 |
Daniel with Patriarch |
ይገርማል! ከማኅበሩ አመራሮች መካከል እንደሚገኙበት የተጠቆሙት እነዳንኤል ሰይፈ ሚካኤል፣ አእመረ አሸብርና ንቡረ እድ ኤልያስ ኣብርሃ ባቀረቡትና ቅዱስ ሲኖዶስ ለዳግመኛ ዝግጅት ውድቅ ባደረገው የማኅበራት መተዳደርያ ደንብ ‹ጥናት› ሰነድ ላይ፡- “ራሳቸውን ብቸኛ ተጠሪ ያደርጋሉ፤ ከሲኖዶሱ የበላይ ኾነው ሌላ ሲኖዶስ እንዳያቋቁሙ፣ የፖለቲካ መድረክ እንዳይኾኑ ያሰጋሉ፤ ከአጥቢያ ቤተ ክርስቲያንና ከአስተዳደራዊ መዋቅር ውጭ ቄስና ዲያቆን ይቀጥራሉ፤ ለቤተ ክርስቲያን ልማትና ዕድገት የአጥቢያ መዋቅር በቂ ኾኖ ሳለ ከአጥቢያ መዋቅር ውጭ የኾኑና በአጥቢያ አስተዳደር ይኹን በሀ/ስብከትና በመንበረ ፓትርያርክ ቁጥጥር የማይደረግባቸው ናቸው፤” በማለት የወነጀሏቸው በአባ ሰረቀ የተለመደ አነጋገር “ነጋዴዎች” ያሏቸውን ሌሎች ማኅበራትን ነበር፡፡ ምነው እነርሱስ ለዚህ ሰነፉ ወይስ የጥናቱ ዓላማ ሌላ ነበር?
በደንቡ ረቂቅ ላይ እንደተገለጸው÷ “ጉባኤው” ከታወቀ የመርሐ ግብር ዝግጅት ጋራ ለተያያዘ ዕቅድ ካልኾነ በቀር ገንዘብ አይሰበስብም (ፋይናንስ አያንቀሳቅስም)፤ በንግድ አይሰማራም፤ ቅርንጫፍ አይኖረውም ተብሏል፡፡ ይኹንና “ጉባኤው” በያዘው ዓላማ ስም ኀይለ ጊዮርጊስ ለአሜሪካ ምንጮቹ ወይም ለፕሮቴስታንት አጋሮቹ የልመና አቁማዳውን አይከፍትም ለማለት ባይቻልም ለጊዜው ለመሰብሰቢያ (ጽ/ቤት) ቢሮ ኪራይ ለመክፈል፣ የቢሮ ዕቃዎችን ለማሟላት ይኹን ምናልባትም ጸሐፊ ለመቅጠር የሚያሳስበው ነገር አይኖርም፡፡ ኧረ እሱ እቴ -የዓለም አብያተ ክርስቲያን የክብር ፕሬዝዳንት (የሚቀጥለው ዓመት ያበቃል መሰል) የኾኑት አቡነ ጳውሎስ÷ የዓለም አብያተ ክርስቲያን እንግዶቻቸውን በሚያሳርፉበት “የፓትርያርኮች ማረፊያ” ሕንጻ ሦስተኛ ፎቅላይ የተሟላ ቢሮ ተሰጥቶታላ! ይህ ዜና እስከተጠናቀረበት ቀን ድረስ “ጉባኤው” በቢሮው ከአራት ያላነሰ ጊዜ ተሰብስቦበታል ተብሏል፡፡ ገንዘብስ ቢያስፈልግ እኒያ ደጋግ ምእመናን ከመቀነታቸው ፈተው የሚሰጡት አይጓደል እንጂ ለጊዜያዊ ሥራ ማስኪያጃ ከቍልቢ ንዋያተ ቅድሳት ማደራጃ የተቆነጠረ ብር በበጀት እንደተመደበለት ተጠቁሟል፡፡
ይደንቃል! እነዳንኤል ሰይፈ ሚካኤል “ቤተ ክርስቲያን መምሪያ አቋቁማ በምትሠራባቸው ጉዳዮች ላይ ተመሳሳይ ክፍሎችን በማደራጀት ያልተሰጣቸውን የውክልና ሥራ በመሥራት የልመና ቋት ከፍተው ገንዘብ ያካብታሉ” ብለው ባስቀመጡት ውንጀላ እነርሱው ሲገቡበት፡፡ ቅንነቱ ካለ÷ ከመንበረ ፓትርያርኩ የሥራ ክፍሎች መካከል የቀድሞው “ዕቅድና ጥናት መምሪያ” (ሕገ ቤተ ክርስቲያን፣ 1984 ዓ.ም፣ ምዕ.7 አንቀጽ 22) የአሁኑ “ዕቅድና ልማት መምሪያ” በአግባቡ ቢጠናከር ሊፈጽመው የሚችለውን ተግባር ነጥቃችኹኮ ነው ለተንኰላችኹ የምትዶልቱት! ዛሬ የረባ የሥራ ዝርዝር እንኳ የሌለው፣ በሰው ኀይልና በሥራ ማስኬጃ በጀት የተራቆተ መምሪያ ለአብያተ ክርስቲያን ሕንጻ ግንባታ፣ ዕድሳት እና ሲሚንቶ ግዥ ፈቃድ እየሰጠ ገቢ አስገኘኹ ከማለት፣ “በመልካም አስተዳደርና ልማታዊ ጉዳዮች ጥናት አደርጋለኹ” ብሎ በቃል ከመናገር በቀር ሌላ ምን የረባ ሥራ ይዞአል?
