Tuesday, 29 May 2012

በዓለ መከር(በዓለ ሠዊት)-በዓለ ኀምሳ - ከዲ.ብርሃኑ አድማስ የፌስቡክ ገጽ ላይ የተወሰደ


በዓለ መከር(በዓለ ሠዊት)-በዓለ ኀምሳ






በብሉይ ኪዳን ፋሲካ ከተከበረ ከሰባት ሱባኤ (ዐርባ አጠኝ ቀናት ካለፉ) በኋላ በሃምሳኛዉ ቀን በዓለ መከር ወይም በዓለ ሠዊት ይከበራል፡፡/ዘጸ 23፣16 ዘኁ 28፣ 26/ ይህ በዓል ከስሙ እንደምንረዳዉ አማኞች ወይም እሥራኤል ከአዝመራቸዉ ቀድሞ የደረሰዉን (ቀዳምያቱን) ይዘዉ ለእግዚአብሔር የሚያቀርቡበትና እርሱንም የሚያመሰግኑበት በዓል ነዉ፡፡ ምሳሌነቱም ከእግዚአብሔር ርቆ ከኖረዉ የሰዉ ዘር የሚጠበቀዉን ቀዳሚ ፍሬ ማመላከት ነበር፡፡ ይህም ማለት እግዚአብሔር ከአዳም ዘር ለርሱ የሚሆን ትዉልድን መፈለጉን ያሳይ ነበር ማለት ነዉ፡፡ በዚሁም መሠረት እርሱ ወደ ምድራችን መጥቶ የሰዉን ዘር ለድኅነት በትምህርትና በተአምራት ሲያዘጋጅ ቆየ፡፡ ይህንንም ሲያስረዳ ‹‹አዝመራዉ እንደ ነጣ ዐይናችሁን አንሱና ተመልከቱ››// በማለት ገልጦታል፡፡ጊዜዉ ሲደርስም ድኅነታችን ይፈጽም ዘንድ ራሱን መሥዋዕት አድርጎ አቀረበ፡፡ ፋሲካችን ክርስቶስ ታረደ፤ /1ኛ ቆሮ 5፣7/ ኃይሉንም በትንሣኤዉ ገለጸ፡፡ ይህ በሆነ በኀምሳኛዉ ቀንም መንፈስ ቅዱስን ሰደደላቸዉ፡፡ በዚህም ዕለት ቀድሞ ይከበር የነበረዉ ምሳሌያዊ በዓል አማናዊነቱን አግኝቶ ‹‹የነጣዉ አዝመራ ›› ሲል ጌታ ከገለጸዉ የሰዉ ዘር ቀዳምያቱ ለጌታ ቀረቡለት፡፡ መጽሐፍ እንደሚል‹‹ ከሰማይ በታች ካሉ ሕዝብ ሁሉ በጸሎት የተጉት›› /ሐዋ 2፣5/ በዚያ ቀዳምያት ሆነዉ ቀረቡ፤ ጸጋ መንፈስ ቅዱስን ሀብት ሰማያዊንም ተቀበሉ፡፡ከእነርሱም በኋላ ሌሎች አምስት ሺሕ ሰዎች ተከታይ ቀዳምያት የሁለተኛዉ መሥዋዕት(ከጠቦቶቹ ጋር የሚቀርበዉ) ሆነዉ እንደ ጥሩ የእህል ቁርባን ለአምላካቸዉ ተሰጡ፡፡ እነዚህ ስምንት ሺህ ነፍሳትም ለአምላካቸዉ የቀረቡ መሥዋዕቶች ስለነበሩ ፈቃደ ሥጋቸዉን ገደሉ፡፡ ስለዚህም ‹‹ ያመኑትም ሕዝብ አንድ ልብ አንዲትም ነፍስ ነበሩአቸዉ፣ ገንዘባቸዉንም ሁሉ በአንድነት ነበረ እንጂ ካለዉ አንድ ነገር ስንኳ የራሱ እንደ ሆነ ማንም አልተናገረም››/ሐዋ 4፣32/ ተብሎ እንደተጻፈ ሁለንተናቸዉ የእግዚአብሔር ሆነ፡፡ አንድ ሰዉ አንድ ነፍስ (አንድ ፈቃድ) መሆን ባልቻለበት በዚህ ዘመን ብዙዎች ሰዎች ‹‹አንድ ልብ አንዲትም ነፍስ ነበሩአቸዉ›› የሚለዉን መረዳትም ሆነ መስማት ምን ያህል ይከብድ ይሆን? በርግጥም ከባድ ነዉ፡፡ ለእነርሱ የተቻለዉ ሁሉም ፈቃደ ሥጋቸዉን ገድለዉ ልቡናቸዉን ለእግዚአብሔር ስለሰጡ በሁሉም ዘንድ ፈቃደ እግዚአብሔር አደረች፤ ስለዚህም በእነርሱ ባደረዉ በአንዱ በእግዚአብሔር አንድ ሆኑ፡፡ ስለዚህም የቤተ ክርስቲያን ቀዳምያቶች እነርሱ ሆኑ፡፡ እነርሱንም ተከትሎ ሌላዉ አዝመራ ተሰበሰበ፡፡ እነ ልድያን ፣ ቆርነሌዎስን፣ የመሰሉ ልቡናቸዉ ለቃለ እግዚአብሔር እና ለእዉነት የተከፈተላቸዉ ሰዎች በየዕለቱ በሐዋርያት አዝመራ ሰብሳቢነት ወደ ወንጌል ጎተራ ይከማቹ ጀመረ፡፡ ‹‹እኔም እናንተ ያልደከማችሁበትን ታጭዱ ዘንድ ሰደድኋችሁ፤ ሌሎች ደከሙ እናንተም በድካማቸው ገባችሁ››? /ዮሐ 4፣38/ ሲል ጌታ የተናገረዉም ይፈጸም ጀመረ፡፡ ‹‹ የሚያምኑትም ከፊት ይልቅ ለጌታ ይጨመሩለት ነበር፤ ወንዶችና ሴቶችም ብዙ ነበሩ››/ሐዋ 5፣14/ ተብሎ እንደተጻፈ የቤተ ክርስቲያን አዝመራ ተከማቸ፡፡ ስለዚህም ከቀዳምያቱ ወደ እህል ቁርባኑ ከዚህም በላይ የመሥዋዕት በግ እየሆኑ ለአምላካቸዉ ቀረቡ፡፡ቤተ ክርስቲያንም በአገልግሎት እየሰፋች በሰማዕትነት እያበበች ቅድስናን እያፈራችና እየሰፋች ሔደች፡፡
የክርስቲያኖች በዓለ ኀምሳም አከባበር በዚሁ ቢቀጥልም እኛ ዘንድ ግን በዚሁ መንፈስ ተጠብቆ አልደረሰም፡፡ ደርሶንማ ቢሆን ኖሮ በዓለ ኀምሳችን እንደዚያ ዘመን ሰዎች ፈቃደ ሥጋችንን ገድለን የመንፈስ ፍሬ አፍርተን ለእግዚአብሔር ቁርባን የሚሆነዉን ቀዳምያት የምናቀርብበት በዓል ሊሆን ይገባዉ ነበር፡፡ ነገር ግን የዛሬይቱ ቤተ ክርስቲያን የምታቀርበዉ እንደ ሐዋርያት ያመኑ ምእመናን ነዉ ወይስ ሌላ ብለን ስንጠይቅ ኅሊናችን የሚነግረንን መልስ እናዉቀዋለን፡፡ የሐዋርያት ታዛዦችና በሥራ የሚላላኳቸዉ በጸጋ የከበሩ ሀብተ ፈዉስና ተአምራት የተሰጣቸዉ አርድእትና ዲያቆናት ነበሩ፡፡ በእኛ ዘመን ባለችዉ በእኛ ቤተ ክርስቲያንስ? እነዚያ ከመንፈስ ቅዱስ ጋር ይማከሩ ነበረ የእኛስ ዘመን መሪዎች ከየትኛዉ መንፈስ ይማከራሉ? የቤተ ክርስቲያኗ መሪዎች በርግጥም እንደ ጥንቱ ሰዉን ለጸጋ መንፈስ ቅዱስ የሚያበቁ አባቶችና መምህራን ናቸዉ ወይስ ለገንዘብ፣ ለክብርና ለዝና እንዲሁም ለሌሎች ጥቅሞች የሚራኮቱ ስግብግቦች? በልሳኖች እስኪናገሩ ድረስ በጸጋ የከበሩ አገልጋዮች ወይስ ሁሉንም ነገር ለገነዘብ ማግኛ ሊያዉሉት የሚሯሯጡ ሲሞኖች? በርገጥ አሁን ለክርስቶስ እያቀረብነዉ ያለዉ ምንድን ነዉ? የመንፈስ ፍሬዎችን ወይስ የሥጋ ፍሬዎችን? ሺዎችን አንድ እናደርጋለን ወይስ ጥቂቶቹንም እንከፋፍላለን? ሌሎች የዘሩትን በእነርሱ ተገብተን እንደ ሐዋርያት እናጭዳለን ወይስ የሰበሰቡትንም እንበትናለን? የሚያቀርቡትና የሚያማክሩትስ እነማንን ነዉ? እንደ ጳዉሎስ ሲላስን ወይስ እንደ ባላቅ በለዓምን? እንደ ሐዋርያት እመቤታችንን ወይስ እንደ አክዓብ ኤልዛቤልን?ፈርዖን በዮሴፍ ናቡከደነጾርም በዳንኤል ሲጠቀሙ እነ ሳዖል ወደ ምዋርተኛዋ ሴት መሔዳቸዉ ለምን ይሆን? ወይ ተገላቢጦሽ!!!በርግጥም ያሳስባል፡፡ ይሁን እንጂ እግዚአብሔር ባወቀ ከኤልያስ እንኳ የተሰወሩ ቅዱሳን እንደነበሩ ሁሉ አሁንም በየ አጥቢያዉ እንደ አልባሌ የሚቆጠሩ እንደ ደንቆሮም የሚታዩ ንጹሐን አገልጋዮች በየገዳሙና በየመናብርቱም አባቶች አይጠፉም፡፡
አብዛኛዉን ስናየዉ ግን በርግጥም ቤተ ክርስቲያን በዓለ ኀምሳን እያከበረች ነዉ ለማለት አይቻልም፡፡ በዓለ ኀምሳ የፍሬ በዓል እንጂ የገለባ በዓል አይደለም፡፡ የአንድነት እንጂ የመለያየት በዓል አይደለም፡፡ የትሕትናና የጸጋ በዓል እንጂ የዐመጻና የኃጢኣት በዓል አይደለም፡፡ ወንጌልና የምሥራች የሚታወጂበት እነጂ ደባና ተንኮል እንደ ዘሃ የሚዘጉበት በዓል አይደለም፡፡ የቅንነትና የጽድቅ በዓል እንጂ የመሠርይነትና የወንጀል በዓል አይደለም፡፡ እዉነቱን እዉነት ሐሰቱን ሐሰት በሉ ተብለናልና እስኪ በእዉነትና በቅንነት ቤታችንን እንመርምረዉ፡፡በከበረዉ መንፈሳዊ ሀብታችን ማኅሌቱ ቢቆምም ኪዳኑ ተደርሶ ቅደሴዉ ተቀድሶ ብንመለስም የጸጋ ፍንጣሪ ቀርቶ የእርቅ ወሬ አይሰማም፡፡ ከቶ ለምን ይሆን ይህ ሁሉ የሐስትና የአስመሳይነት ሕይዎት እንዲህ የነገሰዉ?
ታዲያ እኛ ያቀረብንለት እሸት የምንድን ነዉ? ‹‹የሰባቱንም ሱባዔ በዓል ታደርጋለህ፥ እርሱም የስንዴ መከር በኵራት ነው በዓመቱም ፍጻሜ የመክተቻ በዓል ታደርጋለህ›› /ዘጸ 34፣ 22 / ተብሎ እንደ ተጻፈዉ ስንዴ ነዉ ወይስ ኩርንችት? እኛ እጂ ላይ የሚታየዉ ፍሬ የወይኑ ዘለላ፣ ወይም የገብስ ዛላ ወይም የባቄላ ነዶ ወይስ እሾህና አለብላቢት? ሐዋርያዉ ቅዱስ ጳዉሎስ ‹‹አትሳቱ እግዚአብሔር አይዘበትበትም፤ ሰዉ የሚዘራዉን ሁሉ ያንኑ ደግሞ ያጭዳል›› /ገላ 6፣7/ ይላል፡፡ ስለዚህ እኛም ሁላችን የምናጭደዉ የዘራነዉን ነዉ ማለት ነዉ፡፡ በእዉነት እንዴት ይህን ሁሉ ዐመጻና ጥፋት እናጭዳለን? ይህ የአሁኑ ሌብነትና ዝርፊያ ማንአለብኝነትና ሥርዓት አልበኝነትስ ደግሞ ምን ያፈራልን ይሆን? ለቤተ ክርስቲያን ተቆረቆርን የምንለዉስ ከእዉነት ይሆን ወይስ በሥጋ ገበያ ስለተበለጥን? መጽሐፍ ‹‹ ጥጋቱን እርሻ እረሱ በእሾህም ላይ አትዝሩ›› /ኤር 4፣ 4/ በማለት ቅናታችን ሥጋዊ ሀሳባችንም ምድራዊ እንዳይሆን፤ ይልቁንም በብልጣብልጥነትና በተጥባበ ነገር ፣ቤተ ክርስቲያንን ይጎዳሉ በምንላቸዉም መጥፎ ነገር እንኳ ሳንመኝ እንድነፈጽመዉ ያዝዘናል፡፡ ክፉ በምንላቸዉ ሁሉ ላይ ክፉ የምንመኝ አንዳች መጥፎ ነገር በመፈጸም መልካም የሚመጣ የሚመስለን እንዳንኖርም ያሰጋል፡፡ ሐዋርያዉ ‹‹ በገዛ ሥጋዉ የሚዘራ ከሥጋ መበስበስን ያጭዳል›› /ገላ 6፣8/ እንዳለ መዓቱን እየጨመርን የመከራችንን ዘመን እናረዝመዉ እንደሆን እነጂ ዕርቅና ሰላምን፣ በረከትና ጸጋን ልናገኝ አንችልም፡፡ በተቀመጥንበት ቦታና በሚመስለን ነገር ልናጠቃዉም በምንፈልገዉ ሰዉ ተለያየን እንጂ በክፉ ሀሳብ አልተበላለጥንምም ማለት ነዉ፡፡ እግዚአብሔር ደግሞ ለሰዉ ፊት አያዳላምና መቅሰፍቱን በጋራ ያካፍለናል፡፡
እኛ ምእመናኑም ራሳችንን መጠየቅ ይኖርብናል፡፡ እነዚያ የጥንቶቹ አማኞች ቀዳምያታቸዉ ምን ነበር? መጽሐፍ ስለ እነርሱ ‹‹ በሁሉም ላይ ታላቅ ጸጋ ነበረባቸዉ›› /ሐዋ 4፣33/ ይላል፤ እኛስ? ፍሬያችንስ ከመንፈስ ነዉ ወይስ ከሥጋ? እስኪ ራሳችንን እንመርምረዉ፡፡ በእግዚአብሔር ፊት ይዘነዉ የምንቀርበዉ ምንድን ነዉ? ጥል፣ ክርክር፣ ቁጣ፣ አድመኛነት ወይስ በጎነት፣ የዉሃት ፣ ራስን መግዛት? ወሬና ሐሜት ወይስ ፍቅርና መተሳሰብ? ….. ከቶ ምንድን ነዉ? የመንፍስን ፍሬዎች ወይስ የሥጋን ፍሬዎች? የቤተ ክርስቲያንን ሥራ በእልህና በዐመጻ እሠራለሁ ብሎ መነሣት ለኣማኝ በእሳት እንደ መጫዎት ያለ ነዉ፡፡ በተሳሳተ መንገድና በሥጋዊ ሃሳብ አሸናፊ በመሆን እግዚአብሔርን ለማገልገል መነሣትም አንተ ያሳየኸን መንገድ የተሳሳተ ነዉ ብሎ ጌታን እንደመዉቀስ ያለ ነዉ፡፡ መንፈሳዊ ነገርን በሥጋዊና ግልፍተኛ በሆነ ስሜት ለመሥራት እንደመነሣት ያለም ጎጂ ነገር የለም፡፡ ይህማ ቢቻል ኖሮ ቅዱስ ጴጥሮስ የ ማልኮስን ጆሮ በመቁረጡ አይወቀስም ነበር፡፡ እግዚአብሔርን በጉልበት እናግዝህ ማለት ነዉና እጂግ ጸያፍ ነዉ፡፡ይህን ለሚያደርጉ ‹‹ኃይል የእግዚአብሔር ነዉ እያሉ›› መዘመርም አይቻልም፡፡ ለእኛ ከሚያስፈልገዉ ዉጭ የኃይል እርምጃ የሚያስፈልጋቸዉ ካሉም እግዚአብሔር መንገድ አለዉ፡፡ ሐዋርያዉ ስለ ባለ ሥልጣን ሲጽፍ ‹‹በከንቱ ግን ሰይፍ አይታጠቅምና ክፉ ብታደርግ ፍራ፤ ቁጣዉን ለማሳየት ክፉ አድራጊዉን የሚበቀል የእግዚአብሔር አገልጋይ ነዉና›› /ሮሜ 7፣4/ ያለዉ ይህንኑ ያመለክታል፡፡
እንግዲህስ እግዚአብሔር ይቀበልልን ዘንድ ሰዉነታችን የተቀደሰ አድርገን እናቅርብ፡፡ በእዉነት ሁላችንም ተመሳሳይ ባንሆን ኖሮ ይህ ሁሉ ነገር ሊፈጸም አይችልም ነበር፡፡ ነገር ግን ሁላችንም በዐመፃ ተካከልን፤ በበደልም ተመሳሰልን፤ ስለዚህም ከእግዚአብሔር የሚያስፈርድ ሊገኝ አልቻለምና በሥጋ የዘራነዉን በሥጋ ለማጨድ ተገደድን፡፡ ስለዚህ ፈጥነን እንመለስ፡፡ ልቡናችንን አለስልሰን ፣ ንጹሑን ዘር ቃለ እግዚአብሔርን አብቅለን ለፍሬ እናብቃዉ፡፡ ያን ጊዜ እኛም በዘመነ ሐዋርያት እንደነበሩት ሰዎች ለመንፈስ ቅዱስ ጸጋ የምንቀርብ ቀዳምያት ለሰማዕትነትም የምንመረጥ ባለመቶዎች ለመሆን እንበቃለን፡፡ ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡

Saturday, 26 May 2012


ቅዱስ ሲኖዶስ ‹በቦታው› የተገኘበት ስብሰባ እና መግለጫ


·   የመግለጫው የመጀመሪያ ረቂቅምልአተ ጉባኤው ያልመከረባቸውንዐበይት ጉዳዮች ያካተተ እንደነበርተጠቁሟል፤ የዋልድባ እና የነ አባፋኑኤል የሐሰት ስኬት በሥርዋጽገብቶበት ነበር
·     አባ ጳውሎስ ምልአተ ጉባኤው ስለማኅበረ ቅዱሳን ውሳኔ ባስተላለፈበትቃለ ጉባኤ ላይ አልፈርምምብለዋል፤ ስለማኅበሩ በመግለጫው ላይ የሰፈረውን አንቀጽም አላነብም” የሚል አተካራ ውስጥገብተው ነበር
·     ብፁዕ አቡነ ሳሙኤልን ከኮሚሽኑ ሊቀ ጳጳስነት አንሥቶ ወደ ጉጂና ቦረና ሊበን ዞኖች ሀ/ስብከትለማዛወር በፓትርያ የቀረበው ሐሳብ ውድቅ ተደርጎ ብፁዕ አቡነ ገብርኤል ደርበውእንዲመሩ ተወስኗል
·      አገር ዓቀፍ የሰንበት ት/ቤቶች አንድነት መሥራች ጉባኤ ከግንቦት 26 - 27 ቀን 2004 ዓ.ም በአዲስ አበባ ይካሄዳል፡፡

 (ደጀ ሰላም፤ ግንቦት 17/2004 ዓ.ም፤ May 27/ 2012/ READ THIS ARTICLE IN PDF)፦ የርክበ ካህናት ቅዱስሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ 2004 . መደበኛ ስብሰባ ከትናንት በስቲያ፣ ግንቦት 15 ቀን 2004 ዓ.ም ከቀትር በኋላ ባለዐሥር ነጥብ የአቋም መግለጫ በማውጣት ተጠናቋል፡፡ ሚያዝያ 30 ቀን በመክፈቻ ጸሎት ተጀምሮ ለ16 ቀናት የዘለቀው ምልአተ ጉባኤው በመጨረሻው ቀን በአንድ በኩል የቅዱስ ሲኖዶሱ ወሳኝ የበላይነት የተመሰከረበት፣ በሌላ በኩል ደግሞ ፓትርያርክ አቡነ ጳውሎስ የቅዱስ ሲኖዶሱን ማእከላዊ አሠራርና ውሳኔ በልብ ይኹን በተግባር ለመቀበል ገና እየተቸገሩ መኾኑ የተጋለጠበት ኾኖ መዋሉ ተዘግቧል፡፡

የስብሰባው ምንጮች እንደሚያስረዱት በዕለቱ ጋዜጣዊ መግለጫውን ለመጥራት ታቅዶ የነበረው ከረፋዱ 4፡00 ላይ የነበረ ቢኾንም በኋላ ወደ 10፡00 ይህም ቆይቶ ወደ 11፡30 እንዲሸጋሸግ ተደርጓል ስብሰባው ሲካሄድበት ወደከረመው የመንበረ ፓትርያርኩ ቤተ መጻሕፍት ወመዘክር ቀድመው የደረሱ ጋዜጠኞችም ቢያንስ ከአንድ ሰዓት በላይ ለመጠበቅ ተገደዋል፡፡ በመጨረሻ በቅዱስ ሲኖዶሱ ዋና ጸሐፊ ብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤል ግብዣ ወደ አዳራሹ የዘለቁት ጋዜጠኞች የጠበቃቸው ትዕይንት ከጠዋት አንሥቶ በቤቱ የቆየውን ውጥረት የሚያሳብቅ ነበር፡፡

ጋዜጠኞቹ ወደ አዳራሹ ግር ብለው ገብተው የሥራ መሣሪያዎቻቸውን ቦታ ቦታ አስያዙ የመግለጫው አንድ ገጽ ወረቀት በእያንዳንዳቸው የምልአተ ጉባኤው አባላት ፊት ተዘርግቷል፡፡ ፓትርያርኩን ጨምሮ ሁሉም አባቶች የእጅ መስቀላቸውን በቀኝ እጃቸው እንደ ጨበጡ በጠረጴዛው ላይ አኑረው በተጠንቀቅ ተቀምጠዋል፡፡ የፓትርያርኩ ልዩ ጽ/ቤት የፕሬስ ጉዳዮች ሓላፊ አቶ ስታሊን ገብረ ሥላሴ ከጋዜጣዊ መግለጫው ቀደም ብለው የወጡ ብፁዓን አባቶችን ስምና አህጉረ ስብከት የሚገልጹ ወረቀቶችን ከጉባኤው ጠረጴዛ ላይ አነሣሱ፡፡ ከዚህ በኋላ በአዳራሹ የሰፈነው ድባብ ጫታ (deafening silence) ሊባል የሚችል ነበር፡፡ ፓትርያርክ አቡነ ጳውሎስ ከአሁን አሁን መግለጫውን በንባብ ማሰማት ይጀምራሉ ተብሎ ሲጠበቅ እንዲያው ወረቀቱን አተኩረው እየተመለከቱ ጫ÷ እርጭ÷ ድምቡጭ አሉ፤ ገረገሩ፡፡

መቼም ግድ ነውና ከቆይታ በኋላ እንደምንም ማንበብ ጀመሩ፤ አሁን ሁሉም አባቶች በየአንፃራቸው የተቀመጠውን ወረቀት ይዘው የርእሰ መንበሩን ንባብ በጥታ÷ በርጋታ መከታተል ጀመሩ፤ በተለይ የብፁዕ ዋና ጸሐፊው ደግሞ ለየት ይላል፡፡ “ፓትርያርኩ መግለጫውን ለማንበብ ባይፈቅዱ ወይም አንዱንም አንቀጽ ከመነገር ቢያስቀሩ በቀጥታ ብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤል ጣልቃ ገብተው ማንበብ እንዲጀምሩ አቋም ተወስዶ ነበር” ይላሉ ከመግለጫው አስቀድሞ በአቡነ ጳውሎስና በብዙኀኑ አባላት መካከል ተፈጥሮ የነበረውን ውዝግብ የሚያስረዱ የስብሰባው ምንጮች፡፡

