስ አውሎው አልቀየሳት
ሞገድ ማዕበል አልሰበራት
ስርግው ልሂቅ ተአምረኛ
ጣራ ክዳኗን ዶፍ አልበሳው
ግድግዳዋን ግለት አልበገረው
ነፋስ አውሎው አልቀየሳት
ሞገድ ማዕበል አልሰበራት
ቀደሰ ማህደሮ ልዑል
እግዚአብሔር ውስተ ማዕከላ ኢትተሀወክ
እግዚአብሔር ውስተ ማዕከላ ኢትተሀወክ
ተገረምኩ...
እኔስ:-
አይኔን አላሸሁ
ኋላዬን አላየሁ
ስራዬማ...
አካሌ ዋና አይችልም
ሰውነቴ ንፍር አያልፍም
እኔስ:-
አይኔን አላሸሁ
ኋላዬን አላየሁ
ስራዬማ...
አካሌ ዋና አይችልም
ሰውነቴ ንፍር አያልፍም
ተፈሳህኩ ርኢክዋ
ለሐመር የዋህ
ለሐመር የዋህ
ገባሁ...
በታላቋ መርከብ ተከለልኩ
ከስጥመት ከንፍረት ተሰወርኩ
በታላቋ መርከብ ተከለልኩ
ከስጥመት ከንፍረት ተሰወርኩ
ገረምክኒ...
በጣራዋ ታቅፌ
በአጥሯ ተደግፌ
በጣራዋ ታቅፌ
በአጥሯ ተደግፌ
ወገኔ...
ከውስጥ ሲገቡባት
በክዳኗ ሲጠለሏት
ለካ...
ሐሴት
ድህነት
እናት ናት::
ከውስጥ ሲገቡባት
በክዳኗ ሲጠለሏት
ለካ...
ሐሴት
ድህነት
እናት ናት::
ተደሰትኩ...
ሳይ:-
ከውስጥ ወደ ደጅ
ፍጥረት ሲሰጥም ሲፈጅ
ሳይ:-
ከውስጥ ወደ ደጅ
ፍጥረት ሲሰጥም ሲፈጅ
ምስኪን...
'ዋና እችላለሁ' ያለ
...................ሲሰጥም አየሁት
'ንፍር አይበግረኝ' ያለ
...................ሲቀቀል አየሁት
'ዋና እችላለሁ' ያለ
...................ሲሰጥም አየሁት
'ንፍር አይበግረኝ' ያለ
...................ሲቀቀል አየሁት
መርከቢቷ ተንሳፈፈች ቀዘፈች
ውስጧ አይሞላ ለሁሉ ነች::
ውስጧ አይሞላ ለሁሉ ነች::
እኔስ...
በመርከቤ አለሁ
ከጥፋቱ እድናለሁ::
በመርከቤ አለሁ
ከጥፋቱ እድናለሁ::
..........=//=.........
/'ሐመር' ድንግል ሆይ እጽፍልሽ ዘንድ እኔ ማነኝ?/
/'ሐመር' ድንግል ሆይ እጽፍልሽ ዘንድ እኔ ማነኝ?/
(ሰኔ21/2004ዓ.ም.)
Sunday, 24 June 2012
"እባካችሁ ተፋቱልን" በዲ/ን ብርሃኑ አድማስ ከፌስ ቡክ ገጽ ላይ የተወሰደ
ይህ ጽሑፍ በአዲስ ጉዳይ መጽሔት ሃይማኖት ዐምድ ‹‹ ፖለቲካና ሃይማኖት›› በሚለዉ ርእሰ ጉዳይ ከተስተናገደ በኋላ በመጽሔቱ የቦታ ዉስንነት ምክንያት የቀነስኳቸዉን ሁለት አንቀጾች በማካተት የቀረበ ነዉ፤ መልካም ንባብ፡፡
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በዐቢይ ጾም የሚዉሉት እሑዶች እያንዳንዳቸዉ አንድ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ተአምርን የሚያስታዉስ ስም አላቸዉ፡፡ ለምናገረዉ ታሪክ መነሻ የሆነዉ አራተኛዉ እሑድም መጻጉዕ ይባላል፡፡ በዚህም ጌታችን በምድር ላይ በሽተኞችን የፈወሰበት ተአምራት፣ 38 ዓመት ያህል አንድ አልጋ ላይ ተኝቶ መዳኑን ሲጠባበቅ ከኖረ በኋላ በጌታ በተፈወሰዉና በተለምዶ ‹‹ መጻጉዕ›› (በሽተኛዉ ማለት ነዉ እንጂ የመጠሪያ ስም አልነበረም) እየተባለ በሚጠራዉ ሰዉ ታሪክ መነሻነት ይታሰባል፡፡ በወንጌል እንደተጻፈዉ ጌታ ወደ በሽተኛዉ ከደረሰ በኋላ አስቀድሞ ልትድን ትወዳለህን ሲል ጠየቀዉ፡፡ መልሱን ከሰማ በኋላም ‹‹ ተነሣ አልጋህን ተሸክመህ ሒድ›› ሲል አዘዘዉና ያ በሽተኛ ወዲያዉ ተነሥቶ ድኖ አልጋዉን ተሸክሞ ሔደ፡፡ ታዲያ በዐብዮቱ ዋዜማ አካባቢ በነበረዉ የመጻጉዕ እሑድ እንዲህ ሆነ ይባላል /ዮሐ 5፤1-10/ ፡፡ በዕለቱ ንጉሡም በተገኙበት ቅዳሴዉ ከተቀደሰ በኋላ በተነበበዉ ወንጌል ላይ የሚያስተምሩት እስካሁን የሊቅነትና የእዉነተኛ ኦርቶዶክሳዊ ስብከት መለኪያ ተደርገዉ ከሚጠቀሱት እጂግ በጣም ጥቂት የሀገራችን ሊቃዉንት አንዱ የነበሩት መልአከ ሰላም ሳሙኤል ተረፈ ‹‹ተንሥእ ወንሣእ ዐራተከ ወሑር፤ ተነሥ አልጋህን ተሸክመህ ሒድ›› በሚለዉ ኃይለ ቃል መነሻነት ትምህርቱን ይሰጣሉ፡፡ በጊዜዉ ነበርን፤ የተደረገዉን አይተናል ሰምተናል የሚሉ ሰዎች እንደ ነገሩኝ ንጉሡ በዚህ ትምህርት በጣም ተበሳጭተዉ ነበር፡፡ ምክንያቱም ‹‹ አልጋህን ተሸክመህ ተነሥና ሂድ›› የሚለኝ እኔን ነዉ ብለዉ በጊዜዉ ከነበረዉ የሶሻሊስት ርእዮተ ዓለም አራማጅ የተማሪዎች እንቅስቃሴዎች ጋር አገናኝተዉ ስለተመለከቱት የተሰበከዉ በሙሉ ወንጌል ሳይሆን አዲሱ ፖለቲካ መስሏቸዉ ነበር ይባላል፡፡ መልአከ ሰላም ሳሙኤልም ብዙ ሳይቆዩ ስለሞቱ ለአንዳንድ ሰዎች ትምህርቱን ለሞታቸዉ ምክንያት አድርገዉ እንዲናገሩ ምክንያት ሆኗቸዋል፡፡
በርግጥ እንዲህ ዓይነት ነገር የተጀመረዉ በዐጼ ኃይለ ሥላሴ ዘመን አይደለም፡፡ ጌታችን ራሱ በሔሮድስም የተሳደደዉ በዚሁ ምክንያትም ብዙ ሕጻናት ያለቁት የርሱን መንግሥት የሚቀማዉ ስለመሰለዉ ነበር፡፡ ከዚያም በኋላ አይሁድ ጌታን የከሰሱት ነገሩን ከፖለቲካ ጋር አያይዘዉ ነበር፡፡ለመንግሥት ግብር አትክፈሉ ይላል፣ በመንግሥት ላይ ዐመጽ ያነሳሳል፣….. ምን ያልተባለ ነገር አለ፡፡ከዚያ ጊዜ ጀምሮ በሁለት ሺሕ ዐመታት የክርስትና ጉዞአችን ዉስጥ እዉነተኛዎቹ የሃይማኖት አባቶች ድርጊታቸዉ ሁሉ መንግሥትን መቃወም ተደርጎ ስለሚቆጠር አንዳንድ ጉድለት ያለባቸዉ ሆድ አምላኮች ከመንግሥታት ጋር ተለጥፈዉ በሚሠሩት ብዙ ተንኮል ብዙ ደም ፈስሷል፤ ብዙ ግፍም ተፈጽሟል፡፡ የሚያሳዝነዉ ከሁለት ሺሕ ዐመታትም በኋላ መንገዱ ሳይለወጥ ይሔዉ እንገፋፋበታለን፡፡ ችግሩ ግን የፖለቲካና የሃይማኖት ግጭቶች ሳይሆን የሃይማኖተኞችና የፖለቲከኞች ሕገወጥ ጋብቻ የሚፈጥረዉ ችግር ነዉ፡፡
ፖለቲካ በየትኛዉም ርእዮተ ዓለም ይሁን ሕዝብን የማስተዳደርና ሀገርንና የሀገርን ጥቅም የማስጠበቂያ መንገድ ነዉ፡፡ የርእዮተ ዐለም ልዩነትና ብዛት ሀገርንና ሕዝብን የተሻለ ተጠቃሚ ለማድረግ የሚካሔድ የአስተሳሰብ ልዩነት፣ የፍልስፍና ልዩነት ሁሉ ለኔ እንደ ትራንስፖርት ልዩነት ነዉ፡፡ ሁሉም የራሱ ጠንካራ ጎንም ደካማ ጎንም አለዉ፡፡ አንድ ዐይነት አንኳ ብቻ ቢሆንም እንደ ሾፌሮቹ፣ እንደ አብራሪዎቹ ወይም እንደ ነጂዎቹ አቅም፣ እዉቀት፣ ክህሎት እና ሥነ ምግባርም ጭምር ይለያያል፡፡ እነዚህ ሁሉ በሰዉ ለሰዉ የተሰሩ በሰዉ የሚመሩ፣ የሚነዱ ናቸዉ፡፡ በራሳቸዉ ፈቃድና ስሜት መሔድ የሚችሉ አይደሉም፡፡ ፖለቲካም አስተሳሰብ፣ አመለካከት ወይም ፍልስፍና ስለሆነ ማደሪያዉም የሰዉ ጭንቅላት ነውና በግዘፍ አንየዉ አንጂ ልክ እንደ አዉሮፕላኑ፣ ባቡሩ፣ መርከቡ መኪናዉ ሁሉ በሰዉ ለሰዉ የተፈጠረ በሰዉም የሚመራ የተለያየም ሆነ ተመሳሳይ እንደየመሪዎቹ ሁኔታዉ የሚለዋወጥ፣ የሚፈጠር፣ የሚያድግ፣ የሚሻሻል፣ የሚጠፋ የሚሞት፣ የሚጠቅም፣ የሚጎዳ ሐሳበ ሰብእ ብቻ እንደሆነ ይገባኛል፡፡ ስለዚህ የሚፈጥሩት ሰዎችም አንዳንዶቹ ከሃይማኖት፣ አንዳንዶቹ ከአለማመን፣ አንዳንዶቹ ከፍልስፍና፣ አንዳንዶቹም ከምጣኔ ሀብታዊና ከመሳሰሉት ተነሥተዉ መሆኑ የታወቀ ነዉ፡፡ ስለዚህ ፖለቲካ ‹‹ፖለቲካ›› በተባለ ኮረጆ የተጠረቀ ወይም በዚህ ስም የምንጠራዉ ርእዮተ ዓለሙ ምንም ይሁን ምን ዓላማዉ ሰዎችን በተስማሙበትም ይሁን በተለያዩበት በምድር ላይ ማስተዳደር የሆነ ሥርዓተ መንግሥት ነዉ፡፡ ፖለቲከኛም ሥራዉ በአመነበትና በተቀበለዉ ርእዮተ ዓለም መንግሥት መሥርቶ ሰዎችን በምድር ላይ ተመችቷቸዉ እንዲኖሩ የሚቻለዉን ሁሉ ማድረግ ነዉ፤ ቢሳካለትም ባይሳካለትም፡፡
ሃይማኖት ደግሞ ሰዉ በተረዳዉና በአመነዉ መንገድ ከሞት በኋላ ያለዉን ሕይወት እያሰበ በምድራዊ ሕይወቱ የሚተገብረዉና ከአምላኩ የሚኖረዉ መንፈሳዊ ግንኙነት (እምነትና አምልኮ) ነዉ፡፡ የክርስትና ሃይማኖት ደግሞ የመገለጥ ሃይማኖት ነዉ፡፡ ምክንያቱም እግዚአብሔር አንደኛ በጊዜ ቦታ የማይወሰን (beyond space-time) ዳግመኛም በሁሉም ቦታ ያለ (Omnipresent) ረቂቅ መንፈስ ስለሆነ ሰዉ ሊያየዉ አይችልም፡፡ለዓለም መፈጠርም ብቸኛዉ አድራጊ (ultimate cause) እርሱ ስለሆነ ሊደረስበት የሚችል(discoverable) አይደለም፡፡ ስለዚህ ልናዉቀዉ የምንችለዉ እርሱ ራሱ ስለራሱ የነገረንን ያህል ብቻ ነዉ፡፡ መጽሐፍ ቅዱስም እግዚአብሔር በተገለጠላቸዉ ነቢያትና በሥጋ በተገለጠ ጊዜ በአስተማራቸዉና በሾማቸዉ ደቀ መዛሙርቱ በመንፈስ ቅዱስ ምሪት በሰዉ ቋንቋ የተጻፈ መለኮታዊ ሐሳብ፣ ትምህርት፣ ምክር፣ ምሥጢረ ሃይማኖት ነዉ፡፡ ዓላማዉም ሰዎችን ከሞት በኋላ ስላለዉ ዘላለማዊ ሕይወት በዚህ ምድር እያሉ እግዚአብሔር በገለጠዉ መንገድ ብቻ ማዘጋጀት ነዉ፡፡ በርግጥ በምድራዊ ሕይወታችንም ከሌሎች ሰዎች ጋር ስለሚኖረን ግንኙነትም ይነግረናል፡፡ ምክንያቱም ይሕ ግንኙነታችንና አኗኗራችን ለሰማያዊ ሕይወታችንም መሠረት ስለሆነ፡፡ ስለዚህ የሃይማኖት መሪ የሆነ አንድ ክህነት ያለዉ ሰዉም ዓላማ በሃይማኖቱ ሕግና ሥርዓት መሠረት ሰዎችን ለመንግሥተ እግዚአብሔር ማዘጋጀት ብቻ ነዉ፡፡