ለነገሩ ዘመናዊ የሥራ አመራር አደረጃጀትን በመከተል ሳይኾን ለሰዎች ቦታና ሓላፊነት ከማሰብ አኳያ ብቻከሚገባው በላይ የተንዛዛ መዋቅር ይዞ በመጓዝ ላይ በሚገኘው ቤተ ክህነት÷ ሲሻው የቤተ መጻሕፍት ወመዘክር ሓላፊ፣ በል ሲለው ደግሞ በሌሉ የሥራ ክፍሎች እና ባልተሟላ የሰው ኀይል የቱሪዝም መምሪያን ጨምሮ፣ የቅርስ ጥበቃንም ጠቅልሎ ራሱን “የቅርስ ጥበቃና የቤተ መጻሕፍት ወመዘክር እንዲሁም የቱሪዝም መምሪያ ሓላፊ” ብሎ የሚሠይም ሓላፊ ባለበት ቤት ብዙ መጠበቅ አይቻልም፡፡
እንዲያው ለአማካሪነቱስ ቢኾን በ2001 ዓ.ም የርክበ ካህናት ቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ውሳኔ ተቋቁሞ የነበረውና ሰባት ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳትን በአባልነት ይዞ የነበረው የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ቅዱስ ሲኖዶስን ለማገዝ በልዩ ልዩ የሞያ ዘርፎች ሊያደራጃቸው ያሰባቸው የመማክርት መዋቅሮች አልነበሩትምን? አቡነ ጳውሎስ ወይም እናንተ ስታስቡት ርቱዕ ኾኖ ተገኘ ማለት ነው? ለነገሩ በየትኛው ብቃታችኹ ታማክራላችኹ? ምቀኝነት፣ ብኩንነት፣ ጎጠኝነት፣ ኑፋቄና ተንኰል እንደኾን ዕውቀት አይኾን!! በዘመድ አዝማድ አድሏዊ አሠራር፣ ሙስናና ኑፋቄ የበከተው፣ ለመንግሥትም የፖለቲካ ዕዳ የኾነው የአቡነ ጳውሎስ የኻያ ዓመት ዐምባገነናዊ አስተዳደርስ እንዲህ ዐይነቱ ወግ ማዕርግ መች ይወድለታል - ቅ/ሲኖዶሱን እና ፓትርያርኩን እናማክራለን የምትሉት ለክፋታችኹ ኾኖ እንጂ!!
“ጉባኤ አርድእት” ለተቋቋመበት የክፋት ዓላማ ዐይነተኛ ምስክሩ÷ ቅዱስ ሲኖዶስ በጥቅምቱና በግንቦቱ መደበኛ ስብሰባዎች አቡነ ጳውሎስ በመነጋገርያ አጀንዳነት አቅርበውት÷ “ወቅቱ አይደለም” በሚል ውድቅ ያደረገውን የሕገ ቤተ ክርስቲያን ማሻሻል ጉዳይ÷ ከአጥቢያ አብያተ ክርስቲያን እስከ አህጉረ ስብከት ድረስ ጥቅመኛ አለቆችንና የሥራ ሓላፊዎችን አነሣስቶ በብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳትን ላይ በሚፈጥሩት ጫና አቋማቸውን በማስቀየር ለማስፈጸም የጀመረው ሙከራ ነው፡፡ ቡድኑ በራሱ ሥልጣን ረቂቅ እስከማዘጋጀት የደረሰበት የቤተ ክርስቲያን የበላይ ሓላፊ ቅ/ሲኖዶስ መምሪያ የኾነውን ሕገ ቤተ ክርስቲያን የማሻሻል ዓላማ÷ በአገልግሎት፣ አስተዳደርና ልማት ፍትሐዊ እና መንፈሳዊ አመራር እና አሠራር ተረጋግጦ ቤተ ክህነታችን አብነታዊ የእምነት ተቋም እንዲኾን የማድረግ አይደለም፡፡
የቡድኑ ዋነኛ ዓላማ ቤተ ክርስቲያንን 16 ዓመት ወደኋላ መመለስ ነው፡፡ ይህም የቅዱስ ሲኖዶሱ የበላይ አካልነት በፓትርያርኩ የበላይነት የተተካበት፣ የቅ/ሲኖዶስ ሥልጣንና ሓላፊነት የሚገለጽበት ጽ/ቤቱ እና ውሳኔዎቹ ተግባራዊ የሚደረጉበት የመ/ፓ/ጠ/ቤ/ጽ/ቤት እንዳይሠራ ዋና ጸሐፊው እና ዋና ሥራ አስኪያጁ በአቡነ ጳውሎስ ምርጫ የሚሾሙበት፤ በቅ/ሲኖዶሱ ጉባኤ የአጀንዳ አቀራረብ፣ የስብሰባ አመራርና የውሳኔ አሰጣጥ የፓትርያርኩን ግላዊ ውሳኔ ገዝፎ የነበረበት፤ በዚህም ሳቢያ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳቱ ራሳቸው የተቃውሞ እንቅስቃሴ የጀመሩበት፣ ከ90 በመቶው ያላነሰው አገልጋይና ሠራተኛ በቅጥር፣ ዝውውር፣ የደረጃ ዕድገት፣ የደሞዝ አከፋፈልና ስንብት ረገድ በጉቦ፣ ዝምድና፣ አድልዎ፣ ወገናዊነት እና ጥቅማጥቅም የተበደለበት፣ ለዕቅበተ ሃይማኖት የሚሰጠው ትምህርተ ወንጌል አጽጾ ምእመናንና ቅርስ ነዋያተ ቅድሳታችን ለአደጋ የተጋለጡበት የ1988 ዓ.ም ሕገ ቤተ ክርስቲያን ዐይነት ሰነድ መልሶ ማቋቋም ነው፡፡