በዕለቱ ጠዋት በነበረው የምልአተ ጉባኤው ውሎ በቀረቡ ጉዳዮች ሁሉ አቡነ ጳውሎስ የቅዱስ ሲኖዶሱን የበላይ አመራርነት እየተፈታተኑም ቢኾን ለመቀበል የተገደዱበት፣ በተወሰኑ ጉዳዮች ደግሞ አሻፈረኝ እንዳሉ የቀሩበት ነበር፡፡ ለአብነት ያህል በየስብሰባው መሀል እንደሚደረገው በአጀንዳ ተ.ቁ (15) በተመለከተው “ስለ ሰንበት ት/ቤቶች ማ/መምሪያ እና ማኅበረ ቅዱሳን ጉዳይ” ከአንድ ቀን በፊት የተደረሰበትን ውሳኔ በሚገልጸው ቃለ ጉባኤ ላይ እንዲፈርሙበት ሲጠየቁ “አልፈርምም” ብለዋል፡፡ በዚህ የተነሣ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት በኹኔታው እስኪሰላቹ ድረስ ምልልስ የተደረገ ቢኾንም ፓትርያርኩ በእንቢታቸው በመጽናታቸው “ምልአተ ጉባኤው እስከ ወሰነ ድረስ እርስዎ ባለመፈረምዎ የሚመጣ ለውጥ የለም” በሚል ወደ ሌላ ጉዳይ ታልፏል፡፡

በሌላ በኩል አቡነ ጳውሎስ ዝውውር በሚል የልማትና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ሳሙኤል ከኮሚሽኑ ተነሥተው ወደ ጉጂና ቦረና ሊበን ዞኖች ሀገረ ስብከት እንዲዛወሩ፣ ለዚህም የሚፈልጉትን መኪና ይዘው እንዲሄዱ ይጠይቃሉ፡፡ ጥያቄውን ፓትርያርኩ ቀደም ሲል ከ‹ታማኞቻቸው› ጋራ መክረው በኋላ ለብፁዕ ዋና ጸሐፊውና ብፁዕ ዋና ሥራ አስኪያጁ ያስታወቁትና ተቀባይነት ያጣ እንደ ነበር ነው የሚነገረው፡፡በመጀመሪያ ወደ ጋምቤላ በኋላ ደግሞ ወደ ጉጂ ቦረናና ሊበን ዞኖች ሀገረ ስብከት የተቀየረውንና ከመደበኛ ስብሰባው ሁለት ሳምንት በፊት ጀምሮ ሲወራ የቆየውን የብፁዕ አቡነ ሳሙኤል ይነሡልኝ - ይዛወሩልኝ ጥያቄ ግን የምልአተ ጉባኤው አባላት ወዲያው ነበር የተቃወሙት፡፡

በርግጥ የጉጂ ቦረና እና ሊበን ዞኖች ሀ/ስብከት ከመጋቢት ወር 2003 ዓ.ም ጀምሮ ያለ ሥራ አስኪያጅ፣ ከጥቅምት ወር 2004 ዓ.ም ወዲህ ደግሞ ያለ ሊቀ ጳጳስ እንዳለ ይታወቃል፡፡ ምእመኑ የተቀበላቸው እና ከየዞኖቹ መንግሥታዊ አካላት ጋራ ተግባብተው በመሥራት የሚታወቁት ሥራ አስኪያጁ መጋቤ ጥበባት ሲያምር ተክለ ማርያም መዋቅሩን ባልጠበቀ ውሳኔ ከብፁዕ ሊቀ ጳጳሱ አቡነ ዮሴፍ ስምምነት ውጭ እንዲነሡ በመደረጋቸው፣ ከቀድሞው ሊቀ ጳጳስ ጋራ በተያያዘ ከሻኪሶ ቅድስት ማርያም ተወስዶ አለመመለሱ ከተነገረለት ብር 40,000 እና ለሀገረ ስብከቱ የካህናት ማሠልጠኛ ማሠርያ ከሀገረ ማርያም ወረዳ ምእመናን ተስብስቦ ርክክብ ሳይደረግበት ቀልጦ ከቀረው ብር 32,000 ጋራ በተገናኘ ሀገረ ስብከቱ ሰላሙ እንደታወከም የተዘገበ ነው፡፡

በዚህም በጥቅምቱ ቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ በተዛወሩት ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ ምትክ ብፁዕ አቡነ ዮሴፍ ከባሌ ሀገረ ስብከት ጋራ ደርበው እንዲመሩት ተወስኖ ነበር፡፡ ይኹንና መንበረ ጵጵስናው ባሌ በመኾኑ ከቦረና ወደ ባሌ ለመሄድ ቀናትን የሚፈጅ፣ አገልጋዩንና አብያተ ክርስቲያኒቱን ለወጪ የሚዳርግ፣ በሚያነሣው አስተዳደራዊ ጥያቄ ሳቢያ እስርና እንግልትን ጨምሮ በብዙ ችግሮች ተከቦ አባታዊ ቡራኬና ከፍተኛ ክትትል ለሚሻው የጠረፍ አገር ምእመንም አስቸጋሪ በመኾኑ ራሱን ችሎ ሊቀ ጳጳስ እንዲመደብለት÷ ይህም ካልኾነ ከመልክአ ምድራዊ አመቺነትና ከአስተዳደር አኳያ ከሲዳማ (ሐዋሳ) ሀገረ ስብከት ጋራ ተደርቦ በክፍሉ ሊቀ ጳጳስ እየተመራ እንዲቆይ ከሊበን፣ አዶላ፣ አዶ ሻኪሶ፣ ሀገረ ማርያም እና ያቤሎ ወረዳዎች የተውጣጡ የምእመኑ ተወካዮች ከሰኔ ወር 2003 ዓ.ም ጀምሮ ጥያቄ ሲያቀርቡ እንደ ነበር ይታወሳል፡፡

ከዚህ አኳያ ፓትርያርክ አቡነ ጳውሎስ ብፁዕ አቡነ ሳሙኤል ከኮሚሽኑ ተነሥተው ወደ ሀገረ ስብከቱ ተዛውረው እንዲሄዱ መጠየቃቸው በራሱ ችግር የሌለበት ቢኾንም መነሻው ግን ይህ አልነበረም፤ የይነሡልኝ - ይዛወሩልኝ ውስጠ ዘ ብቻ ከአዲስ አበባ ይራቁልኝ ዐይነት ነበር ይላሉ አስተያየት ሰጪዎች፡፡ የዝውውሩን ጥያቄ የተቃወሙት ብፁዕ አቡነ ፊልጶስ በበኩላቸው ከጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ዋና ሥራ አስኪያጅነት ጋራ የቤቶች እና ሕንጻዎች አስተዳደር ድርጅት ቦርድ ሰብሳቢነቱ ስለተደራረበባቸው ብፁዕ አቡነ ሳሙኤል የኮሚሽኑን ሊቀ ጵጵስና እንደያዙ እንዲያግዟቸው ጠይቀው ነበር፡፡

ከቤቱ የገጠማቸውን ተቃውሞ አጥብቀው የተከላከሉት አቡነ ጳውሎስ÷ በመጨረሻ ብፁዕ አቡነ ገብርኤል አሁን ከያዙት የሲዳማ ሀገረ ስብከት ጋራ የጉጂ ቦረናና ሊበን ዞኖችን ሀገረ ስብከት ደርበው እንዲመሩ ምልአተ ጉባኤው የወሰነውን ለመቀበል ተገደዋል፡፡ በዚህም የፓትርያርኩ ጣልቃ ገብነት እስከሌለ ድረስ ከምእመኑ የተወከሉ የሀገር ሽማግሌዎች የጠየቁትን ያህል ባይሆንም እፎይታ እንደሚያገኙበት ተስፋ ተደርጓል፡፡ እዚህ ላይ ሳይጠቀስ የማይታለፈው÷ ቤቱ ብፁዕነታቸው ሀገረ ስብከቱ ካለው አንጻራዊ ቅርበት አኳያ ደርበው እንዲመሩ ሲጠይቅ ፓትርያርኩ ብፁዕ አቡነ ገብርኤልን÷ “ቦረና ብዙ ችግር አለ፤ እርሳቸው ማኅበረ ቅዱሳን ናቸው”በሚል መክሰሳቸው ነው፡፡ ይገርማል፤ መፍቀሬ ፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ብሎጎች ማኅበረ ቅዱሳንን በችግር ፈጣሪነት በመክሰስ አንድ ዐይነት ሥዕል ለመፍጠር ከሚነዙት አሉባልታ ጋራ አንድና ያው የኾነው ንግግራቸው በተለይ በዚህ መደበኛ ስብሰባ የተደጋገመባቸውና የበቃቸው የሚመስሉት ብፁዕ አቡነ ገብርኤልም “አዎ! ማኅበረ ቅዱሳን ነኝ፤ አላፍርበትም” ሲሉ ቀጥተኛ ምላሽ እንደሰጧቸው ተሰምቷል፡፡

የኾነው ኾኖ ብፁዕ አቡነ ሳሙኤል በነበሩበት የልማትና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን ይቀጥላሉ፡፡ ይልቁንስ በዋሽንግተን ዲሲ ሀገረ ስብከት ቀኖና ቤተ ክርስቲያንን ጠብቀው፣ መዋቅርን (ቃለ ዐዋዲን) አክብረው ለቤተ ክርስቲያን አሐቲነት ባለመሥራታቸው ብርቱ አቤቱታ የተነሣባቸው የብፁዕ አቡነ ፋኑኤል ነገር በምልአተ ጉባኤው ቀደምት ውሎዎች የተነካካ ቢኾንም አንዳች ውሳኔ ሳያርፍበት በቋሚ ሲኖዶሱ እና በመንበረ ፓትርያርኩ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት በኩል እንዲታይ ነው በይደር የተተወው፡፡ አቡነ ፋኑኤል የሀገረ ስብከቱን ጸሐፊ ቀሲስ ዶ/ር መስፍን ተገኝን ክህነት አላግባብ በመያዝ የፈጸሙት ግዙፍ ስሕተትም በዚሁ መንገድ ‹እንደሚፈታ› (እልባት እንደሚያገኝ) ተስፋ ተደርጓል፡፡

ቅዱስ ሲኖዶስ የማኅበረ ቅዱሳንን መተዳደርያ ደንብ የማኅበሩ አገልግሎት ከደረሰበት ደረጃና ሊያሠራው በሚችልበት አግባብ ተጠንቶ እንዲሻሻል፣ ይኸው ርምጃም ከቃለ ዐዋዲው ማሻሻያ ጋራ ተጣጥሞ ለጥቅምት ቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ እንዲቀርብ ወስኗል፤ እስከዚያው ድረስ የማኅበሩ ተጠሪነት ለብፁዕ ዋና ሥራ አስኪያጁ ኾኖ ከብፁዕነታቸው አመራር እየተቀበለ እንዲሠራ ትእዛዝ ሰጥቷል፡፡ ይህ የመዋቅራዊ ተጠሪነት ለውጥ ከማኅበሩ አገልገሎት ማደግና መስፋፋት ጋራ ተያይዞ በአንዳንድ የማኅበሩ አመራር አባላት ሳይቀር ሲብላላ የነበረ ቢኾንም የቅርብ መነሻ የኾነው ግን ከመምሪያው ሓላፊዎች ጋራ በተለይም ካለፉት ሰባት ዓመታት ወዲህ ተፈጥሮ የቆየው ውዝግብ ሊቋጭ ባለመቻሉ፤ ከውዝግቡና ሰንበት ት/ቤቶች ከደረሱበት ደረጃ ጋራ በተያያዘ የአመራር ብቃታቸው አጠራጣሪ ኾኖ የተገኙት የመምሪያው ምክትል ዋና ሓላፊና ጸሐፊ እንዲነሡ የመምሪያው ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ቀሌምንጦስ ቢጠይቁም ፓትርያርኩ ፈቃደኛ ኾነው ባለመገኘታቸው መኾኑ ተመልክቷል፡፡

ይህን ተከትሎ ብፁዕ አቡነ ገሪማ የክስም የጥያቄም መንፈስ ባለው የማኅበሩ መተዳደርያ ደንብ ትችታቸው ማኅበሩ ከማደራጃ መምሪያው ወጥቶ ለብፁዕ ዋና ሥራ አስኪያጁ ተጠሪ እንዲኾን ያቀረቡትን ሐሳብ በመያዝ ምልአተ ጉባኤው በሙሉ ልብ የተቀበለውና ያስተላለፈው ውሳኔ በመምሪያው ሓላፊዎችና በማኅበሩ መካከል ተፈጥሮ የቆየው ውዝግብ ማሳረጊያ መስሎ ታይቷል፡፡ ይህ ታሪካዊ ውሳኔ ምልአተ ጉባኤው ከአንድ ቀን በፊት ስለ ውዝግቡ ቀርበው እንዲያስረዱ የጠራቸውና በሕገ ወጥ መንገድ ዋና ሓላፊ የኾኑት መ/ር ዕንቍ ባሕርይ ተከሥተ፣ የቀድሞው ዋና ሓላፊ መልአከ ጽዮን አባ ኅሩይ ወንድይፍራውና የማኅበረ ቅዱሳን አመራሮች የመቅረባቸውን አስፈላጊነት አስቀርቶታል ተብሏል፡፡

ለራሱ ያህል የሚበቃ የአቋቋም ሞያ ያለው መ/ር ዕንቍ ባሕርይ በመምሪያው ዋና ሓላፊነት ይቆያል፡፡ መቼም መ/ር ዕንቍ ባሕርይ መምሪያው ለ20 ዓመት የቆየበት (የደከመበት?) ኾኖ ሳለ፣ መምሪያውም ከአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የሰንበት ት/ቤቶች አንድነት አመራር ጋራ በመኾን ከ200 ወጣቶች በላይ ለሚገኙበት ታላቅ አገር ዓቀፍ የሰንበት ት/ቤቶች አንድነት መሥራች ጉባኤ እየተዘጋጀ ባለበት ወቅት [ከግንቦት 26 - 27 ቀን 2004 ዓ.ም በአዲስ አበባ የሚካሄደው ይህ አገር ዓቀፍ መድረክ በይፋ ከሚታወቁት አጀንዳዎቹ ውጭ ለግል ጥላቻዎች ማስተጋቢያ እንዳይኾን ስጋቱ አለ] እንደ ኀይለ ጊዮርጊስ ጥላሁን ካሉ ዦቢራዎች ጋራ ባስፈጸመው የሽፍትነት መታዘዝ ያገኘው ሥልጣን ነውና እንደ ባህሉ ‹ሹመት ያዳብር› አንለውም፡፡

ለዚህ ዘገባ የቅዱስ ሲኖዶሱ የመጨረሻ ጉዳይ የሚኾነው በመግለጫው ዝግጅት ሂደት የታየው ‹ድራማ› ነው፡፡ የስብሰባው ምንጮች እንደተናገሩት ጠዋት ላይ በውይይት መሀል ተዘጋጅቶ የቀረበው የጋዜጣዊ መግለጫው ይዘት በአንድ በኩል÷ በ16ቱ ቀናት ውስጥ ምልአተ ጉባኤው ያልመከረባቸውንና ውሳኔ ያላሳለፈባቸውን አንገብጋቢ አጀንዳዎች አቋም እንደተያዘባቸው አስመስሎ ያቀረበ፤ በሌላ በኩል ደግሞ÷ በምልአተ ጉባኤው ተመክሮባቸው ውሳኔ የተላለፈባቸውን አጀንዳዎች የውሳኔ ይዘት አሳስቶ የሚያቀርብ ነበር፡፡

ለአስረጅ ያህል፡- በወልቃይት ስኳር ልማት ፕሮጀክት ሳቢያ በዋልድባ ገዳም ህልውናና ክብር ላይ የተነሣውን ስጋት ምልአተ ጉባኤው በአጀንዳ ይዞ መነጋገር ሲገባው አልተነጋገረበትም፡፡ ይኹንና ጠዋት ተረቅቆ በቀረበው መግለጫ ላይ ፕሮጀክቱን የሚቃወሙት የፖቲካ ዓላማ ያላቸው ኀይሎች እንደኾኑና ቤተ ክርስቲያን ግን ልማቱን እንደምትደግፍ የሚናገር አንቀጽ እንደነበረው ተገልጧል፡፡ “የፖቲካ ዓላማ ያላቸው”የሚለው ክስ ይቆየንና መቼም ጥሩና ትክክለኛ ነገርን የሚጠላ ቢኖር ዲያብሎስ ነውና ቤተ ክርስቲያን ጥሩና ትክክለኛ ልማትን አትቃወምም፤ አይገባትምም፡፡ መንግሥትም አዘውትሮ እንደሚናገረው ትክክለኛ ልማት ፍትሐዊና ተደራሽ ነው፡፡ አዎ፣ ይህ የታመነ ነው እንላለን፤ ነገር ግን በተለይ ባለንበት ዘመን የልማት አስተሳሰብ፣ ዕቅድና ትግበራ ትክክለኛነት ተደራሽነቱና ፍትሐዊነቱ ብቻ አይደለም፤ አግባብነቱስ የሚል ጥያቄም በኾነ ደረጃም መነሣት ይኖርበታል፡፡

በአጀንዳ ተ.ቁ (5) ስለ ማኅበራት በተመለከተው ጉዳይ ምልአተ ጉባኤው የወሰነው÷ የቀረበው የመተዳደርያ ደንብ ዝግጅት ሰነድ ጥናት ወይም ትችት እንጂ የሕግ አቀራረብ እንደሌለውና በቀረበበት መልኩ ሊጸድቅ እንደማይችል፤ በውስጠ ዘ መልካም አገልግሎት እየሰጡ የሚገኙ ማኅበራትን የማድቀቅና የማፈራረስ ተልእኮ እንዳለው፤ ይህም በመኾኑ ብፁዓን አባቶች፣ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያንና የሕግ ዐዋቂዎች በእውነትም ፈር ሊይዝ የሚገባውን የማኅበራቱን ብዛት የተገነዘበና ሊያሠራቸው የሚችል ሕግ አርቅቀው እንዲያቀርቡ ነበር፡፡ ይኹንና በጠዋቱ የመግለጫ ረቂቅ የቀረበው ግን ክፉኛ በተተቸው የዜና ቤተ ክርስቲያን ርእሰ አንቀጽ እንደተገለጸው፣ ጥናት ተብዬውም እንደሚለው ቅዱስ ሲኖዶሱ “ማኅበራት አያስፈልጉም” ብሎ እንደ ወሰነ አስመስሎ ያቀረበ ነበር፡፡

ቅዱስ ሲኖዶስ አቡነ ፋኑኤል የስቴት (ወረዳ) ቤተ ክህነቶችን በዋሽንግተን ዲሲና ካሊፎርኒያ አህጉረ ስብከት ማቋቋማቸውን በውል አንሥቶ በመነጋገር በአንድነት ያሳለፈው የውሳኔ ሐሳብ አልነበረም፡፡ በመኾኑም ይኸው ከምልአተ ጉባኤው አጀንዳዎችና ውሳኔዎች ውጭ አቋሞችን ይዞ የመጣው መግለጫ በቀላሉ ነበር ውድቅ የተደረገው ፡፡ ዋልድባን አስመልክቶ በቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ ዓመታዊ ሪፖርት ተካትቶ የቀረበላቸው ነገር እንደሌለና እንዳልተነጋገሩበት ያስታወሱት የምልአተ ጉባኤው አባላት ባልተነጋገሩበት ጉዳይ መግለጫ ሊያወጡ እንደማይችሉ ነበር ያስቀመጡት፡፡ በማኅበራት ጉዳይ “ማኅበራት አያስፈልጉም” የሚል ውሳኔ እንዳልተላለፈና ሰነዱ ዳግመኛ ተጠንቶ እንዲቀርብ ማዘዛቸውን ተናግረዋል፡፡ ለድጋፍ ሸመታ የተሰነቀረው የአቡነ ፋኑኤል ‹የወሬ ፍሬ› “ኧረ እንዲያውስ ምን ተሠርቶ? ደብረ በጥብጥ ከመኾን በቀር” በሚል ተዘብቶበታል፡፡

በቀዳሚው ዜና ዘገባችን ላይ እንደገለጽነውና በርካታ ደጀ ሰላማውያንም እንዳመለከቱት ጋዜጣዊ መግለጫው የተሰጠበት ቀን ግንቦት 15 ኾኖ ሳለ በጽሑፍ በቀረበው መግለጫ መጨረሻ ላይ ግንቦት 10 የመባሉ ስሕተት መንሥኤ ይኸው ከምልአተ ጉባኤ አጀንዳዎችና ውሳኔዎች ውጭ ቀደም ብሎ ተዘጋጅቶ የቆየ ሐሰተኛ መግለጫ በፈጠረው ማምታት የተፈጠረ ሊኾን ይችላል፡፡

ስለኾነም በቤቱ ለውሳኔው የሚታመንለት ወዳጅ ያጣው ቅዱስ ሲኖዶሱ ደኀራዊውና ይፋዊውን መግለጫ አርቅቀው እንዲያቀርቡ ቀደም ሲል በመናፍቅነት ያወገዛቸውን ድርጅቶችና ግለሰቦች ውሳኔ በጽሑፍ እንዲያዘጋጁ ሠይሟቸው የነበሩትን አራት አባቶች ዳግመኛ ሠይሟል፡፡ እነርሱም “ከ20 ዓመት በኋላ ቅዱስ ሲኖዶሱን በቦታው ለመገኘት ያበቃ ነው” የተባለለትን ጋዜጣዊ መግለጫ አርቅቆ አቅርቧል፤ ቅዱስ ሲኖዶሱም ክራሞቱን የሚመስል ጋዜጣዊ መግለጫ እንዲያነቡ ለፓትርያርኩ ይሰጣቸዋል፤ ቅዱስነታቸውም የመግለጫዋን አንዲት አንቀጽ ካልገደፍኹ ‹በመቃብሬ ላይ› ይላሉ፡፡

በየጉዳዩ ልምምጥ የበቃው ምልአተ ጉባኤውም በመነጋገርያ አጀንዳ ማጽደቅ ምልልስ ወቅት እንዳደረገው የቅዱስ ሲኖዶሱ ዋና ጸሐፊ ብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤል በውጭ በትንሹ ከአንድ ሰዓት በላይ የጠበቁት ጋዜጠኞችን እንዲያስገቡና ራሳቸው ብፁዕነታቸው እንዲያነቡ ይስማማሉ፡፡ ቅዱስ ሲኖዶሱ ቍርጥ ውሳኔ ባደረገ ጊዜ ሁሉ ከአቋማቸው ሸተት የሚሉት ፓትርያርክ አቡነ ጳውሎስም “እገድፋታለኹ እንጂ አላነባትም” ያሏትን ‹አንቀጸ ማኅበረ ቅዱሳን› ቀጸሏት፡፡ ንባቡ ግድፈተ አንቀጽ ቢኖርበት የመጣፍ መምሩ ብፁዕ አባ ሕዝቅኤል ከታጎለበት ለማቃናት ተዘጋጅተው ይጠባበቁ ነበር፡፡

ቅዱስነታቸውን እዚህ ውሳኔ ላይ ለማድረስ በተደረገው የተራዘመ ምልልስ የተዳከሙ፣ የተቆጡም አንዳንድ ብፁዓን አባቶች ከጋዜጣዊ መግለጫው በፊት ወጥተው ሲሄዱ ታይተዋል፤ ጋዜጣዊ መግለጫውም እንዳለቀ ለመቆየት የታገሡት በመጠን ነበሩ፡፡ ርእሰ መንበሩ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ንባባቸውን እንደ ጨረሱ የፕሬስ ጉዳዮች ሓላፊያቸው አቶ ስታሊን ገብረ ሥላሴ ወደ መነጋገርያው ቀርበው መርሐ ግብሩ ማብቃቱን በመናገር ጋዜጠኞችን አሰናበተዋል፡፡

ምልአተ ጉባኤው በመጨረሻ በሕገ ቤተ ክርስቲያን መሠረት በሁለት ዙሮች ለቀጣይ ስድስት ወራት የቋሚ ሲኖዶስ አባላት የሚኾኑ አራት አራት ብፁዓን አባቶችን መርጧል፡፡ በዚህም መሠረት እስከ መጪው ነሐሴ ወር መጨረሻ ድረስ አቡነ ገሪማ፣ አቡነ ሉቃስ፣ አቡነ ሰላማ እና አቡነ ኤርሚያስ የቋሚ ሲኖዶስ አባላት ኾነው የምልአተ ጉባኤውን ውሳኔዎች እንዲያስፈጽሙና ሌሎችም የቅዱስ ሲኖዶሱን ሥራዎች እንዲያከናውኑ መርጧቸዋል፡፡