በአጭሩ ሃይማኖት ሐሳበ እግዚአብሔር ፖለቲካ ደግሞ ሐሳበ ሰብእ፤ የሃይማኖት ዓላማዉ ሰዎችን ለመንግሥተ ሰማይ ማዘጋጀት የፖለቲካ ደግሞ ሰዎችን በምድራዊ ሕይወታቸዉ እንዲመቻቸዉ ማድረግ ሲሆን የሃይማኖት አባት ስለ እግዚአብሔር መንግሥት በምድር የሚሠራ የእግዚአብሔር ወኪል ሲሆን አንድ ፖለቲከኛ ደግሞ ስለቆመለት ምድራዊ መንግሥት እየሰበከ ሕዝብን ለማስተዳደር የሚሠራ የመንግሥት ወኪል ነዉ፡፡ ስለዚህ ሃይማትና ፖለቲካ ሳይጣሉና ሳይጋጩ ነገር ግን ሳይገናኙና ሳይዋሐዱም እንደ ትይዩ መስመሮች (parallel lines) የራሳቸዉን መም ጠብቀዉ ሊኖሩ የሚችሉ ነገሮች ናቸዉ፡፡ ይህ ማለት ግን ፖለቲከኞች ክርስቲያን አይሆኑም ሃይማኖተኞችም ስለሚያስተዳድራቸዉ መንግሥት ስሜትና ምላሽ አይኖራቸዉም ማለት አይደለም፡፡
አሁን እነዚህን ሁለቱን የሚያገናኟቸዉ ሰዎች ናቸዉ፡፡ ሊያስማሟቸዉም ሊያጣሏቸዉም የሚችሉት እነርሱ ናቸዉ፡፡ ምክንያቱም ሁለቱም የሚያድሩትም የሚኖሩትም በሰዎች ኅሊና ዉስጥ ነዉ፡፡ ስለዚህ ሃይማኖትንም ሆነ ፖለቲካን በኅሊናቸዉ ያሳደሩት ሰዎች የተረዱና ሌላ ርካሽ ጥቅምን የማይፈልጉ እውነተኞች ከሆኑ ሁለቱም ሰዉን በምድር ሊጠብቁትና በሰላም ሊመሩት ለሰማዩም እንዳመነበት ሃይማቱን ይዞ ሊያኖሩት ይችላሉ፤ ይገባቸዋልም፡፡ ፖለቲከኞች ርቱዕ ሃይማኖተኞች በሚሆኑበት ጊዜ ዉክልናቸዉ እግዚአብሔራዊ ጠባይን ስለሚይዝ ፍትሕ ርትዕ አያጓድሉም፡፡ ምክንያቱም የሚያምኑት እግዚአብሔር ለሚያምንበትም ለማያምንበትም፤ ለኃጥኡም ለጻድቁም ፀሐይን እንደሚያወጣዉ፣ ዝናምን እንደሚያዘንመዉ፣ መግቦቱንም እንደማያጓድለዉ ልክ እንዲሁ ፈሪሃ እግዚአብሔር ያለዉ መሪም በመንግሠታዊ አስተዳደሩ ዉስጥ ላሉት የሌሎች ሃይማኖት ተከታዮች ብቻ ሳይሆን የእርሱን የፖለቲካ ርእዮተ ዓለም ለማይከተሉም ጭምር ያለ አድሎ እንደ እግዚአብሔር ያስተዳድራል፡፡ ሌላዉ ቀርቶ መሪዉ አድልቶ ሌሎቹን በሃይማኖታቸዉ ምክንያት ቢበድል ይህ ለመሪዉ ለራሱ ኃጢኣት ይሆንበታል እንጂ በእግዚአብሔር የሚያስመሰግነዉ የሃይማኖት ሥራ ሊሆን አይችልም፡፡ ይህ እንግዲህ ሃይማኖት ለፖለቲካዉ ሊያደርገዉ የሚችለዉ ትንሹ አስተዋጽኦ ነበር፡፡ ስለዚህ አንድ ሃይማኖተኛ ፖለቲካን የሚርቀዉና የሚፈራዉ ሊሆን አይችልም ነበር፡፡ የሚያስኮንነዉም ፖለቲከኛ መሆኑ ሳይን ፖለቲከኛ ሆኖም ሆነ ሳይሆን የሚሠራዉ ሥራ ነዉ፡፡ ሥራዉ ንጹሕና ትክክል እስከሆነ ድረስ ግን እንዲያዉም ፖለቲከኛ ሆኖ ሀገሩን ማገልገሉ የበለጠ ጽድቅ ይሆንለታል እንጂ የሚያስወቅሰዉ ሊሆን አይችልም፡፡ ነገር ግን ብዙ ጊዜ ፖለቲከኞች እንዲህ ዓይነቱን ርቱዕነት ስለሚፈሩት ሃይማኖትን በምልዓት ሊሰሙት ይፈራሉ፡፡
ልክ እንዲሁ የፖለቲካን አስፈላጊነት በአግባቡ የተረዱ የሃይማኖት መሪዎች መኖራቸዉ ጠቀሜታዉ እጂግ ብዙ ነዉ፡፡ አንድ የፖለቲካ ፓርቲ ዉስጥ የተለያየ ሃይማኖት ተከታዮች በርዕዮተ ዓለም አንድነት እንደሚገናኙ ሁሉ ልክ እንዲሁ ደግሞ የተለያየ የፖለቲካ ርእዮተ ዓለም ያላቸው ሰዎች በሃይማኖት አንድነት ምክንያት አንድ የሃይማኖት ተቋም ውስጥ ሊገናኙ ይችላሉ፡፡ ምክንያቱም ቤተ ከርስቲያኒቱ የሁሉም እናት ናት፡፡ መልካም እናት ገበሬውንም፣ ነጋዴዉንም፣ የተማረዉንም ያልተማረውንም ልጇን አኩል እንደምትወድና በኑሮ ምርጫ፣ በሥራ፣ ፣ … ቢለያዩ በእናትነት አንድ አድርጋ አገናኝታ ቢጣሉም ዳኝታ እንደምታኖራቸዉ ቤተ ክርስቲያንም ለፖለቲከኞች እንዲሁ ናት፡፡ ስለዚህ ቤተ ክርስቲያን ሲመጡና ሲገቡ (በእኛ) ጫማቸዉን አውልቀዉ እንዲገቡ እንደምታደርገው ሁሉ እንደዚሁ ፖለቲካዊ አሳባቸዉን ትተዉ( በዚያ ለመቀስቀስና የራሳቸዉ ደጋፊ ለማድረግ እንዳይሠሩ እየተቆጣጠረች) በእርሷ እንዲስተናገዱ ማድረግ ይጠበቅባታል፡፡ በሃይማኖት ሥርዓቷ ጠበቅ አድርጋ የምትጠብቃቸዉ ከሆነማ ዐመጻና ክፋትን ስለሚያርቁ መሠረታቸዉም ማገልገል እንጂ የራስን ጥቅም ማካበት ስለማይሆን በተለያየ የፖለቲካ ፓርቲ ውስጥ እንኳ ቢሆኑ በሰላምና በፍቅር እንዲኖሩ ታስችላቸዋለች፡፡ ይህ መሆን ቢችል ቤተ ክርስቲያን የፖለቲካ ሥራ ሳትሠራ ፖለቲከኞችን በማስተካከል ሀገርንም ሕዝብንም ጠቀመች ማለት ነዉ፡፡ እንደዚህ ዓይነት መመጋገብና መጠባበቅ የሚገኝበት ቢሆን ኖሮ ቀጣፊዎች፣ ለመጣዉ ሁሉ አራጋቢ የሆኑና ያልተፈጠረዉን ፈጥረዉ ተናግረዉና አጣልተዉ ጠቃሚ መስለዉ የሚኖሩ አጭበርባሪዎች ቦታ አይኖራቸዉም ነበር፡፡ ፖለቲካም እንደ ጭራቅ የሚፈራ፣ እንደ ኃጢአትም ያስኮንናል የማይባል፣ የሌቦች፣ የተንኮለኞች፣ የክፉዎችና የጨካኞች ተደርጎ አይታሰብም ነበር፡፡ ሃይማኖትንም ጥላና ጥግ አድርገዉ ለመጠቀም የሚያስቡ የሃይማኖት ለምድ የለበሱ ፖለቲከኞች አይቀልዱበትም ነበር፡፡
ችግር እየሆነና ግጭቱን የሃይማኖትና የፖለቲካ ያስመሰለው ግን ይህ አይመስለኝም፡፡ ቀደም ብየ በመግቢያየ እንደገለጽኩት የሃይማኖት አባቶችን ያህል ተሰሚነት የሌላቸዉ የፖለቲካ ሰዎች ሕዝቡን የሚያጡትና ሌሎች የሚጠቀሙበት ሲመስላቸዉ ፍርሃታቸዉ ያይላል፡፡ በርግጥ የፍርሃታቸዉ ምንጭ ይዘዉት በሚመሩበት የፖለቲካ ርእዮተ ዓለም ወይም በመሪዎቹ ላይ የሕዝባቸዉ አመኔታ ማጣት፣ ወይም ከሥልጣን ጥም የተነሣ ረጂም ዘመን እንኖርባቸዋለን ብለዉ የመረጧቸዉ መንገዶች አዛላቂነት አለመኖር ሊሆን ይችላል፡፡ በዚህ ጊዜ በሆነ ዘዴ ይህን ኃይል ለመጠቀም ያስባሉ፡፡
ብዙ ጊዜ ሃይማኖቱን ጠብቆ ከሚኖረዉ አብዛኛዉ እነርሱን የሚቃወም ይመስላቸዋል፤ በዚህ ጊዜ በሃይማኖት መሪዎች በኩል ሕዝቡን ለመያዝ ይሞክራሉ፡፡ ልክ እንደዚሁ ደግሞ ሃይማኖትን ሰውን ለመንግሥተ እግዚአብሔር ማዘጋጃ መሆኑን ረስተው ከሃይማኖት ተቋማት የግል ጥቅማቸዉን ሊያጋብሱ የሚሯሯጡ ቀሳጥያን አይጠፉም፡፡ እነዚህኞቹም የሚመሩት የሃይማኖት ተከታይ ሲነቃባቸው ደግሞ የመንግሥትን ድጋፍ በማግኘት ያለ ሃሳብ የሚፈልጉትን እያደረጉ ለመኖር ያስባሉ፡፡ በዚህ ጊዜ ሁለቱም ይሳሳቡና በሕጋዊና ርቱዓዊ መንገድ ከመረዳዳት ይልቅ ሁለቱም የቆሙለትን ዓላማ ትተዉ ጥቅምን፣ የሥልጣን መባለግንና የመሳሰሉትን ከወሸሙ በኋላ እንደገና ሁለቱ ሕገ ወጥ ጋብቻ ይፈጽማሉ፡፡ ስለዚህ ፖለቲካና ሃይማኖት ሳይጋቡ ፖለቲከኛዉና ሃይማኖተኛዉ በሚፈጽሙት የተሳከረ የአስተሳሰብ ወሲብ ሕዝባቸዉን ሲያሳዝኑ የቆሙለትንም ዓላማ ሲያዋርዱ ይኖራሉ፡፡ ለአቅመ ሃይማኖት ያልደረሱ ፖለቲከኞችና ለአቅመ ፖለቲካም ያልደረሱ ሃይመኖተኞች የሚፈጽሙት የጋብቻ ዉል በቤተሰብ ሕጉ በወንጀልነት ያልተካተተ ቢሆንም በተፈጥሮና በፈጣሪ ሕግ የሚያስቀጣ ሕገ ወጥ ብቻ ሳይሆን ያላቻ ጋብቻም ነዉ፡፡ ይህ ጋብቻ ደግሞ ልጅ የሚያስገኝ ሳይሆን ለብዙዎቹ ሕይወት መጥፋት ምክንያት የሆነ የሞተ ጋብቻም ነዉ፡፡እነዚህ ያላቻና ሕገ ወጥ ጋብቻዎች ቢቆሙ ሃይማኖትና ፖለቲካ በመሠረተ ሐሳብ እንደ ትይዩ መስመር የሚጓዙ በሕዝቡ ሕይዎት ደግሞ አንዱ ያጎደለዉን ሌላዉ የሚሞላበት (complimentary) ይሆኑ ነበር፡፡ በአምዱ ውሱንነት ምክንያት ያልዘረዘርኳውን ጠቀሜታዎችም ሊያስገኙ ይችሉ ነበር፡፡ ነገር ግን በድብቅ እንደሚካሄድ የዚህ ዓለም ወሲብ ባለተገባ ግንኙነት ሰክረዉ ይቀራሉ፡፡ ፍች የተከለከለዉና የማይጠቅመዉም ለባልና ሚስት ነዉና እባካችሁ በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ ሆናችሁ ከመንግሥታዊም ሆነ ከከተቀናቃኝ ፓርቲዎች ጋር ሕገወጥና ያላቻ ጋብቻ የፈጸማችሁ የሃይማኖት አገልጋዮች በተለይ መሪዎቹ ተፋቱልን፡፡ ሰዉን ሥጋዉንና ደሙን አቁርባችሁ አንድ ለአንድ አጋቡ ተባላችሁ እንጂ እናንተዉ በጥቅምና በሥልጣን ብልግና ቆርባችሁ ከፖለቲከኞች ጋር ተጋቡ አልተባላችሁም፡፡ በዚህ መፋታት ይቻላልና እባካችሁ ተፋቱልን፡፡ እናንተ ስትፋቱ እኛም በሕይወት እንኖራለን፡፡
Saturday, 23 June 2012
‹‹አእምሮሽ የተመሰገነ ይሁን!›› ዲያቆን ኅብረት የሺጥላ ከፌስቡ ገጹ ላይ የተወሰደ