ከ1984 ዓ.ም ጀምሮ በሥራ ላይ የነበረውን ሕግ ያሻሻለው እና በሚያዝያ ወር 1988 ዓ.ም የወጣው ሕገ ቤተ ክርስቲያን÷ የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት ከፍተኛ ተቃውሞ እያሰሙበት በአቡነ ጳውሎስ ፍላጎትና ተጽዕኖ እንደጸደቀ÷ በቤተ ክርስቲያን አመራርና አስተዳደር የተፈጸመውን አድሏዊ አሠራር፣ አስተዳደራዊ በደልና የገንዘብ ምዝበራ ለማጣራት÷ ኅዳር ሁለት ቀን 1990 ዓ.ም በቋሚ ሲኖዶስ የተቋቋመው አጣሪ ኮሚሽን ሐምሌ 10 ቀን 1990 ዓ.ም ለምልዐተ ጉባኤው ያቀረበው ባለ53 ገጽ ክፍል አንድ ሪፖርት አረጋግጧል፡፡
“በቅዱስ ሲኖዶስ አመራርና በሕገ ቤተ ክርስቲያን አተረጓጎም” ዙሪያ በአጣሪ ኮሚሽኑ ሪፖርት ገጽ 14 ላይ እንደተገለጸው÷ ሚያዝያ 30 ቀን 1988 ዓ.ም ጸድቆ ሥራ ላይ የዋለውን ሕገ ቤተ ክርስቲያን ያረቀቀውና ያዘጋጀው በቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ተመርጦ ያልተሠየመና ለዚህ ተግባር የተሟላ ግንዛቤ አላቸው ተብለው የማይገመቱ ግለሰቦች ነበሩ - ልክ እንደ አሁኖቹ የ”ጉባኤ አርድእት” አባላት ማለት ነው፡፡ በ1984 ዓ.ም የቅዱስ ሲኖዶስን ተግባር አስመልክቶ ምዕራፍ 1 ቁጥር 3፣ “የቅዱስ ሲኖዶስ ዓላማ” በሚል ርእስ ሥር “ቅዱስ ሲኖዶስ በጠቅላላው የቤተ ክርስቲያን አስተዳደር የበላይ ሓላፊ” እንደኾነ በመግለጽ “ፓትርያርኩ የቅዱስ ሲኖዶስ ሰብሳቢ (ርእሰ መንበር) ነው” ይላል፡፡ እስከ 1984 ዓ.ም ድረስ በሥራ ላይ የነበረው የ1971 ዓ.ም ሕገ ቤተ ክርስቲያን የሚያስቀምጠው ይህንኑ ሐሳብ ነው፡፡
ይኹንና ሚያዝያ 30 ቀን 1988 ዓ.ም ምልዓተ ጉባኤው ባልመረጣቸው ሰዎች ተዘጋጅቶ በፓትርያርኩ ፍላጎትና ተጽዕኖ የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት እየተቃወሙ በጸደቀው ሕገ ቤተ ክርስቲያን ምዕራፍ 3 አንቀጽ 5 ላይ የሰፈረው ግን “ቅዱስ ሲኖዶስ በቅዱስ ፓትርያርኩ አመራር ሰጭነትና ሰብሳቢነት የሚከተሉት ሥልጣንና ተግባር ይኖሩታል” በሚል ነው ተተክቶ ሲያበቃ ነው ተሻሻለ የተባለው፡፡ የአጣሪ ኮሚሽኑ አባላት ስለዚህ ዐይነቱ ማሻሻያ በሰጡት አስተያየት÷ “ይህ ኀይለ ቃል (በቅዱስ ፓትርያርኩ አመራር ሰጭነት) በዚህ ሕገ ቤተ ክርስቲያን ላይ የተጨመረና የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የመጨረሻው አካል ቅዱስ ሲኖዶስ መኾኑ ቀርቶ በቅዱስ ፓትርያርኩ አመራር ሥር የሚገለጽ የበታች አካል እንደኾነ፣ በአንጻሩ ፓትርያርኩ ከሰብሳቢነት ያለፈ በሲኖዶሱ ላይ የበላይነትን የሚያጎናጽፈው ኾኖ ስለሚታይእዚህ ላይ የቀረበው ቅሬታ አግባብነት ያለው መኾኑ ታምኖበታል፡፡” ይላል፡፡
 |
ርእሰ ደብር መሐሪ ኀይሉ |
ከአጣሪ ኮሚሽኑ ሪፖርት በኋላ ተዘጋጅቶ በ1991 ዓ.ም የጸደቀውና እስከ አሁን በሥራ ላይ የሚገኘው ሕገ ቤተ ክርስቲያን ምዕራፍ 2 አንቀጽ 5 ላይ “በመንፈስ ቅዱስ የሚመራው ቅዱስ ሲኖዶስ የመንበረ ሐዋርያት ወራሽ ስለኾነ በቤተ ክርስቲያኒቱ የመጨረሻው ከፍተኛ የሥልጣን ባለቤት ነው፤ ሕጎችን፣ ልዩ ልዩ ደንቦችንና መምሪያዎችን የማውጣትና የዳኝነት ሥልጣን አለው፡፡” ይላል፡፡ በአንቀጽ 15 ቁጥር 1 እና 2 ላይም “ፓትርያርኩ በተሰጠው ሓላፊነት መሠረት ሃይማኖትንና ቀኖና ቤተ ክርስቲያንን ይጠብቃል፤ ያስጠብቃል፤ የቅዱስ ሲኖዶስን ጉባኤ በሊቀ መንበርነት ይመራል፡፡” ይላል፡፡ እንግዲህ በ”ጉባኤ አርድእት” አመራሮች ኮሚሽን አድራጊነትበተጻፈው ዜና ቤተ ክርስቲያን ጋዜጣ ላይ “የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩን መብት የሚጋፋ ነው፤ ቅዱስነታቸውን አላሠራቸውም፤ ይታረም፤ ይሻሻል፤” በሚል ዘመቻ የተከፈተበት ሕገ ቤተ ክርስቲያን ይህ ነው፡፡