የዘንድሮው የርክበ ካህናት ቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ በታሪክ የሚታወሱ ክዋኔዎች የታዩበትና ደማቅ ውሳኔዎችም የተላለፉበት መኾኑ አያጠያይቅም፡፡ ከውሳኔዎቹ ውስጥ የሚበዙት ደጀ ሰላማውያንእግዚአብሔርን ያመሰገኑበት፣ ለብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ያላቸውን አክብሮትና ድጋፍ የገለጹበት ማኅበረ ቅዱሳንን አስመልክቶ የተላለፈው ውሳኔ ነው፡፡ መፍቀሬ ፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ብሎጎች ከዛሬ ነገ ይፈርሳል እያሉ ሲያሟርቱበት እና እንደ ኀይለ ጊዮርጊስ ጥላሁን ያሉት ምንደኞች በየመሸታ ቤቱ ሳይቀር እየተምነሸነሹ ጮቤ የረገጡበት ሟርት ግን አልሠራም፡፡ በምትኩ በፈረንጆቹ አባባል በመጨረሻ “በጠላቶቹ መቃብር ላይ የሣቀው”ማኅበሩ ነው፡፡

በብዙዎች ግንዛቤ የመዋቅራዊ ተጠሪነት ለውጥ ውሳኔው ማኅበሩ እንደ ተቋም ከነበረበት ቦታ አኳያ ከጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ከፍተኛ አካላት አንዱ የሚያደርገውና መዋቅራዊ ዕድገትን የሚያቀዳጀው ነው፤ መዋቅራዊ ዕድገቱ ቀና መነሻዎች ካሉት ከፍተኛ ሓላፊነትንም ጭምር ይዞ የሚመጣና ማኅበሩም ለዚያ የሚመጥን አቅም እንዲገነባ የሚያስገድደው ነውና፡፡ ውሳኔው ማኅበሩን ለዚህ ዐይነቱ በረከት የማብቃት መግፍኤ ያለው መኾኑን በሚጠራጠሩ ወገኖች ዘንድ ደግሞ የመዋቅራዊ ተጠሪነት ለውጥ ውሳኔው የማኅበሩን መሠረታዊ ዓላማዎች በተለይም የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ግቢ ጉባኤያት አገልግሎቱንና ቀጣይ ግንኙነቱን ጥያቄ ውስጥ ያስገባል፤ በአባላቱ መካከል የዘወትር አጀንዳ የኾነው በድርጅታዊ ቁመናው ተነጥሎ የመቅረት ስጋትን ያባብሳል፡፡ የመዋቅራዊ ተጠሪነት ለውጥ ውሳኔው ማኅበሩን ከእነ ዕንቍ ባሕርይ የሁልጊዜ ‹አበባዬ› አተካራ ለመገላገል ብቻ የተወሰደ አድርገው ያዩትም አልጠፉም፡፡

ብቻ አንድ ነገር ግልጽ ነው - የውሳኔውን የትመጣና ምንነት በውል ለሚረዱት የማኅበሩ ስትራቴጅስቶች ውሳኔው አሁን በቅዱስ ሲኖዶስ ሥልጣን ደረጃ ግዘፍ ነስቶ ከመውጣቱ በፊት÷ በማኅበሩ የተከታታይ ስትራቴጅያዊ ዕቅድ ዝግጅቶች ሂደት ከማኅበሩ አገልግሎት ማደግና ከአገልግሎት አድማሱ መስፋፋት የተነሣ በተልእኮ መፈጸሚያ ሥልጣን ወይም ግዴታዎች ትንተና (Mandate analysis) ወቅት በተደጋጋሚ እንደሚነሣ ለሚወራው ክርክር አንድ ዐይነት ምላሽ ሊኾን እንደሚችል፡፡ የማኅበሩ ተምኔት በብርቱ ለሚያስጨንቃቸው ትጉህና ብዙኀን አባላቱ ግን ውሳኔው ገና የሐሳቦች ግብግብ መካሄድ የጀመረበትን የክርክር ምዕራፍ ያበሠረ ኾኗል፡፡

የሚመለከተው የማኅበሩ አመራር በቀጣይ አራትና አምስት የመተዳደርያ ደንቡ ማሻሻያ ወራት ከአባላቱም ይኹን ከአገልግሎት አጋሮቹ የሚመነጩ ወርቃማ ሐሳቦችን፣ ጥናታዊ መነሻዎችን የሚያቍትባቸውን ግልጽ መድረኮች በየደረጃው በቶሎ ቢያመቻች ፍጻሜው ለቤተ ክርስቲያን የአስተዳደር መዋቅር መጠናከርና ለሐዋርያዊ አገልግሎቷ መስፋፋት የሚተርፍ፣ ለአገራችን ሰላምና ልማት የሚበጅ ድምር ውጤት ያለው ለውጥ እንደሚያመጣ ደጀ ሰላም በጽኑዕ ታምናለች፡፡

በሌላ በኩል ቅዱስ ሲኖዶስ በዘንድሮው የርክበ ካህናት ምልአተ ጉባኤው ለሃይማኖታዊ ጉዳይ ሰፊ ትኩረት መስጠቱ በቀጣይም በመሰል ወቅታዊ ጉዳዮች በዚህ ሊገፋ እንደሚችል አቅጣጫ የሰጠበት ነው፡፡ በዚህ መደበኛ ስብሰባ ፍጹም ውግዘት የተላለፈባቸው መናፍቃን ማኅበራትና ግለሰቦች ቀድሞውኑ በግልጽ የሚታወቁቱ በመኾናቸው የውሳኔው ትእምርታዊነት ያለው ዋጋ በጣም ከፍተኛ ነው፡፡ በተለይም የውሳኔው መሠረት የኾኑ ማስረጃዎችን በመሰብሰብና በማጠናቀር ጊዜያቸውንና ገንዘባቸውን ለሠዉት፣ ቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ እስኪሰጥ ድረስ ለምእመኑ ግንዛቤ በመስጠት ለደከሙት ልዩ ልዩ ተቋማትና ግለሰቦች÷ በዚህም ሂደት ለክስና ለእስር የተዳረጉትን (የፍርድ ጊዜውን በጥብአት ለመጨረስ የወሰነውን ወንድማችን መ/ር ዘመድኩን በቀለን ያስታውሷል) ወገኖች ሁሉ ደጀ ሰላም በድጋሚ ልባዊ ምስጋና ታቀርባለች፡፡

የምልአተ ጉባኤው አባላት በአጀንዳው አቀራረጽ ሂደት ባሳዩት ርብርብ የቅዱስ ሲኖዶሱን አመራር የበላይነት ማስከበራቸው በእጅጉ ያስመሰግናቸዋል፡፡ በውይይቱ ሂደትና በውሳኔ አሰጣጥ ላይ የታየው ዐምባነንነትንና ሰርጎ ገብ አጀንዳዎችን ለመከላከል የተጀመረው ቁርጠኝነት፣ መግባባትና ጥንቃቄም ተጠናክሮ መቀጠል የሚኖርበት ነው፡፡ በመጨረሻም ምልአተ ጉባኤው “በዘመናችን የተከፈለች ቤተ ክርስቲያን ለትውልድ አናስረክም”በሚል ለቤተ ክርስቲያን ሰላምና አንድነት ጉባኤ አባላት በሰጠው ድጋፍ በቅዱስ ሲኖዶስና በሰሜን አሜሪካ በሚገኙት አባቶች መካከል የተጀመረው የዕርቀ ሰላም ውይይት ተጠናክሮ እንዲቀጥል መስማማቱ በዘውዱ ላይ እንደ ምትጨመረዋ የመጨረሻ ዕንቍ ምልአተ ጉባኤው በድል የሚያንቆጠቍጠው ነው፡፡ ከዚህ በኋላ የበርካታ ደጀ ሰላማውያን ጥያቄ አንደኛ፡- አፈጻጸም፤ ሁለተኛ፡- አፈጻጸም፤ ሦስተኛ፡- አፈጻጸም የሚል ነው፡፡

ለቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔዎች ተግባራዊነት እንትጋ!!

ቸር ወሬ ያሰማን፤
አሜን፡፡

Thursday, 24 May 2012

የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ ባለአስር የአቋም መግለጫ በማውጣት ተጠናቀቀ


ጽጌ ስጦታውና ሰባት ግለሰቦች ማዕርገ ክህነታቸው ተገፎ እንዲወገዙ ተወሰነ


·         ቅዱስ ሲኖዶስ በውሳኔው መግለጫ ዝግጅት ላይ ጥንቃቄ አድርጓል፤ በመላው ዓለምየሚሠራጨውን መግለጫ በጽሑፍ የሚያዘጋጁት ከምልአተ ጉባኤው የተመረጡ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ናቸው።
·      አባ ሰረቀ በተጠየቁበት ጉዳይ እምነታቸውንበጽሑፍ ይገልጣሉ፤ ለ”እውነትና ንጋት” ሌላማስተባበያ መጽሐፍ እንዲጽፉ ተወስኗል።
·        ሊቀ ካህናት ጌታቸው ዶኒ ለፕሮቴስንታንት ቤተ እምነት የጻፉት ደብዳቤየእርሳቸው ላለመኾኑ በጽሑፍ ያረጋግጣሉ።
·        በጋሻው ደሳለኝ ተጨማሪ ስሕተቶቹ ተመርምረውና ራሱም ተጠይቆ የውሳኔ ሐሳብእንዲቀርብ ተወስኗል።

·         ሊቃውንት ጉባኤው በቤተ ክርስቲያናችን ላይ የሚነሡ ማንኛውንም የሃይማኖት፣ የሥርዐትና የታሪክ ጥያቄዎች ለመመለስ በሚያስችል የሰው ኀይልና በልዩ በጀትእንዲጠናከር ተወስኗል።
 (ደጀ ሰላም፤ ግንቦት 15/2004 ዓ.ም፤ May 23/ 2012)፦ የርክበ ካህናት ቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ በትናንት፣ ግንቦት 15 ቀን 2004 ዓ.ም የቀትር በኋላ ውሎው በቅዱስ ሲኖዶስ የተሠየመው የብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳትና የሊቃውንት ጉባኤ አባላት ጥምር ኮሚቴ በሐሰተኛ ትምህርታቸው ሊወገዙና ሊለዩ ይገባቸዋልባላቸው የፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ኑፋቄ አራማጅ ግለሰቦች ላይ ያቀረበውን ጥናታዊ መግለጫና የውሳኔ ሐሳብ መርምሮ አጸደቀ፡፡


በምልአተ ጉባኤው ውሳኔ መሠረት ግለሰቦቹ በቀረቡባቸው ማስረጃዎች የለየላቸው መናፍቃን መኾናቸውን የተረጋገጠ በመኾኑ ውግዘት ይተላለፍባቸዋል፤ የቤተ ክርስቲያንን ክብር በመዳፈራቸው በሕግ ይጠየቃሉ፤በቤተ ክርስቲያን የዜና አውታሮችም ማንነታቸው ተጠቅሶ በሐሰተኛ ትምህርታቸው ተወግዘው የተለዩ ለመኾናቸው ለምእመናን መግለጫ ይወጣባቸዋል፡፡


በዚህም መሠረት፡-
1)    ጽጌ ስጦታው፡- ይህ ግለሰብ በ1995 ዓ.ም ሚያዝያ ወር ለቅዱስ ሲኖዶስ ባስገባው የይቅርታ ይደረግልኝ ደብዳቤ “ያስተማርኹት፣ የተናገርኹትና የጻፍኹት ሁሉ ስሕተት መኾኑን ስላመንኹ ይህን ሁሉ ስሕተቴን ቅዱስ ሲኖዶስ ተረድቶልኝ ይቅርታ እንዲያደርግልኝና ትምህርቱን እንድማር ይፈቀድልኝ ዘንድ በታላቅ ትሕትና አመለክታለኹ” የሚል ነበር፡፡ በዚህም መሠረት ንስሐ እንዲገባ ተመክሮ ነበር፤ ነገር ግን ምክሩን ሊጠቀምበት እንዳልቻለ ታውቋል፡፡ ይህ ግለሰብ በተደጋጋሚ ተመክሮ ያልተመለሰ የለየለት መናፍቅ ኾኖ ከቤተ ክርስቲያን የወጣና የተለየ መኾኑ የተረጋገጠ ነው፡፡ በመኾኑም ውግዘት እንዲተላለፍበትና ይኸውም በሁሉ የቤተ ክርስቲያኒቱ የዜና አውታሮች ለምእመናን እንዲገለጽ ቅዱስ ሲኖዶስ ወስኗል፡፡