ዲያቆን ህብረት የሺጥላ
ዘወትር ከአባታችን ሆይ ቀጥሎ በምናደርሰው ‹‹በሰላመ ገብርኤል›› በተሰኘው የጸሎት ክፍል ውስጥ ‹‹በሐሳብሽ ድንግል ነሽ በሥጋሽም ድንግል ነሽ›› የሚል የምስጋናና የምስክርነት ቃል ይገኛል፡፡ በተመሳሳይ መንገድ በመልክዓ ማርያም ውስጥም ‹‹ሰላም ለሕሊናኪ ሐልዮ ሠናያት ልማዱ ወገቢረ ምሕረት መፍቅዱ›› ማለትም ‹‹ምሕረት ማድረግ ለሚወድ መልካም መልካሙን ማሰብ ልማዱ ለሆነ ሕሊናሽ ሰላም እላለሁ!›› የሚል የምስጋና ቃል አለ፡፡ የተአምረ ማርያም መቅድም ደግሞ የድንግል ማርያምን ሕሊና ከመላእክት ሕሊና ጋር ያስተያይና በልጦ ሲያገኘው በመደነቅ እንዲህ እያለ ያመሰግናል፡፡ ‹‹ሥጋዊ ነገር ከማሰብ መጠበቅ ከአዳም ልጆች ለማን ተሰጠው? ኃጢአትን ከማሰብ መጠበቅ ለመላእክት እንኳን አልተቻላቸውም፡፡ በቀደመው ወራት ያልተሰጣቸውን ሽተው በድለው ከሰማይ ወደ ምድር ወርደዋልና፡፡›› ከዚህም ጋር አያይዞ ‹‹የእመቤታችን ማርያም አሳብ እንደ አምላክ አሳብ ነው፡፡›› ይህም አሳብዋ ንጹሕና መልካም ብቻ መሆኑን ያስረዳናል፡: እኛ ክርስቲያኖች ‹‹እግዚአብሔርን እንድንመስል›› ታዘናል፡፡ (1ጢሞ4.7-8፤ 1ቆሮ11.1) ይህም በመልክ አይደለም፡፡ በሥራና በአመለካከት እንጂ፡፡ እግዚአብሔርን በአመለካከት መምሰል የማይቻል ቢሆን ኖሮ እግዚአብሔርን ምሰሉ አንባልም ነበር፡፡ በመልክ ስለመምሰል የሚናገር ቢሆን ኖሮ ደግሞ መልክን የሚፈጥረው ፈጣሪ ስለሆን ‹‹ምሰሉ›› አንባልም ነበር፡፡ የሚደንቅ ነው! እኛ ፈጣሪን በአሳብና በአመለካከት እንድንመስለው ታዘዝን፡፡ ድንግል ማርያም ግን መስላ ስለተገኘች ‹‹አሳብዋ እንደ አምላክ አሳብ ነው፡፡›› የሚል ምስክርነት ተሰጠላት፡፡ ቀደም ሲል ስለ ድንግል ማርያም ፍጹም የሕሊና ድንግልናና በጎነት ከአዋልድ መጻሕፍት ያስቀደምኩት ሆን ብዬ ነው፡፡ ይህንን ትምህርት መጽሐፍ ቅዱስ እንዴት እንደሚደግፈው ማሳየት ያስፈልጋልና እነሆ! ብዙ ሰዎች ስለ ድንግል ማርያም የሕሊና ንጽሕና ስንናገር በምን አውቃችው ነው? ለማለት ይዳዳቸዋል፡፡ በእርግጥ እኛ እንኳን የድንግል ማርያምን ሕሊና የኃጥአንንም ሕሊና የምናውቅበት ችሎታ የለንም፡፡ የጻድቃን ሕሊና ከኃጥአን ይልቅ እጅግ ይጠልቃል፡፡ የድንግል ማርያም ሕሊና ደግሞ ከሁሉ ይልቅ ጥልቅ ነው፡፡ ‹‹መንፈሳዊ ሰው በማንም አይመረመርም እርሱ ግን ሁሉን ይመረምራል›› ከተባለ ሰው ፍጹም መንፈሳዊት ድንግል ማርያምን ሊመረምር እንዴት ይችላል? (1ቆሮ2.15) ታዲያ ‹‹በሐሳብሽ ድንግል ነሽ›› እያላችሁ ጠዋትና ማታ የምትዘምሩት የእርሷን ሐሳብ በምን አውቃችው? ለሚሉን መልሳችን፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ድንግል ማርያም አሳብ ስለሚናገር ነው እንላቸዋለን፡፡ የት ቦታ ቢሉንም ቅዱስ ሉቃስ ሲጽፍ ‹‹ይህ እንዴት ያለ ሰላምታ ነው ብላ አሰበች›› ይላል፡፡ (ሉቃ1.29) ‹‹አሰበች›› ማለቱን ልብ በሉ፡፡ ይህን አለች ቢል ሰምቶ ነው፤ ይህን ሠራች ቢል አይቶ ነው ይባላል፡፡ ‹‹አሰበች›› ሲል ምን እንላለን? የክርስቲያኖች መልስ አንድ ነው፡፡ መንፈስ ቅዱስ ምን እንዳሰበች ገልጾለት ነው እንላለን፡፡ ሰይጣንና መናፍቃን የሚሉት አያጡምና ምናልባት ገምቶ ነው ሊሉ ይችላሉ፡፡ መቼም በዚህ አይሳቅም!!! መጸለይ ነው እንጂ፡፡ ይህ ብቻ አይደለም! በየርእሰ ጉዳዩ የድንግል ማርያም አሳብ ምን እንደሚመስል መንፈስ ቅዱስ ሲገልጥ ኖሮአል፡፡ ከዚህ የተነሣ ወንጌላዊው ሉቃስ አንድ ጊዜ ብቻ ሳይሆን ደጋግሞ ‹‹ይህን ሁሉ ነገር በልቧ እያሰበች ትጠብቀው ነበር፡፡›› ሲል መስክሯል፡፡ (ሉቃ2.19፤ ሉቃ2.51) መንፈስ ቅዱስ በልቧ ያለውን ካልገለጠለት ‹‹በልቧ እያሰበች ትጠብቀው ነበር›› እያለ ሊናገር እንዴት ደፈረ? በሰው ልብ ያለውን ከመንፈስ ቅዱስና ከሰውዬው በቀር ማንም ሊያውቅ እንደማይችል ቅዱስ ጳውሎስ ጽፎ የለምን? (1ቆሮ2.11) ድንግል ማርያም በሕሊናዋ የዚህ ዓለም ምኞት አልነበራትም፡፡ እንኳን ኃጢአቱና ኃጢአት ያልሆነውም ሥጋዊ አኗኗር በልቧ አልነበረም፡፡ ይህም ማለት ‹‹አግብቼ ወልጄ መልካም እየሠራሁ ቤተሰቦቼን እየረዳሁ እኖራለሁ›› የሚለው አሳብና ምኞት በውስጧ አልነበረም፡፡ ይህም ፈጣራ ሳይሆን በቅዱስ ዳዊት የትንቢት ቃል ይታወቃል፡፡ ስለ እርሷ ‹‹ልጄ ሆይ ስሚ ጆሮሽን አዘንብዪ የእናትሽንና የአባትሽን ቤት እርሺ›› ብሏል፡፡ ምእመናን! አባቷ ዳዊት እረ ስሚኝ፣ ጆሮ ስጪኝ እያለ ለምኖ ሲያመሰግናት ስሙ!! ‹‹እርሺ›› ማለት ምን ማለት ነው? አታስቢ ማለት አይደለምን? የምትረሳውስ ምንድር ነው? የእናት የአባቷን ቤት ነው፡፡ ይህ ማለት የእናት የአባትሽን ቤት አትመኚ! እንደ እነርሱ አግብቼ፣ ወልጄ እኖራለሁ ብለሽ አታስቢ ማለት ነው፡፡ ልብ በሉ! ቅዱስ ዳዊት ነቢይ ነው፡፡ እርሷ ይህን ዓለም እንድትረሳ የመከራት እንዳይመስላችሁ፡፡ እንደምትረሳው አውቆ በፈሊጥ ትንቢት ተናገረ እንጂ፡፡ አነጋገሩ እኮ ‹‹አቤቱ ተነሥ›› እንደሚለው ዓይነት ትንቢት ነው፡፡ ቅዱስ ዳዊት ይህን ቃል ብዙ ጊዜ ደጋግሞ ስለኢየሱስ ክርስቶስ ትንሣኤ ተናግሮታል፡፡ (መዝ131.8) ኢየሱስ ክርስቶስ ዳዊት ‹‹ተነሥ›› ስላለው የተነሣ ይመስላችኋል? እንደሚነሣ አውቆ ትንቢት መናገሩ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ እንዲሁ ‹‹እርሺ›› ቢልም እንደምትረሳው አውቆ ትንቢት ተናገረ እንጂ ያስረሳት ዳዊት አይደለም፡፡ ታዲያ እንዲህ ኃጢአትን ሁሉ የዘነጋ ሕሊና ለማን ተሰጠው? እንዲህ ያለ ንጽሕናንና ቅድስናን የማያመሰግን አንደበት እንደምን ያለ ነው? እንዴት ያለ በደል ነው? እንዴትስ ያለ ድፍረት ነው? በበደል የረከስን ስንሆን ኃጢአትም ነግሣብን ሳለ ራስን ከፍ ለማድረግ ላላፈርን ለኛ ወዮታ ይገባል! እንኳን ከኀልዮ ኃጢአት ከተግባሩም ላልሸሸን ለኛ ኀዘን ይገባል፡፡ ‹‹እርሷ እንደኛው ናት!›› የሚሉ አርሲሳን /መናፍቃን/ ቦታቸው የት ይሆን? ሰው ባለማወቁ መጥፋቱን አያውቅም፡፡ መሬታዊው ሰው ደረጃውን አላዋቀምና ለዚህ ስንፍናው ከእግዚአብሔር ዘንድ ምላሹ ምን ይሆን? ወደ ቀደመ ነገራችን እንመለስ! ድንግል ማርያም መልአኩን ‹‹ወንድ ስለማላውቅ ይህ እንዴት ይሆናል›› አለችው፡፡ መልአኩ ‹‹እነሆ ትጸንሻለሽ›› ባላት ጊዜ ታዲያ ምን ብርቅ አለው? ‹‹ሴት ልጅ ጊዜዋ ሲደርስ ታገባለች፤ ትጸንሳለች›› ልትለው ትችል ነበር፡፡ እርሷ ግን ‹‹ይህ እንዴት ይሆናል?›› አለችው፡፡ ይህም ጥያቄዋ የልቧን መታተም ያስረዳል፡፡ አንዲት ሴት ባል ባይታጭላትና ባታገባ እንኳን ትወልጃለሽ ስትባል ‹‹ይሆን ይሆናል›› ትላለች፡፡ ወንድ ግን በተፈጥሮው የሚወልደው እርሱ ስላልሆነ ትወልዳለህ ቢሉት ‹‹እንዴት ይሆናል?›› ይላል፡፡ የድንግል ማርያም ንግግር የሁለተኛውን ይመስላል፡፡ የወንድ መውለድ የማይጠበቅ ነገር እንደሆነ በእርሷ ዘንድ መውለድ የማታስበው ጉዳይ ነውና ‹‹እንዴት ይሆናል›› አለች፡፡ እንደዚሁም መልአኩን ‹‹ወንድ ስለማላውቅ›› ብላዋለች፡፡ ይህም ለወደፊት እንኳን ወንድ ላለማወቅ ሕሊናዋን የዘጋች መሆኗን ያስረዳል፡፡ አለማወቋም ጾታ የመለየትና ያለመለየት ጉዳይ አይደለም በግብር ነው እንጂ፡፡ ለዮሴፍ የታጨችው ለተቃርቦ ቢሆን ኖሮ ወንድ ስለማላውቅ ባለችው ጊዜ መልአኩም መልሶ ምነው ዮሴፍ አለ አይደል ሊላት በቻለ ነበር፡፡ ነገር ግን መልአኩ እንደዘመናችን መናፍቃን አያስብምና የልቧን ንጽሕና አይቶ በግብረ መንፈስ ቅዱስ አምላክን እንደምትወልድ ነገራት፡፡ ለማሳመንም ‹‹ለእግዚአብሔር የሚሳነው ነገር የለም›› አላት እርሷም ነገሩን በጥንቃቄ መርምራ ስታበቃ ‹‹ይደረግልኝ›› ብላ በትሕትና ቃሉን ተቀበለችው፡፡ ያን ጊዜ አካላዊ ቃል ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍስዋ ነፍስ ነሥቶ የዕለት ጽንስ ሆኖ በማኅፀኗ አደረ፡፡ የሕሊናዋ ነገር እንደዚህ ከሆነ ቅዱስ ዳዊት ‹‹አእምሮሽ የተመሰገነ ይሁን!›› በማለት ሰው እንዳይገድል እጁን ከደም የከለከለችውን ሴት አእምሮ ካመሰገነ እኛ ክርስቲያኖች ድንግል ማርያም በቀን ስንት ጊዜ ‹‹በሐሳብሽ ድንግል ነሽ›› እያልን ልናመሰግናት ይገባን ይሆን? (1ሳሙ25.33)
ይቆየን!