በአጣሪ ኮሚሽኑ ሪፖርት መሠረት ሕገ ቤተ ክርስቲያኑ ከ1968 ዓ.ም ጀምሮ ሲሻሻል እንደመጣ የተመለከተ ሲኾን ይህም የቅዱስ ሲኖዶስን አካላት ደረጃ፣ ሥልጣንና ተግባር በሚገባ በሚወስን መልኩ መኾን እንዳለበት አሳስቧል፡፡ በእነ ኀይለ ጊዮርጊስ የሚመራውን የ”ጉባኤ አርድእት” አባላት የቆረቆራቸው ግን ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳቱ ለአቡነ ጳውሎስ “ሽቅብ መልስ መስጠታቸው”፣ እንዳሻቸው ኤጲስ ቆጶሳትንና የአህጉረ ስብከት ሥራ አስኪያጆችን ለመሾም እና ከአንዱ ሀገረ ስብከት ወደ ሌላው ለማዘዋወር አለመቻላቸው ነው፡፡ በሕገ ቤተ ክርስቲያኑ (91) መሠረት ኤጲስ ቆጶሳት የሚሾሙት በቅዱስ ሲኖዶስ ሲታመንበትና አስፈላጊ ኾኖ ሲገኝ ቅዱስ ሲኖዶሰ በሚሠይመው አስመራጭ ኮሚቴ አማካይነት ተመርጠው ሲቀርቡ ነው፡፡ ኤጲስ ቆጶሳት ከሀገረ ስብከታቸው የሚነሡት ለቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ ቀርቦ፣ ተጠንቶ ሲወሰን ነው፡፡ የአህጉረ ስብከት ሥራ አስኪያጆች የሚሾሙት የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ለብፁዕ ዋና ሥራ አስኪያጁ በማቅረብ ፓትርያርኩ ሲስማማበት በብፁዕ ዋና ሥራ አስኪያጁ ፊርማ ነው፡፡
በዲድስቅልያ እንደተጻፈው የዜና ቤተ ክርስቲያን ርእሰ አንቀጽም እንደገለጸው ፓትርያርኩን “እንደ ንጉሥ መፍራት፣ እንደ አባት መውደድ፣ እንደ እግዚአብሔር ማመን” የተገባ ነው፤ እንደቀድሞው የራሳቸውንና የቤተ ክርስቲያንን ክብር የሚያስጠብቁ ጳጳሳት ይሾሙ ዘንድ የምእመናን ተሳትፎ መኖሩ አስፈላጊ ነው፡፡ እንደ ፍትሕ መንፈሳዊ ድንጋጌ ተሿሚዎቹ በትምህርት ደረጃቸው ብሉያትንና ሐዲሳትን የተማሩ፣ አራቱን ወንጌላት የሚተረጉሙ፣ የግል ሀብትና ንብረት የማያፈሩ፣ ከቅጽረ ቤተ ክርስቲያን ውጭ የማይኖሩና ንጽሕናቸውና ቅድስናቸው በሕዝበ ክርስቲያኑ የማይጠየቅ ሊኾን ይገባል፡፡
ነገር ግን እኒህ ሁሉ ድንጋጌዎች የኢትዮጵያ ፓትርያርክ (ርእሰ አበው) ለመኾን በተሾሙበት ቀን የፈጸሙትን ቃለ መሐላ በመዘንጋት ሃይማኖትን የሚያፋልስ፣ ቀኖና ቤተ ክርስቲያንን የሚጥስ ተግባር እየፈጸሙ በመኾናቸው በካህናትንና ምእመናን ዘንድ ታማኝነታቸውንና መንፈሳዊ ተቀባይነታቸውን ማጣታቸውእየተረጋገጠ በመጣው በአቡነ ጳውሎስ ዘመነ ፕትርክና እንዲኾን አይጠበቅም፡፡ በተለይም የቅ/ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ስብሰባዎችን እንደ ተግዳሮት ከማየታቸውም አልፎ “እየተሠቃየኹ ነው፤ መንግሥት አንድ ርምጃ መውሰድ አለበት፤ መንግሥት ርምጃ ካልወሰደ አልሰበስብም” በሚሉት ፓትርያርክ አቡነ ጳውሎስ ዘመን እንደምን ሊታሰብ ይችላል?
የ”ጉባኤ አርድእት” አመራሮች ግን በፓትርያርኩ ይኹንታና በገዛ ሥልጣናቸው ያረቀቁትን “ሕገ ቤተ ክርስቲያን” ቀደም ሲል እንደተተገለጸው በነውጥ (mob) ለማስፈጸም እንዲመቻቸው የድጋፍ ፊርማ ማሰባሰብበሚል የጠቅላይ ቤተ ክህነቱን መምሪያ ሓላፊዎችና ሠራተኞች ግራ እያጋቡ ነው፡፡ ከሠራተኛው ተሰበሰበ የተባለው ፊርማም፣ በቂም ባይሆን በፓትርያርኩ አማካይነት ለቅ/ሲኖዶስ ይቀርባል፡፡ ከተለያዩ ምንጮች በሚቀርቡላቸው መረጃዎች ሂደቱን በጥሞና እየተከታተሉ የሚገኙት ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት እና ቋሚ ሲኖዶሱ ግን የ”ጉባኤ አርድእት”ን ሕጋዊነት ይኹን የሕገ ቤተ ክርስቲያኑን የጓሮ በር ማሻሻያ እንደማይቀበሉት ስጋት ስለገባቸው ተጨማሪ ማስተማማኛ መያዝ አልያም ወደ ቀጣዩ ደረጃ ለመሄድ አስበዋል፡፡
 |
ንቡረ እድ ኤልያስ |
ቀጣዩ ደረጃ የመንግሥትን ጣልቃ ገብነት መጠየቅ ነው፡፡ ከዚያ በመለስ ግን ከቅዱስ ሲኖዶስ በኩል ያለውን ዕድል አሟጦ ለመጠቀም ሌሎች ሁለት ቡድኖችን ጨምሮ ማደራጀት አስፈልጓቸዋል፡፡ ከእነርሱም አንዱ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅ በኾኑትና በአሁኑ ወቅት “ሲሾም ያልበላ ሲሻር ይቆጨዋል” በሚለው ብሂል የተነከሩት ንቡረ እድ ኤልያስ ኣብርሃ ናቸው፡፡ የንቡረ እዱ ነገረ ሥራ በአፏ ማር ይዛ እሬት አርግዛይሉት ዐይነት ነው፤ ሲበዛ ፈሊጠኛ እና ጠንቃቃ ናቸው፤ ነገር ግን ከምእመኑ እይታ ሊሰወሩ አይችሉም፡፡
