ገጾቻችን

Tuesday, 5 March 2013

ፍቅርና ሃይማኖት - ነፍስና ሥጋ በዲ/ን ብርሃኑ አድማስ


(ምንጭ፡አዲስ ጉዳይ መጽሔት፣ ቅጽ 7፣ ቁጥር 153፣ የካቲት 2005)
 በአሁኑ ጊዜ ‹‹ፍቅር››ን የማይጠራው አለ ለማለት አይቻልም፡፡ አፍቃሪ -ተፈቃሪው፣ አጣይ-አፋቃሪው ፣ ሸምጋይ አስታራቂው፣ የሥነ ልቡና ባለሙያው፣ ጸሐፊ ደራሲው፣ አንባቢ ተርጓሚው፣ ሃይማኖት ሰባኪው፣ ልጅ አዋቂው፣ ከተሜ ገጠሬው ፣...ሁሉም ፍቅር ፍቅር ይላል፡፡ የሁሉም ፍቅር ግን አንድ ነው ለማለት የሚቻል አይመስለኝም፡፡ ‹‹ አምላክ›› የሚለውን ቃል የምንጠቀመው ሁሉ ‹‹ አምላክ›› በምንለው አካል እንደምንለያየው ማለት ነው፡፡ ለምን ቀናሽ? ለምን ገደልህ? ለምን ከሳህ?ለምን ታመምሽ? ለምን ተጣላህ?... ለሚሉት ድኅረ ፈተና ወመከራ ጥያቄዎች ብዙ ጊዜ መልሳቸው ‹‹ ስለ ምወደው! ስለምወዳት!›› የሚለውነው፡፡ ይኸ የገረማቸውም እረ ለመሆኑ ‹‹ፍቅር›› ራሱ ምንድን ነው? ሲሉ ይጠይቃሉ፡፡ በርግጥም ፍቅር ራሱ ምንድን ነው?
ፍቅር የኖረው ሊኖርም የሚችለው ከአንድ በላይ የሆኑ አካላት ባላቸው ወይም በሚኖራቸው ግንኙነት ውስጥ ብቻ ነው፡፡ እግዚአብሔር ራሱ ፍቅር ነው የሚባለውም አንድ (በመለኮቱ፣...) ቢሆንም ሦስትነትም ስላለው ነው፡፡ ሦስትነት ባይኖረው ኖሮ ፍቅር ሊሆንም ሊባልም አይችልም ነበር፡፡ ፍቅር በአንድ አካል ህልውና ብቻ ሊገኝ አይችልምና፡፡ ከፍጥረታት ጋር ባለው ግንኙነት ይኖረዋል እንዳንልም ከመፍጠሩ በፊት ፍቅር አልነበረውም ያሰኛል፤ ይህ ደግሞ ጎደሎ ያደርገውና ከአምላክነት ግብርም ያወጣዋል፡፡ በሌላ ቋንቋ ሦስትነት ባይኖረው ባለፈጠረን ነበር ቢያሰኝም ሊሆን የማይችል ነውና ያለሦስትነት የሚኖር የፍቅር አምላክ ሊኖር አይችልም ማለት ነው፡፡ እግዚአብሔር ዓለምን ከመፍጠሩ በፊት ይወደን ስለነበረም ነው የፈጠረን ፣ የመረጠን፤ መዳኛችንንም ያዘጋጀልን፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹ ዓለም ሳይፈጠር፥ በፊቱ ቅዱሳንና ነውር የሌለን በፍቅር እንሆን ዘንድ በክርስቶስ መረጠን ›› /ኤፌ 1፤4/ ያለው ለዚህ ነውና፡፡ ስለዚህም ዓለምን ከመፍጠሩ በፊት ሊያፈቅረን የቻለው ፈቅሩ ከራሱ ባሕርይ የመነጨ ከዚያም ገና ሳንፈጠር ወደ እኛ የተዘረጋ ነበር ማለት ነው፡፡ ስለዚህ የፍቅር መገኛውም እግዚአብሔር ብቻ ነው ማለት ነው፡፡
