Sunday, 2 September 2012

በዚህ ወቅት የቤተክርስቲያን አበውም ሆነ ምዕመናን ለረሷቸው የዋልድባ መነኮሳት ትሁን ይህቺ ዜማ 



የፓትርያርኩ ቀብር ላይ ትልቁ ስህተት


(አንድ አድርገን ነሐሴ 27 2004 ዓ.ም)፡-ፓትርያርኩ ቅዳሴውን አቋርጠው ፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ህዳሴውን አቋርጠው ከዚህኛ ዓለም ወደዚያኛው ዓለም ከሄዱ ቀናት ተቆጥረዋል ፤ ቤተመንግሰቱም ሆነ ቤተክህነቱ አስጨናቂ የሆነ የሀዘን ድባብ ወርሶታል ፤ የፓትርያርኩ አስከሬን ለ6 ቀናት አፈር ሳይቀምስ ሲቆይ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ደግሞ ለ13 ቀናት ያህል ቆይቷል ፤ የፓትርያርኩን ሥርዓተ ፍትሐት ላይ የምስራቅ አብያተ ክርስትያናት ፤ የግብጽ ኦርቶዶክስ ፤ የአርመንና የህንድ ኦርቶዶክስም ጸሎተ ፍትሀት አድርገዋል ፤ ከእነዚህ አብያተክርስትያናት ጋር የኢትዮጵያ ኦርዶክስ ተዋህዶ እምነት የዶግማና የእመነት አንድነት ስላላት  ጸሎተ ፍትሀት ማድረጋቸው በስርዓተ ቤተክርስትያናችን ተቀባይነት አለው፡፡ 


በዋልድባ የመነኰሳቱ ስደት፣ እስርና ድብደባ ተባብሶ ቀጥሏል

·         የተሰደዱት መነኰሳትና መናንያን ቁጥር 13 ደርሷል::
·         ሁለት መነኰሳት በማይ ገባ ወረዳ ታስረዋል::
·         በጠ/ሚኒስትሩና በፓትርያርኩ አሟሟት “ውዥንብር ፈጥራችኋል” በሚል ተከሰዋል::
(ደጀ ሰላም፤ ነሐሴ 27/2004 ዓ.ም፤ September 2/ 2012/ READ THIS NEWS IN PDF)፦  በቤተ መንግሥቱም በቤተ ክህነቱም በተመሳሳይ ወቅት የደረሰብን ሐዘን አነጋጋሪ ከመኾን አልፎ ፍትሐ እግዚአብሔር የተፈጸመበት፣ የእግዚአብሔር መልእክትም የተላለፈበት እንደ ኾነ እየተነገረ ነው፡፡ እንደ አቶ ስየ ኣብርሃ ያሉ የተቃውሞ ፖለቲካ መሪዎች ሳይቀሩ በኹኔታው ላይ ቆም ብለን እንድናስብ እየመከሩ ናቸው፡፡

Friday, 31 August 2012


ቤተ ክርስቲያንና የፓትርያርክ ምርጫ (ዲያቆን ብርሃኑ አድማስ)

ቤተ ክርስቲያን አንዲት፣ ቅድስት፣ ኩላዊትና ሐዋርያዊት መሆኗን ጥንታውያን አብያተ ክርስቲያን ሁሉ ይቀበላሉ፤ በመሠረተ እምነታቸው ውስጥም አካትተው በጸሎትና በአስተምህሮ ይጠቀሙበታል፡፡የዚህ መሠረታዊ ምክንያቱ ደግሞ ከዘመነ ሐዋርያት ጀምሮ ይህ ትምህርት ቢኖርም ነገር ግን መልእክቱን በአግባቡ ካለመረዳት የተነሣ እነ አርዮስና መቅዶንዮስ
በትውፊት ከሐዋርያት ጀምሮ የመጣውን የቅዱሳት መጻሕፍት ትርጓሜ መሠረት መቀበልን ቸል ብለው በራሳቸው መንገድ ሔደው ስለሳቱ በጉባኤ ኒቅያ በማያሻማ መንገድ ቤተ ክርስቲያን አንዲት፣ቅድስት፣ ሐዋርያዊት እና ኩላዊት መሆኗን አስቀመጡ፡፡ በኋላ በጉባኤ ቁስጥንጥንያ ደግሞ ሁላችንም እንድንጸልይበት በተዘጋጀው አንቀጸ ሃይማኖት ላይ (ጸሎተ ሃይማኖት) ‹‹ ወነአምን በአሐቲ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን እንተ ላዕለ ኩሉ ጉባኤ ዘሐዋርያት›› የሚለው የጸሎታችን መፈጸሚያ እንዲሆን ተደነገገ፡፡ በዚህም መሠረት እነዚህን ዓለም አቀፍ ጉባኤያት የሚቀበሉ ሁሉ የሚቀበሉትና የሚመሩበት መሠረታዊ ትምህርተ ሃይማኖት /doctrine/ሆነ፡፡