ከተሾሙ በስድስት ወራት ውስጥ የሚሳብላቸውን ሙክትና የሚጠቀለልላቸውን ውስኪ ሳይጨምር ገርጂ አካባቢ አጥረው ባቆዩት መሬት በጀመሩት G+3 መኖርያ ቤት ሕንጻ ግንባታ ጥቅመኛ የደብር አለቆች የሚያራግፉላቸው መኪና አሸዋ እና ድንጋይ ለጉድ ነው፡፡ የንቡረ እዱ ድርሻ ቸገረኝ ብሎ መናገር ሳይሆን ቤት እየሠራኹ ነው ብሎ ማወጅ ብቻ ነው፡፡ ንቡረ እዱ ድምፃዊ ናቸው፤ ድጓም ሞያቸው ነው፡፡ ታዲያ ለቅኝት ነው ቢሉ ወይ ለአገልግሎት÷ በየአጥቢያው ጎራ ብለው በቆሙ፣ በቀደሱና ባስተማሩ ቁጥር በትንሹ ከብር 25,000 ያላነሰ እንደሚቀበሉ ይወራል፤ ከሚቀበሉት ሁሉ ግማሹ የቅዱስነታቸው መኾኑን ሹክ ስለሚሉ አጥቢያው ከፍተኛ ገቢ ‹የተመደበበት› ከኾነ መጠኑ ከተጠቀሰውም ጫን ሳይል እንደማይቀር ይነገራል፡፡
የ1990ው አጣሪ ኮሚሽን ጥቅምት 23 ቀን 1991 ዓ.ም ለቋሚ ሲኖዶስ ባቀረበው ክፍል ሁለት ሪፖርት፣ ገጽ 27 ላይ እንደሚገልጸው÷ ከእንዲህ ዐይነቶቹ የደብር አለቆች ብዙዎቹ አነስተኛ ገቢ ካለው ደብር ከፍተኛ ገቢ ወዳለው ደብር ለመዘዋወር አልያም ቦታቸውን ለማጽናት የሚፈልጉ ናቸው፤ ዝውውራቸው በፓትርያርኩ የሚወሰን በመኾኑ ለንቡረ እዱ እና ከእርሳቸው በታች በየደረጃ ለሚገኙቱ “አመቻቾች” የሚወጣውን የታቦት ብር ማሰብ ነው እንግዲህ፡፡ ሌላውን ቡድን የሚመሩት÷ ለአቡነ ጳውሎስ ባላቸው የሥጋ ዝምድና የሚታወቁትና በብፁዕ አቡነ ፊልጶስ ከነበራቸው የመምሪያ ሓላፊነት ደረጃ ዝቅ ተደርገው በልማት ኮሚሽን የትራንስፖርት ክፍል ሓላፊነት እንዲሠሩ በመመደባቸው ግንኙነታቸው ሻክሮ የቆየው ሊቀ ኅሩያን ያሬድ ከበደ ናቸው፡፡ ከአቡነ ጳውሎስ ሐውልተ ስምዕ ጋራ በተያያዘ የእጅጋየሁ በየነ ሚና በመግዘፉ ከአቡነ ጳውሎስ ጋራ ተጨማሪ ቅራኔ ውስጥ የገቡት ሊቀ ኅሩያን ያሬድ÷ ለአቡነ ጳውሎስ ዕቅድ ሰሞኑን ለዕርቅ እየተለመኑ እንደኾነና ዕርቁን ተከትሎ ወደቀድሞው ከፍተኛ ሓላፊነታቸው ሳይመለሱ እንደማይቀር ተሰምቷል፤ ብፁዕ ዋና ሥራ አስኪያጁ ሹመቱን እንደማይቀበሉት የተረጋገጠ ቢኾንም፡፡
ንቡረ እድ ኤልያስ እና ሊቀ ኅሩያን ያሬድ እርስ በርሳቸው ስምምነት እንደሌላቸው የታወቀ ቢኾንም÷ በተሰጣቸው ተልእኮና ግብ ግን አንድ ናቸው፡፡ ይኸውም በተለይ ንቡረ እድ÷ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት አድባራትና ገዳማት አለቆችንና ጸሐፊዎችን እንደ እጅጋየሁ በየነ ካሉት ጋራ በመኾን ሲቀሰቅሱና ሲያነሣሡ ሁለተኛው ደግሞ ተመሳሳዩን ተግባር በተለይ በአህጉረ ስብከት ሥራ አስኪያጆች መካከል፣ በታላላቅ አድባራትና ገዳማት አስተዳደሮች ላይ ያካሂዳሉ ተብሏል፡፡ የሁለቱም ቡድኖች ስምሪት መገናኛው ኮሩ÷ አቡነ ጳውሎስን በመቋቋም ጽኑ አቋም ያሳዩትን በተለይም ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት አቡነ ሕዝቅኤልን፣ አቡነ ፊልጶስን፣ አቡነ ቄርሎስን፣ አቡነ ገብርኤልን፣ አቡነ ናትናኤልን፣ አቡነ አብርሃምን፣ አቡነ ዲዮስቆሮስንና አቡነ ሉቃስን በየአህጉረ ስብከት ጽ/ቤቶቻቸው÷ በተለይ ከሥራ አስኪያጆቻቸው ጋራ÷ በዜና ቤተ ክርስቲያን ጋዜጣ ፍንጭ የተሰጠበትን÷ ጥቅም ላይ የተመሠረተ ግጭት መፍጠር፣ ተበደሉ የተባሉ አገልጋዮችንና የተለያዩ ቡድኖችን ቅሬታ በማስፋፋት ክስንና ሁከትን ማባባስ፣ እንዳመቺነቱም በቀጥታ ማስፈራራትና ጫና አቋማቸውን በማላላት መድረኩን የአቡነ ጳውሎስ መፈንጫ ማድረግ ነው፡፡ ከእኒህ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ጋራ አቡነ ሳሙኤልንና አቡነ ጢሞቴዎስን የመሳሰሉትን ብፁዓን አባቶች÷ “መኖርያ ቤታቸው የማኅበረ ቅዱሳን መሰብሰቢያ ነው፤ አጀንዳ የሚቀረጽበት ነው” በሚል የፖለቲካ ውንጀላ የማሸማቀቅ ሙከራዎችን የማካሄድ ዕቅድ ተይዟል፡፡