2)   መጋቤ ጥበብ ሰሎሞን መኰንን፡- “ኦርቶዶክሳዊነት እንዲህ ነው!” (1999 ዓ.ም) እና “በውኑ በማርያም ማመን ይገባሃልን?” በሚሉ ርእሶች ባሳተማቸው ክሕደትና ኑፋቄ የመላባቸው መጽሐፎቹ የክርስቶስን አምላክነት የሚክድ፣ የእመቤታችንን ንጽሕና፣ ቅድስናና አማላጅነት የሚቃወምና የሚነቅፍ በአጠቃላይ የቤተ ክርስቲያናችንን አስተምህሮ የሚያፋልሱ መኾኑ ስለተረጋገጠ ጸሐፊውም ኾነ መጽሐፉ ሊወገዙ እንደሚገባ ቅዱስ ሲኖዶስ አምኖበታል፡፡ በመኾኑም ይህ አሳሳች ሐሳብ ምእመናንን እንዳያደናግር የቅዱስ ሲኖዶስ ቀኖናዊ ውሳኔ በቤተ ክርስቲያናችን የዜና አውታሮች ለምእመናን እንዲገለጽ ተወስኗል፡፡


3)   ዲያቆን ደረጀ ገዙ ከኑፋቄ ጓደኛው በዛ ሰፈርህ ጋራ የኑፋቄ ትምህርት ያስተማረና “መቅደስ የገቡ መናፍቃን” በሚል ርእስ የኑፋቄ መጽሐፍ ያሳተመ ነው፡፡ በባሕር ዳር እና አዲስ አበባ ከተሞች የአስተማረው ትምህርት ኑፋቄ የተመላበት እንደ ኾነ የቀረበበት ማስረጃ ያረጋግጣል፡፡ የበዛ ሰፈርህ የኑፋቄ ትምህርትም ከዲያቆን ደረጀ ገዙ ጋራ አንድ ነው፡፡ በመኾኑም በቀረበው ማስረጃ ተራ ቁጥር (3) እና (4) የተገለጹት እኒህ ሁለት ግለሰቦች በማስረጃ ተደግፎ በቀረበው የሐሰት ትምህርታቸው ተወግዘው እንዲለዩ ቅዱስ ሲኖዶስ ወስኗል፡፡ ይኸው የቅዱስ ሲኖዶስ ቀኖናዊ አቋም በቤተ ክርስቲያን የዜና አውታሮች ለምእመናን እንዲገለጽም ትእዛዝ ሰጥቷል፡፡


4)   አግዛቸው ተፈራ እና ሁለት ግለሰቦች፡- ይህ ግለሰብ በአሰላ ከተማ ደብረ መድኃኒት መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን ሰንበት ት/ቤት ሲያገለግል የኑፋቄ ትምህርት በማስተማሩ በሰንበት ት/ቤቱ አባላት ክትትልና በሰበካ ጉባኤው ጥንካሬ ማንነቱ ተጋልጦ አልመለስ ሲል ከአገልግሎቱ የታገደ ነው፡፡ ከሚወገዙት የመናፍቃን ድርጅቶች አንዱ የ‹ማኅበረ በኵር› በኾነው ‹ጮራ› መጽሔት በዋና አዘጋጅነት ተቀጥሮ እየሠራ የሚገኘው ግለሰቡ “የለውጥ ያለህ” (2001 ዓ.ም) ፣ “የተቀበረ መክሊት” (1993 ዓ.ም) እና “አልተሳሳትንም”(2003 ዓ.ም) በሚሉ ርእሶች ባሳተማቸው ክሕደትና ኑፋቄ የተመላባቸው መጽሐፎቹ “ቤተ ክርስቲያን ኢ-መጽሐፍ ቅዱሳዊ አስተምህሮዎች ስላሏት የአስተምህሮ ለውጥ ያስፈልጋታል፤ በእንግዳ ትምህርቶችና የፈጠራ ድርሰቶች ነው የምትመራው፤” ሲል ጽፏል፡፡

ዲያቆን አግዛቸው ተፈራ ÷ አቶ አሰፋ ተገኝ እና አቶ ብሥራት ጌታቸው ከሚባሉ ሌሎች ሁለት ግለሰቦች ጋራ በመፈጸሙት የመናፍቅነት ተግባር የአርሲ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ናትናኤል፣ የአምስት አድባራት የሰበካ ጉባኤ አባላትና ካህናት በተገኙበት ሰኔ 4 ቀን 1991 ዓ.ም ቀርበው እንዲጠየቁ ከተደረገ በኋላ ከስሕተታቸው የማይመለሱ መኾናቸው በመረጋገጡ በማንኛውም መንፈሳዊ ተግባር እንዳይሳተፉ መታገዳቸውን ቅዱስ ሲኖዶስ በቀረበለት ማስረጃ አረጋግጧል፡፡ በመኾኑም ቅዱስ ሲኖዶሱ በአግዛቸው ተፈራና ሁለቱ ግለሰቦች ላይ የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ናትናኤል የወሰዱባቸውን ቀኖናዊ ውሳኔ አጽንቷል፤ ይኸው ቀኖናዊ ውሳኔም በቤተ ክርስቲያኒቱ ብዙኀን መገናኛ ለምእመናን እንዲገለጽ ቅዱስ ሲኖዶስ ወስኗል፡፡

በጋሻው ደሳለኝን በተመለከተ ርእሰ መንበሩ አቡነ ጳውሎስ በግለሰቡ የተጻፈ ነው የተባለውን ደብዳቤ ለምልአተ ጉባኤው በንባብ አሰምተዋል፡፡ ፓትርያርኩ ከእጅጋየሁ በየነና ሌሎች የጨለማው ቡድን አባላት ጋራ ሳይመክሩበት እንዳልቀረ የተገመተው የበጋሻው ደብዳቤ ÷ እርሱ ከሚጠየቅበት ጉዳይ ንጹሕ መኾኑንና “ከሳሼ ማኅበረ ቅዱሳን እንጂ ቤተ ክርስቲያን አይደለችም” የሚል ነው፡፡



የሃይማኖት ሕጸጽ ጥቆማ የቀረበባቸውን ግለሰቦች ጉዳይ ባጣራው ጥምር ኮሚቴ በተደጋጋሚ ለጥያቄ ተፈልጎ ያልቀረበው በጋሻው በእጅጋየሁ በየነ ተበረታቶ በፓትርያርኩ ተተግኖ ያቀረበው ጥያቄ ግን በምልአተ ጉባኤው ዘንድ ተቀባይነት አላገኘም፡፡ ይልቁንም ጥምር ኮሚቴው በጋሻው ኤሽታኦል” (2001 ዓ.ም) በተሰኘው መጽሐፉ በዐላዋቂ ድፍረትና ጥንቃቄ በሚጎድላቸው ንግግሮቹ የተናገረውን ማስረጃ በመቀበል በቤተ ክርስቲያናችን ያልተለመደና ከቤተ ክርስቲያናችን አስተምህሮ ውጭ የኾነ ፍጹም ስሕተት መኾኑን አረጋግጧል፡፡

ምልአተ ጉባኤው ግን በዚህ ብቻ ሳይወሰን ሌሎች የበጋሻው ዐበይት ሕጸጾች የሚገኙባቸው መጽሐፎቹና ሲዲዎቹ ለምን ተጨምረው እንዳልተመረመሩ ጠይቋል፤ ይህ ጥያቄ በብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ኮሚቴ አባል የኾኑት ብፁዕ አቡነ ቀውስጦስ ሳይቀሩ ያነሡት ነበር፡፡ ለጥያቄው የተሰጠው ምላሽ የካሴት ወይም ቪሲዲ ማስረጃዎች ተመሳስለው ለሚሠሩ የተጭበረበሩ ይዘቶች የተጋለጡ መኾኑንና የባለሞያ እገዛና ሞያዊ ምክር የሚሰጥ አካል እንደሚያስፈልግ የሚያመለክት ነው፡፡ በመኾኑም ቅዱስ ሲኖዶስ በጋሻው ደሳለኝ ለጥያቄ በተደጋጋሚ ተጠርቶ አለመገኘቱን ከግምት በማስገባት፣ በምሳሌነት የቀረበውን “በራስ ቅል ኮረብታ ክርስቶስና ዲያብሎስ ቁማር ተጫወቱ. . .” የሚለውን የድፍረት  ንግግሩን እንደ መነሻ በመውሰድ ሌሎች ካሴቶቹ ወይም ሲዲዎቹ (ከዘጠኝ ያላነሱ እንደሚኾኑ ተገምቷል) በአግባቡ እንዲመረመሩ ወስኗል፡፡ግለሰቡ ወደፊት ቀርቦ እንዲጠየቅና በሚሰጠው መልስ ጉዳዩ እንዲታይ ጥምር ኮሚቴው በሪፖርቱ ያስቀመጠውን አስተያየት ቅዱስ ሲኖዶስ በመቀበል በጋሻው ተጠርቶና ተጠይቆ ከውሳኔ ሐሳብ ጋራ ለጥቅምት ቅዱስ ሲኖዶሰ ምልአተ ጉባኤ የውሳኔ ሐሳብ እንዲቀርብለት ትእዛዝ ሰጥቷል፡፡

ከበጋሻው ቀደም ሲል ከተጠቀሰው በተጨማሪ “ነሁሽታን” በተባለው ሲዲው÷ “ድነናልኮ እኛ፤ ጠበል ያድነናል፤ መስቀል ያድነናል፤ የኾነ ነገር ያድነናል አትበል”፤ “ሴትዮዋ ገብርኤልን አትግፋኝ አለችው” እያለ ይዘባርቃል፡፡ “ጠላቶችህ ዋሹብኽ” በተሰኘው የስብከት ሲዲው÷ “እግዚአብሔር ቆራሌ ሰብሳቢ ነው”፤ “ጌታ መከራው እየመጣ እያለ ወደ ጌቴ ሰማኒ ሄደና ቅልጥ አድርጎ ከሐዋርያት ጋራ ይዘምራል፤” “ራዕያችን በጨረቃ ላይ ቤተ መቅደስ መሥራት ነው”፤ “ለካ ትወዱናላችኹ፤ ታከብሩናላችኹ፤ እኛ ቀለል አድርገን ነበር የምናገለግለው፤. . . ለካ ይህ ሁሉ ሕዝብ በእኛ ላይ ተደግፏል፤ እኛ ብንወድቅ ለካ ይህ ሁሉ ሕዝብ ይወድቅ ነበር፤ እኛ ብንሸነፍ ይህ ሁሉ ሕዝብ ይሸነፍ ነበር፤. . . ይህ መስቀል የማያመጣው ጣጣ የለም”፤ “የመማጸኛ ከተማ” በተሰኘው ደግሞ “ከጌታ ጨርቅ ይልቅ እመቤታችን አትበልጥም”፤ በሉቃ.8÷43 ላይ የሚገኘውን ታሪክ በመጥቀስ “ደም ሲፈሳት የነበረችው ሴት በጌታ ጨርቅ አምና ዳነች፤ እርሷ በእናቱ አይደለም፤ በአባቱም አይደለም በእርሱ ጨርቅ አመነች” በማለት ይዘባርቃል፡፡

በተለያየ ቦታ ባሰማቸው ስብከቶቹም “ለማርያም ከበሮ አይመታም ለጌታ እንጂ”፤ “ሥላሴ አትበሉ”፤ “ሥላሴ አትበሉ ተባለ እንጂ በሥላሴ አትመኑ አልተባለም”፤ “ቅዱስ ጳውሎስ ፋሲካችን እርሱ ነው አለ፤ ማን ነው እርሱ - ኢየሱስ ክርስቶስ፤ እግዚአብሔርና ኢየሱስ ክርስቶስ የሚለውን አትቀላቅሉ እባካችኹ፤ የምናስተምርም ሰዎች ለይተን እናስተምራቸው፤ ኢየሱስ የሚለውን ስም ሽሽት እግዚአብሔር፣ ሥላሴ፣ ወደዚህ ወደዚያ አትበሉ”፤ “በዕድር ደንብ ነው ያለው እስከ አሁን፣ የወንጌል ሕግ አልገባውም፤ የንፍሮ ቀቃይ ልጅ. . .”የሚሉት ጥንቃቄ በጎደላቸውና ድፍረት በተመላባቸው ንግግሮቹ ብዙዎችን አሳስቷል፡፡