‹‹የጎንደር ምንቸት ውጣ … የትግሬ ምንቸት ግባ›› በቤተ ክህነት (ነመራ ዋቀዮ ቶላ )

ይህ የቤተ ክክነታችን ችግር እውነታን የዳሰሰ ጡመራ የዛሬ አራት ዓመት አካባቢ ደጀ ሰላም ብሎግ አስነብባን ነበረ:: አሁንም በተለምዶ ስደተኛ ሲኖዶስ እየተባለ የሚጠራው ቡድን “መንበሩ ለእኔ ይገባኛል” እያለ ነው::ስደተኛው ሲኖዶስ የመሰረቱት በስደት ላይ ያሉት የጎንደር ተወላጅ የሆኑት ብፁዓን  አበው “በትግሬዎቹ/በወያኔ ተገፍተን መንበራችን ተቀማን” እያሉ ለ20 ዓመታት ያህል ምእመናን ሲያምሱ ኖረዋል:: በዚህም ምክንያት ቤተ ክርስቲያኒቷ በፍቅር መስፋፋት ሲገባት በውጩ ዓለም በጥላቻ እና በጎጠኝነት ለቁጥር በሚያስቸግር ሁኔታ ተከፋፍላለች:: እውነት የጎደሬዎቹ ወደ መንበር መምጣት የቤተ ክርስቲያኒቱ ችግር ይፈታ ይሆን??? አሐቲ ተዋሕዶ በአባቶች መካከል የተፈጠረው መከፋፈል አጥብቃ ትቃወማለች:: ጎጠኝነትን ግን ታወግዛለች::  በስደት ላይ የሚገኙት ብፁዓን አባቶች ከቅዱስ ሲኖዶስ ጋር ታርቀው ወደ አገራችው እንዲመለሱም እንፈልጋለን:: የአባቶች መታረቅ የሚመጣው ግን እውነታዎች ሳይደባበቁ በግልጽ አውጥተው ሲነጋገሩ ብቻ ነው ብላ አሐቲ ተዋሕዶ ታምናለች:: የሚከተለውን የነመራ ዋቀዮ ቶላ ጽሑፍ አንብቡት:: መልካም ንባብ::

የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን የተዘረጋባትን የተሐድሶ ወጥመድ ይፋ አድርጓል የተባለ “ሰነድ” ይፋ ሆነ

(ደጀ ሰላም፤ ፌብሩዋሪ 5/2011፤ ጥር 29/2003 ዓ.ም)፦ 

ከ1920ዎቹ ሁለተኛ አጋማሽ ጀምሮ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን አስተምህሮ እና ትውፊት በመለወጥ ፕሮቴስታንታዊ ለማድረግ በተለያዩ የቤተ ክርስቲያኒቱ አካላት እና መዋቅሮች ላይ ትኩረት ሰጥተው የሚሠሩ የተሐድሶ ኑፋቄ ማኅበራት እና ድርጅቶች በተለዋዋጭ ስልቶች ሲማስኑ መቆየታቸው ይታወቃል፡፡ ይህ ጥረታቸው ያሰቡትን ያህል ያልተራመደላቸው የተሐድሶ መናፍቃኑ ቤተ ክርስቲያኒቱን ‹‹ከውስጥ እያጠቁ ወደ ውጭ በመገስገስ እና ከውጭ ከበባውን አጠናክሮ ወደ ውስጥ በመግፋት›› ሙሉ በሙሉ ለመቆጣጠር አልያም ውጥንቅጧን አውጥቶ ለሁለት ለመክፈል ስልት ቀይሰው፣ በተለይም የቤተ ክርስቲያኒቱን የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ማእከል አድርገው በመንቀሳቀስ ላይ ስለመሆናቸው የሚገልጽ ሰነድ ሰሞኑን ለደጀ ሰላም ደርሷል፡፡

Thursday, 30 August 2012


ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆርዮስ የት ነዎት?