የፍቅር ምንጩ እግዚአብሔር ነው ማለት ደግሞ ፍቅር ጥንቱንም የተቀደሰና የተለየ አንድነት፣ ኃይል ወይም ደግሞ የልዩና እውነተኛ ግንኙነት መፍጠሪያም ማሠሪያም ነው ማለት ነው፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹ፍቅር ለዘወትር አይወድቅም፤ ትንቢት ቢሆን ግን ይሻራል፤ ልሳኖች ቢሆኑ ይቀራሉ፤ እውቀትም ቢሆን ይሻራል›› /1ኛ ቆሮ 13 ፤ 8/ የሚለውም ለዚህ ነው፡፡ ‹‹ልዩ›› የሚያሰኘው እንደሌሎቹ ሊወድቅ ወይም ሊሻር አለመቻሉ ነውና፡፡ ከዚህ መሠረታዊ ባሕርዩ ተነሥተን ስንመረምረው በብዙዎቻችን መካከል ያለውና ‹‹ ፍቅር›› ብለን የምንጠራው ግንኙነት ፍቅር ላይሆን ይችላል ማለት ነው፡፡
ፍቅር ያልሆነውን‹‹ ፍቅር›› ከመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች ልናየው እንችላለን፡፡ ለምሳሌ በዘፍጥረት 39 ላይ በምናየው የዮሴፍ ታሪክ ውስጥ ‹‹ ከዚህም በኋላ እንዲህ ሆነየጌታው ሚስት በዮሴፍ ላይ ዓይንዋን ጣለች። ከእኔም ጋር ተኛ አለችው።... የዮሴፍም ጌታ ወሰደው፥ የንጉሡ እስረኞችም ወደሚታሰሩበት ስፍራ ወደ ግዞት ቤት አገባው ከዚያም በግዞት ነበረ›› ተብሎ እንደተጻፈ የጲጥፋራ ሚስት ዮሴፍን መውደዷ ቢገለጽም እርሱ ሀሳቧን ባለተቀበለላት ጊዜ ግን ወደ እስር ቤት እንዲወርድ ነው ያስደረገችው፡፡ ታዲያ ይህ መጎዳዳት ያለበት ግንኙነት ፍቅር ሊባል እንደምን ይችላል? ከዚህ በላይ የከፋ አደጋ የሚፈጽምባቸው ድርጊቶች ሁሉ ፍቅር እንዴት ሊሆኑ ይችላሉ? ገንዘብ በጣም የሚወድ አንድ ሰው ገንዘቡን የሚወድደው ለገንዘቡ ጥቅም ሊሆን ይችላልን? በዚህ ድርጊቱስ ይህ ሰው ቁሳዊ የሆነውን ገንዘብን እንኳ የሚወድ ተብሎስ ሊመሰገን ይችላልን? እንዲያውም ይህን ሰው በቅጽል ጥሩት ብንባል ስግብግብ ሰው ነው ልንለው እንችላለን፡፡ ልክ በዚሁ አንጻር ራሳቸውን ለመጥቀም ሲሉ ሰዎችን ‹‹እንወዳቸዋለን›› የሚሏቸውን ሰዎች ቢሰግዱላቸውና ካላቸው ብዙውን ቢሰጧቸውም ይወዷቸዋል ልንል አንችልም፡፡ ምክንያቱም ያን የሚያደርጉት ገንዘብ ወዳጅ ሰው ሊረካ የማይችለውን የስግብግብነት ጥሙን ማርካት የሚቻል መስሎት ለገንዘብ ሲል ማንኛውንም ወንጀል ለመፈጸም ዕረፍት የለሽ ሆኖ ትጉኅ እንደሚመስለው እነዚህም እውነተኛ አፍቃሪ ለመምሰል ብዙ ቢደክሙም አላማቸው ከዚያ ሰው የሚፈልጉትን ጥቅም ሩካቤም ከሆነ እርሱን ፈጽመው ስግብግብነታቸውን ማስታገስ ብቻ ነው፡፡ የዳዊት ልጅ አምኖን እኅቱን ትዕማርን አፈቀርኳት ብሎ ምግብ መብላት ተስኖት ታምሞ ተኛ፡፡ እርሷን አግኝቶ ፍላጎቱን ከፈጸመ በኋላ ግን ‹‹ ከዚያም በኋላ አምኖን ፈጽሞጠላት፤ አስቀድሞም ከወደዳት ውድ ይልቅ በኋላ የጠላት ጥል በለጠ። አምኖንም ተነሥተሽ ሂጂ አላት›› /2ኛ ሳሙ 1315 / ተብሎ እንደተጻፈ ፈቃዱን ከፈጸመና ስግብግብነቱን ካስታገሠ በኋላ ለአንድ ቀን እንኳን ሊያዝንላት አልቻለም፡፡ ከዚህ ዓይነትና መሰል ድርጊቶች መማር የተሳናቸው ሞኞችም አሁንም ስግብግብነታቸውን ሊያረኩ በሚኳትኑ ሰዎች ተጠምደው ሲከንፉ የነገው አይታየቸውም፤ መካሪ ቢመጣም እንኳ የእነርሱ ‹ፍቅር› ከሌሎች እንዴት ልዩ እንደሆነ ይተርካሉ እንጂ አይሰሙም፡፤ ‹‹ የቀነጣ ፍቅር ቆሎ ያጓርሳል›› የሚለው አባባልም ፍቅር ከመሰለ የስግብግቦች ወጥመድ እንድንወጣ የተነገረ ማንቂያ ደውል ሳይሆን የእነርሱ ፍቅረኛ ልዩ ስለሆነ ቆሎ እንደ እንጀራ ጠቅልሎ ማጉረስ የሚችል ጀግና መሆኑንን ለማወደስ የተነገረ ምስጋና ይመስላቸዋል፡፡ አንዳንዶች እንደዚህ ያሉ መስመር የለቀቁ ድርጊቶችን ‹‹ ፍቅር›› እንዲህ አደረገ ሲሉ፤ ፍቅር እንዴት እንዲህ ያደርጋል? ስንላቸው መልሳቸው ‹‹ ወይ ያልተያዘ ሰው!›› ይሆናል፡፡ እኔም እያልኩ ያለሁት ሰዎች እንዲህ ባለ ነገር አይያዙም፤እንደ እንቅልፍ የሚያንገላጅጅ እንደ ወባም የሚያንቀጠቅጥ ነገር አያጋጥማቸውም አይደለም፡፡ እኔ የምለው ሰዎችማ ይያዛሉ፤ ብዙ ነግርም ሊያጋጥማቸው ይችላል፡፡ የተያዙት ግን በፍቅር ሳይሆን በስግብግብነት ነው፤ ነገሩም ሌላውን መውደድ ሳይሆን ራስን በጣም በጣም በጣም መውደድ፤ ሁሉም ለእኔ ይሁን የሚያሰኝ መጎምጀትም ነው የምለው፡፡ እንዲህ ያለውን የስግብግብነትና የማስመሰል ፍቅር ደግሞ መጽሐፍ ‹‹ በአፋቸው ብዙ ፍቅር ይገልጣሉ፥ ልባቸው ግን ስስታቸውን ትከተላለች›› /ሕዝ 33፤31/ ሲል ይገልጸዋል፡፡
እውነተኛ ፍቅር ግን ጠላትን መልሶ ወዳጅ እስኪያደርግ ድረስ ወደ ፍቅር ይማርካል እንጂ ራሱን ለጸብና ለበቀል አሳልፎ እስኪሰጥ ድረስ አይማረክም፡፡ ‹‹ ፍቅር ይታገሣል፥ ቸርነትንም ያደርጋል፤ ፍቅር አይቀናም፤ ፍቅር አይመካም፥ አይታበይም፤...›› /1ኛ ቆሮ 13 ፤ 4/ ተብሎ እንደተጻፈው ከፍቅር የተነሣ ሊፈጸም የሚችል ምንም ዓይነት መጥፎ ድርጊት የለም፡፡ መፍቀሬ ጥበብ ሰሎሞን ‹‹ፍቅር እንደ ሞት የበረታች ናትና›› /መኃ 8፤ 6/ ሲል የገለጸው ከሞት በኋላ ሌላ ነገር የማድረግ ኃይል እንደሌለን ሁሉ ከፍቅርም በኋላ ተቃራኒውን ልናደርግበት የምንችለው ኃይል ልናገኝ አንችልም፡፡ ወደ መጥፎው ከተመለስንማ ጥንቱንም ፍቅር አልነበረም ማለት ነው፡፡ ስለዚህ እውነተኛ ፍቅር በየትኛውም መንገድ ቢፈጸም የማዳን ኃይል ያለው እንጂ የጸብ የበቀልና የመሳሰሉት ድርጊቶች የሉበትም፡፡