Wednesday, 20 June 2012
አቡነ ጳውሎስ በእነ ኀይለ ጊዮርጊስ አስተባባሪነት “ጉባኤ አርድእት” የተሰኘ ቡድን እያደራጁ ነው
አርእስተ ጉዳዮች፡- (READ THIS ARTICLE IN PDF)
- · አቡነ ጳውሎስ በግንቦቱ ቅ/ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ መናጋቱ የተረጋገጠውን የዐምባገነንት ሥልጣናቸውን ያድሱልኛል ያሏቸውን ሦስት ቡድኖችን አቋቁመዋል፤ “ጉባኤ አርድእት” አንዱ ነው።
- · የ”ጉባኤ አርድእት” መተዳደርያ ደንብ ከሰሞኑበአቡነ ጳውሎስ ፊርማ እንደሚጸድቅ እየተነገረ ነው፤ በጽርሐ መንበረ ፓትርያርኩ ቢሮ ተሰጥቶታል፤ ምንጩ ያልታወቀ በጀትም ተመድቦለታል፤ 25 መሥራች አባላት እና 180 ተባባሪ አባላት እንዳሉት ተገልጧል፡፡ ቋሚ ሲኖዶሱ እና ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ሂደቱን በትኩረት እየተከታተሉት ነው።
- · ኀይለ ጊዮርጊስ ጥላሁንን ጨምሮ በአእመረ አሸብር፣ ዳንኤል ሰይፈ ሚካኤል፣ ንቡረ እድ ተስፋይ ተወልደ እና ንቡረ እድ ኤልያስ ኣብርሃ የሚመራ ነው የተባለው “ጉባኤ አርድእት” የአቡነ ጳውሎስን የጠቅላይነት ሥልጣን የሚያጠናክር የሕገ ቤተ ክርስቲያን ‹ማሻሻያ› ረቂቅ አዘጋጅቷል፤
- · “ቤተ ክርስቲያን ራሷ ማኅበር ስለሆነች በተቋም የተደራጀ ሌላ ማኅበር አያስፈልጋትም” በሚል እንደ ማኅበረ ቅዱሳን እና የነገረ መለኰት ምሩቃን ማኅበርያሉትን ማኅበራት ለማዳከምና ለማፍረስ ይሠራል፤ ይህም ካልተሳካ ራሱን ወደ “ማኅበረ አርድእት” ለውጦ በማኅበራቱ ላይ የማያባራ ቀውስ ለመፍጠር ይንቀሳቀሳል፤ “ከማኅበረ ቅዱሳን ያኮረፉ” የሚባሉ ሰዎችን ሰብስቦ ማኅበረ ቅዱሳንን ማጥቃት አንዱ ስልቱ ነው፤
- · በሰላም፣ ልማትና ሰብአዊ ተራድኦ ዙሪያ ከተደራጁ የወጣት ማኅበራት ጋራ እሠራለኹ በሚል አባላትን በአፈሳ ለመመልመልና መንግሥትን በማወናበድ የፖለቲካ ድጋፍ ለመሸመት ይጠቀምበታል፤
- · በቅ/ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ጠንካራ አቋም የያዙ ብፁዓን አባቶችን በፖለቲከኛነት በመወንጀል፣ በአሉባልታዎች ስማቸውን በማጥፋት፣ በየአህጉረ ስብከታቸው ሁከት በመፍጠር የተቀናጀ የማሸማቀቅ ዘመቻ ይከፍታል፤ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት አቡነ ፊልጶስ፣ አቡነ ሕዝቅኤል፣ አቡነ ቄርሎስ፣ አቡነ ናትናኤል፣ አቡነ ቀውስጦስ፣ አቡነ አብርሃም፣ አቡነ ዲዮስቆሮስ እና አቡነ ገብርኤል የወቅቱ ዒላማዎች ናቸው፤
- · አቡነ ጳውሎስ የግንቦቱ ቅ/ሲኖዶስ ጉባኤ ካሳለፋቸው ውሳኔዎች በአራቱ ቃለ ጉባኤአልፈረሙም፤ ቋሚ ሲኖዶስ ፓትርያርኩ አራቱንም ቃለ ጉባኤ ካልፈረሙ በእርሳቸው ርእሰ መንበርነት እንደማይሰበሰብ በመግለጽ አቡነ ጳውሎስን አስጠንቅቋል፤
- · በአቡነ ጳውሎስ ደብዳቤ “በጄነራል ዳይሬክተር ማዕርግ የኢ.ፌ.ዴ.ሪ መንግሥት ዲፕሎማቲክ ፓስፖርት” እንደተሰጠው የሚነገርለት የ”ጉባኤ አርድእት” ቀንደኛ አስተባባሪ ኀይለ ጊዮርጊስ ጥላሁን “ጉባኤ እግዚአብሔር” (Ethiopia Assemblies of God) የተሰኘ የፕሮቴስታንት ቤተ እምነት እንደሚያዘወትር፤ በፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ኑፋቄ አራማጅነቱ ተወግ የተባረረውን የሃይማኖተ አበው አባላት በጎጠኝነት ስሜት እያነሣሣ ወደ ቤተ ክርስቲያን ለመመለስ እየዶለተ መኾኑ ተገልጧል፣
(ደጀ ሰላም፤ ሰኔ 11/2004 ዓ.ም፤ ጁን 18/ 2012):- ክብር - ሥልጣን - ጥቅም፤ የኻያ ዓመት የአቡነ ጳውሎስ ዘመነ ፕትርክና ራሮት ስለ መኾናቸው ብዙዎች ይስማማሉ፤ ራሮቱ የቤተ ክርስቲያናችን የበላይ አካል የኾነውን የቅዱስ ሲኖዶስ አመራርና አሠራር ክፉኛ ከመፈታተኑ የተነሣ “በስም እንጂ በተግባር የሌለ”እስከማሰኘት የደረሰበት ኹኔታ አጋጥሟል፤ የቤተ ክርስቲያናችን ከፍተኛ የአመራርና የአስተዳደር ማእከል የኾነው የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት በዕቅድና ዕቅዱን በሚደግፍ የሰው ኀይልና በጀት ተደግፎ የሚመራ አብነታዊ ተቋም ሳይሆን የአድልዎ አሠራር፣ የአስተዳደር በደልና የሀብት ምዝበራ መለዮው የኾነ ግዙፍ ግን የበሰበሰ መዋቅር ለመሰኘት በቅቷል፡፡ በአጭር አነጋገር የሚከተለው የአንድ አዛውንት ፖለቲከኛ ቃል ከእንግዲህ ውድቀት እና ውርደት እንጂ ሌላ የመኾን ተስፋ የማይታይበትን የአቡነ ጳውሎስ ዘመነ ፕትርክናበማጠቃለል ሊገልጸው ይችላል - “ቤተ ክርስቲያኒቱ በጠና ታማለች ካልን አቡነ ጳውሎስ ገደሏት፤ የለም÷ከዚያም በፊት ሞታ ነበር ካልን አቡነ ጳውሎስ ቀበሯት ለማለት እንችላለን፡፡”
ክርስቶስ በደሙ የዋጃት፣ መንጋዋን ይጠብቁ ዘንድ እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳትን እረኛ አድርጎ የሾመላት ቤተ ክርስቲያን ግን አትሞትም፤ አትቀበርምም፡፡ ታማለች ወይ ሞታለች ብንል የመከራዋን ጽናት ለመግለጽ ነው፤ ጉዞዋ በመስቀል ላይ ነውና፡፡ ይልቁንስ በውስጧ ተሰግስገው ሕመም ለሚኾኑባት፣ ሞቷንም ለሚሹት ለእነርሱ የመውጊያውን ብረት እንደ መርገጥ ለራሳቸው ይብስባቸዋል እንጂ ቤተ ክርስቲያን ትናንትም፣ ዛሬም ለዘላለሙም ሕያው ናት - በእግዚአብሔር ቸርነት፣ በቅዱሳኑ ረድኤት፣ በቀናዒ ልጆቿ መስዋዕትነት፡፡ በዘንድሮው የርክበ ካህናት ቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ የታየው ዕቅበተ ሃይማኖት እና የቅዱስ ሲኖዶሱን የበላይ አመራርነት በወሳኝነት ያስጠበቀው የብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት አንድነት የዚህ እውነታ ማረጋገጫ ነው፡፡
በመጪው ሐምሌ ወር ኻያኛ ዓመት በዓለ ሢመታቸውን እንደለመዱት በብዙ መቶ ሺሕ (በውስጥ ዐዋቂዎች መረጃ እስከ ብር አምስት መቶ ሺሕ) ብር የፍሰስ ተፋሰስ ወጪ (extravagance) ለማክበር እየተዘጋጁ ለሚገኙት አቡነ ጳውሎስ ግን የዘንድሮው ርክበ ካህናት ቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ሂደትና ፍጻሜ በአንድ ገጽታው መጋለጥን፣ በሌላ ገጽታው ደግሞ የ‹ኀይላቸው› ማእከል የተናጋበትን ያልታሰበ ውጤት ያስገኘ ነበር፡፡ በፓትርያርክነት (አበ ብዙኀን) ሥልጣናቸው ሊያሳዩት ከሚገባው አባታዊ ጽድቅ እና ፍትሕ ይልቅ በእልክና ቂም በቀለኝነት የጸኑት አቡነ ጳውሎስ በቅዱስ ሲኖዶሱ መደበኛ ስብሰባ ማብቃት ማግስት ማሰላሰል የጀመሩት ይህን ውጤት በመቀልበስ ዐምባገነናዊ ሥልጣናቸውን የሚያድሱበትን፣ ተንኰል እና ክፋት የመላበትን የዐመፅ መንገድ ነው፡፡
ንቡረ እድ ተስፋይ ተወልደ
|
በይበልጥም ይኸው ጽነታቸው ቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔውን እንዲያስፈጽሙለት እስከ ነሐሴ ወር መጨረሻ በቋሚ ሲኖዶስ አባልነት ከመረጣቸው ብፁዓን አባቶች ጋራ ግልጽ የወጣ መፋጠጥ ውስጥ ያስገባቸው ከመኾኑ የተነሣ በየዕለቱ በክፋታቸው እንዲብሱ አድርጓቸዋል፡፡ አቡነ ጳውሎስ የርክበ ካህናት ቅ/ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ካሳለፋቸው ውሳኔዎች የተለየ አቋም ባራመዱባቸው÷ በተለይም፡- በሰሜን አሜሪካ በስደት ከሚገኙ አባቶች ጋራ ስለሚካሄደው ዕርቀ ሰላም መቀጠል፤ ሕገ ቤተ ክርስቲያኑ በዋናነት የአቡነ ጳውሎስን ሥልጣን በሚያጠናክር አኳኋን ካልተሻሻለ በሚል ዜና ቤተ ክርስቲያን ጋዜጣ የቅ/ሲኖዶስን ወሳኝነትና የብፁዓን አባቶችን ክብር በመዳፈር ያወጣው ዘገባ አግባብነት በሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያንና በሕግ ዐዋቂዎች እንዲመረመር፤ የልማትና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን በአዲሱ የመያዶች ዐዋጅ ምዝገባ መሠረት ከአቡነ ጳውሎስ ተጽዕኖ እና ከእርሳቸው ፈጻምያነ ፈቃድ ጥቅመኝነት ነጻ በሚያደርገው ጠቅላላ ጉባኤና ቦርድ እንዲመራ፤ ማኅበረ ቅዱሳን ከሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ወጥቶ በብፁዕ ዋና ሥራ አስኪያጁ አመራር ሥር እንዲኾን ውሳኔ በሰፈረባቸው አራት ቃለ ጉባኤ ላይ እስከ አሁን አልፈረሙም፡፡
አቡነ ጳውሎስ በብዙኀን መገናኛ ፊት በንባብ መግለጫ በሰጡባቸው ውሳኔዎች ላይ አለመፈረማቸው ቃለ ጉባኤው ከቅዱስ ሲኖዶስ መዝገብ ቤት ወጥቶ ወደ ጠቅላይ ቤተ ክህነቱ መዝገብ የሚመራበትን ጊዜ ያዘገየዋል እንጂ በተግባር ከመፈጸም አይገታቸውም፤ እስከ አሁንም እየተመሩ ያሉት በቅዱስ ሲኖዶሱ ዋና ጸሐፊ በብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤል ፊርማ ነው፡፡ ይኹንና አቡነ ጳውሎስ በርእሰ መንበርነት የሚመሩት ቅ/ሲኖዶስ ያሳለፋቸውን ውሳኔዎች ለመንበረ ፓትርያርኩ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት የማስተላለፍ እና አፈጻጸማቸውንም የመከታተል ሓላፊነት ያለበት ቋሚ ሲኖዶስ እንደ ቀድሞው ጊዜ በቸልታ ሊያልፈው አልፈቀደም፡፡ ቋሚ ሲኖዶሱ “ኹኔታው የቅ/ሲኖዶሱን የበላይነት እንደማይቀበሉና ለውሳኔዎቹም ተገዥ እንዳልኾኑ ያሳያልና በሁሉም ላይ እስካልፈረሙ ድረስ ከእርስዎ ጋራ አንሰበሰብም” በሚል ቁርጥ አቋሙን እንዳስታወቃቸው ነው የተሰማው፤ በጉዳዩ ላይ መግለጫ ሊያወጣ እንደሚችል ነው እየተነገረ ያለው፡፡
በምልዓተ ጉባኤው ስብሰባ የመነጋገርያ አጀንዳ ማጽደቅ ወቅት ርእሰ መንበሩ አቡነ ጳውሎስ ባሳዩት ግትርነት ሳቢያ÷ ብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤልን በሰብሳቢነት መርጦ ለመቀጠል የተደረሰበት የአቋም ቁርጠኝነት በቋሚ ሲኖዶሱ ካልተደገመ በቀር አሁን ከያዙት የእልክ ቍልቍለት የሚላቀቁ የማይመስሉት አቡነ ጳውሎስ ግን የክፋት መንገዳቸውን በመቀጠል የተፍረከረከውን ዐምባገነንታቸውን የሚያድሱበትን ሕጋዊ ልባስ ለመፈብረክ፣ እየተቋቋሟቸው ያሉትን ብፁዓን አባቶችና ሌሎች ወገኖች ስም በማጥፋት፣ በማስፈራራት፣ በማወክና የኀይል ርምጃ በመውሰድ ጭምር ጸጥ ለማሰኘት አበክረው በመሥራት ላይ ይገኛሉ፤ ይህን ያስፈጽሙልኛል ያሏቸውን የተለያዩ የዐመፅ ቡድኖች በማሰባሰብ እና በማደራጀትም ላይ ናቸው፡፡
ጉዳዩን በቅርበት የሚከታተለው የፀረ - ፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ የመረጃ መርበብ ለደጀ ሰላም በላከው ዘገባ እንደገለጸው÷ አቡነ ጳውሎስ የሕግ መሠረት በመስጠት እያቋቋሙት የሚገኙት ዋነኛው የዐመፅ ቡድን “ጉባኤ አርድእት ዘኦርቶዶክስ ተዋሕዶ”ይባላል፡፡ የዚህ ቡድን ዋነኛ አስተባባሪ ያለ መ/ፓ/ጠ/ቤተ ክህነት ዕውቅና በሰሜን አሜሪካ በሚገኙት ሦስት አህጉረ ስብከት ላይ አራተኛ ሀ/ስብከት በመጨመር የአራቱም አህጉረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅና ያለ ቅ/ሲኖዶስ ዕውቅና የተቋቋመው ቀኖና ቤተ ክርስቲያንን፣ ቃለ ዐዋዲውንና ሕገ ቤተ ክርስቲያንን የሚፃረር በመኾኑ እንዲዘጋ የተወሰነበት የውጭ ጉዳይ ተጠሪ ጽ/ቤት ባለሙሉ ሥልጣን ኾኖ በአቡነ ጳውሎስ ብቸኛ ውሳኔ የተሾመው ኀይለ ጊዮርጊስ ጥላሁን (በጠቅላይ ቤተ ክህነቱ በሚታወቅበት ስሙ - ሃይለ ሰይጣን) የተባለው ግለሰብ ነው፡፡