  •  ቅዱስነታቸው ስለ ራሳቸው እና ስለ ፕትርክናው ሊናገሩ ይገባቸዋል።

(ደጀ ሰላም፤ ነሐሴ 25/2004 ዓ.ም፤ ኦገስት 31/ 2012/READ THIS ARTICLE IN PDF)፦  ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስአርፈው መንበረ ፕትርክናው ባዶ ከሆነ እነሆ ቀናት ተቆጠሩ፡፡ ቅዱስ ሲኖዶስ ባለው ሥልጣን መሠረት ተተኪው ፓትርያርክ እስከሚሰየም ድረስ አቃቤ መንበረ ፓትርያርክ” ይሆኑ ዘንድ ብፁዕ አቡነ ናትናኤልን ሰይሟል። ቤተ ክርስቲያኒቱ 5ኛውን ፓትርያርኳን በሐዘን እያሰበች ባለችበት በአሁኑ ወቅት “ቀጣዩ ማን ነው?” የሚለው ጥያቄ በስፋት በመጠየቅ ላይ ይገኛል። ድምጻቸው ቀላል ያልሆኑ ኦርቶዶክሳውያንም “እግዚአብሔር ለቤተ ክርስቲያኒቱ አንድነት ሊሰጥ ዕድል ከፍቶልን ሳለ፣ የቀደሙትን አራተኛውን ፓትርያርክ ወደ መንበራቸው መመለስ ሲገባ የምን አዲስ ምርጫ ነው?” እያሉ ነው። ለደጀ ሰላም የደረሱ ብዙ መልእክቶችም ይህንን በማበከር ላይ ይገኛሉ። በዚህ አጋጣሚ ደጀ ሰላም” አንድ ሁነኛ ጥያቄ ማቅረብ ትፈልጋለች። የቀድሞው ፓትርያርክ አቡነ መርቆርዮስ የት ነዎት? ድምጽዎትን ለምን አንሰማም? ሐሳብዎን ለምን አይገልጹም? ከምዕመኖችዎ ጋር በቱርጁማን፣ በስማ በለው፣ በተላላኪ፣ በሦስተኛ ወገን መነጋገር መቼ ነው የሚያበቃው ለማለት እንወዳለን። አንባብያንም ሐሳባችሁን እንድታካፍሉን እንጋብዛለን።
ቸር ወሬ ያሰማን፤
አሜን፡፡

ዮሐንስ ሐፂር


ዱስ ዮሐንስ ሐፂር በዲ/ን መላኩ እዘዘው
ዮሐንስ ሐፂር በላይኛው ግብጽ ቴባን በምትባል መንደር በ339 ዓ.ም ተወለደ፡፡ ወደ ገዳም አስቄጥስ የገባው በልጅነቱ ሲሆን ያን ጊዜ አበምኔቱ አባ ባሞይ ይባል ነበር፡፡ አባ ዮሐንስ በተመሥጦው እና በታዛዥነቱ የታወቀ አባት ነበር፡፡ በመጀመርያው የአስቄጥስ ጥፋት ጊዜ ገዳሙን ትቶ ወደ ቁልዝም ተጓዘ፡፡ ያረፈውም በዚያ ነው፡፡
የዮሐንስ ሐጺርን ትምህርቶች ከዚህ እንደሚከተለው አቅርበነዋል ፡፡
1. የጠላቱን ከተማ ለመቆጣጠር የዘመተ ንጉሥ አስቀድሞ የውኃውን መንገድ ይዘጋል፣ የእህሉንም መግቢያ ይይዛል፡፡ ያን ጊዜ ጠላቶቹ ይራባሉ፣ ይጠማሉ፡፡ በመጨረሻም እጃቸውን ይሰጣሉ፡፡ የነፍስን ፆር ለማሸነፍም በተመሳሳይ መንገድ መጠቀም ይገባል፡፡ አንድ ሰው በጾምና በረኃብ ከጸና የነፍሱ ጠላቶች ይዳከማሉ፡፡
2. እኔ በትልቅ ዋርካ ሥር የተቀመጠንና አራዊት ሊጣሉት የመጣን ሰው እመስላለሁ፡፡ ሊቋቋማቸው እንደማይችል ከተረዳ ሸሽቶ ወደ ዛፉ በመውጣት ነፍሱን ያድናል፡፡ በእኔም የተፈጸመው ይኼው ነው፡፡ በበዓቴ ተቀምጬ ክፉ ሃሳቦች ሊቃወሙኝ ሲመጡ፣ ልቋቋማቸው እንደማልችል ባወቅኩ ጊዜ በጸሎት ወደ እግዚአብሔር ሸሽቼ እመሽጋለሁ፡፡ በዚያም ከጠላቶቼ ፍላፃ እድናለሁ፡፡ 