በመኾኑም በጋሻው በዐላዋቂ ድፍረት ቀኖና ቤተ ክርስቲያንን በመጣስ ለተናገራቸው ገና በጥምር ኮሚቴው ፊት ቀርቦ የሚጠየቅ እንጂ አንዳንድ መፍቀሬ ፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ብሎጎች በችኮላ እንዳናፈሱት ከሚጠየቅበት ጉዳይ “ነጻ የተባለ ወይም ነጻ የወጣ” አይደለም፡፡
ጥምር ኮሚቴው በአባ ሰረቀ ላይ ያቀረበውን በተመለከተ ባቀረበው ሪፖርት ጥር 18 ቀን 1997 ዓ.ም በዩናይትድ ስቴትስ ኦፍ አሜሪካ የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክን ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ማቲያስ ለቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት በጻፉት 12 ገጽ የጽሑፍ መግለጫ ገጽ 5 ላይ“እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ከአዳም በዘር የሚተላለፍ የውርስ ኀጢአት (ጥንተ አብሶ) ነበረባት፤”የሚለውን የቀሲስ አስተርኣየ ጽጌን ትምህርት ደግፎ ሰባት አባላት ያሉበት ጉባኤ ባሳለፈው ውሳኔ የአባ ሰረቀ ብርሃን ወልደ ሳሙኤል (ቆሞስ) ስም በስድስተኛ ተራ ቁጥር ተጠቅሶ መገኘቱን የጽሑፍ መግለጫው ያረጋግጣል፡፡

ራሳቸው አባ ሰረቀ “እውነትና ንጋት” በሚል ርእስ ባሳተሙት መጽሐፍ በገጽ 38 ላይ ስለዚሁ ጉዳይ የተገለጸውን ሙሉውን ቃል የሰፈረበትን እትም አሰራጭተዋል፡፡ የወቅቱን የተሐድሶ መናፍቃንና ተዛማጅ ችግሮች አስመልክቶ ከአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሰንበት ት/ቤቶች በጋራ የሰጠው 41 ገጽ መግለጫ ስም የሌለው የ12 ሰዎች ፊርማ ብቻ ይዞ በቀረበው ጽሑፍ በገጽ 17 ላይ “የተሐድሶ ኑፋቄ አራማጆች እነማን ናቸው?” በማለት በጥያቄ ምልክት ከጠቀሷቸው ሰዎች በሁለተኛው ተራ ቁጥር አባ ሰረቀ ብርሃን ወልደ ሳሙኤል መኾናቸውን ያሳያል፡፡

ማኅበረ ቅዱሳን ለአጣሪ ኮሚቴው ባቀረበው ሰነድ ላይ አባ ሰረቀ ብርሃን ወልደ ሳሙኤል “ከአጽራረ ቤተ ክርስቲያን ጋራ አብረው መሥራታቸውንና አብረው የሚሠሩ በሌላ እምነት ያሉ አስቸጋሪ ሰዎችን” ለማስረጃ ያህል አቅርበዋቸዋል፡፡ እኒህም፡- ሀ) ብርሃኑ አበጋዝ - የታወቀ የተሐድሶ አባል፤ ለ) ሙሉጌታ ወልደ ገብርኤል - በኑፋቄው ከቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ የተባረረ የለየለት ፕሮቴስታንት፤ (አሁንም በየድረ ገጹ ላይ የክህደት ጽሑፎቹን በማውጣት ላይ የሚገኝ)፤ ሐ) አባ ኀይለ ሚካኤል ተክለ ሃይማኖት - በሄዱበት ቦታ ሁሉ ችግር የሚፈጥሩና በኑፋቄ የሚታወቁ ግለሰብ በማለት በአባሪ 11 ገጽ ማስረጃ አስደግፈው ለአጣሪ ኮሚቴው አቅርበውታል፡፡

አባ ሰረቀ በእመቤታችን ንጽሕና ላይ አቋማቸው ምን እንደኾነ ወይም ከማን ወገን እንደኾነ ለይተው እንዲያሳውቁ ከሰሜን አሜሪካ ለቅዱስ ሲኖዶስ የተላከው ደብዳቤ ተነቦላቸው እንዲሰሙት ከተደረገ በኋላ ተጠይቀዋል፡፡ 

እርሳቸውም ሲመልሱ፡-
“ስለ ነገረ ማርያም አስተምህሮ በአሜሪካ በቀሲስ አስትርኣየ ጽጌና በማኅበረ ካህናቱ በተደረገው ውይይት በቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ እንዲሰጥበት ወደ ኢትዮጵያ መላካችን የታወቀ ነው፡፡ በዚህ ኹኔታ ላይ የእኔ አቋም የቤተ ክርስቲያኔ ቅዱስ ሲኖዶስ የሰጠውና የሚሰጠው ውሳኔ ነው፡፡ ይኸውም “የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን እምነት፣ ሥርዐተ አምልኮና የውጭ ግንኙነት” በሚል ርእስ ቅዱስ ሲኖዶስ ፈቅዶ በታተመው የቤተ ክርስቲያናችን ትምህርት ስለ ነገረ ማርያም አስተምህሮ የተገለጸው ትምህርት ቀድሞም የማምነው፣ አሁንም የማረጋግጠው እርሱን ነው፡፡ከዚህ ውጭ ስለ ነገረ ማርያም አስተምህሮ የተናገርኹት፣ ያስተማርኹትና የጻፍኹት የለም፡፡ በነገረ ማርያም ላይ ያለኝ አቋምና ጽኑዕ እምነት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ በወሰነው ውሳኔ ብቻ ነው፤ አምላካችኹ ያየኛል፡፡ ከዚህ የተለየ ዓላማና ተልእኮ የለኝም፡፡” 
በማለት አሁንም ያለውን የእምነት አቋማቸውን ስለ መግለጻቸው የአጣሪ ኮሚቴው ሪፖርት ያብራራል፡፡ ይህን የአባ ሠረቀ ብርሃንን ምስክርነት መሠረት በማድረግ የሪፖርቱ የውሳኔ ሐሳብ አባ ሠረቀ ብርሃን የተጠቀሰው የነገረ ማርያም አስተምህሮ የሚያስጠይቃቸው ኾኖ ያልተገኘ መኾኑን ጉባኤው መገንዘቡን ያስረዳል፡፡ ስለዚህም ቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ ይሰጥበት ዘንድ የውሳኔ ሐሳቡን አቅርቧል፡፡

የውሳኔ ሐሳቡን ሙሉ በሙሉ የተቀበለው የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤም ባለ ሁለት ነጥብ ውሳኔዎችን አሳልፏል፡፡ ይኸውም አንደኛ፡- ቆሞስ አባ ሠረቀ ብርሃን ወልደ ሳሙኤል “በነገረ ማርያም ላይ ያለኝ አቋምና ጽኑዕ እምነት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ በወሰነው ውሳኔ ብቻ ነው፤” ሲሉ በቃል ለአጣሪ ኮሚቴው የተናገሩትን በጽሑፍ ገልጸው እንዲያቀርቡ፤ ሁለተኛ፡- “እውነትና ንጋት” በሚልመጽሐፍ መሰል የመዝገብ ቤት ጥራዝ ያነሷቸውን ሐሳቦች በተመሳሳይ መጽሐፍ እንዲያስተባብሉ ትእዛዝ ሰጥቷል፡፡

በጥቅምቱ ቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ውሳኔ ለሰባት ዓመት በውዝግብ ከመሩት የሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ዋና ሓላፊነታቸው ተነሥተው የትምህርትና ማሠልጠኛ መምሪያ ሓላፊ ኾነው በመሥራት ላይ የሚገኙት ቆሞስ አባ ሠረቀ ብርሃን ወልደ ሳሙኤል ይህን የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ውሳኔ በተግባር ተፈጻሚ እንደሚያደርጉ ይጠበቃል፡፡ ይህን እስካላደረጉ ድረስ ግን በእርሳቸው ላይ የተነሡት ጥያቄዎችና ጥርጣሬዎች አብረዋቸው ይቆያሉ ማለት ነው፡፡

ቆሞስ አባ ሠረቀ ብርሃን በምስክርነታቸው የጠቀሱት፣ የእነ ቀሲስ አስተርኣየ ጽጌንና የአባ ጳውሎስን የነገረ መለኰት ዶክትሬት ዲግሪ ማሟያ ጥናት የሚያስተባብለውና በቅዱስ ሲኖዶስ ፈቃድ ሰባት ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳትና 11 ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ያዘጋጁት መጽሐፍ ቤተ ክርስቲያናችን በእመቤታችን ክብር፣ ንጽሕናና ቅድስና ስላላት የእምነት አቋም የሚከተለውን ይላል፡- “ቤተ ክርስቲያናችን የምታምነውና የምታስተምረው፡- አምላክን በድንግልና ፀንሳ በድንግልና የወለደች እመቤታችን ድንግል ማርያም ከአዳም ዘር የተላለፈ ኃጢአት (ጥንተ አብሶ) ያላገኛት፣ መርገመ ሥጋ፣ መርገመ ነፍስ የሌለባት፣ ገና ከመወለዷ አስቀድሞ በአምላክ ኅሊና ታስባ ትኖር የነበረች፣ በሰው ልማድና ጠባይ ከሚደርሰው ሥጋዊ ሐሳብና ፈቃድ ሁሉ የተጠበቀች፣ ከተለዩ የተለየች ንጽሕት ቅድስተ ቅዱሳን ናት፡፡”

የአዲስ አበባ 131 ሰንበት ት/ቤቶች አንድነት 12 አመራር አባላት የወቅቱ የተሐድሶ መናፍቃን እንቅስቃሴን አስመልክቶ ባቀረቡት 41 ገጽ ሰነድ ጥቆማ ከቀረበባቸው 67 ግለሰቦች መካከል በአጣሪ ኮሚቴው ተጠርተውና ተጠይቀው ለምልአተ ጉባኤው የውሳኔ ሐሳብ የቀረበባቸው ሊቀ ካህናት ጌታቸው ዶኒ ብቻ ናቸው፡፡ በማስረጃው ገጽ 20 ላይ የተሐድሶ መናፍቃን ኑፋቄ አራማጅ ናቸው በሚል ከተዘረዘሩት ግለሰቦች ውስጥ በተ.ቁ ዘጠኝ ላይ የሚገኙት ሊቀ ካህናት ጌታቸው ዶኒ፡- “ለኢትዮጵያ ወንጌላዊት መካነ ኢየሱስ ቤተ ክርስቲያን. . .የእናንተ እምነት አስተማሪ በመኾን ተከታይ ለመኾን ባቀረብኹት ጥያቄ መሠረት በአባልነት ተመዝግቤ በመሳተፍ ላይ እገኛለኹ፤. . .” በሚል ቀን ባልተገለጸበት ነገር ግን ፊርማና ቲተራቸው ያለበት ማመልከቻ በሰነድ ማስረጃነት ቀርቦባቸዋል፡፡


በሌላ በኩል በቁ/ል/መ/ፈ/አ/9/2000 በቀን 14/01/2000 ዓ.ም በአቶ ብርሃነ ደሬሳ ከንቲባነት ይመራ ለነበረው የአዲስ አበባ ከተማ ባለአደራ ጊዜያዊ አስተዳደር በጻፉት ፊርማና ቲተራቸውን በያዘ ደብዳቤ በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ በቀበሌ 02/04 እየተንቀሳቀሰ ለሚገኘው የቅን ልቡና መንፈሳዊ ፈውስ አገልግሎት የእምነትተቋም ሕገ መንግሥት በሰጠው መብት እንደ ማንኛውም አገር በቀል የእምነት ተቋም ከፍትሕ ሚኒስቴር ሕጋዊ የሰውነት መብት አግኝቶና ተመዝግቦ ያለ የእምነት ተቋም ነው፤” ሲሉ ጽፈዋል፡፡ በቁጥር 11/6361/ፈ/3076 በቀን 10/08/99 ዓ.ም ለፍትሕ ሚኒስቴር በተጻፈ ደብዳቤ “የቅን ልቡና መንፈሳዊ ፈውስ አገልግሎት” እንደ አንድ አገር በቀል ማኅበር ሕጋዊ ሰውነት አግኝቶ እንዲንቀሳቀስ የተጠየቀበት ማመልከቻ ከማስረጃው ጋራ የተያያዘ ሲኾን በቀን 02/11/99 ዓ.ም ደግሞ የአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ አብያተ ክርስቲያን በአንድነት በወረዳው ቤተ ክህነት ጽ/ቤት ተሰብስበው ሊቀ ካህናት ጌታቸው የቤተ ክርስቲያኒቱን ሕግና ሥርዐት በመጣስ እየተንቀሳቀሱ በመኾኑ ክትትል እንዲደረግባቸው ለመንበረ ፓትርያርክና ለሚመለከተው ሁሉ የጻፉት ስም ዝርዝርና ፊርማ ያለበት ጽሑፍ ለአጣሪ ኮሚቴው በማስረጃነት ቀርቧል፡፡