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በመርበቡ ልዩ ክትትል እየተደረገበት ያለው ኀይለ ጊዮርጊስ ጥላሁን÷ የሀብት መሠረቱን አሜሪካ ያደረገው ‘’Ethiopia Assemblies of God’’÷ ኢትዮጵያ ውስጥ በሚታወቅበት ስሙ ደግሞ“ጉባኤ እግዚአብሔር” የተሰኘውን የፕሮቴስታንት ቤተ እምነት እንደሚያዘወትር ተደርሶበታል፡፡ አሁን በምንገኝበት ጾመ ሐዋርያት እንኳን ያገኘውን ሲጠርግ የተገኘው ኀይለ ጊዮርጊስ “ከጾም የማይተዋወቅ፣ የፕሮቴስታንት ዜማዎችን አዘውትሮ የሚያዳምጥና የሚያዜም፣ ማዕተቡን የበጠሰ የለየለት ፕሮቴስታንት ነው” የሚለው የግብረ ኀይሉ መረጃ÷ በተጠቀሰው ቤተ እምነት ማዘውተር ብቻ ሳይሆን በቤተ እምነቱ ፓስተር ኾኖ እንዲቀጠር ጭምር ዶ/ር ቤተ ማርያም በተባለው የዲኖሚኔሽኑ አንቀሳቃሽ ጥያቄ ቀርቦለት እንደነበርም አመልክቷል፡፡
በአዲስ አበባ ቦሌ፣ መገናኛ እና ስድስት ኪሎ (ጃንሜዳ አቅራቢያ) ሰፋፊ አዳራሾች ያሉትን፤ ዲፕሎማቶች፣ ከመንግሥት ባለሥልጣናትና ከተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎችም (እንደ ፕ/ር በየነ ጴጥሮስ) ጥቂቶቹ የሚገኙበትን ይህን ቤተ እምነት የሚያንቀሳቅሰው ዶ/ር ቤተ ማርያም÷ ብፁዕ አቡነ ቴዎፍሎስ ለከፍተኛ ትምህርት ወደ ውጭ ልከዋቸው ሳይመለሱ ከቀሩትና በዚያው ወደ ፕሮቴስታንትነት ከኮበለሉት ግለሰቦች አንዱ ነበር፡፡
ኀይለ ጊዮርጊስ ከከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ እና የከፍተኛ ትምህርት ተቋም ተማሪነት ዘመኑ አንሥቶ በሚታወቀው ጎጠኝነቱ÷ በ1984 ዓ.ም በፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ኑፋቄ አራማጅነቱ ተመክሮ አልመለስ በማለቱ ከጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ተወግዞ የተባረረውን ማኅበር የሃይማኖተ አበው አባላትን በተወላጅነት ስሜት በመሳሳብ ወደ ጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ለመመለስ ጥረት መጀመሩንም መረጃው ያብራራል፡፡ በቅርቡ ባካሄዱት ጉባኤያቸው ላይም ተገኝቶ የመድረክ ንግግር ማድረጉንም የሚያመለክተው መረጃው÷ እርሱ በጎጠኝነት የሚያደርገውንና ሌሎችንም ዱለታውን የሚደግፈው የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ቅርስ ጥበቃ፣ ቱሪዝምና ቤተ መጻሕፍት ወመዘክር መመሪያ ሓላፊ ዳንኤል ሰይፈ ሚካኤል እንደሚያበረታታው ገልጧል፡፡
ከእኔ በላይ ዐዋቂ ላሳር በሚለው ጠባዩ ሁሉን ካልያዝኹ፣ ሁሉን ካልጨበጥኹ በሚል ነገር ግን በውጤት አልባነቱ ተለይቶ የሚታወቀው ዳንኤል ሰይፈ ሚካኤል÷ ቅ/ሲኖዶስ መንፈሳውያን ማኅበራት የሚመሩበት መተዳደርያ ደንብ እንዲወጣ ያስተላለፈውን መምሪያ በመጥለፍ÷ አቡነ ጳውሎስ ከመደቡለት አእመረ አሸብርና ንቡረ እድ ኤልያስ አብርሃ ጋራ በመኾን “ቤተ ክርስቲያን ራሷ ማኅበር ስለሆነች በተቋም የተደራጀ ሌላ ማኅበር አያስፈልጋትም፤ ካልኾነም እንደ ኮሚቴ፣ ክበብ ያሉት ስሞች ሊሰጣቸው ይገባል፤” የሚል የሕግ ረቂቅ አይሉት ጥናት በማቅረብ እንደ ነገረ መለኰት ምሩቃን ማኅበር፣ ማኅበረ ቅዱሳንና ደጆችሽ አይዘጉ በመሳሰሉት መንፈሳውያን ማኅበራት ላይ የቋጠረውን ቂምና ጥላቻ ለመወጣት ያልተሳካና የማይሳካ ሙከራ ያደረገ ግለሰብ ነው፡፡
በትናንትናው ዕለት ከእነ አሰግድ ሣህሉ ጋራ ከቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ የተመረቀው የስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልእኮ መምሪያ ሓላፊ አእመረ አሸብር÷ የኀይለ ጊዮርጊስን የጎጠኝነት ስሜት በመበዝበዝ በ1990 ዓ.ም ከሰዋስወ ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ ማሠልጠኛ ኮሌጅ ከሌሎች ሦስት መምህራንና አምስት ደቀ መዛሙርት ጋራ ተባሮ የነበረበትንና እስከ ደብረ ማርቆስ ድረስ የሚታወቅበትን የኑፋቄ ፕሮጀክቱን ለማሳካት÷ ለበጎ ታስቦ በተቀረጸው አዲሱ የስብከተ ወንጌል መምሪያ ስም የሚያደባ ግለሰብ ነው፡፡ እንግዲህ አቡነ ጳውሎስ እንዲህ ካሉት አካላትና ግለሰቦች ጋራ የሚሯሯጠውን ኀይለ ጊዮርጊስን ነው÷ በሕገ ወጡ የዋሽንግተን ዲሲ “የውጭ ጉዳይ ተጠሪ ጽ/ቤት ባለሙሉ ሥልጣንና የሁሉም አህጉረ ስብከት ሥራ አስኪያጅ” በማድረግ በጻፉለት ደብዳቤ÷ “በጀነራል ዳይሬክተር ማዕርግ የኢ.ፌ.ዴ.ሪ መንግሥት ዲፕሎማቲክ ፓስፖርት” ለማግኘት እንዳበቁት እየተነገረ ያለው፡፡
ፓትርያርኩ ቤተ ክርስቲያናችን እንደ ነባር አገራዊ ተቋም ያላትን ክብርና ዕውቅና በመጠቀም ለኤምባሲዎችና ለመንግሥት በሚያቀርቡት በዚህ ዐይነቱ ጥያቄ የሚገለገሉበት እንደ ኀይለ ጊዮርጊስ ያሉት ግለሰቦች ከኾኑ÷ በዚህ ስመ ማዕርግ በቤተ ክርስቲያን ላይ ሊፈጸም የሚችለውን ደባ ለመገመት አያዳግትም፡፡ ለዚህ ደግሞ ቀደም ሲል ከተመለከተው የፕሮቴስታንት ቤተ እምነት እና ተወግዞ ከተባረረው ሃይማኖተ አበው ጋራ ጥብቅ ዝምድና ላለውና ከሰሞኑም የ”ጉባኤ አርድእት”ን (ተቺዎቻችው ጉባኤ አራጆች ይሏቸዋል) መተዳደርያ ደንብ በአቡነ ጳውሎስ ፊርማ ብቻ ለማጸደቅ የሚሯሯጠው ኀይለ ጊዮርጊስ÷ የፀረ-ኤች.አይ.ቪ/ኤድስ መከላከልና መቆጣጠር ፕሮጀክት አስተባባሪ ከነበረበት የልማትና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን ባሕር ዳር ቅርንጫፍ እስከ የአትላንታው/አሜሪካው ሲዲሲ ድረስ የቆየበት በማጭበርበር፣ ሙስና እና ሴሰኝነት የተሞላ ግለ ማኅደሩ ዐይነተኛ ማረጋገጫ ነው፡፡
በርግጥ እንደ አብዛኞቻችን ኢትዮጵያዊ ቤተሰብ በዳንግላ አጉንታ ማርያም ደብር ከደጋግ ቤተሰቦቹ ተወልዶ ሲያበቃ በማንነቱ አፍሮ “የፊታውራሪ ዘር ነኝ” ማለት ለሚቀናው ኀይለ ጊዮርጊስ በ”ጄነራል ዳይሬክተር”ማዕርግ ዲፕሎማቲክ ፓስፖርት ማግኘቱ አይበዛበትም፤ እርሱ ሲናገር እንደተሰማው መንግሥት ለአምባሳደርነትም ጠይቆት ነበርና፡፡ ኧረ ምን መንግሥት ብቻ÷ አቡነ ጳውሎስም በጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ምክትል ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ተስፋዬ ውብሸት ምትክ አልያም በልማት ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነርነት ቦታ ለመሾም ልመና ቀረሽ ማግባባት አድርገውለት እንዳልተስማማ ሳይቀር ያወራል፡፡ አምባሳደርነቱ ለምን እንደቀረበት እንጃ እንጂ የአቡነ ጳውሎስን ልመና እንኳ ያልተቀበለው “ቦታው ገንዘብ ስለሌለው” መኾኑንም ጭምር በግልጽ ይናገራል - ኀይለ ጊዮርጊስ ማንን ይፈራል፤ ማንንስ ያፍራል!!
እግረ መንገዳችንን÷ አቡነ ጳውሎስ በግንቦቱ ቅ/ሲኖዶስ ስብሰባ በተለይም÷ የጠቅላይ ቤተ ክህነቱን የቁጠባና ተንቀሳቃሽ ሒሳቦች ከብፁዕ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ አቡነ ሕዝቅኤል እና ከብፁዕ ዋና ሥራ አስኪያጁ አቡነ ፊልጶስ በተጨማሪ ብፁዕ አቡነ ገሪማ ታክለውበት በሦስት ሰዎች ፊርማ ለማንቀሳቀስ ያቀረቡትን ሐሳብ የተቃወሙትን፣ የልማት ኮሚሽኑን የቁጠባና ተንቀሳቃሽ ሒሳብ ደግሞ ሊቀ ጳጳሱ ብፁዕ አቡነ ሳሙኤል እንዳይፈርሙ ማገዳቸውን ውድቅ በማድረግ ጠንካራ አቋም ይዘው የተሟገቷቸውንና እንዲያውም ብፁዕ አቡነ ሳሙኤል የቤቶችና ሕንፃዎች አስተዳደር ቦርድ ሰብሳቢነታቸውን እንዲያግዟቸው ያቀረቡት ጥያቄ የምልዓተ ጉባኤውን ድጋፍ ያስገኘላቸውን ብፁዕ ዋና ሥራ አስኪያጁን በመጥላታቸው ከእርሳቸው ጋራ እንደ እርሳቸው አቋም የያዙትን ምክትል ሥራ አስኪያጁን አቶ ተስፋዬ ውብሸትንም ለማስወገድ መፈለጋቸውን እንረዳለን፡፡
የዚህ መሣርያ ኾኖ የሚንቀሳቀሰውና ውሎውን በአቡነ ጳውሎስ ቢሮ ያደረገው ኀይለ ጊዮርጊስ አቶ ተስፋዬንና ምናልባትም ለ”ጉባኤ አርድእት” ምልመላ አልመች ያሉትን እንደ ሊቀ ማእምራን ፋንታሁን ሙጬ ያሉትን የመምሪያ ሓላፊዎች በቅርቡ እንደሚያስወግዳቸው ድምፁን ከፍ አድርጎ እየተናገረ ይገኛል፤ እርሱ ራሱ ሰሞኑን በእብሪቱ ከገባበት የምክትል ዋና ሥራ አስኪያጁ ቢሮ በነጎድጓዳዊ መዐት (ቁጣ) ተዋርዶ ተባረረ እንጂ!!
ሰሞኑን መተዳደርያ ደንቡን ለሐሳቡ አመንጪ አቡነ ጳውሎስ አቅርቦ የአጽድቆት ፊርማቸውን የሚጠባበቀው“ጉባኤ አርድእት ዘርኦርቶዶክስ ተዋሕዶ” የስያሜውን ትርጉም ሲያስረዳ÷ ሰባ ሁለቱ አርድእት የቅዱሳን ሐዋርያት “ተላላኪዎች እና ረዳቶች” እንደነበሩ በማስታወስ ማኅበሩም በሐዋርያት መንበር ለተሾሙት ጳጳሳት ‹ረዳት እና አማካሪ› ኾኖ እንደሚሠራ ይገልጻል፡፡ በተጨማሪም “ወነአምን በአሐቲ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን እንተ ላዕለ ኵሉ ጉባኤ ዘሐዋርያት” ከሚለው ጥቅስ በመነሣት ቤተ ክርስቲያን ራሷ ማኅበር ነችና በውስጧ በተቋም የተደራጀ ሌላ ማኅበር እንደማያስፈልጋት አስረጅ መኾኑን ያብራራል፡፡ ከዚህ በመነሣት “ጉባኤ አርድእት” የሚለው ስያሜ ለቤተ ክርስቲያን ብቸኛ ተጠሪ እና ሌላ ማኅበር እንደማያስፈልግ መግለጫ እንደ ኾነ ስለ ስያሜው ምንነት በትርጉሙ ላይ የተሰጠው ብያኔ ያመለክታል፡፡
ዋና ዋና ዓላማዎቹን ሲያስረዳም “ሌላ ማኅበር አያስፈልግም” የሚለውን በማጽናት “ጉባኤው” ለቅዱስ ሲኖዶስ ግብአት የሚኾኑ የፖሊሲ ሐሳቦችንና አቅጣጫዎችን በመስጠት እንደሚያማክርና ፓትርያርኩን እንደሚያግዝ፤ የጥናትና ምርምር ሥራዎችን በመሥራት የቤተ ክርስቲያንን አስተዳደር እንደሚያጠናክር፤ በሰላም፣ ልማትና ሰብአዊ ተራድኦ ዙሪያ እንደሚሠማራና ለዚህም ወርክሾፖችንና ኮንፈረንሶችን በማዘጋጀት መንግሥትን ጭምር እንደሚያግዝ ይገልጻል፡፡
Daniel with Patriarch |
ይገርማል! ከማኅበሩ አመራሮች መካከል እንደሚገኙበት የተጠቆሙት እነዳንኤል ሰይፈ ሚካኤል፣ አእመረ አሸብርና ንቡረ እድ ኤልያስ ኣብርሃ ባቀረቡትና ቅዱስ ሲኖዶስ ለዳግመኛ ዝግጅት ውድቅ ባደረገው የማኅበራት መተዳደርያ ደንብ ‹ጥናት› ሰነድ ላይ፡- “ራሳቸውን ብቸኛ ተጠሪ ያደርጋሉ፤ ከሲኖዶሱ የበላይ ኾነው ሌላ ሲኖዶስ እንዳያቋቁሙ፣ የፖለቲካ መድረክ እንዳይኾኑ ያሰጋሉ፤ ከአጥቢያ ቤተ ክርስቲያንና ከአስተዳደራዊ መዋቅር ውጭ ቄስና ዲያቆን ይቀጥራሉ፤ ለቤተ ክርስቲያን ልማትና ዕድገት የአጥቢያ መዋቅር በቂ ኾኖ ሳለ ከአጥቢያ መዋቅር ውጭ የኾኑና በአጥቢያ አስተዳደር ይኹን በሀ/ስብከትና በመንበረ ፓትርያርክ ቁጥጥር የማይደረግባቸው ናቸው፤” በማለት የወነጀሏቸው በአባ ሰረቀ የተለመደ አነጋገር “ነጋዴዎች” ያሏቸውን ሌሎች ማኅበራትን ነበር፡፡ ምነው እነርሱስ ለዚህ ሰነፉ ወይስ የጥናቱ ዓላማ ሌላ ነበር?