3. መለወጥ የምትፈልግን ነፍስ በተመለከተ አባ ዮሐንስ እንዲህ አለ፡- በአንዲት ከተማ ውስጥ ብዙ ወዳጆች የነበሯት አንዲት አመንዝራ ሴት ነበረች፡፡ ከገዥዎቹ አንዱ ቀረባትና ‹መልካም ሴት ለመሆን ቃል ግቢልኝና አገባሻለሁ› አላት፡፡ እርሷም ቃል ገባችለትና ተጋቡ፡፡ ወደ ቤቱም ወሰዳት፡፡ የቀድሞ አፍቃሪዎቿ ያቺን ሴት ፈለጓት፣ እርስ በርሳቸውም ‹ያ ልዑል ወደ ቤቱ ወስዷታል፤ ወደ ቤቱ ብንሄድ ይቀጣናል፡፡ ነገር ግን በጓሮ በኩል እንሂድ፣ ለርሷም እናፏጭላት፣ የፉጨቱን ድምፅ ስትሰማ ከድርሱ ወርዳ ወደኛ ትመጣለች፣በዚህም ያለ ችግር እናገኛታለን› ተባባሉ፡፡ ወደ ቤቷም ጓሮ ተጉዘው ያፏጩ ጀመር፡፡ እርሷ ግን የፉጨቱን ድምፅ ስትሰማ ጆሮዎቿን ደፈነች፡፡ ወደ ውስጣዊው እልፍኝም ገባች፡፡ በሩንም ጥርቅም አድርጋ ዘጋች፡፡ ይህቺ ሴት የኛ ነፍስ ምሳሌ ናት፡፡ ወዳጆቿ የተባሉም ፈተናዎቿ ናቸው፤ ገዥ የተባለውም ክርስቶስ ነው፣ እልፍኝ የተባለውም ዘለዓለማዊው ቤት ነው፡፡ እነዚያ የሚያፏጩት ክፉዎች አጋንንት ናቸው፤ ነገር ግን ነፍስ ሁልጊዝም በክርስቶስ አምባነት ትሸሸጋዋለች፡፡

4. አባ ዮሐንስ ልቡናው ከእግዚአብሔር ጋር ስለነበረ ምድራዊ ነገሮችን ይዘነጋ ነበር፡፡ አንድ ቀን አንድ ወንድም ቅርጫት ሊወስድ ወደ አባ ዮሐንስ በኣት መጣ፡፡ አባ ዮሐንስም ምን ፈልጐ እንደሆነ ጠየቀው፡፡ ያም ወንድም ‹ቅርጫት ፈልጌ ነው› አለው፡፡ አባ ዮሐንስ ወደ በኣቱ ተመለሰና ዘንግቶት ወደ ሽመና ሥራው አመራ፡፡ ጥቂት ቆይቶ ያ ወንድም አንኳኳ፣ አባ ዮሐንስም ወጥቶ ‹ምን ፈልገህ ነው› አለው ‹ቅርጫት ስጠኝ ብየህ ነበር› ሲል መለሰለት፡፡ ተመልሶ ወደ በኣቱ ሲገባ ልቡናው በሰማያዊ ነገር ስለተመሰጠ ዘንግቶት ወደ ሽመናው ሥራ እንደገና ገባ፡፡ ለሦስተኛ ጊዜ ያ ወንድም ሲያንኳኳ አባ ዮሐንስ ተመልሶ ወጣና ‹ምን ፈልገህ ነው?› አለው፡፡ ‹ቅርጫት ስጠኝ ብየህ ነበር› አለና መለሰለት፡፡ አባ ዮሐንስም እጁን ይዞ እየጐተተ ወደ በኣቱ አስገባውና ‹ቅርጫት ከፈለግህ ያዝና ሂድ፣ በእውነቱ እንዲህ ላሉት ነገሮች እኔ ጊዜ የለኝም› አለው፡፡