በዚህ ረገድ የ”ጉባኤ አርድእት” ዋነኛ አመራሮች በመፍቀሬ ፕሮቴስታንታዊ ብሎጎች ላይ ከቅ/ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ከመጀመር አስቀድሞ በጉባኤው የሥራ ቀናትና በስብሰባው መጠናቀቅ ማግስት የቀጠሉት የብፁዓን አባቶችን ስም የማጥፋት ተግባር ለእኒህ ቡድኖች የሚሰጥ ድጋፍ እንደኾነ ይታመናል፡፡ ይኸው የውግዘት ናዳ እና የስም አጥፊነት ተግባር የእንቅስቃሴው ዋነኛ ዒላማ በኾነው ማኅበረ ቅዱሳን ላይም በተመሳሳይ መልኩ እንደሚፈጸም ይጠበቃል፡፡ ምልአተ ጉባኤው ስለ ማኅበሩ የመዋቅራዊ ተጠሪነት ለውጥ ያሳለፈው ውሳኔ እያደር የቆረቆራቸው፣ ከእጃቸው ሳይታሰብ እንዳመለጠ ሰለባ ያንገበገባቸው አቡነ ጳውሎስ በቃለ ጉባኤው ላይ ካለመፈረማቸውም በላይ ቃለ ጉባኤው በወቅቱ ከቅዱስ ሲኖዶስ መዝገብ ቤት ወጥቶ ወደ ጠቅላይ ቤተ ክህነቱ መዝገብ ቤት እንዳይመራ በማዘግየት÷ የምሥረታው ኻያኛ ዓመት በዓል አከባበር ዕቅድ አካል የነበረው የጉዞ መርሐ ግብሩ እንዲሰናከል በማድረግ ቀዝቃዛ በቀላቸውን ጀምረዋል፤ ሰው የከለከሉትን አብልጦ ይሻልና በቁጥሩ ከ12,500 የማያንስ ምእመን በክልከላው እልክ ተጋብቶ የጠቅላይ ቤተ ክህነቱን ቅጽር መላወሻ እስኪጠፋ በማጥለቅለቅ፣ በዝማሬው፣ በቃለ እግዚአብሔሩ በማድመቅ በተግባር አስተባበለባቸው እንጂ!!
 |
Enqu Baherey |
“ጉባኤ አርድእት” በሌላ ገጽታው÷ አቡነ ጳውሎስ ምልአተ ጉባኤው ለማኅበሩ ባስተላለፈው ውሳኔ አንጻር የጀመሩት ማኅበረ ቅዱሳንን የማዳከምና የማፍረስ ስልታዊ ዘመቻ እንደኾነ የሚገልጹ ምጮንች፣ “ጉባኤ አርድእት” ሰሞኑን ለፓትርያርኩ አቅርቦ በሚያጸድቀው መተዳደርያ ደንቡ መሠረት ለመዝለቅ የማይቻለው ከኾነ÷ በጥቅምቱ ቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ረቂቁ ቀርቦ እንደሚጸድቅ በሚጠበቀው የማኅበራት መተዳደርያ ደንብ መሠረት “ጉባኤ አርድእት” ዕውቅና ጠይቆ ራሱን ወደ “ማኅበረ አርድእት” በመለወጥ ተግዳሮቱን እንደሚቀጥል ተጠቁሟል፡፡ በዚህ ወቅትየ”ማኅበረ አርድእት” ዋነኛ ሥራ የሚኾነው ከማኅበረ ቅዱሳን ጋራ በሠባራ ሰንጣራው ምክንያት ቀጥተኛ ግጭትን በማስፋፋት በሚፈጠረው ጠቅላላ ነውጥ “ማኅበራት አያስፈልጉም” የሚለውን ቅዠታቸውን እውን ወደሚያደርግ ርምጃ ማቀላጠፍ ነው፡፡ ከላይ የተጠቀሱት ቡድኖች በአህጉረ ስብከት፣ በተመረጡ አድባራትና ገዳማት አስተዳደሮች ላይ የነውጥ መሠረታቸውን በማስፋት በጠቅላይ ቤተ ክህነቱና በብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ላይ ጫና ለመፍጠር የሚያደርጉት እንቅስቃሴ በሌላ ገጽታው የዚህን “ጉባኤ/ማኅበር” ተቀባይነት የማረጋገጥ ተልእኮ እንዳለው ተገልጧል፡፡ በታዛቢዎች ጥቆማ÷ ራሳቸው አቡነ ጳውሎስ ትናንት፣ ሰኔ 10 ቀን 2004 ዓ.ም በተከናወነው የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ ደቀ መዛሙርት ምረቃ በዓል ላይ “ወነአምን በአሐቲ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን እንተ ላዕለ ኵሉ ጉባኤ ዘሐዋርያት” የሚለውን ኀይለ ቃል “ጉባኤ አርድእት” ባቀረበው መተዳደርያ ደንብ ላይ ከተብራራበት መንገድ ጋራ አመሳስለው ማቅረባቸው ራሳቸውን የዘመቻው አካል ስለማድረጋቸው የተረጋገጠበት አጋጣሚ ነበር፡፡
አቡነ ጳውሎስ፣ ንቡረ እድ ኤልያስ ኣብርሃ እና አባ ሰረቀ ቀደም ሲል በተለይ ለፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር እንዳቀረቡት የሚገመተውን ክስ መሠረት አድርጎ ሚኒስቴሩ÷ “የሃይማኖት አክራሪነትና የፀረ-አክራሪነት ትግላችን” በሚል ርእስ ባዘጋጀው የከፍተኛ አመራር ሥልጠና ሰነድ እና ሰሞኑን ለንባብ በበቃው የኢሕአዴግ የንድፈ ሐሳብ መጽሔት÷ “በሰላምና ሕገ መንግሥቱ ዙሪያ ሀገራዊ መግባባት መፍጠር” በሚል ርእስ በቀረበው ጽሑፍ÷ ማኅበረ ቅዱሳን እንደ ወሃቢያ ሁሉ “በኦርቶዶክስ ክርስትና ሃይማኖት ማዕቀፍ የአክራሪነትና የጽንፈኝነት አመለካከትና ተግባር የሚንጸባረቅበት አደረጃጀት (ሴክት)” ተደርጎ ተቀምጧል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሚያዝያ ወር መጀመሪያ ላይ በፓርላማ ቀርበው በተመሳሳይ ጉዳይ ላይ ከተናገሩ ወዲህ እንኳ በማኅበሩ ሚዲያዎች የተሰጡት ምላሾች ሰሞኑን በየክልሉ በቀጠሉት ሥልጠናዎች ላይ እንኳ ከግምት የገቡበት ኹኔታ አይታይም፡፡