ማስረጃዎቹ ለሊቀ ካህናት ጌታቸው ዶኒ ከተነበቡላቸው በኋላ ሲመልሱ “ለኢትዮጵያ ወንጌላዊት መካነ ኢየሱስ” ተጻፈ የተባለው ደብዳቤ “የእኔ አይደለም፤ ወደዚህ የእምነት ተቋም የመግባቱም ፍላጎት የለኝም፤ አስፈላጊም ከኾነ በፎረንሲክ ይመርመር” በማለት ቃላቸውን ሰጥተዋል፡፡
“የቅን ልቡና መንፈሳዊ ፈውስ አገልግሎት የእምነት ተቋም” በማቋቋም ሥርዐተ ቤተ ክርስቲያንን በመጣስ ስለ መንቀሳቀሳቸው ሲጠየቁም “በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት በደረሰብኝ የአስተዳደር በደልና ችግር ምክንያት የቅን ልቦና መንፈሳዊ የፈውስ አገልግሎት የእምነት ተቋም በማለት ከፍትሕ ሚኒስቴር አስፈቅጄ ስንቀሳቀስ መቆየቴ ግልጽ ነው፡፡ ይህን ስሠራ ከኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክን የተለየ ትምህርት አላስተማርኹም፤ ጽሑፍ አልጻፍኹም፤ ድርጅቱን ያቋቋምኹበት ምክንያት ከቋሚ ሥራዬ ስፈናቀል ለቤተሰቦቼ የማበላው ዳቦ ስላጣኹ ሃይማኖቴንና ክህነቴን ጠብቄ መንፈሳዊ የፈውስ አገልግሎት ስሰጥ ቆይቻለኹ፤ በመጨረሻም ይቅርታ እንዲደረግልኝ ለብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አመልክቼ ይቅርታ ከተደረገልኝ በኋላ የቅን ልቡና የመንፈሳዊ ፈውስ አገልግሎት የእምነት ተቋም የሚለውን ፈቃድ መልሼ በቤተ ክርስቲያኔ በተለያየ የሥራ ዘርፍ ተመድቤ እያገለገልኹ እገኛለኹ” 
በማለት ቃላቸውን ሰጥተዋል፡፡ ይቅርታ ተደርጎላቸው በሥራ የተመደቡ መኾኑን የሚያስረዳ ደብዳቤም አቅርበዋል፡፡
የአጣሪ ኮሚቴው ዐቢይ ጉባኤ ሊቀ ካህናት ጌታቸው ዶኒ ‹ለወንጌላዊት መካነ ኢየሱስ› ጻፉት የተባለውን ስምና ቲተራቸውን የያዘ ደብዳቤ እርሳቸው የጻፉት አለመኾኑን የመሰከሩት ቃል ወደፊት መጣራት እንደሚያስፈልገው በማመን አልፎታል፡፡ አቋቁመውት የነበረውን ድርጅት ፈቃድ መልሰው ይቅርታ ተደርጎላቸው በቤተ ክርስቲያናችን ሥራ መመደባቸውን ደግሞ ተቀብሎታል፡፡

ይህን የአጣሪ ኮሚቴውን ዐቢይ ጉባኤ የውሳኔ ሐሳብ የመረመረው የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ በሊቀ ካህናት ጌታቸው ዶኒ ላይ ባለሁለት ነጥብ ውሳኔዎችን አሳልፏል፡፡ በዚህም መሠረት አንደኛ፡- ሊቀ ካህናት ጌታቸው ለ“ኢትዮጵያ ወንጌላዊት መካነ ኢየሱስ” የእምነታቸው አስተማሪ ለመኾን አባል ለመኾን እንደሚፈልጉ የተጠየቀበትን ማመልከቻ እርሳቸው እንዳልጻፉትና የዚህም ፍላጎት እንደሌላቸው ለአጣሪ ኮሚቴው የተናገሩትን ቃል በጽሑፍ እንዲገልጹ፤ ሁለተኛ፡- “የቅን ልቡና መንፈሳዊ ፈውስ አገልግሎት የእምነት ተቋም” በሚል ስላቋቋሙት ድርጅት ይቅርታ የጠየቁ በመኾኑ ቀኖና እንዲሰጣቸው ወስኗል፡፡


ብፁዕ አቡነ ቀውስጦስ በዘንድሮው የርክበ ካህናት ቅዱስ ሲኖዶስ መደበኛ ስብሰባ መክፈቻ ጸሎት ወቅት በሰጡት የጉባኤው ትኩረት አመላካች ትምህርት ላይ እንደዘገብነው÷ ቅዱስ ሲኖዶሱ ግንባር ቀደም አጀንዳ ባደረገውና ቀናትን በወሰደው የሃይማኖት ጉዳይ ከ1990 ዓ.ም ወዲህ ዐበይት ውሳኔዎችን ማሳለፉን ተከትሎ የፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ እንቅስቃሴ አራማጅ ድርጅቶችና ግለሰቦች እንደ ኀይለ ጊዮርጊስ ጥላሁን ካሉት የውስጥ አርበኞቻቸው ጋራ በመኾን መጠነ ሰፊ የስም ማጥፋት ዘመቻዎችና ሌሎችም ዐይነት ጥቃቶችን እንደሚከፍቱ (ግብረ መልስ እንደሚሰጡ) ግምት ወስዷል፡፡ በአሁኑ ወቅት እኒህ ግልጽ የወጡና በውስጥ በኦርቶዶከሳዊ ካባ የሚንቀሳቀሱ አጽራረ ቤተ ክርስቲያን የውሳኔዎችን ተፈጻሚነት ለመቀልበስም ይኹን በብፁዓን አባቶች ላይ ሊያደርሱ የሚችሉትን ቀጥተኛ ጥቃት እነርሱ ራሳቸው በመረጡት መንገድ ለመመከት ብቃቱም ዝግጁነትም እንዳለ በገሃድ እንዲያውቁት ያስፈልጋል፡፡


ይህ እንደተጠበቀ ኾኖ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ የሊቃውንት ጉባኤ መምሪያው ግልጽ የወጡ አጽራረ ቤተ ክርስቲያን ባፍም በመጣፍም ሊከፍቱት ለሚችሉት ዘመቻ ብቁና ዙሪያ መለስ ምላሽ ለመስጠት በሚችልበት አኳኋን ድርጁና ዝግጁ እንዲኾን ትኩረት ሰጥቶ ተነጋግሮበታል፡፡ በዚህም መሠረት ሊቃውንት ጉባኤው በተጨማሪ የሰው ኀይልና በልዩ በጀት ተጠናክሮ በምልአተ ጉባኤው ውሳኔ እንደተገለጸው እስከ ዛሬ ለተጻፉት የኑፋቄ ሥራዎች ምላሽ እንዲሰጥ፣ በተከታታይ ለሚመጣውም ምላሽ እያዘጋጀ እንዲቀጥል ቅዱስ ሲኖዶሱ ወስኗል፡፡


ምልአተ ጉባኤው ሃይማኖታዊ ጉዳዮችን አስመልክቶ በፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ኑፋቄ አራማጅ ድርጅቶችና ግለሰቦች ላይ ያሳለፈው ውሳኔ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አስተዳደር በሚገኝበት ሁሉና በመላው ዓለም ላሉ ኦርቶዶክሳውያን በሚረዱበት ቋንቋ ተዘጋጅቶ እንዲሰራጭ ለማድረግ ጥንቃቄ የተሞላበት ርምጃ ወስዷል፡፡ ይህም ከወትሮው በተለየ አኳኋን የምልአተ ጉባኤውን ቃለ ጉባኤ በሚይዙ የቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት ሠራተኞች ሳይኾን በራሳቸው በብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳቱ እንዲዘጋጅ መወሰኑ ነው፡፡


በዚህም መሠረት የርክበ ካህናት ቅዱስ ሲኖዶስ በአጀንዳ ተ.ቁ (13) “ስለ ሃይማኖት ሕጸጽ በኮሚቴው የሚቀርበውን ሪፖርት መስማትና መወሰን” በሚለው ርእሰ ጉዳይ ላይ በመነጋገር ያሳለፋቸውን ውሳኔዎች በጽሑፍ አዘጋጅተው እንዲያቀርቡ አራት ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት የሚገኙበትን ኮሚቴ ሠይሟል፡፡ እነርሱም፡-1)ብፁዕ አቡነ ገሪማ፣ 2)ብፁዕ አቡነ ቀውስጦስ፣ 3)ብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤል እና 4)ብፁዕ አቡነ ቀሌምንጦስ ናቸው፡፡


በትናንቱ ከቀትር በኋላ የቅዱስ ሲኖዶስ መደበኛ ስብሰባ በርእሰ መንበሩ አቡነ ጳውሎስ አመራር ላይ የታየው ለውጥ በብዙዎቹ የምልአተ ጉባኤው አባላት ላይ ያሳደረው ስሜት ሳይገለጽ የሚታለፍ እንዳልኾነ የስብሰባው ምንጮች ይጠቁማሉ፡፡ ይህም ፓትርያርክ አቡነ ጳውሎስ የግለሰቦቹ ኑፋቄ አንድ በአንድ እየተነበበ የውሳኔ ሐሳቡ ላይ ውይይት በሚካሄድበት ወቅት ከቀትር በፊትና ሰሞኑን ከያዙት ዝንባሌ በተለየ ኹኔታ እየቀደሙ የውግዘት ሐሳብ አቅራቢ መኾናቸው ነው፡፡


ደጀ ሰላም እምነት ይህ ቆይቶ እውንነቱ የሚረጋገጥ የዝንባሌ ለውጥ ከመጀመሪያው የስብሰባው ቀን አንሥቶ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳቱ በማዘናጊያ አጀንዳዎች ብዙም ሳይጠመዱ ርእሰ ጉዳያቸውን ለይተው በማወቅ በንቃትና በአንድነት ተግባብተው በመወያየት የነበራቸው የተዋሐደ ጥረት ውጤት ነው፡፡ በዚህም ድሉ ለቀናዒ ኦርቶዶክሳውያን አገልጋዮችና ምእመናን ሁሉ ነው፡፡ በተለይም የየራሳቸውን ድርሻ በመወጣት ለዚህ ውጤት መገኘት ቀጥተኛ አስተዋጽኦ የነበራቸው የየአህጉረ ስብከት አጥቢያ አብያተ ክርስቲያን ሰበካ ጉባኤያትና ሰንበት ት/ቤቶች፣ በበጎ ፈቃድ የተሰባሰቡ የፀረ - ተሐድሶ ሰባክያን ጥምረት፣ የጥምቀት ልጆች አንድነት እንዲሁም የማኅበረ ቅዱሳን አመራርና አባላት መንፈሳዊ ጥብአት ነው፡፡


ደጀ ሰላም የብፁዓን አባቶቻችንን ጉባኤ የቅዱሳን ሐዋርያትና የሠለስቱ ምእት ጉባኤ በማድረግ እንደ አንድ ልብ መካሪ እንደ አንድ ቃል ተናጋሪ በማድረግ ለዚህ አንጸባራቂ ውሳኔ ያበቃውን ልዑል እግዚአብሔር ታመሰግናለች፡፡ ለብፁዓን አባቶቻችን ሰላምን፣ ረጅም ዕድሜንና ጤናን ከደገኛ አገልግሎታቸው ጋራ እንዲሰጣቸው፣ በሌሎቹም የቤተ ክርስቲያን አንገብጋቢ ጉዳዮች ተመሳሳይ ውጤት እንዲያስመዘግቡ ልባዊ መሻቷን በፊቱ ታቀርባለች፡፡ በየመዋቅሩና በየሥፍራው ለሚገኙ ለፀረ - ፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ አደረጃጀቶች ሁሉ ስኬቱ የእናንተ ነው፤ እንኳን ደስ አላችኹ!! ውሳኔው በየአካባቢያችን ያለውን ተፈጻሚነትም በንቃትና በቀጣይነት እንከታተለው በማለት መልእክቷል ታስተላልፋለች፡፡

ይትባረክ እግዚአብሔር አምላከ አበዊነ!!
ቸር ወሬ ያሰማን፤
አሜን፡፡