5. አንድ ቀን አንድ ሰው ወደ አባ ዮሐንስ ሐፂር በኣት መጣና ሥራውን እያየ ያመሰግነው ጀምር፡፡ አባ ዮሐንስ ዝም አለውና ገመድ መሥራቱን ቀጠለ፡፡ እንግዳውም እንደገና ወሬውን ቀጠለ፣ አባ ዮሐንስም ጸጥ አለው፡፡ ለሦስተኛ ጊዜ እንግዳው ወሬ ሲያበዛ፡፡ ‹አንተ ወደ በኣቴ በመግባትህ እግዚአብሔር ወጥቶ ሄደ› ብሎ ተናገረው፡፡

6. አባ ዮሐንስ እንዲህ አለ፡- ‹የብሕትውናን ኑሮ በከተማ ውስጥ የሚኖር አንድ ሽማግሌ ነበረ፡፡ ያ ሰው በከተማው ውስጥ ከፍተኛ ቦታ የሚሰጠውና ባለዝናም ነበር፡፡ አንድ አረጋዊ አባት ከማረፉ በፊት ያንን ሰው ሊያየው እንደሚፈልግ ለዚያ ሰው ጥሪ ደረሰው፡፡ ያም ሰው በቀን ከተጓዝኩ ሰዎች ስለሚከተሉኝ ለኔ የተለየ ክብር ይሰጡኛል ብሎ አሰበ፡፡ ስለዚህም በሌሊት ሰው ሳያየው ለመጓዝ ወሰነ፡፡ በመሸ ጊዜም አሁን ማንም አያየኝም ብሎ ተነሣና ጉዞ ጀመረ፡፡ ነገር ግን ሁለት መላእክት ታዝዘው መብራተ ይዘው መንገዱን ይመሩት ነበር፡፡ ይህንን የተመለከቱ የከተማው ሰዎች ወደ እርሱ ተሰባሰቡ፣ መላ ከተማው ያንን የመላእክት ብርሃን እያየ ከኋላ ተከተለው፡፡ ከክብር በሸሸ ቁጥር የበለጠ ክብርን አገኘ፡፡ በዚህም ‹ራሱን ከፍ የሚያደርግ ሁሉ ይዋረዳል፣ ራሱንም የሚያዋርድ ሁሉ ከፍ ከፍ ይላል› የሚለው የወንጌል ቃል ተፈጸመ፡፡ (ሉቃ. 14.11)

7. አባ ጴሜን አባ ዮሐንስ እንዲህ ብሎ መናገሩን ገልጧል ‹ቅዱሳን በአንድ ቦታ የበቀሉ ዛፎችን ይመስላሉ፡፡ ከአንድ ምንጭ ጠጥተው፣ ልዩ ልዩ ዓይነት ፍሬ ያፈራሉ፡፡ የአንድ ቅዱስ ሥራ ከሌላው ይለያል፣ ነገር ግን በሁሉም አድሮ የሚሠራው አንድ መንፈስ ቅዱስ ነው፡፡
ዋቢ መጽሐፍ በበረሓው ጉያ ውስጥ
በረከተ ቅዱሳን ይደርብን

Monday, 27 August 2012


የዋልድባ አብረንታንት መነኰሳት መሰደድ ጀምረዋል


  • ባለፉት ጥቂት ቀናት ከስድስት ያላነሱ መነኰሳት ተሰደዋል
  • “ታጋይ ገድላችኹ እናንተ አትኖሩም” (የፀለምት - ማይ ፀብሪ ወረዳ ሓላፊዎች)።

 (ደጀ ሰላም፤ ነሐሴ 21/2004 ዓ.ም፤ ኦገስት 27/ 2012/ READ THIS NEWS IN PDF)፦ በዋልድባ አብረንታንት ገዳም መነኰሳት ላይ ባተኰረውና ካለፉት አራት ቀናት ጀምሮ እየተባባሰ በቀጠለው እስርና እንግልት ሳቢያ ከስድስት ያላነሱ መነኰሳት የፀለምት - ማይ ፀብሪ የፀጥታ ኀይሎች በሚያደርሱባቸው ግፍ ሳቢያ ወደ ሌሎች ገዳማት መሰደዳቸውን፣ በተቀሩትም አባቶች ላይ ድብደባ እየተፈጸመባቸው መኾኑን የሥፍራው ምንጮች እየገለጹ ናቸው፡፡