ምንም እንኳ ፍቅር የእግዚአብሔር የባሕርይ ገንዘብ በመሆኑ ከፍጥረት ሁሉ በፊት የነበረ ቢሆንም አሁን የምናውቃቸውን የፍቅር ዓይነቶች በአራት ልንከፍላቸው እንችላለን፡፡ የመጀመሪያው ፈጣሪ ለፍጥረቱ በተለይም ለሰው ያለው ፍቅር ነው፡፡ ይህ ፍቅር መጠኑን እንኳ በአግባቡ ልናውቀው የማንችለው በማድነቅ ብቻ የምንቀበለው ያዳነን የሚያድነንም ፍጹም ፍቅር ነው፡፡ ሁለተኛውም ሰው ለእግዚአብሔር ለአምላኩ ሊኖረው የሚገባው ፍቅር ሲሆን ይህም ‹‹ እግዚአብሔር አምላክህን በፍጹም ልብህ ... ውደድ›› በሚል የታዘዝነው በሰው ዘንድ ፍጹም ሆኖ ሊኖር የሚገባው ፍቅር ነው፡፡ ሦስተኛው ደግሞ ‹‹ ባልንጀራህን እንደራስህ አድርገህ ውደድ›› ተብሎ መጠኑ የተሠራለትና ‹‹እንደ ራስህ አድርገህ›› በሚል ቃል ከስግብግብነትና ከስስት ነጻ የወጣ እንዲሆን ጥበቃ የተሠራለት ፍቅር ነው፡፡ አራተኛውና አስገራሚው ደግሞ በባልና በሚስት መካከል ሊኖር የሚገባው ፍቅር ነው፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ የባልና የሚስትን ውሕደት በክርስቶስና በቤተ ክርስቲያን መስሎ በተናገረበት አንቀጹ ‹‹ ባሎች ሆይ፥ ክርስቶስ ደግሞ ቤተ ክርስቲያንን እንደ ወደዳት ሚስቶቻችሁን ውደዱ›› /ኤፌ 5፤ 25/ ሲል ዓይነቱንና መጠኑን ክርስቶስ ለሰው ድኅነት በፈጸመው መሥዋዕትነት የገለጸለው ፍቅር ነው፡፡
በዚህ የተመለሰውም ፍጹም የሚያድን ቅድመ ሁኔታ የሌለበት ሊሆን ስለሚገባው ነው፡፡ ነቢዩ ዳዊትም ስለዚህ ማንኛውም ሰው ከፈጣሪው ጋር፤ከሰው ጋር፤ ከትዳር አጋሩ ጋር ያሉት ግንኙነቶች ሁሉ የተመሠረቱት በፍቅር ላይ ነው፡፡ ፍቅር የሕግ ፍጻሜ ነውና /ሮሜ 13 ፤ 10 ፣ 1ኛ ጢሞ 1፤5/ ፡፡ እንዲህ ከሆነ ዘንድ ያለ ፍቅር ‹‹ፍቅር›› የሆነውን እግዚአብሔርንም ሆነ የእርሱ የሆኑትን ሁሉ ልናውቅ በሃይማኖትም ልንኖርና ልንጠቀም አንችልም፡፡ ‹‹... ፍቅር ከሌለኝ ከንቱ ነኝ›› /1ኛ ቆሮ 13፤2/ ተብሎ ተጽፏልና፡፡ ስለዚህ ያለ ፍቅር የሚደረግ ሃይማኖታዊ ተግባር ሁሉ ነፍስ የተለየው ሥጋ ነውና ‹‹ ፍቅርን ተከታተሉ›› /1ኛ ቆሮ 14 ፤ 1/ ተብሎ እንደተጻፈው ባንይዘው እንኳ እንከታተለው፡፡

No comments:

Post a Comment