የወቅቱ የመንግሥት ፕሮፓጋንዳ አቅጣጫ ኾኖ የተያዘውን የአክራሪነት ዲስኩር እንደ ጥሩ አጋጣሚ የወሰዱት እነኀይለ ጊዮርጊስ ታዲያ÷ በመንግሥት ሚዲያዎች የሚወጡ መግለጫዎችንና በግንባሩ ሰነዶች ላይ የሰፈሩ ጽሑፎችን እያጋነኑ መንግሥት ማኅበሩን “ከጥቂት ወራት ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ እንደሚዘጋው”፣ የማኅበሩን አመራሮችና አባላትንም ከዛሬ ነገ ለቃቅሞ እንደሚያስራቸው ውስጥ ዐወቅ መስለው ሽብር እየነዙ ይገኛሉ -“ጠላትኽን ውኃ ሲወስደው እንትፍ ብለህ ጨምርበት” ዐይነት የበቀል ጥማት ነው፡፡
አክራሪነትን ከቀናዒነት መለየት፣ የአክራሪነት እና ጽንፈኝነት እንቅስቃሴን በመሠረቱ አጥብቆ መኰነን፣ በሕገ መንግሥቱ የተደነገገውን የሃይማኖትና መንግሥት መለያየት አምኖ የእምነት ነጻነትን መቀበል አንድ ነገር ኾኖ÷ በቤተ ክርስቲያኒቱ ቅዱስ ሲኖዶስ ታውቆ የጸደቀ መተዳደርያ ደንብ ያለውና የሚሠራውን የሚያውቅ፣ መዋቅሮቹን ከሚለፈፈው የፖለቲካ(?) ጣልቃ ገብነት በጥብቅ የሚቆጣጠርና ለባዕድ (ውጫዊ) ተጽዕኖ የማይጎናበስ ማኅበር በማይመለከተው ዲስኩር ይኹን የሽብር ወሬ ሊጨናነቅ አይገባውም፡፡ እንዲያውም ማኅበሩ የራሱን ህልውና ማእከል አድርጎ ከመንቀሳቀስ ይልቅ÷ በቅርቡ ተሻሽሎ በሚጸድቅለትና የተሻለ ማንዴት በሚያሰጠው መተዳደርያ ደንቡ በመታገዝ÷ ከጠቅላይ ቤተ ክህነቱና በየደረጃው ከሚገኙት መዋቅሮቹ ጋራ እንደ ሰምና ፈትል ተጣጥሞ በተቋማዊ ብቃት ማእዝናዊ መለኪያዎች ምሳሌያዊ የኾነ፤ በአስተዳደር፣ ልማት እና መንፈሳዊ አገልግሎት የተጠናከረ ቤተ ክህነት በመፍጠር ረገድ የበኩሉን ለመወጣት መዘጋጀት እንደሚኖርበት አስተያየት እየተሰጠ ይገኛል፡፡
እነኀይለ ጊዮርጊስ ለማኅበረ ቅዱሳን የሸረቡለት የጥፋት ድግስ አላበቃም፤ ሌላም አሥቂኝ ሙከራ ሊያደርጉ እየተሰናዱ ነው፡፡ ይኸውም እንደ እነርሱ አባባል “ከማኅበረ ቅዱሳን በተለያየ ጊዜና በተለያየ ምክንያት አኩርፈው የወጡ አባላትን በመሰብሰብና ሌላ ማኅበረ ቅዱሳን በማቋቋም የፊቱን በኋላው መተካት”ነው፡፡ ለዚህም በአንድ ወቅት “ስማቸው ለሰማይና ለምድር የከበደ” የተባሉ ግለሰቦችን በፊታውራሪነት ከማሰለፍ ጀምሮ በርከት ያሉ “አኩራፊ አባላት”ን ማሰባሰባቸውን እየገለጹ ይገኛሉ፡፡ እነኀይለ ጊዮርጊስ ለዚህ ከፋፋይ ተንኰላቸው በጄ የሚላቸው ጥቂት ግለሰቦች እንደማያጡ ቢገመትም የማኅበሩ አባላትና አጋር አካላት ሁሉ ይህን ተንኰል ዐውቀው እንዲጠነቀቁ ማድረግ ተገቢ ነው፡፡
“ጉባኤ አርድእት” በሚለው ስማቸውና “ማኅበራት አያስፈልጉም” በሚለው ዓላማቸው መካከል እንኳ ትልቅ መጣረስ እንዳለ ለማያስተውሉት እነኀይለ ጊዮርጊስ÷ በኻያኛው ዓመት የማኅበሩ ምሥረታ በዓል ላይ እንደተገለጸው÷ ማኅበረ ቅዱሳን ቤተ ክርስቲያንን የማገልገል አንድ ናሙና እንጂ ብቸኛው አይደለም፤ ብዙ ማኅበራት ነበሩ፤ አሉም፡፡ ከእነርሱም መካከል በቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ እና በቅዱስ ፍሬምናጦስ አባ ሰላማ ከሣቴ ብርሃን መንፈሳዊ ኮሌጅ ምሩቃን በመቋቋም ላይ የሚገኘው የነገረ መለኰት ምሩቃን ማኅበርአንዱ ነው፡፡
የነገረ መለኰት ምሩቃን ማኅበር ዋና ዓላማ÷ የወንጌል ትምህርት ባልተዳረሰባቸው አካባቢዎች ሐዋርያዊ አገልግሎት መስጠት፤ የቤተ ክርስቲያኒቱ ዶግማ፣ ሥርዐት፣ ትውፊትና ንዋያተ ቅድሳት በአግባቡ እንዲጠበቁ የበኩሉን አስተዋፅኦ ማድረግ ነው፡፡ እስከ አሁን ድረስ በከምባታ አላባ ጠምባሮ ሀ/ስብከት፤ በሐዲያና ስልጤ ሀገረ ስብከት እና በአሶሳ ሀገረ ስብከት በአጠቃላይ ከ7000 ሰዎች በላይ በማኅበሩ ሐዋርያዊ አገልግሎት ተጠምቀዋል፡፡
ማኅበረ ቅዱሳንም ይኹን የነገረ መለኰት ምሩቃን ማኅበር በእነ ኀይለ ጊዮርጊስ “ጉባኤ አርድእት” ደባ አይዳከሙም፤ አይፈራርሱም፤ እንደ ተቋም አገልግሎታቸውን ለማሰናከል ቢቻል እንኳ አስተሳሰባቸውን ለማጥፋት እና ቤተ ክርስቲያንን ለመቆጣጠር አይቻልም፡፡
የ”ጉባኤ አርድእት” መሥራች አባላት እነማን ናቸው?