በደንቡ ረቂቅ ላይ እንደተገለጸው÷ “ጉባኤው” ከታወቀ የመርሐ ግብር ዝግጅት ጋራ ለተያያዘ ዕቅድ ካልኾነ በቀር ገንዘብ አይሰበስብም (ፋይናንስ አያንቀሳቅስም)፤ በንግድ አይሰማራም፤ ቅርንጫፍ አይኖረውም ተብሏል፡፡ ይኹንና “ጉባኤው” በያዘው ዓላማ ስም ኀይለ ጊዮርጊስ ለአሜሪካ ምንጮቹ ወይም ለፕሮቴስታንት አጋሮቹ የልመና አቁማዳውን አይከፍትም ለማለት ባይቻልም ለጊዜው ለመሰብሰቢያ (ጽ/ቤት) ቢሮ ኪራይ ለመክፈል፣ የቢሮ ዕቃዎችን ለማሟላት ይኹን ምናልባትም ጸሐፊ ለመቅጠር የሚያሳስበው ነገር አይኖርም፡፡ ኧረ እሱ እቴ -የዓለም አብያተ ክርስቲያን የክብር ፕሬዝዳንት (የሚቀጥለው ዓመት ያበቃል መሰል) የኾኑት አቡነ ጳውሎስ÷ የዓለም አብያተ ክርስቲያን እንግዶቻቸውን በሚያሳርፉበት “የፓትርያርኮች ማረፊያ” ሕንጻ ሦስተኛ ፎቅላይ የተሟላ ቢሮ ተሰጥቶታላ! ይህ ዜና እስከተጠናቀረበት ቀን ድረስ “ጉባኤው” በቢሮው ከአራት ያላነሰ ጊዜ ተሰብስቦበታል ተብሏል፡፡ ገንዘብስ ቢያስፈልግ እኒያ ደጋግ ምእመናን ከመቀነታቸው ፈተው የሚሰጡት አይጓደል እንጂ ለጊዜያዊ ሥራ ማስኪያጃ ከቍልቢ ንዋያተ ቅድሳት ማደራጃ የተቆነጠረ ብር በበጀት እንደተመደበለት ተጠቁሟል፡፡
ይደንቃል! እነዳንኤል ሰይፈ ሚካኤል “ቤተ ክርስቲያን መምሪያ አቋቁማ በምትሠራባቸው ጉዳዮች ላይ ተመሳሳይ ክፍሎችን በማደራጀት ያልተሰጣቸውን የውክልና ሥራ በመሥራት የልመና ቋት ከፍተው ገንዘብ ያካብታሉ” ብለው ባስቀመጡት ውንጀላ እነርሱው ሲገቡበት፡፡ ቅንነቱ ካለ÷ ከመንበረ ፓትርያርኩ የሥራ ክፍሎች መካከል የቀድሞው “ዕቅድና ጥናት መምሪያ” (ሕገ ቤተ ክርስቲያን፣ 1984 ዓ.ም፣ ምዕ.7 አንቀጽ 22) የአሁኑ “ዕቅድና ልማት መምሪያ” በአግባቡ ቢጠናከር ሊፈጽመው የሚችለውን ተግባር ነጥቃችኹኮ ነው ለተንኰላችኹ የምትዶልቱት! ዛሬ የረባ የሥራ ዝርዝር እንኳ የሌለው፣ በሰው ኀይልና በሥራ ማስኬጃ በጀት የተራቆተ መምሪያ ለአብያተ ክርስቲያን ሕንጻ ግንባታ፣ ዕድሳት እና ሲሚንቶ ግዥ ፈቃድ እየሰጠ ገቢ አስገኘኹ ከማለት፣ “በመልካም አስተዳደርና ልማታዊ ጉዳዮች ጥናት አደርጋለኹ” ብሎ በቃል ከመናገር በቀር ሌላ ምን የረባ ሥራ ይዞአል?
ለነገሩ ዘመናዊ የሥራ አመራር አደረጃጀትን በመከተል ሳይኾን ለሰዎች ቦታና ሓላፊነት ከማሰብ አኳያ ብቻከሚገባው በላይ የተንዛዛ መዋቅር ይዞ በመጓዝ ላይ በሚገኘው ቤተ ክህነት÷ ሲሻው የቤተ መጻሕፍት ወመዘክር ሓላፊ፣ በል ሲለው ደግሞ በሌሉ የሥራ ክፍሎች እና ባልተሟላ የሰው ኀይል የቱሪዝም መምሪያን ጨምሮ፣ የቅርስ ጥበቃንም ጠቅልሎ ራሱን “የቅርስ ጥበቃና የቤተ መጻሕፍት ወመዘክር እንዲሁም የቱሪዝም መምሪያ ሓላፊ” ብሎ የሚሠይም ሓላፊ ባለበት ቤት ብዙ መጠበቅ አይቻልም፡፡
እንዲያው ለአማካሪነቱስ ቢኾን በ2001 ዓ.ም የርክበ ካህናት ቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ውሳኔ ተቋቁሞ የነበረውና ሰባት ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳትን በአባልነት ይዞ የነበረው የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ቅዱስ ሲኖዶስን ለማገዝ በልዩ ልዩ የሞያ ዘርፎች ሊያደራጃቸው ያሰባቸው የመማክርት መዋቅሮች አልነበሩትምን? አቡነ ጳውሎስ ወይም እናንተ ስታስቡት ርቱዕ ኾኖ ተገኘ ማለት ነው? ለነገሩ በየትኛው ብቃታችኹ ታማክራላችኹ? ምቀኝነት፣ ብኩንነት፣ ጎጠኝነት፣ ኑፋቄና ተንኰል እንደኾን ዕውቀት አይኾን!! በዘመድ አዝማድ አድሏዊ አሠራር፣ ሙስናና ኑፋቄ የበከተው፣ ለመንግሥትም የፖለቲካ ዕዳ የኾነው የአቡነ ጳውሎስ የኻያ ዓመት ዐምባገነናዊ አስተዳደርስ እንዲህ ዐይነቱ ወግ ማዕርግ መች ይወድለታል - ቅ/ሲኖዶሱን እና ፓትርያርኩን እናማክራለን የምትሉት ለክፋታችኹ ኾኖ እንጂ!!
“ጉባኤ አርድእት” ለተቋቋመበት የክፋት ዓላማ ዐይነተኛ ምስክሩ÷ ቅዱስ ሲኖዶስ በጥቅምቱና በግንቦቱ መደበኛ ስብሰባዎች አቡነ ጳውሎስ በመነጋገርያ አጀንዳነት አቅርበውት÷ “ወቅቱ አይደለም” በሚል ውድቅ ያደረገውን የሕገ ቤተ ክርስቲያን ማሻሻል ጉዳይ÷ ከአጥቢያ አብያተ ክርስቲያን እስከ አህጉረ ስብከት ድረስ ጥቅመኛ አለቆችንና የሥራ ሓላፊዎችን አነሣስቶ በብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳትን ላይ በሚፈጥሩት ጫና አቋማቸውን በማስቀየር ለማስፈጸም የጀመረው ሙከራ ነው፡፡ ቡድኑ በራሱ ሥልጣን ረቂቅ እስከማዘጋጀት የደረሰበት የቤተ ክርስቲያን የበላይ ሓላፊ ቅ/ሲኖዶስ መምሪያ የኾነውን ሕገ ቤተ ክርስቲያን የማሻሻል ዓላማ÷ በአገልግሎት፣ አስተዳደርና ልማት ፍትሐዊ እና መንፈሳዊ አመራር እና አሠራር ተረጋግጦ ቤተ ክህነታችን አብነታዊ የእምነት ተቋም እንዲኾን የማድረግ አይደለም፡፡
የቡድኑ ዋነኛ ዓላማ ቤተ ክርስቲያንን 16 ዓመት ወደኋላ መመለስ ነው፡፡ ይህም የቅዱስ ሲኖዶሱ የበላይ አካልነት በፓትርያርኩ የበላይነት የተተካበት፣ የቅ/ሲኖዶስ ሥልጣንና ሓላፊነት የሚገለጽበት ጽ/ቤቱ እና ውሳኔዎቹ ተግባራዊ የሚደረጉበት የመ/ፓ/ጠ/ቤ/ጽ/ቤት እንዳይሠራ ዋና ጸሐፊው እና ዋና ሥራ አስኪያጁ በአቡነ ጳውሎስ ምርጫ የሚሾሙበት፤ በቅ/ሲኖዶሱ ጉባኤ የአጀንዳ አቀራረብ፣ የስብሰባ አመራርና የውሳኔ አሰጣጥ የፓትርያርኩን ግላዊ ውሳኔ ገዝፎ የነበረበት፤ በዚህም ሳቢያ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳቱ ራሳቸው የተቃውሞ እንቅስቃሴ የጀመሩበት፣ ከ90 በመቶው ያላነሰው አገልጋይና ሠራተኛ በቅጥር፣ ዝውውር፣ የደረጃ ዕድገት፣ የደሞዝ አከፋፈልና ስንብት ረገድ በጉቦ፣ ዝምድና፣ አድልዎ፣ ወገናዊነት እና ጥቅማጥቅም የተበደለበት፣ ለዕቅበተ ሃይማኖት የሚሰጠው ትምህርተ ወንጌል አጽጾ ምእመናንና ቅርስ ነዋያተ ቅድሳታችን ለአደጋ የተጋለጡበት የ1988 ዓ.ም ሕገ ቤተ ክርስቲያን ዐይነት ሰነድ መልሶ ማቋቋም ነው፡፡
ከ1984 ዓ.ም ጀምሮ በሥራ ላይ የነበረውን ሕግ ያሻሻለው እና በሚያዝያ ወር 1988 ዓ.ም የወጣው ሕገ ቤተ ክርስቲያን÷ የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት ከፍተኛ ተቃውሞ እያሰሙበት በአቡነ ጳውሎስ ፍላጎትና ተጽዕኖ እንደጸደቀ÷ በቤተ ክርስቲያን አመራርና አስተዳደር የተፈጸመውን አድሏዊ አሠራር፣ አስተዳደራዊ በደልና የገንዘብ ምዝበራ ለማጣራት÷ ኅዳር ሁለት ቀን 1990 ዓ.ም በቋሚ ሲኖዶስ የተቋቋመው አጣሪ ኮሚሽን ሐምሌ 10 ቀን 1990 ዓ.ም ለምልዐተ ጉባኤው ያቀረበው ባለ53 ገጽ ክፍል አንድ ሪፖርት አረጋግጧል፡፡
“በቅዱስ ሲኖዶስ አመራርና በሕገ ቤተ ክርስቲያን አተረጓጎም” ዙሪያ በአጣሪ ኮሚሽኑ ሪፖርት ገጽ 14 ላይ እንደተገለጸው÷ ሚያዝያ 30 ቀን 1988 ዓ.ም ጸድቆ ሥራ ላይ የዋለውን ሕገ ቤተ ክርስቲያን ያረቀቀውና ያዘጋጀው በቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ተመርጦ ያልተሠየመና ለዚህ ተግባር የተሟላ ግንዛቤ አላቸው ተብለው የማይገመቱ ግለሰቦች ነበሩ - ልክ እንደ አሁኖቹ የ”ጉባኤ አርድእት” አባላት ማለት ነው፡፡ በ1984 ዓ.ም የቅዱስ ሲኖዶስን ተግባር አስመልክቶ ምዕራፍ 1 ቁጥር 3፣ “የቅዱስ ሲኖዶስ ዓላማ” በሚል ርእስ ሥር “ቅዱስ ሲኖዶስ በጠቅላላው የቤተ ክርስቲያን አስተዳደር የበላይ ሓላፊ” እንደኾነ በመግለጽ “ፓትርያርኩ የቅዱስ ሲኖዶስ ሰብሳቢ (ርእሰ መንበር) ነው” ይላል፡፡ እስከ 1984 ዓ.ም ድረስ በሥራ ላይ የነበረው የ1971 ዓ.ም ሕገ ቤተ ክርስቲያን የሚያስቀምጠው ይህንኑ ሐሳብ ነው፡፡
ይኹንና ሚያዝያ 30 ቀን 1988 ዓ.ም ምልዓተ ጉባኤው ባልመረጣቸው ሰዎች ተዘጋጅቶ በፓትርያርኩ ፍላጎትና ተጽዕኖ የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት እየተቃወሙ በጸደቀው ሕገ ቤተ ክርስቲያን ምዕራፍ 3 አንቀጽ 5 ላይ የሰፈረው ግን “ቅዱስ ሲኖዶስ በቅዱስ ፓትርያርኩ አመራር ሰጭነትና ሰብሳቢነት የሚከተሉት ሥልጣንና ተግባር ይኖሩታል” በሚል ነው ተተክቶ ሲያበቃ ነው ተሻሻለ የተባለው፡፡ የአጣሪ ኮሚሽኑ አባላት ስለዚህ ዐይነቱ ማሻሻያ በሰጡት አስተያየት÷ “ይህ ኀይለ ቃል (በቅዱስ ፓትርያርኩ አመራር ሰጭነት) በዚህ ሕገ ቤተ ክርስቲያን ላይ የተጨመረና የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የመጨረሻው አካል ቅዱስ ሲኖዶስ መኾኑ ቀርቶ በቅዱስ ፓትርያርኩ አመራር ሥር የሚገለጽ የበታች አካል እንደኾነ፣ በአንጻሩ ፓትርያርኩ ከሰብሳቢነት ያለፈ በሲኖዶሱ ላይ የበላይነትን የሚያጎናጽፈው ኾኖ ስለሚታይእዚህ ላይ የቀረበው ቅሬታ አግባብነት ያለው መኾኑ ታምኖበታል፡፡” ይላል፡፡
ርእሰ ደብር መሐሪ ኀይሉ |
ከአጣሪ ኮሚሽኑ ሪፖርት በኋላ ተዘጋጅቶ በ1991 ዓ.ም የጸደቀውና እስከ አሁን በሥራ ላይ የሚገኘው ሕገ ቤተ ክርስቲያን ምዕራፍ 2 አንቀጽ 5 ላይ “በመንፈስ ቅዱስ የሚመራው ቅዱስ ሲኖዶስ የመንበረ ሐዋርያት ወራሽ ስለኾነ በቤተ ክርስቲያኒቱ የመጨረሻው ከፍተኛ የሥልጣን ባለቤት ነው፤ ሕጎችን፣ ልዩ ልዩ ደንቦችንና መምሪያዎችን የማውጣትና የዳኝነት ሥልጣን አለው፡፡” ይላል፡፡ በአንቀጽ 15 ቁጥር 1 እና 2 ላይም “ፓትርያርኩ በተሰጠው ሓላፊነት መሠረት ሃይማኖትንና ቀኖና ቤተ ክርስቲያንን ይጠብቃል፤ ያስጠብቃል፤ የቅዱስ ሲኖዶስን ጉባኤ በሊቀ መንበርነት ይመራል፡፡” ይላል፡፡ እንግዲህ በ”ጉባኤ አርድእት” አመራሮች ኮሚሽን አድራጊነትበተጻፈው ዜና ቤተ ክርስቲያን ጋዜጣ ላይ “የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩን መብት የሚጋፋ ነው፤ ቅዱስነታቸውን አላሠራቸውም፤ ይታረም፤ ይሻሻል፤” በሚል ዘመቻ የተከፈተበት ሕገ ቤተ ክርስቲያን ይህ ነው፡፡
በአጣሪ ኮሚሽኑ ሪፖርት መሠረት ሕገ ቤተ ክርስቲያኑ ከ1968 ዓ.ም ጀምሮ ሲሻሻል እንደመጣ የተመለከተ ሲኾን ይህም የቅዱስ ሲኖዶስን አካላት ደረጃ፣ ሥልጣንና ተግባር በሚገባ በሚወስን መልኩ መኾን እንዳለበት አሳስቧል፡፡ በእነ ኀይለ ጊዮርጊስ የሚመራውን የ”ጉባኤ አርድእት” አባላት የቆረቆራቸው ግን ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳቱ ለአቡነ ጳውሎስ “ሽቅብ መልስ መስጠታቸው”፣ እንዳሻቸው ኤጲስ ቆጶሳትንና የአህጉረ ስብከት ሥራ አስኪያጆችን ለመሾም እና ከአንዱ ሀገረ ስብከት ወደ ሌላው ለማዘዋወር አለመቻላቸው ነው፡፡ በሕገ ቤተ ክርስቲያኑ (91) መሠረት ኤጲስ ቆጶሳት የሚሾሙት በቅዱስ ሲኖዶስ ሲታመንበትና አስፈላጊ ኾኖ ሲገኝ ቅዱስ ሲኖዶሰ በሚሠይመው አስመራጭ ኮሚቴ አማካይነት ተመርጠው ሲቀርቡ ነው፡፡ ኤጲስ ቆጶሳት ከሀገረ ስብከታቸው የሚነሡት ለቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ ቀርቦ፣ ተጠንቶ ሲወሰን ነው፡፡ የአህጉረ ስብከት ሥራ አስኪያጆች የሚሾሙት የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ለብፁዕ ዋና ሥራ አስኪያጁ በማቅረብ ፓትርያርኩ ሲስማማበት በብፁዕ ዋና ሥራ አስኪያጁ ፊርማ ነው፡፡
በዲድስቅልያ እንደተጻፈው የዜና ቤተ ክርስቲያን ርእሰ አንቀጽም እንደገለጸው ፓትርያርኩን “እንደ ንጉሥ መፍራት፣ እንደ አባት መውደድ፣ እንደ እግዚአብሔር ማመን” የተገባ ነው፤ እንደቀድሞው የራሳቸውንና የቤተ ክርስቲያንን ክብር የሚያስጠብቁ ጳጳሳት ይሾሙ ዘንድ የምእመናን ተሳትፎ መኖሩ አስፈላጊ ነው፡፡ እንደ ፍትሕ መንፈሳዊ ድንጋጌ ተሿሚዎቹ በትምህርት ደረጃቸው ብሉያትንና ሐዲሳትን የተማሩ፣ አራቱን ወንጌላት የሚተረጉሙ፣ የግል ሀብትና ንብረት የማያፈሩ፣ ከቅጽረ ቤተ ክርስቲያን ውጭ የማይኖሩና ንጽሕናቸውና ቅድስናቸው በሕዝበ ክርስቲያኑ የማይጠየቅ ሊኾን ይገባል፡፡
ነገር ግን እኒህ ሁሉ ድንጋጌዎች የኢትዮጵያ ፓትርያርክ (ርእሰ አበው) ለመኾን በተሾሙበት ቀን የፈጸሙትን ቃለ መሐላ በመዘንጋት ሃይማኖትን የሚያፋልስ፣ ቀኖና ቤተ ክርስቲያንን የሚጥስ ተግባር እየፈጸሙ በመኾናቸው በካህናትንና ምእመናን ዘንድ ታማኝነታቸውንና መንፈሳዊ ተቀባይነታቸውን ማጣታቸውእየተረጋገጠ በመጣው በአቡነ ጳውሎስ ዘመነ ፕትርክና እንዲኾን አይጠበቅም፡፡ በተለይም የቅ/ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ስብሰባዎችን እንደ ተግዳሮት ከማየታቸውም አልፎ “እየተሠቃየኹ ነው፤ መንግሥት አንድ ርምጃ መውሰድ አለበት፤ መንግሥት ርምጃ ካልወሰደ አልሰበስብም” በሚሉት ፓትርያርክ አቡነ ጳውሎስ ዘመን እንደምን ሊታሰብ ይችላል?
የ”ጉባኤ አርድእት” አመራሮች ግን በፓትርያርኩ ይኹንታና በገዛ ሥልጣናቸው ያረቀቁትን “ሕገ ቤተ ክርስቲያን” ቀደም ሲል እንደተተገለጸው በነውጥ (mob) ለማስፈጸም እንዲመቻቸው የድጋፍ ፊርማ ማሰባሰብበሚል የጠቅላይ ቤተ ክህነቱን መምሪያ ሓላፊዎችና ሠራተኞች ግራ እያጋቡ ነው፡፡ ከሠራተኛው ተሰበሰበ የተባለው ፊርማም፣ በቂም ባይሆን በፓትርያርኩ አማካይነት ለቅ/ሲኖዶስ ይቀርባል፡፡ ከተለያዩ ምንጮች በሚቀርቡላቸው መረጃዎች ሂደቱን በጥሞና እየተከታተሉ የሚገኙት ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት እና ቋሚ ሲኖዶሱ ግን የ”ጉባኤ አርድእት”ን ሕጋዊነት ይኹን የሕገ ቤተ ክርስቲያኑን የጓሮ በር ማሻሻያ እንደማይቀበሉት ስጋት ስለገባቸው ተጨማሪ ማስተማማኛ መያዝ አልያም ወደ ቀጣዩ ደረጃ ለመሄድ አስበዋል፡፡
ንቡረ እድ ኤልያስ |
ቀጣዩ ደረጃ የመንግሥትን ጣልቃ ገብነት መጠየቅ ነው፡፡ ከዚያ በመለስ ግን ከቅዱስ ሲኖዶስ በኩል ያለውን ዕድል አሟጦ ለመጠቀም ሌሎች ሁለት ቡድኖችን ጨምሮ ማደራጀት አስፈልጓቸዋል፡፡ ከእነርሱም አንዱ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅ በኾኑትና በአሁኑ ወቅት “ሲሾም ያልበላ ሲሻር ይቆጨዋል” በሚለው ብሂል የተነከሩት ንቡረ እድ ኤልያስ ኣብርሃ ናቸው፡፡ የንቡረ እዱ ነገረ ሥራ በአፏ ማር ይዛ እሬት አርግዛይሉት ዐይነት ነው፤ ሲበዛ ፈሊጠኛ እና ጠንቃቃ ናቸው፤ ነገር ግን ከምእመኑ እይታ ሊሰወሩ አይችሉም፡፡
ከተሾሙ በስድስት ወራት ውስጥ የሚሳብላቸውን ሙክትና የሚጠቀለልላቸውን ውስኪ ሳይጨምር ገርጂ አካባቢ አጥረው ባቆዩት መሬት በጀመሩት G+3 መኖርያ ቤት ሕንጻ ግንባታ ጥቅመኛ የደብር አለቆች የሚያራግፉላቸው መኪና አሸዋ እና ድንጋይ ለጉድ ነው፡፡ የንቡረ እዱ ድርሻ ቸገረኝ ብሎ መናገር ሳይሆን ቤት እየሠራኹ ነው ብሎ ማወጅ ብቻ ነው፡፡ ንቡረ እዱ ድምፃዊ ናቸው፤ ድጓም ሞያቸው ነው፡፡ ታዲያ ለቅኝት ነው ቢሉ ወይ ለአገልግሎት÷ በየአጥቢያው ጎራ ብለው በቆሙ፣ በቀደሱና ባስተማሩ ቁጥር በትንሹ ከብር 25,000 ያላነሰ እንደሚቀበሉ ይወራል፤ ከሚቀበሉት ሁሉ ግማሹ የቅዱስነታቸው መኾኑን ሹክ ስለሚሉ አጥቢያው ከፍተኛ ገቢ ‹የተመደበበት› ከኾነ መጠኑ ከተጠቀሰውም ጫን ሳይል እንደማይቀር ይነገራል፡፡
የ1990ው አጣሪ ኮሚሽን ጥቅምት 23 ቀን 1991 ዓ.ም ለቋሚ ሲኖዶስ ባቀረበው ክፍል ሁለት ሪፖርት፣ ገጽ 27 ላይ እንደሚገልጸው÷ ከእንዲህ ዐይነቶቹ የደብር አለቆች ብዙዎቹ አነስተኛ ገቢ ካለው ደብር ከፍተኛ ገቢ ወዳለው ደብር ለመዘዋወር አልያም ቦታቸውን ለማጽናት የሚፈልጉ ናቸው፤ ዝውውራቸው በፓትርያርኩ የሚወሰን በመኾኑ ለንቡረ እዱ እና ከእርሳቸው በታች በየደረጃ ለሚገኙቱ “አመቻቾች” የሚወጣውን የታቦት ብር ማሰብ ነው እንግዲህ፡፡ ሌላውን ቡድን የሚመሩት÷ ለአቡነ ጳውሎስ ባላቸው የሥጋ ዝምድና የሚታወቁትና በብፁዕ አቡነ ፊልጶስ ከነበራቸው የመምሪያ ሓላፊነት ደረጃ ዝቅ ተደርገው በልማት ኮሚሽን የትራንስፖርት ክፍል ሓላፊነት እንዲሠሩ በመመደባቸው ግንኙነታቸው ሻክሮ የቆየው ሊቀ ኅሩያን ያሬድ ከበደ ናቸው፡፡ ከአቡነ ጳውሎስ ሐውልተ ስምዕ ጋራ በተያያዘ የእጅጋየሁ በየነ ሚና በመግዘፉ ከአቡነ ጳውሎስ ጋራ ተጨማሪ ቅራኔ ውስጥ የገቡት ሊቀ ኅሩያን ያሬድ÷ ለአቡነ ጳውሎስ ዕቅድ ሰሞኑን ለዕርቅ እየተለመኑ እንደኾነና ዕርቁን ተከትሎ ወደቀድሞው ከፍተኛ ሓላፊነታቸው ሳይመለሱ እንደማይቀር ተሰምቷል፤ ብፁዕ ዋና ሥራ አስኪያጁ ሹመቱን እንደማይቀበሉት የተረጋገጠ ቢኾንም፡፡
ንቡረ እድ ኤልያስ እና ሊቀ ኅሩያን ያሬድ እርስ በርሳቸው ስምምነት እንደሌላቸው የታወቀ ቢኾንም÷ በተሰጣቸው ተልእኮና ግብ ግን አንድ ናቸው፡፡ ይኸውም በተለይ ንቡረ እድ÷ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት አድባራትና ገዳማት አለቆችንና ጸሐፊዎችን እንደ እጅጋየሁ በየነ ካሉት ጋራ በመኾን ሲቀሰቅሱና ሲያነሣሡ ሁለተኛው ደግሞ ተመሳሳዩን ተግባር በተለይ በአህጉረ ስብከት ሥራ አስኪያጆች መካከል፣ በታላላቅ አድባራትና ገዳማት አስተዳደሮች ላይ ያካሂዳሉ ተብሏል፡፡ የሁለቱም ቡድኖች ስምሪት መገናኛው ኮሩ÷ አቡነ ጳውሎስን በመቋቋም ጽኑ አቋም ያሳዩትን በተለይም ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት አቡነ ሕዝቅኤልን፣ አቡነ ፊልጶስን፣ አቡነ ቄርሎስን፣ አቡነ ገብርኤልን፣ አቡነ ናትናኤልን፣ አቡነ አብርሃምን፣ አቡነ ዲዮስቆሮስንና አቡነ ሉቃስን በየአህጉረ ስብከት ጽ/ቤቶቻቸው÷ በተለይ ከሥራ አስኪያጆቻቸው ጋራ÷ በዜና ቤተ ክርስቲያን ጋዜጣ ፍንጭ የተሰጠበትን÷ ጥቅም ላይ የተመሠረተ ግጭት መፍጠር፣ ተበደሉ የተባሉ አገልጋዮችንና የተለያዩ ቡድኖችን ቅሬታ በማስፋፋት ክስንና ሁከትን ማባባስ፣ እንዳመቺነቱም በቀጥታ ማስፈራራትና ጫና አቋማቸውን በማላላት መድረኩን የአቡነ ጳውሎስ መፈንጫ ማድረግ ነው፡፡ ከእኒህ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ጋራ አቡነ ሳሙኤልንና አቡነ ጢሞቴዎስን የመሳሰሉትን ብፁዓን አባቶች÷ “መኖርያ ቤታቸው የማኅበረ ቅዱሳን መሰብሰቢያ ነው፤ አጀንዳ የሚቀረጽበት ነው” በሚል የፖለቲካ ውንጀላ የማሸማቀቅ ሙከራዎችን የማካሄድ ዕቅድ ተይዟል፡፡
በዚህ ረገድ የ”ጉባኤ አርድእት” ዋነኛ አመራሮች በመፍቀሬ ፕሮቴስታንታዊ ብሎጎች ላይ ከቅ/ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ከመጀመር አስቀድሞ በጉባኤው የሥራ ቀናትና በስብሰባው መጠናቀቅ ማግስት የቀጠሉት የብፁዓን አባቶችን ስም የማጥፋት ተግባር ለእኒህ ቡድኖች የሚሰጥ ድጋፍ እንደኾነ ይታመናል፡፡ ይኸው የውግዘት ናዳ እና የስም አጥፊነት ተግባር የእንቅስቃሴው ዋነኛ ዒላማ በኾነው ማኅበረ ቅዱሳን ላይም በተመሳሳይ መልኩ እንደሚፈጸም ይጠበቃል፡፡ ምልአተ ጉባኤው ስለ ማኅበሩ የመዋቅራዊ ተጠሪነት ለውጥ ያሳለፈው ውሳኔ እያደር የቆረቆራቸው፣ ከእጃቸው ሳይታሰብ እንዳመለጠ ሰለባ ያንገበገባቸው አቡነ ጳውሎስ በቃለ ጉባኤው ላይ ካለመፈረማቸውም በላይ ቃለ ጉባኤው በወቅቱ ከቅዱስ ሲኖዶስ መዝገብ ቤት ወጥቶ ወደ ጠቅላይ ቤተ ክህነቱ መዝገብ ቤት እንዳይመራ በማዘግየት÷ የምሥረታው ኻያኛ ዓመት በዓል አከባበር ዕቅድ አካል የነበረው የጉዞ መርሐ ግብሩ እንዲሰናከል በማድረግ ቀዝቃዛ በቀላቸውን ጀምረዋል፤ ሰው የከለከሉትን አብልጦ ይሻልና በቁጥሩ ከ12,500 የማያንስ ምእመን በክልከላው እልክ ተጋብቶ የጠቅላይ ቤተ ክህነቱን ቅጽር መላወሻ እስኪጠፋ በማጥለቅለቅ፣ በዝማሬው፣ በቃለ እግዚአብሔሩ በማድመቅ በተግባር አስተባበለባቸው እንጂ!!