የ”ጉባኤ አርድእት” መሥራች አባላት 25 ሲኾኑ “ተባባሪ አባላት” ናቸው ያሏቸው ደግሞ 180 ያህል ናቸው፡፡ ከመሥራች አባላት ብዙዎቹ የመምሪያ ሓላፊዎች፣ ከሦስቱ የቤተ ክርስቲያኒቱ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማትና ከመንግሥት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የተውጣጡ ናቸው የተባሉ ናቸው፡፡ ከደረሰን የመሥራች አባላት ዝርዝር መረጃ ውስጥ በአሁኑ ወቅት “ጉባኤ አርድእት”ን በሰብሳቢነት የሚመራው አእመረ አሸብር ነው፤ ምክትል ሰብሳቢው ደግሞ በቅርቡ የሽሬ ሀ/ስብከትን በሥራ አስኪያጅነት ሲመሩ ቆይተው÷ በጡረታ በተገለሉት ሊቀ ማእምራን ኀይለ ሥላሴ ዘማርያም ምትክ÷ የካህናት አስተዳደር መምሪያ ሓላፊ የኾኑት ንቡረ እድ ተስፋይ ተወልደ ናቸው፡፡ ንቡረ እድ ተስፋይ በሽሬ ሀ/ስብከት ሥራ አስኪያጅነታቸው ወቅት÷ ከዋልድባ ገዳም ጋራ በተያያዘ ስለሚነሡት ተቃውሞዎች÷ የሀ/ስብከታቸው መዝገብ ቤት ሳያውቅ በግላቸው ለመንግሥት በሚጽፏቸው ደብዳቤዎች ማኅበሩን በፖለቲከኛነት ሲከሱ ቆይተዋል፡፡ የጉባኤው ጸሐፊ ደግሞ ዳንኤል ሰይፈ ሚካኤል ነው፡፡
የአባላት ዝርዝር - በሰነዱ ላይ በተቀመጠው ቅደም ተከተል መሠረት
1. ንቡረ እድ ኤልያስ ኣብርሃ
2. ቆሞስ አባ ሠረቀ ብርሃን ወልደ ሳሙኤል
3. ንቡረ እድ ተስፋይ ተወልደ
4. ርእሰ ደብር መሐሪ ኀይሉ
5. መጋቤ ሥርዐት ዳንኤል ወልደ ገሪማ
6. መጋቤ ብሉይ አእመረ አሸብር
7. ዶ/ር ሐዲስ የሻነህ
8. መ/ር ዳንኤል ሰይፈ ሚካኤል
9. ቀሲስ ሰሎሞን ቶልቻ
10. መ/ር ብርሃኔ ገብረ ጻድቃን (የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ የማታው መርሐ ግብር አስተባባሪ)
11. ያሬድ ክብረት (በአውሮፓ የ”ጉባኤ አርድእት” ሓላፊ)
12. ሊቀ ሥዩማን ኀይለ ጊዮርጊስ ጥላሁን
13. መኰንን ተስፋይ
14. መ/ር ዕንቍ ባሕርይ ተከሥተ
15. ተስፋይ ሃደራ
16. ተወልደ ገብሩ
17. መ/ር መኰንን ወልደ ትንሣኤ
18. መርከብ መኩርያ
19. ተመስገን ዮሐንስ
20. አብርሃም አዱኛ*
21. ብርሃኑ ካሳ
22. ሊቀ ጉባኤ ዳዊት ታደሰ
23. ሊቀ ትጉሃን ገብረ ክርስቶስ ኀይለ ማርያም - የእስክንድር ገብረ ክርስቶስ አባት (ቅ/ሲኖዶስ ጽ/ቤት)
24. መሪጌታ ታምር ገብረ መስቀል
25. መጋቤ ሠናያት አሰፋ ሥዩም - ቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት ናቸው፡፡
* አብርሃም አዱኛ፡- የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ የቀድሞ ምሩቅ እና የነገረ መለኰት ምሩቃን ማኅበር አባል ናቸው፡፡ በአ.አ.ዩ መምህር ሲኾኑ ከ”ጉባኤ አርድእት” መሥራቾች መካከል መኾናቸውን የሰሙ ወይም የተስማሙ ለመኾናቸው ምንጮቹ ጥርጣሬ አላቸው፡፡
ተጨማሪ ዜናዎችን ይከታተሉ
ቸር ወሬ ያሰማን፤