Enqu Baherey |
“ጉባኤ አርድእት” በሌላ ገጽታው÷ አቡነ ጳውሎስ ምልአተ ጉባኤው ለማኅበሩ ባስተላለፈው ውሳኔ አንጻር የጀመሩት ማኅበረ ቅዱሳንን የማዳከምና የማፍረስ ስልታዊ ዘመቻ እንደኾነ የሚገልጹ ምጮንች፣ “ጉባኤ አርድእት” ሰሞኑን ለፓትርያርኩ አቅርቦ በሚያጸድቀው መተዳደርያ ደንቡ መሠረት ለመዝለቅ የማይቻለው ከኾነ÷ በጥቅምቱ ቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ረቂቁ ቀርቦ እንደሚጸድቅ በሚጠበቀው የማኅበራት መተዳደርያ ደንብ መሠረት “ጉባኤ አርድእት” ዕውቅና ጠይቆ ራሱን ወደ “ማኅበረ አርድእት” በመለወጥ ተግዳሮቱን እንደሚቀጥል ተጠቁሟል፡፡ በዚህ ወቅትየ”ማኅበረ አርድእት” ዋነኛ ሥራ የሚኾነው ከማኅበረ ቅዱሳን ጋራ በሠባራ ሰንጣራው ምክንያት ቀጥተኛ ግጭትን በማስፋፋት በሚፈጠረው ጠቅላላ ነውጥ “ማኅበራት አያስፈልጉም” የሚለውን ቅዠታቸውን እውን ወደሚያደርግ ርምጃ ማቀላጠፍ ነው፡፡ ከላይ የተጠቀሱት ቡድኖች በአህጉረ ስብከት፣ በተመረጡ አድባራትና ገዳማት አስተዳደሮች ላይ የነውጥ መሠረታቸውን በማስፋት በጠቅላይ ቤተ ክህነቱና በብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ላይ ጫና ለመፍጠር የሚያደርጉት እንቅስቃሴ በሌላ ገጽታው የዚህን “ጉባኤ/ማኅበር” ተቀባይነት የማረጋገጥ ተልእኮ እንዳለው ተገልጧል፡፡ በታዛቢዎች ጥቆማ÷ ራሳቸው አቡነ ጳውሎስ ትናንት፣ ሰኔ 10 ቀን 2004 ዓ.ም በተከናወነው የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ ደቀ መዛሙርት ምረቃ በዓል ላይ “ወነአምን በአሐቲ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን እንተ ላዕለ ኵሉ ጉባኤ ዘሐዋርያት” የሚለውን ኀይለ ቃል “ጉባኤ አርድእት” ባቀረበው መተዳደርያ ደንብ ላይ ከተብራራበት መንገድ ጋራ አመሳስለው ማቅረባቸው ራሳቸውን የዘመቻው አካል ስለማድረጋቸው የተረጋገጠበት አጋጣሚ ነበር፡፡
አቡነ ጳውሎስ፣ ንቡረ እድ ኤልያስ ኣብርሃ እና አባ ሰረቀ ቀደም ሲል በተለይ ለፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር እንዳቀረቡት የሚገመተውን ክስ መሠረት አድርጎ ሚኒስቴሩ÷ “የሃይማኖት አክራሪነትና የፀረ-አክራሪነት ትግላችን” በሚል ርእስ ባዘጋጀው የከፍተኛ አመራር ሥልጠና ሰነድ እና ሰሞኑን ለንባብ በበቃው የኢሕአዴግ የንድፈ ሐሳብ መጽሔት÷ “በሰላምና ሕገ መንግሥቱ ዙሪያ ሀገራዊ መግባባት መፍጠር” በሚል ርእስ በቀረበው ጽሑፍ÷ ማኅበረ ቅዱሳን እንደ ወሃቢያ ሁሉ “በኦርቶዶክስ ክርስትና ሃይማኖት ማዕቀፍ የአክራሪነትና የጽንፈኝነት አመለካከትና ተግባር የሚንጸባረቅበት አደረጃጀት (ሴክት)” ተደርጎ ተቀምጧል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሚያዝያ ወር መጀመሪያ ላይ በፓርላማ ቀርበው በተመሳሳይ ጉዳይ ላይ ከተናገሩ ወዲህ እንኳ በማኅበሩ ሚዲያዎች የተሰጡት ምላሾች ሰሞኑን በየክልሉ በቀጠሉት ሥልጠናዎች ላይ እንኳ ከግምት የገቡበት ኹኔታ አይታይም፡፡
የወቅቱ የመንግሥት ፕሮፓጋንዳ አቅጣጫ ኾኖ የተያዘውን የአክራሪነት ዲስኩር እንደ ጥሩ አጋጣሚ የወሰዱት እነኀይለ ጊዮርጊስ ታዲያ÷ በመንግሥት ሚዲያዎች የሚወጡ መግለጫዎችንና በግንባሩ ሰነዶች ላይ የሰፈሩ ጽሑፎችን እያጋነኑ መንግሥት ማኅበሩን “ከጥቂት ወራት ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ እንደሚዘጋው”፣ የማኅበሩን አመራሮችና አባላትንም ከዛሬ ነገ ለቃቅሞ እንደሚያስራቸው ውስጥ ዐወቅ መስለው ሽብር እየነዙ ይገኛሉ -“ጠላትኽን ውኃ ሲወስደው እንትፍ ብለህ ጨምርበት” ዐይነት የበቀል ጥማት ነው፡፡
አክራሪነትን ከቀናዒነት መለየት፣ የአክራሪነት እና ጽንፈኝነት እንቅስቃሴን በመሠረቱ አጥብቆ መኰነን፣ በሕገ መንግሥቱ የተደነገገውን የሃይማኖትና መንግሥት መለያየት አምኖ የእምነት ነጻነትን መቀበል አንድ ነገር ኾኖ÷ በቤተ ክርስቲያኒቱ ቅዱስ ሲኖዶስ ታውቆ የጸደቀ መተዳደርያ ደንብ ያለውና የሚሠራውን የሚያውቅ፣ መዋቅሮቹን ከሚለፈፈው የፖለቲካ(?) ጣልቃ ገብነት በጥብቅ የሚቆጣጠርና ለባዕድ (ውጫዊ) ተጽዕኖ የማይጎናበስ ማኅበር በማይመለከተው ዲስኩር ይኹን የሽብር ወሬ ሊጨናነቅ አይገባውም፡፡ እንዲያውም ማኅበሩ የራሱን ህልውና ማእከል አድርጎ ከመንቀሳቀስ ይልቅ÷ በቅርቡ ተሻሽሎ በሚጸድቅለትና የተሻለ ማንዴት በሚያሰጠው መተዳደርያ ደንቡ በመታገዝ÷ ከጠቅላይ ቤተ ክህነቱና በየደረጃው ከሚገኙት መዋቅሮቹ ጋራ እንደ ሰምና ፈትል ተጣጥሞ በተቋማዊ ብቃት ማእዝናዊ መለኪያዎች ምሳሌያዊ የኾነ፤ በአስተዳደር፣ ልማት እና መንፈሳዊ አገልግሎት የተጠናከረ ቤተ ክህነት በመፍጠር ረገድ የበኩሉን ለመወጣት መዘጋጀት እንደሚኖርበት አስተያየት እየተሰጠ ይገኛል፡፡
እነኀይለ ጊዮርጊስ ለማኅበረ ቅዱሳን የሸረቡለት የጥፋት ድግስ አላበቃም፤ ሌላም አሥቂኝ ሙከራ ሊያደርጉ እየተሰናዱ ነው፡፡ ይኸውም እንደ እነርሱ አባባል “ከማኅበረ ቅዱሳን በተለያየ ጊዜና በተለያየ ምክንያት አኩርፈው የወጡ አባላትን በመሰብሰብና ሌላ ማኅበረ ቅዱሳን በማቋቋም የፊቱን በኋላው መተካት”ነው፡፡ ለዚህም በአንድ ወቅት “ስማቸው ለሰማይና ለምድር የከበደ” የተባሉ ግለሰቦችን በፊታውራሪነት ከማሰለፍ ጀምሮ በርከት ያሉ “አኩራፊ አባላት”ን ማሰባሰባቸውን እየገለጹ ይገኛሉ፡፡ እነኀይለ ጊዮርጊስ ለዚህ ከፋፋይ ተንኰላቸው በጄ የሚላቸው ጥቂት ግለሰቦች እንደማያጡ ቢገመትም የማኅበሩ አባላትና አጋር አካላት ሁሉ ይህን ተንኰል ዐውቀው እንዲጠነቀቁ ማድረግ ተገቢ ነው፡፡
“ጉባኤ አርድእት” በሚለው ስማቸውና “ማኅበራት አያስፈልጉም” በሚለው ዓላማቸው መካከል እንኳ ትልቅ መጣረስ እንዳለ ለማያስተውሉት እነኀይለ ጊዮርጊስ÷ በኻያኛው ዓመት የማኅበሩ ምሥረታ በዓል ላይ እንደተገለጸው÷ ማኅበረ ቅዱሳን ቤተ ክርስቲያንን የማገልገል አንድ ናሙና እንጂ ብቸኛው አይደለም፤ ብዙ ማኅበራት ነበሩ፤ አሉም፡፡ ከእነርሱም መካከል በቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ እና በቅዱስ ፍሬምናጦስ አባ ሰላማ ከሣቴ ብርሃን መንፈሳዊ ኮሌጅ ምሩቃን በመቋቋም ላይ የሚገኘው የነገረ መለኰት ምሩቃን ማኅበርአንዱ ነው፡፡
የነገረ መለኰት ምሩቃን ማኅበር ዋና ዓላማ÷ የወንጌል ትምህርት ባልተዳረሰባቸው አካባቢዎች ሐዋርያዊ አገልግሎት መስጠት፤ የቤተ ክርስቲያኒቱ ዶግማ፣ ሥርዐት፣ ትውፊትና ንዋያተ ቅድሳት በአግባቡ እንዲጠበቁ የበኩሉን አስተዋፅኦ ማድረግ ነው፡፡ እስከ አሁን ድረስ በከምባታ አላባ ጠምባሮ ሀ/ስብከት፤ በሐዲያና ስልጤ ሀገረ ስብከት እና በአሶሳ ሀገረ ስብከት በአጠቃላይ ከ7000 ሰዎች በላይ በማኅበሩ ሐዋርያዊ አገልግሎት ተጠምቀዋል፡፡
ማኅበረ ቅዱሳንም ይኹን የነገረ መለኰት ምሩቃን ማኅበር በእነ ኀይለ ጊዮርጊስ “ጉባኤ አርድእት” ደባ አይዳከሙም፤ አይፈራርሱም፤ እንደ ተቋም አገልግሎታቸውን ለማሰናከል ቢቻል እንኳ አስተሳሰባቸውን ለማጥፋት እና ቤተ ክርስቲያንን ለመቆጣጠር አይቻልም፡፡
የ”ጉባኤ አርድእት” መሥራች አባላት እነማን ናቸው?
የ”ጉባኤ አርድእት” መሥራች አባላት 25 ሲኾኑ “ተባባሪ አባላት” ናቸው ያሏቸው ደግሞ 180 ያህል ናቸው፡፡ ከመሥራች አባላት ብዙዎቹ የመምሪያ ሓላፊዎች፣ ከሦስቱ የቤተ ክርስቲያኒቱ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማትና ከመንግሥት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የተውጣጡ ናቸው የተባሉ ናቸው፡፡ ከደረሰን የመሥራች አባላት ዝርዝር መረጃ ውስጥ በአሁኑ ወቅት “ጉባኤ አርድእት”ን በሰብሳቢነት የሚመራው አእመረ አሸብር ነው፤ ምክትል ሰብሳቢው ደግሞ በቅርቡ የሽሬ ሀ/ስብከትን በሥራ አስኪያጅነት ሲመሩ ቆይተው÷ በጡረታ በተገለሉት ሊቀ ማእምራን ኀይለ ሥላሴ ዘማርያም ምትክ÷ የካህናት አስተዳደር መምሪያ ሓላፊ የኾኑት ንቡረ እድ ተስፋይ ተወልደ ናቸው፡፡ ንቡረ እድ ተስፋይ በሽሬ ሀ/ስብከት ሥራ አስኪያጅነታቸው ወቅት÷ ከዋልድባ ገዳም ጋራ በተያያዘ ስለሚነሡት ተቃውሞዎች÷ የሀ/ስብከታቸው መዝገብ ቤት ሳያውቅ በግላቸው ለመንግሥት በሚጽፏቸው ደብዳቤዎች ማኅበሩን በፖለቲከኛነት ሲከሱ ቆይተዋል፡፡ የጉባኤው ጸሐፊ ደግሞ ዳንኤል ሰይፈ ሚካኤል ነው፡፡
የአባላት ዝርዝር - በሰነዱ ላይ በተቀመጠው ቅደም ተከተል መሠረት
1. ንቡረ እድ ኤልያስ ኣብርሃ
2. ቆሞስ አባ ሠረቀ ብርሃን ወልደ ሳሙኤል
3. ንቡረ እድ ተስፋይ ተወልደ
4. ርእሰ ደብር መሐሪ ኀይሉ
5. መጋቤ ሥርዐት ዳንኤል ወልደ ገሪማ
6. መጋቤ ብሉይ አእመረ አሸብር
7. ዶ/ር ሐዲስ የሻነህ
8. መ/ር ዳንኤል ሰይፈ ሚካኤል
9. ቀሲስ ሰሎሞን ቶልቻ
10. መ/ር ብርሃኔ ገብረ ጻድቃን (የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ የማታው መርሐ ግብር አስተባባሪ)
11. ያሬድ ክብረት (በአውሮፓ የ”ጉባኤ አርድእት” ሓላፊ)
12. ሊቀ ሥዩማን ኀይለ ጊዮርጊስ ጥላሁን
13. መኰንን ተስፋይ
14. መ/ር ዕንቍ ባሕርይ ተከሥተ
15. ተስፋይ ሃደራ
16. ተወልደ ገብሩ
17. መ/ር መኰንን ወልደ ትንሣኤ
18. መርከብ መኩርያ
19. ተመስገን ዮሐንስ
20. አብርሃም አዱኛ*
21. ብርሃኑ ካሳ
22. ሊቀ ጉባኤ ዳዊት ታደሰ
23. ሊቀ ትጉሃን ገብረ ክርስቶስ ኀይለ ማርያም - የእስክንድር ገብረ ክርስቶስ አባት (ቅ/ሲኖዶስ ጽ/ቤት)
24. መሪጌታ ታምር ገብረ መስቀል
25. መጋቤ ሠናያት አሰፋ ሥዩም - ቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት ናቸው፡፡
* አብርሃም አዱኛ፡- የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ የቀድሞ ምሩቅ እና የነገረ መለኰት ምሩቃን ማኅበር አባል ናቸው፡፡ በአ.አ.ዩ መምህር ሲኾኑ ከ”ጉባኤ አርድእት” መሥራቾች መካከል መኾናቸውን የሰሙ ወይም የተስማሙ ለመኾናቸው ምንጮቹ ጥርጣሬ አላቸው፡፡
ተጨማሪ ዜናዎችን ይከታተሉ
ቸር ወሬ ያሰማን፤
Subscribe to:
Posts (Atom)